Friday, April 10, 2015

"ሰላማችን ክርስቶስ ነው"



"ሰላማችን ክርስቶስ ነው"
ዓለም ዛሬ በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ምክንያት በታላቅ ሥጋት ላይ ወድቃ ትሸበራለች። ድርቅና በረሃማነት የዓለምን ሕዝብ ለረሃብና ለበሽታ አጋልጦታል። ከዓለም ሕዝብ ከፊሉ ያህል በጎርፍ: በረሃብ: በበሽታ: በመሬት መንቀጥቀጥና በዐውሎ ንፋስ ሕይወቱንና ንብረቱን እያጣ ነው።
  ይህም ብቻ አይደለም: አንዱ መንግሥት ከሌላው በፖለቲካ: በድንበር: እየተናቆረ: በንግድ ውድድር እየተጎናተለ ጉልበተኛው መንግሥት ደካማውን እያጠቃ ነው። እንዲያውም የአንዳንድ አገር ሕዝብ እርስ በእርሱ በጦርነት ሲተላለቅ ይታያል። ስለዚህም ነው "ሰላም:ሰላም!" የሚል ድምፅ በዓለማችን ዙሪያ በከፍተኛ ሁኔታ የሚያስተጋባው።
    የርግቧ ሥዕል ከነወይሯ ቀንበጧ በየጋዜጣው: በየመጽሔቱና በየቅ'ስቱ በሠፊው ተሥላ ትታያለች።
የተባበሩት መንግሥታት መልእክተኞችም በየቦታው በአስታራቂነት ይሯሯጣሉ። ይህ በዚህና በዚያ የሚሰማው ጩኸት: የሚደረገው ሩጫና ግርግር የተከሠተውን ውጥረት በመጠኑ ለማርገብ እንጂ እውነተኛውን መሠረታዊ ሰላም ለማስፈን አልቻለም።

እውነተኛው ሰላምስ? መቼ: እንዴት ይገኝ ይሆን? የእግዚአብሔር ቃል ለዚህ መልስ አለው።

  " እርሱ ሰላማችን ነውና: ሁለቱን ያዋሃደ: በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ: ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ: ሰላምንም ያደርግ ዘንድ: ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው። መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን የምሥራች ብሎ ሰበከ። በእርሱም ሥራ በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት አለንና።" ይላል።
 (ኤፌ 2:21-30)
 ሰው ራሱን: መሰሎቹንና ተፈጥሮንም ጭምር መጥላቱንና መጒዳቱ : ከእግዚአብሔር ጋር የመጣላቱ ውጤት ነው። አሁንም ከእግዚአብሔር ጋር እንድንስማማና ሰላም እንዲኖረን የእግዚአብሔር ቃል ይመሰክርልናል።
  ስለሆነም ሰው ሁሉ እግዚአብሔር ባዘጋጀለት የዕርቅ መንገድ ከአምላኩ ጋር ለመታረቅ እሺ ባይነት ቢኖረው ኖሮ " ሰላም በምድር" ይሆን ነበር።
ከክርስቶስ ጋር ያልታረቀች ዓለም ሰላም ይኖራታል ተብሎ አይታሰብም። ስለሆነም የትንሣዔን በዓል ስናከብር በልማዳዊ ሥርዓት " እንኳን አደረሰህ: አደረሳችሁ" ከመባባል ባለፈ በዕለታዊ ኑሮአችን ሁሉ የተለወጠ: ከክርስቶስ ጋር የታረቀ ሰላማዊ የሕይወት መገለጥ ልናሳይ ይገባል። ካልተለወጥን በስተቀር ሰላም በአካባቢያችንና በዐለማችን ሊኖር አይችልም።
አሁንም ነገም "ሰላም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ" ይሁን! እንል ዘንድ ከክርስቶስ ጋር እንታረቅ።
መልካም ትንሳዔ!!
(በ1984 ዓ/ም ከታተመው ጮራ መጽሔት ቁጥር 3 ተሻሽሎ የተወሰደ)