Tuesday, February 26, 2013

የሻርለት ቅ/ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን በአቡነ መርቆሬዎስ የፓትርያርክ አስተዳደር ሥር ለመጠቃለል ወሰነች!



በአሜሪካ ኖርዝ ካሮላይና  በ9400  መንገድ ላይ የምትገኘው የሻርለት ቅ/ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ራሷን ችላ የቆየችበትን ጊዜ ከግምት ውስጥ በማስገባትና አሁን እየታየ ባለው መንፈሳዊውን ሥልጣን ወደቡድናዊ ሽኩቻ የማውረድ እንቅስቃሴ በመገምገም  በአቡነ መርቆሬዎስ ሲኖዶስ ሥር ለመጠቃለል መወሰኗን የቤተክርስቲያኒቱ ሊቀ መንበር ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶ/ር ዮሐንስ ጉግሳ በተለይ ለሚዲያ  ገልጸዋል።


በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረገውን የቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴ በቅርበት እየተከታተሉ እንደቆዩና ጉዞው ሁሉ ከድጡ ወደማጡ እየሆነ በመሄዱ ለዚህ ውሳኔ የቤተ ክርስቲያኒቱን አባላት እንዳደረሳቸውም የገለጹ ሲሆን ከእንግዲህ ወዲያ በኢትዮጵያ ላለው ሲኖዶስ እውቅና ባለመስጠት ውሳኔ ላይ በመድረሳቸው የአቡነ መርቆሬዎስን ፕትርክና ለመቀበል ሁኔታዎች እንዳስገደዷቸውም አብራርተዋል።

ዶ/ር ዮሐንስ ማብራሪያቸውን በመቀጠል፤ የቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነትና ሰላም እንዲጠበቅ የፖለቲካው አመራር እጁን ማስገባት እስካልተወ ድረስ ችግሮች መቼም ሊያበቁ እንደማይችሉ የገመገምን ሲሆን ከእንግዲህ አዲስ አበባ ባለው ሲኖዶስ የሚነሳውን ክርክር እያዳመጥን ምን አዲስ ነገር ይመጣ ይሆን? በማለት ጊዜ ማጥፋት እንደሌለብን በማመናችን ወደዚህ ውሳኔ ደርሰናል ሲሉ ገልጸዋል። ስለሆነም ከእንግዲህ ወዲያ የኖርዝ ካሮላይና ቅ/ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ለአቡነ መርቆሬዎስ አመራር እውቅና በመስጠት ፓትርያርካችን አድርገናቸው ተቀብለናል በማለት አጠቃለዋል።

Monday, February 25, 2013

ያሳዝናል! ያሳዝናል! ያሳዝናል!...... (የሐራ ዘተዋሕዶ ዘገባ)

 (To read in PDF please Click here )

አንድ ጥያቄ እናስቀድም፤ ለመሆኑ ኢትዮጵያ ካለው የአሜሪካ ኤምባሲ ይልቅ የኢትዮጵያ መንግሥት አሜሪካዊ ዜጋ ስለመሆንና አለመሆን ጉዳይ ይመለከተው ይሆን? ለማንኛውም «ሐራ ዘተዋሕዶ» መሳጩን የሲኖዶስ ውይይት በቦታው የነበረ ያህል በአስደማሚ ዘገባ አቅርቧልና እንዲያነቡት እነሆ!

‹‹ቤተ ክርስቲያን ስትጠራኝ እምቢ እላለኹ ወይ ! ! !›› /ብፁዕ አቡነ ማትያስ/

    ‹‹አጃቢ ነን!›› /ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል/

    ‹‹እንኳን አይደለም ፕትርክናው ጵጵስናውም ከብዶኛል፤ እኔ እጠፋለኹ›› /ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ/

    ‹‹እኛ መናጆ ተብለን ነው የገባነው፤ የሚመረጠው አባ ማትያስ ነው›› /ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ/

    ‹‹ነገ በታሪክ የሚጠየቅና የሚወገዝ ሲኖዶስና አባት መኖር የለበትም›› /ብፁዕ አቡነ ገብርኤል/

ከላይ በዋናው ርእስ የተመለከተው÷ ቁጭት እንጂ አቅም ያነሳቸው ንግግሮች የተሰሙት ትላንት፣ የካቲት 16 ቀን 2005 . በፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴው በቀረቡት ዕጩዎች ላይ ለመወያየት የተሰበሰበው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውል ያለው ግልጽ ውሳኔ ላይ ሳይደርስ ከቀትር በኋላ በተጠናቀቀበት ወቅት ነው፡፡

በስብሰባው ሂደት÷ ለፕትርክናው የተሠየሙትን ብፁዕ አቡነ ማትያስን ጨምሮ ተሳትፎ በነበራቸው ብፁዓን አባቶች መካከል የነበረው የከረረ የቃላት ልውውጥ፣ ተሳትፎ ባልነበራቸው ብፁዓን አባቶች ላይ የታየው ስጋትና ድብታ፣ በኮሚቴው ዋና ጸሐፊ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጩ ምትክ የኮሚቴውን ሪፖርት ያቀረበው የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊው ለቅ/ሲኖዶሱ ጠረጴዛና ለአጀንዳው ታላቅነት የማይመጥን፣ ውክልናውና ያጸደቀለትን ማኅበር የሚያስንቅና የሚያስወቅስ ደርዝ የሌለው ንግግር፣ በዋናነትም ስብሰባው የተጠናቀቀበት ውል አልባ ኹኔታ ነው ይህን የሐዘን ንግግር ያናገረው፡፡ በዚህ ቃል ሲናገሩ ከተሰሙት አረጋውያኑ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጥቂቱን ለመጥቀስ÷ አቡነ አትናቴዎስ፣ አቡነ ኤርሚያስ፣ አቡነ አረጋዊ፣ አቡነ ኤፍሬም እና ከዕጩዎች አንዱ አቡነ ማቴዎስ ናቸው፡፡

ስብሰባው ጠዋት 300 ላይ በውዳሴ ማርያም፣ መልክአ ኢየሱስ እና መልክአ ማርያም ጸሎት ከተከፈተ በኋላ ዐቃቤ መንበሩ የዕለቱን የስብሰባ አጀንዳ ሲያስተዋውቁ፣ ‹‹የአስመራጭ ኮሚቴውን ሪፖርት ሰምተን ለማጽደቅ ነው፤›› በሚል ነበር ያስጀመሩት፡፡ የአስመራጭ ኮሚቴው አባላት ተጠርተው ገብተው በሕዝብ ግንኙነት ሓላፊው በኩል የዕጩዎች አመራረጥ፣ ዝርዝርና ማንነት በንባብ ከተሰማ በኋላ የነበረው የስብሰባው ድባብ ግን፣ ሰምቶ ማጽደቁ ቀርቶ የተጋጋሉ ውይይቶችንና ትችቶችን ያስተናገደ፣ ከሕዝብ ግንኙነት ሓላፊው በቀር ብዙኀኑ የኮሚቴው አባላት አንዳች የውስጥ ክፍፍልን በሚያሳብቅ አኳኋን (በተለይም ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ) በእጅጉ አዝነውና ተክዘው የታዩበት፣ ኮሚቴው ከብፁዓን አባቶች ለቀረቡለት ጥያቄዎች የተረጋገጠ መልስ ሊሰጥ ያልቻለበት አሳዛኝ ኹኔታ ነበር፡፡

ኮሚቴው የተረጋገጠ ወይም በቂ ያልኾነ ምላሽ ሊሰጥባቸው ያልቻለባቸውና ለተካረረ መንሥኤ የኾኑ ዋነኛ ነጥቦች፣ የመጀመሪያው÷ ዕጩ ፓትርያሪኮች የቀረበቡበት መንገድ የምርጫ ሕገ ደንቡ ተሟልቶ ያልተፈጸመበት መኾኑ ነው፤ ሁለተኛው÷ የምርጫው ሂደትና ጠቅላላ ኹኔታ ለውጭ ኀይሎች ተጽዕኖ እና ለውስጥ ቡድኖች ፍላጎት የተጋለጠ መኾኑ ነው፡፡ እኒህን አከራካሪ ነጥቦች በየጊዜው ባወጣናቸው ዘገባዎች እያጋለጠናቸው ቆይተናል፤ እስኵ አሁን ደግሞ በስብሰባው ሂደት ከተንሸራሸሩት ሐሳቦች አንጻር በመጠኑ እንመልከታቸው፡፡

በምልአተ ጉባኤው ስብሰባ ከዋነኛ አነጋጋሪ ነጥቦች አንዱ÷ የምርጫው ሂደትና ጠቅላላ ኹኔታ ለውጭ ኀይል ተጽዕኖ እና ለውስጥ ኀይሎች ጥቅማዊ ፍላጎት የተጋለጠ መኾኑ ነው፡፡ የውጭ ኀይል ሲባል ሌላ ማንም ሳይኾን የመንግሥት ተጽዕኖ ማለታችን ነው፡፡


«በር ድብደባን ያየ፤ እስኪያፈጡበት አይጠብቅም»


ምሁራን ታሪክ ራሱን ይደግማል ይላሉ። አቡነ መርቆሬዎስን የደርግ ጳጳስ በማለትና ከእርስዎ ጋር ከእንግዲህ አብረን ልንሰራ አንችልም ማለቱ የሚነገርለት ኢህአዴግ ዛሬ ደግሞ ያንኑ ታሪክ ደግሞ የኢህአዴግን ፓትርያርክ ለመሾም የቤት ሥራውን ማጠናቀቁን ስናይ ኢህአዴግ ዘመናዊ ደርግ ሆኗል ወይም ደርግ ራሱ ተመልሶ መጥቷል የሚያሰኝ ነው። በአቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክነት ምርጫ ላይ የኢህዴግ ድጋፍ መኖሩ ባይካድም እንደዚህ ዓይነት ዓይን ያወጣ ጣልቃ ገብነት ግን በፍጹም አልነበረም። በወቅቱ ሥልጣኑን በለቀቁት ፓትርያርክ ላይ ቅሬታና ኩርፊያ የነበራቸው ወገኖች ብዙ ስለነበሩ የአዲስ ፓትርያርክ ፊት ለማየት ተፈልጎ ስለነበር አብዛኛው ሰው ስለአቡነ ጳውሎስ ትምህርት፤ችሎታ፤በደርግ እስር መሰቃየትና የመሳሰለውን የህይወት ታሪካቸውን ከግንዛቤ አስገብቶ ድምጹን የሰጠው ወገን ብዙም ውትወታና ልመና አላስፈለገውም  ነበር። በመንግሥትም በኩል ከፈቃደኝነቱ በዘለለ እንደዘንድሮው ዓይነት ግልጽ የሆነ ጣልቃ ገብነት ሳያደርግ ምርጫው መጠናቀቁን እናስታውሳለን።  በቀድሞው ዓይን የዛሬውን ስናየው ደርግ የራሱን ፓትርያርክ ሲያስመርጥ ከነበረው ጋር በተመሳሳይ መልኩ ኢህአዴግ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ሁለተኛው ደርግ መሆኑን እያሳየ ይገኛል። ከሁሉም ነገር ሊገባን ያልቻለው ጉዳይ ኢህአዴግ አቡነ ማትያስን ፓትርያርክ አድርጎ በመሾም የሚያተርፈው ምንድነው? አቡነ ማትያስስ ፓትርያርክ ስለሆኑ ኢህአዴግን የሚጠቅሙት እንዴት ነው፤ የሚለው ጥያቄ ግልጽ አልሆነልንም።
«አትረፍ ያለው በሬ ቆዳው ከበሮ ይሆናል» እንዲሉ ሆኖ ይመሩታል ከሚባለው የምእመናን ኅብረት ጋር  የመረጥነው አባታችን ተብለው ፍቅርና ክብር ካልተቸራቸው፤ እንዲሁም ርዕሰ መንበር ለሆኑለት ቅዱስ ሲኖዶስ  በኢህአዴግ ፓትርያርክነት ተፈርጀው በረባ ባልረባው አተካሮ በማስተናገድ ሰላምና እረፍት በማጣት  የተነሳ ዘወትር ያለኢህአዴግ ድጋፍ መኖር የማይችሉ የዘመመ ቤት ሆነው እሳቸውን ለመደገፍ በመታገል ጊዜውን ከሚጨርስ በስተቀር ኢህአዴግ ምንም ዓይነት ትርፍ  ከአቡነ ማትያስ አያገኝም። አቡነ ማትያስም ኢህአዴግን በምንም ጉዳይ ደግፈው ሊያቆሙት አይችሉም። ጉዳዩ በኢህአዴግ በኩል እኔ የፈለግሁት ፓትርያርክ ይሁን ከሚልና አቡነ ማትያስም ከምእመናን የምርጫ ድጋፍ ይልቅ የኢህአዴግን ጥሪ እንደመንፈስ ቅዱስ ምርጫ አድርጎ የመቀበል የሥልጣን ጥማት  ውጤት ነው።  በማንኛውም ሚዛን የወረደ የደካሞች አእምሮ የፈጠረው ስሌት ከመሆን ውጪ አይደለም።