Wednesday, November 30, 2011

ሰዶምና ገሞራ ወደኢትዮጵያ?


ማናቸውም ሰው ከሴት ጋር እንደሚተኛ ከወንድ ጋር ቢተኛ ሁለቱ ጸያፍ ነገር አድርገዋል ፈጽመው ይገደሉ ደማቸው በላያቸው ነው» ዘሌ 20፣13
በኢትዮጵያ የአራቱም ሃይማኖቶች መሪዎች በአዲስ አበባ በቅርቡ በሚካሄደው 16ኛው የአይካሳ ጉባዔን አስታክኮ በአገሪቱ ጸያፍ፣ ከሥነ ምግባር ውጭና ባህልን የሚያንቋሽሽ አጀንዳ ለማስፈጸም ተነሣሥቷል ያሉትን የአንድ ቡድን እንቅስቃሴን በመቃወም ትናንት ሊሰጡት የነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ላልተወሰነ ጊዜ ተላለፈ፡፡
የሪፖርተር ፎቶግራፍ ጋዜጠኛ መሪዎቹ መግለጫ ለመስጠት እንደተዘጋጁ ያነሳውም ፎቶግራፎች እንዲጠፉ ተደረገ፡፡

መሪዎቹን በመወከል መግለጫው ለሌላ ጊዜ መተላለፉን ያስታወቁት ከኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ቄስ ኢተፋ ጎበና ሲሆኑ፣ የጋዜጠኛው ፎቶ ግራፎች እንዲጠፉ ያደረገውም በሥፍራው የነበረ አንድ የደኅንነት አባል ነው፡፡

መግለጫው የሚሰጥበት ትክክለኛው ቀን መቼ ነው ተብሎ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ‹‹ከጉባዔው በፊትም ሆነ በኋላ ሊሆን ይቻላል፡፡ ከዚህ ውጭ ትክክለኛው ቀን ይህ ነው ብዬ ለመናገር ያስቸግረኛል፤›› ሲሉ ቄስ ኢተፋ መልሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ መሪዎች በተወካያቸው አማካይነት መግለጫው ላልተወሰነ ጊዜ መተላለፉን ያስታወቁት፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶክተር ቴዎድሮስ አጽሃኖም በተገኙበት የዝግ ስብሰባ አድርገው በጉዳዩ ላይ ለአንድ ሰዓት ያህል ከተወያዩ በኋላ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የአራቱም ሃይማኖቶች መሪዎች ኅዳር 19 ቀን 2004 ዓ.ም. በ4 ሰዓት ሊሰጡ ያቀዱትን መግለጫ ለመዘገብ ይጠባበቁ ለነበሩ ጋዜጠኞች ‹‹ብርቱ ማሳሰቢያ›› በሚል ርእስ ከታደለው ጽሑፍ ለመረዳት እንደተቻለው፣ ራሱን ዘ አፍሪካን ሜን ፎር ሴክሿል ሄልዝ ኤንድ ራይትስ (አምሸር) ‹‹The African Men for Sexual Health and Rights (AMSHeR)›› ብሎ የሚጠራ የዚህ ቡድን/ድርጅት ዓላማ በአፍሪካ የሚገኙ ግብረሰዶማዊ ወንዶች የተሻለ ሕይወትና ተቀባይነት የሚያገኙበትን መንገድ ማመቻቸት ነው፡፡

ድርጅቱ በ13 አፍሪካ አገሮች መቀመጫቸውን ያደረጉ የ15 ግብረሰዶማዊነት እንደ በጎ ምግባር የሚያንጸባርቁ ድርጅቶች ያዋቀሩት የጋራ ድርጅት መሆኑን ጽሑፉ አስረድቷል፡፡

አምሸር ከአይካስ ጉባዔ ጋር አስታኮ ‹‹ቅድመ ኮንፈረንስ›› በሚል ርእስ ቅዳሜ ኅዳር 23 ቀን 2004 ዓ.ም. በጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል ከ25 አገሮች ለተውጣጡ 200 ታዳሚዎች ኤምኤስኤም ኤንድ ኤችአይቪ (Men who have sex with men and HIV) በሚል  አጀንዳ ላይ ውይይት ለማካሄድ አቅዷል፡፡

የውይይቱ መሪ ቃል ‹‹የራስ ማድረግ፣ ማሳደግና ቀጣይነት›› የሚል መሆኑን ጽሑፉ ጠቁሞ፣ አምሸር በዕለቱ አይካስ ከሚያነሳቸው የውይይት ነጥቦች ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው፣ ነገር ግን ግብረሰዶማዊነትና ግብረሰዶማዊ የመሆን መብትን በአዎንታዊ መልኩ የሚያንጸባርቁ የውይይትና የልምድ ልውውጥ መድረኮችን ለማካሔድ ማቀዱን አስረድቷል፡፡

በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ ግብረሰዶማዊነት ወንጀል እንደሆነ በግልጽ ተቀምጦ ሳለና ከ97 በመቶ በላይ ኢትዮጵያውያን ድርጊቱን እንደ አጸያፊና ኢሞራላዊ አድርገው የሚቆጥሩት መሆኑ እየታወቀ፣ ይህንን ስብሰባ ለማድረግ አምሸር ማቀዱ በኢትዮጵያ ሕግና ለኢትዮጵያውያን ሞራል ቦታ ያልሰጠ መሆኑን ያሳያል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የዚህ ኢሞራላዊ ስብሰባ በቅድመ ጉባዔ ስም ከ16ኛው አይካሳ ጉባዔ በፊት መደረግ በጉባዔው ላይ አሉታዊ አንድምታ እንዲያጎለበት ያደርጋል ተብሎ ታምኖበታል፡፡

አምሸር በጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል የሚያካሒደው የቅድመ አይካሳ ስብሰባ የማነቃቂያ ጉባዔ ዋና ዓላማዎች፣ በአፍሪካ የወንድ ለወንድ ግብረሰዶማዊ ግንኙነቶችን እውን የማስደረግ ጉዳይ ለኤችአይቪ/ኤድስ ስርጭት አስተዋጽኦ ስለሚያደርግ ትኩረት እንዲገኝ ማስቻል፣ ግብረሰዶማዊነት ሕጋዊ እንዲሆን ከማስቻል አኳያ አፍሪካዊ ምላሽና ነጸብራቅ ማሳየት፣ ኤችአይቪን ከመከላከልና ከመቆጣጠር አንጻር ግብረ ሶዶማዊነትን ሕጋዊ ማድረግ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ በመለየት ለተግባራዊነቱ አቅጣጫን መቀየስ ነው፡፡

ይህንን ስብሰባ የተሳካ ለማድረግ የዕለቱ ተጋባዥ ተናጋሪዎችም ሚሼል ሲዲቤ የተባበሩት መንግሥታት የኤችአይቪ ዋና ዳይሬክተር፣ ዶክተር ደብረ ወርቅ ዘውዴ የግሎባል ፈንድ ፀረ የኤችአይቪ፣ ቲቢ፣ የአባለዘር በሽታዎችና ወባ ፕሮግራም ምክትል ዳይሬክተር፣ አምባሳደር ኤሪክ ጎስቢ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የኤችአይቪ አስተባባሪ፣ የተከበሩ ሬኔ አላፒኒ ጋንሱ የቀድሞ የአፍሪካ ሰብዓዊ መብቶች ሊቀመንበርና የወቅቱ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኙ ወገኖችና ይበልጥ ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሰብዓዊ መብት አስከባሪ ኮሚቴ ሊቀመንበርና የአይካሳ ተወካይ ናቸው፡፡

ስብሰባው በ15 አገሮች ላይ በጤናና በግብረሰዶማዊያን መብቶች ዙርያ የተዘጋጁ ተሞክሮዎች ይቀርብበታል፡፡ በዕለቱ ከተለያዩ 25 አገሮች የተውጣጡ 200 ተሳታፊዎች እንደሚታደሙበት የተገመተ ሲሆን፣ ይህ ስብሰባ ለግብረሰዶማውያኑ  አዲስ ትስስር ለመፍጠርና ለመቀናጀት፣ ልምድን ለማዳበር ምርጥ ተሞክሮዎችን ለማስፋፋትና ለሚቀጥለው ትውልድ ይህንኑ ዘይቤ ለማስተላለፍ ለየት ያለ ዕድል የሚፈጥር መሆኑ ይታመንበታል፡፡

አቶ ሚኪያስ ሲሳይ የአይካሳ የኮሙዩኒኬሽንና ፕሮሞሽን ሥራ አስኪያጅ ስለዚሁ ጉዳይ በስልክ ተጠይቀው፣ ጽሑፉ እንዳልደረሳቸውና ምንም እንደማያውቁ ገልጸዋል፡፡ በ16ኛው የአይካሳ ጉባዔ ላይም እንዲህ ዓይነት ቡድን ወይም ድርጅት ስለመሳተፉ የሚያውቁት ነገር እንደሌለም ተናግረዋል፡፡

ስብሰባው የሚካሔድበት ጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል ሥራ አስኪያጅ ወ/ት ሮማን ታፈሰወርቅ፣ ‹‹ቅዳሜ የሚካሔድ ስብሰባ የለም፤ ውሸት ነው፤ የወሬው ምንጭ ከየት እንደመጣ አናውቅም፣ በእኛ ስም መጥፎ ወሬ እየተወራብን ነው፤›› ብለዋል፡፡

ሥራ አስኪያጇ ‹‹ዝም ብሎ ወሬ ነው›› ብለው ቢያስተባብሉም፣ አምሸር በድረ ገጹ ‹‹ቅድመ አይካሳ ኮንፈረንስ›› የሚካሔደው ስብሰባ ‹‹የራስ ማድረግ፣ ማሳደግና ቀጣይነት›› (Claim, Scale-Up and Sustain) በሚል መሪ ቃል ኅዳር 23 ቀን 2004 ዓ.ም. ከጧቱ 2 ሰዓት ተኩል እስከ 11 ሰዓት ተኩል ድረስ በጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል ይካሔዳል ብሏል፡፡

በተያያዘ ዜና መንበሩን በኬንያ ያደረገው ግብረሰዶማዊው ተቋም ኢሽታር ኤምኤስ ኤም፣ ለኢንጄንደር ሔልዝ ስታፍ እና ሬንቦ ኢትዮጵያ ከመስከረም 14 ቀን እስከ መስከረም 20 ቀን 2004 ዓ.ም. ድረስ ስለግብረሰዶም የምክክርና ጥናት መድረክ ማከናወኑ፣ በተለይም በመደገፍና በማስተባበር ሚናውን መወጣቱን የአምሸር ድረ ገጽ ዘግቧል፡፡ መሠረቱን በኢትዮጵያ ያደረገው ሬንቦ ኢትዮጵያ፣ በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ የግብረሰዶም አራማጅ ወጣቶች፣ ወንድ አዳሪዎችና ሌሎችም መካከል ኤችአይቪ ኤድስና የአባላዘር በሽታን ለመቀነስ የሚንቀሳቀስ ተቋም ነው፡፡

ግብረሰዶማዊው የኬንያው ተቋም ኢሽታር ካነገበው ዓለማዎች መካከል በግብረሰዶም ዙርያ የአቻ ለአቻ ትምህርት የኬንያን አምሳያ በኢትዮጵያ ማዳረስ እንደሆነ ኅዳር 5 ቀን 2004 ዓ.ም. ‹‹Ishtar MSM Hosts Engender health and Rainbow Ethiopia›› በሚል ርእስ የተሰራጨው ዘገባ አመልክቷል፡፡

በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ (1996) ክፍል ሁለት ‹‹ለተፈጥሮ ባሕርይ ተቃራኒ የሆነ የግብረ ሥጋ ግንኙነቶች›› በሚል ርእስ በአንቀጽ 629፣ ግብረሰዶም እና ለንጽህና ክብር ተቃራኒ የሆኑ ሌሎች ድርጊቶች በሚል ርእስ፣ ‹‹ማንም ሰው ከእርሱ ጋር አንድ ዓይነት ጾታ ካለው ከሌላ ሰው ጋር ግብረሰዶም ወይም ለንጽህና ክብር ወይም ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆነውን ሌላ ድርጊት የፈጸመ ማንኛውም ሰው ከቀላል እስራት እስከ ከባድ ወንጀል ቅጣት እንደሚጠብቀው ይደነግጋል፡፡

በአንቀጽ 631 ደግሞ ‹‹ለአካለ መጠን ባልደረሱ ልጆች ላይ የሚፈጸሙ የግብረሰዶም ጥቃትና ለክብረ ንጽህና ተቃራኒ የሆነ ሌላ ድርጊት›› በሚል ርእስ፣ ንኡስ አንቀጽ 1. ማንም ሰው ከእርሱ ጋር አንድ ዓይነት ጾታ ባለውና ለአካለ መጠን ባልደረሰ ልጅ ላይ የግብረሰዶም ጥቃት የፈጸመ እንደሆነ፤ የተበዳዩ ዕድሜ አሥራ ሦስት ዓመት ሆኖ አሥራ ስምንት ዓመት ያልሞላው ሲሆን፣ ከሦስት ዓመት እስከ አሥራ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እሥራት ይቀጣል፡፡ የተበዳዩ ዕድሜ ከአሥራ ሦስት ዓመት በታች ሲሆን፣ ከአሥራ አምስት ዓመት እስከ ሃያ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡ በተጨማሪም አንዲት ሴት ለአካለ መጠን ባልደረሰች ልጅ ላይ የግብረሰዶም ጥቃት የፈጸመች እንደሆነ፣ ከአሥር ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ትቀጣለች በማለት ደንግጓል፡፡ 
source- Ethiopian reporter