Wednesday, August 26, 2015

በአመልካች ጣትህ ሌላው ላይ ስትጠቁም፤ ሦስቱ ጣቶችህ ይመሰክሩብሃል!





  አንዳንድ ሰዎች የራሳቸውን ግፍ፤ ዐመጻና ኃጢአት ለመሸፈን የአቻቸውን በደልና ዐመጻ በማቅረብ ለመደበቅ ይሞክራሉ። ነገር ግን የሌላው ሰው ዐመጻና በደል መቁጠር የራስን የኃጢአት ደብዳቤ አይፍቀውም። በየትኛውም ማእዘን የሚገኙ ዐመጸኞች ከዐመጻቸው እስካልተመለሱ ድረስ ዐመጻቸው ሰላማዊውን ሊያጠፋ ይችላል።  ከኋላ ይሁኑ ከፊት ዐመጸኞች የቆሙበት ሥፍራ ብቻውን ንጹሐን አያደርጋቸውም። ይልቁንም ሰላማዊው ላይ በሽታቸው እንዳይጋባ ቢቻል ሸክማቸውን በንስሐ እንዲያራግፉ ሊነገራቸው፤ ሸክሙ ተስማምቶናል ካሉም ራሳቸው ተሸክመው ገለል እንዲሉ ሊደረግ ይገባል።  ተፈጥሮ የሰጣትን ሁለት መልክ በመጠቀም ለማሳሳት ሞክራለች ተብሎ በምሳሌ እንደሚነገርላት የሌሊት ወፍ ከአይጦች ዘንድ ሄዳ ጥርሷን በማሳየት «እኔ የእናንተ ወገን ነኝ» ካለች በኋላ ከወፎችም ማኅበር ተቀላቅላ ክንፏን እያራገበች «የተከበራችሁ ወገኖቼ እንደምን አላችሁ!» እንዳለችው እንስሳ በሁለት ገጽ ለማታለል የሚሞክሩ የዘመኑ ተለዋዋጮች ራሳቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ ሸክም ሆነው ሳሉ የችግሯ ደራሽ ለመምሰል መሞከራቸው በዚህ ዘመን እንደማይቻል በግልጽ ሊያውቁት ይገባል።

   ሰሞኑን የምንመለከተው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደአዞ ሐረግ በጎን በቅሎ በዋናው ግንድ ላይ የተጠመጠመው በቅዱሳን ስም የሚጠራው ማኅበር ተራራ የሚያክል የራሱን ኃጢአትና ዐመጻ ላይደበቅ ሸሽጎ የሙስና ተዋጊና የቤተ ክርስቲያኒቱ አዳኝ ለመሆን ሲታትር እያየን ሲሆን በሞት የሚፈላለጋቸውንም ፓትርያርክ በማወዳደስ ላይ መጠመዱ «ቁርበት አንጥፉልኝ» የተባለውን ብሂል እንድናስታውስ አድርጎናል።

  እኛም ነገሩ ቢገርመን «አመልካች ጣትህን ስትጠቁም፤ ሦስቱ ጣቶችህ በራስህ ላይ ይመሰክሩብሃል» ልንለው ወደድን። ሙሰኞቹም፤ ማኅበሩም የቤተ ክርስቲያኒቱ ጠንቅ ከመሆን ባለፈ አንዳቸው የአንዳቸው አጣሪ፤ ጠቋሚና አባራሪ ሊሆኑ በፍጹም አይችሉም። ከዚህ በፊት በማኅበሩም ላይ ሆነ በነፍሰ በላ ሙሰኞቹ ላይ ተከታታይ ጽሁፍ በማቅረብ ሁሉ አጥፊዎች  መሆናቸውን በግልጽ ተናግረናል። አሁንም የምንናገረው ያንኑ በመድገም ነው። የምናሰምርበትም እውነት «ከማኅበሩና ከሙሰኞቹ የትኛው በመወገድ ሊቀድም ይገባል? የሚለው ካልሆነ በስተቀር በሁለቱም አላስፈላጊነት ላይ አንዳችም ብዥታ የለንም»

   ስለሆነም በማኅበሩ ላይ ከዚህ በፊት በፓትርያርኩ የተያዙ አቋሞች በሙሰኞች ማጥራት ሽፋን የሚታለፍ ወይም የሚቀየር ከሆነ ከሁለት ጅቦች መካከል አንዱን ጅብ ምርጫ የመውሰድ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመታደግ የሚደረግ እንቅስቃሴ አይደለም እንላለን። በመካከላቸው የመጠንና የዓይነት ካልሆነ በስተቀር ቤተ ክርስቲያኒቱን በሚግጡ ጅቦች መካከል የተግባር ልዩነት ስለሌለ ሁሉም ቦታቸውን ሊይዙ የሚገባቸው የጥፋት ኃይሎች መሆናቸው አያጠያይቅም። እንደምንመለከተው ያለው መገፋፋት በሦስት የሚከፈል ይመስለናል።

  1ኛው- ጫንቃው የደነደነ ማኅበር ከቦታው ሊወገድ የተገባው ቢሆንም  የተወሰኑ አስተዳዳሪዎችና ከታች ያሉ ዘራፊዎች፤ ቅዱስ ነኝ የሚለውን ማኅበር የሚጠሉት ማኅበሩ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ስላደረሰው በደልና ግፍ በመቆርቆር ብቻ ሳይሆን በስለላ መረቡ ስለተጠለፉና እዳ በደላቸው ስለተጻፈባቸው፤ ከሚከተላቸው ፍርሃትና ድንጋጤ ለመገላገል ሲሉ በሐቅ ከሚታገሉት ጋር በኅብረት የሚጮኹ አንድ ቡድን ናቸው።

 2/ ማኅበሩ ቤተ ክርስቲያኒቱን መስሎና አኅሎ በላይዋ ላይ ነግሶ በስሟ መነገዱ የታያቸው፤ በመንገድ ላይ ቆሞ እንቅፋት የሆናቸው፤ ለስውር ዓላማው የስለላ ቡድኑን ያወቁ፤ የቤተክርስቲያኒቱን ልጆች ለራሱ መመልመሉ የቆጫቸው፤የገቢ አቅሙን እያደለበ፤ ሀብቷን ለራሱ ዓላማ ሲጠቀም የተመለከቱ፤ የኃጢአት በደል ጸሐፊ፤ ለሲኖዶስ ክፍፍል ረጅም እጅ ያለው መሆኑን የተረዱ በትክክል አምነው የሚታገሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች በሁለተኛ ረድፍ አሉ። ይህ ረድፍ ድምጹን የሚሰማና የሚያስተባብረው የበላይ አመራር ቢኖር ኖሮ ውጤታማ ሥራ ለመስራት የሚችልና በሙሰኛ አስተዳዳሪዎችም ይሁን በማኅበሩ ተግባር የመረረው ቡድን ነው ።

  3/ ራሱን ቅዱስ፤ ጻድቅና የቤተ ክርስቲያኒቱ መድኅን አድርጎ የተነሳ፤ በገንዘቡ፤ በኃይሉ፤ በአስተዳደሩ፤ በሴራ መዋቅሩና በእንቅስቃሴው አደገኛ የሆነ፤ የራሱን የሲኖዶስ አባላት ያደረጃ፤ ስለቤተክርስቲያኒቱ ሳይሆን ከጥቅሙ ጋር ለቆመ ሰይጣንም ቢሆን የሚተባበር፤ ሰዎችን በማጥመድ አገልጋይ ለማድረግ የሚተጋ፤ የሰዎች የእዳ በደል መዝጋቢ፤ ሰላይ፤ በዝሙት የረከሰ፤ ነጋዴ፤ አስመሳይና አታላይ ነገር ግን በሩቅ ሲያዩት ቆዳው ከእባብ የለሰለሰ ማኅበር፤ ማኅበረ ቅዱሳን የሚባለው በሦስተኛ ረድፍ አለ።
በዚህ መካከል ከወዲህም ከወዲያም የሚዘምቱ፤ ነገር የሚያማቱ፤ የሚያወሻክቱ፤ የአስመሳዮች ቡድን እንደወቅቱ ሁኔታ፤ ኃይል ወዳጋደለበት የሚያጋድሉ የአስተሳሰብ ድሆች ከሲኖዶስ ጀምሮ በየደረጃው ቢኖሩም ተጽእኖ ፈጣሪ ሆነው ለእክል የሚበቃ አቅም የላቸውም።

 በሦስቱ ረድፎች ያለውን የኃይል አሰላለፍ ተመልክቶ ተገቢ ከሆነው ወገናዊ ኃይል ጋር በመቆም እንቅስቃሴ መውሰድ የተገባ ቢሆንም እስካሁን ከወሬ ባለፈ የሚታይ እርምጃ ብዙም ሲወሰድ አይታይም።
ወቅቱ በፈጠረው የቤተክርስቲያኒቱ ተግዳሮትና የችግር እሳት መካከል የተገኙትት ፓትርያርክ ማትያስ ምን ዓይነት እርምጃ፤ መቼና ከማን ጋር ሆነው መውሰድ ይችላሉ? የሚለው ጥያቄ ምላሽ የሚያሻው ወቅታዊ ጉዳይ ይመስለናል። አካሄዱን በሳተ፤ ውጤቱም ምን ሊሆን እንደሚችል ባልተጠና ውሳኔ የሚወሰድ እርምጃ ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል። ስለሆነም በገበያ ግርግር መካከል የሚዘለው ማኅበር የራሱን የቤት ሥራ ሳይጨርስ «ከፓትርያርኩ ጋር አለሁ፤ አለሁ» የሚለው ጉዳይ አሳሳቢ ነው።
ስለማኅበሩም ይሁን ማኅበሩን በሚደግፉ ነገር ግን ብዙ ችግር ባለባቸው ሰዎች ዙሪያ ትንፍሽ የማይለው «ሐራ» የተባለው ብሎግ የማኅበሩ ቀኝ እጅ ስለሆኑት አባ ማቴዎስ ለሙስና ውጊያ የመዘጋጀታቸውን ዜና መስራቱ እንዲሁም የፓትርያርኩን ፈቃደኝነት አደበላልቆ ማቅረቡ ችግሩን ለመቅረፍ ሳይሆን የማኅበሩን ጉዳይ ለመሸፈን አጋጣሚ ማግኘቱን የሚያመለክት ነው።
 ስለሆነም ለፓትርያርኩ የመፍትሄ ሃሳብ ሊሆኑ የሚችሉ ነጥቦችን ለመጠቆም እንወዳለን።

  1/ በቅድሚያ ፓትርያርኩ ብቻቸውን ተንቀሳቅሰው፤ ብቻቸውን ጮኸው፤ ብቻቸውን ታግለው የሚያመጡት ውጤት እንደሌለ በመረዳት የተሻለ ግንዛቤ፤ እውቀትና የአስተዳደር ክህሎት ያላቸውን የቤተ ክርስቲያኒቱ ችግር ግድ የሚላቸውን ሰዎች በሥራ አጋርነት በዙሪያቸው ማሰባሰብ ያስፈልጋቸዋል። ከጳጳሳቱም ብዙዎቹ በማኅበሩ የተጠለፉ ወይም ከሙስናና ከዘረኝነት ጋር የተሳሰሩ ስለሆነ ከጳጳሳቱም ሆነ ከበታች ሹማምንት መካከል ጥንቃቄ የታከለበት ምርጫ መደረግ አለበት። የፓትርያርኩ ልዩ ፀሐፊ፤ የፕሮቶኮል ሹም፤ የውጪ ግንኙነት ክፍል፤ የፓትርያርኩ ቢሮ ኃላፊ እና ሌሎች ተጨማሪ ክፍሎችን ማደራጀት ያስፈልጋል። የፓርትያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት በሆነው አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ውስጥ ሥራ አስኪያጅ፤ የሀገረ ስብከቱ ፀሐፊ፤ የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ወዘተ ክፍሎች ፓትርያርኩ ለሚያደርጓቸው ቀጣይ እርምጃዎች ወሳኝ ስለሆኑ ይህንን በተጠናና መልኩ እንደገና ማዋቀር የግድ ይላል። የፓትርያርኩ ጽ/ቤት የየዕለት የሥራ ውሎ ከበታች ክፍሎች ሪፖርት በመቀበልና ለፓትርያርኩ በማቅረብ ተከታታይ የሥራ መመሪያና ትእዛዝ በማስተላለፍ ያልተቋረጠ ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል።

2/ እንደአጭር ጊዜ የማስተካከያ እርምጃ  ከላይ በተራ ቁጥር 1 በተመለከተው ነጥብ ውስጥ ያሉ አካሎችና ሌሎች አጋዦች ያሉበት አጣሪ ኮሚሽን በማዋቀር በሚያደርጉት ምርመራ በሙስና የከበሩ፤ ከሌላቸው ደመወዝና ልዩ ገቢ ውጪ ሃብት ያከማቹ፤ አላግባብ የበለለጸጉ፤ የገንዘብ ብክነትን ያስከተሉ አሰራሮች ሁሉ ዝርዝር መረጃቸውና ከነመፍትሄ ሃሳቦቻቸው በማቅረብ ማስተካከያና የሕግ እርምጃ በማስወሰድ በፍጥነት መግታት ተገቢ ወቅታዊ እንቅስቃሴ መሆን አለበት እንላለን። ነገር ግን እንደረጅም ግብ ሊታይ የሚገባው ጉዳይ በፓትርያርኩ የሚመራ የመዋቅር ጥናትና ማሻሻያ መምሪያ በማቋቋም ከዘመናዊ አስተዳደር ጋር ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማዘመን የመዋቅር ማሻሻያ ጥናት መደረግ ይገባል። 

ከዚያ ባሻገር በማኅበሩ ግፊት፤ በአስፈጻሚ ጳጳሳቱ በኩል ሙስናን እናጣራለን ማለቱ «በቆሻሻ መጥረጊያ ቤት መወልወል ይሆናል»

3/ ማኅበረ ቅዱሳን ከዚህ በፊት እንደተወሰነው ሀብትና ንብረቱን እንዲያስመዘግብ፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሞዴላ ሞዴሎች እንዲጠቀም፤ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ያለውን ሂሳብ በቤተ ክርስቲያኒቱ ኦዲት እንዲያስመረምር፤ ለወደፊትም በቤተ ክርስቲያኒቱ ተወስኖ በሚሰጠው ደንብ እንዲመራ የተላለፈውን ውሳኔ ያለምንም ማመንታት ተግባራዊ ማድረግ የግድ ይላል። በዚህ ዙሪያ ፓትርያርኩ የገቡትን ቃል በመጠበቅ ማስፈጸም እንዳለባቸው እናምናለን።
ስለሆነም ስለሙስናና ስለገንዘብ ብክነት ለመናገር በዘረኝነትና በእከከኝ ልከክህ የተሳሰሩ የጥቅም ተጋሪ ጳጳሳቱና ከኋላ በሚገፋቸው ማኅበር ሳይሆን እጃቸው ንጹህ የሆነ፤ የቤተ ክርስቲያኒቱን የጣሪያ ሳር ያልመዘዙ ልጆችዋ በኩል በመሆኑ ፓትርያርኩ ቆም ብለው በአስተውሎት እንዲመለከቱት ልናሳስብ እንወዳለን። እርግጥ ነው፤ ቤተ ክርስቲያን ችግር ላይ ነች። ነገር ግን ችግሯን ተተግነው ደረስንላት የሚሉ ሁሉ የየራሳቸውን ስውር ዓላማ ደብቀው የተነሱ ስለሆነ ጥንቃቄ መወሰድ ይገባዋል።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፤ 

በቅንነት የምንገልጽልዎ ነገር የቤተ ክርስቲያኒቱ ችግር የሚያንገበግባቸው፤ በታማኝነት፤ በፈሪሃ እግዚአብሔር ለማገልገል መንፈሳዊነቱም ፈቃደኝነቱም ያላቸው የተማሩ ልጆች ስላሉአት በጥንቃቄ አጥንተው ለቀጣይ እርምጃ እንዲበራቱ እንጠይቃለን። ማኅበሩም አጋጣሚዎችን ለራሱ በሚመቸው መልኩ እየተጠቀመ፤ የተወሰነበትን ውሳኔዎች ለማስቀልበስ የሚሄድበትን መንገድ ሊዘነጉ አይገባም። ቁርጠነቱ ካለ ሙሰኞችንም፤ ማኅበሩንም ቦታ ቦታቸውን ለማስያዝ ሰውም፤ ጊዜም፤ ኃይልም አለ!!

Saturday, August 22, 2015

ዘማሪት ዘርፌ ከበደ በማኅበረ ቅዱሳን ከተጠመደባት ወጥመድ በእግዚአብሔር ርዳታ ዳነች!


ባለፈው እሁድ ማለትም 10/12/2007 ዓ/ም በአዳማ ከተማ፣ በሥላሴ ቤተክርስቲያን፣ በተካሄደው ታላቅ ጉባኤ ዘማሪት ዘርፌ ከበደን በሕዝብ ሁሉ ፊት ‹‹በድንጋይ ወግሮ ማስወገርን›› ዓላማ አድርጎ ወደ ጉባኤው በነጎደው ማህበር ቅዱሳን ወጥመድ፤ እግዚአብር በችሎቱ ያዳናት፡፡ ይህ የጥፋት ማኅበር በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ጠብንና ሁከትን በምዕመናኑ መካከል የመፍጠር አጀንዳ ከመሸከሙ የተነሳ እንዲህ ዓይነት የወረደ አህዛባዊ ወጥመድ አጥምዶ በእግዚአብሔር ጉባኤው ውስጥ መግባቱ ለብዙዎች ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳን ያነገበ ጽንፈኛ ማህበር መሆኑን ፍንትው አድርጎ ያሳየ ሆኖል፡፡

    ዘማሪት ዘርፌ ከበደ በቤተክርስቲያናችን ደንብና ስርዓት በመዘመር በሕዝብ ሁሉ ፊት በአንድ ልብ በአንድ መንፈስ እግዚአብሔርን እያከበረች ባለበት ወቅት ነው፤ ባለ-ጊዜ በሆነ አንድ የማህበሩን ራዕይ በሚያራምድ ግለሰብ፤ መድረክ ላይ በእጇ የጨበጠችውን ማይክ በመንጠቅ፣ በግብዝነት በነሆለለ አዕምሮ ቢስነት በጥፊ ለመምታት ሙከራ ያደረገው፡፡ በሰዓቱ በሺዎች የሚቆጠር ምእመናን በመንፈስ መቃኘት ተወስኖ፣ በቅድስት ቤተክርስቲያን ዐውደ ምህረት ተሰባስቦ፣ የአንድነት የምስጋና ድምጽ ወደ ክቡር ዙፋን፣ ወደ ጸባኦት እንዲህ ሲል ይዘምር ነበር፡-

‹‹የማልደራደርበት የማልቀብረው እውነት፣ አንገት የማያስደፋ የማላፍርበት፣ ኢየሱስ የሚለው ስም እስትንፋሴ ነው፣ እውነቱ ይሄ ነው››፡፡ አስከትሎም ደግሞ በዚሁ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ኢየሱስን በሚያከበረው መንፈስ በመቀጣጠል ይሄው ሕዝብ፡- ‹‹የኔ ናርዶስ የኔ ቤዛ፣ በመዓዛው ልቤን ገዛ፣ ያንን መዳፍ ተመልክቼ፣ ተከተልኩት ሁሉን ትቼ"

 እያለ በአንድ ልብ እያመሰገነ ባለበት ቅጽበት ነው እግዚአብሔር ሲከብር በአንዳች ቁጣ የሚሞላው፣ በአንዳችም ሽንፈት ወራዳ ሥራን ሲሰራ የሚታወቀው፣ የጨለማው ዓለም ገዥ ዲያብሎስ በአደራጃቸው ጋሻ ጃግሬዎቹ በማኅበረ ቅዱሳን በኩል በስጋ አካል መዋጋት የጀመረው፡፡ በዚህ ሽብር መሐል ነው መጋቢ ምስጢር ቀሲስ ገብረሚካኤል የማነ በመነሳት ከወጋሪዎቿ እጅ ባላቸው የቤተክርስቲያኒቱ ስልጣንና አክብሮት በመንጠቅ ሥራ ተጠምደው ሳሉ፤ የአዳማ ከተማ ፖሊስ በስፍራው ደርሶ ዘማሪት ዘርፌን ከጽንፈኛው ማህበር ወጥመድ ያያዳኗት፡፡ መጽሐፍ እንደሚል፡- ‹‹ነፍሳችን እንደ ወፍ ከአዳኞች ወጥመድ አመለጠች። ወጥመድ ተሰበረ እኛም አመለጥን።›› መዝ 124፡-7፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን የተመለከቱ፣ በዚህ አንካሳ ማኅበር ሽብር ክፉኛ ልባቸው የተሰበረ ምዕመናን ‹‹በጉባኤው ውስጥ በሐዘን እንባ ፊታቸው›› ሲታጠብ ተስተውሏል፡፡ ማህበረ ቅዱሳን የቤተክርስቲያን የወቅቱ ፈተናና መከፋፈል ምክንያት መሆኑ አሁን አሁን በግላጭ መታየት ጀምሯል፡፡

    እንዲህ ዓይነት የወረደ ግብር በማኅበረ ቅዱሳን ሁከት ፈጣሪነት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ምዕመናንና ብርቅዬ አገልጋዮቿ ላይ መፈጸሙ እንግዳ እንዳልሆነ የሚታወቅ ነው፡፡ ለዛም ነው ብዙዎች የደብር አለቆችና ካህናት በአንድ ድምጽ ማኅበሩ ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳውን በቤተክርስቲያኒቱ ስም እየፈጸመ እንዳለ የመሰከሩትን በማስረጃነት በመጥቀስ ሆነ ብሎ ‹‹ቤተክርስቲያኒቱን በሽብር ለማናጥ እየሰራ›› ነው ሲሉ የሚከሱት፡:

    ከዚህ በፊትም ይሄው ማህበር ባሰለፋቸው ጨካኝ ወንቤዴዎቹ በመታገዝ፤ ግንቦት 8 ቀን 2005 ዓ/ም በቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን፣ የቀሲስ ሊቀ መዘምራን ትዝታው ሳሙኤልን ደም ማፍሰሳቸውንና በአምቡላንስም ለፈጣን ህክምና ሆስፒታል ድረስ ለመሄድ ተገዶ እንደነበር የምናስታውሰው ነው፡፡ ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ ቀሲስ ትዝታው ሳሙኤል በማኅበረ ቅዱሳን በኩል በቅድስት ቤተክርስቲናችን ላይ እየደረሰ ስላለው እኩይ ተግባር ለአባ ሰረቀ ብርሃን ያቀረበውን ግልጽ ጥያቄ  ማየት ይችላሉ፡-

    በቅርቡ አፍሪካ ሕብረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን፣ በሴኔ ወር 12 ቀን 2007 ዓ/ም እንዲሁ በደቀመዝሙር ዘማሪ ዲያቆን ከፍያለው ቱፋ ላይ ከፍተኛ ድብደባ መፈጸሙና ለቀናት ያክል በህክምና ሲረዳ መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡ ድብደባቸው ሳይሆን የሚገርመው ቅድስት ቤተክርስቲያን ግቢ ውስጥ በማን አለብኝነት መፈንጨታቸና አገልጋዮችን እየደበደቡ ሞባይል ቀፎና ገንዘብ የመዝረፋቸው ነገር ነው የሚደንቀው፡፡

ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ዲያቆን ከፍያለው ቱፋን ደብድበው ከጣሉት በኋላ የ4500 ብር ስማርት ፎንና ገንዘብ ሰርቀው ሲያበቁ ‹‹አንተ ተሐድሶ፣ አንተ ጴንጤ፣ ደበደብንህ፣ ምንትሆን እንግዲህ›› እያሉ መንፈሳዊ መስለው መቆማቸው ነው፡፡ እግዚአብሔር ከዚህ ዓይነቱ አዕምሮ ቢስነትና ድንዛዜ የቅድስት ቤተክርስቲያንን ምዕመን ይጠብቅልን!
ይህን መረጃ ያቀበላችሁኝ የአዳማ ሥላሴ ቤተክርስቲያን መዘምራንን እግዚአብሔር አምላክ ይባርካችሁ! የጨለማውን ሥራ እንዲህ በብርሃን ጸዳል መግለጡ ተገቢ ነውና!
ከውስጥ አዋቂ ምንጭ

Wednesday, August 19, 2015

ቅዱሳን መላእክትና ቅዱሳን ሰዎች በሁሉም ሥፍራ በአንድ ጊዜ መገኘት ይችላሉን?


1/ እንደመግቢያ፤

   መላእክትና ሰዎች በእግዚአብሔር ግብር የተፈጠሩ ፍጡራን ናቸው።  በኦሪት ዘፍጥረት የመጀመሪያዎች ሁለት ምዕራፎች እንደተመለከተው በላይ በሰማይ፤ ከታች በምድርና በጥልቅ ውሃማ አካሎች ሁሉ እግዚአብሔር በለይኩን ቃሉ (ከአዳም በስተቀር) የፈጠራቸውን ሥነ ፍጥረቶች እናገኛለን። በመሠረተ እምነት ደረጃ ፍጡር ስንል ፈጣሪ ወይም አስገኚ ያለው ነገር ማለታችን ነው። መፍጠር ወይም የሌለውን ነገር ማስገኘት ማለት አንድን ነገር መሥራት ወይም መፈብረክ ማለት አይደለም። የነገረ መለኮት ምሁራን መፍጠርን ወይም ማስገኘትን ሲገልጹ «from nothing to something» በማለት ይገልጹታል። «ከምንምነት ወደአንድ ነገርነት» ማምጣት ማለት ነው።  እግዚአብሔር ለመፍጠር መነሻ ሃሳብ ወይም ጥሬ ነገር /substance/ አያስፈልገውም።  

   ፍጡራን ግን ይህንን ማድረግ አይቻላቸውም። ለምሳሌ ወንበር የሠራ ሰው ፈበረከ ወይም ሠራ ቢባል እንጂ «ፈጠረ ወይም አስገኘ» ሊባል የተገባው አይደለም ይላሉ ምሁራኑ። ምክንያቱም «ወንበር» የተባለውን ቁስ ለመሥራት  አንዳንድ ነገሮች «something» የግድ ያስፈልጉታልና ነው። ይህም የሥራ ጉዞ «from something to something» በቅርጽ፤ በመጠንና በይዘት ይለውጠዋል እንጂ /from nothing to something/ ከምንም ነገር ሳይነሳ «ወንበር» የተባለውን ቁስ ማቅረብ አለመቻሉ የጉድለቱ አንድ አስረጂ እንደሆነ በአመክንዮ ያቀርባሉ።  ያንንም ወንበር እንኳን ለመሥራት ወይም ለመፈብረክ የግድ የሚያስፈልጉት ጥሬ ሀብቶች /raw materials/ የሠራተኛው የራሱ ግኝቶች አይደሉም። 

   ስለሆነም ፍጡራን በሙሉ ያላቸው ሁኔታ፤ ችሎታና ብቃት ያልተወሰነ፤ በአፈጣጠር ያልተገደበ አይደለም። በሥራቸው ሁሉ ምሉዕነት ያለው፤ ጉድለት አልቦነትም የማይጎበኘው አይደለም። መላእክትና ሰዎች መነሻም፤ መድረሻም አላቸው። መነሻና መድረሻ ያለው ፍጥረት ደግሞ በአንድ ጊዜ በስፍሐትና በምልዓት በሁሉ ሥፍራ መገኘት አይችልም። በሥራው ሁሉ በብቃትና በራሱ ኃይል የማከናውን ፍጹምነት የለውም።

 የእግዚአብሔር ባህርይ ግን ከዚህ የተለየ ነው። እግዚአብሔር የሁሉ ነገር ፈጣሪና አስገኚ ስለሆነ መነሻም መድረሻም የለውም። ኋለኛ የሌለው ፊተኛ፤ ፊተኛም የሌለው ኋለኛ እሱ ብቻ በመሆኑ አልፋና ኦሜጋ እንለዋለን።
መጽሐፍ ቅዱስ « በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ፈጠረ» ዘፍ 1፤1 ሲል እግዚአብሔር ከምንም ነገር «from nothing to something»  ለመፍጠር ወይም ለማስገኘት ምንም ተጨማሪ ነገር እንዳላስፈለገውና እሱ ብቻ እንደተቻለው እንረዳለን። ሰማይና ምድርን ግን የፍጥረት መነሻ ሆነው ተከስተዋል። ሁለቱም በሥፍራ፤ በቦታና በሁኔታ ተወስነዋል። ምድር በውስጧ የተገኙት ፍጥረታትም ሁሉ መነሻና መድረሻ፤ መጠነ ውሱንነትና መጠነ አኽሎኝነት ይዘው መገኘታቸውን በእያንዳንዱ የሥነ ፍጥረታት ጠባይዓት ላይ እንመለከታለን። ከፍጥረታት አንዱ ክፍል የሆነው የሰው ልጅን ብንመለከት በፍጥረተ ጠባዩ  የአስተሳሰብ፤ የአፈጣጠርና የማንነት ብቃት በተሰጠው እሱነቱ ልክ ተወስኖ ይገኝበታል።

  እርግጥ ነው፤ ስለሃይማኖት ጥሩ ግንዛቤ ያለው ሰው ያለብዙ ምክንያታዊ ውጣ ውረድ «ፍጡራን በአንድ ጊዜ በሁሉ ሥፍራ መገኘት አይችሉም!» ብሎ መልስ ሊሰጥ ይችላል። ደግሞም የሚሠመርበት እውነት፤ በሁሉ ሥፍራ፤ በአንድ ጊዜ፤ በስፍሐትና በምልዐት  (በምሉዕ ኵለሄነት) የመገኘት ብቃት ከእግዚአብሔር በስተቀር ለፍጡር አይቻለውም የሚለውን እውነት አምኖ መቀበል ነው። ሁሉን ቻይነት/Omnipotence/ ከእግዚአብሔር በቀር ለማን ይቻለዋል? ለማንም!!

«ከማኅፀን የሠራህ፥ የሚቤዥህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሁሉን የፈጠርሁ፥ ሰማያትን ለብቻዬ የዘረጋሁ ምድርንም ያጸናሁ እግዚአብሔር እኔ ነኝ ከእኔ ጋር ማን ነበረ?» ኢሳ 44፤24

በላይ በሰማይ፤ በታች በምድር በሁሉም ሥፍራ ያለና የሚኖር፤ የሚሰማም፤ መልስ የሚሰጥም እግዚአብሔር ብቻ ነው።
ቅዱሳን መላእክት ይሁኑ ቅዱሳን ሰዎች በሰማይ ሥፍራቸው ሳሉ በምድር የሚደረገውን ሁሉ ያውቃሉ? ያያሉ? ይሰማሉ? በፍጹም አያውቁም፤ አያዩም፤ አይሰሙም።  በሰማይ ሳሉ በምድር ያለውንም የሚያውቁ ከሆነ በስፍሐትና በምልዓት ይገኛሉ ማለት ነው። ይህ ደግሞ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ያለ ስህተት ነው። ከላይ ለመግለጥ እንደተሞከረው በአንድ ጊዜ በሁሉም ስፍራ የመገኘትን ብቃት የፈጣሪ እንጂ የፍጡራን እንዳልሆነ የገለጽነውን እውነታ የሚጻረር ይሆናል።  

2/ «እግዚአብሔር ብቻውን በሁሉ ሥፍራ አለ» የምንለው ለምንድነው?

መልሱ አጭር ነው። እግዚአብሔር በላይ በሰማይ፤ በታች በምድርም፤ በሁሉ ሥፍራ መገኘት የሚችለው በላይ በሰማይ ይሁን በታች በምድር ላለው ነገር ሁሉ ፈጣሪና አስገኚ ስለሆነ ነው።
 ከባዶነት ወደአንድ ነገርነት ማምጣት የቻለ ፈጣሪ፤ በፈጠረው ነገር ሊገደብ፤ ሊወሰን፤ ሊከለከል አይችልም። ፍጥረታት ግን በዚህ ብቃት ውስጥ ሊገቡ አይችሉም። ምክንያቱም ፍጥረታት በቦታ፤ በሁኔታና በአፈጣጠር ውሱን ስለሆኑና ከፈጣራቸው እግዚአብሔር ጋር ሊስተካከሉ ስለማይችሉ ነው። የቅዱሳን መላእክትና የቅዱሳን ሰዎች ብቃት እግዚአብሔር በሰጣቸው መጠንና ፈቃድ የተወሰነ ነው።  መላእክቱ ይሁኑ ሰዎች ፍጡር እንጂ ፈጣሪዎች ባለመሆናቸው ፍጥረተ ዓለም ይወስናቸዋል። እግዚአብሔር ግን እንዲህ አይደለም። በትንቢተ ዳንኤል ላይ እንዲህ እንደተመለከተው፤
«በምድርም የሚኖሩ ሁሉ እንደ ምናምን ይቈጠራሉ፤ በሰማይም ሠራዊት በምድርም ላይ በሚኖሩ መካከል እንደ ፈቃዱ ያደርጋል፤ እጁንም የሚከለክላት ወይም ምን ታደርጋለህ? የሚለው የለም» ዳን 4፤35

3/ የቅዱሳን መላእክት ውሱንነትና በስፍሐት አለመገኘት

እያየን በመጣነው ከእግዚአብሔር ስፉሕነትና ከፍጥረታት ውሱንነት የተነሳ መላእክት በምልዐት በሰማይም በምድርም ሊገኙ እንደማይችሉ  እናምናለን። ነገር ግን ከላይ የገለጽነውን ጉዳይ ዳግም ማንሳት ያስፈለገን ዐቢይ ምክንያት ብዙ ሰዎች የመላእክትን ውሱን መሆን፤ በሁሉ ሥፍራ በአንድ ጊዜ አለመገኘት አምነው ሲያበቁ  ከዚህ ተቃራኒ በሆነ አቋም  ቅዱሳን መላእክት በአንድ ጊዜ በሰማይና በምድር የመገኘት ብቃት እንዳላቸው የሚያስተምሩና አምነው የሚያሳምኑ  ሰዎች በመኖራቸው  ነው። 

   ሰው በአንድ ጊዜ አማኝም፤ ከሀዲም መሆን አይችልም። ምክንያቱም  ጣፋጭ ፍሬ የሚሰጥ ዛፍ ፤ በጭራሽ መራራና ጣፋጭ ፍሬ በአንድ ጊዜ ማፍራት እንደማይቻለው ሁሉ በእምነት የቅዱሳን መላእክትንም ሆነ የቅዱሳን ሰዎችን የውሱንነት ተፈጥሮ ካመንን በኋላ በምንም ዓይነት መንገድ ከዚህ በተጻራሪ መቆም ስለማይቻለን ነው።
ብዙ ጊዜ ሰዎች አምኛለሁ ባሉበት እምነት ውስጥ ክህደት መሰል ነገር የለም ብለው የሚከራከሩት ስላመኑት እምነት በቂ እውቀትና ግንዛቤ ስለሌላቸው ነው። ለዚህ ጥሩ አብነት የሚሆነን ነጥብ፤ በአንድ ወቅት ሰዱቃውያን ወደ ጌታችን፤ አምላካችንና መድኃኒታችን  ኢየሱስ ክርስቶስ ቀርበው ትንሣኤ ሙታንን ለመቃወም «በምድር ሰባት ባል ያገባች ሴት በሰማይ ለማንኛቸው ትሆናለች?» ብለው በጠየቁት ጊዜ የሰጣቸው መልስ  በየትኛውም ዘመንና ጊዜ ለሚነሳ ጥያቄ እንደአስረጂ አቅርበን እዚህ ላይ ብንጠቅሰው ተገቢ ይመስለናል።
«ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ትስታላችሁ» ማቴ 22፤29 አላቸው።

  እግዚአብሔርን የሙታን ብቻ አምላክ አድርጎ መንሥኤ ኃይሉን መካድ ከባድ ስህተት ነው። መጻሕፍት የሕያዋን አምላክ ብለው ሲመሰክሩ ይህንንም አለማወቅ ስንፍና ነው። ለዚህ ሁሉ ምክንያቱ አንድ ነው።
  ሰዎች «እናምንበታለን» ባሉት ነገር ውስጥ የሚገቡ ስህተቶች ሁሉ ተቀባይነት አግኝተው ሃይማኖታዊ ካባን የሚላበሱት «መጻሕፍቱንና የእግዚአብሔርን ኃይል» በደንብ ካለመረዳታቸው በሚመጣ ጉድለት እንደሆነ ሁሉ፤ በዚህም ዘመን ያሉ ስህተቶችን እንዲሁ እንገነዘባቸዋለን።  ሰዱቃውያን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን በእጃቸው ይዘው ሲያበቁ ስለትንሣኤ ሙታን አለመኖር አምነው መቀመጣቸው ላያስገርም ይችላል። ምክንያቱም ሰዎች የእግዚአብሔር ኃይል መገለጫ መንገዶችን ወደሚናገሩ ወደ ቅዱሳት መጻሕፍቱ ይሄዳሉ እንጂ መጻሕፍቱ ወደሰዎቹ ሊመጡ አይችሉም ነው።  በእጃቸው ያለው መጻሕፍትማ  የሚሉት እንደዚህ ነበር።

«ስለ ትንሣኤ ሙታን ግን እኔ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ የሚል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ እናንተ የተባለውን አላነበባችሁምን? የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም»  እያለ እውነቱን ቢናገርም እያየበቡ ስለማያስተውሉ የትንሣውን ኃይል ክደዋል (ማቴ 22-31-32 ፤  ዘጸ 3፤6 )

ሰዱቃውያኑ ከተቀበሏቸው መጻሕፍት ውስጥ የተጻፈውን አለማወቃቸው የሚያስረዳን ነገር መጻሕፍትን በመያዝ ወይም በማንበብ  እውነት ሁልጊዜ ይገለጣል ማለት አይደለም።  መረዳቱ ካላቸው ሰዎችም ዘንድ ለኛ ያልተገለጠን እውነት ስለሚኖር ሌሎችን በመጠየቅ ወይም የሚሉትን በማስተዋልና እንደእግዚአብሔር ቃል በመመርመር ወዳልደረስንበት እውነት ልንደርስ እንችላለን። እንደዚሁ ሁሉ በዚህ ዘመንም ያሉ ሰዎች የቅዱሳን መላእክትንንና የቅዱሳን ሰዎችን ውሱንነትና በምልዐት ያለመገኘት ተፈጥሮ አምነው ሲያበቁ በተግባር ግን ከዚህ አስተሳሰብ በተቃራኒ ቆመው የመገኘታቸው ነገር በመጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነታ ውስጥ ለመኖር ካለመቻል የመጣ እክል ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። 

4/ በሰማይ ሥፍራ ያሉ ቅዱሳን በዓለመ ምልዓትይገኛሉን?

ፍጡራን ውሱንና በሁሉ ሥፍራ የመገኘት ብቃት እንደሌላቸው ከላይ በተደጋጋሚ ለማሳየት በሞከርነው ላይ ካመንን በዓለማት ሁሉ በምልዓት ሊገኙ አይችሉም ብለን ደፍረን መናገር እንችላለን። እንደመላእክቱ ሁሉ ቅዱሳን ሰዎች በተወሰነ ሥፍራ፤ በተወሰነ  መጠንና  በተፈቀደላቸው ዓለም የሚኖሩ እንጂ ምሉዕ በኵለኄ ስላይደሉ እንደፈጣሪ ሁሉን አዋቂነት የላቸውም ብንልም ስህተት አይደለም። ከዚህ በተለየ አስተሳሰብ ላይ ከሆንን ደግሞ ሊሆን የሚችለው ነገር ሁሉን ቻይ በሆነው በእግዚአብሔር ኃይልና ፍጡር በሆነው ፍጥረት መካከል ያለውን ልዩነት አለመረዳት ስለሚሆን እምነቱ በክህደት የተሞላ ይሆናል። በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የፈጣሪን ኃይል ለፍጡራን ከመስጠት የበለጠ ክህደት የለም። እግዚአብሔርን የሚመስል ምንም ነገር ሊኖር አይችልምና።

«አቤቱ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ በሰማይ ወይም በምድር አንተን የሚመስል አምላክ የለም፤ በፍጹም ልባቸው በፊትህ ለሚሄዱ ባሪያዎችህ ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ» 2ኛ ዜና 6፤14

መላእክት ቅዱሳን በመሆናቸው ወይም ቅዱሳን ሰዎች አምላካቸው ስላከበራቸው እግዚአብሔርን የሚመስል ባህርይ እንዳላቸው አድርጎ ማሰብ  አስነዋሪ ነገር ነው። ቅዱሳን በዓለመ ሥጋ ሳሉ ወይም በዓለመ መላእክት የሚገኙ መላእክት የሚሠሩት ሥራ በእግዚአብሔር ፈቃድና በተሰጣቸው ጸጋ ይወሰናል። በዚህ ምድር የሚኖሩ ቅዱሳን ሙት ቢያስነሱ፤ ደዌ ቢፈውሱ ከተሰጣቸው ጸጋ አኳያ እንጂ በተፈጥሮ ካላቸው ብቃት የተነሳ አይደለም።  በዚያም ጸጋ ቢሆን የሚመሰገነውና ሊመሰገን የተገባው የጸጋው ባለቤት እግዚአብሔር ብቻ ነው። ቅዱሳኑን ማክበር አንድ ነገር ነው፤ ነገር ግን በማክበር ሽፋን ወይም እግዚአብሔር በነሱ በኩል በሠራው አስደናቂ ነገር የተነሳ ለእነሱ ምሥጋናና ውዳሴ እንድንሰጥ የሚያደርገን አንዳችም መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ የለም። ጸጋ ማለት እግዚአብሔር በወደደው መንገድ የራሱን ሥራ የሚሠራበት ኃይል እንጂ ሠራተኞቹ ይመሰገኑበት ዘንድ የተሰጠ የውዳሴያቸው መሣሪያ አይደለም።

«አሁንም ጸጋን ይሰጠን ዘንድ እግዚአብሔርን ለምኑ፤ ይህ ከእጃችሁ የተሰጠ ሲሆን ከቶ ፊታችሁን ይቀበላልን? ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር» ሚል 1፤9

ጸጋ የሚሰጥ፤ የሚከለከል ኃይል ነው። ጸጋ ሰጪው በፈቀደው መጠን ለፈቀደው ጉዳይ የሚሰራበት መንገድ እንጂ ወሰን የሌለውና ሁሉን ለማድረግ ክበበ ተፈጥሮን አልፎ የሚሄድ ምሉዕ ኃይል ያለው ማለት አይደለም።

«እንደ ተሰጠንም ጸጋ ልዩ ልዩ ስጦታ አለን» ሮሜ 12፤6


«ሐዋርያትም የጌታን የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ በታላቅ ኃይል ይመሰክሩ ነበር፤ በሁሉም ላይ ታላቅ ጸጋ ነበረባቸው» የሐዋ 4፤33

በአንድ ወቅት ሐዋርያው ጳውሎስ ልስጥራን በሚባል ሀገር በገባ ጊዜ በልስጥራን የተባለ ከልጅነቱ ጀምሮ እግሩ ሽባ የሆነና የሰለለ ሰው አግኝቶ በኢየሱስ ስም ከፈወሰው በኋላ  አማልክት ከሰማይ ወርደዋል ብለው ሲያበቁ ሕዝቡና የድያ ካህን ኮርማ ሊሰዋላቸው ፈለገ። ጳውሎስና በርናባስ ግን ልብሳቸውን ቀደው እንዲህ አሉ።

«እንዲህም አሉ። እናንተ ሰዎች፥ ይህን ስለ ምን ታደርጋላችሁ? እኛ ደግሞ እንደ እናንተ የምንሰማ ሰዎች ነን፥ ከዚህም ከንቱ ነገር ሰማይንና ምድርን ባሕርንም በእነርሱም ያለውን ሁሉ ወደ ፈጠረ ወደ ሕያው እግዚአብሔር ዘወር ትሉ ዘንድ ወንጌልን እንሰብካለን» የሐዋ 14፤14-15

የቅዱሳን መላእክትም ይሁን የቅዱሳን ሰዎች ዋና የእምነታቸው ማእከል ራሳቸውን በምሥጋናውና በተሠራው ቦታ ማስቀመጥ ሳይሆን እግዚአብሔር በእነሱ በኩል እንዲከብር ማድረግ ነው።  ከጳውሎስ ተአምራት የተማርነው ነገር ተአምራቱን የሠራው ጳውሎስ ሳይሆን መክበር ያለበት የተአምራቱ ባለቤት እግዚአብሔር ብቻ እንዲከብር ሰዎች ሁሉ ዓይናቸውን በእግዚአብሔር ላይ እንዲጥሉ በኃይለ ቃል ሲናገራቸው የምናነበውም ለዚህ ነው።

5/ በሰማያት ሥፍራ ያሉ ቅዱሳኑ መላእክትና ቅዱሳን ሰዎች የሰዎችን ልመናና ጸሎት ሰምተው ምላሽ ሊሰጡ ይችላሉን?

የቅዱሳኑን ውሱንነትና በምልዓት ያለመገኘት ብቃት መመልከት ያስፈለገን ከዚህ በታች ለምናቀርባቸው ጭብጦች ገላጭ አስረጂ እንዲሆኑን ከመፈለግ የተነሳ ነው። ውሱንነትና በምልዓት አለመገኘት ማለት ከታች ለሚነሱት ነጥቦች መልስ ይሰጡናል።
እዚህ ላይ ሁለት የተለያዩ ነጥቦችን ልናነሳ እንገደዳለን። አንደኛው ቅዱሳን መላእክት በሰማያት ባለ የምሥጋና ዓለም እያሉ በምድር የሚደረገውን ነገር ሁሉ ያውቃሉ ወይ? የሚለውንና በገነት ያሉ ቅዱሳን በምድር የሚደረገውን ሁሉ ማየት ወይም መስማት ይችላሉ ወይ? የሚለውን ነጥብ ለይቶ መመልከት ተገቢ ነው።
 ከቅዱሳን መላእክትና ከቅዱሳን ሰዎች ተፈጥሮ የተነሳ በምልዐት ያለመገኘትን ጉድለት የተነሳ በገነት ወይም በዓለመ መላእክት ያሉ ቅዱሳን በዚህ ክበበ ዓለም ያለውን ነገር ሁሉ በአንዴ ሰምተው፤ በአንዴ አውቀው፤ ምላሽ ሊሰጡ አይችሉም። በወሰነ ነፍሳዊ አካል በገነት ሳሉ በዚህ ምድርም የመገኘት ብቃት የሌላቸው ከመሆኑም ባሻገር በተፈጥሮአቸውም  በገነት ሳሉ  በምድር ያሉ ሰዎችን ጸሎት በብቃት በመስማት ምላሽ ለመስጠት  ስላይደለ የሁሉን አዋቂነትና ሰሚነት ችሎታ የላቸውምና በምድር ላይ ሆነን በገነት ይሰሙናል ልንል የተገባ አይደለም። ይህን የማድረግ ባህርይ የእግዚአብሔር የብቻው ነው። 

   በዚህች ባለንባት ምድር በየትኛውም ማእዘነ ዓለም በስማቸው የሚደረገን ልመና በገነት ሳሉ ይሰማሉ ማለት ፈጣሪ ናቸው ብሎ በክህደት አዘቅት ውስጥ መውደቅ ማለት ነው።
ቅዱሳን መላእክትን እግዚአብሔር ለፈለገው ዓላማ ሲልካቸው ወይም እንዲገኙ በተሰወነላቸው ሥፍራ ከመገኘት በስተቀር በፈቃዳቸው ወይም ሰዎች ስለጠሯቸው እንደፍላጎታቸው ሊሄዱ አይችሉም፤ ያልተወሰነ የመስማት ብቃትም የላቸውም።  በኢጣሊቄ ይኖር ለነበረ ጭፍራ፤ የመቶ አለቃ የሆነው ቆርኔሌዎስ ጸሎቱና ምጽዋቱ በእግዚአብሔር ዘንድ ስለተወደደ ስሙ ያልተገለጸ የእግዚአብሔር መልአክ በተልእኰ መጥቶ መልእክት ማድረሱንና ማድረግ ስለሚገባው ነገር ሲናገረው እናነባለን።

እዚህ ላይ ሊሠመርበት የሚገባቸው ነጥቦች ሦስት ናቸው።

ሀ/ የመልአኩ ድርሻ  ማንነቱን ማስተዋወቅ ወይም የራሱን ሃሳብ መግለጽ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላለፈውን መልእክት ማስረዳት ብቻ ነው። ከነበረበት ሰማያዊ ሥፍራም በተልእኰ ወደቆርኔሌዎስ ሲሄድ የነበረበትን ዓለመ መላእክት ለቆ ይወርዳል እንጂ በስፍሐት በነበረበት ቦታም በተመሳሳይ ሁኔታ ሊገኝ አይችልም። መውጣትና መውረድ ያስፈለገውም ለዚህ ነው።
ለ/ መልአኩ ከቆርኔሌዎስ ቤት የተገኘው መልአኩ በስሙ ስለተደረገው ጸሎትና ምጽዋት ምላሽ ሊከፍለው መምጣቱን ለመንገር ሳይሆን ቆርኔሌዎስ በአምላኩ ስም ያደረገው ነገር በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ማግኘቱን  በመግለጽ የእግዚአብሔር መልእክት ለማድረስ ብቻ ነው።
ሐ/ በዚህ ሥፍራ ስሙ ያልተገለጸውን የመልአክ ስም በምትሃት ጠቅሰን በመናገር መልእክት አድራሽነቱን እንደባለቤት ቆጥረን እንድናመሰግነው የሚያደርገን አንዳች ነገር የለም።

 ይሁን እንጂ በዘጸአተ እስራኤል ታሪክ ላይ ያልተገለጸው መልአክ፤ ሚካኤል እንደመራቸው ተደርጎ የተጠራውና በትንቢተ ዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ እንደተመለከተውም፤ ሠለስቱ ደቂቅን ከእቶን እሳት ያዳናቸው፤  እግዚአብሔር ባወቀ ያልገለጸውን የመልአክ ስም በመስጠት ሚካኤልና ገብርኤል ናቸው እያሉ የስህተት ትምህርቶች ምሥጋናውን ሁሉ  ከእግዚአብሔር ላይ ለመውሰድ የተደረገ ትግል ከመሆን አያልፍም። በእግዚአብሔር ሥፍራ ላልተገለጹ መላእክት ክብርና ምስጋናን በመስጠት እግዚአብሔርን ማስቀናት የጠላት ሴራ ውጤት ነው። በእርግጥም ይህንን የሚያደርገው ሰይጣን ነው።  ምክንያቱም በቅዱሳን መላእክት ስም ተሸሽጎ ሰዎችን ከእግዚአብሔር ፈቃድ ለማስወጣት የብርሃን መልአክ ነኝ ቢል ማስመሰል የቆየ ተግባሩ ነው።  በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መንፈስ ቅዱስ  ሳይገልጽ በዝምታ ያለፈውን ነገር እንዳለ ለሱ በመስጠት በዝምታ እንደመተው የመሰለ ማለፊያ እውቀት የለም።

   እንደዚሁ ሁሉ ወደቆርኔሌዎስ የተላከውን መልአከ ማንነት እግዚአብሔር ብቻ ባወቀው ሁኔታ ስላልተገለጸ ከዝምታ ባለፈ ወደስም ገላጭነት የሚያሸጋግረን ምክንያት የለም። «እንደአናንያ፤ እንደአዛርያ፤ እንደሚሳኤል፤ አድነን ገብርኤል» እንድንል የሚያደርገን ከመጽሐፉ ባለቤትም የተሻለ እውነት እኛ ዘንድ የለም።
ስለሆነም ቅዱሳን መላእክቱ ሰዎች ወደእግዚአብሔር በሚያቀርቡት ልመናና ጸሎት ወይም እግዚአብሔር እንዲራዱ፤ እንዲታደጉ ሲልካቸው በትእዛዝ ብቻ ተልእኰአቸውን ለመፈጸም ከሚመጡ በስተቀር ሰዎች ስማቸውን ስለጠሩ፤ በስማቸውም ስለተማጸኑ፤ ለዚያ የሚሆን ዋጋ ለመስጠት ደስ ተሰኝተው፤ ላደረጉትም ትድግና ምስጋና ለመቀበል ሽተው በጭራሽ አይመጡም። ምክንያታችንም ከላይ ስንገልጽ እንደመጣነው መላእክቱም ይሁኑ ቅዱሳኑ በሰማይ ሳሉ በምድር ላይ በስማቸው የተደረገውን የሰዎችን ሁሉ ልመና መስማት፤ መቀበልና ምላሽ የመስጠት ብቃት ስለሌላቸው ነው። በምልዓት ተገኝቶ የመስማትና ጸሎት የመቀበል ችሎታ የእግዚአብሔር ብቻ ስለሆነ!!

ክፍል ሁለት ይቀጥላል ….

Saturday, August 1, 2015

ኤሎሄ ኢየሱስ!

እንደምነህ ጌታ፤ ቸሩ ፈጣሪያችን፤
እኛማ አለነው፤ ከተባለ ኖርን።  
አልደላን፤ አልሞቀን በርዶን፤ አልተመቸን፤  
መግባትና መውጣት፤
ማልቀስና ማዘን ድሩን አድርቶብን፤                                                                                                                        
አንዱ ሲወጣብን፤ አንዱ ሲሄድብን።                                                                                                     
እነሆ አለነው፤ የሰው መንገድ ሆነን።

በናፍቆት ስንጠብቅ፤ ኑረትን የኖርነው
ሌሎች የገቡባት ሰማይ ቤት እንዴት ነው?
እመጣለሁ ብለህ ቆየህሳ  ምነው ?
እኛማ .....እኛማ
ለሹመኛ አለቃ፤ ማመልከቻ ፅፈን
ለወፈ ሰማይ ሕዝብ፣ መድረክ ላይ ለፍፈን
ጸሎት ቤታችንን፤ እኛው ላይ ቆልፈን
የምድር አተካራ፤ ህግጋቱን አልፈን                                                                                                                                    
ቢጨንቀን፤ቢጠበን
ሁለት ሽህ ዘመን፤ እነሆ አለፈን     
ስጋችንን ለብሰህ፤ ካየነው ዐይንህን።

የመምጣትህ ተስፋ ርቆ እየዳመነ                                                                                                       
እምነት ተስፋ ፍቅር እየመነመነ
ቢዘገይ ሰዓቱ ...እምነትን ዘንግተን                                                                                                                           
የልባችን ምኞት፤ ቢያይል መሻታችን                                                                                                       
የሰጠኸውን ትተን ያላልከውን ሆንን                                                                                                         
ችላ ብለን አደርን፤ ረሳንህ ጌታችን
ጠብቀን ጠብቀን ሁለት ሽህ ዘመን።

ሲሰግዱ ሰግዳለሁ፤ ሳይታጎል ጾሜ                                                                                                      
ሲበሉም በላለሁ፤ ልማዴን ደግሜ                                                                                                                                              
እልልታም፤ ዝማሬም ሲነቅፉም ቀድሜ                                                                                                                         
ምሰሶ ዐይኔ ውስጥ እኔም ተሸክሜ፤                                                                                                      
እነሆ አለሁኝ በዘልዛላ እድሜ።
የንስሐ ዘመን ቢኖረኝ ጥቂት                                                                                                                     
የቀረህ መሰለኝ ያንተ መዘግየት
ጥቂት ልጠይቅህ አቤቱ ጌታ ሆይ                                                                                                                              
ከነቅዱሳንህ አንተ ደህና ነህ ወይ?
ከምር እንደሚያሙት ምጽአት ቀረ እንዴ ?
በቶማስ ልቡና ጠረጠርኩ አንዳንዴ !                                                                                                                                  
ታውቀዋለህና ያለውን በሆዴ።
መጠርጠሬስ በእውነት ከእምነቴ ነው እንጅ፤                                                                                                 
አይደለም ከክዳት ለመውጣት ከደጅ፤                                                                                                       
ዘመኑን ከፋና እድሜን የሚፈጅ፤                                                                                                         
ኃጢአት ነገሰ፤ ለጠላትም ወዳጅ                                                                                                                    
ባየኸው ትውልዱን ሆኖልህ የማይበጅ።                                                                                                             
አንተ የሰጠኸው ረዳቱ ቀረና                                                                                                                
ራሱን አወቀ አሉ፤ ወንዱንመረጠና፤                                                                                                                                                                                                                       
ይሄ ሁሉ ሆነ ረዝሞ መዘግየትህ                                                                                                                
ኧረ መቼ ይሆን የመምጫ ዘመንህ?
የሆነስ ሆነና ሰማይ ቤት እንዴት ነው
አብረሃም ሰላም ነው ...
እዛስ ቤት ገነባ? ወይስ በድንኳን ነው ?
እኛማ ይሄውልህ ...
በቤት ኪራይ ችንካር እየተሰቀልን
‹‹ኤሎሄ›› እንላለን ጎጆ እንድጥልልን ....
ወደላይ ገነባን ወደጎን አሰፋን
ወደላይም ከላይ ወደጎንም ከጎን
እንደጉድ ተገፋን
ቤት ለእንግዳ ማለት ጭራሹኑ ጠፋን !!
አባታችን ሙሴ እንዴት ነው ለክብሩ
ውቅያኖስ መክፈያው ደህና ናት ብትሩ ?
እኛማ ይሄውልህ ....
እንጀራ ፍለጋ ባህር ስናቋርጥ
የተስፋዋን ምድር ቀን ሞልቶ ሳንረግጥ
የትም ውሃ በላን የትም አሳ ላሰን
ን ገ ር ል ን ና ብትሩን ያውሰን ....
በትር ያለው መሪ መቼም አላገኘን፤                                                                                                              
ዘመን የሚያሻግር እባክህ ላክልን።
እናልህ ጌታ ሆይ ....
ከተስፋዋ ምድር ወደሌላ ተስፋ አለን እየኳተን
መሄጃው ሲገርመን
መመለሻ መንገድ መቆሚያ ቦታ አጥተን ...!
ላባታችን ሙሴ እንደምትልልን ...
የመሄድ ዘመን ነው
ባህር የሚያሻግር
በትርህን ላክልን ...

ሰማይ ቤት እንዴት ነው ? ...                                                                                                                                                         
ዳዊትስ ደህና ነው ?
ዛሬም ይዘምራል ..መሰንቆበገና?                                                                                                                                            
ሃሌ፤ ሃሌ ሉያ የሰማይ ምስጋና፤                                                                                                         
ጎልያድስ የት ነው? በዚያ በቁመና።
እኛማ እኛማ
እልፍ አላፍ ጎልያድ ከቦን ሲደነፋ
ወንጭፉን ጠቅልሎ ምነው ዳዊት ጠፋ?
ብሎሃል በልልን
 ጌታ ሆይ ከሰማህ                                                                                                                                         
ከዘመን ጎልያድ ታደገን እባክህ                                                                                           
ሙተናል፤ ቆስለናል፤                                                                                                                            
ወንጭፍ እምነታችን ተጠቅልሎ ወድቋል።
ለረከሰ ጠጠር ለሞላ ወርዋሪ
‹‹ወንጭፍህን ስጠው ለዚህ ታሪክ አውሪ››

እንዴት ነህ ጌታ ሆይ ... ሰማይ ቤት እንዴት ነው ?
የሙሴ አልጋ  ወራሽ  ኢያሱ ሰላም ነው ....?
ያቆማትን ፀሐይ ግቢ ቢላት ምነው ...?
ያው እንደምታውቀው
ዐሥራ ሦስት ወር ፀሐይ                                                                                                                     
ወርኀ ክረምት ሸሸ፤ እየበዛ ሀጋይ                                                                                                            
ራሳችን ፈረሰ፤ምድሪቱ ደረቀች፤                                                                                                               
ወንዙ መነመነ፤ ባዶ እርቃን ቀረች።                                                                                                         
እባክህን ጌታ ሆይ ወይ ቶሎ ናልን፤                                                                                                   
ምትቆይ ከሆነም ኤልያስ ይምጣልን                                                                                                             
በጻድቅ ጸሎቱ ዝናም ያውርድልን፤                                                                                                           
በጎ ሰው ከጠፋ ዘመናት አለፈን።

ወራቱ በሙሉ ፀሐይ እያዘለ
የተሾመው ሁሉ ‹ፀሐይ ነኝ› እያለ
የሰው ጀምበር በዝቶ
ባቃጠላት ምድጃ አገር
ምን ታምር ይኖራል .... በዚህኛው ዘመን፤                                                                                                            
ታሪክ አውሪ ትውልድ፤ ኤልያስ የለውም፤                                                                                                              
ሹመቱ ምድራዊ፤መንፈሱም ሥጋውም።

ኧረ ጌታ ናልን  በናትህ ....በውድህ
በጭንቅ አላማጇ፤ ለአቅሌሲያ ብለህ
ወይ ዝናብ ላክልን ወይ ዝናብ ሁነህ ና
ማጣፊያው አጠረን፤ ሙቀት ገደለና !

ሔዋንስ ደህና ናት ?
ያው የልጅ ልጆቿ
በእግሯ ተተክተን፤
የፍሬው ሲገርምህ
ግንዱንም አንክተን፤
ፍጥረተአዳም                                                                                                                                                               
ገምጠነዋል ሥሩን።
                                                                                                                                             
የባሰ ሳይመጣ ቶሎ ድረስልን፤                                                                                                                        
አንድም ሰው አታገኝ የቆየህ እንደሆን                                                                                                        
ማራናታ እያልን ይኼው እንጮሃለን
አውራ እንደሌለው መንጋ ተበትነን
ቀበሮ ጨረሰን፤ ፈጀን፤ አቃጠለን                                                                                                                  
ኤሎሄ ኢየሱስ ቶሎ ድረስልን።

(ከጌታቸው ይመር ግጥሞች ለንባብ እንዲመች ተደርጎ በመካነ ጦማሩ የተስተካከለ)

Wednesday, July 22, 2015

" እርስ በርስዋ የምትለያይ መንግሥት ሁላ ትጠፋለች"

ፕሮቴስታንት፣ ካቶሊክ፣ ኦርቶዶክስ ብንባልም የእምነታችን ጀማሪና ፈፃሚ ግን ያው አንዱ ክርስቶስ ነው። በዚህ ዘመን ይቅርና በሐዋሪያት ዘመን እንኳ ክርስቲያኖች እርስ በእርስ በመከፋፈልና በመገፋፋት ያስቸግሩ ነበር። ጴጥሮስ (ኬፋ) ያስተማራቸው፣ ጳውሎስ ያስተማራቸው እንዲሁም ሌሎች ያስተማሩዋቸው ክርስቲያኖች ለየብቻቸው መደራጀታቸውና መራራቃቸው ሐዋሪያው ጳውሎስን አስመርሮት እንዲህ ብሎ ፅፎላቸው ነበር፦ 1ኛ ቆሮንቶስ 1፥ 10 "ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ። ወንድሞቼ ሆይ፥ በመካከላችሁ ክርክር እንዳለ ስለ እናንተ የቀሎዔ ቤተ ሰዎች አስታውቀውኛልና። ይህንም እላለሁ። እያንዳንዳችሁ። እኔ የጳውሎስ ነኝ፥ እኔስ የአጵሎስ ነኝ፥ እኔ ግን የኬፋ ነኝ፥ እኔስ የክርስቶስ ነኝ ትላላችሁ። ክርስቶስ ተከፍሎአልን? ጳውሎስስ ስለ እናንተ ተሰቀለን? ወይስ በጳውሎስ ስም ተጠመቃችሁን?"

በእኛ ዘመንም ቢሆን ክርስቶስ አልተከፈለም። በመካከላችንም ወይ በፕሮቴስታንት ወይ በኦርቶዶክስ ወይ በካቶሊክ ስም የተጠመቀ የለም። የተሰቀለውም አንድ ሲሆን፣ በታዘዝነው መሰረት በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ሁላችን ተጠምቀናል። ክርስትና አንድ ሲሆን አብያተክርስቲያናት ግን እንዳመለካከታችን መጠን ብዙ ናቸው። ልዩነት ችግር የሚሆነው እኛ ስናደርገው ነው፣ ካወቅንበት ግን ዉበት ነው።

============================
አለም ላይ እንዳለው ብዛት እና ተፅዕኖ የመፍጠር አቅም የትና የት መድረስ ይችል የነበረው የተከበረው ሐይማኖታችን፣ በኋላቀር አስተሳሰባችንና እኔ ብቻ ልደመጥ ባይነታችን እርስ በእርሱ ተጠላልፎ ወደ ፊት ዳዴ እንኳን ማለት ተስኖታል። ለዚህ ሁሉ ተጠያቂ እኛው ነን። ጥፋታችንን ሳንቀበል መፍትሄ ማምጣት አይቻልም። ወላጆች እንደሌላቸው ልጆች በየቦታው ተበታትነናል። ለአንድ ዓላማ ልንቆምለት የምንችለው ትልቅ ሐይማኖት እና እውነት ይዘን፣ ነገር ግን እንደ ህፃናት በተገኘችው ጥቃቅን ቀዳዳ ሁሉ መበጣበጥ በጣም አሳዛኝ ነገር ነው። ተልኮአችንን ረስተነዋል። ውጪ ያሉትን ለክርስትና መማረክ ሲገባን የራሳችንን ወንድም በመታገል ጉልበታችንን እዛው ቤት ውስጥ እያፈሰስነው ነው። የራሳችንን ቤት እኛው እያፈረስነው ነው። ወደ ፍቅር እንመለስ!!

==========================
ማቴዎስ 12፥ 25 " እርስ በርስዋ የምትለያይ መንግሥት ሁላ ትጠፋለች፥ እርስ በርሱ የሚለያይ ከተማም ሁሉ ወይም ቤት አይቆምም።"

===========================
መዝሙረ ዳዊት 133 ፥ 1 "ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ፥ እነሆ፥ መልካም ነው፥ እነሆም፥ ያማረ ነው።"

===========================
ዮሐንስ 17፥ 20-23 "ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ፥ ከቃላቸው የተነሣ በእኔ ስለሚያምኑ ደግሞ እንጂ ስለ እነዚህ ብቻ አልለምንም፤ አንተ እንደ ላክኸኝ ዓለም ያምን ዘንድ፥ አንተ፥ አባት ሆይ፥ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ፥ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ እለምናለሁ። እኛም አንድ እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ፤ እኔም በእነርሱ አንተም በእኔ ስትሆን፥ በአንድ ፍጹማን እንዲሆኑ፥ የሰጠኸኝን ክብር እኔ ሰጥቻቸዋለሁ፤ እንዲሁም ዓለም አንተ እንደ ላክኸኝ በወደድኸኝም መጠን እነርሱን እንደ ወደድሃቸው ያውቃል።"

===========================
ስለ ክርስቲያኖች አንድነት ብዙ የተባለ ቢኖርም ለዛሬ እነዚህን አይተናል። ስህተትን ማረም ከሁሉም ይጠበቃል። በየአብያተክርስቲያናቱ ያሉ መሪዎችም ራሳቸውን መፈተሽ እና ከሚከፋፍል እና ከጥላቻ የራቀ ትምህርት ማስተማር ይኖርባቸዋል። እንዲያ ካልሆነ ግን እግዚአብሔርን ማገልገልም ሆነ መከተል ከንቱ ነው። የፍቅርና የአንድነት አምላክ እንጂ የጥላቻ እና የመከፋፈል አይደለምና። ወንድሙን ጠልቶ እግዚአብሔርን እወዳለሁ የሚል እራሱን ያታልላል።

እያልኩ ያለሁት ያሉንን አብያተክርስቲያናት አፍርሰን አንድ ቤተክርስቲያን እናቋቁም ሳይሆን፣ በያለንበት ህብረት ማድረግ ይቻላል። ከልዩነቶቻችን በላይ አንድነታችንን እናጉላው የሚል ነው።

እንግዲህ በመካከላችን ያለውን አላስፈላጊ ርቀት እናጥብብ፣ ህብረት እናድርግ፣ እንፈላለግ፣ ይቅር እንባባል። አንድነት ውስጥ ያሉ የአመለካከት ልዩነቶች ውበት ናቸው እንጂ በራሳቸው ችግር አይደሉም። መንገዳችንንም እናስተካክል፣ እግዚአብሔርንም በአንድነት እንፈልግ።

===========================
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ 7፥ 14 "በስሜ የተጠሩት ሕዝቤ ሰውነታቸውን አዋርደው ቢጸልዩ፥ ፊቴንም ቢፈልጉ፥ ከክፉ መንገዳቸውም ቢመለሱ፥ በሰማይ ሆኜ እሰማለሁ፥ ኃጢአታቸውንም ይቅር እላለሁ፥ ምድራቸውንም እፈውሳለሁ።"
===========================

በዚህ መልእክት የምትስማሙ መልእክቱን ለሌሎች ወንድሞችና እህቶች ሃሳቡን ለሌሎች አካፍሉ። እንዲህ ባለው ሀሳብ ደስተኛ የማይሆኑ አንዳንድ ግለሰቦች በየአብያተክርስቲያናቱ ቢኖሩ ለጊዜው ነው ተዋቸው፣ እግዚአብሔርን በሚገባ እስኪያውቁት ነው።


Lewi Ephrem's

Thursday, July 9, 2015

የኦሮሞ ኢስላሚስቶች ለአረፋ በዓል ሄደው በሳዑዲ ያደረጉትን ይመልከቱ!

  
    በኦሮሚያ ክልል የተነሱ የአብዱል ወሀብ ጥራዝ ነጠቅ  ተከታይ ወሀቢስቶች በጅማ፤ በኢሉባቦር፤ በአርሲና በባሌ የተለያዩ ቦታዎች በኦፊሴል የተነገረና ያልተነገረ የሽብር እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ቆይተዋል። በአማራ ክልል ደግሞ የወሎ አክራሪ ወሀቢስቶች ቤተ ክርስቲያን ከማቃጠል አንስቶ ሰው እስከመግደል መድረሳቸውን በማስረጃ የተረጋገጠ እውነት ነው። በስልጤና ወራቤ የከተሙ አሸባሪ ፋናቲኮች ተመሳሳይ ድርጊት ላይ ተሰማርተው መገኘታቸውም ፀሐይ የሞቀው፤ ሀገር ያወቀው ጉዳይ ነው። እነዚህ ሱሪያቸውን የሚያሳጥሩ፤ ካልሲያቸውን የሚያሳዩ፤ የአፍንጫቸውን ስር ጸጉር ሙልጭ አድርገው በመላጨት ጢማቸውን የሚያሳድጉ፤ ግንባራቸው ላይ የተነቀሱ እስኪመስል ድረስ ከመሬት ሲጋጩ የጠቆረ ሰውነት ከማንነት ጋር የተሸከሙ አክራሪዎች የሌላውን መብት እስካልነኩ ድረስ ተቃውሞ የማይቀርብበት ቢሆንም የድርጊታቸው ዋነኛ ምስክር ግን ለማሸበር ልዩ ምልክታቸው ሆኖ መገኘቱ ነው። ወሀቢስቶች ከሱኒና ከሱና ውጪ ያለው ሁሉ ካፊርና ከሀዲ ነው።          ለዚህም ዓላማ ግብ መንታት መታገል፤ መዋጋትና መግደል ብሎም መሞት ጂሀድ ነው። በዚህ ዓላማ ላይ መሞት በጀና/ ገነት/ ልዩ ዓለም የሚያስገኝ ሲሆን 72 ደናግላን ሴቶች ድንግላቸውን በጂሀድ ለሞተው አሸባሪ ለማስረከብ በጥቋቁር ቀሚስ ተሸፋፍነው እንደሚጠብቋቸው ያምናሉ።
ከዚህ በታች የሚታየው ቪዲዮ በሳዑዲ የአረፋ በዓል ለማክበር የሄዱ አክራሪዎች የወቅቱ የኢትዮጵያ ባንዲራ የሆነውን ዓርማ ከተሰቀለበት አውርደው የኦነግን ባንዲራ ሲሰቅሉ ያሳያል። «ሱባንአላህ» የሚለው የኦሮሞ ኢስላሚስት አክራሪ የአማራ ባንዲራ ወርዶ የኦሮሞ መንግሥት በቅርቡ በኦሮሚያ ይቋቋማል ይላል። በዚህ ዓይነት ኦነግ አሸባሪ አይደለምን?
እንግዲህ እነዚህ የመሳሰሉ አሸባሪዎች ናቸው፤ ኢትዮጵያ ተመልሰው ሕዝብን ከሕዝብ፤ ሃይማኖትን ከሃይማኖት ሲያጋጩ የሚስተዋለው።
ደግመን ደጋግመን የምንለው እውነታ ቢኖር ኢትዮጵያ ውስጥ ምቹ ሁኔታ ጠፍቶ እንጂ ለቁጥር የሚያታክቱ አሸባሪዎች አሉ። «አስቀድሞ ነበር፤ መጥኖ መደቆስ፤
አሁን ምን ያደርጋል፤ድስት ጥዶ ማልቀስ»
እንዳይሆን ሰላምን፤ ፍቅርን፤አንድነት፤ ኅብረትንና በጋራ አብሮ መኖርን በሚፈልጉ የእስልምና እምነት ተከታዮች በኩል አካባቢንና ውስጥን የማጥራት ሥራ ከታችኛው እርከን አንስቶ እንዲደረግ ከዚህ በፊት ስንለው እንደቆየነው ሁሉ አሁንም ደግመን ለማስታወስ እንወዳለን።


Tuesday, June 30, 2015

ክርስትናን አጋድመው ያረዱት..."


(ያሬድ ሹመቴ)

ከዚህ በታች የማስነብባችሁን ጽሁፍ ከዚህ ቀደም በጨርቆስ ተገኝቼ የሰማውትን በዚሁ መገናኛ መድረካችን ላይ አስነብቤያችሁ ነበር።
ከሰሞኑን በአሜሪካን ሀገር በግብረ ሰዶም ተግባር ላይ እጅግ አስነዋሪ የጋብቻ ህግ መጽደቁን ተከትሎ ልንነጋገርበትና መንፈሳዊ ምግብ እንሰንቅበት ዘንድ የመጋቢ ሀዲስ እሸቱን ስብከት ከመድረኩ የሰማውትን ለንባብ እንዲመች አድርጌ በማቀናበር በድጋሚ እነሆ ብያለው።
"ሰው ብቻ አትሁኑ" መ.ሀ.እሽቱ
"...ሰው ብቻ ማለት ምንድን ማለት ነው? ብዬ ሳስብ፤ የሚበላ፣ የሚጠጣ፣ በሚለብሰው ልብስ፣ በሚነዳው መኪና የኑሮን ስኬት የሚለካ ማለት ነው። እስከ ሞት የሚኖር ማለት ነው፦ እንደ እንስሳ።
"...ታላቁ ሊቅ ዮሀንስ አፈወርቅ እንዲህ ይላል 'ሰው እግዚአብሄር ሲለየው' ይላል። ሰው እግዚአብሄ ሲለየው፤ ጠባዩ እንደ አራዊት፤ አመጋገቡ እንደ እንስሳ፣ ሆኖ መልኩ ብቻ የእግዚአብሄር ሆኖ ይቀራል። በጣም ቀለል ባለ አገላለጽ ሲም ካርዱ የወጣ ሞባይል ማለት ነው። ጥሪ የማይቀበል። ለጉትቻ ማንጠልጠያ ብቻ የተሰራም ጆሮ አለ።"
"...እኔ በዕውነቱ ከተማው ፈርሶ እየተሰራ ነው እየተባለ አይናማዎቹ ሲያወሩም ሲያስወሩም እሰማለው። ፈርሶ መሰራት ያለበት የሰዉ አስተሳሰብ ነው።... የሰዉ አስተሳሰብ ፈርሶ ካልተሰራ፤ የተሰራ ከተማ ይፈርሳል። ጃፓንና ቻይና ሀገራቸውን ያለሙት መጀመሪያ አስተሳሰባቸውን አልምተው ነው። አስተሳሰቡ ያልለማ ህዝብ የለማውን ያወድማል።"
"...ምንድነው አሁን ያሳየሁዋቹ? (ትንሽ ጣታቸውን አውጥተው ወደላይ እያሳዮ) ይህች ጣት ብትታምም ሀኪም ቤት ብቻዋን ነው የምትሄው?... የማይመለከታቸው እነ ጉበት፣ እናፍንጫ፣ እነ እግር፣ አብረው ነው የሚሄዱት።"
"...ከረባት የሚታሰረው የት ላይ ነው?... አንገት ላይ የታሰረ ከረባት አካሄድን ይቀይራል። አሁን እግር ምን አገባው እውነት ለመናገር? (ከፍተኛ ሳቅ) ውድ መነጽር አይናቸው ላይ ያደረጉ ሰዋች አካሄዳቸውን ሁሉ ነው የሚቀየረው። አይን መነጽር ያደረገው መላ የሰውነት አካላትን ተክቶ ነው። ለዚህ ነው ታላቁ ሊቅ ዮሀንስ አፈወርቅ "እኛ የሰውነት ክፍሎች ነን ክርስቶስ ግን ራስ ነው" ያለው። ሰው እጁ ተቆርጦ ይኖራል፤ አይኑ ጠፍቶ ትኖራል። እራሱ ተቆርጦ ግን አይኖርም። እራስ ክርስቶስ ነው። እኛ ብንሞት (የሰማይ ህይወት) ይቀጥላል። የክርስትናው እራስ ክርስቶስ ስለሆነ።"
"ቤታችሁ ገብታችሁ እንድታጤኑት ነው። እነዛ... (ምንትስ) የምንላቸው ክርስቲያኖችን አርደዋል... ምዕራባውያኑ ደግሞ ክርስትናን እራሱን አርደውታል።....ወንድ ለወንድ፣ ሴት ለሴት፣ በቤተክርስቲያናቸው እያጋቡ፤ ክርስትናን አጋድመው ያረዱ ምዕራባውያን ናቸው። (ይህን ሁሉ ያመጣውም) የምዕራባውያን ልክ ያጣ ነጻነትና ገደብ ያለፈ ዝርክርክነት ነው።"
"እንደምታዩት እኔ አይነ ስውር ነኝ። ቀላል አይደለም.... እንክዋን ዘውትር ዓይን አጥቶ አንድ ቀን መብራት ሲሄድ ስንት እንደምታማሩ ታውቅታላችሁ። አንድ ቀን ግን አልቅሼ አላውቅም። ከሞት ወዲያ መብራት አለ። ከመቃብር በላይ መብራት አለ። ... ወደ መቃብር ሲወርድ ማንም ዓይነ ስውር ነው። ማንም አይኑ እያየ የተቀበረ የለም። ተስፋችን ግን ምንድን ነው? ከሞት ወዲያ ህይወት አለ። ከሞት ወዲያ ብርሀን አለ።"
"...አንድ አንድ ጊዜ እመኛለሁ። እማይረባ እማይረባ ነገር ስናይ (ዓይናችንን) የሚያጠፋ ቆጣሪ ቢኖር... መልካም ነገር እስክናይ ድረስ ለጊዜው የሚያጠፋ ቆጣሪ ቢኖር።
"አሁን እንደው ጆሮ በካርድ የሚሰራ ቢሆን ሀሜት እንሰማ ነበር?(ከፍተኛ ሳቅ)... የምንፈልገውን (ብቻ) አውርተን ስዊች ኦፍ እናደርገው ነበር። ስንት ዞማ ጸጉር ይዞ አስተሳሰቡ የከረደደ አለ።
"ጀርመን ሀገር ሄጄ ሲነግሩኝ፤ ባለ አምስት ኮከብ የውሻ ሆቴል አለ ተባለ። እኛ ሀገር አምስት ኮከብ ሆቴል ገብተው የበሉ ትንሽ ዝና (ሀብት) እና ትንሽ ስልጣን ያላቸው ናቸው። ማን ይገባል ከነሱ ውጪ። ግን ሰዋች ነን። የጀርመን ውሻ ዛሬም ውሻ ነው ለዘላለምም ውሻ ነው። እኛ ግን ሰው ነን።
እንደ ሰው አስቡ (ምዕመናን) በማርያም።"
" እስኪ እንደው ትዳራችሁን ገምግሙት ደስተኛ ናችሁ? እንደሰው እየኖራችሁ ነው? ሚስቶቻችሁን ታከብራላችሁ? ፖለቲከኞቹ የኪነጥበብ ሰዎቹ (እዚህ) አላቹ ሲባል ሰምቻለሁ። ቆም ብላችሁ ልታስቡ ይገባል።"
" እኛም የሀይማኖት ሰዎች ሰበክን ሰበክን፤ ስብከቱ የህዝቡን አመለካከት መቀየር ትቶ የኛን ኑሮ ቀየረ።(ከፍተኛ ሳቅ)... የሰበክነው ክርስቶስ ሳይታወቅ እኛ እንታወቃለን። ማስታወቂያ ሰርተው ዝነኛ የሆኑ ሰዎች አሉ። ምርቱ ተሽጠ? ወይስ አልተሸጠም?" (ከፍተኛ ሳቅ)
" ተርቦ ያበላን፣ በክራይ ቤት እየኖረ እኛን በቪላ ቤት ያኖረን፣ እሱ በግሩ እየሄደ ለኛ መኪና የገዛልንን፤ ዝነኛ ያደረገንን ህዝብ እኛ አመለካከቱን ልንቀይረው ይገባል። አለባበስን መቀየር ቀላል ነው አስተሳሰብን መቀየር ግን ዋጋ ያጠይቃል።"
"የግሪክ ፈላስፎች እነ ሶቅራጥስ የህዝቡን አመለካከር ለመቀየር ደከሙ። ዛሬ በኢኮኖሚ ውድቀት የምትንገላታ ግሪክ ናት፦ የነ ሶቅራጥስ ሀገር። 'ሀገር ሲያረጅ ጃርት ያፈራል' ይባላል። እኛ እንክዋን ይክበር ይመስገን ኢትዮጵያውያን ነን።"
"አሁንም ደግሜ እናገራለው። ይሄን ችግር ያደረሱብን ኢትዮጵያውያን አይደሉም። (እዚህ ያሉት) ጎረቤቶቻችንን እነ መሀመድ እነ ከድጃ... ስጋዎቻችን፣ ደሞቻችን፣ አካሎቻችን ናቸው።"
"ልብ ካለ ሊቢያ ሄዶ እናዛን መፋለም ነው። '... ቢያሸንፈው ወደ ሚስቱ ሮጠ' ይባላል። አንድ አንድ አባ ወራ አለ ቡና ቤት ሄዶ ከዚያ መልስ ቅዳ (ሂሳብ በኔ ነው) ይላል። (ሚስቱ) የወር ወጪ ስትጠይቀው፤ ጥጦ እንደተነጠቀ ህጻን የሚያለቅስ።"
"...ወቀሳ አበዛሁ?(የተሰበሰበው ህዝብ ከሳቅ ጋር አላበዙም አለ) ማርያምን?... ኮሶ የሚጠጣው ስለሚጣፍጥ አይደለም ስለሚያሽር(ስለሚያድን) ነው። ለመጣፈጥማ ስኩዋር ይሻል ነበር ግን ወስፋት ነው ትርፉ።" (ሳቅ)
"...የንጉሰ ነገስቱ የክርስቶስ አልጋ ወራሾች ነን... የደስታችሁ ልኬት የደስታችሁ ሚዛን ምግብና መጠጥ አይሁን፤ መኪናና ቤት ዝናንም አታርጉ። እኛ መለኪያችን ጽድቅ ነው። መከኪያችን መንግስተ ሰማያት ነው። ያ የምንገባበት ቤት ደግም የተዋበ፣ የደመቀ፣ መብራት ውሀ የማይሄድበት፤ 24 ሰኣት ክርስቶስ የሚያበራበት፤ 24 ሰኣት የህይወት ውሀ የሚጠጣበት፤ ሀብታም፤ ደሀ፣ተራሰው የማይባልበት፣ እገሌ ግባ እገሌ ውጣ የማይባልበት ቦታ ነው። ደህና እደሩ"
መጋቤ አዲስ እሸቱን ቃለ ህይወት ያሰማልን...
አሜን!

Sunday, June 28, 2015

" ጥበበኞች ነን ሲሉ ደንቆሮ ሆኑ፥" (ሮሜ 1:22)

my finger to you? (blogger)


                                ፍቅር ፍቅር ነው” ኦባማ

" እንዲሁም ወንዶች ደግሞ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፤ ወንዶችም በወንዶች ነውር አድርገው በስሕተታቸው የሚገባውን ብድራት በራሳቸው ተቀበሉ።" " እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱት መጠን እግዚአብሔር የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው"
ሮሜ1፣27-28

ወንድ ከወንድ፤ ሴትም ከሴት ጋር ጋብቻ መፈጸም ይችላሉ፤ ለእነርሱ የጋብቻ ሠርቲፊኬት መከልከል ሕገመንግሥቱን ይጥሳል በማለት የአሜሪካው ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተመሳሳይ ጾታ ያላቸው መጋባት እንደሚችሉ ወሰነ፡፡ ለጋብቻ ቅድስናና ክቡርነት የሚከራከሩ “የእግዚአብሔርን ሕግ ምድራዊ ፍርድ ቤት ይህን መለወጥ አይችልም” በማለት ውሳኔውን አጥብቀው ተቃውመዋል፡፡ በምንም መልኩ ይገለጽ ፍቅር ፍቅር ነው በማለት ፕሬዚዳንት ኦባማ ውሳኔውን ደግፈዋል፡፡

 ዋናውን (ዓቃቤ ፍትህ) ጨምሮ ዘጠኝ የፍትህ ዳኞች የያዘው የአሜሪካው ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዚህ የሰዶማውያን ጋብቻ ላይ ውሳኔ እንዲያስተላልፍ ጉዳዩ ከቀረበለት ጊዜያት ተቆጥረዋል፡፡ በአሜሪካ የፍትሕ ሥርዓት ምዕራፍ ከፋች የተባለለት ውሳኔ አርብ ዕለት ሲተላለፍ የፍትሕ ዳኞቹ በአምስት ለአራት በመወሰን ነው ያጸደቁት፡፡ ይህ ጠባብ ልዩነት የታየበት ውሳኔ ሲተላለፍ አምስቱን ደጋፊዎች ወክለው አስተያየታቸውን የጻፉት የፍትሕ ዳኛ አንቶኒ ኬኔዲ ናቸው፡፡ እርሳቸውም ሲጽፉ “ከጋብቻ አንድነት የሚበልጥ የለም፤ ምክንያቱምታላቅ የሆነ ፍቅር፣ ታማኝነት፣ መስዋዕትነትና ቤተሰብን ያካተተ በመሆኑ ነው፡፡ ሁለት ከመሆን ይልቅ አንድ በመሆን የሚገኘው ኅብረት ይበልጣል በማለት ሰዎች የጋብቻ ኅብረት ይፈጥራሉ” ብለዋል፡፡ ሲቀጥሉም “ይህንን ጉዳይ በተመለከተ አቤቱታቸውን ያቀረቡት እንዳሳዩት ጋብቻ ማለት ሞትን አልፎ የሚሄድ ፍቅር መሆኑን ነው፤ … እነዚህ ሰዎች የጋብቻን ክቡርነት ያቃልላሉ ማለት እነርሱን አለመረዳት ነው፤ እንዲያውን እነርሱ ጋብቻን እንደሚያከብሩ ነው በመማጸን የሚናገሩት፤ ጋብቻን በጣም ስለሚያከብሩ ነው ተፈጻሚነቱን በእነርሱ ህይወት ማየት የሚፈልጉት፤ ጥንታዊ ከሆኑ ተቋማት አንዱ ከሆነው ጋብቻ ተገልለውና በብቸኝነት ተኮንነው ላለመኖር ነው ተስፋቸው” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

 ውሳኔውን ከተቃወሙት የአራቱን በመወከል አስተያየት የጻፉት ዓቃቤ የፍትሕ ዳኛው ዮሐንስ ሮበርትስ ናቸው፡፡ እርሳቸው ውሳኔው በርካታዎች ሊያስደስት ይችላል ካሉ በኋላ ሲጽፉ “አብላጫውን ድምጽ የሰጡት ውሳኔ በጥልቅ ልብን የሚነካና ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው፤ ጋብቻ በአንድ ወንድ እና በአንዲት ሴት መካከል የሚፈጸም ኅብረት ነው የሚለው ዓለምአቀፋዊ ትርጉም በምንም ዓይነት መልኩ ታሪካዊ አጋጣሚ አይደለም፤ ጋብቻ በፖለቲካ ትግል፣ በግኝት መልክ፣ በበሽታ፣ በጦርነት፣ በሃይማኖታዊ ሥርዓተ ሕግ ወይም አንዳች የዓለምን ታሪክ ባናወጠ ኃይል የተከሰተ አይደለም፤ እንዲሁም ወንድና ወንድ ወይም ሴትና ሴት ተጋቢዎችን ለማግለል ተብሎ የተደረገ የቅድመታሪካዊ ውሳኔ ውጤትም አይደለም” ብለዋል፡፡ ሲቀጥሉም “ጋብቻ የተከሰተው ወሳኝ የሆነን ፍላጎት ለማሟላት ነው፤ ይህም ደግሞ ከእናትና አባት ልጆችን በመውለድ እነርሱን በተረጋጋ ሁኔታ ለማሳደግ ራስን አሣልፎ በመስጠት የህይወት ሙሉ ውሳኔ በማድረግ ነው” ብለዋል፡፡

የውሳኔው እንደምታ

የጋብቻን ክቡርነት የሚሰብኩና ጋብቻ በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል መወሰን አለበት የሚሉ ወገኖች በዚህ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ክፉኛ ሃዘን ገብቷቸዋል፤ የወደፊቱም ሁኔታ አስግቷቸዋል፡፡ ውሳኔውን ተከትሎ የሚከሰቱት ነገሮች ማኅበረሰቡን በእጅጉ የሚበጠብጡ እንደሚሆኑም ካሁኑ እየተነገረ ነው፡፡
ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ሲያሳልፍ የጋብቻን ሃይማኖታዊ ገጽታ አልተመለከተም የሚሉ ወገኖች በተለይ መጽሐፍ ቅዱስ ሰዶማውያንን በተመለከተ የሚናገረውን ከሮሜ መጽሐፍ አንደኛው ምዕራፍ ላይ ያለውን ይጠቅሳሉ፡፡ “እግዚአብሔርን እያወቁ እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን ስላላከበሩትና ስላላመሰገኑት የሚያመካኙት አጡ፤ ነገር ግን በአሳባቸው ከንቱ ሆኑ የማያስተውለውም ልባቸው ጨለመ። … ስለዚህ እርስ በርሳቸው ሥጋቸውን ሊያዋርዱ እግዚአብሔር በልባቸው ፍትወት ወደ ርኵስነት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ይህም የእግዚአብሔርን እውነት በውሸት ስለ ለወጡ በፈጣሪም ፈንታ የተፈጠረውን ስላመለኩና ስላገለገሉ ነው፤ … ስለዚህ እግዚአብሔር ለሚያስነውር ምኞት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የሚገባውን ሥራ (ከወንድ ጋር መገናኘት ትተው) ለባሕርያቸው በማይገባው (እርስ በርሳቸው በማድረግ) ለወጡ፤ እንዲሁም ወንዶች ደግሞ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፤ ወንዶችም በወንዶች ነውር አድርገው በስሕተታቸው የሚገባውን ብድራት በራሳቸው ተቀበሉ። እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱት መጠን እግዚአብሔር የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው፤ … ጥበበኞች ነን ሲሉ ደንቆሮ ሆኑ”፡፡

ይህ ብቻ ሳይሆን በዚህ ውሳኔ ምክንያት በርካታ ግለሰቦችና ተቋማትም አደጋ ላይ እንደሚወድቁ እየተነገረ ነው፡፡ ለምሳሌ በጋብቻ ሥርዓት ላይ አገልግሎት የሚሰጡ የሠርግ ኬክ ጋጋሪዎች፣ አበባ አዘጋጆች፣ የሠርግ ዕቅድ አውጪዎች፣ ፎቶግራፍ አንሺዎች፣ ወዘተ በእምነታቸው ምክንያት ለሰዶማውያን ጋብቻ አገልግሎት አንሰጥም በሚሉበት ጊዜ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ቅጣት የሚቀበሉ ይሆናሉ፡፡ በኮሎራዶ ጠቅላይ ግዛት አንድ ኬክ ጋጋሪ እንዲሁም በኒውዮርክ ግዛት የገጠር ቤታቸውን ለሠርገኞች የሚያከራዩ ለሰዶማውያን አገልግሎት አንሰጥም በማለታቸውና ግዛቶቹ የሰዶማውያንን ጋብቻ ያጸደቁ በመሆናቸው ፍርድቤት ቀጥቷቸዋል፡፡ ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ በኋላ ግን በየትኛውም ግዛት ቅጣቱ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ከአምሳዎቹ የአሜሪካ ግዛቶች 14ቱ በሰዶማውያን ጋብቻ ላይ ዕገዳ ያደረጉት ከአርቡ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ በኋላ ዕገዳቸውን ማንሳት አለባቸው፡፡


“ተመሳሳይ ጾታ” ብሎ “ጋብቻ” የሚለው ቃል አብሮ አይሄድም በማለት የሚከራከሩ ወገኖች ጋብቻ የሚለው ቃል የሚውለው ለተቃራኒ ጾታ ብቻ ነው ይላሉ፡፡ ከዚህም ሲያልፍ የተቃራኒ ጾታዎች ግንኙነት ብቻ ነው ልጆችን ማፍራት የሚችለው ይላሉ፡፡ ሰዶማውያን ወይም ተመሳሳይ ጾታ ያላቸው ሲጋቡ የሚያፈሩት ልጅ የለም፡፡ ሴቶቹ ተጋቢዎች የወንድ ዘር ከዘር ባንክ በመግዛትና ውስጣቸው በህክምና በማስጨመር ቢወልዱም ወንድ ተጋቢዎች ግን በጉዲፈቻነት ሌሎች በተቃራኒ ጾታ ግንኙነት የፈጠሩትን ልጅ ወስደው ነው የሚያሳድጉት፡፡ ስለሆነም ሁለቱ ተጋቢዎች በተፈጥሮ ለመውለድ የማይችሉ በመሆናቸው በጥቅሉ ከሚታወቀው ጋብቻ እኩል ተደርጎ መወሰድ የለበትም ይላሉ፡፡ እንዲያውም የሰዶማውያን ጋብቻ የሰው ዘር እንደ ብርቅዬ እንስሳ እንዲጠፋ ድጋፍ የሚሰጥ ነው እስከማለት አጥብቀው ይከራከራሉ፡፡

ይህንን ውሳኔ ተከትሎ ካሁን በኋላ ሰዶማውያን የፈለጉትን ልጅ በጉዲፈቻነት ለማሳደግ ልክ እንደ አንድ ባልና ሚስት ፈቃድ ማግኘት ይችላሉ፡፡ ይህ ፈቃድ በሰዶማውያን “ወላጆች” አድጎ በነርሱ መስመር የሚቀጥል ልጅ ለማሳደግና ሰዶማዊነት እንደ መደበኛ ተግባር እንዲቆጠር ለማድረግ በር ከፋች ይሆናል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ከሃይማኖታቸው አንጻር የሰዶማዊነትን ትክክለኛ አለመሆን የሚሰብኩ ካህናት በሰብዓዊ መብት ረገጣ እስር ቤት የሚጣሉበት ቀን ሩቅ አይሆንም፡፡ በየአምልኮ ቦታው የሚሄዱ ሰዶማውያን ልጆችን ከማስተማር ጀምሮ በአምልኮ ቤቶቹ አገልግሎት እንዳይሳተፉ መከልከል አይቻልም፡፡ በመሆኑም መጪው ትውልድ ከሥነምግባር አኳያ በትምህርት ቤት ብቻ ሳይሆን በአምልኮ ሥፍራዎችም የሰዶማውያን ጋብቻ ትክክል ነው በማለት እያመነ እንዲያድግ ይቀረጻል፡፡

የፍርድ ቤቱ ውሳኔ እንደተሰማ ተቃውሟቸውን ያሰሙት የሉዊዚያናው አገረ ገዥ ቦቢ ጂንዳል ሲሆኑ እርሳቸውም ዘለግ ያለ መግለጫ አውጥተዋል፡፡ ለመጪው የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የሚወዳደሩት ጂንዳል “ውሳኔው ሰዶማዊነትን በመቃወም ሰዎች የሃይማኖት ነጻነታቸውን በገሃድ እንዳይለማመዱ ጥቃት የሚሰነዝር ነው” ብለውታል፡፡ ሲቀጥሉም “ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ያስተላለፈው የሕዝብ አስተያየትን በመከተል መሆኑ የሚያስደንቅ አይደለም፤ ሆኖም ውሳኔው ጠቅላይ ግዛቶች በሚያስተዳድሯቸው ግዛቶች ላይ የሚፈልጉት ሕግ እንዳያወጡ ወይም እንዳይቃወሙ መብታቸውን የሚረግጥ ነው፤ በመሠረቱ በአንድ ሰውና በአንዲት ሴት መካከል ጋብቻ እንዲሆን የመሠረተው እግዚአብሔር ነው፤ ማንኛውም ምድራዊ ፍርድ ቤት ይህን መለወጥ አይችልም” ብለዋል፡፡


የጠቅላይ ፍርድቤቱ ውሳኔ እንደተሰማ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በሰጡት መግለጫ ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡ “ፍቅር ፍቅር ነው” በማለት የተናገሩት ኦባማ የግብረሰዶማውያን ጋብቻ ሕጋዊ እንዲሆን በተለይ በሁለተኛው የአስተዳደር ዘመናቸው ጥረዋል፡፡ ውሳኔው “ለአሜሪካ ድል ነው” በማለት በወጣትነት ዘመናቸው ሰዶማዊ ነበሩ ተብለው በአንዳንዶች የሚታሙት ኦባማ በካሜራ ፊት አውድሰውታል፡፡


ኦባማ የሰዶማውያን መብት በአገራቸው ብቻ ሳይሆን በአፍሪካም እንዲከበር አበርትተው ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ባለፈው ምዕራብ አፍሪካን በጎበኙበት ወቅት ይህንኑ ጉዳይ አንስተው ያደረጉት ንግግር በአፍሪካውያን ዘንድ ተደማጭነት ያጣ ብቻ ሳይሆን የከረረ ተቃውሞም ገጥሞት ነበር፡፡ ሆኖም ግን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የአሜሪካ ሸሪክ በመሆን የአሜሪካንን ጥቅም ጎረቤት አገርን በመውረርም ሆነ ወታደራዊ ቤዝ በመስጠት የሚያስከብሩ የአፍሪካ አገራት በዚህ የሰዶማውያን መብት ጥበቃ ወጥመድ ውስጥ ይወድቃሉ የሚለው አስተያየት ሲሰማ ይደመጣል፡፡ አሜሪካ የበጀት ድጎማ የምታደርገውም ሆነ አምባገነኖችን በጭፍን የምትደግፈው በምላሹ የምታገኘውን በማሰብ እንደሆነ የሚናገሩ ወገኖች አሜሪካ ገንዘቧ ሰጥታ ይፈጸምልኝ የምትለውን ሳታገኝ የምትቀርበት ምንም ምክንያት አይኖርም ይላሉ፡፡
ከዚህ አንጻር በኢትዮጵያ ውስጥ እየተስፋፋ በመጣው የወሲብ ልቅነትና የሰዶማውያን ሁኔታ ሳይንሳዊ መረጃ ማቅረብ የሚያዳግትበት ቢሆንም ከውጭ ድጋፍና ተጽዕኖ ጋር የተሳሰረ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው የተሾሙት ፓትሪሽያ ሃስላክ የሹመት ጥያቄያቸውን ለአሜሪካው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት በማቅረብ በውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ፊት ቀርበው ሲመሰክሩ እንዲህ ብለው ነበር፤ “(የአምባሳደርነት ሹመቴ) ከጸደቀ በጾታ ላይ የሚደረግን ጥቃት እንዲሁም በግብረሰዶማዊያን ኅብረተሰብ ላይ የሚፈጸመውን መድልዖ አስመልክቶ እኛ (አሜሪካውያን) የምንከተለው የፖሊሲ አቅጣጫና ጥረት (በኢትዮጵያም እንዲሆን) የሚቻለኝን ሁሉ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኔን እገልጻለሁ”፡፡


በሐምሌ ወር ማገባደጃ አካባቢ ባራክ ኦባማ ኢትዮጵያን እንደሚጎበኙ ባለፈው ሰሞን መነገሩ ይታወሳል፡፡


(Golgul web news)

Monday, May 25, 2015

የጴንጤዎቹ እንደዶክሌ ቀልደኛው ዳዊት ሞላልኝ የሰው ሕጋዊ ሚስት ቀማ!!

ጌታ ለእኔ የማይፈርደው እስከ መቼ ነው? የእግዚያብሔር ቤተሰቦች የእውነት ቃል በእናንተ ካለ እስቲ ፍረዱ !
ፓስተር ዳዊት ሞላልኝ የተባለ ግለሰብ ህጋዊ የትዳር አጋሬን ባለቤቴን በቁሜ ነጠቀኝ::
አቶ ግርማ ዱሜሶ








ይህንን ጽሁፍ እራሳቸው አዘጋጅተው ከእነ ፎቶግራፋቸው የላኩት ግለሰብ ነዋሪነታቸው በሰሜን አሜርካ በአትላንታ ጆርጂያ ግዛት የሚኖሩት አቶ ግርማ ዱሜሶ የተባሉ ግለሰብ ህጋዊ ባለቤቴን ወ/ሮ ትግስት አበበ ደምሴን ፓስተር ዳዊት ሞላልኝ የተባለ ግለሰብ አስነውሮብኝ ትዳሬን አፍርሶታል:: እኔም እነዚህ ሁለት ግለሰቦች ባደረሱብኝ ከባድ የህይወት ወንጀል በተደጋጋሚ ሁለቱም ግለሰቦች በቤተክርስትያን በኩል እንዲጠየቁልኝ እና ክርስቲያናዊ ይቅር እንድንባባል በተደጋጋሚ አሜርካ ውስጥ ለሚገኙ የኢትዮጵያናውያን ቤተክርስትያኖችን ጠይቄ ከቤተክርስትያኖቹ ምላሽ አጥቼያለሁ ስለሆነም ውድ የእግዚያብሔር ቤተሰቦች የሆናችሁ እውነተኛ ክርስቲያኖች ይህንን እውነተኛ ታሪኬን አንብባችሁ ፍርዳችሁን እንድትሰጡኝ በጌታ ኢየሱስ ስም እማጸናችኋለሁ

ቀን 03/16/2015

ለቄስ ዶ/ር ቶሎሳ ጉዲና

አትላንታ ጆርጂያ (USA )

ጉዳዩ ፡ በኔና በትዳሬ ላይ የደረሰውን በደል ፤ ነውርና ጥቃት ይመለከታል!

በእግዚአብሔር የተወደድክና በጣም የማከብርህ መንፈሳዊ አባቴ ( ፓስተሬ ) ነህና “አንተ “ ብልህ እንደ ድፍረት እንደማትቆጥርብኝ ተስፋ አደርጋለሁ ። ተወልጄ ባደኩበት ማህበረሰብና እንዲሁም በእግዚአብሄር ቃል ውስጥም ቢሆን ሰው ፈጣሪን የሚያህል አምላኩና የሥጋ ወላጅ አባቱን “አንተ “ እንጂ “እርስዎ አምላኬ ሆይ “ ብሎ ስጣራ አልሰማሁም ።

በመሆኑም በሚገባኝ መንገድ ከልቤ በሆነ አክብሮት የጌታ ሰላም ፤ ምህረት ፤ጥበቃና ቸርነት እየተመኘሁልህ ፤ እንዲሁም ረጂም ዕድሜና በረከት ይብዛልህ ለማለት እወዳለሁ።

ፓ/ር ፡

ምንም እንኳን አንተን ማድከምና ማሰልቸት ቢሆንም ከዚህ ቀደም በአካልና በሰልክ ደጋግሜ ያጫወትኩህን (በሰፊው የተነጋገርንብትን ) እና አሁንም ድረስ የተቸገርኩበትን ብርቱ ጉዳዬን ከዚህ እንደምከተለው እንደገና ልገልጽልህ ወደድኩ ። ያም ጉዳይ ቀደም ሲል አንተም የሚታውቀውና በቅርቡም በቢሮህ ተገኝቼ በዝርዝር ገልጬልህ በተነጋገርነው መሰረት ሚስቴ የነበረችው ወ/ሮ ትግስት አበበ ደምሴና ፓ/ር ዳዊት ሞላልኝ አበጋዝ የሚባሉ ግለሰቦች ያደረሱብኝን በደልና ጥቃት የሚመለከት ነው ፡፤

እነዚህ ግለሰቦች እንደ ሌሎቹ ቅዱሳን አማኞች መልካምና ጥሩ ስነ-ምግባር ያላቸው እውነተኛ አገልጋዮች መስለውኝ አመንኳቸውና በቅንነትና በየዋህነት በልበ-ንጽህና ቀረብኳቸው እንጂ ከኋላዬ ዞረው ፈጣሪን በመዳፈር ለብቻቸው የተደበቀ እና ስውር የሆነ የግል ሚስጢርና ግንኙነት ኖሮአቸው ነውርን በትዳሬ ላይ ሊሰሩ ይችላሉ ብዬ ለማሰብ አንዳች ስጋትና ግምት አልነበረኝም ፤ ትዳሬን አፍርሰው ህይዎቴን አደጋ ላይ ይጥሉኛል ፤ ለከፋ ብስጭትና ኪሳራ ይዳርጉኛል ፤ ያዋርዱኛል ብዬ ጨርሶ አላሰብኩም ነበር ።

ይሁን እንጂ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች በመሆናቸው እምነት ጥዬባቸው ሳለ በገርነቴና በቀናነቴ በነዚህ በእግዚአብሔር አገልጋይ ተብዬዎች በደል ደረሰብኝ ፤ ተጎዳሁ ፤ ተጠቃሁ ።በዚህ በተፈጸመብኝ በደል የተነሳ እጅግ በጣም አዝኛለሁ ። በዋናነት የበደለኝም ብልጣ-ብልጡ አፈ-ጮሌ ፤ አስመሳይ መንፈሳዊ ሰው መሳይ ዳዊት ሞላልኝ የተባለ የ “FBI “ ቤተክርስቲያን ፓ/ርና መሪ ግለሰብ ነው ።

ይህ ያለንበት ዘመን በተለያየ ስፍራ በሃይማኖታዊና በመንፈሳዊነት ስም የምመላለሱ መንፈሰዊ ዱሪዬዎች እጅግ የበዙበት ወቅት በመሆኑ በእግዚአብሄርና በአገልግሎት ስም እያመኻኙ ባለቤቱ የከደነውን አለፈቃድ የሚከፍቱ ፤ ያስቀመጠውን አንስተው የሚወስዱ ፤ የሰውን ኑሮ የሚያናጉ ንጹሕ ፍቅር ባላቸው ጥንዶች መካከል እየገቡ በሰላምና ደስታ ፋንታ ጭቅጭቅንና ሃዘንን የሚያደርሱ የፍቅርና የቅድስና ጠላት የሆኑ ጉዶች የፈሉበት ጊዜ ነው ቢባል ያጋነንኩ አይመስለኝም ።

ፓ/ር ዳዊት ከዚህ ቀደም ማንንም ገጥሞት በማያውቅ ሁኔታ በሃይማኖት ተጀቡኖ ፤ በአገልጋይነት ሰበብ ተሸፍኖ፤ በእግዚአብሄር ስም እየነገደ ፤ በንቀት ድፍረት ተሞልቶ የሥጋ ፊላጎቱን ማርኪያና መደሰቻ ሲል ትዳሬን አፈራርሶታል ።ይህንንም ያደረጉት በተጋባን ዕለት ካረፍንበት ሆቴል ሙሽሪት( ወ/ሮ ትግስት) ቬሎ ልብሷን ቀይራ እኔን በሆቴል ውስጥ ጎልታኝ ሁለቱ ግን የግል ሥጋዊ ፊላጎታቸውን ለመፈጸም አንዴ ብቻ ሳይሆን ሁለቴ የድፍረት ሙከራ ፈጽመውብኝ አክሽፈዋለሁ ፤በመቀጠልም በቤተዘመድ በታላቅ እህቴ ቤት በተዘጋጀልን የመልስና ቅልቅል ጥሪ ላይም በዕለቱ የተጠሩት የሥጋ ዘመዶቼ እንኳ ሳይታደሙ በሚያስደነግጥ ሁኔታ እኔን (ሙሽራውንም) ሆነ ዘመዶቼን በንቀት ተመልክተውን ከምንም ሳይቆጥሩን አሳዝነውን እና አሳፍረው ግብዣውን አቋርጠው ተያይዘው መሄዳቸው ፤ በሌላ ቀን ደግሞ ወደ አረፍንበት ሆቴል ድረስ በራሱ መኪና ልወስዳት ሲመጣ ፈቃደኛ አለመሆኔን ለመግለጽ ቢሞክርም ጉልቤው ዳዊትና ሚስቴ ራሷ “ አንተን ያወቅንህ ገና ቅርብ ጊዜ ነው ፤ እኛ ግን የቆዬ ጓደኝነትና የጋራ አገልግሎት አለን ፤ ስለዚህ ከተስማማህ እረፍና ቁጭ በል ካልተመቸህ የራስህ ጉዳይ “ ብለው ዓይኔ እያየ ያለፈቃዴ ሚስቴን ነጥቆኝ ሄዷል ።

እንዲሁም ሌላ ጊዜ ደግም አብረን በአውሮፕላን እየተጓዝን ሳለን እኔን ባሏን “ አንተ መጽሐፍ አንብብ ፤ ዳዊት ብቻውን ነውና እሱ ወደ ተቀመጠበት ወንበር ሄጄ ላጫውተው “ በማለት በአውሮፕላን ውስጥም እንኳ ለብቸኝነት ዳርጋኛለች ። በአንድ ወቅት ደግሞ አንድ

ከተማ ውስጥ አብሬን በተመሳሳይ ሆቴል ውስጥ ባደርንበት ጊዜ (ዕለት) “ከዳዊት ጋር የአገልግሎት ጉዳይ የሆነ የሚናወራው ነገር አለን “ በማለት lab top computer ይዛ ያረፍኩበትን ሆቴል መኝታ ክፍል በር ዘግታብኝ ከሄደች በኋላ የት እንዳደረች ሳላውቅ በ2ኛው ቀን ምግብ መመገቢያው ውስጥ ከግለሰቡ (ዳዊት ) ጋር ቁርስ ስበሉ ለዚያውም ከሩቅ እስካ አየኋቸው ሰዓት ድረስ የትና ምን ሲሰሩ እንዳደሩ እግዚአብሔርና እነሱ ብቻ ናቸው የሚያውቁት ።

በሌላውም የምሳና የእራት ፤ እንዲሁም የቁርስና ቡና ሰዓታት እሷ ሁሌ ከሰውዬው (ዳዊት ) ጋር በመሆን ለብቻቸው ተጣብቀው ስላሉ (ስለምቀመጡ ) ከሙሽራዋ ሚስቴ ጋር ማዕድ ለመቆረስ እንኳ አልታደልኩም ነበር ።የስልክ አጠቃቀሟም ቢሆን ባለሁለት ቀፎ ስለሆነ ከዳዊት ጋር በስልክ ስታወራ ከኔ ርቃ ወይም መኝታ ቤት ገብታ ዘግታ በመቆለፍ ስለሆነ አብሬያት በቆየሁባቸው ጥቂት ወራት የብቸኝነትን ህይዎት ነበር የተጋፈጥኩት ።

አትላንታ ከተማ ተመልሰን በገዛ ቤታችን በእንግድነት ሰውዬውን ( ዳዊትን ) ባስጠጋነው ወቅትም ቢሆን እኔን ሳሎን ( ምግብ ቤት ውስጥ) ትተውኝ “ ስለ አገልግሎት የምንመካከረው ጉዳይ አለን” ወዘተ .. በማለት በራሴ መኝታ ቤት ወይም እንዲተኛበት በሰጠነው መኝታ ክፍል ውስጥ ቢያንስ ለ2 እና ከዚያ በላይ ሰዓታት ያህል በር በመቆለፍ ያደረጉትን አገልግሎት ፈጣሪ ብቻ ይመልከተው ከማለት ሌላ ለማውራት የማይቻለኝ የሚቀፍና ህሊናን የሚያደማ ነገር ነው ።

ይህ ብቻም ሳይሆን ባጋጣሚ እኔ አስቀድሜ ወደ መኝታ ቤቴ ውስጥ ከገባሁ ደግሞ ሌላ ሰበብ ይፈጥሩና “ ከዳዊት ጋር የሚንሰራው አጣዳፊ ጉዳይ አለኝ “ በማለት ኮምፒዩተሯን ይዛ እስከ እኩለ-ሌልት አንዳንዴም እስኪነጋ በሌላው ክፍል ወይም በሳሎናችን ውስጥ አብረው ያድሩ እንደነበር እነሱ ራሳቸው (ዳዊትና ትግስት ) ባሉበት ያንተ ረዳት ፓስተሮችም በተገኙበት ቢሮህ ውስጥ ለበርካታ ሳዓታት ( 7 ሰዓት ) ሙሉ በግልጽ ስንነጋገር አለመካዳቸው የሚታወስ ነው ።

ይህ ድንበርና ገደብ የለሽ መንፈሳዊ ሽፋንና ሃይማኖታዊ ሰበብ ከባል ስልጣንና ፈቃድ ውጪ የተሰወረ ሚስጢራዊ አገልግሎት ሊደረግ ሲታሰብ ምን ሊሆን እንደሚችል ፍርዱን ለፈጣሪና አመዛዛኝ ህሊና ላለው ሰው ሁሉ ትቻለሁ ።

ሌላው ደግሞ በአጋጣሚ እንኳ እግሯን አንድ ነገር ስያደናቅፋት ፤ ዕቃ ስወድቅባት እና ድንገት የሆነ ድንጋጤ ስሠማት በቁልምጫ “ዴቭ ድረስልኝ “ ስትል መስማት፤ እንዲሁም ከወላጆቿ ፤ከሥጋ ዘመዶቿና አብሮ አደግ ጓደኞቿ እንዲሁም ከኔና እሷ ፎቶግራፎች ይልቅ የዳዊትን ፎቶዎዎች በመኝታዬ ራስጌና ግርጌ ፤በሳሎን ቤትና የማድ ቤት ( ኩሽና ) ማቀዝቀዣ ላይ ዘወትር ማየት አዕምሮን የሚያደማና ህሊናን የሚያቆሽሽ ትዕይንት ነበር ። እስቲ አትታዝቡኝና በሷ ልብና አምሮ ውስጥ ይህ ዳዊት ምኗ ይሆን ? እኔስ ምኗ ነበርኩ ?

በአጋጣሚ ይህንን ደስ የማይል ታሪክና ዜና ለሚሰሙትም ሆነ እሮሮዬን ለሚያነቡት ሁሉ ለማለት የሚፈልገው ነገር ቢኖር 1ኛ እንዲህ ያለው እልህን ጭሮ ለከፋ ወንጀል የሚገፋፋው አደናጋሪና አጠያያቂ ክፉ ፈተና በገዛ ቤቴ ስለገጠመኝ እንኳን መሸከምና መታገስ ቀርቶ ለመስማትም ሆነ ለማውራት የማይቻለው የስቃይ ጦርነት እየተፈራረቀብኝ በእግዚአብሔር ጸጋ እስካሁን ድረስ በህይዎት መኖሬ እኔን እራሴ ስገርመኝና ስደንቀኝ የሚኖር የጌታ ጥበቃና ውለታ ነው ። እግዚአብሔር አምላክ የማይቻለውን አስችሎ ከክፉ ሁሉ ጠብቆ ነፍሴን ስላኖራት ክብር ምስጋና ይህንለት እላለሁ ፤ 2ኛ የተወደደች ፤ እግዚአብሔርን የሚታውቅ ፤ የምትፈራ ፤ በቃሉም የምትመራ ፤ ለፈጣሪ ፤ ለባሏ ፤ለህሊናዋ ፤ለኑሮዋ ታማኝ የሆነች መልካም ሴት ( ሚስት ) አግኝቶ አዕምሮው ካልተቃወሰ ( የጤና ችግር ከላጋጠመው ) በቀር ማን በዋዛ ሚስቱን ይጥላል ? ( ይተዋል ) ? ያልታደልኩትን እኔን ካልሆነ በቀር እንዲህ ዓይነቱ ውንብድና ፤ ሃፍረት የሌለው ጥቃት በማን ላይስ ደርሶ ያውቃል ?

ይህ ከመሆኑ በፊት ምንም እንኳን በውቅቱ የገባሁበት አጣብቂኝ ለማውራትም እንኳ የሚቀፍ ፤ ውስብስብ ፤ የከረፋ ቆሻሻና ጸያፍ ከመሆኑ የተነሳ ልታገሱት የማይቻል ቢህንም ፤ ለብዙ ዘመን ተጠምቼ ፤ ተመኝቼና በትዕግስት ጠብቄ ያገኘሁት ፤ ብዙ ዋጋ የከፈልኩበት ትዳሬ ስለሆነ ሙሉ ለሙሉ ከመበላሸቱ በፊት እስቲ ይሁን ብዬ ፤ ይቅር ለእግዚአብሔር በማለት ሁሉን ረስቼ ፤የማይቻለውን ችዬ ፤የማይረሳውን ረስቼ ፤ ነገን ብቻ ተስፋ በማድረግ እንደገና ጠጋግኜ ለማዳን የሞከርኩት ትዳሬ አፈር ድሜ በልቷል ።

እንዲህም እንኳን ሆኖ ወዲያውኑም ውዬ ሳላድር ባንድም ሆነ በሌላ ፤ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በኔ ሰበብ የእግዚአብሔር ቤት መጠቋቋሚያና መሳለቂያ ከሚሆን ፤ሌሎች ቅዱሳንና እውነተኛ ታማኝ የሆኑ አገልጋዮችና መሪዎች ስም በመጥፎ ምሳሌ አብሮ ከሚነሳ ( ከሚጠፋ) ፤አገልግሎታቸው ከሚተች ፤ራዕያቸው ፤ ዓላማቸውና ትጋታቸው ዋጋ እንዳያጣ ፤ሳይጣን ከሚደሰት ፤ ሁላችንም የዓለም አጀንዳ ከሚንሆን፤ እግዚአብሔርንና መንፈሱን ከማሳዘን ፤ በተለይም በእምነታቸው ያልበረቱ አዳዲስ አማኞች ግራ እንዳይጋቡ እኔው ደግሜ ደጋግሜ ልጎዳና የሚቻል ከሆነ እስቲ እንደገና ትዳሩን ወደ ነበረበት ልመልሰው በማለት ያሰብኩት ቀናነት ዋጋና ትኩረት ተነፈገው።

ይህ ሁሉ ሆኖ ሰውየው ( ፓ/ር ዳዊት ) ይህንን ለፈጸመበት ጥፋትና አስነዋሪ ተግባር እስካሁን አልተገሰጸም ፤ አልተወቀሰም ፤ አልተከሰሰም ይቅርታም አልጠየቀም ። ነገር ግን የከበረውን ትዳሬን አፍርሶ እሱ ግን ዛሬም እያሾፈ በሰላም ይኖራል ፤ እንዳውም ይባስ ብሎ ቤተክርስቲያንን ይመራል ፤ የእግዚአብሄርን ቃልና ፈቃድ አስተምራለሁ ፤ የክርስቶስን ዓላማ እያራመድኩ፤ እያስፈጸምኩ ነኝ ይላል ።ግብረ አበሩ የሆነችውም ወ/ሮ ትግስት የራሷን ትዳር ንዳ ዛሬም አብረው በመሆን ሥፍራና ጊዜ እየቀያየሩ በየአብያተክርስቲያናቱ ዘንድ የተለመደውን ተራ ግርግር እየፈጠሩ መንፈሳዊ አገልጋይ ለመባል እየጣሩ ናቸው ። በኔ ላይ በለመዱት ዓይነት አኳኋን በተመሳሳይ ሁኔታ የኔ ዓይነቶቹን ሌሎች የእግዚአብሔር ህዝብ መተራመስ የለበትምና ድርጊቱ ተገላልጦ የማያዳግም ትምህርት ተሰጥቶ ህዝበ-እግዚዝብሔር ከመታለልና ተመሳሳይ ሰለባ ከመሆን መዳን አለበት ።

እነዚህ ፌዘኛ ግለሰቦች ፤ እጥቤ አሿፊ ጩሉሌዎች ሃፍረትና ይሉኝታ የሌላቸው ደንታ-ቢስ ባይሆኑ ነው እንጂ እንኳን በቤተ-እግዚአብሔር ውስጥ ካህን የሆነ ሰው ቀርቶ በዓለም ያሉቱ ካሃዲዎች ዘንድም እንኳ እንዲህ ዓይነቱን ወንጀል ስፈጽሙ ተሰምቶና ተደርጎ አይታወቅም ። እኔ ተራ እቃ ( ንብረት ) ብቻ አይደለም የጠፋብኝ ፤ ገንዘብና ጊዜ ብቻ አልነበረም የባከነብኝ ።ነገር ግን ትዳሬ እኮ ነው የፈረሰው ፤ መተኪያ የሌለውና የዚህ ምድር አስፈላጊ እና እግዚአብሔር ባርኮ ከፈቀደልን እድሎችና መብቶች አንዱ ነው ትዳር::

በሌላ አባባል ትዳር ከእግዚአብሔር ቃልና መመሪያ ውጪ ሌላ ፎርሙላ የለውም ፤ “ ሰው እናት አባቱን ይተዋል ከሚስት (ከባል ) ጋር አንድ ይሆናል፤(ይጣበቃል) “ እንደሚል አንድ ሥጋ ፤አንድ አካል ፤አንድ መንፈስ በመሆን አንድ ዓላማ ይዘው ጥንዶች በፍቅር የሚጣመሩበት ነው ። በዚህ ዓላማ የተጣመሩ ጥንዶች አንዳቸው ከሌላኛው የተለየ ፊላጎት እና የተደበቀ ልዩ ሚስጢርና ፊላጎት ሊኖራቸው አይገባም ፤

ነገር ግን ያልታደለው የኛ ትዳር ግን ገና ስፈጠር ከአጀማመሩ በጨቅላነቱ በአጭር የቀጩት ቢሆንም ትዳሬ ለኔ ህይወትና የከበረ የአምላኬ ስጦታ ነበር ። ትዳር አንዴ ብቻ ነው ፤ ማፍቀርም የምቻለው አንዲትን ሴት ፤ ለዚያውም ከተቻለ አንዴ ጊዜ ብቻ ። ዳስታም ቢሆን ሁሌ የለም፤ በየዓመቱ ሠርግ ለማድረግም የማይታሰብ ነው ። የሆነው ሆኖ ለአንዲት ደቂቃ ( ዕለትም ) እንኳ ቢሆን ያፈቀርኳትን ሴትና የከበረውን ትዳሬን በቀላሉ በፓ/ር ዳዊት ሞላልኝ ምክንያት አጥቻለሁ ።

ስለዚህ የከበረና የናፈቅኩት ፤ የተመኘሁት ጅምር ደስታዬ በእንጭጩ ከመቅጽበት በመቀጨቱ ወደ ሃዘንና ውርደት ተቀይሮ አንገት አስደፍቶኛል ፤እልሀኛ ፤ ቂመኛና በምሬት የተሞላሁ ተናዳጅ አድርጎኝ ሄዷል ።ነገ ደግሞ ምን እንደሚሆንና ምን እንደሚገጥመኝ እርግጠኛ አይደለሁም ።

ይህ ግለሰብ (ዳዊት) ግን ኑሮዬን አፍርሶ ፤ ህይዎቴን አበላሽቶ እንዲህ እንደ ቀልድ እያሾፈ ሊኖር ነው ? ካደረሰብኝ ብርቱ ፈተና የተነሳ በህይወት ለመኖር የማያስችል ፤ ለወንጀል የሚገፋፋ ፤ ለከፋ በሽታና ጥልቅ ሃዘን የምዳርግ ነው የገጠመኝ ። አረ ለመሆኑ በትዳርና በርስት ቀልድ አለ ? በዓይንና በሚስትስ መጫወት ይፈቀዳል ? እንኳን ግፍና በደል በግልጽ በቤቴ ተፈጽሞብኝ ቀርቶ ድርጊቱ ደግሞ ከጥርጣሬ ያለፈ የአደባባይ ጥቃት መሆኑ ይቅርና እንዲሁ በጥርጣሬም እንኳን ቢሆን በሚስቴ የልቅነት ድርጊት የተነሳ የመቅናትም ሆኔ የተጣመመውን የማቅናት መብቱ ለኔ የሚገባኝ ህጋዊ ባል (አባወራ ) አይደለሁምን ?

እስቲ ፍረዱኝ አንድ መንፈሳዊ አገልጋይ በአገልግሎት አሳቦ የራሱን ሚስት እቤቱ አስቀምጦ “ዘመዴ( ካዝኔ) ናት “ እያለ አንዲትን ሌላ ሴት እንደ ኮሮጆ ሸክፏት ፤ እንደ ሻንጣ እየጎተተ ከሀገር ሀገር ፤ ከከተማ ወደ ከተማ በየሆቴሉ ሁሉ አስከትሎ ስጓዝ ትንሽ እንኳን ይሉኝታ አይዘውም ? ያቺስ ሴት ብትሆን የ”ሶሎ ዘማሪ ፤ የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋች ፤ ወይም በመድረክ ላይ የቋንቋ አስተርጓሚ (ሰባኪ ) ሳትሆን የራሷን መደበኛ ኑሮ ትታ እንደ ጭን ገረድ በየሀገሩና መንደሩ የማንንም ወጠምሻ ጎሮምሳ ተከትላው እየዞረች አብራው በየሆቴሉ አብራው ስታድር ሁለቱም ህሊና የላቸውም ዎይ ?

ሁለቱም በገዛ ህሊናቸው ባይኮረኮሩ ፤በመንፈስ ቅዱስ ለምን አልተወቀሱም ? አዕምሮ ቢደነዝዝ ፤ ህሊናቸው የማይወቅሳቸው ፤ የአውዋቂን ምክርና ተግሳጽ የማይሰሙ ፤የህዝብን ትዝብትና ግልምጫን ከምንም የማይቆጥሩ ቢሆኑም ከነአካቴው ሁሉም ይቅርብኝ እንጂ እኔ ግን ትዳሬን በማንም ማስነካት ፤ ሚስቴንም ከማንም ጋር መጋራት ስላልፈለኩ ሳልወድ በግድ ከመካከላቸው ወጣሁ ።በዚህም በዘመኔ ሁሉ የማልረሳ የህይዎት ጠባሳ እና ስብራት ትቶልኛል ፤ አንዳንዴ ቁጭ ብዬ እያሰላሰልኩ ሳስብ ባልጠፋ ሰው ከነዚህ ቅንነት ከጎደላቸው ሰዎች ጋር እኔ ስገጣጠም እግዚአብሔር ለምን ዝም አለኝ ? ይህ ሁሉ ጉዳት ፤ መቁሰል ፤ መድማት ፤ መፈራገጥ ፤መላላጥ ብሎም ለብርቱ ሃዘን መጋለጥ ለማን ይጠቅም ይሆን ? ማንስ ይከብርበት ይሆን ? ማን ከስሮ ቀርቶ ማንስ ያተርፍ ይሆን ? እንዳው ባጭሩ ይህ ዳዊት የሚባል ሰውዬ እንዲህ አቃጥሎኝ አዋርዶኝ እስከመጨረሻው የሚሳካለት መስሎት ይሆን ? ደስታዬን እንዲህ በአጭር

አጨልሞ እሱ ግን እንደ ፈነጨ ሊኖር ? ለማንኛውም የመጨረሻውን ውጤትና ድምዳሜ በያንዳንዷ ሰኮንድና ደቂቃ ከአምላኬ በትዕግስት እጠብቃለሁ ።

ዶ/ር ፡

ፓ/ር ዳዊት የበደለኝ በብዙ አቅጣጫ ነው ፤ለምሳሌ አስቀድመን በጋራ በተስማማነው መግባባት መሰረት በራሱ ቤተክርስቲያን (FBI ) ባለሙያዎች ተቀርጸው የተሰሩትን የሠርጌን ቪዲዮና ከ5000 በላይ የሆኑ ፎቶግራፎችን ኮፒም ሆነ ኦሪጂናል ቅጂዎችን እስከ ዛሬ ድረስ እንዳለገኝ ከልክሎ በማስቀረቱ እንኳን ለዘመድ አዝማድ ፤ ጎደኞቼና ጎረቤቶቼ ፤ የስራ ባልደረቦቼ ፤ ለአብሮ አደጎቼ ይቅርና እኔ ራሴ የጉዳዩ ባለቤት የሆንኩት የሠርጌን ማስታወሻ የማየትና በታሪክነቱ ለማስቀመጥ ዳዊት ከልክሎኛል ። የጋብቻ ወረቀቴንም (Marriage Certificate ) እስካሁን ድረስ በጉልበቱ አስቀርቶታል ።

እኔ ብቻ ሳልሆን መልካም ትዳር እንዲገጥመኝ ተመኝተውልኝ ለጋብቻችን መሳካት የጸለዩ ፤ የለፉ ወገኖች ፤ የረዱን እና በብዙ የደከሙልን ፤ እሩቅና የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲንደርስ ከልባቸው ያማጡ ጓደኞችና የስጋ ዘመዶቼ ሁሉ ጭምር በደረሰብኝ ሁኔታ አፍረዋል ፤ አዝነዋል ፤ተበሳጭተዋልም ።

በቆየው የሀገራችን አባባል “ከምርት እንክርዳድ አይጠፋም” እንዲሉ ጥቂት ግለሰቦች (የነዳዊት ግብረአበሮች ) ካላቸው ተመሳሳይ ሥነምግባር እና ባህሪ፤ የግል ጓደኝነት ፤ ውለታና ቀረቤታ የተነሳ ግድፈትና ነውራቸውን ሊያስተባብሉ ፤ እርኩሰትንና ቅጥፈትን አድበስብሰው ነጻ ናቸው ለማለት ደፋ ቀና ሲሉ ፤ የጥፋተኛውን ወንጀል ሸፋፍነው ነውረኛውን በጉያቸው ወሽቀው በመደበቅ ፤ሃቅን በሃሰት በመጨፍለቅ ፤ እኔን በማግለል ለነገራችን ቅርበት የሌላቸውን ንጹሃንን በማታለል ፤ እውነትን በማፈን ፍትህን ለማዛባት ትርምስ ፈጥረው ቅዱሳንን ግራ ለማጋባት ሞክረው ነበር ።

ነገር ግን እኔን የገረመኝና ያናደደኝ “ በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት “ ዓይነት አባባል ካልሆነ በቀር የገጠመኝ መከራና ፈተና ከመርግ ይልቅ እጅግ የሚከብደው ውርደትና ሃዘን ፤ ጥቃት ሁሉ እነሱን ገጥሞ ቢሆን ኖሮ ( ራሳቸው በኔ ቦታ ቢሆኑ ኖሮ ) ያለማጋነን ነፍሳቸውን በዛፍ ላይ የሚያንጠለጥሉ ፤ ምናልባትም አዕምሮያቸውን ስተው ፤ ጨርቃቸውን ጥለው የሚያብዱ ወይም ደግሞ በንብረትና በሰው ህይዎት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርሱ እንደሚችሉ አልጠራጠርም ። ፓ/ር ዳዊት ራሱ እኔን የገጠመኝ ዕጣ-ፋንታ ገጥሞት ቢሆን ኖሮ ምን ይውጠው ነበር ? ሁሉም ቢጤዎቹ ካንድ ጉድጓድ የተቀዱ ፤ አንድን ጽዋ በጋራ የጨለጡ አሳፋሪዎች እና selfish ስለሆኑ ታዘብኳቸው ።

መቼም ቢሆን እንደ ሰው ያልሆነ እግዚአብሔር ጻዲቅና መልካም አምላክ ነውና ምህረት ፤ ቸርነት ፤ ጥበቃው ፤ ፍቅሩ ፤ ርህራሄው ያማያልቅበት ፤ ወረት የሌለው በመሆኑ ራራልኝና አጽናንቶ የማይቻለውን እንዲችል ረዳኝና ከክፉው ሁሉ ጠብቆ እስካሁን በህይዎት አኖረኝ እንጂ የተጋራጠብኝ ፈተና ማንም ብርቱ ነኝ ባይ ልታገሰውና ልቋቋመው የማይቻል ከባድ አደጋ ነበር ። የራራልኝ እግዚአብሄር ይመስገን ፤ ነገንም በርሱ ፈቃድ እኖራለሁ ፤ አሜን ።

ለመሆኑ በማንአለብኝነት ይህንን ሁሉ ጥቃት የሚፈጽም ይህ ጉልቤ ጀብደኛ (ዳዊት ) ማን ነው ? “ከወፈሩ አይፈሩ” ነው ነገሩ ? ወይስ ምንን ተማምኖ ? ይህንን ሁሉ በደልና ግፍ ሰው አይቶ ባይፈርድልኝ እግዚአብሔርስ ይወደዋል ዎይ ? ይህ ግድየለሽ ሰላሜን አደፍርሶ ፤እና ህይዎቴን አበላሽቶ ፤ ኑሮዬን አናግቶ እሱ ግን ልፈነጭ ? አይደረግማ !!

የፈጸመውን ድርጊት ተናግሮ ፤ ጥፋቱ ተዘርዝሮ ስህተቱ ተብራርቶ ነውርና ድፍረቱ ተገልጦ ለአደባባይ መቅረብ አለበት ። ምናልባት በመንፈሳዊ አገልግሎት ሽፋንና ሰበብ ያካባተው ሃብት ፤ ያተረፈው ዝናና ክብር አለኝ ብሎ ስለምያስወራ ፤ እንዲሁም የጥፋቱ ተባባሪ ቢጤዎች ፤ ጓደኛና ምኑንም በውል ያልተረዱ ቅንና የዋሆች ያለእውቀት ደጋፊዎች ልኖሩ ስለምችሉ ከሰው ዘንድ እውነተኛ ፍርድ ላላገኝ እችላለሁ ፤ ቢሆንም ከቲፎዞ (ደጋፊ) ብዛት የተነሳ የፍትህ ዳኛና ሃቀኛ ምስክር ስለማይገኝ ፤ ትዳሬ ፈርሶ ፤ህይዎቴ ተበላሽቶ ፤ ራዕዬ ተጨናግፎ ፤ ተስፋዬ ጨልሞ ከአቅሜ በላይ የሆነ አበሳና ውርደት ተሸክሜ ለመኖር ለኔ እጅግ ከባድ ነው ።

ፓ/ር፡

ከዚህ ቀደም ውድ ጊዜህን ሰውተህ ከረዳቶችህ ጋር በመካከላችን ተገኝተህ ለበርካታ ሰዓታት እኛን ( ዳዊት ፤ ትግስትንና እኔን ) ስታወያየን አንተ ራስህ ሰምተህ ፤ አይተህ ፤ግንዛቤ እንዳገኘሀው (እንዳረጋገጥከው ) ፓ/ር ዳዊት እኔና ሚስቴን ባጋባበት ዕለት ወዲያውኑ ከመቅጽበት ከሚስቴ ጋር እንዲንለያይ ዋና ምክንያት ሆኗል፤ ለዚያውም አንዴ ብቻ ሳይሆን ሁለቴ ሦስቴም እንጂ ።

ይህ ድርጊት በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በአበሻ ታሪክ በኔ ብቻ ካልሆነ በቀር የት ሀገር ? መቼ ? በነማን ላይ ደርሶ ያውቃል ? እነዴትስ በጫጉላ ሽርሽር ወቅት ( honey moon time ) ሙሽሪት ሙሽራውን ትታ ፓስተሯን ለመዝናናት በሚል ሰበብና ድፍረት የቃል ኪዳን ሙሽራ ባሏን በሆቴል ውስጥ እንዲሁም በሌላ ጊዜ ደግም በባዶ መኖሪያ ቤት ውስጥ ጥላ ፤ጨርቋን ጥላ እና አዕምሮዋን ስታ ለ7 ቀንና ሌሊት ያህል የምትጠፋው ? በገዛ ቤታችን ውስጥስ ቢሆን ባልን ሳሎን ውስጥ ትቶ ከፓ/ር ጋር መኝታ ቤት ገብቶ በር በመቆለፍ ለሰዓታት ያህል አገልግሎት ላይ ነን ማለትና…ወዘተ ጸያፍና ድፍረት የተሞላባቸው አሳፋሪ ድርጊቶችን መፈጸም የጤና ነው ? ወይስ የእብደት ?

እንዲህ ዓይነቱ ነውርና ልቅ የሆነው ጥፋት ከልክ ያለፈ ፤ መረን የለቀቀ ፤ሚዛኑን የሳተ ፤ ከድንበርም የዘለለ ስለሆነ ልሸከመው የማልችለው በቤቴ ፤ በትዳሬ እየተፈጸመ ነውና የከፋ ነገር ከመምጣቱ በፊት ይታሰብበት በማለት በግልጽ ውይይትና ምክክር አድርገን እናስወግድ ፤ መፍትሄ በመፈለግ እርማት እንውሰድበት የሚል ገንቢ እና ቀና ሃሳብ እንደ አገልጋይ ክርስቲያንና አማኝ በአክብሮት ያቀረብኩላቸው አቤቱታ ና ጥያቄ “ ጌታ ይገስጽህ ! ይህ ሰው (ፓ/ር ዳዊት ) በእግዚአብሔር የተቀባ ፤ የተለቀለቀ መንፈሳዊ ሰው ነው ፤ ስለዚህ ጌታ በቀባው ላይ እጅህን አታንሳ ፤ “ ተብዬ ተኮነንኩ ። ራሱ ዳዊትም ቢሆን “ ያቀረብከው ጥያቄ ለኔ የሚመጥን አይደለም “ በማለት ናቀኝ እንጂ ጆሮውን እንኳ ለጥቂት ለደቂቃ ያህል ልሰጠኝ አልፈለገም ፡፡ በዚህም ተግባሩ የኔን መብት ለራሱ አደረገ ፤ እኔን ግን ለውርደት ለጭንቀት ፤ ለሃዘንና ለኪሳራ ዳረገ። አሁን በዚህች ደቂቃና ሰከንድ ይህንን ደብዳቤ በማዘጋጅበት ሳምንት (ቀናት ) በሀገር ቤት ኢትዪኦጵያ ውስጥ ከዚህቺው ሴት ጋር አብረው ናቸው ። ጨርሰው ልላቀቁ ስላልቻሉ በረቀቀ ሚስጢር ያለሀፍረት አሁንም አብረው እንደተጣበቁ ናቸው ።

ፓ/ር ፡

ምናልባት “ድፍረት ፤ ንቀት ፤ ትዕቢት ወዘተ…የተባሉትን ዓረፍተነገሮች (ቃላት) ለምን ተጠቀምክ ? ለምንስ ደጋገምክ ? ትለኝ ይሆን ?በጣም የሚያናድደው ፤የሚያስገርመውና አሳፋሪው ነገር ይህ ግለሰብ ራሱን ነቢይ እያስባለ መገለጥ ቢጤ እያቀነባበረ የእግዚአብሔርን ቃል እየጠቃቀሰ “ የዓዞ እንቧ “ እንደተባለው የሀገራችን አባባል “ኢየሱስ ያድናል “ ወዘተ….በሚል ቋንቋ የዋሁን ህዝበ-እግዚአብሔር ፊት በእግዚአብሔር ፑልፒት ላይ እየተንጎራደደ መፈክር እያሰማ የትዳርን ክቡርነት ፤ የባልና ሚስትን ህጋዊ ግንኙነት (አብሮነት) ከፈጣሪ የሆነና የተቀደሰ ቃል ኪዳን መሆኑ እንደት ተሰወረበት ? የራሱን ሚስት እቤቱ አስቀምጦ በአፍላ ፍቅራችንና ጅምር ትዳራችን ወስጥ እንደ እርጎ ዝንብ ጥልቅ ብሎ ለምን ገባብን ?

ለነገሩማ ቀድሞውንም ቢሆን ሴራቸው ስላልገባኝ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸው በሚል አምኜ ቀረብኳቸው እንጂ እነሱ ግን ያኔም ቢሆን ማስመሰል በተሞላበት የህሰት ትንቢት አደንቁረውኝ ፤በመገለጥ አዋክበውና አጣድፈውኝ ለስውር ዓላማቸውና የግል ጥቅማቸው ማሟያ አቅደው ለይስሙላ ከአጠገባቸው ሊያስቀምጡኝ ፈለጉ እንጂ ያኔ ያላወቅኩት ቆይቼም ቢሆን በኋላ እንዳረጋገጥኩት ለ5 ዓመታት ያህል ዘልቆ የቆየ ግነኝነትና አሳፋሪ ቃል-ኪዳን ነበራቸው ።

በሀገራችን አባባል “ የአይጥ ምስክር ዲንቢጥ ናት “ እንደተባለው ካልሆነ በቀር እነዚያ ቢጤዎቹስ ቢህኑ “ እሱ ዳዊት የፈጸመብህ ድርጊት አግባብ ባይሆንም ጸጥ ፤ ለጥ ብለህ ተቀበልና ዝም በል ። አለበለዚያ ትቀሰፋለህ ፤ ወደ ሲኦል ትገባለህ፤ ለሳይጣን አሳልፎ ይሰጥሃል ፤ ትረገማለህ “ ወዘተ.. እያሉ አስፈራርተው ሲያሸማቅቁ ፤ በሌላ በኩል ደግሞ “ የሚናከብረውና በጌታ የተቀባ ፤የተለቀለቀ ፤በመገለጥና ጥበብ ብሎም የፈውስ ጸጋ ስጦታ አገልግሎቱ እጅግ የጠለቀ ፤ የመጠቀ ነውና የተደረገብህን ድርጊት ሁሉ አሜን ብለህ አርፈህ ኑር” በሚል ማባበል እኔን አታሎ ለማዘናጋት ለሃጥያት ሲተባበሩ ፤በሃሰት ሲመሰክሩ ፤ አንዳች ፈጣሪን ባይፈሩ ፤ለማንም ባይራሩ ፤ ለሃቅ ባይቆረቆሩ ፤ በእግዚአብሔርም ሳይጠሩ ለክብራቸው ፤ ለዝናቸው ፤ ለጥቅማቸውና ለእንጀራቸው ያንን ያህል በድርቅና ከተከራከሩ ትዳሬ ደግሞ ለኔ ከእንጀራና ሆድ የሚበልጥ ፤ ከዝና ፤ ከክብርና ጊዜያዊ ጥቅም ያለፈ ህይዎትና ኑሮዬ መሆኑን ለማወቅ እንዴት ተቸገሩ ?

ስለዚ ይህ መቼም “ በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት “ እንዲሉ ንቀት ፤ ትዕቢት፤ ድፍረትና “ ነጌ በኔ” አለማለት ካልሆነ በቀር ሌላ አንዳችም ምክንያት ሊኖር አይችልም እንዳውም በኔ ቦታ ሆኖ ካዩት ከድፍረት ያለፈ ጭካኔ ነው እላለሁ ። እኔ ደግሞ ተበድዬ ፤ ተጎድቼ ፤ ተጠቅቼ ፤ ተደፍሬና ተንቄ ሽንፈትን አሜን ብዬ በውርደትና በሃዘን የተሞላ ህይዎት ለመኖር ስለማልፈልግ አንድ ስፍራ ላይ ባንድ ወቅት

ባንዴ መቋጨትና መቆረጥ አለበት ። ያንን ለማምጣት ደግሞ እስከ ህይዎቴ ፍጻሜ ድረስ ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ነኝ ፤ የእውነት አምላክ ፤የቅኖች ወዳጅ ፤ የምስኪኖች አለኝታ የሆነው ፈጣሪዬ ደግሞ ለአረመኔዎችና ለነውረኞች አሳልፎ ስለማይሰጠኝ ፤ ጥቃቴንም ስለማይወድ በሱ እየታመንኩ ላደርገው የወሰንኩትን በአርሱ ታምኜ እፈጽማለሁ ።

አዎን ከዚህ በላይ ያልኩት ሁሉ በኔ ላይ የተፈጸመ እውነት የሆነ ዓይን ያወጣ ጥርሱን ያገጠጠ ብልግናና በቃላት የማይገለጽ ከባድ በደልና ግፍ ነበር ። ዛሬ ዛሬ በየቦታው አፈ-ጮማ አተራማሽ መተተኛና ፈጣጣ ጋጠ-ወጥ ጮሌ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቤት እያጥለቀለቀ የስንቱ ምስኪኖች ትዳር ደቀቀ ? አረ የፍትህ ያለህ ! የጽድቅ ያለህ ! የቅድስና ያለህ ! አለቅን ፤ ደቀቅን !! እባካችሁ ድረሱልን !!!

ለመሆኑ ትዳርን ማፍረስ ቤተክርስቲያንን ማፍረስ አይደለምን ? ለዚያውም የቤተእምነት መሪና አገልጋይ ሆኖ የንጹሃንን ትዳር እያረከሱ ፤ ቤተሰብን እያፈረሱ ቤተክርስቲያንን እያስወቀሱ “የተቀባ ፤የበቃ “ ወዘተ … አገልጋይ መሆን ይቻላል ? ትንቢት እየተናገሩ መገለጥ እየቀበጣጠሩ የትዳርን ክቡርነት እንዴት ዘነጉ ? ሚስት ለባል ፤ ባልም ለሚስት ብቻ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ለነሱ ብቻ ሲባል ሌላ ነቢይ መቅጠር ( ልዩ መላዕክት ከሰማይ ማስመጣት ) አለብን ዎይ ? “እግዚአብሔር እንዲህና እንድያ ብሎሃል” እያለ ሌት ተቀን እየሰበከ እራሱ ግን ለምን አልኖረበትም ? ራሱ ልፈጽመው ያልቻለውን በጉልበት ልያሽክመን ለምን ይጥራል ?

ደግሞስ የኔ አንዲቷ ነጠላ ህይዎት (ነፍስ) ቤተክርስቲያን አይደለችምን ? የእግዚአብሔር መንፈስ ማደሪያ ፤ የክብሩም መገለጫ ቤተክርስቲያን አይደለሁም ዎይ ? ይህ ዓይኑን በጨው የታጠበ ደፋር ግለሰብ ህይዎቴንና ዕድሌን አበላሽቶ ደስታዬን ወደ ሃዘን ለውጦ ቤተክርስቲያንን ሊመራ ?ህዝብን ሊያገለግል ? “ It is not fair “ (ፍትሃዊና አግባብ አይደለም ) ፤ እሷስ ወ/ሮ ትግስት ብትሆን ልማደኛ ባትሆን ኖሮ ከበፊተኛው ስህተቷ ለምን አልታረመችም ? ከኔ በፊት ጀምሮ ነጋ ጠባ የትዳር ቀበኛና ጸር “Allergy “ (የፓስተሮች ቀማሽ ) ይመስል በበፊቱ ነውርና ስህተቷ ትምህርትም ሆነ ምክር ችግርና ግሳጼው ሁሉ መታረም ስገባት እንዴት እንደገና ለአግልግሎት በቃች ? ከኔ በፊት የነበራትን ትዳሯንም እንዲሁ በተመሳሳይ ተግባር ከሌላኛው ፓስተሯ ጋር በዝሙት ተጠርጥራ ትዳሯ እንደፈረሰ ከኔ በቀር ሁሉም የአከባቢያችን መንፈሳዊ መሪዎች የሚታውቁት የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው ። የራሷን ጽንስ (የኑሮ ጅምር ) አጨናግፋ (አኮላሽታ ) ፤ በተለያየ ጊዜና ወቅት ካገባቻቻው ባሎቿ መካከል አንዱንም እንኳ በአግባቡ ይዛ የራሷ ለማድረግ አቅቷት ሁሉንም በየተራ በየቦታው በአደባባይ እያፈረጠች ፤ እንደገና አዘናግታ ከሌሎች ተረኞች ጋር የምትከንፍ ያልሰከነች ሴት አሁን ከሰሞኑ ደግሞ ስፍራና ቤተክርስቲያን ቀይራና ለዋውጣ አዳዲሶቹን መሪዎች ጥብቅ ብላ የቤተእምነቱን ቁልፍ እንዴት ተረከበቻቸው ?

ለማስመሰልና ለጉራ፤ ብሎም ለዝና ብሎም ለድብቅ ዓላማ ካልሆነ በስተቀር የራሱን ቤት ያቃተው ሰው የእግዚአብሔርን ቤት ለመጠበቅና ለማገልገል እንዴት ተገባው ? ለማጭበርበር ካልሆነ በቀር የራሱን ጽንስና ራዕይ ገሎ የሰው ቤት ሄዶ የሌላውን ልጅ ተንከባክቦ ለማስተማር ቀርቶ ጉንጭ እንኳን ለመሳም ሃላፊነት የሚጣልበት ስበእና አለው ለማለት አያስችልም ።እንዲህ ዓይነቱ ሰው ካለ ራዕይ ለመጠበቅ ከቶ አይቻለውም ፤ ምክንያቱም እውነተኛ አገልግሎትና ታማኝነት ከራስ ቤትና ትዳር መጀመር ስለምገባው ። እውነተኛዋ የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ካለች እንዲህ ዓይነቱን ዓይን ያዋጣ ድፍረትና ተራ ቁማር መዋጋት ተጋቢ ይመስለኛል ።

ምክንያቱም በኔ በኩል የችግሩ ሰለባ ከመሆኔም በላይ እንደ ባለ አዕምሮ ሳሰላስል እነዚህ እና ቢጤዎቻቸው ባለቤቱ የከደነውን ያለፈቃድ የሚከፍቱ ፤ አንዱ የገነባውን የሚንዱ ፤በፈጣሪ ስም ፤ በሃይማኖት ሰበብ ተገቢ ያልሆነን ተግባርን የሚሰሩ ፤ለማንም የማይራሩ ከስህተታቸው የማይማሩ ፤ የራሳቸውን ትተው የሰውን ሚስት ( ባል ) ለመቅመስ ሌት ተቀን የሚዞሩ ፤ ለከበረው ትዳርና ጤነኛ ፍቅር እንቅፋት ብቻ ሳይሆኑ ለሰሩት ጥፋትና ስህተት በንቀት ጆሮ ዳባ ብለው (ችላ ባይ ከመሆናቸው የተነሳ )ጉዳቴ ዕለት በዕለት ይበልጥ እየተሰማኝ ስለሆነ የሚወስነው ውሳኔ እየክፋ እንደመጣ ተገንዝቤያለሁ ።

በመሆኑም ስማቸው ከዚህ በላይ በተደጋጋሚ የጠቀስኳችው ግለሰቦች (ፓ/ር ዳዊትና ግብረ አበሩ ወ/ሮ ትግስት ) እንዲሁም ቢጤዎቻቸው በሰው ላይ በደልና ነውር እያደረሱ ፤የንጹሃንን ትዳር እያፈረሱ በእግዚአብሔር ቤትና በቅዱሳን መካከል መሽገው ፤ሃጥያታቸውን ሸሽገው ሚስኪኖችን አንገት እያስደፉ ፤ የሰላማዊ ኑሮን ጣዕምና ትርጉም እያጠፉ መላውን ቅድዱሳን በሃሜትና በአሉባልታ እያተራመሱ ቤተ-እምነቶችን መነጋገሪያ ፤ መሳለቂያ እያደረጉ መቀጠል ተገቢ አይደለምና ጉዳዩን ለህዝብ ሚዲያ እና ለመላው አብያተ-ክርስቲያናት ለማቅረብ ወደድኩ ።

አዎን ፤ በቃ ፤ የእግዚአብሔር ቤት ይህንን ከመሳሰለ የነውር ተግባር ከነዚህ ዓይነቶቹ አስመሳይ ነውረኞች ልጠራ ይገባል ፤እኔም ከእንግዲህ ጥፋተኛው ቅጣቱን እስኪቀበል ፤ ነውረኛው በነውሩ እስኪጸጸት ፤ እግዚአብሔርን ፤ ህዝቡንና ተበዳዩን ይቅርታ እስኪጠይቅ ፤ ቁስሌ እስኪጠገን ፤ህመሜ እስኪፈወስ ፤ ምናልባት ተመሳስለው እና ተደብቀው በየቦታው የተሸሸጉ ነውረኞች ካሉ ያጨለሙት

ተስፋዬ እስኪታደስ ፤ ሃላፊነት የጎደላቸው መንፈሳዊ ጀብደኞች ያኮላሹት ራዕዬ እስኪመለስ ፤ የጌታ ፈቃዱ ሆኖ በህይዎት እስካለሁ ይህንን ስድ አልለቀውም ።

ሌላው ቢቀር እንኳ የዚህን ጨዋ መሳዪ ተግባር ሰው ሁሉ ይስማውና ባላጌዎች ይፈሩበት ፤ ጥፋተኞች ይታረሙበት ፤ ትውልድ ይማርበት ፤ያፈለገው ንሰሃ ይግባበት ፤ዱሪዬዎች አደብ ይግዙበት ፤ ዝንጉዎች ይጠንቀቁበት ፤የተጎዳው አእምሮና መንፈሴ ይታደስበት ፤ እግዚአብሔር ይክበርበት ።

እንዲሁም ተመሳሳይ በደልና ግፍ በሰውር በቅዱሳን የግል ኑሮና ቤተሰብ ህይዎት ላይ እየተፈራረቀባቸው በአጓጉል ኋላ ቀርና በሃይማኖት ስም ማስፈራሪያነት ከደረሰባቸው በደልና ጥቃት ጋር ተሸማቀው “ታሪኬ ከበደለኝ ሰው ጋር አብሮ ከሚጋለጥ ጥቃቱን ተሸክሜ ፤የጎዱኝን ነውረኞች አበሳ ደብቄ ልኑር “ የሚሉት ሳይቀሩ ሌባውን ሌባ ፤ነውረኛውን ነውረኛ ፤ዋሾ አስመሳዩን ቀጣፊ ፤ወዘተ…እያሉ በድፍረት ተናግረው ለማጋለጥ ጉልበት ያግኙበት።

በሌላ በኩል ሰውዬው ( ፓ/ር ዳዊት ) ብልጣ-ብልጥ ፤ አስመሳይ ጮሌ ፤ ምላሱ ቅቤ ፤ልቡ ጩቤ ስለሆነ ፤የገነነ ዝና ፤ እውቅና ፤ ገንዘብና ብዙ ቢጤዎች ስላሉት ብቻ እኔው ተጠቅቼ ፤ፍትህ አጥቼ ፤ በቀሪ ዘመኔ ሁሉ ተቀጥቼ አልኖርምና ሃቀኛ ዳኛ ፤አመዛዛኝ ህሊና ፤ ከአድልዎ የጸዱ ፍትህን የሚያስከብሩ ፤ ለእግዚብሔርና ቤቱ የሚቆረቆሩ ፤ ህዝበ-እግዛብሔርን የሚያፈቅሩ፤ በጽድቅ የሚኖሩ ፤ለሚስኪኖች የሚከራከሩ ፤ነውረኛ ጥፋት ፈጻሚዎችን በድፍረት በመገሰጽ የሚመክሩ የሚያስተምሩ በፍቅር የሚገሩ ፤ ነውርንና እርኩሰትን የሚጸየፉ እውነተኛ የእግዚአብሔር አገልጋይ ዳኞች አሁንም በአምላኬ ቤት ልኖሩ እንደሚችሉ እርግጠኛ በመሆን ይህንን ጉዳቴን ፤ አበሳዬንና ገበናዬን ዘርዝሬ አቅርቤያለሁ ።

ፓ/ር፡

ይህንንም ሳደርግ አንተ ብቻ ሳትሆን ሌሎች የእግዚአብሔር ሰዎች ፤ የጌታ አገልጋዮች ፤መንፈሳዊ መሪዎችና መላው ቅድሳን ሁሉ “ እኛ በቦታው አልነበርንም ፤ አልሰማንም ፤ አላየንምና አንዳች ነገር ከቶ አያገባንም” ወዘተ… እንዳይሉ ይህንን ደብዳቤና የከዚህ ቀደሞቹን ዝርዝር ጉዳዮች የያዙ ኮፒዎችን ሁሉም በያሉበት አድራሻ በተከታታይ የሚልክላቸው (የማሰራጭ ) መህኑን አልሸሽግም ።

ለዚህም ዋና ምክንያቴ ኪሳራዬ ባይካስም ፤ጉዳቴ ስብራቴ ባይጠገንም ፤ ቁጭት እልሄ በርዶ ቁስሌ ባይፈወስም ትዳሬን እንደሆነ እስከመጨረሻው ያጣሁ፤ የፈራረሰ እና ያከተመለት ፤ የሞተ ነገር ቢሆንም እኔ ተጎድቼ ፤ተዋርጄ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሌላው ትውልድ ዘላቂ መፍትሄና ያማያዳግም ትምህርት ያገኝበታል ብዬ በመገመት ነው ፤ አዎን ከተቻለ የኔ ትዳር ተኮላሽቶ ታሪኬም ተበላሽቶ ከእንግዲህ ግን የምስኪን ወገኖቼን ትዳርና ኑሮ ከሚያኮላሹና ከሚያበላሹ አገልጋይ ተብዬ መንፈሳዊ ዱሪየዎች ለመታደግ ነው።

ፓ/ር ፡ እጅግ በጣም የማከብርህ ትልቅ የእግዚአብሔር አገልጋይና መሪ ነህ ። ፓስተሬ እንደ መሆንህ መጠን በአከባቢዬ አንድ የእግዚአብሔር ሰው የሚለው እና የጉዳዬን ዝርዝር ታሪክ በቅርበት የሚያውቅ ካንተ የበለጠ ከእግዚአብሔር በቀር ሌላ ማንም የለም ።

ከመነሻው እስከሁን ያለውን ታሪኬን ከሞላ-ጎደል ታውቀዋለህ ፤ በተለይም ጉዳቴን ፤ ስብራቴን ፤ሃዜኔና እንባዬን ፤ እንዲሁም ጥልቅ ቁጭቴን መገመት ከቶ አያቅትህም ብዬ አስባለሁ ። ስለሆነም ከዚህ ቀደም ከአንዴም ሁለቴ በኛ ጉዳይ እንባህን ስታፈስ ደጋግሜ አይቸሃለሁ ።በሌሎች ቅዱሳን ዘንድም ቢሆን የነዚህ ነውረኞች ነውርና ቀልድ ከማንም የተሰወረ አይደለም ፤ ያለንበት ወቅት ከምንጊዜውም በለይ በእርኩሰትና በክፋት የተሞላ ሆኗል ፤ ክህደት በመብዛቱ ቅጥፈት ነግሶ ዘመኑ እጅግ ከባድ ሆኖብናል ።

ስለዚህ እውነት ታፍኖ ሃቅ በመታነቁ ምክንያት ፍትህን አስከብሮ ለጽድቅ የሚፈርድ ዳኛ ይቅርና የቅርብ የሆነ ታማኝ ጓደኛ የታጣበት አስደንጋጭ ወቅት ላይ ደርሰናል። እኔ ያለእግዚአብሔር በቀር ሃብት ፤ ዘመድ፤ ወገንና ደጋፊ የለኝም ።

በዚህ ቁርጥና ፈታኝ ወሳኝ ወቅት አንተ ግን እንደ አባት ፤ የእምነት ሰው ፤ የቤተከርስቲያን መሪና የህዝብ አገልጋይ የመፍትሄ ምክርህ ፤ እገዛህ ፤ አስተያየትና ውሳኔህ ምንድን ነው ?

በተጨማሪም የተፈጸመብኝ በደል ፤ ግፍና ጥቃት ዘርዝሬ ከላይ በጠቀስኩት መሰረት ለሚዲያዎችም ጭምር ለማሰራጨት የወሰንኩ መሆኔን በክብሮት እየገለጽኩ ከፈጣሪዬና ካአንዲት ነፍሴ በቀር አንዳች ለሌለኝ ለኔ ለብቸኛውና ምስኪኑ ሰው አሁንም እንዲትጸልይልኝ ጭምር በጌታ አደራ እላለሁ ።

በጌታ እወደሃለህ

እጅግም አከብርሃለሁ

እግዚአብሔርና ቃሉ ብቻ እውነትና ትክክል ናቸው !

ከእንግዲህ በዘመኔ ሁሉ ማንንም አላምንም !!

እውነት ብትቀጥን እንጂ ጨርሳ ተበጥሳ አታውቅም !!!

ግርማ ዱሜሶ

Email; gelgela09@yahoo.com

ግልባጭ ፡

ለኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት በሙሉየእግዚአብሔር ቅዱሳን ሁሉ በያሉበትአበሻ ነክ ለሆኑ የኢትዮጵያዊያን ሚዲያዎችና ድህረ-ገጾች በሙሉ ።