Monday, February 18, 2013

ኢትዮጵያን የእስልምና ሀገር ለማድረግ ከሃሳብ ያለፈ እንቅስቃሴ አለ!

( ክፍል ሁለት )

አንዳንድ ግለሰቦችና ማኅበራት ማለትም ማኅበረ ቅዱሳንና አፈቀላጤው ዳንኤል ክብረትን  ጨምሮ ባለፉት ጊዜያት በኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው የእስልምና አክራሪ እንቅስቃሴ የምስል፤የጽሁፍና  የድምጽ መረጃ ለማቅረብ ሞክረው ነበር። እነዚህ ክፍሎች የቆሙበትን ዓላማ ወደጎን ትተን በወቅቱ ስለአክራሪ እንቅስቃሴ  የአስጊነት ደረጃ መናገራቸውንም ደግፈነዋል። ቤተክህነቱ ዝምታን በመምረጡና መንግሥትም ለማዳመጥ ባለመፈለጉ በሎሌችም ወገኖች ጭምር ሲነገር የቆየው ችግር ዛሬ ላይ ለያዥ ያስቸገረ እስከመሆን ባልደረሰም ነበር።

  መንግሥት አብዛኛውን ጊዜ እሱን የሚጠቅም መስሎ እስከታየው ድረስ  ሊያስከትሉ የሚችሉ ጉዳቶችን ከኢምንት ይቆጥራቸዋል ወይም ይንቃቸዋል።  የማንም ስስ ስሜት ተጎዳ አልተጎዳ፤  የራሱ ጉዳይ  እስከማይመስለው ድረስ የሚሰሙ ድምጾችን ወደጎን ትቶ ረጅም መንገድ  በመሄድ  ዓላማውን ሲተገብር  የሌሎች መንጫጫት ግድ የሚሰጠው  አይደለም።  በዚህ የተነሳ ጠቃሚ የልማት እንቅስቃሴዎች ሳይቀሩ እንደጉዳት የሚታዩበትን አጋጣሚ እየፈጠሩ ይገኛሉ።

  ኢትዮጵያ ውስጥ የእስልምና አክራሪ እንቅስቃሴ ስለመኖሩ ሲነገር የቆየው ረጅም ጊዜ አስቆጥሯል። ችግሮች ገዝፈው የስጋት ደረጃቸው ከማደጉ በፊት አስፈላጊውን እርምት በወቅቱ መውሰድ ሲገባው አሁን ተበጠበጥኩኝ ብሎ ዛሬ ላይ ተነስቶ «ሐረካት» በሚል ድምጽ እሱም በተራው ቢጮህ  ማን ይስማው?  ለዓመታት በአክራሪዎች ጉዳት ያለቀሱ ወገኖችን እምባ ማበስ አቅቶት  ዛሬ ምን አገኘ? የሚሉ ጥያቄዎች የሚሰሙት ለዚህ ይመስለናል። በአጭሩ በወቅቱ የእኛ የተጎጂዎችን  ድምጽ ለመስማት ባለመፈለግህ አሁን በተራችን ያንተን ድምጽ አንሰማም ነው እየተባለ ያለው። ችግሩ አክራሪዎች የሉም ማለት ሳይሆን በአክራሪዎች ላይ መወሰድ የነበረበት የእርምት እርምጃ ዘግይቷል ነው የሚሰማው ድምጽ።  ይህንን የጊዜ መተላለፍን አጋጣሚ ደግሞ የፖለቲካ ነጋዴዎች ይጠቀሙበታል። አክራሪ፤ ተጎጂ፤ መንግሥትና ፖለቲካ በየራሳቸው መንገድ ሄደዋል።

ሌላው ችግር ልማት የሚባለው ነገር ነው። በመሠረቱ ልማት ለአንድ ሀገር እድገት ወሳኝ ነው። ለድህነታችንም  ዋናው ምክንያት ልማት አለመኖሩ ነው። ይህንን ችግር ለመቅረፍ መንግሥት ቢሰራ የሚጠላ የለም።  በእርግጥ መንግሥትን የሚጠሉ አካሎች ልማቱን በአሉታዊ ጎኑ በመፍታት ለትርፍ አይሰሩበትም አይባልም። መንግሥት አሉታዊ ጎኖችን ለመቀነስ የልማቱን ሃሳብ በሕዝብ ልብ ውስጥ ከማስቀመጡ በፊት በራሱ ጉልበት ለመወጣት ይፈልጋል። ከዚህ ውስጥ የዛሬማ ወንዝ የስኳር ልማት ተጠቃሽ ነው። ከዋልድባ ገዳም ጋር የሚዋሰነውን የስኳር ልማት ለማስፋፋት መንግሥት አስቀድሞ ወደሕዝብ ማወያየት መግባት ያልፈለገው ፤ አወያይቶ የሚመጣውን  የእምቢታና የተቃውሞ ድምጽ ከማስተናገድ ይልቅ ሥራውን ጀምሮ የሚመጣውን ተቃውሞ ማቃለል ይሻላል ከሚል እሳቤ የተነሳ ይመስለኛል።  ይህ  የልማት ስልት ከእስልምናው የሰለፊ እንቅስቃሴ ጋር በተመሳሳይ ጊዜ በመደረጉ ዋልድባ ተነካብን ከሚሉ ሰልፈኞች ጋር በአንድ ጎራ የማይስማሙትን እንዲስማሙ እድል ከፍቷል። ጳጳሳት ነን የሚሉቱ ሳይቀር «አላህ አክባር» የሚል አዛን እስከማሰማት የደረሱት የፍቅር መጠናቸው ዛሬ ድንገት ስለጨመረ ሳይሆን መንግሥት ሁለቱንም  ወገኖች ምን ያመጣሉ? በሚል ስንጥር  በአንድ ወቅት ስለወጋቸው ብቻ ነው። ይህ ደግሞ ለፖለቲካ ነጋዴዎች ጥሩ የትርፍ ጊዜ ነው። ንግድ ደግሞ አዋጭ ቦታና ሰዓት ይጠብቃል። እውነት ለመናገር በዚህ የተነሳ «ጂሐዳዊ ሐረካት» የተባለው ፊልም ከቀልድ ጫወታነቱ ያለፈ አልሆነም።  


 ችግሩ ደግሞ መንግሥት ቢበደል እንኳን ሌላውን ለማሳመን ከእንግዲህ እያጣ የሚሄደው አቅም ነው። « የማዝነው በመዋሸትህ ሳይሆን ዳግመኛ ላምንህ ባለመቻሌ ነው» የሚባለው ይሄኔ ነው። እንዳለመታመን ደግሞ ኪሳራ የለም። ሕገ ወጥ ቤት ሲፈርስ  ሕገ ወጡ ነገር ቤት ሰሪዎቹ ሳይሆን ሕገ ወጡ ነገር መንግሥት ባለበት ሀገር በግልጽ ሲሰራ ለማየት አለመቻል ነው። ቤት መሬት ላይ የሚተከል ግዙፍ አካል እንጂ ቀን ቀን ኪስ የሚከቱት ማታ፤ ማታ አውጥተው የሚያስቀምጡት ቦርሳ አይደለም።  አንድን ችግር እስኪፋፋ መጠበቅ የችግሩ ሰለባ በሆነው  ዓይን ውስጥ በርበሬ መነስነስ ይሆናል። እርምት፤ እርምጃና ልማት ማካሄድ በተጠና ስልትና ወቅት መሆን ሲገባው ምን ያመጣሉ የሚለው ጀብድ አዋጭ መንገድ አይደለም። ሀገር የሚመራ መንግሥት መንፈሳዊ ሆኖ የጽድቅ አገልግሎት መስጠት ባይችል ለታሪክና ለትውልድ የሚተርፍ  መልካም ሥራ መፈጸም ይጠቅበታል እንላለን። መልካም ሥራን በሰዓቱ መሥራት በራሱ ሕጉን መፈጸም ነውና።

ይህ ሁሉ ሆኖ ኢትዮጵያ ውስጥ የእስልምናም ይሁን የክርስትና አክራሪነት የለም የሚሉ ወገኖች መኖራቸው እውነት ነው። እውነቱ ግን ኢትዮጵያን ወደእስልምና ለመቀየር እንቅስቃሴ መኖሩ ነው። የእስልምናው አክራሪ ሸሪአ ሕገ መንግሥታችን ይሆናል የሚል ዓላማን ያነገበ ነው። የክርስትናው አክራሪ እኔ የምለውን የማይቀበል ሁሉ ይጠረጋል የሚል ነው። ሲፈጸም የቆየውም እንቅስቃሴ የሚያሳየው ይህንን ስልት ወደ ከፍተኛው እርከን ማሳደግ ነው። አክራሪው የሰለፊ እስላም ምኞቱን ለመተግበር የእስልምናውን የሥልጣን ማማ መቆጣጠር ሲፈልግ  የኦርቶዶክስ ክርስትናው ሰለፊ ደግሞ ሲኖዶሱን በራሱ ሰዎች የመቆጣጠር ስልትን ይከተላል። ልዩነቱ የሚነሳው የኦርቶዶክሱ ሰለፊ፤ እስልምና ይጥፋ አለማለቱ ሲሆን የእስልምናው ሰለፊ ግን ከእኔ በቀር አንዳች እምነት መኖር የለበትም የሚል መሆኑ ነው።

ለዛሬ የእስልምናው ሰለፊ አክራሪ እንቅስቃሴ ማሳያ የሆነውን የድምጽ መረጃ /Muslim interfaith/ በተባለው የአክራሪዎች መድረክ ላይ የተደረገውን ውይይት አቅርበናል። ያልተዋጣለትን የጂሃዳዊ ሀረካት ፊልም በመመልከትና ራስን በማዘናጋት አክራሪ የለም  ማለት ተገቢ አይደለም እንላለን።