Thursday, October 30, 2014

«የሚያስፈራሩን ከሆነ ወደየገዳማችን እንሄድልዎታለን!» አባ አብርሃም፤ «ወደየትኛው ገዳምዎ? ለመሆኑ ገዳም ያውቃሉ?» ፓትርያርክ ማትያስ


ቅዱስ ፓትርያርኩ ስለማኅበረ ቅዱሳን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለውን የፈረጠመ ጡንቻ ሲገልጹ «የፈርዖን አገዛዝ» ነበር ያሉት። ማኅበረ ቅዱሳን የደርግ መንግሥት መውደቅ የወለደውና በዓለት ስንጥቅ መካከል የበቀለ ዛፍ ነው። ዓለቱን አንቆ ይዞ በላዩ ላይ የለመለመ ነገር ግን ከአለቱ መካከል ከወጣ ኅልውና የሌለው ሥር አልባ መሆኑም እርግጥ ነው።  ይህን ሽብልቅ ገብቶ የፈረጠመውን ዛፍ ከማነቃነቅ ባለፈ ከሥሩ ነግሎ ለመጣል ጊዜና ሰው የተገናኙት ዘንድሮ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ዘመነ ፕትርክና ነው። ዋና ዓላማውም ከመሠሪና ስውር የቤተ ክርስቲያን ውስጥ ወረራ ብቸኛዋን ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያንን መታደግ መሆኑን ቅዱስ ፓትርያርኩ በግልጽ ደጋግመው ተናግረዋል።

 «ጊዜ ገቢር ለእግዚአብሔር» እንዲል መጽሐፉ ዘንድሮ ቀኑ ደርሶ ማኅበረ ቅዱሳንም ሆነ በማኅበረ ቅዱሳን እስትንፋስ የሚንቀሳቀሱ ተላላኪ ጳጳሳቱ የቤተ ክርስቲያኒቱን እጅ ጠምዝዘው ለማስረከብ ደፋ ቀና የሚሉበት ዘመን ግብዓተ መሬቱ እየተፈጸመ ይገኛል። ከትናንት በስቲያ በነበረው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ ላይ የጉድ ሙዳይ የሚባለው ሊቀጳጳስ አባ አብርሃም በአቡነ ጳውሎስ ላይ የለመደ አፉን በአቡነ ማትያስ ላይ በመክፈት «የመንግሥትን ኃይል ተማምነው አያስፈራሩን፤ የሚያስፈራሩን ከሆነ ሲኖዶሱን ለቀንልዎ ወደየገዳማችን እንሄድልዎታለን» ብሎ እስከመናገር የደረሰ ሲሆን ቅዱስ ፓትርያርኩም ለሱም ይሁን ለቢጤ ወንድሞቹ ራስ ምታት የሆነ ምላሽ በመስጠት ዝም ጭጭ እንዲል አድርገውታል።

«ኧረ ለመሆኑ የእርስዎ ገዳም የት ነው? እስኪ ንገሩኝ የትኛው ገዳም ነው ያገለገሉት?  ደግሞስ እኔ አባ ማትያስ ለእርስዎ አንሼ ነው የመንግሥትን እርዳታ የምጠይቀው? ምነው! ቤተ ክርስቲያን እንደተሸከመችዎ አውቀው አርፈው ቢቀመጡ?!» በማለት የጳጳሱን ጉድ ጫፍ ጫፉን በመናገር አፉን እንዳስያዙት የውስጥ ምንጮች ገልጸዋል።

ተመሳሳይ በሽታ የነበረባቸው የማኅበሩ ጳጳሳት የጓደኛቸው ጉድ ፊታቸው ሲነገር በመስማታቸው የተሸማቀቁ ሲሆን አንዳንዶቹ በብስጭት ጉባዔውን ለመረበሽና ለምን ተነካን? የማለት ያህል ሲቁነጠነጡ ታይተዋል። ይሁን እንጂ ከቅዱስ ፓትርያርኩ የተሰጣቸው ምላሽ «ምን አለፋችሁ? ዘንድሮ ማኅበረ ቅዱሳንን በሕግና በሥርዓት ሳላስገባው አልተወውም!» በማለት ቁርጡን እንደነገሯቸው ተያይዞ የደረሰው ዜና ያስረዳል።
ቀደም ሲል የማኅበሩ ደጋፊ የነበሩ አንዳንድ ጳጳሳት ግን የፓትርያርኩን የጠነከረ አቋም ያጤኑ በሚመስል መልኩ ተዐቅቦን መርጠዋል። እነአባ ኤልያስ፤አባ ሉቃስ፤ አባ ቀውስጦስና በእድሜ ገፋ ያሉት ጳጳሳት ጥቂት የታገሉ ቢሆንም ከአባ ገብርኤል በስተቀር ወሎዬዎቹ ሊቃነ ጳጳሳት ግን ዝምታን መምረጣቸው ተዘግቧል። ምናልባትም «እነዚህ እኮ መንግሥትን ከአንድ ክፍለ ሀገር፤ ወደ ሌላ ክ/ሀገር ማዛወር የቻሉ ናቸው፤ ዛሬ አቤሲዲ ቆጥረውማ ማን ይችላቸዋል?» የተባለው ኃይለ ቃል ሳይከነክናቸው የቀረ አይመስልም።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የተደረሰበት ውሳኔ እንደሚያሳየው ማኅበረ ቅዱሳን አፈንግጦ ከወጣበት የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ተመልሶ በሥሩ እንዲተዳደር፤ በቤተ ክህነቱ ሞዴላ ሞዴሎች እንዲጠቀም፤ እስከዛሬ የፈጸመው የገቢና ወጪው አጠቃላይ ሂሳብ በቤተ ክህነት ባለሙያዎች እንዲመረመር፤ አዲስ በሚረቀቀውና ፀድቆ በሚሰጠው የመተዳደሪያ ደንብ በቤተ ክህነቱ ቁጥጥር እንዲንቀሳቀስ፤ ማንኛውንም ሥራ ቤተ ክህነቱን እያስፈቀደ እንዲፈጽም የሚያስገድደው ውሳኔ የተላለፈበት መሆኑም ተዘግቧል። ድንቅ ውሳኔና ተገቢነቱም ትክክለኛ እንደሆነ አስምረንበታል።

 ድሮም በዚህ ዓይነቱ ልክና ገደብ ባለው አካሄድ ይስራ ከመባሉ ውጪ ይፍረስ፤ ይውደም ያለው  ማንም አልነበረም። ነገር ግን ማኅበሩ ያለውን ዓላማ ከግብ ለማድረስ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕግና ሥርዓት ዘለለ መልኩ በአባላት ጳጳሶቹ በኩል እንደሚመቸው አጣሞ በማስቀረጽ መንቀሳቀሱ እንዲገደብ ካለመፈለጉ የተነሳ ወደመላተም አድርሶታል።

የሚደርስበትን ጥላቻና ተቃውሞ ለመሸፈንና በቅዱስ ሲኖዶስ ሥር ለመሸሸግ በመፈለግ «ሲኖዶሱ ቀርጾ ከሰጠኝ መተዳደሪያ ደንብ ውጪ አልንቀሳቀስም» እያለ መደዴ አካሄዱን ሕጋዊ ለማስመሰል ይፈልጋል። እንደነአባ የጉድ ሙዳይ አባላቱ የሰጡትን ገደብ አልባ መተዳደሪያ ደንብ በማሞካሸት በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ የተጻፈ ለማስመሰል መሞከሩ ራሱን ከሚያታልልበት በስተቀር ማንንም ማሞኘት አይችልም። «የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው» በሚል ስልት የሚያጨበጭቡለት ጥቂቶች ባይታጡም አብዛኛው የቤተ ክህነት ሰው ዓይንህን ላፈር ካለው ውሎ አድሯል።
ጳጳሳቱ በማኅበረ ቅዱሳን አዚም ነፍዘው ቤተ ክርስቲያኒቱን አጨብጭበው ለማስረከብ በደረሱበት ሰዓት ፓትርያርክ አባ ማትያስ ደርሰው ልጓም አልባ ሩጫውን ገደብ ሰጥተውታል። ምናልባትም በማኅበሩ ግፍና መከራ የወረደባቸው ማኅበረ ካህናት፤ በኃጢአት ገመናቸውን እየገለበ የሚያሳድዳቸው ማኅበረ መነኮሳትና በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት ያለቀሱት ልቅሶና ያፈሰሱት እንባ ከመንበረ ጸባዖት ደርሶ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የመጣ ፍርድ ይሆን ይሆናል።
ወደፊትም ማኅበሩ ጊዜ በመግዛት የራሱን ሌላ አማራጭ ለመፍጠር እስትንፋሱን ያሰባስብ ይሆናል እንጂ አሁን በሚሰጠው ሕግና ሥርዓት ይተዳደራል ተብሎ አይጠበቅም። ለሁሉም አሁን የተያዘው የፓትርያርኩ እርምጃ በቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት ዘንድ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ያለው ነው።
 ሁላችንም ይበል ብለናል!

Wednesday, October 29, 2014

«የነብር ጅራት አይዙም፤ ከያዙም አይለቁም!»

በጥያቄ እንጀምር! ማኅበረ ቅዱሳን ይፍረስ፤ ይበተን አልተባለም። ወደሕግና ሥርዓት ይገባ ነው እየተባለ ያለው። ማኅበሩ ይሁን ማፈሪያ ሊቃነ ጳጳሳቱ በዚህ አባባል የሚናደዱት ለምንድነው? «ደረጃ፤ ቦታና መጠን ተበጅቶለት መቀጠል ይገባዋል» የሚለውን የማኅበረ ካህናቱን ድምጽ ለመስማት ያለመፈለግ ምክንያት ከምን የመነጨ ነው? እኮ አሳማኝ ምክንያት አቅርቡ!!
 አለበለዚያ «እኛ ሊቃነ ጳጳሳት ስለሆንና ጉባዔው በድምጽ ብልጫ ስለሚመራ የአድማ እጃችንን ቀስረን ማኅበረ ቅዱሳን የሚደሰትበትን እንወስናለን» የሚለው ፈሊጥ የተበላ ዕቁብ ነውና ዘንድሮ አይሠራም።  በትክክል ዘንድሮ አልሠራም፤ አይሠራምም።

 ሊቃነ ጳጳሳቱ በየአህጉረ ስብከታቸው የካህናት ማሰልጠኛ ኮሌጆችን በመክፈት፤ የሴሚናሪ ትምህርት ቤቶችን በማስፋፋት የመንፈሣዊና ሳይንሳዊ እውቀት ባለቤት እንዲሆን ለቤተ ክርስቲያን እድገት እንዲሁም ፤ ለህብረተሰቡ ደግሞ በአካባቢ ልማት ተሣትፎ፤ በመንገድ ሥራ፤ በጤና ጣቢያና በንጹህ ውሃ አቅርቦት ተግባር ላይ በመትጋት ያንን ድሃ ምእመን ሕዝባቸውን መርዳት፤ መደገፍና በሥራ ማሳየት ሲገባቸው ተሸፋፍነው በመቀመጥ ሠራተኛ ሲቀጥሩ፤ ሲያባርሩ፤ ደመወዝ ሲቀንሱና ከቦታ ቦታ ሲያዘዋውሩ እድሜአቸውን ይፈጃሉ። ንቡረ እድ አባ ገ/ማርያም የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ በነበሩበት ጊዜ ሊቀ ጳጳስ አባ ቀውስጦስ ከራሳቸው ብሔርና ጎጥ ብቻ የመጣውን እየለዩ ለመቅጠር ሲታገሉ በተነሳ አለመስማማት የሙስና አፍ የዘጉትን ሥራ አስኪያጅ አይታዘዘኝም በሚል ውንጀላ ከስሰው እንዲቀየሩ ማስደረጋቸው አይዘነጋም። አሁን ደግሞ አባ ቀውስጦስ «ሞቴን ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር ያድርገው» እያሉ ለያዥ ለገራዥ እያስቸገሩ እንዳሉ ይሰማል። ለምእመናን ልጆቹ በእኩል ዓይን አባት ይሆን ዘንድ ቃል የገባ ሊቀ ጳጳስ በዘረኝነትና በጎጠኝነት ሲታወር ሥጋውያኑማ እንዴት ይሆኑ?
የጎጃሙ ለጎጃም፤ የወሎው ለወሎ፤የጎንደሩ ለጎንደር፤ የሸዋው ለሸዋ የዘረኝነትን ገመድ የሚጎትት ሊቀ ጳጳስ ቤተ ክርስቲያንን እያወካት እንደሚገኝ ፀሀይ የሞቀው፤ አገር ያወቀው ጉዳይ ነው። እነማን? እንዴትና የት? ለሚለው በማስረጃ የተደገፈ ዝርዝር ማቅረብ ይቻላል።
ከብዙ መልካምና ጥሩ ነገሮቻቸው መካከል ሙት ወቃሽ አያድርገንና ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የፈጸሟቸው ስህተቶች ለጵጵስና ማዕረግ ቀርቶ ለአንዲት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪነት የማይበቁ ሰዎችን የመሾማቸው ጉዳይ ትልቁ ስህተታቸው ነበር። እሳቸውም በሕይወት ሳሉ ሊሾሙ የማይገባቸውን ሰዎች በመሾማቸው ይጸጸቱ እንደነበር እናውቃለን። ዛሬም የዚያ ስህተት ውጤት የሆኑ ሊቃነ ጳጳሳት ስንት ሥራና አገልግሎት ባለባት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለአንድ ማኅበር ጥብቅና ቆመው «ሞታችንን ከማኅበረ ቅዱሳን ጓሮ ያድርገው» ሲሉ ይታያሉ። ከተመቻቸውና ከሞቃቸው ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር ሞታችንን ያድርገው ያሉት ይሁንላቸው። ነገር ግን ማኅበረ ቅዱሳን ራሱ ወደሕግና ሥርዓት ካልገባ መሞቱ አይቀርም። ያን ጊዜ ምን ሊውጣቸው ይሆን?

ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ የማኅበረ ካህናቱ ሙሉ ድጋፍ እንዳላቸው ይታወቃል። ማኅበሩን ሥርዓተ አልበኛ የሚያሰኙ ተግባራቱ የማኅበሩን የመጨረሻ እድል ይወስናሉ። የጳጳሳቱ ጩኸት መነሻውና መድረሻው ከጎጥ፤ ከጥቅምና ከፍርሃት የመነጨ እንጂ ለቤተ ክርስቲያን ከማሰብ አይደለም። ምክንያቱም ማኅበረ ቅዱሳን ሳይኖር ቤተክርስቲያን ነበረችና። ማኅበረ ቅዱሳንም ባይኖር ትኖራለች።  ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በሊቀ ጳጳሳቱ አድማ እንዳይፈቱ አደራችን ጥብቅ ነው። ከሕግና ከኃይል በላይ የሚሆን ማንም የለምና በበሉበት ለሚጮኹት ቦታ ሳይሰጡ ሥርዓትና ደንብ የማስገባት እርምጃዎትን ይቀጥሉ ዘንድ አበክረን እናሳስባለን። ዘንድሮን ነካክተው ከተዉት ይሄ የተደራጀ አውሬ እስከመጪው ዓመት ይበላዎታል። አቡነ ጳውሎስንም የበላው እንደዚሁ ነው። ዕድሜአቸውን በዐሥር ዓመት አሳጠርነው እያሉ የሚፎክሩት እስከየት የመጓዝ እልክ እንዳላቸው ማሳያ ነውና ይጠንቀቁ። ክፉ ሥራቸውን የሚጸየፍ እግዚአብሔር ይረዳዎታል።

«የነብር ጅራት አይዙም፤ ከያዙም አይለቁም!»






Friday, October 24, 2014

የቅዱስ ፓትርያርኩ የሲኖዶስ ጉባዔ መክፈቻ ንግግር (እዚህ ይጫኑ)



ሐራ ተዋሕዶ የተባለው የማኅበረ ቅዱሳን ቀኝ ክንፍ መካነ ጦማር ቅዱስ ፓትርያርኩ በሲኖዶሱ መክፈቻ ላይ ባቀረቡት ንግግር ተወገዙ፤ ውሳኔም ተላለፈባቸው ሲል ከብራዘር ሁድ ጳጳሳቱ ጋር ያለውን የምስጢር ትስስር በሚያሳብቅ መልኩ ዘገባውን አቅርቧል። ማኅበሩ የሲኖዶስ አባል ሆኖ በጉባዔው ላይ በመገኘት የጉባዔው ተካፋይ መሆን አይጠበቅበትም። በሱ ምትክ የጉባዔውን እስትንፋስ እየለኩ ምስጢር የሚያካፍሉ አባላት የሆኑ ጳጳሳት እንዳሉት ይታወቃል። ማኅበሩን ያናደደውና ደረጃውን ያልጠበቀ የፓትርያርኩ የመክፈቻ ንግግር ያሰኘው ነገር ቅዱስ ፓትርያርኩ ከመቼውም ጊዜ በላይ ስለማኅበሩ ቀጥተኛ አቋም ይዘው በመክፈቻ ንግግራቸው ላይ አበክረው ስላሳሰቡ ከደረሰበት ጭንቀት የተነሳ መሆኑ ይገባናል። የፓትርያርኩን ንግግር ደረጃ የሚያወጣና ማስጠንቀቂያ የሚሰጥ እሱ ማነው? አባ ሉቃስ? አባ ማቴዎስ?
በዚህ ዓመት ስለማኅበረ ቅዱሳን አቅምና ጡንቻ የመጨረሻ ገደብ ካልተደረገበት የነብርን ጅራት ይዞ እንደመልቀቅ ይቆጠራል። ጳጳሳቱም ቢሆን ክብራቸውን ካልጠበቁና ለማኅበሩ በአድማ ተሰልፈው ከቆሙ በተመዘገበ ግለ ታሪካቸው ቦታ ቦታቸውን እንዲይዙ ሊደረግ ይገባል። በአጭር ቃል ባለትዳሮቹና የልጅ አባቶቹ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ ማዕረግ ወርደው ከምዕመናን አንድነት ሊቀላቀሉ የሚገባው ዓመትም ይህ ዓመት ነው። ሳይገባቸው ከፍታ ላይ የተቀመጡ ሰዎች ባለበት አስተዳደር ምን ጊዜም ሁከት፤ ክፍፍልና እርስ በእርስ መለያየት መኖሩ እርግጥ ነው።
ይህ ዓመት ቤተ ክርስቲያንን የሚያምሱ፤ በአድማ የሚወስኑ ሰዎች ሰልፍ የሚሰበርበት እንዲሆን እንመኛለን።