Wednesday, June 20, 2012

ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎቹን አስመረቀ



(ምንጭ፦ ዐውደ ምህረት)
    መምህር አሰግድ ሳሕሉም ከተመራቂዎቹ አንዱ ነው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በስሯ ከምታስተዳድራቸው መንፈሳዊ ኮሌጆች መካከል አንዱና 69 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ የሆነው አንጋፋው ቅድስት ሥላሴ ኮሌጅ ያስተማራቸውን ደቀ መዛሙርት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በተገኙበት አስመረቀ። የምረቃ ፕሮግራሙ ደማቅ የነበረ ሲሆን ተማሪዎቹ ቤተክርስቲያንን በቅንንነትና በመልካም ሥነ ምግባር ለማገልገል ቃል ገብተዋል። አዳራሹ በተመራቂዎችና በቤተሰቦቻቸው የተሞላ የነበረ ሲሆን በእያንዳንዱ ተማሪ ፊትም የሚታየው ደስታ ስሜት ልዩ ነበር። በዕለቱ አባታዊ ቡራኬ የሰጡት  ቅዱስ ፓትርያርኩም  “…ያለፉትን ዘመናት መሰናክሎችን እያለፍን መምጣታችን ስለምናውቅ ያለፉትንም ያለፍነው በራሳችን ስላልሆነ አሻጋሪውን አምላክ ከሁሉ በፊት እናመሰግናለን። እናንተ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በኃላፊነት ላይ ነው ያላችሁት እያስረከብናችሁ ነው። በዚህ የተመደበ ሌላ ሥራ የለውም የወንጌል ሥራ በትርፍ ጊዜ የሚሰራ አይደለም። ሁሉንም የምንማረው በጊዜ ነው። ከዚህ በፊት ተምረው የወጡ ብዙ ናቸው። በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ያሉ የገቡትን ኪዳን ይፈጽሙ አይፈጽሙ ተመልካቹ አምላክ ነው። መለኮታዊ አደራ ስለሆነ።….” በማለት አባታዊ መልዕክት አስተላልፈዋል።

Tuesday, June 19, 2012

«አዎ! ዛሬም ሰዎች የእምነት ነጻነታቸው ይታፈናል!»


    የዛሬን አያድርገውና አፄ ሱስንዮስ ኮትልከዋል/ካቶሊክ ሆነዋል/ በሚል የምታ ነጋሪት፤ ክተት ሠራዊት ዘመቻ የጎንደር አደባባይ  በደም መጨቅየቱን፤ ሰማዕትነት አያምልጥህ በሚል  ጥሪ በአንድ ቀን ብቻ ከስምንት ሺህ ሰዎች በላይ ማለቃቸውን  ከተዘገበው አንብበናል። አፄ ሱስንዮስም ካቶሊክ ከመሆናቸው የተነሳ እግዚአብሔር ተቆጥቶ ምላሳቸው አንድ ክንድ ያህል ተጎልጉሎና ወደ ቀደመ መጠኑ አልመለስ ብሎ ካስቸገረ በኋላ እያጓጎሩ እንደሞቱ በጽሁፍም፤ በአደባባይም እስከዛሬ ይተረካል። የያኔው ካቶሊክና የዛሬው የኢትዮጵያ ካቶሊክ በእግዚአብሔር ዘንድ ያላቸው ቅጣት ይለያይ እንደሆነ የአፄውን የትረካ ታሪክ ፈጣሪዎችን  እየጠየቅን፤ እኛ ግን እስከሚገባን ድረስ  ሱስንዮስ ካቶሊክ ለመሆን እምነቱን ስለለወጠ  እግዚአብሔር ምላሱን አንድ ክንድ ጎልጉሎ ገደለው የሚለው  ታሪክ የፈጠራ ውጤትና ካቶሊክነት  ከተቀበልክ ምላስህ እየተጎለጎለ ትሞታለህ የሚል  ሽብር በህዝቡ ውስጥ ለመርጨት ረበናት የፈጠሩት ተንኮል እንጂ  ዛሬ በኢትዮጵያ ያሉ ካቶሊኮች ሁሉ ምላሳቸው እየተጎለጎለ በየሜዳው ሞተው ባለቁ ነበር።  እየጨመሩ እንጂ እየጠፉ መሆናቸውን አላየንም።

የሚያሳዝነው ነገር እግዚአብሔርን  ጨካኝና  ርኅራኄ የለሽ አድርጎ በመሳል ይኼው ተረት እስከ ዛሬ በአደባባይ እየተነገረ መገኘቱ ነው።  ሰዎች የእውነትን ወንጌል በተከታዮቻቸው መካከል በማዳረስ ከእምነታቸው ሳይናወጡ፤ ጸንተው ከአምላካቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት የጠበቀ እንዲሆን ማድረግ ሲያቅታቸውና ሌላ ተገዳዳሪ እምነት ብቅ ብሎ ቀዬና መንደሩን ሰፈርና ሀገሩን በትምህርቱ ሲበጠብጠው፤  ወዮልህ! ኮንትሮባንድ ሃይማኖት መጣልህ፤ ከእነሱ አዳራሽ ከገባህ አትመለስም፤ ምናምን ያቀምሱሃል! ወደሚል የጭራቅ ሊበላህ ነው ማስፈራሪያ ጩኸታቸው ይገባሉ። ወንጌሉን በሰዎች ልቡና ዘርተው መልካም ፍሬ ማፍራት ሲሳናቸው ከማስፈራሪያው ባሻገር መጤ የተባሉትን ቤተ እምነቶች ወደማፍረስና አማኞቹንም ወደ መግደል ይወርዳሉ። ዛሬ ወንጌላውያን የሚባሉት ኢትዮጵያውያን ቤተ እምነቶች አሁን ላሉበት ደረጃ የደረሱት ተገድለው፤ ተሰደው፤ ታስረው፤ ተገርፈው፤ ተቃጥለው ስለመሆኑ ማንም ኅሊና ያለው ሰው የሚዘነጋው ነገር አይደለም። 

Monday, June 18, 2012

«ፍቅር ለይኩን ያቀረበው ትችት ውሃ የማይቋጥር ወንፊት ነው»

 
በአባ ሰላማ ድረ ገጽ ላይ «ፍቅር ለይኩን» የተባለ ሰው ስለየትኞቹ  ስም አጥፊ ብሎጎች ለመናገር እንደፈለገ ስማቸውን  ባይገልጽም እሱን ደስ ያላሰኘውን ነጥብ በማመልከት፤ የሰዎችንም ኃጢአት መዘርዘር ጥሩ እንዳልሆነ  መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶችን በማስረጃ አቅርቦ ምክርና ተግሳጽ ለመስጠት ሲሞክር ተመልክተናል።
ይህ በአባ ሰላማ ድረ ገጽ ላይ ጽሁፉን ያቀረበው «ፍቅር ለይኩን» የተባለው ሰው ፤ በፖለቲካው ዓለም ደከመን፤ ሰለቸን  ሳይሉ የኢሕአዴግን መንግሥት በማጥላላትና በመቃወም ሌሊትና ቀን በሚደክሙት ድረ ገጾች ላይ የተለያዩ ፖለቲካዊ መጣጥፎችንና አንዳንዴም መንፈሳዊ መሰል የነቀፋ ጽሁፎችን  የሚያቀርበው የደቡብ አፍሪካው «ፍቅር ለይኩን»  መሆኑን የምናውቀው ከስሙ ባሻገር «ሻሎም፤ ሰላም» በሚለው የጽሁፉ ማሰረጊያ  ቃል የተነሳ እሱነቱን ብንገምት ከእውታው የራቅን አይመስለንም።
ከዚህ ተነስተን ስለአቶ ፍቅር ለይኩን  ጽሁፍ ጥቂት ለማለት እንወዳለን።
 አቶ ፍቅር ስለአባቶች መዋረድና አለመከበር ተገቢ መሞገቻ ይሆነው ለመከራከሪያነት የተጠቀመበትን ዐውደ ጥቅስ  በማስቀደም እንጀምር።
‹‹ደፋሮችና ኩሩዎች ሆነው ሥልጣን ያላቸውን ሲሳደቡ አይንቀጠቀጡም፣ ዳሩ ግን መላእክት በኃይልና በብርታት ከእነርሱ ይልቅ ምንም ቢበልጡ በጌታ ፊት በእነርሱ ዘንድ የስድብን ፍርድ አያመጡም…፡፡›› ፪ጴጥ ፪፣፲፩፡፡
ይህን ጥቅስ አቶ ፍቅር ለይኩን ያቀረበው ምንም ይስሩ ምንም፤ ምንም ያድርጉ፤ የቱንም ያህል ይበድሉ፤  ስለ ጳጳሳት አትናገሩ፤ ምክንያቱም ወንጌል አትናገሩ ብሏልና ሲል የአፍ መዝጊያ ጥቅስ በማቅረብ ሊሞግተን ይፈልጋል። ጥቅሱ ስለማን እና ስለምን እየተናገረ እንደሆነ ግን አያብራራም። መቼም ምግባረ ብልሹና የጥፋት ኃይል ለሆኑ ሹመኞች ሁሉ እንድንገዛ የተነገረ ነው  እንደማይለን ተስፋ እናደርጋለን። እንደዚያማ ከሆነ አቶ ፍቅር የኢህአዴግ መንግሥት ክፉና መሰሪ ነው፤ የአባ ጳውሎስ አስተዳደር አጥፊና ከፋፋይ ነው እያሉ ለኢህአዴግ ውድቀት በሚሰሩ ድረ ገጾች ላይ ጽሁፎቹን ሲለቀልቅ ባልዋለም ነበር። ምክንያቱም ወንጌል እንደዚህ ሲል ያስጠነቅቀዋልና።
ስለ ጌታ ብላችሁ ለሰው ሥርዓት ሁሉ ተገዙ፤ ለንጉሥም ቢሆን፥ ከሁሉ በላይ ነውና፤
ለመኳንንትም ቢሆን፥ ክፉ የሚያደርጉትን ለመቅጣት በጎም የሚያደርጉትን ለማመስገን ከእርሱ ተልከዋልና ተገዙ። 1ኛ ጴጥ 2፤13-14
ኢህአዴግን መቃወምም ሆነ መደገፍ መብት በመሆኑ ጸረ ኢህአዴግ ድረ ገጾች አቋማቸውን ግልጽ አድርገዋል። የማያሻማ ሆኖ «ለንጉሥም ቢሆን ተገዙ፤ ክፉ የሚያደርጉም ቢሆኑ መኳንንቱ ከላይ ተልከዋልና» የሚለውን የወንጌል ቃል ጨቋኞች፤ አምባገነኖችንና አላውያን መሪዎችን ሁሉ አሜን ብለን እንድንሸከም የሚናገር ቃል አይደለም ከሚል ጽንሰ ሃሳብ የተነሳ እየታገሉ ይገኛሉ። አቶ ፍቅር ደግሞ በነዚያው ድረ ገጾች ስሜቱን በጽሁፍ እየገለጸ ሲያበቃ  ከወንጌል ቃል ጠቅሶ ለምግባረ ብልሹዎችና ለሥርዓት አፍራሾችም ቢሆን ተገዙ በማለት ሊያስተምረን ይፈልጋል። ምነው ጽሁፎቹን ለሚያቀርብባቸው ድረ ገጾች የእናንተ ተቃውሞ ቃለ እግዚአብሔርን የተጻረረና ሕገ እግዚአብሔርን ያፈረሰ ስለሆነ አርፋችሁ ተቀመጡ፤ ዝም ብላችሁም ለኢህአዴግ ተገዙ! የሚል ምክርና ጽሁፍ ያላቀረበላቸው? ብለን ስንጠይቅ የምናገኘው መልስ እኔና መሰሎቼ የምንጠላው ሲጻፍበት እንጂ የምናወዳቸው ሲነኩብን ያመናል የሚል ቃና ይሰጠናል።