Wednesday, August 22, 2012

የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አስከሬን ወደ ሀገር ቤት ተመለሰ።




የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስከሬን ትናንት ማታ አራት ሰዓት አካባቢ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ደርሷል። ሚኒስትሮች፤ አምባሳደሮችና ቤተሰቦቻቸው በተገኙበት አስከሬናቸው ታጅቦ ወደ ቤተመንግሥት አምርቷል። ብዙዎችም በልቅሶ ሸኝተዋል። የቀብር ሥርዓቱን የሚያስፈጽሙ አባላት የተዋቀሩ ሲሆን ወደፊት በሚገለጽ መርሃ ግብር ቀብራቸው እንደሚፈጸም ቀደም ሲል ተገልጿል።
ላለፉት 21 ዓመታት የሀገሪቱ መሪ ሆነው ያገለገሉት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን በመንግሥት ቴሌቪዥን ከተለገጸ በኋላ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፤ ታዋቂ ግለሰቦች፤ የውጭ ሀገራት መሪዎችና ዲፕሎማቶች የሀዘን መግለጫዎቻቸውን እየላኩ ይገኛሉ። የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥርዓተ ቀብር እስኪፈጸም ድረስ የሀዘን ቀን እንዲሆንና የሀገሪቱም ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ መወሰኑን አውጇል።

በዚሁ በተቃራኒ መልኩ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት ደስ የተሰኙ፤ የኢትዮጵያ ነጻነትና የፖለቲካ አፈና አበቃለት የሚሉ፤ እኛ መግደል ቢያቅተን እግዚአብሔር ወይም አላህ ገደልልን የሚሉ ድምጾች እየተስተጋቡ ይገኛሉ። በተለይም ከወደ ዳያስፖራው ያሉ ኢትዮጵያውያን እንኳን ሞቱልን የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም።  በተለይም በፓልቶክ የቀጥታ ውይይቶች ላይ «ዛሬ ነው ድሌ» የሚሉ ጭፈራዎችን ሲያስተጋቡ መስማት አስገራሚው  ነው። በእርግጥ አቶ መለስን ጠንካራ፤ ታታሪ፤ ብልህና አዋቂ አድርገው የሚደግፏቸው ጥብቅ  አጋርና ወዳጆች እንዳሏቸው ሁሉ እንደ ማንኛውም ሰውና እንደ አንድ ሀገር መሪ ሊኖርባቸው በሚችል ሰውኛ ድክመቶች፤ የሚወቀሷቸው ወይም ባለባቸው ጉድለት የሚያዝኑባቸውም ጥቂቶች አይደሉም።
ነገር ግን እግዚአብሔር እንደወደደ ባደረገው ስልጣኑ ላይ ገብተው የሚጠሏቸው ሰዎች በመዝፈን፤ በመሳለቅና «ዛሬ ነው ድሌ» በማለት በሞት ላይ ፌሽታ ማድረግ በምንም  መመዘኛ ከሰብአዊነት አእምሮ የሚነጭ ሊሆን አይችልም።
ደጋፊዎችም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ፍጹማዊ ሰው እንደነበሩ አድርገው ከማሰብ እንዲርቁ፤ የሚጠሏቸውም በሞታቸው እልል ከማለት የጥላቻ ሁሉ ጥግ እንዲወጡ ለማስገንዘብ እንወዳለን። 
ሞት የሁሉም ሰው ጽዋ ነውና ከፊታችን ባለው ነገር ላይ ደስ ከመሰኘት ይልቅ ከሞት በኋላ ባለው ሕይወት ውስጥ የእያንዳንዳችን ድርሻ ምን ሊሆን እንደሚችል ማሰቡ ላይ ማተኮሩ የተሻለ ነው።


በሌላ መልኩም «ደጀ ሰላም» ብሎግ የቅዱስ ፓትርያርኩ የጠለቀ ሀዘኑን በመግለጽ የብሎጉን የፊት ገጽ ለዚሁ መግለጫ ማዋሉን ስንመለከት ደጀ ሰላም ብሎግ፤ ፓትርያርኩ ከሞቱለት በኋላ እንደዚህ ፍቅር ያሲያዘው ነገር አልገለጽ ብሎናል። ምክንያቱም ስማቸውን ሲያጠፋ፤ የሙስና አባት፤ የቤተክርስቲያኒቱ ጠላቶች ወዳጅ፤ የተሀድሶዎች ጋሻ እያለ ሲጠራቸው እንዳልነበርና፤ በስልጣን ላይ እስካሉ ድረስ የቤተክርስቲያን ሰላም የለም ይል የነበረውን ዘገባዎቹን ሁሉ ትቶ አሁን የልብ ወዳጄና ዘላለማዊ እረፍት ሊያሰጣቸው የሚችል የመልካም ስራ ባለቤት ናቸው ብሎ ያመነ በመምሰል ከአብርሃም እቅር ይረፉልኝ ማለቱ ተሳልቆ ካልሆነ በስተቀር ሲወዳቸው ለኖረ አባት የቀረበ ጸሎት አይደለም። ድሮም ክፉ ሰው በከንፈሩ ይሸነግላል ተብሎ ተጽፏልና ይህ ሸንጋይ ድረ ገጽ ከሞቱልኝ ወዲህ ምን አገባኝ፤ ከአብርሃም እቅፍ ያኑርልኝ የማልል፤ ባለቤቱ ከፈለገ እንጦሮጦስ ይጨምራቸው የሚል የክፉ ሰው ሽንገላ ጸሎት ካልሆነ በስተቀር ደጀ ሰላምና አባ ጳውሎስ ዓይንና ናጫ እንደሆኑ እስከሞታቸው ድረስ መዝለቃቸውን ማንም ኅሊና ያለው ሰው ያውቀዋል። አንድም ቀን በሰላም አባትነት፤ በእምነት አባትነት፤ በፍቅር አባትነት፤ አመስግኗቸው እንደማያውቅ የማናውቀው ይመስለው ይሆን?

ደጀ ሰላም ሆይ እስኪሞቱልህ ድረስ ስትወቅሳቸው ኖረህ፤ ከሞቱልህ በኋላ መጸለይህ ለእሳቸው ያለህን ፍቅር እየገለጽህ ነው ወይስ ቋሚዎቹን ሰዎች እንደምወዳቸው እወቁልኝ ለማለት ነው? የልብንማ እግዚአብሔር ይመረምራል።

Tuesday, August 21, 2012

ሰበር ዜና፤ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ተገለጸ።




ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አረፉ።
ሕወሀትን በመምራትና ኢህአዴግን በማዋቀር ትልቅ ሚና የነበራቸውና ከደርግ ውድቀት በኋላም የሀገሪቱ ርእስ መንግሥት ሆነው ላለፉት 21 ዓመት የቆዩት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን ዛሬ ነሀሴ 15/2004 ዓ/ም በይፋ ለሕዝብ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተነግሯል።
አቶ መለስ ዜናዊ እድሜአቸውን ሙሉ በትግል ያሳለፉ፤ በዚሁ ትግል ውስጥ እያሉ በሞት የተለዩ ትልቅ መሪ ነበሩ። በሞታቸው ሃዘናችንም ጥልቅ ነው።
እግዚአብሔር ለወዳጅ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የሀዘን ጽናቱን ይስጥ!

Monday, August 20, 2012

ሰበር ዜና፤ በማኅበረ ቅዱሳን ትእዛዝ የተሰበሰበው ሲኖዶስ አቡነ ናትናኤልን በዐቃቤ መንበርነት ሾመ።



ሸምቆ ወጊው ማኅበር ብጹእ አቡነ ናትናኤልን ዐቃቤ መንበር ለማድረግ ዛሬ 14/12/ 2004 ዓ/ም  ሲኖዶሱን በጠራው ዘመቻ መሠረት ይህንኑ አስፈጽሞ ዓላማውን አሳክቷል።
ከዓውደ ምሕረት ብሎግ ያገኘነውን ዘገባ እንዳካፈልናችሁ ሁሉ ጉዳዩን በቅርብ ስንከታተል ቆይተን የዛሬው የሲኖዶስ ጉባዔ በማኅበረ ቅዱሳን እቅድ መሠረት ብጹእ አቡነ ናትናኤልን ዐቃቤ መንበር ማስደረግ እንደቻለ ምንጮቻችን አስረድተዋል። ብጹእ አቡነ ናትኤል ከእርጅና የተነሳ ራሳቸውን መቆጣጠር ከማይችሉበት ደረጃ መድረሳቸው እየታወቀ በአስቸኳይ መምረጥ ያስፈለገው አቅም ኖሯቸው ስራ ይሸፍናሉ ተብሎ ሳይሆን ከሳቸው ጀርባ የሚፈለገውን ስራ ለማከናወን እንዲቻልና የፓትርያርክነቱን ስልጣን በእነ አቡነ ጢሞቴዎስ አቀናባሪነት ወደ አቡነ ማትያስ እንደማቅ እቅድ ደግሞ ወደ አቡነ ሉቃስ ላይ ለመወርወር እቅድ እንደተያዘ ውስጥ አዋቂ ምንጮቻችን አስረድተዋል።

የሲኖዶሱ ዋርካ አቡነ ጳውሎስ ከወደቁለት ወዲህ ሸምቆ ወጊው ማኅበር «አልጋ ባልጋ ነው መንገዱ፤ ወደ ቅዱስ ሲኖዶስ ሰርጎ ለመግባት ሲሄዱ» የሚል መዝሙር መዘመር ከሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት ይቻላል። ተጨማሪ ዘገባ እንደደረሰን እናቀርባለን።