Wednesday, November 9, 2011

ክብር ለሚገባው ክብር ስጡ!



ሮሜ 13፣7 «ለሁሉ የሚገባውን አስረክቡ፤ ግብር ለሚገባው ግብርን፥ ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን፥ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፥ ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ»

ክብር ለአንድ ነገር ዋጋ መስጠትን ይመለክታል። ዋጋው ደግሞ በዓይነት፣በገንዘብ፣በጉልበትና
በሃሳብ ወይም በመንፈስ ሊገለጥ ይችላል። የሰው ልጅ በሕይወቱ ዘመን ይህንን ዋጋ ሲከፍል ኖሯል፤ ይኖራልም። ሰው ለፈጣሪውና ለሚያመልከው፤ ለሚበልጠው፤ ለሚወደው፤ ለሚፈራው፤ ለሚመራው ክብርን ይሰጣል። ምናልባት የሚሰጥበት መንገድና የሚሰጥበት ምክንያት ይለያይ እንደሆነ እንጂ ክብርን ስለመስጠት ሃሳብ ጥያቄን የሚያስነሳ ጉዳይ እንዳልሆነ እንስማማለን።

ሰው ፈጣሪው ስላደረገለትና ስለሚያደርግለት ነገር ሁሉ ክብርንና ምሥጋናን ይሰጣል። ክብርን የሚሰጠው ስለተደረገለት ብቻ ሳይሆን ፈጣሪ በመሆኑ ክብር ስለሚገባውም ጭምር ነው።

ነቢዩ ሙሴና ሕዝቡ እግዚአብሔር ከጠላት እንዳዳናቸው ደስታቸውን በዝማሬ ገልጠው ክብር ሰጥተውታል።

«በዚያም ጊዜ ሙሴና የእስራኤል ልጆች ይህንን መዝሙር ለእግዚአብሔር ዘመሩ፥ እንዲህም ብለው ተናገሩ። በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ» ዘጸ ፲፭፣፩

ክብሩ ከፍ ከፍ ያለ፣ ኃይልና ሥልጣን በእጁ የሚገኝ፣ ማድረግ የሚፈልገውን ከማድረግ የሚከለክለው ለሌለ ምስጋና ይገባዋል ሲሉ ተገቢውን ክብር ሲሰጡ እናያለን። ስለተደረገላቸው ብቻ ሳይሆን ክብሩ ፍጹማዊ በመሆኑ ለመለኰታዊነቱ ተገቢ ክብር እንደሆነም ሌላ ሥፍራም እንደዚሁ ምሥጋና ሲሰጡ እናገኛቸዋለን።

«በተራራው ራስ ላይ በእስራኤል ልጆች ፊት የእግዚአብሔር ክብር መታየት እንደሚያቃጥል እሳት ነበረ» ዘጸ ፳፬፣፲፯

ክብሩ ታላቅና ሰው ሊቀርበው የማይችል መለኮታዊ እሳት ስለሆነ ክብርና ምስጋና የተገባው ነበረ። የእግዚአብሔር ክብር በቦታና በሥፍራ አይወሰንም፣ መለኮታዊ አገዛዙ ሁሉን የመላ ስለሆነም ጭምር ክብር ይገባዋል። ሁሉን በሙላት መሸፈን የሚችል ያለእሱ ማንም የለምና።



ነገር ግን እኔ ሕያው ነኝና በእውነት የእግዚአብሔር ክብር ምድርን ሁሉ ይሞላል»ዘኁ፲፬፣፳፩
በሁሉ ሥፍራ ያለ፤ የሚገኝ የክብር አምላክ እንደእግዚአብሔር ብቻ ነው። ሌሎች ይከበራሉ ወይም ክብር ይገባቸዋል ብንል በራሳቸው የሌላቸውን ነገር ከሌላ የሚቀበሉ ምሉዕነት በራሳቸው የሌላቸው ናቸው። እግዚአብሔር ግን በሁሉ ስፍራ የመላ ስለሆነ ክብርና ግርማው፣ ኃይልና ደስታው ከሌላ ከማንም የሚሰጠው ሳይሆን በራሱ መለኰታዊ ሥልጣኑ ውስጥ የሚገኝ ነው።

«ክብርና ግርማ በፊቱ፥ ኃይልና ደስታ በስፍራው ውስጥ ናቸው» ፩ኛ ዜና ፲፮፣፳፯
የእግዚአብሔርን ክብር ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ እንዴት እንደተሰሩ፤ ማን እንዳጸናቸው ሌሎች ፍጥረታትም ክብሩን ይገልጻሉ፤ ይናገራሉ።
«ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፥ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል» መዝ ፲፣፩ የእግዚአብሔር ክብር ታላቅ መሆኑ የሚታወቀው እስራኤላውያን ስለተደረገላቸው ነገር ስላከበሩት ወይንም ማንም የማይደርስበት መለኰታዊ እሳት በመሆኑ ወይንም ክብሩ ሁሉንም ሥፍራ የመላ ስለሆነ ወይንም ፍጥረታት ሁሉ ስለመሰከሩ ሳይሆን:
«እርሱ ብቻ የማይሞት ነው፤ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ይኖራል፤ አንድ ሰው እንኳ አላየውም ሊያይም አይቻለውም፤ ለእርሱ ክብርና የዘላለም ኃይል ይሁን፤ አሜን» ፩ኛ ጢሞ ፫፣፲፮ እንዳለው እርሱ የማይሞት፣ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን የሚኖር፣ አንድም ስንኳ ያላየው፤ ሊያየውም የማይቻለው፣ ክብርና ኃይል ለእርሱ ብቻ የሆነ ስለሆነ ነው።

እኛም ለዚህ የክብር አምላክ ብቻ አምልኰና ስግደት ልንሰጠው ይገባል። ሁሉን የፈጠረ፤ ክብርና ምስጋና የሚገባው በመሆኑ ሀያ አራቱ ሽማግሌዎች ከፊቱ ወድቀው አክሊላቸውን አውርደው፣ክብርና ምስጋና ሲሰጡት ዮሐንስ በራእዩ ተመልክቷል።
«ሀያ አራቱ ሽማግሌዎች በዙፋን ላይ በተቀመጠው ፊት ወድቀው፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም በሕይወት ለሚኖረው እየሰገዱ። ጌታችንና አምላካችን ሆይ፥ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር ውዳሴ ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል እያሉ በዙፋኑ ፊት አክሊላቸውን ያኖራሉ» ራእ ፬፣፲፩
ለእግዚአብሔር የሚሰጠውና ሊሰጥ የሚገባው ክብር ከላይ በአጭሩ ለማስቀመጥ እንደተሞከረው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጭብጥ አንጻር ሲሆን ሌሎችስ ክብር የሚገባቸው ይኖራሉ? ካሉስ እንማን ናቸው? እንዴትና እስከየት ድረስ ነው ክብራቸው? የሚለውን መመልከቱ ጠቃሚ ስለሆነ እሱንም በጥቂቱ እንመልከት።

"የሌሎች ክብርና አከባበር እንዴት ነው?

"፩ኛ-እናትና አባት፣

እናትና አባት ራሳቸው የእግዚአብሔር ሥራዎች ስለሆነ ለእግዚአብሔር የሚገባው ምስጋና ሊሰጣቸው እንደማይገባ ጥያቄ አያስነሳም። እነሱ ራሳቸው የሚያከብሩት አምላክ ስላለ ለእነርሱ በልጅነታችን የምንሰጠው ክብር ባላቸው ደረጃ ነው። የመጀመሪያዋ የሰው ልጆች እናት ሔዋን ናት፤ መጽሐፍ ቅዱስ የሕያዋን ሁሉ እናት ይላታል።

«አዳምም ለሚስቱ ሔዋን ብሎ ስም አወጣ፥ የሕያዋን ሁሉ እናት ናትና» ዘፍ ፫፣፳

ለእናቶች የሚገባው ክብር ከሔዋን፣ ለአባቶችም የሚገባው ክብር ከአዳም ይጀምራል። እናትህንና አባትህን አክብር ሲል የሕያዋን ሁሉ እናት እና የሕያዋን ሁሉ አባት ከሆኑት አዳምና ሔዋን ሊጀምር የግድ ነው። ምክንያቱም አዳምና ሔዋን በሌሉበት መመስገንን ሊቀበል የሚችል የሥጋ አባትና እናት ባልኖረም ነበርና የሕያዋን ሁሉ ተብሎ ተነገረን።

"«አባትህንና እናትህን አክብር እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድር ዕድሜህ እንዲረዝም» ዘጸ ፳፣፲፪ በሚለው ቃል ደግሞ እድሜአችን እንዲረዝምና እንዲባረክ በሥጋ የወለዱንን እናትና አባት

እናከብራለን። እንታዘዛለን፤ የሚነግሩንን እንጠብቃለን፣ እኛ ልጆቻቸው በእውቀት እንበለጽግ ዘንድ የሚሰጡንን ትምህርትና ጥበብ እንይዛለን፣ መጽሐፍ እንደነገረን።
«ልጄ ሆይ፥ የአባትህን ትእዛዝ ጠብቅ፥ የእናትህንም ሕግ አትተው»ምሳ፮፣፳
«የወለደህን አባትህን ስማ፥ እናትህም ባረጀች ጊዜ አትናቃት» ምሳ ፳፫፣፳፪
«አባትህና እናትህ ደስ ይበላቸው፥ አንተንም የወለደች ደስ ይበላት» ምሳ ፳፫፣፳፭
«በአባትዋ የምታላግጥን የእናትዋንም ትእዛዝ የምትንቅን ዓይን የሸለቆ ቍራዎች ይጐጠጕጡአታል፥ አሞራዎችም ይበሉአታል» ምሳ ፴፣፲፯
«አባትህንና እናትህን አክብር፥ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ አለው»ማቴ፲፱፣፲፱
«ሙሴ፣ አባትህንና እናትህን አክብር፤ ደግሞ አባቱን ወይም እናቱን የሰደበ ፈጽሞ ይሙት ብሎአልና» ማር ፲፯፣፲

ይህ እንግዲህ ለወለዱን እናትና አባት የምንሰጠው ክብር ነው። በመውለዳቸው ብቻ የሚያገኙት ክብር ነው።


፪ኛ- ነገሥታትና መኳንንት
«ምሳሌ 8፥15 ነገሥታት በእኔ ይነግሣሉ፥ ሹማምቶችም የቀናውን ነገር ይደነግጋሉ» እንዳለው የምድር ነገሥታት ሁሉ የሚነግሡት የነገሥታት ንጉሥ በሆነው በእግዚአብሔር ፈቃድ ብቻ ነው። አንዳንዶቻችን በራሳቸው ትግልና ጥበብ ወይም ባገኙት ጊዜና አጋጣሚ የገዢነትን ዙፋን የተፈናጠጡ ይመስለን ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ነገሥታት በእኔ ይነግሳሉ ሲል አስረግጦ ይነግረናል። ክፉ ገዢዎችና መሪዎች እንዲነግሱብን የተደረገው ለምንድነው ብንል «በመጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ ፲፪፥፲፬
«እግዚአብሔርን ብትፈሩ ብታመልኩትም፥ ቃሉንም ብትሰሙ፥ በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ላይ ባታምፁ፥ እናንተና በእናንተ ላይ የነገሠው ንጉሥ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ብትከተሉ፥ መልካም ይሆንላችኋል. በሚለው ቃል የተነሳ ሰዎች እግዚአብሔር እንደሚፈልገው ሳያመልኩትና ሳይገዙለት የሚመጣ የራሳችን የሥራ ውጤት እንጂ እግዚአብሔር ጨካኝ ገዢ እንዲሾም ፍላጎቱ ሆኖ አይደለም። ምንም እንኳን ክፉ ገዢዎች ቢሆኑም የተጫነው ሸክም እንዲቀልና በመልካም የሚመራን መሪ እንዲሰጠን ለሾማቸው መገዛት ይገባል።

፩ኛ የጴጥሮስ መልእክት፪፥፲፫ ስለ ጌታ ብላችሁ ለሰው ሥርዓት ሁሉ ተገዙ፤ ለንጉሥም ቢሆን፥ ከሁሉ በላይ ነውና»

ስለዚህ ገዢዎችና ሹማምንቶች በእግዚአብሔር የሚነግሱ ስለሆነ ክብራቸው እስኪመለኩ ወይም እስኪሰገድላቸው አይደለም። ምክንያቱም ሰጪና ነሺ ንጉሥ በላያቸው ስላለ ነው። በዘመናት ውስጥ ለእኔ ስገዱ፤ አምልኩ ያሉ ገዢዎች ሲኖሩ የፍርሃት ስግደትና አምልኰ የሰጡ እንዳሉም ታይቷል፤ እንደዚሁም አንሰግድም፤ አናመልክም ያሉም ለእሳት፤ ለአውሬ ተጥለዋል። ለሞት ተዳርገዋል።

ይሁን እንጂ ገዢዎችን የምናከብረው እግዚአብሔር ስለሾማቸው ብቻ ነው። ስግደት አይገባቸውም፤አምልኰም ድርሻቸው አይደለም። መሪዎች መጀመሪያና መጨረሻ ስላላቸው ይህ አይገባቸውም።

፫ኛ- ቅዱሳን

ቅዱስ ማለት ልዩ፣ የተለየ ፤ምስጉን፣ የተመሰገነ ማለት እንደሆነ ሁሉ ቅድስናውና የተቀደሰበት መነሻና መድረሻ፤ ልዩ የሆነለት ዓላማና ግብ አለው ማለት ነው።

ስለዚህ ቅዱሳንን ቅዱስ ብለን ስንጠራቸው ለእግዚአብሔር የተለዩ፤ የተመረጡ፤ ለአገልግሎቱ የታዘዙ፤ ዓላማቸው ፈቃዱን መፈጸምና ግባቸው ከእርሱ ጋር መኖርን በሕይወታቸው ያሳዩ ስለሆነ ነው።


«ዘሌ20፥7 እንግዲህ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና ሰውነታችሁን ቀድሱ፥ ቅዱሳንም ሁኑ» ቅዱሳን እግዚአብሔርን ያከብራሉ፤ ያመሰግናሉ።

መዝ ፻፵፭፤፲፥10 አቤቱ፥ ሥራህ ሁሉ ያመሰግኑሃል፥ ቅዱሳንህም ይባርኩሃል» ለእግዚአብሔር ፈቃድ በመታዘዝ ከኃጢአት ተለይተው የሚኖሩ ሁሉ ቅዱሳን ናቸው።

«ዘሌ20፥26 እኔ እግዚአብሔር ቅዱስ ነኝና፥ ለእኔም ትሆኑ ዘንድ ከአሕዛብ ለይቻችኋለሁና ቅዱሳን ትሆኑልኛላችሁ

«መዝ ፹፱፣፲፭ አቤቱ፥ ሰማያት ተኣምራትህን እውነትህንም ደግሞ በቅዱሳን ማኅበር ያመሰግናሉ» የክርስቶስን ትእዛዛት የሚጠብቁ፤ በመንገዱም የሚሄዱ ሁሉ ቅዱሳን ቅርጫፎቹ ናቸው።
«ሮሜ ፲፩፣፲፮ በኵራቱም ቅዱስ ከሆነ ብሆው ደግሞ ቅዱስ ነው፤ ሥሩም ቅዱስ ከሆነ ቅርንጫፎቹ ደግሞ ቅዱሳን ናቸው»

፩ኛ ቆሮ ፩፣፪ በቆሮንቶስ ላለች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፥ በክርስቶስ ኢየሱስ ለተቀደሱት፥ የእነርሱና የእኛ ጌታ የሆነውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በየስፍራው ከሚጠሩት ሁሉ ጋር ቅዱሳን ለመሆን ለተጠሩት»

ክርስቶስ ኢየሱስ የሞተልን በቀደመው ሰው በኩል ያጣነውን ቅድስና በእርሱ ሞት ሞትን ገድሎ የቅድስና ርስታችንን ሊመልስ ነው። ለእርሱ የተለየን ልጆች ሊያደርገን ነው።

«ቆላስ 1፥13-14 እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን»

በማለት ሐዋርያው ጳውሎስ እንደተናገረው ከጭለማ አገዛዝ የወጣነውንና በዚያ በወጣንበት የልጅነት ፍቅሩ መንግሥት የምንኖር ሁላችንን እንጂ ለእነእገሌ ወይም ለእነእገሊት ብቻ የተሰጠ አይደለም።

በ፩ኛ ዮሐ መልእክት ላይ

፪፥፳፱ ጻድቅ እንደ ሆነ ካወቃችሁ ጽድቅን የሚያደርግ ሁሉ ከእርሱ እንደ ተወለደ እወቁ።
፫፥፯ ልጆች ሆይ፥ ማንም አያስታችሁ፤ እርሱ ጻድቅ እንደ ሆነ ጽድቅን የሚያደርግ ጻድቅ ነው» በሚል ቃል የተጻፈው የማይካድ ቃል ነውና ጽድቅን የሚያደርግ እርሱ ቅዱስ ነው።

እንግዲህ ቅዱሳን ማለት የእግዚአብሔርን ቃል የፈጸሙ፤ የጠበቁ፣ የታዘዙ፣ በወንጌል የተሰጠውን የመዳን ቃል የሕይወታቸው መመሪያ ያደረጉ፣ በችግር፣ በመከራ፣ በስቃይ፣ በመገረፍ ወይም በመሰደድ እና በመሳሰለው ጸንተው የተገኙ ሁሉና እንደዴማስ ወደኋላ ሳይመለሱ፣ እንደእሪያ በቀደመው የኃጢአት ጭቃቸው በመኖር ዘመናቸውን ያልጨረሱ ናቸው ማለት ነው።

ይህ ቃል ያንን ያረጋግጥልናል።

1ኛ የጴጥሮስ መልእክት1፥15-16 ዳሩ ግን እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ-

በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ።

፫/ሀ -ቅድስና እንደዚህ ከሆነ የሚሰጠው ክብርስ?

መቼም ቢሆን ለቅዱሳን ስግደትና አምልኰ ስጡ፣ ውዳሴና ምስጋና አፍስሱላቸው የሚል መጽሐፍ የለም። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከእውቀት ማነስ እንደዚህ ዓይነት የሰሩ ሰዎች ቅዱሳን ለሆኑ የክርስቶስ አማኞች ያንን ያደርጉ ዘንድ አያደፋፍርም።

ለመላእክት ስግደት ይገባል ከሚሉ ሰዎች የሚቀርበው መረጃ የመጀመሪያው ጥቅስ በዘኁልቊ
፳፪፣፴፩ ላይ በለዓም የተባለው ሟርተኛ ሰው ታሪክ ነው። በለዓለም የእግዚአብሔር ሰው አልነበረም። ስራው ማሟረት ነው። መርገምና መመረቅ!

ዘኁል ፳፪፥፯ ላይ እንዲህ ይላል፣

የሞዓብ ሽማግሌዎችና የምድያም ሽማግሌዎችም የምዋርቱን ዋጋ በእጃቸው ይዘው ሄዱ ወደ በለዓምም መጡ፥ የባላቅንም ቃል ነገሩት።

በለዓም እንግዲህ እንዲህ ዓይነት ገንዘብ እየተቀበለ በሟርት የሚኖር ሰው ነው ማለት ነው። ገንዘብ ተከፍሎት በክፉ መንፈስ እስራኤልን ያጠፋ ዘንድ ለተዘጋጀው ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ እንዳይራገም ከለከለው፤ ሳይወድ እርግማኑን ወደ ምርቃት ለወጠው። ከሞዓብ ሰዎች ጋር እየሄደ ሳለ የተቀመጠባት አህያ መልዓኩን አይታ ከግንብ ስታጣብቀውና በሰው አፍ ስታናግረው የነበረውን ታሪክ እናነባለን። እሱም መልዓኩን አይቶ መሬት ወድቆ እንደሰገደም ይነግረናል።

ዘኁል ፳፪፥፴፩ እግዚአብሔርም የበለዓምን ዓይኖች ከፈተ የእግዚአብሔርን መልአክ በመንገድ ላይ ቆሞ የተመዘዘም ሰይፍ በእጁ ይዞ አየ ሰገደም፥ በግምባሩም ወደቀ።

ይህንን ቃል እየጠቀሱ የበለዓምን ስግደትና ለመላእክት ወድቆ መደፋት እንደሚገባ ይደግፈናል ከሚሉ ሰዎች በመረጃነት ይቀርባል። ይሁን እንጂ ሊታወቅ የሚገባው ነገር ፣

፩/ በለዓም ሟርተኛ እንጂ የእግዚአብሔር ሰው አልነበረም።

፪/ በለዓም የእስራኤል ሕዝብ ባለጋራ ሆኖ ለእርግማን ገንዘብ የተቀበለ የአዲስ ኪዳኑ ዓይነት ሲሞን መሰርይ ነው።

የሐዋ 8፥9 ሲሞን የሚሉት አንድ ሰው ግን እኔ ታላቅ ነኝ ብሎ፥ እየጠነቈለ የሰማርያንም ወገን እያስገረመ ቀድሞ በከተማ ነበረ»

፫/በለዓም ኅሊናው ለእርግማን፣ ዓይኑ በገንዘብ የተሸፈነ ሰው ስለነበረ አህያዋ ያየችውን ነገር እንኳን ለማየት አልቻለም ። መልዓኩን ያየው አህያው ነግራው ነው።

ከአህያ ያነሰ ዓይን የነበረውና ቅድስናን የማያውቃት ሟርተኛ ሰው የሰገደውን እንደቅድስና ሥራ ቆጥሮ እኛም እንስገድ ማለት የበለዓም ወንድሞች እንሁን ማለት ነው እንጂ እግዚአብሔርን የሚያመልኩ ሰዎች አርአያና ምሳሌ አድርገው በለዓምን አይከተሉም። ብዙዎች የበለዓምን ወይም የአቢሚሌክን፤ የኤልሳዕን ወዘተርፈ ታሪክ በምሳሌነት ሲያቀርቡ ከዚህ በታች ስላለው ግልጽ እውነት መቀበልን አይፈልጉም። እግዚአብሔር ደግሞ ሁለት ቃል ይናገር ዘንድ ሰው አይደለምና የተነገረውን አምኖ መፈጸም ያስፈልጋል።

ዮሐንስ በራእዩ የጻፈልን ነገር እሱ ስግደትን ሊፈጽም በፈለገ ጊዜ መልዓኩ እንዳታደርግ፣ ተጠንቀቅ ብሎ ማስጠንቀቂያን ሰጥቶታል።

ራእ19፥10

ልሰግድለትም በእግሩ ፊት ተደፋሁ። እርሱም፦ እንዳታደርገው ተጠንቀቅ፤ ከአንተ ጋር የኢየሱስም ምስክር ካላቸው ከወንድሞችህ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ፤ የኢየሱስ ምስክር የትንቢት መንፈስ ነውና አለኝ።

ራእ 22፥9

እርሱም፦ እንዳታደርገው ተጠንቀቅ፤ ከአንተ ጋር ከወንድሞችህም ከነቢያት ጋር የዚህንም መጽሐፍ ቃል ከሚጠብቁ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ አለኝ።

ቅዱሳን ለመላእክት ስግደት ማድረግ የሚገባቸው ቢሆን ኖሮ መልአኩ ዮሐንስን«ተጠንቀቅ» ከሚለው ይልቅ አመሰግናለሁ፣ ይገባኛል ባለው ነበር። ከእግዚአብሔር በስተቀር ስግደትና አምልኰ ለቅዱሳን የተገባ እንዳይደለ በግልጽ ቃል «ለእግዚአብሔር ስገድ» ብሎታል። የዮሐንስን ራእይ ቃል ልዩ የሚያደርገው ነገር ስግደትን በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻ የትንቢትና ራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተቀመጠ መሆኑ ነው።

የብሉይ ኪዳን የሌዋውያን ሥርዓት መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተገኘ ብቻ ዛሬም ሊሰራበት የግድ ነው አይባልም፣ ምክንያቱም አዲስ ሥርዓት በክርስቶስ ወንጌል ተተክሏና ነው።

«፪ኛ ቆሮ ፲፭፣፲፯ ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል»

እንደዚሁ ሰዎች ሲሰግዱ ወይም ሲያመልኩ የነበረውን የእምነት ክስተትና ድርጊቶች በመልአኩ ቃል እንደተነገረው ስግደት ሁሉ ተጠቃሎ ለእግዚአብሔር ብቻ መደረግ እንዳለበት በመጨረሻ የሰጠው ማሰሪያ ቃል ተቀባይነት አለው።

የዮሐንስ ራእይ ምዕራፍ ፳፪

፱- እርሱም፦ እንዳታደርገው ተጠንቀቅ፤ ከአንተ ጋር ከወንድሞችህም ከነቢያት ጋር የዚህንም መጽሐፍ ቃል ከሚጠብቁ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ አለኝ።

፲- ለእኔም። ዘመኑ ቀርቦአልና የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል በማኅተም አትዝጋው።

፲፩- ዓመፀኛው ወደ ፊት ያምፅ፥ ርኵሱም ወደ ፊት ይርከስ፥ ጻድቁም ወደ ፊት ጽድቅ ያድርግ፥ ቅዱሱም ወደፊት ይቀደስ አለ።

፲፪- እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፥ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ።

፲፫- አልፋና ዖሜጋ፥ ፊተኛውና ኋለኛው፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ።

፲፬- ወደ ሕይወት ዛፍ ለመድረስ ሥልጣን እንዲኖራቸው በደጆችዋም ወደ ከተማይቱም እንዲገቡ ልብሳቸውን የሚያጥቡ ብፁዓን ናቸው።

ልብሳችንን ከቀደመው ኃጢአታችን አጥበን ወደጽድቅ ከተማ ለመግባት የዚህን የመጽሐፍ ቃል ጠብቁ እንዳለው እንጠብቃለን። ከእንግዲህ ስግደት ለእግዚአብሔር ነው ብሎ ማኅተሙን ክፍት ትቶታል፤ የፈቀደ እንደቀደመው ከእግዚአብሔር ውጭ ለሌላውም ፍጥረት ከመልዓኩ ቃል ተላልፎ እንዲሰግድ፤ ዐመጹንም፤ ርኵሰቱንም እንዲፈጽም የምርጫ እድል ተትቶለታል። ክርስቶስ ቶሎ መጥቶ ዋጋውን ይሰጠዋል።

እኛ እናትና አባቶቻችንን፤ ቅዱሳን መላእክትን፤ ቅዱሳን ሰዎችን፤ ጻድቃንን፤ ሰማእታትን እናከብራለን፤ የክርስቶስ የክብሩ መገለጫዎች ስለሆኑ እንወዳቸዋለን፤ እናፈቅራቸዋለን። ነገር ግን አንሰግድላቸውም፤ አንንበረከክላቸውም። ምክንያቱም እንዳታደርግ፤ ተጠንቀቅ በሚል ቃል ማኅተም ሊዘጋ መልአኩ ተናግሯልና። በዚህ ምድር እንኳን ለማኅተም ከተዘጋጀ ደብዳቤ በኋላ የሚጨመር ቃል ፎርጅድ ይባላል። የተጭበረበረ እንደማለት ነው።

ክብር ለሚገባቸው ክብር እንሰጣለን፤ ስግደትና አምልኰን ለእግዚአብሔር ብቻ!!!

«ዘአንገሠከ ክርስቶስ እምአጽናፈ ሰማይ ወምድር፤ በታሕቴሁ ለእግዚአብሔር ሰዓል ለነ አቡነ» ተክለሃይማኖት (ስብሐተ ፍቍር) ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ በመላ የነገሠ እግዚአብሔር ብቻ ነው። ተክለሃይማኖትም ከሰማይ በታች ከምድር በላይ የነገሱ አይደሉም። ሰማይንና ምድርን የሚመላ ክብር የእግዚአብሔር ብቻ ነው። መጽሐፍ እንደዚህ እንዳለ «ነገር ግን እኔ ሕያው ነኝና በእውነት የእግዚአብሔር ክብር ምድርን ሁሉ ይሞላል»ዘኁ፲፬፣፳፩»

መዝ ፻፵፰፣፲፫ «የእግዚአብሔርን ስም ያመስግኑ ስሙ ብቻውን ከፍ ከፍ ብሎአልና፥ ምስጋናውም በሰማይና በምድር ላይ ነው» እግዚአብሔር በክብሩ በሞላበት ቦታ ሌላ ሰው ሊሞላ አይችልም። የሰው ሙላት ፍጹም ሳይሆን በጊዜ፣ በቦታና በመጠን የሚወሰን ነው።
ታዲያ እነዚህ ሰዎች ምንድነው የሚሉት? ክህደታቸውን በማጠናከር እንዲህም ሲሉ ሌሊትና ቀን ይጮሃሉ።
«እማዕምቅቲሃ ለሲኦል ሶበ ጸዋዕኩከ፤ ታውጽዓኒ ነዓ ማኅጸንተከ፣ ጊዮርጊስ እዴየ እኂዘከ»
ከጥልቁ ሲኦል በጠራሁህ ጊዜ እኔን የአደራ ገንዘብህን እጄን ይዘህ ታወጣኝ ዘንድ ና! ማለት ነው። ሰዎቹ ሲኦል መግባታቸውን አስቀድመው ያወቁ ይመስላል። ያው ወደጥልቁ መውረዳቸውን። እንግዲህ ጊዮርጊስን የሚለምኑት ከተፈረደባቸው ሲኦል እጃቸውን ይዞ እንዲያወጣቸው ነው። የሚገርመው ይህ ቀልድና በእግዚአብሔር የፍርድ አሰራር ላይ እንደማሾፍ ይቆጠራል። ምክንያቱም ሰው ሲኦል ከወረደ መውጣት አይችልም። ገነት ከገባም ከሲኦል ያለውን ሰው ማውጣት አይችልምና ነው። ወንጌል እንዲህ ይላል።
ሉቃ ፲፮፤፳፮«ከዚህም ሁሉ ጋር ከዚህ ወደ እናንተ ሊያልፉ የሚፈልጉ እንዳይችሉ፥ ወዲያ ያሉ ደግሞ ወደ እኛ እንዳይሻገሩ በእኛና በእናንተ መካከል ታላቅ ገደል ተደርጎአል አለ»
ይህንን የተናገረው አበ ብዙሃን አብርም ነው። ይህ እንግዲህ በሲኦል ፍርደኞችና በገነት ጻድቃን መካከል እግዚአብሔር ያስቀመጠውና መሸጋገር እንዳይቻል ያደረገው ህግ ነው። ታዲያ እነዚህ ስብሐተ ፍቍር አድራሽ እጣ ፈንታቸው ሲኦል መሆን ከወዲሁ ያወቁ ሰዎች አብርሃም የተናገረውን አልሰሙም ወይስ ለእነሱ ይህ ሕግ አይሰራም?
እነዚህ ጥልቁ ገብቼ ስጣራ የሚሉ ሰዎች ንጉሳቸው አብዶን ይባላል፤ ለጥሪም እድል አይሰጣቸውም። ይልቅስ ይህንን ቃል ትታችሁ በሕይወት ለመኖር ወስኑ።

ራእ 9፥11
በእነርሱም ላይ ንጉሥ አላቸው እርሱም የጥልቅ መልአክ ነው፥ ስሙም በዕብራይስጥ አብዶን በግሪክም አጶልዮን ይባላል»

«እምቅድመ ሰማያት ወምድር ሐልወትኪ፣ ፀሐይ ወወርኅ ኢቀደሙኪ፣ መላእክተ ሰማይ ይትለአኩኪ» ስብሐተ ፍቍር ዘማርያም።
ማርያም ከሐናና ከኢያቄም ከመወለዷ በፊት አልተፈጠረችም። ይህ ክህደት ነው። ያልተፈጠረች ሆና ሳለ መላእክት የሚያገለግሏት እንዴት ሆኖ ነው? እግዚአብሔር ግን እንዲህ ሲል ይጠይቃል። መመለስ የሚቻለው እሱ ማነው?

ኢሳ ፵፬፥፳፬
«ከማኅፀን የሠራህ፥ የሚቤዥህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሁሉን የፈጠርሁ፥ ሰማያትን ለብቻዬ የዘረጋሁ ምድርንም ያጸናሁ እግዚአብሔር እኔ ነኝ ከእኔ ጋር ማን ነበረ?»
እንግዲህ ማርያም ነበረች በሉና ተከራከሩ!! በሌላ ቦታም ሰማይና ምድር መቅደማቸውን ከዚያም ሰው መፈጠሩን ይናገራል።

ኢሳ፵፭፥፲፪
እኔ ምድርን ሠርቻለሁ ሰውንም በእርስዋ ላይ ፈጥሬአለሁ እኔ በእጄ ሰማያትን ዘርግቼአለሁ፥ ሠራዊታቸውንም ሁሉ አዝዣለሁ። ሰማይና ምድር ሳይዘረጉ ማርያም ነበረች፤መላእክትም ያገለግሏት ነበር ማለት እብደት ብቻ ሳይሆን ክህደት ነው። ድንግል ማርያም በዚህ ውሸት አትከብርም። ማርያም እናትና አባት የነበራት፤ በድንግልና ቃል ክርስቶስን የወለደች እንጂ አረፍተ ዘመን ያልተቆጠረላት መንፈስ አይደለችም። «ናዛዚቱ ለዮሴፍ፤ የውሃቱ ለአቤል» የሚሉ ድምጾች በየቅዳሴ ማርያሙ ይሰማሉ። ማርያም፤ በዮሴፍ እስራትና በስደቱ ጊዜ አልነበረችም፤ ያ ማለት ሳትወለድ ነበረች ወይም ቆይታ ሰው ሆነች እንጂ መንፈስ ናት ማለት ነው። (ሎቱ ስብሐት እንላለን)

ቅዱሳንን ማክበር ማለት እነሱ ያላሉትንና የማይሉትን ሰዎች በልብወለድ ፈጠራ መናገር ማለት ነው? መናፍቃን ማለት የሌለውን የሚናገሩ፤ ያለውን እውነት የሚጠራጠሩ ናቸው። መናፍቃን ማለት በአንድ በኩል እግዚአብሔርን አምናለሁ፤ እድናለሁ እያሉ በሌላ በኩል ደግሞ ይሄ ነገር አያዋጥም፣ ሲኦል መውረዴ አይቀርም፣ ስለዚህ ጊዮርጊስ ከአብዶን አውጣኝ የሚሉ የሁለት ወገን ሰዎች ናቸው።
ክብር ለሚገባቸው ክብር መስጠት ማለት የማይባለውን ማለት፣ ማድረግ የማይቻላቸውን መጠየቅ ወይም ያለቦታቸው ማምለክና ማስመለክ ማለት አይደለም። ቃሉን አንብበንና ተረድተን ከቃሉ ለመስማማት እንሞክር። ከእኛ ወዲያ ላሳር ማለት አያዋጣም። አንድ ውሸት ብዙ ዓመት ሳይታወቅበት ስለኖረ እውነት አይሆንም፤ እውነቱ የተገለጠው በቅርቡ ስለሆነ እድሜህ ገና ነውና ለመታመን አይበቃም አይባልም። እግዚአብሔር ግን ፤
ኢሳ ፵፰፤፲፩ ስለ እኔ፥ ስለ ራሴ አደርገዋለሁ ስሜ ተነቅፎአልና ክብሬንም ለሌላ አልሰጥም» ይለናል። የእግዚአብሔርን ክብር ለሰዎች አንስጥ። ያከበርን መስሎን አንካድ። ቅዱሳኑ ያላሉትን አንበል። ይህ የተሃድሶና የጴንጤ ወሬ ነው የሚል እልከኝነት እውነቱ እንዳይወጣ ለጊዜው ያዘገየው እንደሆነ እንጂ ቀብሮ ሊያስቀረው በፍጹም አይችልም

የማቴዎስ ወንጌል ፲፤፳፮

"እንግዲህ አትፍሩአቸው፤ የማይገለጥ የተከደነ፥ የማይታወቅም

ከማስተዋል የተቀማ ልባችሁን እግዚአብሔርን በማምለክ ማስተዋል ይለውጥላችሁ! ከሚባል ሌላ ለእልከኞች ምን ይባል ይሆን?