Friday, January 13, 2012

የተስፋው ቃል!





«እኛ በመንፈስ ከእምነት የጽድቅን ተስፋ እንጠባበቃለንና» ገላ ፭፣፭
በተስፋ የሚጠብቅ ክርስቲያን ትክክለኛ እምነትን የያዘ ነው። ፍጹም የሆነ እምነት በሌለበት የጽድቅን ተስፋ መጠባበቅ የለም። ስለሚጠባበቁት ተስፋ ፍጻሜ እምነት ሊኖር የግድ ነው።
ወንድና ሴት ሊጋቡ ሲወስኑ በጋብቻ ውስጥ ሳሉ ስለሚሆነው ነገር ሁሉ አስቀድመው በተስፋ አምነው ይፈጽማሉ። በጋብቻቸው ልጆችን ይወልዱ ዘንድ ተስፋ አድርገው ያምናሉ እንጂ እየወለዱ አይጋቡም። ሴትም በጽንሷ መጨረሻ ወራት ልጇን ትወልድ ዘንድ በተስፋ ትጠብቃለች እንጂ የጽንስ ውጤት ምን እንደሆነ ሳታውቅ ጽንስን አትለማመድም። ስለሚሆነው ነገር ባለው ጽኑ እምነት የተነሳ ውጤቱን በተስፋ መጠበቅ የግድ ይሆናል ማለት ነው።
አንድ ሰው ቃል ከገባለት ሌላ ሰው የተገባለትን ቃል ፍጻሜ በተስፋ ይጠብቃል። የገባለት ቃል ፍጻሜው ምንም ይሁን ምንም የተስፋውን ቃል ያይ ዘንድ በልቡ አስቀምጦ ይጠብቃል።
እንደዚሁ ሁሉ የተበደለ እንደሆነ የሚያምን ማንም ቢኖር ወደፍርድ አደባባይ ቢሄድ የበደሉን ዋጋ መልካም ፍርድን በተስፋ ይጠብቃል። በተስፋ ስለሚጠብቀው ነገር የጸና እምነት ባይኖረው ወደፍርድ አደባባይ በደሉን ይዞ ሊሄድ አይችልም።
ኦርቶዶክስ ይሁን እስላም፣ ይሁዲ ይሁን ጄሆቫ ዊትነስ፣ ፕሮቴስታንት ይሁን ካልቪኒስት የሁሉም ሃይማኖት ተከታይ በሚያምነው ሃይማኖት ውስጥ የመጨረሻ ግቡን በተስፋ ይጠባበቃል። ውጤቱ ምንም ይሁን ምንም የሚጠባበቀውን ተስፋ በእምነት ሳይቀበል ሃይማኖታዊ ልምምዱን በኑሮው ሁሉ ሊተገብር አይችልም።
ተስፋውን የሚጠባበቀው ከማመን ነው። ማመን ደግሞ ከመስማት ነው። በተስፋው ነገር ላይ እምነት ሳይኖረው ተስፋ አያደርግም። የሚያምነው ደግሞ ስለሚጠባበቀው ተስፋ በደንብ በመስማት ነው። ሳይሰማ እንዴት ያምናል? መጽሐፉም «እምነት ከመስማት ነው» ያለውም ለዚህ አይደል!!

Friday, January 6, 2012

እኔ ማነኝ?



(by dejebirhan)

«እኔ ማነኝ? አንተስ ወንድሜ ማነህ?»

እኔ አበባ ነኝ ፣ የማለዳ ጤዛ ያረፈብኝ፣

ፍካት፣ ድምቀት የከበበኝ፣

ያይን ስስት፣መዐዛ ሽታ፣ የሞላብኝ፣

የንብ ቀሰም፣ ጣፋጭ ማር ነኝ፣

የከበርኩኝ፣ ውበትን የታጠርኩኝ፣

አበባ ነኝ፣ አበባ ነኝ፣

«እኔ ማነኝ፣ እንዴት አልኩኝ?

«አንተስ ማነህ፣ ለምን አልኩኝ?።

                                  ጠያቂ አዋቂ፣ ያ'በው ወግ፣

                                 ጸገየ እጽ ፣ የፍጥረት ሕግ፣

                              ለካስ ነበር-ወደማታው፣ መጠውለግ፣

                                      የመፍረስ ጫፍ ፣ ሌላ ጥግ፣

ታዲያስ እኔ ማነኝ?

ፍካት ድምቀት፣ የማይዘልቀኝ፣

ውበት ጤዛ፣ የሚያረግፈኝ፣

ከሰሎሞን የተሻልኩኝ፣ውበት የደረብኩኝ፣

ሆኜ ሳለሁ፣ ባዶ ገላ ያሸነፈኝ፣ እኔ ማነኝ?

                                   መልስ አገኘሁ፣ የራሱ ካደረገኝ፣

                                    ሳልፈልገው ከፈለገኝ።

                                   እኔ የኔ አይደለሁም፣

                               ውበቴን ሽንፈት አይጥለውም፣

                               መርገፍ ልብሴ፣ ወልቆ አይቀርም፣

አበባዬ ክርስቶስ ነው፣

እርቃኔን የሸፈነው፣

የኔን ከለሜዳ የለበሰው፣

ክብሩን ለኔ ያወረሰው፣

ሞት ሸማዬን የገሰሰው፣

እኔ ማነኝ? ብዬ ስለው፣

አበባህ ረግፎ የማትቀረው፣

አንተ የኔ ነህ፣ ሲለኝ ሰማሁ፣

እኔም ያንተ፣ ቃሌን ሰጠሁ፣

ዛሬም አለሁ፣ ነገም አለሁ፣

አበባዬ አይረግፍም፣ ዛሬም አብባለሁ፣

ነገም በሰማይ አብቤ፣ አብሬው እኖራለሁ።

                                አንተስ ወንድሜ ማነህ? ያለኸው የትነው?፣

                                  የወደቅኸው፣ ከወዴት ነው?፣

                                  ስታበዛ ሩጫ፣ ልብስ ስትሻ፣

                                 የትም የለ፣ ማካካሻ፣

                                     የዚህ ዓለም ማረሳሻ፣

                                ይልቅ ና አበባ ሰው፣

                                መርገፍ ገላ፣ ከሚፈርሰው፣

                               አዲስ አርጎ፣ የሚያድሰው፣

                                 ክርስቶስን ልበሰው!!!!
«ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ» ኤፌ 4፣24



Thursday, January 5, 2012

የአባታችሁን ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ!



ደጀሰላምና አንድ አድርገን የተባሉ ብሎጎችን እንጠይቃለን
 

                              ወንጌል ደግሞ«የአባታችሁን ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ» ይላችኋል።ዮሐ ፰፣፵፬

(by dejebirhan)ይህንን ቃል የተናገረው የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ለፈሪሳውያን ካህናት ነበር። ጌታ የመጣው የታሰሩትን እንዲፈቱ፣ በሞት ጥላ ስር ያሉ ወደሕይወት እንዲመጡ ነበርና የመንግሥቱን ወንጌል በቃል እያስተማረ፣ ኃይሉንም በግብር እየገለጠ የመጣ የይቅርታና የምህረት ባለ ቤት መሆኑን አሳይቷል። ከዚህም ውስጥ አንዱ የሆነው ጉዳይ ፈሪሳውያን በዝሙት የተያዘችውን ሴት በክስ ወንበር አቁመዋት እንደሕጋቸው በድንጋይ ተወግራ የምትገደል መሆኑን ቢያውቁም ጌታችንን ሊፈትኑትና የሚከሱበትን ምክንያት ሲሹ ፈታኝ በሆነው መንፈስ እየተነዱ ዘማዊቷን ከፊቱ አቅርበው የሙሴ ሕግ ተወግራ ትገደል ይላል፣ አንተስ በሕግህ ምን ትላለህ? ብለው ሲጠይቁት «መላልሰው በጠየቁት ጊዜ ግን ቀና ብሎ። ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ በድንጋይ ይውገራት አላቸው» ዮሐ ፰፣፯
ኃጢአት ያልሰራ ማንም ፈሪሳዊ ካህን አልነበረምና ውልቅ ፣ውልቅ እያሉ እሱና ሴትየዋ በመቅረታቸው ፣ ከሳሾችሽ ወዴት አሉ? ሲላት «አንድም» ብላ መለሰች፣ እሱም «ሂጂ፣ ከአሁን ጀምሮ ኃጢአት ደግመሽ አትስሪ» ብሎ በፈውስና በሰላም እንዳሰናበታት እናነባለን።
ጌታ ብርሃን በመሆኑ በጨለማ ላሉ ሊያበራ እንጂ በአንድም ስንኳ ሊፈርድ እንዳልመጣ፣ የሚፈርድበት በልጁ ባላመኑ ሁሉ ላይ አብ መሆኑን፣ ኢየሱስ ቢፈርድም እንኳን ፍርዱ እውነት እንጂ በዘማዊቷ ላይ ህግ ጠቅሰው ለመፍረድ እንደሚሹ ፈሪሳውያን እንዳይደለ፣ ለራሱ የሚመሰክር አባቱ መሆኑንና ራሱም ቢመሰክር ምስክሩ እውነት መሆኑን የሚገልጸው የወንጌል ቃል በሰፊው ተጽፎልን እናገኛለን።
ስለራስህ ራስህ እንዴት ትመሰክራለህ? እውነት አርነት ያወጣኋችል እንዴት ትለናለህ? አንተ አባቴ ብትል እኛስ አብርሃምን የሚያክል አባት አለን ብለው ሲሞግቱ በየዘመናቱ እንደተነሱት ፈሪሳውያን በዘመናችንም በተነገረው ዘላለማዊ ቃል ትንቢት ሆኖ የሚመሳሰሉበትን አንድነት  እንረዳለን። ይኸውም፣
1/ ስለኢየሱስ የሚመሰክረው አብ ነው። ራሱ ቢመሰክርም ምስክሩ እውነት ነው። ፈሪሳውያኑ ራሳቸው ህግ ጠቃሽ፣ ራሳቸው ፈራጅ፣ ራሳቸው ፈታኝ ሆነው ከሚታዩ በስተቀር አንድም የእውነት ምስክር የሌላቸው የኃጢአት ባሪያዎች ናቸው። ዮሐ ፰፣፴፬
2/ኢየሱስ በኃጢአት ላሉ መፈታትንና በሞት ጥላ ስር ላሉ መዳንን ሊሰጥ መጥቷል። ዘማዊቷን «ሂጂ፣ ደግመሽ ኃጢአት አትስሪ »ሲላትና በነጻ ከእስራት ሲያወጣት የያኔው ፈሪሳውያንም ይሁኑ የዘመኑ፣ በጨለማ የኃጢአት ዓለም ሳሉ አንድ ዘማዊ፣ ወይም በስጋ ድካም የሚሰራውን ብዙ ብዙ ኃጢአት እየጻፉ የሚከሱ፣ በድንጋይ ወግረው ለመግደል አደባባይ የሚቆሙ ናቸው። ምክንያቱም እነሱ «እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፥ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና» ዮሐ፰፣፵፬ በማለት ማንነታቸውን ገልጿል። ይባስ ብለውም ራሳቸው የሰይጣንን ስራ እየሰሩ ሳለ በተቃራኒው የራሳቸውን ግብር ለኢየሱስ ሰጥተው «አንተ ሳምራዊ እንደሆንክና ጋኔን እንዳለብህ እናያለን» ሲሉ ሰድበውታል። በእነሱ ዘንድ ሳምራዊ የሆነ ሰው ሁሉ ጋኔን አለበት፣ ከእነሱ ውጪ የተለየ ሃሳብም ያለው ጋኔን የያዘው ነው ማለት ነው። ዛሬም የዘር ውርስ ፈሪሳዊነትን የተረከቡት የሚጠሉትን አንተ ርኩስ ሳምራዊ ብለው ጎራ ይለዩበታል፣ ያለ የሌለ ኃይላቸውን ይዘው ይዘምቱበታል።
ከዚህ በላይ ያየነው የእግዚአብሔር ምርጦች ነን፣ የአብርሃም ልጆች ነን፣ የሙሴን ሕግ የምንጠብቅ ጥንቁቆች ነን እያሉ ነገር ግን እገሌ ተሃድሶ፣ እገሌ ሳምራዊ፣ እገሌ ሰዱቃዊ፣ እገሌ ደግሞ ኦርቶዶክሳዊ ነው በማለት እራሳቸው መርምረው፣ እራሳቸው መጽሐፍ ገልጠው፣ እራሳቸው በፍርድ ወንበር ተቀምጠው ከፈረዱ በኋላ አንደኛውን ወገን በድንጋይ ወግረው ለመግደል፣ የራሳችን የሚሉትን ወገን ደግሞ ከፍ ከፍ ሲያደርጉ ይታያሉ።
ያዕቆብ ፬፣፲፬«ሕግን የሚሰጥና የሚፈርድ አንድ ነው፤ እርሱም ሊያድን ሊያጠፋም የሚችል ነው፤ በሌላው ግን የምትፈርድ አንተ ማን ነህ? »የሚለው ቃል እነርሱ ዘንድ አይሰራም።
ዛሬም በዚህ ዘመን ክርስቶስ የሞተለትን አንድ ደካማ ወይም ኃጢአት ያሸነፈውን ወይም እነሱ ላቆሙት ህግ አልገዛም ያለውን ሰው ክስ መስርተውበት በሕጋቸው ወግረው ለመግደል፣ ራሳቸው ለኃጢአት ባሪያ ሆነው ሳሉ፣ ሌላውን ጋኔን አለብህ የሚሉ፣ የአብርሃምን ስራ ሳይሰሩ አብርሃም አባት አለን የሚሉ፣ የአባታቸውን የዲያብሎስን ስራ እየፈጸሙ በክስ አደባባይ የሚያቆሙ፣ ስም የሚያጠፉ፣ የሚደበድቡ፣ የሚወነጅሉ፣ የሀሰት አባት ልጆች መሆናቸውን የሚመሰክሩ ፈሪሳውያን በዚህ ዘመንም ሞልተዋል። ከእነዚህም ውስጥ ግንባር ቀደሞቹ ማኅበረ ቅዱሳን፣ እንደዚሁም ዓይንና ጆሮ ሆነውለት የሚሰሩ ደጀሰላምና አንድ አድርገን የተባሉ በስም ስለሰላምና አንድ መሆን የሚመስሉ፣ በግብር ግን ሰላምና አንድነት እንዳይመጣ ሌሊትና ቀን የሚደክሙት ተጠቃሾች ናቸው። ይህም በማስረጃ ይረጋገጣል።ውድ አንባቢያን አስተዋይ ልቦና ኖሮን እንደእግዚአብሔር ቃል እውነቱን በማወቅ ለወንጌሉ ምስክር ልንሆን እንደሚገባን በአጽንዖት አሳስባለሁ!!
ከታች ያለውን አስረጂዎች ይመልከቱ።