Sunday, November 6, 2011

እኔ በእግዚአብሔር የምታወቅበት ማንነት!


በዚህ ምድር ሳለን እውቀታችን ያች ትንሿ ጭንቅላታችን በሚመጥናት መልኩ የያዘችውን ያህል ብቻ ታውቃለች። ከዚያ በላይ ልሁን ብትልም መስፋት ከምትችለው በላይ አትወጣም። ዓለም ባላት እውቀት የምታውቀው ማወቅ የቻለችውን ያህል ብቻ ነው። የሰው አእምሮ ከምታውቀው በላይ ለመሆን ብትሞክር የእውቀት መቋጠሪያዋ ይበጠስና የያዘችው ማፍሰስ ሲጀምር ሰው ለመባል ያበቃትን ማንነት ትስትና አጠቃላይ እኛነታችንን ወደ ሌላ ምዕራፍ ታሸጋግራለች። ወደ እብደት ወይም ወደ እንስሳት ጠባይዓት ማለት ነው።
አንደኛው የዓለም ጦርነትም ይሁን ሁለተኛው የዓለም ጦርነት መነሻቸው ሰው ካለው እውቀት በላይ ለማምጣት በተመኘ እውቀት የተከሰተ ነው። ምናልባትም ሶስተኛው የዓለም ጦርነት ሊመጣ የሚችለውና የከፋ የሚያደርገውም የሰው እውቀት ከማወቅ ጣሪያ በላይ ለመውጣት በሚያደርገው ጥረት ወዳለማወቅ ተሻግሮ የሚጎትተው እብደትና የእንስሳነት ጠባይ መገለጫ ሊሆን ይችላል።
ይህንንም ጥንታውያን አበው«እጅግም ስለት፤ ይቀዳል አፎት»ይላሉ። መጽሐፍ ቅዱስም የእግዚአብሔር ቁጣ እንዲርቅና የተመዘዘው ሰይፍ እንዲመለስ ሲያመለክት እንዲህ ሲል ይነግረናል። «አንተ የእግዚአብሔር ሰይፍ ሆይ፥ ዝም የማትለው እስከ መቼ ነው? ወደ ሰገባህ ግባ ጸጥ ብለህም ዕረፍ » ኤር 47፤6
በምድራችን ላይ የሚታየው የጦርነት፤ የእልቂት፤የእርስ በእርስ መበላላት፤ የበሽታና የረሃብ ክስተቶች ሁሉ የሰው እውቀት ያመጣው ጣጣ እንጂ የፈጣሪ ፈቃድ አይደለም። ምክንያቱም የያዝነው የዘመኑ እውቀት ስለቱ ለመኖርያ የተሰጠውን አፎት ዓለምን እየቀደደ በመገኘቱ ሰው ሰውኛነቱን ወደመካድ እብደትና እንስሳነት እውቀት እየተሸጋገረ በመገኘቱ የተነሳ ነው። እንዲሁም ይህ ሰይፍ ወደሰገባው (አፎቱ) የማይመለሰው የሰው ልጅ ያለው እውቀት እግዚአብሔር እሱን (የሰው ልጅን) እንዴት እንደሚያውቀው ለማወቅ ከመፈለግ ውጪ ስለሆነ ነው። በአጭር አገላለጽ ሰው ስለእግዚአብሔር ያለው እውቀት እሱ ማወቅ የሚችለውንና ለማወቅ የሚፈልገውን ያህል ሲሆን በአንጻሩ እግዚአብሔር ሰውን እንዴት እያወቀው እንደሆነ ለማወቅ አልቻለም ማለት ነው።


ጥሩ አብነት የሚሆነን የመጀመሪያው ሰው አዳም ከጥፋት በሆነች እውቀት በበደለ ጊዜ በበለስ ቅጠል ተሸፍኖ መሸሸጉ የሚነግረን ነገር ቢኖር ያገኘው እውቀት እግዚአብሔርን እንዴት እያወቀው እንዳለ ሲሆን በአንጻሩ እውቀቱ አለማወቅ የሚሆነው እግዚአብሔር አዳምን እንዴት እንደሚያውቀው ለማወቅ አለመቻሉ ነበር። ያገኘው እውቀት እንዴት አድርጎ ተደብቆ መኖር እንደሚችል እንጂ እግዚአብሔር በየትኛው ማንነት እያወቀው እንዳለ የሚያውቅ ስላልነበረ የእውቀቱ ሰይፍ የእንስሳን ቆዳ ከመልበስ አላዳነውም።
ዛሬም እንደዚሁ የሰው ልጅ እግዚአብሔርን የሚያውቀው እግዚአብሔር እኔን እንዴት ያውቀኛል ብሎ ሳይሆን እኔ እግዚአብሔርን እንዴት አውቀዋለሁ በሚል እውቀት ተመስርቶ ነው። ያ ማለት የሰው ልጅ እውቀት የመጀመሪያውን ሰው አዳምን መስሏል ማለት ነው።
በሌላ ቦታም ስምዖን ጴጥሮስ ኢየሱስን እንዴት እንደሚያውቀው በነበረው እውቀት በልበ ሙሉነት ሲናገር አይተናል። «ጴጥሮስም፦ ጌታ ሆይ፥ አሁን ልከተልህ አለመቻሌ ስለ ምንድር ነው? ነፍሴን ስንኳ ስለ አንተ እሰጣለሁ አለው»ዮሐ 13፤37
ይህ እንግዲህ ጴጥሮስ ስለኢየሱስ ያለው እውቀት እንጂ ኢየሱስ ጴጥሮስን እንዴት እንደሚያውቀው ማወቅን የተሞላ እውቀት ስላልነበረ ይህንን የእውቀቱን ጉድለት ባላሳየም ነበር። «ጴጥሮስም እንደ ገና ካደ፥ ወዲያውም ዶሮ ጮኸ»ዮሐ 18፤27
ጴጥሮስ ያለው መረዳት ኢየሱስን እንዴት ባለ ማወቅ እያወቀው እንደነበረ ሲሆን በተቃራኒው እውቀቱ እሱ እንዳወቀው ሳይሆን ኢየሱስ እንዴት እያወቀው እንደሆነ ሲያውቅ እንደዚህ ሲል እናገኘዋለን። «ምሳ ከበሉ በኋላም ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን። የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን? አለው። አዎን ጌታ ሆይ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። ግልገሎቼን አሰማራ አለው» ዮሐ 21፤15

ዛሬም የዚህ ዓለም እውቀት እምነት ያለውም ይሁን የሌለው ያለው ማወቅ እንዴት እያወቀ እንዳለ እንጂ እሱ በሌላው ዘንድ እንዴት እየታወቀ እንዳለ በማያውቅ እውቀት ውስጥ መኖሩ ነው።
ይህም እውቀት ወደእብደትና እንስሳዊ ባህርይ እንዲያመራ አድርጎታል። እምነት አለኝ የሚለው ያለው መረዳት እሱ እንዴት እያወቀ እንዳለ ብቻ ነው። እምነት የሌለውም ቢሆን እውቀቱ እንዴት በለስ ዓለምን እንደሚለብስና ከሌሎች አዋቂዎች መብለጥ እንዳለበት በሚችል እውቀት ውስጥ መሸሸግ ብቻ ነው። ያም መጠላለፍን፤ መገዳደልን፤ መጠላላትን፤ መነቃቀፍን፤ መከዳዳትንና ሽብርን ወለደ። የእውቀት ሰይፋችን የመኖር አፎታችንን ቀደደው።
በግራም በቀኝም ስለሃይማኖት የሚነገር እውቀት አለ፤ እውቀቱ ግን የሚያምንበት አምላክ እሱን እንዴት እያየው እንደሚገኝ የሚያውቅን ለማወቅ በግራም በቀኝም ማግኘቱ ከባድ ነው። ምክንያቱም አብዛኛው በራሱ በለስ ጫካ ውስጥ ለመሸሸግ የሚጣራ እውቀት ስለተሸከመ ይሆናል ወይም እሱ በእግዚአብሔር እንዴት እየታወቀ እንደሆነ የማያውቅ ስለሆነ ነው። ይህን የጽድቅ ፍሬ አልቦነትን እውቀት መያዙን በጎነት፤ ደግነት፤ ፍቅርና ኅብረት ስለማይመሰክሩለት በዚህ ይረጋገጣል። «ለእግዚአብሔርም ክብርና ምስጋና ከኢየሱስ ክርስቶስ የሚገኝ የጽድቅ ፍሬ ሞልቶባችሁ፥ ለክርስቶስ ቀን ተዘጋጅታችሁ ቅኖችና አለ ነውር እንድትሆኑ የሚሻለውን ነገር ፈትናችሁ ትወዱ ዘንድ፥ ፍቅራችሁ በእውቀትና በማስተዋል ሁሉ ከፊት ይልቅ እያደገ እንዲበዛ ይህን እጸልያለሁ» ፊልጵ 1፤9-11
እንግዲህ ክርስቶስን እንዴት እንደሚያውቅ ሳይሆን ክርስቶስ እንዴት እያወቀው እንዳለ የሚያውቅ እምነት ከክርስቶስ የሚገኝ የጽድቅ ፍሬ ይሞላበታል፤ በዚህም ቅንነትና ነውር አልቦ ሆኖ ፍቅር፤ እውቀትና ማስተዋልን እያሳደገ ሌላውን ያሳድጋል እንጂ የፈሪሳውያንና የሰዱቃውያንን ዓይነት የጥልና የክርክር ሸንጎ እውቀትን ለመለያየት አይሰብክም። የሐዋ 23፤7

እያንዳንዳችን እግዚአብሔር እንዴት ባለ ማንነት እንደሚያውቀን ብናውቅ ደግሞ የጽድቅ ፍሬ የሚታይበት ሰው ለመሆን አይቸግረንም ነበር። እግዚአብሔርን ማወቃችን በለስ እውቀት ስር ከመሸሸግ ውጭ ያወጣናል ብንል ሞኝነት ነው። አዳም እግዚአብሔርን ስላላወቀ አልነበረም በለስ እውቀት ስር የገባው ይልቁንም እግዚአብሔር እሱን እንዴት ባለ ማንነት እንደሚያውቀው አለማወቁ ነበር ችግሩ። እንደዚሁ ሁሉ ዛሬም እያንዳንዳችን እግዚአብሔርን እንዴት እንደምናውቀው ሳይሆን እሱ እንዴት ባለማንነት እንደሚያውቀን ማወቅ የግድ ይሆናል።
ምናልባትም በእግዚአብሔር ላይ ባለን እውቀት የተሻልንና የተመሰከረልን ሊሆን ይችላል። እውቀታችን እምነቱ የሚጠይቀውን እውቀት በጥልቅ ተረድተነውም ይሆናል። እውቀት ጥሩ ነው። ያ ማለት ግን እግዚአብሔርን የማወቅ እውቀት ይዘናል ማለት አይደለም።
ለምናውቀው እግዚአብሔር እንዴት እየኖርን ነው? የምንታወቀው እንዴት ነው? ዝሙትና ርኩሰት፤ መዳራትና ማመንዘር፤ መክዳትና መጠራጠር፤ ስካርና ሴሰኝነት፤ ጥላቻና ምቀኝነት፤ ምኞትና ክፋት፤ ቂምና በቀል፤ ስርቆትና ግድያ፤ ሃሜትና ነቀፋ፤ ሃሰትና ዓለምን መውደድ፤ ትምክህትና ትእቢት የመሳሰለው ሁሉ አንድም በእኛ የእለት ከእለት ሕይወት ውስጥ ከሌሉ በእውነትም እግዚአብሔርን እንዴት እንደምናውቀው ብቻ ሳይሆን እንዴት እንደሚያውቀንም የምናውቀው ሰዎች ሆነናል ማለት ነው።
መዝሙር24፤----
3 ወደ እግዚአብሔር ተራራ ማን ይወጣል? በቅድስናውስ ስፍራ ማን ይቆማል?
4 እጆቹ የነጹ፥ ልቡም ንጹሕ የሆነ፥ ነፍሱን ለከንቱ ያላነሣ፥ ለባልንጀራውም በሽንገላ ያልማለ።
5 እርሱ ከእግዚአብሔር ዘንድ በረከትን ከመድኃኒቱ አምላክም ምሕረትን ይቀበላል።
አዳም ከእግዚአብሔር ተራራ የወረደው ንጹህ እጅ ስላልነበረው ነው። እንደዚሁ ሁሉ አማኞች ንጹህ እጅ ከሌላቸው ወደተራራው አይወጡም። ልቡ ከላይ ከተዘረዘሩት ኃጢአቶች ሁሉ ንጹህ ከሆነ በቅድስናው ሥፍራ መቆም ይቻለዋል። በረከትንና ምሕረትን ያገኛል። ዓለም ዛሬ የቸገራት ይህንን አጥታ ነው። እግዚአብሔርን አውቃለሁ ትላለች፤ ለእግዚአብሔር እንደሚገባ የመኖር እውቀት ስለሌላት የእግዚአብሔርም የበረከት እጅ ርቋት ይገኛል።

ትንቢተ ኢሳይያስ
1፥19
እሺ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ፥ የምድርን በረከት ትበላላችሁ

እግዚአብሔር እንደሚፈልገው ከሆንን በረከትን፤ የማንፈልግና እንደእራሳችን እውቀት የምንኖር ከሆነ ግን
መዝ109፥17
መርገምን ወደደ ወደ እርሱም መጣች በረከትንም አልመረጠም ከእርሱም ራቀች።

ያለው ቃል ተፈጻሚ ይሆንብናል።
ዓለም በቦንብ ምርትና በኒውክለር እሽቅድምድም መጠመዷ የሰው ልጅ መርገምን የመምረጡ ማሳያ ነው። እግዚአብሔር እንደሚወደው ለመኖር ባለፈለገ እውቀት፤ ያለችው ዓለም በፍርሃትና ከዚህ ፍርሃት በመላቀቅ ራስን ማዳን በሚል እሳቤ መሳሪያ ሲሸምትና ሲያመርት የሚታይ ሲሆን በተቃራኒው በበሽታ፤ በሽብር፤ በድርቅና በጦርነት በማለቅ የበረከት መጥፋት ችግሮች ተወጥሮ መታየቱም የዘወትር ክስተት ሆኗል።
የሎጥ ባሕር ሰዶም ከመቃብር ወጥታ በሰው ልብ ውስጥ ሰፍታ በሕግ ጋብቻዋን አንግሳለች።
በእምነት ውስጥ አለሁ የምትለዋም ዓለም እንደራሷ እውቀት እንጂ እግዚአብሔር እንድትሆን በሚፈልገው ዓይነትና በሚያያት መልኩ ማየት የሚችል እውቀት ስለሌላት ከበረከትና ከሰላም ርቃ መታየቷ አረጋጋጭ ሁነት ነው።
ኦሪት ዘሌዋውያን
26፥6
በምድራችሁም ላይ ሰላምን እሰጣለሁ፥ ማንም ሳያስፈራችሁ ትተኛላችሁ ክፉዎችንም አራዊት ከምድራችሁ አጠፋለሁ፥ ሰይፍም በምድራችሁ ላይ አያልፍም።
ይለናል። እኛ ግን ይህ ርቆናል። ሰላም ጠፍቶ፤ ሳንፈራ መተኛት አቅቶናል። ክፉዎች አራዊት በምድራችን ሰለሞሉ ሰይፍ አልፎብናል። ምክንያቱም እግዚአብሔር እንድንሆንለት ከሚፈልገው ርቀናልና ነው።
እያንዳንዳችን ራሳችንን ለዚህ እውቀት ብናዘጋጅ ሰላማችን በደጃችን ይሆናል። በአካባቢያችን ያለው አስፈሪ የሁከት፤ የብጥብጥና የጸብ አውሬ ጠፍቶ በሰላም እንተኛለን። ይህንን የተናገረው እግዚአብሔር ነው።

ኢዮብ 22፤21አሁንም ከእርሱ ጋር ተስማማ፥ ሰላምም ይኑርህ በዚያም በጎነት ታገኛለህ» እንዳለው
ዘወትር «እግዚአብሔር እንዴት ያውቀኛል?» ብለህ ራስህን ተመልከት!!! እንደምታውቀው ብቻ ሳይሆን እንዲያውቅህ በሚፈለገው መልካም ማንነት ኑር!! ማወቅህ የበለስ ቅጠል ከሚያለብስ እውቀት የወጣና፤ የት ነው ያለኸው? ከሚል አስፈሪ ጥያቄ ለመዳን ተሸሽጌ የሚል የድካም መልስ እንዳትሰጥ በለስ ዛፍ ላይ ራሱን ሰቅሎ የሞትከውን ሞት በሞተው ልጁ በኩል ወደወጣህበት የብርሃን ተራራ እውቀት አሁን ውጣ!!! ያኔ በእግዚአብሔር የምትታወቅበትን ማንነት ታውቃለሁ!