Thursday, April 11, 2024

ጸጋ ምንድነው? What is Grace?

ጸጋ ምንድነው? (What is Grace?) (ክፍል ሦስት) በባለፈው ፅሑፋችን ከሦስቱ የኃጢአት በሮች አንዱ የሆነውን የሥጋን ልቅ የሆነውን ፍላጎትና መሻት በመንፈሳዊ ጉልበት በሚዛን ለማስጠበቅ ጸጋ እንዴት እንደሚያስፈልገን ተመልክተናል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው “ነገር ግን እላለሁ፥ በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ።”ገላ 5፥16 ምክንያቱም “ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው።” ሮሜ 8፥6 በምድር ላይ በሕይወት እስካለን እኛ አማኞች መጠበቅ ከሚገቡን የኃጢአት በሮች የመጀመሪያው የሥጋችንን መሻት መቆጣጠር ነው። ሥጋ ተፈጥሮዋ አራት የማይስማሙ ባህርያትን የተሸከመች ስለሆነ ፍላጎትዋ ገደብ የለውም። መገደብና መወሰን ያለብን አምነንበትና ዘላለማዊ ሕይወትን ባገኘንበት በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ነው። መንፈሱ ይመራናል፣ ያስተምረናል፣ ይመክረናል። ነገር ግን ሥጋን ተሸክመን የምንኖረው በዚህ ዓለም ውስጥ ስለሆነ የሥጋን ፈተና ለማሸነፍ የዓለምን ጠባይ ማወቅ ደግሞ ግድ ይለናል። 2/ ዓለም፣ ዓለም ሌላው የኃጢአትና የመከራ በር ናት። ሕይወት ያለው ሥጋችንን ተሸክመን የምንዞረው በዚህ በተረገመች ዓለም ውስጥ ነው። “አዳምንም አለው፦ የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና፥ ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም በልተሃልና ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ፤”ዘፍ 3፥17 ይህች ዓለም በሰው ልጅ የተነሳ የተረገመች ዓለም ከሆነች ለሰው ልጆች ዘላለማዊ መኖሪያ አልተሰራችም ማለት ነው። ስለዚህ ከዘላለማዊ መኖሪያችን የወጣን የዚህች ዓለም መጻተኛና ስደተኛ ሆነናል ማለት ነው። ስደተኛና መጻተኛ ደግሞ ኑሮው ጊዜአዊ ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ ለውድቀት የዳረገን የሥጋችንን ምኞት ሲገልጸው እናንተ የዚህች ዓለም ስደተኛ፣ መጻተኛ ናችሁ ይለናል። “ወዳጆች ሆይ፥ ነፍስን ከሚዋጋ ሥጋዊ ምኞት ትርቁ ዘንድ እንግዶችና መጻተኞች እንደ መሆናችሁ እለምናችኋለሁ፤” 1ኛ ጴጥ 2፥11 ስለዚህ ዓለም ለኛ የስደት ሀገራችን ናት እንጂ የሰማያዊ ዜግነት መኖሪያችን አይደለችም። በዚህ ዓለም ስንኖር እንደስደተኛ እንጂ እንደባለሀገር የፈለግነውን የማድረግ መብቱ የለንም። ስደተኞችና መጻተኞች የመሆናችንን ምስክርነት ስናረጋግጥ እንደዚህ እንላለን። "ሀገራችን በሰማይ ነው።"ፊልጵ 3:20 በስደተኝነት በምንኖርባት በዚህ ዓለም ልክ ለዘለዓለም እንደሚኖር ሰው ከዓለም ጋር ተስማምተን መኖር አንችልም። ዓለም የምታቀርብልንን ግብዣ፣ መሻትና ለዓይን የሚያስጎመዠውን ነገር ሁሉ የማድረግ ፈቃድም የለንም። ምክንያቱም ስደተኛ ወይም እንግዳ በተሰደደበትና በእንግድነት በሚኖርበት ሀገር የፈለገውን መሆን ስለማይችል ነው! አባታችን አብርሃም ከከለዳውያን ዑር ወደተስፋይቱ ምድር ወደከነዓን ውጣ ተብሎ በእግዚአብሔር በታዘዘ ጊዜ ተስፋ የሰጠውን የአምላኩን ትእዛዝ ተቀብሎ ቢወጣም አብርሃም በከነዓን ዘመኑን ሙሉ ይኖር የኖረው እንደእንግዳ በድንኳን ነበር። ምክንያቱም የአብርሃም ተስፋው እግዚአብሔር የሰራትን፣ በተስፋ የሚያልማትን ሰማያዊ ከተማ ስለነበር በእድሜው ሙሉ በከነዓን እንግዳ ሆኖ ኖሯል። ዕብ 11፣ 9—10 "ለእንግዶች እንደሚሆን በተስፋ ቃል በተሰጠው አገር በድንኳን ኖሮ፥ ያን የተስፋ ቃል አብረውት ከሚወርሱ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር፥ እንደ መጻተኛ በእምነት ተቀመጠ፤ መሠረት ያላትን፥ እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ ይጠብቅ ነበርና።" ስለሆነም የእኛም የክርስቲያኖች አኗኗር በዚህ ዓለም እንደእንግዳና መጻተኛ እንጂ ተስፋችን በዚህ ዓለም እንደተፈፀመ አድርገን መሆን የለበትም። “ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም።”1ኛ ዮሐ 2፥15-16 የሥልጣንህ ማማ ከደመናው ጣራ ቢደርስ፣ ገንዘብህ እንደተራራ ቢቆለል፣ እውቀትህ በአደባባይ ቢነገር፣ ዝናህ ዓለሙን ሁሉ ቢናኝ ይሄ ሊያስመካህ አይገባም። “የሚገዙም ምንም እንደሌላቸው፥ በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ፤ የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና።”1ኛ ቆሮ 7፥31 ወደድክም ጠላህም ዓለም የሰጠችህ የውሸት ስለሆነ የሰጠችህን ሁሉ አንድ ቀን ትቀማሃለች። "ሺህ ዓመት ንገሡ" የተባሉ ሁሉ ጨርሶ እንዳልነገሱ ሆነው ከዚህች ዓለም ፊት ተሰውረዋል። ሰሎሞን እንኳን ከዚህች ዓለም በሆነች ጥበብና ብዕል/ሀብት/ የበለጸገ ሰው ምንም እንደሌለው መሆንን መርጧል። መክብብ 2፣ 10—12 ዓይኖቼንም ከፈለጉት ሁሉ አልከለከልኋቸውም፤ ልቤም በድካሜ ሁሉ ደስ ይለው ነበርና ልቤን ከደስታ ሁሉ አላራቅሁትም፤ ከድካሜም ሁሉ ይህ እድል ፈንታዬ ሆነ። እጄ የሠራቻችን ሥራዬን ሁሉ የደከምሁበትንም ድካሜን ሁሉ ተመለከትሁ፤ እነሆ፥ ሁሉ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነበር፥ ከፀሐይ በታችም ትርፍ አልነበረም። እኔም ጥበብን ዕብደትንና ስንፍናን አይ ዘንድ ተመለከትሁ፤ በፊት ከተደረገው በቀር፥ ከንጉሥ በኋላ የሚመጣው ሰው ምን ያደርጋል? ይላል። የዚህ ዓለም የሆነውን ነገር ሁሉ እየተከተሉ መኖር ንፋስን እንደመከተል ነው። ንፋስን ተከትሎ የጨበጠው እንደሌለ ሁሉ ዓለምን መከተል የከንቱ ከንቱን እንደመከተል ነው። ሰባኪው በእድሜው መጨረሻ ዘመናት የደረሰበት መደምደሚያ እንዲህ የሚል ነበር። አንተንም፣ እኔንም የሚያዋጣን፣ ሰሎሞንን የጠቀመው ምክር እሱ ነው። መክብብ 12፣ 7—8 አፈርም ወደ ነበረበት ምድር ሳይመለስ፥ ነፍስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ። ሰባኪው፦ ከንቱ፥ ከንቱ፤ ሁሉ ከንቱ ነው ይላል። (%ይቀጥላል)

Thursday, March 28, 2024

ጸጋ ምንድነው? What is Grace?

ይህ ፅሑፍ ከባለፈው ፅሑፋችን የቀጠለ ነው። በባለፈው ፅሑፋችን "የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ግንብ ሳይሆን ሰው ራሱ ነው፣ በእግዚአብሔር የተቀደሰው" ካልን በኋላ የተቀደሰ ቤተ መቅደስ መሆን የሚቻለው እንዴት ነው? በሚለው ጥያቄ ላይ ተመርኩዘን ዛሬ ደግሞ በዚሁ ዙሪያ የተወሰነውን ሐተታ እናቀርባለን። መልካም ንባብ! በጌታችን፣ በአምላካችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑ ሁሉ የኃጢአታቸውን ሥርየት አግኝተው የዘላለምን ሕይወት ይወርሱ ዘንድ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው ይጠራሉ። “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።” ዮሐ 3፥16 አብ በአንድያ ልጁ በኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ ልጆቹ እንድንሆንለት በመፈለጉ የተነሳ ከቀዳማዊው የአዳም ኃጢአት፣ ሥርየት ያገኘንበትን ሰማያዊ ስጦታ ልጅነትን ሰጥቶናል። በዚህም የተነሳ የዐመጻ ልጆች እንዳልነበርን ሁሉ (ዕብ 8:12) አባ፣ አባት ብለን የምንጠራበትን የልጅነት መንፈስ (ሮሜ 8:15) ካገኘን በኋላ ልጅነታችንን በመጠበቅ መኖር ያለብን እንዴት ነው? የሚለው ጉዳይ የግድ ሊታወቅ የሚገባው መንፈሳዊ እውቀት ነው። በዚህ ምድር ላይ ለሚኖር ሰው ሁሉ የነፍስ የኃጢአት በሮቹ ሦስት ናቸው። አምነው ባልዳኑ ሰዎች ላይ ሦስቱም የኃጢአት በሮች ክፍት ስለሆኑ በኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት እስኪያምኑ ድረስ በዚህ ፅሑፍ ስለጸጋ አስፈላጊነት ልንመክራቸው አንደፍርም። *ሦስቱ የኃጢአት በሮች ምንድናቸው? እንዴትስ ይሰራሉ? ሦስቱ የኃጢአት በሮች የተባሉት፣ 1/ ሥጋ 2/ ዓለም 3/ የወደቀው መልአክ ናቸው። ያመኑና የዳኑ ክርስቲያኖች በሙሉ እነዚህን የኃጢአት በሮች ምንነት ማወቅና ለመዝጋት የሚችሉበት አስፈላጊ ኃይላቸው ጸጋ /grace/ይባላል። የእግዚአብሔር ልጅ መሆን የቻልንበትን ድነት/ድኅነት/ ይሄንን ምድር ለቀን እስክንሄድ ድረስ አስጠብቀን መገኘት የግድ ነው። አንዴ ድኛለሁና ከእንግዲህ የፈለኩትን መሆን እችላለሁ አይባልም። ይሄንንም ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ እያለ መንፈሳዊ ማሳሰቢያ ይሰጠናል። "እንግዲህ ለምኞቱ እንድትታዘዙ በሚሞት ሥጋችሁ ኃጢአት አይንገሥ፤ ብልቶቻችሁንም የዓመፃ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለኃጢአት አታቅርቡ፥ ነገር ግን ከሙታን ተለይታችሁ በሕይወት እንደምትኖሩ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፥ ብልቶቻችሁንም የጽድቅ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ።" (ሮሜ 6: 12—13) ስለሆነም ከድነት በኋላ አማኝ ሁሉ ራሱን በጽድቅና በቅድስና መጠበቅ አለበት። ይሄን ከባድ የሚመስል ነገር ግን የመንፈሳዊ ብቃት ኃይል የሆነውና ጸጋ የተባለው የታላቅ ምስጢር እውቀት ያስፈልገዋል። ጸጋ የሚገኘው እንዴት ነው? የሚለውን ከማየታችን በፊት ጸጋ የሚከላከላቸውን ሦስቱን የነፍስ የኃጢአት በሮችን ማወቅ አለብን። የኃጢአት በሮቹን ካወቅን በሚሰጠን ጸጋ እንዴት መዝጋት እንደምንችልና አስፈላጊ እንደሆነ በደንብ ይገባናል። 1/ ሥጋ፣ የለበስነው ሥጋ ፈራሽና በስባሽ ነው። በዳግም ትንሣኤ በአዲስ መልክ እስኪለወጥ ድረስ “እኛም ሁላችን በመጋረጃ በማይከደን ፊት የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያብለጨለጭን መንፈስ ከሚሆን ጌታ እንደሚደረግ ያን መልክ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን።”2ኛ ቆሮ 3፥18 "እንለወጣለን" የሚለውን የግሪኩ ቃል"μεταμορφούμεθα" ሜታሞርፌውሜታ ይለዋል።ይህም ከአንድ ከነበረበት ሁኔታ ወዳልነበረበት ሌላ ሁኔታ መለወጥ ማለት ነው። ለምሳሌ ቢራቢሮን ለመወጥ ይመለከቷል! ነፍስ ወደተገኘችበት ወደሰማይ ስትወጣ ሥጋ የምትኖረው በዚህ ምድር ነው። ምክንያቱም ሥጋ የተሠራችው ከዚሁ የምድር አፈር ስለሆነ ነው። እግዚአብሔር ያበጀውን የምድር አፈር ሕይወት የሰጠው የሕይወትን እስትንፋስ እፍ ባለባት ጊዜ ነው። ሥጋ በራሱ ሕይወት የለውም። የሥጋ ሕይወቱ ነፍስ እስካለበት ድረስ ብቻ ነው። ከደቂቃዎች በፊት አንድ ወንበር ላይ ቁጭ ብላ ስታወራ የነበረች ሥጋ፣ ነፍስ ትቷት ቢወጣ በድን ሆና ትቀራለች። ነፍስ ከመለየቷ በፊትና ከተለየች በኋላ ሥጋ እዚያው ወንበሩ ላይ ቁጭ ብሎ ይገኛል። ልዩነቱ ነፍስ ስለሌለበት ሥጋው ሕይወት የለውም። ነገር ግን ነፍስ እስካለችበት ድረስ ሥጋ ሕይወት ስለሚኖረው የተዋቀረችበት የዐራት ባህርያቷ መሻትና አደገኛ የማይስማሙ ፍላጎቶች አሏት። መሻቷንና ፍላጎቶቿን ማወቅና መቆጣጠር ያለበት ባለቤቷ የሆነው የዳነው ሰው ራሱ ሲሆን ይህም ኃይል የእግዚአብሔር ጸጋ ይባላል። ሰው የነፍስና የሥጋ ውሁድ ሆኖ ድነቱን/መዳኑን/ መጠበቅ የሚችለው በመንፈሱ ነው። በኢየሱስ አምኖ የዳነ ሰው ሥጋውን መቆጣጠር የሚችለው ከእግዚአብሔር ጋር ባለው መንፈስ ሲሆን በየዕለት ግንኝነቱ የሚያግዘውንና የሚረዳው ጸጋ እንዲበዛለት ያደርጋል። “እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።” ዕብ 4፥16 ምክንያቱም ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ እያለ አበክሮ የሚነግረን ራሳችንን ማሸነፍ የምንችልበት ይህ ጸጋ ከውድቀት ይታደገናልና ነው። "ነገር ግን እላለሁ፥ በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ። ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና፥ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ፤ ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም።" (ገላ 5:16—17) ሥጋ ከምትበላውና ከምትጠጣው ሙቀት የተነሳ ወሲባዊ ፍላጎቷ ተቀስቅሶ ከትዳር በፊት ይሁን በኋላ ከተመኘኋት ጋር ላመንዝር ትላለች። የነፍስ መንፈሳዊ እውቀት ደግሞ “ከዝሙት ሽሹ። ሰው የሚያደርገው ኃጢአት ሁሉ ከሥጋ ውጭ ነው፤ ዝሙትን የሚሠራ ግን በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢአትን ይሠራል።” (1ኛ ቆሮ 6፥18) ብሎ ይቆጣጠራታል። ሥጋ ልስረቅ፣ ልዋሽ፣ ላታልል፣ መሻቴን ሁሉ እንድፈፅም አትከልክሉኝ ትላለች። ጾም፣ ጸሎት አድካሚ ነው። ይሄ ሁሉ ለምኔ ነው? ልቀቁኝ፣ በአምሮቴ ልኑርበት ትላለች። ለዚህም ነው ሐዋርያው ጳውሎስ "“በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም።” ሮሜ 8፥8 በማለት እቅጩን የነገረን። ለዚህም ነው፣ የሥጋን አምሮትና የመሻት በር ለመዝጋት ጸጋ የተባለው ኃይል የሚያስፈልገን። የእግዚአብሔር የበዛው ደግነቱ፣ በልጁ ሞት የዘላለምን ሕይወት ከሰጠን በኋላ የተፈጠርንበትን የሥጋ ፍላጎት መቆጣጠር የምንችልበትን ጸጋ የተባለውን ኃይልም አብሮ ሰጥቶናል። ወሲብ ለሥጋ የተሰጠ የአምላክ ፈቃድ ነው። ነገር ግን ኃጢአት የሚሆነው አለቦታውና አለጊዜው ስንጠቀመው ነው። ቅድመ ይሁን ድኅረ ጋብቻ ወሲብ ሁሉ ዐመፅ ነው። ምክንያቱም፣ “እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞቱ ዘንድ አላችሁና፤ በመንፈስ ግን የሰውነትን ሥራ ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ።”ሮሜ 8፥13 “ዳሩ ግን ማግባት ወደሚገባው ዕድሜ በደረሰ ጊዜ ስለ ድንግልናው ያፈረ ሰው ቢኖር፥ የወደደውን ያድርግ፤ ኃጢአት የለበትም፤ ይጋቡ።”1ኛ ቆሮ 7፥36 መብልና መጠጥ የሥጋ ባሕርያት ናቸው። ነገር ግን የምንበላውንና የምንጠጣውን መለየት፣ ሆዴ ይሙላ፣ ደረቴ ይቅላ ባለማለት ሥጋን ለመጎሰም በጾምና ጸሎት የምንጠመድበትን ኃይል ለማግኘት ጸጋ የተባለ ጉልበት ያስፈልገናል። “መብል ለሆድ ነው፥ ሆድም ለመብል ነው፤ እግዚአብሔር ግን ይህንም ያንም ያጠፋቸዋል። ሥጋ ግን ለጌታ ነው እንጂ ለዝሙት አይደለም፤ ጌታም ለሥጋ ነው፤”1ኛ ቆሮ 6፥13 እዚህ ላይ በኢየሱስ አምነው ያልዳኑ ሰዎች ማለትም ሥጋና ነፍሳቸው ከእግዚአብሔር ባልሆነ መንፈስ ቁጥጥር ሥር የሚገኙ ስለሆነ ከጸጋው ተለይተው ስለወደቁ ሁሉም ኃጢአቶች በነሱ ላይ አቅም ኖሮት የፈለገውን ይሰራል። “ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው፥ ዲያብሎስ ከመጀመሪያ ኃጢአትን ያደርጋልና።” (1ኛ ዮሐ 3፥8) (...ይቀጥላል%)

Tuesday, March 12, 2024

እግዚአብሔር ሰው በሠራው ቤተ መቅደስ አይኖርም!

ይህ አባባል እግዚአብሔር ሰው በሠራው መቅደስ ዛሬ ይኖራል ብለው ለሚያምኑ ሰዎች ጆሮን ጭው የሚያደርግ ቃል ነው። ነገር ግን እውነቱ እግዚአብሔር ዛሬ ሰው በሠራው መቅደስ አለመኖሩ ነው። ምክንያቱም እግዚአብሔር አዝዞት፣ ወርድና ቁመቱን ነግሮት የተሠራ ምድራዊ ቤተመቅደስ ዛሬ የለምና ነው። የቀደመችቱን የእስራኤል ቤተ መቅደስ ወርዱንና ቁመቱን፣ ስፋትና ርዝመቱን፣ ጽላቱንና ታቦቱን፣ ኤፉዱንና አልባሳተ ካህናቱን፣  መጋረጃዎቹንና ቀለማቱን፣ በአጠቃላይ የቤተ መቅደሱን ንዋያተ ቅድሳት የመረጠው እግዚአብሔር ራሱ ነበር እንጂ ምድራውያን ሰዎች አልነበሩም። ያቺ እግዚአብሔር ይገለጽባት የነበረችው ቤተ መቅደስ ዛሬ የለችም። በሙሴ የነበረው የመገናኛው ድንኳን እግዚአብሔር ራሱ ባዘዘው መሠረት የተሠራ ነው። (ዘጸ36:1) በሰሎሞን ዘመን ወደሕንጻ ቤተ መቅደስ ሲቀየር ለዳዊት ከወገቡ የሚወጣው ልጁ እንደሚሰራለት እግዚአብሔር ራሱ ተናግሮ ስለነበር እንጂ ሰሎሞን ከልቡ አንቅቶ የሰራው አልነበረም። (2ኛ ዜና 6:9) ይህ ሰሎሞን ያሠራው ቤተ መቅደስ የፈረሰበትን ታሪክ መጽሐፍ ቅዱሳችን ሲነግረን ሕዝቡ እንደአሳቡ፣ እንደፈቃዱና እንደትእዛዙ ባለመሄዱ የተነሳ የደረሰባቸውን መከራ እንዲህ ይተርክልናል።  “ሴዴቅያስም በነገሠ በዘጠኝኛው ዓመት በአሥረኛው ወር ከወሩም በአሥረኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርና ሠራዊቱ ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው ከበቡአት፤ በዙሪያዋም ዕርድ ሠሩባት።  (2ኛ ነገሥት ምዕራፍ 25ን  ያንብቡ) ቤተ መቅደሱ በናቡከደነጾር ፈርሶ፣ ንዋያተ ቅድሳቱ ተዘርፎ፣ ሕዝቦ ለባርነት ተግዞ ከተወሰደ በኋላ ኢየሩሳሌም ዳዋ ወርሷት ነበር። “እናንተንም ከአሕዛብ መካከል እበትናችኋለሁ፥ ሰይፍንም አስመዝዝባችኋለሁ፤ ምድራችሁም የተፈታች ትሆናለች፥ ከተሞቻችሁም ባድማ ይሆናሉ።”   ዘሌ 26፥33 ያለው ቃል ተፈጽሟል። ሁለተኛው ቤተ መቅደስ ተመልሶ የተሠራው በታላቁ ሄሮድስ ሲሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሞቱ በተናገረበት አንቀጽ የ2ኛውንም ቤተ መቅደስ መፍረስ ሲተነብይ እንዲህ ብሎ ነበር። “ኢየሱስም መልሶ፦ ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው።” ዮሐ 2፥19 አይሁዶችም ሲመልሱለት፣ "ወይቤልዎ ፡ አይሁድ ፡ በአርብዓ ፡ ወስድስቱ ፡ ዓመት ፡ ተሐንጸ ፡ ዝንቱ ፡ ቤተ ፡ መቅደስ ፡ ወአንተሰ ፡ በሠሉስ ፡ መዋዕል ፡ ታነሥኦ?" ይህ ቤተ መቅደስ ለማነጽ 46 ዓመት ፈጀ፣ አንተ በሦስት ቀን መልሰህ ትሰራዋለህን? ብለው ጠይቀውታል። ዋናው መልእክቱ ለሰውነቱ ቤተ መቅደስ ቢሆንም ከሕንጻው ቤተ መቅደስም መፍረስ ትንቢት ነበር። ይህ በሄሮድስ የታነጸው ሁለተኛው ቤተ መቅደስ 46 ዓመት የፈጀ ሲሆን ሰሎሞን ካሰራው ቤተ መቅደስ የተለየ ነበር። ምክንያቱም እግዚአብሔር ያዘዘው ቃል ሥርዓት የሚፈጸምበትና የሚከናወንበት ቤተ መቅደስ አልነበረም። ታቦቱ የለም። ታቦቱና ጽላቱ በሌለበት የእግዚአብሔር ክብር አይታይም ማለት ነው። የቤተመቅደሱ ሥርዓት የሌለበት፣ ታቦቱና ጽላቱ የማይገኝበት፣ እግዚአብሔርም በሁለቱ ኪሩብ መካከል በሚታየው የክብር ደመና መካከል  ተገልጾ በአሮን የክህነት ማዕረግ ተሹመዋል የተባሉትንና በወቅቱ ሊቀካህናት የነበሩት ሐናንና ቀያፋን የሚያናግርበት ቤተ መቅደስ አልነበረም። የእግዚአብሔር ድምጽ የሚሰሙበት ቤተ መቅደስ ሆኖ ቢሆን ኖሮ ስለኢየሱስ ድምጽ ይመጣላቸው ነበር። ከዚያ ይልቅ በዚህ በሄሮድስ ቤተ መቅደስ አደባባይ የሕዝቡ የኃጢአት ሥርየትና የደኅንነት መስዋዕት ሳይሆን ይቀርብ የነበረው የገንዘብ ለዋጮችና የርግብ ሻጮች ገበታ ነበር። ገንዘብ ለዋጮቹ ለበዓል ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡትን ሰዎች ገንዘብ የሚመነዝሩ /money exchangers/ ሲሆኑ ርግብ ሻጮቹ ደግሞ ለበደል ሥርየት የሚሆኑ ርግቦችን ለሚመጡ ለእንግዶች የሚሸጡ የነጋዴዎች አደባባይ ሆኖ ነበር። ይህ ተግባር እግዚአብሔር አዝዞ በተሠራው በሰሎሞን ቤተ መቅደስ አደባባይ ተደርጎ ቢሆን ኖሮ ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ የሚለውን ቅጣት ያስከትል ነበር። ኢየሱስም፣ በዚህ ድርጊታቸው በተበሳጭቶ “ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተጽፎአል፥ እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት አላቸው።” (ማቴ 21፥13) ይህ ቤተ መቅደስ እግዚአብሔር የማይከብርበት፣ ሥርዓተ መቅደሱ የማይፈጸምበት ስለነበረ መፍረስ ነበረበት። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ቤተ መቅደሱ እንደሚፈርስ በተናገረው ቃል መሠረት ባረገ በዐርባኛው ዓመት፣ የሮማው ንጉሥ ጥጦስ በ70 ዓ/ ምህረት ገደማ ካፈረሰው በኋላ ላለፉት 2000 ዓመታት ቤተ መቅደስ የሚባል ታሪክ የለም። ከዚያ በኋላም  እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ስሩልኝ ያለው የተለየ ሕዝብና ሀገርም የለም። የቤተመቅደሱን ስፋትና ቁመት፣ የንዋያተ ቅድሳቱን ዝርዝርና ዓይነት የነገረው አንድም ሕዝብ ስለሌለ እግዚአብሔርን ለመገናኘት የምንሄድበት ቤተ መቅደስ በዓለም ላይ የትም ሀገር የለም። ልባቸው ያፈለቀውን፣ ኅሊናቸው ያሰበውን፣ ያላቸው የገንዘብ አቅም የፈቀደላቸውንና በሕንጻ አሠሪ ኮሚቴ በተፈቀደ ዲዛይን በተሠራ ሕንጻ ውስጥ እግዚአብሔርን ይገባበት ዘንድ በወይራና በቅብዐ ሜሮን ግንቡን ረጭተው እግዚአብሔር ሆይ ቀድሰነዋልና ና ግባበት እያሉ ሲጣሩ ውለው ቢያድሩ በዚያ በሰዎች ሃሳብ ሕንጻ ውስጥ እግዚአብሔር የለም። እግዚአብሔር እንደዚያ አድርገው እንዲሰሩለት ያዘዘው ሕዝብና ሀገር ስለሌለ፣ ሰዎች በልባቸው መሻት በሰሩት ቤተ መቅደስ ውስጥ በተሽሞነሞነ ጥሪና ልመና  የሚገባ አምላክ አለ ብለው የሚያስቡ ከሆነ ተሳስተዋል። የሚገባ ካለም ሌላ መንፈስ ይሆን ይሆናል እንጂ የሰማይ አምላክ አይደለም። ሐዋርያት 17፣ 24—25 "ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነውና እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም፤ እርሱም ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ ይሰጣልና አንዳች እንደሚጎድለው በሰው እጅ አይገለገልም"። አሁን ቤተ መቅደሱ አንተ ነህ። ይሄን አንተ ቤተ መቅደስ የሆነው ሰውነትህን አቆሽሸህ ስታበቃ ሕንጻውን ቀድሼዋለሁ ብትል ስህተትም፣ ክህደትም ነው። ለዚህም ነው፣ የቆሸሹ፣ ከኃጢአት ያልተመለሱ፣ ለመመለስም ፍላጎት የሌላቸው ዐመጸኞች ቤተ መቅደስ በሚሉት ሕንጻ ውስጥ ተሰግስገው መደበኛ ኑሮአቸውን የሚኖሩት። እግዚአብሔር እኔ ውስጥ የለም፣ እዚያ እኔ በሠራሁት ሕንጻ ውስጥ አምላኬ ስላለ ጥዋትና ማታ እየሄድኩ ኃጢአቴን ይቅር እንዲለኝ እነግረዋለሁ ብትል ሕንጻ ውስጥ ቁጭ ብሎ የአንተን ኃጢአት የሚሰማ የሰማይ አምላክ ስለሌለ መጀመሪያ ራስህን ቀድስ። ኢየሱስ ከኦሪቱ ቤተ መቅደስ አገልግሎት ይልቅ ወደበለጠው የአዲስ ኪዳን አገልግሎት የመጣው አንተን አማኙን ለመቀደስ እንጂ በድንጋይ የተሠራ ቤት ለመቀደስ አይደለም። “ኢየሱስም መለሰ አለውም፦ የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን።”   — ዮሐንስ 14፥23 እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ ስለተባለ ቤተ መቅደሱ አንተ ራስህ ነህ። ቃሉን ጠብቅ፣ አብ ይወድሃል። ወልድም ይወድሃል። አንተም መኖሪያው ትሆናለህ። አንተ መኖሪያው ካልሆንክ የእግዚአብሔር መኖሪያ የሆነ ሌላ ሕንጻ የለም። ሕንጻው አንተ ነህ። ይሄንን ሕንጻ የሠራው ኢየሱስ ነው። (በቀጣይ ፅሑፋችን "ሰው የእግዚአብሔር መኖሪያ ሕንጻ መሆን እንዴት ይችላል?") የሚለውን እንመለከታለን።