Saturday, February 15, 2014

ፓትርያርኩ ማኅበረ ቅዱሳን የጠራውን ሀገራዊ የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ጉባዔ ማገዳቸው ትክክል ነው!!


«መታገድ» የሚለውን ቃል በአሉታዊ ምልከታ ለማራገብ ካልተሞከረ በስተቀር ባለእባብ ዓርማው ማኅበረ ቅዱሳን የጠራውን ስብሰባ መታገድ በተመለከተ የሚያሳየው  የትርጓሜ እውነታ ግን በትክክለኛነቱ ተቀባይነት ያለው ውሳኔ ነው። ለዚህም ከበቂ በላይ ምክንያቶች አሉን።
1/ ማኅበረ ቅዱሳን የተባለውን ማኅበር ቤተ ክርስቲያኗ ያላቋቋመችውና ከብላቴ ጦር ምላሽ በጎ ፈቃደኞች የመሠረቱት ሲሆን የቤተ ክርስቲያኗ የውክልና ድርሻ ስለሌለው የትኛውንም የቤተ ክርስቲያን አባል በመጥራት መሰብሰብ አይችልም።
2/ ማኅበረ ቅዱሳን በጥቂት ደጋፊዎቹ ተነስቶ የሲኖዶስ አባል የሆኑትን ጳጳሳት በመጠምዘዝ፤ በማስፈራራትና በጥቅማ ጥቅም በማታለል ለራሱ ብቻ የሚጠቅመውን መተዳደሪያ ደንብ በማስጸደቅ ቤተ ክርስቲያንን ተለጥፎ በሕይወት ለመቆየት ከመቻሉ በስተቀር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንደልማት ማኅበር ወይም እንደ በጎ አድራጊ ድርጅት ወይም እንደመንፈሳዊ ተቋም የመሠረተችው አይደለም። ስለዚህ አሀዳዊትና ሐዋርያዊት በሆነችው የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሌላ ማኅበር ሊኖር ስለማይገባው ማኅበረ ቅዱሳን ማንንም የቤተ ክርስቲያን አባል በማደራጀት መንቀሳቀስ አይችልም።
3/ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከቅዱስ ሲኖዶስ አንስቶ በሊቃነ ጳጳሳት የሚመራ የሀገረ ስብከት ጽ/ቤቶች በተዋረድ ያላት ተቋም ሆና ሳለ በሽብልቅ የገባው ማኅበር ይህንን የመዋቅር ሰንሰለት በጥሶ ለራሱ ዓላማና ግብ በመንፈሳዊ ካባ ተጠልሎ ስብሰባ የማካሄድ፤ የመጥራት፤ የማደራጀት፤ የመምራት ስልጣን የለውም።

4/ ማኅበረ ቅዱሳን በልማት ማኅበር ወይም በእርዳታ ድርጅት ወይም ራሱን በቻለ መንፈሳዊ ተቋምነት ወይም በሌላ መሰል ስያሜ የሀገሪቱ ሕግ በሚፈቅደው አግባብ እውቅና አግኝቶ የተፈቀደለትንና የሚችለውን ሀገራዊና መንፈሳዊ ዓላማ ከማከናወን በስተቀር በሲኖዶስና በማኅበር የሚመራ ሁለት አስተዳደር ቤተ ክርስቲያኒቱ መሸከም የለባትም። ስለሆነም የፓትርያርኩ እግድ የስልጣን ተዋረድንና ኃላፊነትን ያገናዘበ በመሆኑ ትክክለኛ ውሳኔ ነው።
5/ ለወደፊትም ቢሆን ቁርጡ በታወቀ ቁመና የማኅበረ ቅዱሳን ማንነት መታወቅ አለበት። ስለሆነም እጅ እየጠመዘዘ ያስጸደቀው መተዳደሪያ ደንብ ቀሪ ሆኖ በራሱ ግዘፈ አካል፤

   ሀ/ በሰንበት ትምህርት ቤቶች አወቃቀር የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ማኅበር ለመሆን ከፈለገ ያለውንና ያፈራውን ሀብትና ንብረት ለቤተ ክርስቲያኒቱ በማስረከብ ለሰንበት ተማሪዎች በተሰጠው የቤተ ክርስቲያኒቱ ተቋማዊ መመሪያ መሰረት መተዳደር አለበት።
  ለ/ የሰንበት ትምህርት ቤቶችን ለማደራጀት በወጣው ህገ ደንብ የመተዳደር ፈቃደኝነቱ ከሌለው የአባልነት ምልመላ፤ የገንዘብ አቅምን የማጎልበት፤ አስተዳደራዊ መዋቅሩን የመዘርጋትና የማንነት አቅም ማጎለበቱ ከቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ውጪ የመሆን አዝማሚያ እንዳለው እያየን ነውና ሀገሪቱ በምትሰጠው መብት በፍትህ ሚኒስትር ተመዝግቦ ሊንቀሳቀስ ይገባዋልና ቅዱስ ፓትርያርኩ የጀመሩትን መልክ የማስያዝ ጅማሮ ከፍጻሜ እንዲያደርሱ እንጠይቃለን።

Monday, February 10, 2014

አዲሱ የሃይማኖት ህግና የሀገሪቱ ህገመንግስት!



 ( ጽሁፍ በሰሎሞን )
(ማስታወሻ ከደጀ ብርሃን) አንዳንዶች እንደሚሉት ሳይሆን ኢትዮጵያ ከሉላዊው ዓለም ውጪ ካለመሆኗም በላይ በአፍሪካ ቀንድ እንደመገኘቷና ካላት የረጅም ዘመን ታሪክ አንጻር ከአሸባሪነት አደጋ ነጻ አይደለችም የሚለውን ሚዛናዊ ስፍር እንቀበላለን። በተለይም ሃይማኖታዊ ፍልስፍና በሚንጠው የክፍለ ዘመኑ የጽንፈኝነት አተያይም ለሀገራችን የሚበጀውን የሰላም ጎዳና ሁሉ መደገፋችን እውነት ነው። ይህንን ሀገራዊ ሰላም ለማስጠበቅ መንግሥት የሚያከናውናቸው ከእምነት ተቋማት ጋር የሚያደርገው የውይይት፤ የመረዳዳትና የጋራ ግንዛቤን የመያዝ የጋራ ኃላፊነት ስምምነቶችንም በበጎነቱ እንጠቅሳለን። ከውይይትና ከጋራ ግንዛቤ ስምምነቶቹም ባሻገር ሕጋዊ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት ጽንፈንነትንና አክራሪነትን ለመከላከል የሚያስችሉ የሕግ አግባቦችንም መቅረጹ ከአስፈላጊነቱ የሚጠቀስ እንደሆነም እንረዳለን። ነገር ግን ፍርሃትን ለማስቀረትና ጽንፈኝነትን ለመዝጋት እንችላለን በሚል ጥቅል እሳቤ የተነሳ መንግሥት ብቻውን ይበጀኛል የሚለውን የሕግ አግባብ ለመቅረጽና ለመተግበር የሚያደርገው ጥረት አያዋጣም ብቻ ሳይሆን ውጤቱ እጅግ አደገኛ ሊሆን እንደሚችል አስቀድሞ አለመገመቱ ያሳስበናል። ሕግ የሚቀረጸው በህጉ ተጠቃሚ የሚሆነውን ሕዝብ ሰላምና ደህንነት በማረጋገጥ ማኅበራዊ ዋስትናውን ማስቀጠል እስከሆነ ድረስ ከዚያ ሕዝብ በተለይም ስስ ከሆነው የሕዝብ የእምነት ስሜት ውጪ ሕግ ለማውጣት መሞከር ከጠቃሚነቱ ጎጂነቱ ስለሚያመዝን መንግስት የሃይማኖት ተቋማትን አስመልክቶ ያወጣውን ሕግ ለማጽደቅ የሚያደርገውን መጣደፍ ቆም ብሎ እንዲመለከት ለማሳሰብ እንወዳለን። በሁሉም ነገር ላይ የሁሉም ስምምነት ይኖራል ተብሎ ባይጠበቅም ሃይማኖትን በተመለከተ የሚወሰዱ የህግ አግባቦች ግን የእምነቱ ባለቤቶች ያደረጉት አብላጫው የጋራ ውይይትና ስምምነት ይበልጥ ውጤታማ ስለሚሆን ሕግ ከማጽደቅ በፊት ውይይቱ ይቅደም እንላለን።)  ከዚህ በታች ያለው ጽሁፍ «በኢትዮ-ክርስቲያን መረጃ መረብ በአቶ ሰሎሞን የቀረበና የእምነት ተቋማትን የመመሪያ ረቂቅ በህገ መንግሥቱና በማኅበረሰባዊ ምልከታ ያለውን የፍትህ ሚዛን ያሳያልና ሳይሰለቹ እንዲያነቡት ጋብዘንዎታል።
መንግሥት ሕገ-መንግስቱን ሊያከበር ይገባል! (ከእምነት ቤቶች) 
  በፌደራል ጉዳዮች ሰብሳቢነት ከተለያዩ ቤተእምነቶች የተሰባሰቡ ተወካዮች በጉዳዩ ላይ እንድንወያይ ስንጠየቅ ይህ  የሀገሪቱን ህገመንግስት ይቃረናል እኛም እዚህ ተወክለን የመጣነው ለሌላ ጉዳይ እንጂ በህግ ላይ ህግ ለማውጣት አይደለም ብለን አጀንዳው እንዲመለስ አድርገናል(ከተስባሲቢዎች አንዱ) 
“ኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መርጠው በላኳቸው ተወካዮቻቸው አማካይነት ሕዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም  የኢትዮጵያ  ፌደራላዊ  ዲሞክራሲያዊ  ሪፐብሊክ  ሕገ  መንግስትን  በአዋጅ  ቁጥር  1/1987 ያጸደቁት”  ሕገ  መንግሥትን  መንግሥት በተለያዩ  ጊዜያት  እየጣሰ  መሆኑን  የሀገሪቱ  የተለያዩ ህብረተሰቦችና ተቋማት መናገር ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡  
 በቅርቡ  ደግሞ  “በፌደራል  ጉዳዮች  ሚኒስቴር  የተዘጋጀ  የሃይማኖት  ድርጅቶች  እና  ማኅበራትን” አስመልክቶ የወጣው “መመሪያ” የተጠቃሻቹ የሃይማኖት  ድርጅቶች  እና  ማኅበራትን  በበቂ  ሁኔታ ሃሳባቸው  ሳይሰማና  በማያውቁት  ሁኔታ  ሥራ  ላይ  በማዋሉ  ምክንያት  የሃይማኖት  ድርጅቶችና ተቋማትን   በተለይም  ደግሞ  የክርስትና  እምነት ተከታዩ ኅብረተሰቡን በእጅጉ የማጉረምረሚያ ሃሳብ ከመሆን አልፎ መንግሥት መመሪያውን በድጋሚ እንዲያስብበት በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያና  ሃይማኖት  የአምስት  ሳንቲም  ግልባጮችና  ፈጽሞ  ሊለያዩ  የማይችሉ  መሆኑን  መንግሥት በ1997 ዓ.ም ያወጣው  እስታስቲክስ  62.8  ከመቶ  ክርስቲያን፣  33.9  ከመቶ  ሙስሊም  ፣  2.7  ከመቶ ባህላዊ እምነት ተከታይ  ፣ 3.3 ከመቶ ሌሎች  እና ስለ እምነታቸው መልስ ያልሰጡ ደግሞ 0.6 ከመቶ መሆኑን ባሳየው  እስታስቲካዊ  መረጃ  አረጋግጣአል፡፡ ይህ እስታስቲካዊ  አሃዝ እንደሚያሳየው  በሀገሪቱ ውስጥ  ያለእምነት  የሚኖር  ከቁጥር  የማይገባ መሆኑንና  በአጠቃላይ  በሃገሪቱ  የሚኖሩ  ዜጎች  100 ፐርሰንት  ሃይማኖተኛ  እንደሆኑ ያሳያል፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያን  ማለት  ሃይማኖተኛ  የበዛባት ሃገር ማለት ሳትሆን ራሷ ሃይማኖት ማለት ናት  ብንል የምንሳሳት አንሆንም፡፡ ስለዚህ መንግሥት ሃይማኖትን  አስመልክቶ የሚያወጣቸው መመሪያዎች ከፍተኛ  ጥንቃቄ የታከለበትና ከሕገመንግሥቱ ሃሳብ ጋር የማይቃረን ማድረግና በሕገ መንግስቱ ውስጥ የተገለጡትን ሃይማኖታዊ መብቶች የማክበርና የማስከበር ኃላፊኑን ካልተወጣ  ሀገሪቱን ወዳልታሰበ ቀውስ ውስጥ ሊከታት ይችላል ብለው ያሳሰባቸው ጥቂቶች አይደሉም፡፡  
 ሕገ መንግሥቱ  በአንቀጽ 27 በግልጽ  ለሕዝቡ ያረጋገጠለትን  ተፈጥሯዊ  የሃይማኖት  ነጻነቱን  ወንጀል እስካልፈጸሙ  ድረስ  ሊያከብርለትና  ሊያስከብርለት  ይገባል  እንጂ  ሊሸራርፍ  የሚችል  ሕግ  ወይም መመሪያ ሊያወጣ በምንም መልኩ ሕገ መንግስታዊ መሠረት የለውም፡፡  
 በአሁኑ ጊዜ ከረቂቂነት አልፎ የሃገሪቱ መመሪያ በመሆን ሥራ ላይ የዋለው የሃይማኖት ድርጅቶችንና ማኅበራትን  አስመልክቶ  የወጣው  መመሪያ  በሚኒስቴሩ  መስሪያ ቤት  የተዘጋጀ  መሆኑንና  መጠቀሻውም “የሃይማኖት  ድርጅቶችን  እና  ማኅበራትን  ለመመዝገብና  ተዛማጅ  አገልግሎቶችን  ለመስጠት  የወጣ መመሪያ  ቁጥር  1/2005 ተብሎ  ሊጠቀስ”  እንደሚችል  “ክፍል  አንድ  ጠቅላላ”  ከሚለው  አንቀጽ  ሥር በንዕስ  አንቀጽ  ሁለት  ላይ  ይናገራል፡፡  ይሄው  መመሪያ  በዘጠኝ  ክፍል  ተከፋፍሎ  45  አንቀጾች  ያሉት ሲሆን በእያንዳንዱ አንቀጽ ሥር ከ 2-15 ንዑስ አንቀጾችን ያቀፈ ነው፡፡  
ወደዚህ  መመሪያ ዝርዝር  ይዘቱ  ከመምጣታችን  በፊት  በሕገ  መንግሥቱ  በአንቀጽ  11 “የመንግሥትና የሃይማኖት  መለያየት”  በሚለው  አንቀጽ  ሥር  ንዑስ  አንቀጽ  1-3  የተቀመጠውን  ብንመለከት “መንግሥትና   ሃይማኖት   የተለያዩ   ናቸው፡፡   መንግሥታዊ   ሃይማኖት   አይኖርም፡፡   መንግሥት በሃይማኖት  ጉዳይ  ጣልቃ  አይገባም፡፡  ሃይማኖትም  በመንግሥት  ጉዳይ  ጣልቃ  አይገባም፡፡” በሚል በግልጽ መንግስትና ሃይማኖትን የማይገናኙ እንደሆኑ ይናገራል፡፡ 
እንደገናም ይሄው ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 27 “የሃይማኖት፣ የእምነትና የአመለካከት ነጻነት”በሚለው አንቀጽ ሥር ንዑስ አንቀጽ1 እና 2 የተቀመጠው ብንመለከት “ማንኛውም ሰው የማሰብ  ፣ የሕሊና እና የሃይማኖት  ነጻነት  አለው፡፡  ይህ  መብት  ማንኛውም  ሰው  የመረጠውን  ሃይማኖት  ወይም  እምነት የመያዝ  ወይም  የመቀበል  ሃይማኖቱንና  እምነቱን  ለብቻ  ወይም  ከሌሎች  ጋር  በመሆን  በይፋ  ወይም በግል የማምለክ የመከተል የመተግበር የማስተማር ወይም የመግለጽ መብትን ያካትታል፡፡ በአንቀጽ 90 ንዑስ  አንቀጽ 2  የተጠቀሰው  እንደተጠበቀ  ሆኖ  (ስለአስኮላ ትምህርት  ቤት የትምህርት ይዘታቸው በሚመለከት የሚናገር አንቀጽ ነው) የሃይማኖት ተከታዮች  ሃይማኖታቸውን ለማስፋፋትና ለማደራጀት የሚያስችላቸው  የሃይማኖት  ትምህርትና  የአስተዳደር  ተቋማት  ማቋቋም  ይችላሉ”  ይላል፡፡(ጽሑፉን ያወፈርንና ያሰመርንበት ልብ ይሉት ዘንድ እኛው ነን) እንደገናም  አንቀጽ  ዘጠኝ በ “ሕገ  መንግስት  የበላይነት” በሚለው  አንቀጽ  ሥር  ንዑስ  አንቀጽ 4 ላይ “ኢትዮጵያ  ያጸደቀቻቸው  ዓለም  አቀፍ  ስምምነቶች  የሃገሪቱ  ሕግ  አካል  ናቸው፡፡”  በሚል  ተቀምጧል፡፡ በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸው ዓለም አቀፋዊ ሕጎችና ቃልኪዳኖች እኤአ የ  1966 የሲቪልና የፓለቲካ መብቶች ዓለም አቀፋዊ ቃልኪዳን ስምምነቶች ውስጥ ሃይማኖታዊ መብትን እውቅና ይሰጣል፡፡ ስለዚህ በሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ 5 በግልጽ እንደተቀመጠው “መንግሥት ሃማኖትና እምነትን  የመግለጽ  መብትን  ሊገድብ  የሚችለው  የሕዝብን  ደህንነት፣  ሰላም፣  ጤናና  ትምህርት፣ የሕዝብን የሞራል  ሁኔታ የሌሎችን ዜጎች መሠረታዊ መብቶች፣ ነጻነቶች እና መንግሥት ከሃይማኖት ነጻ  መሆኑን  ለማረጋገጥ” ካልሆነ በቀር በምንም መልኩ የሃይማኖትን  የትምህርትና የአስተዳደር ተቋማዊ ቅርጾቻቸውን ሊወስንላቸው፣ደንብ ሊቀርጽናቸው፤ እኔ  በምፈልገው  መልኩም  ተደራጁ ሊላቸውና  በመካከላቸውም ጣልቃ እየገባ እንደ አወቃቀራቸውን ሊወስንላቸው አይችልም፡፡  ሃይማኖተኞቹ በሚያምኑት መንገድ መዋቀር ሳይሆን መንግስት በሚፈልገው መንገድ ለመዋቀር ማመን አለባቸው ማለት ነው።
 ይሁን እንጂ መመሪያው እነዚህን ተፈጥሯዊና ሕገ መንግስታዊ የሃይማኖት መብት ክፉኛ የሚጥስ ብቻ ሳይሆን ዕውቀት ጎደል መሆኑ ጭምር ጥቂት ክፍሎችን ብቻ ለዋቢነት እየጠቀስን እንመልከት፡፡            
 በአንቀጽ  5  የሚንስቴሩ  ስልጣንና  ተግባር  በሚለው  ርእስ  ሥር  በንዑስ  አንቀጽ  2  ላይ “በድርጅቶቹ ወይም በማኅበራቱ በሚቀርብ  ደንብ  ላይ  የማሻሻል  አስተያየት  መስጠት፣ ማጽደቅና መመዝገብ”የሚንስቴሩ ሥልጣንና ተግባር  እንደሆነ ይናገራል፡፡  ይህ ማለት ሃይማኖታዊ ድርጅቶችም ሆኑ ማኅበራት በሚኒስቴሩ ለመመዝገብ በሚቀርቡበት ወቅት እነርሱ ከሚከተሉት ሃይማኖታዊ  አስተምህሮ አንጻር የቀረጹትን ደንባቸውን ከመቀበልና ከመመዝገብ ይልቅ ሚኒስቴሩ ደንባቸውን እርሱ በሚፈልገው መሰረት እንዲያሻሽሉ ሃሳብ ያቀርብባቸዋል ማለት ነው፡፡ ይህ “የማሻሻያ አስተያየት መስጠት” የሚለው ቃል  ሚኒስቴሩ  ለሃይማኖት  ተቋማቱ  የሚያቀርበው  “የማሻሻያ  አስተያየት”  ምን  አይነት  አስተያየት እንደሆነ  ግልጽ  ያልሆነ፣  ገደብ  የሌለው  በራሱ  ህሊናና  በራሱ  ፈቃድ  ላይ  ብቻ  የተመሠረተ  በመሆኑ ለራሱ  የሚመች  ሃሳብ  አቅርቦ  ደንባቸውን  ቀርጸው  እንዲያመጡ  ሊያስገድዳቸው የሚችልበት እድል የሰፋ ከመሆኑም በላይ ሃይማኖታዊ ድርጅቶችንና ማኅበራትን ወደፈለገው መስመር ለማስገባት የሚከለክለው ምንም ነገር የለም፡፡ ከነባራዊው የህብረተሰብ አኗኗርና ልምድ ያላፈነገጠ፤ ከሀገሪቱ ሕገ መንግስትና ተዛማጅ ሕጎች በተጻራሪ ያልቆመ መሆኑን ከማረጋገጥ በስተቀር ሃይማኖት ተቋማት ለራሳቸው በሚቀርጹት ደንብ ላይ ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ የማሻሻል ወይም የማስተካከል ስልጣን ከተሰጠው  መንግስት ጣልቃ አይገባም የሚለው ህግ ዋጋ የሌለው ይሆናል።
 ይህም  አንድ  ሃይማኖት  የሚከተል  ተቋም  ወይም  “ሃይማኖታዊ  ድርጅትና  ማኅበራት” ባቀረቡት  ደንብ ላይ ካስተካከለና ከጠመዘዘ አለዚያ ያቀረበላቸውን “አስተያየት” አንቀበልም ካሉ መመዝገብ እንደማይችል ከገለጸ  በሕገ  መንግሥቱ  አንቀጽ  11  እና  27  ንዑስ  አንቀጽ  2  የተቀመጠውን  በተለይም  ደግሞ መንግሥት  በሃይማኖት  ትምህርትና  በአስተዳደር  ተቋማት  ላይ  አይገባም  የሚለውን  ይጥሳል  ማለት ነው፡፡ ሃይማኖቶዊ  ድርጅትም  ሆነ  ማኅበር  የሚወለደው  የሃይማኖቱ  ተከታዮች  ከሚያምኑበት  ሃይማኖታዊ እሳቤና  ምንጭ  አንጻር  በመሆኑ  እምነትና  ማኅበር  ወይም  ሃይማኖትና  ድርጅታዊ  አወቃቀር  የአንድ አካል  ክፍሎች በመሆኑ በመነጣጠል በተለይም ደግሞ እነርሱ የሚተዳደሩበት ደንብ ቀርጾ ማውጣትም ይሆን ባወጡት ላይ “የማሻሻያ አስተያት” እንዲቀበሉ ማድረግ መንግሥት ሃይማኖት ውስጥ አልገባሁም የሚልበት  ምክንያት  አይኖረውም፡፡  ስለዚህም  “የማሻሻያ  አስተያየት”  ከሰጠበት  ደቂቃ  ጀምሮ  ሕገ መንግስቱን ይጥሳል ማለት ነው፡፡   
    ሌላው  በዚሁ  በአንቀጽ  5  የሚንስቴሩ  ስልጣንና  ተግባር  በሚለው  ርእስ  ሥር  በንዑስ  አንቀጽ  9 ላይ “ሞዴል መተዳደሪያ ደንቦች የማዘጋጀት” ስልጣንና ተግባር የሚኒስቴሩ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ይህ ደግሞ የሃይማኖት  ድርጅቶችም  ይሁኑ  ማኅበራቱ  ደንብ  ይዘው  ሲመጡ  “የማሻሻያ  አስተያየት”  ከመስጠት አልፎ ደንብ የሚያዘጋጅላቸውም እራሱ እንደሆነ ይናገራል፡፡ “ሞዴል መተዳደሪያ ደንብ” ማለት እርሱ በሚፈልገው መልኩ የተቀረጸ ይዘት ያለው ሆኖ የተዘጋጀ ማለት ነው፡፡  
 በመሆኑም  ደንብ  የየሃይማኖቱ  ከሚከተሉት  እምነት  አንጻር  ለራሳቸው  የሚመች  የሚያወጡትና የሚከተሉት  እንጂ  ሚኒስቴር  መስሪያ  ቤቱ  የሃይማኖት  ተቋማትና  መተዳደሪያ  ደንብ  ማውጣትና መቅረጽ አይችልም፡፡ የመንግሥት ሚና የፖለቲካ ወይም ሃይማኖቶች ራሳቸው በራሳቸው እንዲዋቀሩና እንዲመሩ  መንገድ  መክፈት  እንጂ  ደንብ  የመቅረጽና  በሚፈልገው  መልኩ  እንዲያምኑና  እንዲዋቀሩ ማድረግ አይደለም፡፡         
 ሌላው  በዚሁ  በአንቀጽ  5  በንዑስ  አንቀጽ 10 ላይ ሚኒስቴሩ  ባወጣው በዚሁ  መመሪያ መሰረት “ለሚሰጣቸው ለምዝገባና ተዛማጅ አገልግሎቶች ክፍያ እንደሚያስከፍል” ያናገራል፡፡ እንዲሁም በአንቀጽ 6 በንዑስ አንቀጽ 5 ላይ ደግሞ “ህጋዊ የምዝገባ ፈቃድ ሳያገኝ በምስረታ ላይ እያለ ከመስራች አባላት በስተቀር  ህዝብን  በመጥራት  ሃይማኖታዊ  ስብሰባ  ማካሄድ  ማስተማር  ወይም  መስበክ  እና  ሌሎች ተመሳሳይ  ድርጊቶችን  መፈጸም  አግባብነት  ባለው  ሕግ  የሚያስጠይቅ  ይሆናል”  ይላል፡፡  በመሆኑም መክፈል  ሳይችሉ  ቀርተው  መመዝገብ  ያልቻሉ  ሃይማኖቶች  በግልም  ይሁን  በቡድን  ሃይማኖታቸውን ማራመድ፣  መስበክ፣  መሰብሰብ፣  ማስተማር  ወይም  ሌላ  ተመሳሳይ  ሃይማኖታዊ  ድርጊት  መፈጸም እንደማይችሉ  የሚናገር  ብቻ  ሳይሆን  ይህን  ያደረጉ  ድሆች  ሃይማነተኞች  በሕግ  የሚጠየቁ  ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ ይህም ተፈጥራዊና ሕገ መንግስት የሰጣቸውን አንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ 1 በግልም ይሁን በቡድን በመሆን በይፋ የማምለክ፣ የመከተል፣ የመተግበር፣ የማስተማር ወይም የመግለጽ መብታቸውን በመንጠቅ ሕገ መንግሥቱን ይጥሳል ማለት ነው፡፡ 
 በሌላ  መልኩም  ይህ  አንቀጽ  6  በንዑስ  አንቀጽ  5  የተቀመጠው    “ህጋዊ  የምዝገባ  ፈቃድ  ሳያገኝ በምስረታ  ላይ  እያለ  ከመስራች  አባላት  በስተቀር  ሕዝብን  በመጥራት  ሃይማኖታዊ  ስብሰባ  ማካሄድ ማስተማር  ወይም  መስበክ  እና  ሌሎች  ተመሳሳይ  ድርጊቶችን  መፈጸም  አግባብነት  ባለው  ሕግ  የሚያስጠይቅ  ይሆናል” የሚለውን  ስንመለከት  አንድ  የግል  እምነት ያለው  ዜጋ  የሚያምነውን  እምነት ለሌሎች  በመስበክ  በማስተማርና  ተከታይ  በማፍራት  ወደ  ሃይማኖታዊ  ማኅበርነት  ስለማይቀየር ሃይማኖቱን  በነጻ  የመግለጽ  ብሎም  የማስፋፋት  ተፈጥሯዊና  ሕገ  መንግስታዊ  መብቱን  ያፍናል ይገድባል፡፡  እርሱን  ብቻ  አይደለም  በንዑስ  አንቀጽ  6  ደግሞ  ይሄ  እንደማኅበር  መመዝገብ  ደረጃ  ላይ ያልደረሰ ዜጋ እርሱ ለሚያደርገው የመስበክ የማስተማር ወይም ሌሎች ሃይማኖታዊ ድርጊት “የደገፈና መሰል ትብብሮችን ያደረገ ማንኛውም ሰው በተመሳሳይ አግባብነት ባለው ሕግ የሚጠየቅ” እንደሚሆንም መመሪያው  ይገልጻል፡፡  ይህም  ሕገ  መንግሥቱን  ሳይጥሱ  ጤናማ  ሃይማኖታዊ  ሥራ  ሲያካሂዱና ሲደግፉ  የነበሩትን  በወንጀል  መጠየቅ  ከሕገ  መንግስታዊ  ድንጋጌዎች  መንፈስ  የሚጻረርና  ወንጀል ባልተፈጸመበት ወንጀል እንደመፍጠር ነው፡፡    ሕገ መንግስቱ በግል የማምለክና የማመን፤ የማስተማር ነጻነትን ሲሰጥ በሃይማኖት ድርጅቶች ማቋቋሚያ ደንብ ላይ ግን በግል ማመን ቀርቶ በማኅበር ወደመደራጀት ብቻ ከፍ ብሏል። ግለሰብ የሚያምነውን ለሌሎች በማካፈል፤ ተከታይ ለማፍራት ካላስተማረ ራሱን እንደማኅበር ቆጥሮ ህጋዊ ፈቃድ ያገኝ ዘንድ የሚገደድበት አግባብ ትክክለኛ አካሄድ አይደለም።
 እንዲያውም  ሃይማኖታዊ  ድርጅቶችና  ማህበራት  ዓለማቀፋዊ  ግንኙነት ለማድረግና  ምቹ  መንገድ እንዲኖራቸው  ራሳቸው  ከማሰብ  አንጻር  ሊመዘገቡ  ወደ  ሚኒስቴሩ  ይሄዳሉ  እንጂ  ካልተመዘገበችሁ ሃይማኖት አይደላችሁም ማለት ተገቢ አይደለም፡፡ እነዚህ ሃይማኖታዊ አገልግሎቶች የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ እስካልጣሱ ድረስ ሊከለከሉ አይገባም፡፡  
 ሌላው ይሄው መመሪያ በአንቀጽ ሰባት “አደረጃጀት” በሚለው ሥር በንዑስ አንቀጽ 1 ላይ “ማንኛውም የሃይማኖት  ድርጅት  ወይም  ማኅበር  በመተዳደሪያ  ደንብ  መሠረት  ጠቅላላ  ጉባኤ፤  የስራ  አስፈጻሚ / አመራር  ቦርድ  ፣  ስራ  አስኪያጅ  /  ፕሬዝዳንት  ፣  ዳይሬክተር  ፣  ኦዲተር  ፣  ሂሳብ  ሹምና  ሌሎች እንደድርጅቱ ወይም ማኅበሩ አደረጃጀት አስፈላጊ የሆኑ የሥራ ክፍሎች ሊኖሩት ይገባል ይላል፡፡” ይህም የሃይማኖት  ድርጅቶችና  ማኅበራት  ከሚከተሉት  እምነትና  ከመንፈሳዊ  መርህ  አንጻር  አደረጃጀታቸውን ያወጣሉ እንጂ መንግሥት አደረጃጀታቸውንና የስልጣን ተዋረዳቸውን እንዲሁም የማዕረግ ስሞቻቸውን ሊያወጣላቸው  አይችልም፡፡  ለምሳሌ  የኢትዮጵያ  ኦርቶዶክስ  ተዋህዶ  ቤተክርስቲያንን  ብንወስድ ሃይማኖቷዊ ቀኖናዋና የራሷ ሕገ ቤተክርስቲያን እንደሚያዘው ቀድሞ በፓትሪያሪኩ የበላይ ጠባቂነትና አመራር  ሰጪነት  በኋላም  ተሻሽሎ   በብጹዐን  ሊቃነ  ጳጳሳት  ምልዐተ  ጉባዔ  እንድትመራ  ከወሰነችበት እለት ጀምሮ አሁን በዚሁ እየሄደች ያለችን ቤተክርስቲያን  ፣ ወደ ፊትም ቤተክርስቲያኗ እንደ ቀኖናዋ መሰረት  እንዳመቻትና  ለራሷ  በምታምነው  አደረጃጀትና  አስተዳደራዊ  መዋቅር  ዘርግታ  ብትሄድ መንግሥት  ጣልቃ  ገብቶ  እንደ  ሃይማኖት  ድርጅት  ወይም  ማኅበር  ተዋቅረሽ  ጠቅላላ  ጉባኤ፤  የስራ አስፈጻሚ /  አመራር  ቦርድ  ፣  ስራ  አስኪያጅ /  ፕሬዝዳንት  ፣  ዳይሬክተር  በሚል  መዋቅር  ውስጥሽን ካላደራጀሽ ሃይማኖት አይደለሽም ሊላት እንደሆነ ይሄው መመሪያ ያስረዳል ማለት ነው፡፡  
ይህ መመሪያ የያዘው እነዚህ ስያሜዎች ማለትም ጠቅላላ ጉባኤ፤ የስራ አስፈጻሚ / አመራር ቦርድ  ፣ ስራ  አስኪያጅ /  ፕሬዝዳንት  ፣  ዳይሬክተር  ፣  ኦዲተር  ፣  ሂሳብ  ሹምና  ሌሎች  ተብለው  የተቀመጡት መዋቅራዊ ስያሜዎች በራሳቸው “ዓለማውያን” ቋንቋዎችና ትርጓሜዎች ያሏቸው እንጂ ሐይማኖታዊ ቋንቋዎች ለመሆናቸው በራሱ አነጋጋሪ ጉዳዮች ናቸው፡፡  
 ሌላም   እንደምሳሌ   የወንጌላውያን   አብያተክርስቲያናትን   ይዘትና   አወቃቀር   ብንመለከት   አንዱ ቤተክርስቲያን  ከሌላው  በመሰረታዊ  ክርስትና  አስተምህሮ  አንድ ቢሆንም  በአስተዳደራዊ  አወቃቀሩ  ግን የተለያየ  ሲሆን  አንዳንዱ  በ “ሐዋርያዊ  አመራር”  የሚያምንና  የተዋቀረ  ሌላው በ “ሽማግሌያዊ አስተዳደር”  የሚያምንና  የተዋቀረ  ሌላው  ደግሞ  በ “ፓስተራል  አስተዳደር”  የሚያምንና  የተዋቀረ ወዘተርፈ  በመሆኑ እነዚህን በአንድ አስተምሯቸውን ተከትሎ  ካዋቀሩት አስተዳደራዊ  አደረጃጀት አውጥቶ  እንደልማት ማኅበር  ጠቅላላ  ጉባኤ፤  የስራ  አስፈጻሚ  /  አመራር  ቦርድ  ፣  ስራ  አስኪያጅ / ፕሬዝዳንት፣  ዳይሬክተር ብላችሁ ተደራጁ ብሎ በ “ማሻሻያ  ሃሳቡ”  ጠምዝዞ  ካላዋቀራቸው አትመዘገቡም  እንደሃይማኖትም  መንቀሳቀስና ማስተማር  መስበክ  አትችሉም  ሊል  እንደሚችል  በግልጽ ያሳያል፡፡  ይህም “መንግስት  በሃይማኖት  አይገባም”  የሚለውንና  “የሃይማኖት  ተከታዮች ሃይማኖታቸውን  ለማስፋፋትና  ለማደራጀት የሚያስችላቸው  የሃይማኖት  ትምህርትና  የአስተዳደር ተቋማት ማቋቋም ይችላሉ” የሚለውን በአንቀጽ  11 ንዑስ አንቀጽ 3 እና አንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ 2የተቀመጠውን የራሳቸውን መብት በመንጠቅ ሕገ መንግሥቱን የሚጻረር መሠረታዊ ስህተት መሆኑን ያሳያል፡፡ 
 ለነገሩ  ወንጌላውያን  አብያተክርስቲያናት  ይህ  አዲሱ  መመሪያ  ከመውጣቱም  በፊት  በነበረው  መመሪያ መሠረት እንደልማት ተቋማትና ድርጅት ይመዘገቡና ስራቸው ሃይማኖታዊ ይሁን ልማታዊ ሳይታወቅ የስራና  የሂሳብ  ሪፖርታቸውን  እንዲሁም  የቀጣይ  የበጀት  ዓመት  የሥራ  እቅዳቸውን  ጭምር ካላቀረቡ በቀር  የሥራ  ፈቃድ  ስለማያገኙ  ይህን  ለማቅረብ  ይገደዱ  ነበር፡፡  መንግስትም  የሃይማኖት  የስራ ሪፖርትና  እቅድ  የበጀት  አስተዳደራቸውንም  ጭምር  የማየትና  የመቀበል  በውጭ  ኦዲትርም እንዲመረመሩ  የማድረግ  ምንም  ሕገ  መንግስታዊ  ሥልጣን  የሌለው  ቢሆንም  ለረጅም  ዘመናት ሲያካሂድባቸው  ኖሯል፡፡ይህም  መንግስት  በሃይማኖቶች  ውስጥ  በትምህርታቸውም  ሆነ  በአስተዳደር ስልጣናቸውና  አወቃቀራቸው  ውስጥ  ገብቶ  እንደነበረ  በሚንስትሩ  የሃይማኖትና  የእምነት  ዳሬክቶሪት የተጨናነቁ መዝገብ  ቤትን ማየት  በቂ  ምስክር  ነው፡፡  በዚህም  በመንግስት  ጣልቃ  ገብነትና የአወቃቀር ውሳኔ ምክንያትና የወንጌላውያን አብያተክርስቲያናት እርስ በርሳቸው በመዋቅሩ እንዳይስማሙ የመካሰስ የመለያየት  እንዲሁም  አላግባብ  የቤተዘመድ  አመራር  እንዲፈጥሩ  ወዘተ  ጭምር  ተገደው  እንዲገቡ ተደርገዋል፡፡          
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሌላው መነሳት ያለበት ነጥብ በዚሁ መመሪያ በአንቀጽ 3 “ትርጓሜ” በሚለው ሥር በንዑስ  አንቀጽ  6 ላይ  “መንፈሳዊ  አገልጋይ  ወይም  ሰባኪ  ወይማ  ዳኢ  ማለት  በሃይማኖት  ድርጅቶቹ ወይም  ማኅበራት  ውስጥ  እውቅና  ኖሯቸው  በክፍያ  ወይም  ያለክፍያ  የሃይማኖት  ትምህርት የሚያስተምሩ  ወይም  የሚሰብኩ  አገልጋዮችን  ያጠቃልላል፤”  ይላል፡፡  እዚህ  ላይ  መመሪያው በየሃይማኖታዊ  ድርጅቶችና ማህበራት  ውስጥ ያሉትን  ልዩ  ልዩ ስያሜዎችና የአገልግሎት ማዕረጋትን በአንድ  መጠቅለሉና  መጥራቱ  መሠረታዊ  ስህተት  ነው፡፡  ይህ  ጠቅልሎ  የመጥራት  ሥራና  ኃላፊነት የየሃይማኖቱ  ድርጅቶችና  ማኅበራት  ተግባርና  ሥልጣን  እንጂ  እንዴትስ  እንዲህ  ብሎ  መጠቅለልና መጥራት ይችላል? የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ በተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት ውስጥ የተለያየ ስምና ማዕርግ ያላቸው፤ ሃይማኖታዊ ተቋሙ የሚፈቅደውን መጠሪያ ይዘው የሚሰብኩ፤ የሚያስተምሩ በዚህ ጥቅል ስያሜ መሰረት ቀሪ ሆኗል ማለት ነው።
 ሌላው  አነጋጋሪ  ጉዳይ  በዚሁ  መመሪያ  አንቀጽ  13 “የውጭ  ዜጎችን  ማሰማራት”   በሚለው  አርእስት ሥር ንዑስ አንቀጽ 5 ላይ  ሃይማኖታዊ ድርጅቱ ወይም ማኅበሩ “ ያሰማራው የውጭ ዜጋ ከመጣበት ዓላማ  ውጪ  በመንቀሳቀስ  ለሚፈጽመው  ጥፋት  በተናጠልና  በጋራ  በሀገሪቱ  ህግ  ተጠያቂ  ይሆናል” የሚለው  ነው፡፡  ይህም  ማለት  አንድ  ፈረንጅ  ከሃይማኖታዊ  ተቃሙ  ወይም  ማህበሩ  ጋር  በመሆን መንፈሳዊ  ሥራ  ለመስራት  ተስማምቶ  በመግባት  መንፈሳዊ  ሥራው  ጋር  ባልተገናኘ  ሁኔታ  ባለው ትርፍ  ጊዜም  ሆነ  በግሉ  ሌላ  ወንጀል  ቢሠራ  ለፈጸመው  ወንጀል  ተቋሙ  ወይም  ማኅበሩ በወንጀል መጠየቁ  አግባብ  አይደለም፡፡  ሃይማኖታዊ  ድርጅቱ  ወይም  ማኅበሩ  ላለው  ሃይማኖታዊ  ተግባር ተስማምቶ አሰማራው እንጂ ሌላ የግል ስህተቱን ሁሉ ተቋሙን ወይም ማኅበሩን ተጠያቂ ማድረግ ከህግ አስተሳሰብ ጋር ፈጽሞ የሚገናኝ አይደለም፡፡ 

 ከዚህ ዓይነቱ ጅምላ ተጠያቂነት ለመዳን ግለሰቡን ለማስተማር ወይም ለማሰራት ያስመጣው ተቋም ሰውየው ለመስራት ከተዋዋለበት ሰዓት ውጪ ያለውን ጊዜ የትም እንዳይንቀሳቀስ የሚጠብቁ ፖሊሶች ወይም አጃቢዎች መመደብ ወይም ጉዳዩን ከጨረሰበት ደቂቃ አንስቶ ባመጣው መንገድ አፍኖ ወደ መጣበት የመመለስ ግዴታ አለበት ማለት ነው።
 በአንቀጽ  18  “የተከለከሉ  ተግባራት”  በሚለው  ርእስ  ሥር  ንዑስ  አንቀጽ  8  ደግሞ  ብንመለከተው መመሪያው ሌላ አስገራሚ ነገርንም ይዟል፡፡ “ከሚመለከተው አካል ፈቃድ ሳያገኙ ከአምልኮ ቦታ ውጪ ሰዎችን  በማሰባሰብ  ባልተፈቀደ  ቦታ  የሃይማኖት  ትምህርት ማስተማር  ወይም  መስበክ” በንዑስ  ቁጥር 12  ደግሞ  ከሌሎች  ጋር  “አብሮ  መስራት”  ፣    በንዑስ  አንቀጽ  13  ደግሞ  “የሃይማኖት  ተግባርን ከበጎአድራጎት ዓላማና ተግባር ጋር ቀላቅሎ መሥራት” ይከለክላል፡፡ 
 ይህም ማለት እንደምሳሌ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነትና አስተምህሮን  ብናይ ለረዥም ዘመናት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የህዝቡን የቤት ለቤት ጽዋ ማህበራት ያለፈቃድ ሰብስቦ እንደወትሮው  ማስተማር  መስበክና  ሃይማኖታዊ  ተግባራት  መፈጸም  ይከለክላል  ማለት  ነው፡፡  የታቦት ንግስ፤ በዓል፤ መንፈሳዊ ጉዞ የመሳሰሉ የቆዩ ልምዶች ሁሉ ዝግ ናቸው ማለት ነው። ቄሱም የነፍስ ልጆቻቸው ከአምልኮ ቦታ (ከቤተክርስቲያን ቅጥር ጊቢ) ውጭ ሰብስቦ ቢሰብክ ቢያስተምር በሕግ ያስጠይቀዋል  ማለት  ነው፡፡  ይህ  ብቻ  አይደለም  የአደባባይ  ክብረ  በዓላትንም  ጭምር  ያለ  መንግስት ፈቃድ እንደወትሮ ቢያካሂዱ መሰብሰብ በዓላቱንም ማካሄድ አይችሉም ማለት ነው፡፡ ይህን ሃይማኖታዊ  ነጻነታቸውን ከሚመለከተው የመንግስት ቢሮ ሄደው “ይሁንታ” ማግኘት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ካላገኙም ቀረ ማለት ነው፡፡ 
ወደ  ካቶሊኩም  ወደ  ወንጌላውያኑም  ተመሳሳይ  እጣ  ፈንታ  ይገጥመዋል፡፡  ከተፈቀደላቸው  የአምልኮ ቤቶች   (ይህም  ተከራይተው  የሚያመልኩበትን  ቤት  ያካትት  አያካት  መመሪያው  ግልጽ  አያደርግም  ) ውጭ  የቤት  ለቤት  ጸሎት  ፕሮግራሞች፣  መጽሐፍ  ቅዱሳዊ  የጥናት  ፕሮግራሞች  በሀዘንና  በደስታ ወቅትም በሚያደርጉት የቤትና የድንኳን አገልግሎቶች ሁሉ የተከለከሉ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡
ሌላው ሃይማኖት የሚወልደው ለሌሎች በጎ የማድረግ የመደገፍ ተግባር ነጥሎ እናንተ እንደ ሐይማኖት መጸለይ  ብቻ  ይገባችኋል  እንጂ  ሃይማኖትን  ከምግባር  አታቀላቅሉ  ብሎ  የሚገልጸው  መመሪያ ለክርስቲያኑ ህብረተሰብ “ተርቤ አብልታችሁኛል  ፣ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛል፣ ታምሜ ጠይቃችሁኛል፣ ታስሬ  ወደ  እኔ  መጥታችኋል  ብሎ  ጌታ  በመጨረሻ    በማቴወስ  ወንጌል  25፡34-46  እንደተገለጸው የሚጠይቀውን ቃልና “ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ  ነው” የሚለውን የያዕቆብ መልእክት ምዕራፍ 2፡18-26ን  የእምነት  መሠረት  የሚጥስ  አሊያም  ነጣጥሎ  በዚህ  መልኩ  ሥጡ  ብሎ  ያለ  እምነት መሰረታቸው  አካሄድ  መግለጹ  ሲሆን  ለእስልምና  እምነት  ተከታይም  ከአምስቱ  የእስልምና  ማእዘናት ውስጥ  በሦስተኛ  ደረጃነት  “ዘካት”  መስጠትን  የሚከለክል  ወይም  ይህንን  እንዴት  መፈጸም እንደሚገባቸው ከሐይማኖታዊ አስተምህሯቸው ውጪ መንግስት መመሪያ እየሰጠ በመሆኑ መንግሥት ሕገ መንግስቱን ጥሶ በሐይማኖት ጣልቃ መግባቱን ያሳያል ፡፡                     
 እንግዲህ  ሕዝቡ  ይህ  ሃይማኖትን  በነጻነት  የመቀበል፣  በግልና  በጋራ  የማራመድ  የማስፋፋትና የማደራጀት  ሕገ  መንግስታዊ  መብቱን  የገፈፈው  መመሪያ  ለውይይት  ለመጀመሪያ  ጊዜ  መንግስት የሃይማኖት  ተቋማትን  በጠራና  ሃሳቡን  በገለጸ  ጊዜ  የኢትዮጵያ  ኦርቶዶክስ  ተዋህዶ  ቤተክርስቲያን “አይመለከተኝም”  ብላ  ስብሰባውን  ረግጣና ጥላ  እንደወጣች  ካቶሊክም  “እኔ  አለም  አቀፋዊ  አወቃቀር እንጂ  ብሔራዊ  ብቻ ስላልሆንኩ አለም አቀፉን ቤተክርስቲያኗን ጠይቁ”ብላ ጥላ  እንደወጣች፣ እስልምናም  በተመሳሳይ “አይመለከተኝም”ብለው ሲወጡ ጥቂት  ፕሮቴስታንት  አካላት  ብቻ ቆይተው የመንግሥትን  ይህን  ሃሳብ  እንዳዳመጡ  የውስጥ ምንጮች ይገልጻሉ፡፡ይሁን እንጂ እነዚህ የእምነት ተቋማት ባይቀበሉትም ቅሉ መመሪያው ጸድቆ እንደመመሪያ እየተተገበረ ሲሆን ብዙዎችን ግራ እያጋባ ይገኛል፡፡             

      

Thursday, February 6, 2014

ቅድስት ድንግል ማርያም ላይ መዋሸት ይቁም! -


By Mesy Yegetalij (facebook)
ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት" ቆላ 3፤17
ቅድስት ድንግል ማርያም ጸጋን የተሞላች፣ በትሕትናዋ፣ በእምነቷ በቅድስናዋ ተወዳዳሪ የሌላት፣ አስደነቂውን መለኮታዊ ምሥጢር በልቧ በመጠበቅ እስከ መስቀል ድረስ የተገኘች ብቸኛዋ እናታችን ናት።
ቅድስት ድንግል ማርያምን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በእምነታቸው ከተመሠከረላቸው ቅዱሳን ሁሉ ልዩ የሚያደርጋት እምነቷ መለኮትን በማሕጸኗ መሸከሟ እና ምሥጢር ጠባቂነቷ ነው። ያለወንድ ዘር ልጅ ትወልጃለሽ፣ ይህን ለማድረግ እግዚአብሔር አይሳነውም ተብሎ ሲነገራት እንደ ቃልህ ይሁንልኝ በማለት አመነች። እጅግ አስደናቂ እምነት ነው፣ ኤልሳቤጥ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልታ ከእግዚአብሔር ዘንድ የነገሩሽን ቃል የምታምኚ አንቺ ብፅእት ነሽ በማለት አክብሮቷን ገለጠች።
ቅዱስ ገብርኤልም የተላከበትን ምክንያት ከመናገሩ በፊት በእግዚአብሔር ፊት ያላትን ክብር ከሰማይ ያየውንና የሰማውን በመለኮታዊው ዙፋን ዘንድ ያላትን ሞገስ ነበር ያበሠራት። ቅዱስ ገብርኤል በእግዚአብሔር ፊት የሚቆም መልአክ እንደመሆኑ መጠን ድንግል ማርያም በሥላሴ መለኮታዊ ክብር የታሰበች መሆኗን ተረድቷል፣ ስለዚህ በርሷ ላይ ያለው የጌታ ክብር ነውና ተጠንቅቆና ተንቀጥቅጦ ነበር የቀረባት። መልአኩ ወደ ድንግል ማርያም ሲቀርብ በታላቅ ትህትና ነበር። ምክንያቱም እግዚአብሔር ከርሷ ጋር ነውና ልኳን እና መጠኗን ይረዳል። እርሷ በመለኮታዊ ክብር ተሸፍና በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ተሞልታለች።
ድንግል ማርያም መልአኩ ካበሠራት ጀምሮ በእርሷ እየተካሄደ ያለውን ምሥጢር ታውቃለች፣ አካላዊ ቃል ከሰማይ ወርዶ በማሕጸኗ አድሮ ተጸንሷል። በዚህ ጊዜ እራሷን በጌታ ፊት ዝቅ አድርጋ "ነፍሴ ጌታ እግዚአብሔርን ታከብረዋለች መንፈሴ በአምላኬና በመድኃኒቴ ሐሴት ታድርጋለች እርሱ በእኔ ታላቅ ሥራ አድርጓልና" ስትል እግዚአብሔርን አከበረች
ድንግል ማርያም እጅግ አስደናቂው ውበቷ ያለው እዚህ ላይ ነው። ነገሩን በልቧ ይዛ ትጠብቀው ነበር እንጂ ለማንም አላወራችም። የጌታን ምሥጢር ያለጊዜው መግለጥ አልፈለገችም፣ ከተጸነሰ ጀምሮ እስከ ሞቱ ድረስ በምሥጢር ያዘችው ። ለሰላሣ ሦስት ዓመት ያህል ዝም በማለት እግዚአብሔርን ጠበቀች፤ ይህ ነው ቅድስተ ቅዱሳን የሚያሰኛት ድንግል ማርያምን "ከሴቶች ሁሉ ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ" ያሰኛምት ይህ ነው። ድንግል ማርያም ከአእምሮ በላይ የሆነ ትግሥት አሳይታለች፤ እውነትም ጸጋን የተመላች ናት የድንግል ማርያም እንደዚህ የመቀደስ ዋና ምክንያት ግን እግዚአብሔር ከርሷ ጋር ስለሆነ ነው።
"አላዋቂ ሳሚ ንፍጥ ይለቀልቃል" እንደተባለው፣ ድንግል ማርያምን እናከብራለን ያሉ ሐሰቶኞች በድንግል ማርያም ላይ የተናገሩትና አሁንም እያስተማሩ ያሉት ግን በመጽሐፍ ቅዱስ የምናውቃት ድንግል ማርያምን አትመስልም። መናፍቃን በድንግል ማርያም ላይ የፈጸሙትን ስም ማጥፋት ጥቂት እንመልከትና እኛም ድንግል ማርያምን ያከበርን እየመሰለን በርሷ ላይ ሐሰትን ከመናገር መቆጠብ አለብን።
በተዓምረ ማርያም የተጻፈውን ውሸት እውነት በሆነው በእግዚአብሔር ቃል እንመርምር፦t

"ዘከመ ጸለየት እግዝእትነ አመ አሠርቱ ወሰደስቱ ለየካቲት እምድህረ እርገቱ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ወዘከመ ነሥአት ኪዳነ ምሕረት ዘኢይትሄሰው"
ትርጉም "ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካረገ በኋላ እመቤታችን እንደጸለየችና የካቲት አሥራ ስድስት ቀን የምሕረት ቃል ኪዳን እንደተቀበለች"
"ኢያንተገት ገዪሰ ወጸልዮ ኀበ መቃብረ ወልዳ ዘውእቱ ጎልጎታ"
ትርጉም "ወደ ልጇ መቃብር እየሄደች መጸለይን አቋርጣ አታውቅም፣ ይኸውም ጎልጎታ ነው"
ይህ ታምር ነው ከተባለ ደራሲው ሊል የሚፈልገው ጌታ ካረገ በኋላ የካቲት አሥራ ስድስት ቀን፣ ጎልጎታ በሚገኘው የጌታ መቃብር ስትጸልይ፣ ጌታ ተገልጦ ቃል ኪዳን እንደሰጣት፣ እመቤታችንም ጌታ ከሞተ ጀምሮ መቃብሩ ላይ ቆማ መጸለይን አቋርጣ እንደማታውቅ፣ ጌታም ሁልጊዜ ይጎበኛት እንደነበር ነው።
ጌታ የተሰቀለው መጋቢት ሃያ ሰባት ሲሆን የተነሣው ደግሞ መጋቢት 30 እንደሆነ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያስረዳል። እንግዲህ እመቤታችን ኪዳን የተቀበለችው የካቲት አሥራ ስድስት ቀን ከሆነ አንድ ዓመት ሙሉ ወደ ጌታ መቃብር ስትመላለስ ነበር ማለት ነው። ይህ ታሪክ የመቤታችንን ስም ያጠፋል፣ ምክንያቱም እመቤታችን በመንፈስ ቅዱስ የተሞላች በእግዚአብሔር የሆነውን ነገር ሁሉ የምታምን ቅድስት ናት። የጌታን ትንሣኤ አይታለች፣ እርገቱንም ተመልክታለች፣ እርሱ ዓለምን ለማዳን ከእርሷ እንደተወለደ፣ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ፣ ለዘለዓለም ሕያው እንደሆነ፣ ከስም ሁሉ በላይ የሆነ ስም እንዳለው፣ በፍጥረት ሁሉ በላይ ከፍ ያለ ጌታ እንደሆነ፣ በዙፋኑ ላይ የተቀመጠ ልዑል፣ ዳግም ለፍርድ እንደሚገለጥ ከማንም በላይ የተረዳች እናት ናት።
ታዲያ ሞቶ እንደቀረና እንዳልተነሣ፣ በአብ ቀኝ በዙፋኑ እንዳልተቀመጠ፣ በማሰብ መቃብሩ ላይ ዕለት ዕለት እየተገኘች እንዴት ልታለቅስ ቻለች? የጌታን ትንሣኤና እርገት በዓይኗ አይታ በደስታ በመሞላት እንደርሷ ያለ ከየት ይገኛል? ኢየሱስ ክርስቶስ ኃጥአንን ሊያድን እንደመጣ ከርሷ በላይ ማን ሊያውቅ ይችላል? ቅድስት ድንግል ማርያም የጌታን እርገት ያየች ስለሆነ በመቃብሩ ላይ ታለቅስ ነበር የሚለው አባባል የደብተራ ተረት ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ ጌታ ካረገ በኋላ እመቤታችን ትጸልይበት የነበረውን ሥፍራ እንዲህ ሲል አስቀምጦታል።
"በዚያም ጊዜ ደብረ ዘይት ከሚባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ... እነዚህ ሁሉ ከሴቶችና ከኢየሱስ እናት ከማርያም ከወንድሞቹም ጋር በአንድ ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር" የሐዋ 1፥12፡14 ይጸልዩበት ስለነበረው ሥፍራ ሲናገርም "በገቡም ጊዜ ወደሚኖሩበት ሰገነት ወጡ" ይላል ቁ 13። ይህ ሰገነት ጽርሐ ጽዮን የተባለው የማርቆስ እናት ቤት ነው። የጸለየችውም ከሐዋርያት ጋር ነበር በዚያ ቤት ሳሉም መንፈስ ቅዱስ እንደወረደላቸውና ምሥጢር ሁሉ እንደተገለጠላቸው እንጂ ሌላ ታሪክ አናነብም። እስከ ዓለም ፍጻሜ እኔ ከናንተ ጋር ነኝ ስላለ ጌታ ከእመቤታችንም ተለይቶ አያውቅም። እናም እመቤታችን ካረገ በኋላ አብሯት እንደሌለና የማታገኘው ይመስል መቃብር ላይ ቆማ የምታለቅስበት ምክንያት የለም። ብዙ ጊዜ መቃብር ላይ እየቆሙ ሲያለቅሱ መኖር የሥጋውያን ሰዎች ሥርዓት ነው።  ሥጋውያን የሞቱ ዘመዶቻቸውን ከተሰናበቱ በኋላ በዓይን ለማየት፤ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ለመመልከት ስለማይችሉ በተስፋ መቁረጥ ተሞልተው በሚወዷቸው ሟቾቻቸው መቃብር ላይ ሄደው ሲያለቅሱ እናያለን። መንፈሳውያን ግን እደዚህ አያደርጉም። ባህሉም የኢትዮጵያውያን እንጂ የእሥራኤላውያን አይደለም። አልቅሰው ከቀበሩ በኋላ ተስፋ እንደሌለው ሰው ዕለት ዕለት መቃብር ላይ ሄደው ያለቅሱ ነበር የሚል ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጽፎ አናገኝም።
እንደ ዘርዓ ያዕቆብ አባባል እመቤታችን የጌታን ምሥጢር በሚገባ እያወቀች መቃብር የምትጎበኝበት ምክንያት ምንድር ነው? ጌታ በመንፈስ ቅዱስ ሙላት ከርሷ ጋር እያለ፤ ከመቃብር ደጃፍ ተቀምጠው የታዩት መላዕክት «ሕያውን ከሙታን መካከል  ስለምን ትፈልጋላችሁ?» መባሉን ያወቀችና የተረዳች እናት መቃብሩ ላይ ዕለት ዕለት እየሄደች  ለአንድ ዓመት አለቀሰች ማለት ስም ማጥፋት ነው። የጌታን እናት ማርያምን ሳይሆን ሌላ የኦርቶዶክሶች ማርያም መሆን አለባት። በእውነቱ ይህ ጠላት የጠነሰሰው ሐሰት እንጂ የጌታየ እናት ቅድስት ድንግል ማርያም ይህን ታሪክ አታውቀውም። ከሁሉም በላይ ጸጋ የበዛላት በእምነት እና በመለኮታዊ ምሥጢር የተሞላች ናት።
መቃብሩ ላይ ቆማ ጸለየችው የተባለው ጸሎት ደግሞ ኢየሱስ ለምን እንደሞተ የማታውቅ እስኪያስመስሏት ድረስ ዋሽተውባታል።
"በእንተ ዘይገብር ተዝካርየ ወዘየሐንጽ ቤተ ክርስቲያን በስምየ ወዘያለብስ እሩቀ በስምየ ወዘይሄውጽ ድውየ ወዘያበልዕ ርኍበ፣ ወዘያሰቲ ጽሙአ፣ አው ዘይናዝዝ፣ ኅዙነ፣ ወዘያስተፌስሕ ትኩዘ አው ዘጸሐፈ ውዳሴየ፣ ወሰመየ ወልዶ ወወለቶ በስምየ ወዘሐለየ ማኅሌተ በስምየ፣ ወበበዓልየ፣ እሥዮ እግዚኦ ዕሴተ ሠናየ ዘዓይን ኢርእየ፣ ወእዝን ኢሰምዓ ውስተ ልበ ሰብእ ዘኢተሃለየ"
ትርጉም "ተዝካሬን የሚያደረግ፣ ቤ/ክርስቲያኔንንም በስሜ የሚያሠራ፣ በስሜ የታረዘ የሚያለብስ፣ የታመመ የሚጎበኝ፣ የተራበ የሚያበላ፣ የተጠማ የሚያጠጣ፣ ወይም ያዘነ የሚያረጋጋ፣ ቢሆን፣ የተከዘ ደስ የሚያሰኝ፣ ወይም ምሥጋናዬን የጻፈ፣ ሴት ልጁን እና ወንድ ልጁን በስሜ የሰየመ፣ እኔም በምከብርበት ቀን፣ ምስጋና ያመሰገነውን፣ አቤቱ ዓይን ያላየውን፣ ጆሮ ያልሰማውን፣ በሰው ልብ ያልታሰበውን፣ በጎ ዋጋ ስጠው" ታምር 12 ቁ 39-42።
እያንዳዱን ልመና በዝርዝር እንመልከተው
"ተዝካሬን የሚያደርግ"
ተዝካር ማለት መታሰቢያ ማለት ነው፣ ድንግል ማርያም ጌታን ከጸነሰች ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ እስከ ወረደበት እስከ በዓለ ሃምሳ ድረስ መጽሐፍ ቅዱስ ያስባታል።
ጌታን የሚያውቅ ሁሉ እናቱንም ያውቃል፣ ስለጌታ መወለድ ስንናገር ማን እንደወለደው መናገር የግድ ነው። ጌታ ሲሰደድ ማን ይዞት እንደተሰደደ መናገር አያጠያይቅም። የድንግል ማርያም መታሰቢያ መልዓኩ ካበሠራት ጀምሮ ጌታን መውለዷ፣ መሰደዷ፣ በሞቱ ጊዜ እስከ መስቀል ድረስ መገኘቷ፣ በሰርጉ ቤት ለባለሠርጉ ያሳየችው ርኅራሄ፣ ወዘተ ነው። ይህም የተጻፈው ታሪኬን ተናገሩልኝ ውዳሴየን  ጻፉልኝ ብላ ስለለመነች ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የተደረገ ነው። እመቤታችን "ተዝካሬን ያደረገ" ብላ ስትጠይቅ እንደ ዘርዓ ያዕቆብ አባባል ድግስ ደግሶ፣ ጠላ ጠምቆ፣ ንፍሮ ቀቅሎ፣ በየወሩም ሆነ በያመቱ የመገበ ሰው ምሕረት እንዲያገኝ ጌታን ለመነችው ማለት ነው።
ጌታ ብራብ አብልታችሁኛል ብጠማ አጠጥታችሁኛል ወዘተ ብሎ የተራበን ማብላት የተጠማን ማጠጣት እንደሚገባን አስተምሮናል። ይህን የልጇን የወዳጇን ቃል ወደራሷ ወስዳ «በስሜ ያበላውን ያጠጣውን» በማለት እመቤታችን አትዋሽም።  «ብራብ አብልታችሁኛል፤ ብጠማ አጠጥታችሁኛል» በማለት ልጇ ያስተማረውን ቃል ከማንም በላይ እሷ ታውቃለችና።
የፍቅር እናት በመጽሐፍ ታሪኳ እንዲጻፍ ማንንም አልጠየቀችም። ለመጽደቅ ከፈለጋችሁ የምስጋናዬንም ድርሳን ጻፉልኝ ብላ ለማንም አልተናገረችም። «ሁሉን ነገር በልቧ ትጠብቅ» የነበረች የፍቅርና የትህትና እናት  ድንግል ማርያም እንደምድራውያን የነገሥታት ቤተሰቦች ሃሳብ ታሪኬን ጻፉልኝ፤ ድርሳኔንም አባዙልኝ፤ ያኔ አጸድቃችኋለሁ ብላለች ማለት ፈጽሞ ሀሰት ነው። መጽሐፍና ድርሳን የኋላ ሠዎች ታሪክን ሰንደው፤ ገድልን ጠርዘው ለማስታወስ እንዲቻል ያዘጋጁት እንጂ «ትውልድ ሁሉ ብጽእት» እንደሚላት የምታውቅ የጌታ እናት ስሟ እንዲታወስና ሰዎች እንዲጸድቁ ሽታ እኔ ስሞት ጻፉልኝ አላለችም።
ታዲያ በየወሩ በምንሰጠው እንጀራ ለዚያዉም በርሷ ስም እንደምንጸድቅ እንዴት አሰበች? በርግጥ ይህ የድንግል ማርያም ልመና ነው? ወይስ መብላት የለመደ ደሞዙን ለማስተካከል ያለ ሥራ በሰው ትከሻ ለመኖር ያሰበ ደብተራ የፈጠረው ፈጠራ?
ደሞዝን ለቤተ ክርስቲያን በአግባቡ በአሥራት በስጦታ ከመጣው ማግኘት ሲቻል ወሩን እና ዓመቱን ቀኑን ሁሉ የመታሰቢያ ቀን በማድረግ ሕዝብን ለመዝረፍ ለምን ታቀደ?
የምናደረግውን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንድናድረገው መጽሐፍ ቅዱስ ያዝዛል "እግዚአብሔርን አብን በእርሱ እያመሰገናችሁ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት" ቆላ 3፥17
እንግዲህ እመቤታችን በመንፈስ ቅዱስ የተሞላች ናትና እራሷን ከጌታ ጋር በማወዳደር "በስሜ መታሰቢያየን ያደረገ" የሚለውን ልመና አላቀረበችም ብለን እንደመድማለን፤ እመቤታችን ትሑትና ዝምተኛ ሁሉንም በልቧ ይዛ እግዚአብሔርን የምትጠብቅ እጅግ የተቀደሰች እናት ናት። ስሜ ይጠራልኝ በሚል ስሜት ልመና አቀረበች ብሎ በማርያም ላይ መናገር ስድብና ድፍረት ነው።