Sunday, November 6, 2011

እኔ በእግዚአብሔር የምታወቅበት ማንነት!


በዚህ ምድር ሳለን እውቀታችን ያች ትንሿ ጭንቅላታችን በሚመጥናት መልኩ የያዘችውን ያህል ብቻ ታውቃለች። ከዚያ በላይ ልሁን ብትልም መስፋት ከምትችለው በላይ አትወጣም። ዓለም ባላት እውቀት የምታውቀው ማወቅ የቻለችውን ያህል ብቻ ነው። የሰው አእምሮ ከምታውቀው በላይ ለመሆን ብትሞክር የእውቀት መቋጠሪያዋ ይበጠስና የያዘችው ማፍሰስ ሲጀምር ሰው ለመባል ያበቃትን ማንነት ትስትና አጠቃላይ እኛነታችንን ወደ ሌላ ምዕራፍ ታሸጋግራለች። ወደ እብደት ወይም ወደ እንስሳት ጠባይዓት ማለት ነው።
አንደኛው የዓለም ጦርነትም ይሁን ሁለተኛው የዓለም ጦርነት መነሻቸው ሰው ካለው እውቀት በላይ ለማምጣት በተመኘ እውቀት የተከሰተ ነው። ምናልባትም ሶስተኛው የዓለም ጦርነት ሊመጣ የሚችለውና የከፋ የሚያደርገውም የሰው እውቀት ከማወቅ ጣሪያ በላይ ለመውጣት በሚያደርገው ጥረት ወዳለማወቅ ተሻግሮ የሚጎትተው እብደትና የእንስሳነት ጠባይ መገለጫ ሊሆን ይችላል።
ይህንንም ጥንታውያን አበው«እጅግም ስለት፤ ይቀዳል አፎት»ይላሉ። መጽሐፍ ቅዱስም የእግዚአብሔር ቁጣ እንዲርቅና የተመዘዘው ሰይፍ እንዲመለስ ሲያመለክት እንዲህ ሲል ይነግረናል። «አንተ የእግዚአብሔር ሰይፍ ሆይ፥ ዝም የማትለው እስከ መቼ ነው? ወደ ሰገባህ ግባ ጸጥ ብለህም ዕረፍ » ኤር 47፤6
በምድራችን ላይ የሚታየው የጦርነት፤ የእልቂት፤የእርስ በእርስ መበላላት፤ የበሽታና የረሃብ ክስተቶች ሁሉ የሰው እውቀት ያመጣው ጣጣ እንጂ የፈጣሪ ፈቃድ አይደለም። ምክንያቱም የያዝነው የዘመኑ እውቀት ስለቱ ለመኖርያ የተሰጠውን አፎት ዓለምን እየቀደደ በመገኘቱ ሰው ሰውኛነቱን ወደመካድ እብደትና እንስሳነት እውቀት እየተሸጋገረ በመገኘቱ የተነሳ ነው። እንዲሁም ይህ ሰይፍ ወደሰገባው (አፎቱ) የማይመለሰው የሰው ልጅ ያለው እውቀት እግዚአብሔር እሱን (የሰው ልጅን) እንዴት እንደሚያውቀው ለማወቅ ከመፈለግ ውጪ ስለሆነ ነው። በአጭር አገላለጽ ሰው ስለእግዚአብሔር ያለው እውቀት እሱ ማወቅ የሚችለውንና ለማወቅ የሚፈልገውን ያህል ሲሆን በአንጻሩ እግዚአብሔር ሰውን እንዴት እያወቀው እንደሆነ ለማወቅ አልቻለም ማለት ነው።

Thursday, November 3, 2011

እርግማንና ረጋሚዎች!



ኢትዮጵያ ቀደም ሲል በኦሪቱ በኋላም በወንጌል የበራላትንና ከእግዚአብሔርም የተሰጣት ከአፍሪካ እስከ በመካከለኛው ምስራቅ ገናና ታሪክ እስከ የመንም ድረስ የነበራትን የግዛት እንዲሁም የጸጋ፤የበረከት፤ መሬቷ ወርቅ፤ ወንዞቿ ወይን፤ ደኖቿ ኤደን፤ ሕዝቦቿ ታታሪ ሆነው የኖሩበትን ዘመን የቀየረውና የገለበጠው ምንኩስና የሚባለው የሰነፎችና «የአጸድቃለሁ፤ እኔም በስራዬ እጸድቃለሁ» የሚለው ማኅበር ከተንሰራፋ በኋላና ወንጌልን አሽቀንጥሮ ቤተመቅደሱን የሞላው ገድል የሚሉት የእግዚአብሔርን ክብር በመጋረድ ቅዱሳን ለተባሉት ክብርና መንቀጥቀጥን እንዲሰጥ የሚያስገድደው መጽሐፍ ቦታውን ከያዘና ተአምር የሚባል የዘርዓ ያዕቆብ የግዝት መጽሐፍ ብዙ ደም አፋስሶ፤ አፍንጫና ጆሮ አስቆርጦ፤ በሕይወት ሳሉ ከጉድጓድ አስቀብሮ የደም መሬት ኢትዮጵያ ላይ ከነገሰ በኋላ ነው። በኦርቶዶክስ ቤ/ክ መጽሐፍ ቅዱስን በደንብ ማንበብ የተጀመረው የፕሮቴስታንት እምነት መጽሐፍ ቅዱስን ይዞ ስለሚሰብክ እሱን ለመቋቋም ተብሎ እንጂ ከእቃ ግምጃ ቤት ወጥቶ አያውቅም። በትግራይ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ መጽሐፍ ቅዱስን ይዞ የታየ ጴንጤ ወይም ካቶሊክ ያሰኝ እንደነበር አይዘነጋም። ድርሳነ ሚካኤልን ወይም የሆነ ተአምርን ከተሸከመ እሱ የወንጌል ሰው ሳይሆን ኦርቶዶክሳዊ እንደሆነ ይቆጠራል።
ሌላው ቀርቶ« ኦርቶዶክሳዊ ሆኖ «ኢየሱስ ጌታ ነው»ብሎ መናገር እንደጴንጤ ያስቆጥራል። ማር 12፤29...ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው» የሚለውን መመስከር ወንጀል ሆኖ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሌለው 78 ሰው ቅርጥፍ አድርጎ በላ የሚባለውን የተረት ታሪክ መናገር እንደክርስቲያን የሚያስቆጥረው በምን ስሌት ነው?

Monday, October 31, 2011

እውነቱን ብንናገር ምን ይለናል?


በዚህች ምድር ላይ ከተስፋፋውና በሰዎች ልቡና ላይ ከተማውን ከመሠረተው አስፈሪ ኃጢአት መካከል እውነትን ለመናገር የሚችል ሰው እየጠፋ መምጣቱ ቀዳሚውን ይዟል። ዓይኑ ያየውን፤ ጆሮው የሰማውን ሽምጥጥ አድርጎ በመካድ ልቡ ያመነጨውን እውነት አድርጎ ማውራትና ማስወራት፤ ይህንንም እንደእውነተኛ ምስክርነት መቁጠር ባህል እየሆነ መጥቷል። ሰዎች ከሥልጣን ኮርቻ ለመፈናጠጥም ሆነ ከሥልጣን ኮርቻ አስፈንጥሮ ለመጣል እውነቱን በሃሰት ቀይሮ እንደዘመናዊ የውጊያ ስልት መሳሪያ አድርጎ ሲጠቀምበትም መታየቱ የአደባባይ ምስጢር ነው። የሀሰት ምስክር ቀርቦበት ሞት የተፈረደበትን፤ ከርቸሌ የወረደውን፤ የተደበደበውን፤ የተንገላታውን፤ መልካም ስሙ የጎደፈውን፤ከማኅበራዊ ኑሮ የተገለለውን፤ ከማእረግ፤ ከሽልማት የታገደውን፤ ረዳት አጥቶ አልቅሶ የቀረውን ሰው ቤቱ ይቁጠረው! በማለት ብቻ ምንም እንዳልተፈጠረ የራሳችንም ሆነ የአካባቢያችንን ሁኔታ ላለመልከት የኅሊናችንን በር መዝጋት እንዴት ይቻለናል? ይልቅስ ለመናገር እንድፈር።
በዚህች ምድር ላይ የሀሰት መንገስ ጉዳይ በሥጋውያን ሰዎች ዘንድ አሳዛኝ መሆኑ ባይካድም አስተሳሰባቸው በሥጋዊ ደማዊ ኅሊና ላይ የሚመሠረት በመሆኑ ሀሰትን እንደመሳሪያ መጠቀማቸው ላይደንቅ ይችላል። አሳፋሪውና አሸማቃቂው ነገር እግዚአብሔርን እናውቃለን፤ የጽድቅ ልጆች ነን በማለት ዘወትር ስለቃሉ በመናገር ላይ ያለነው የእምነት ሰዎች ዘንድ እውነትን በሀሰት ተክተን እንደዘወትር ጸሎት በልባችን ላይ ጽፈን መያዛችንና ጠቃሚ መስሎ በታየን ጊዜና ቦታ ለዓላማችን ማስፈጸሚያ አገልግሎት ላይ ማዋላችን ነው። የሚዋሹ የሃይማኖት ሰዎች ብዙ ጊዜ እውነትን እውነት በምትመስልና ወደእውነት በተጠጋጋች ውበት የሚፈጽሟት ስለሆነ የዋሹ መስሎ አይሰማቸውም ወይም ውሸት መስሎ በተሰማቸው ጊዜ የኅሊናቸውን ቆሻሻ ለማጠብ ትንሽ ናት በምትል ምላሽ ውስጣቸውን አረጋግተው ከመንፈሳዊ ሰውነታቸው ምንም እንዳልጎደለ ራሳቸውን በራሳቸው አሳምነው ያንኑ መደበኛ ውሸታቸውን በተለመደው ጥበብ ይቀጥላሉ።
አንዳንዶቹም መዋሸታቸውን ቢያውቁም ምንም አዲስ ነገር እንዳልተፈጠረና ነባራዊ ክስተት አድርገው በመቁጠር ባገኙት ቦታ ሁሉ የአዞ እንባ እያነቡ፤ ለሃይማኖታቸው የሚውል እስከሆነ ድረስ ይህንኑ በዘመናዊ ውሸት አንዳንዴም ባስ ሲል ዘመነኞቹ «ቀደዳ »የሚሉትን ዓይነት ውሸት የዕለት ሕይወታቸው አድርገው ይዘውት ይታያሉ። ለምሳሌ«ኬንያ ውስጥ አንድ ግለሰብ ባንድ ጊዜ አንድ በርሜል ውሃ ጭልጥ አደረገ የሚልና ጃፓን ከምድር እስከሰማይ የሚደርስ እስክሪብቶ ገበያ ላይ አዋለች» የሚል የውሸትና የቀደዳ ንጽጽሮች ናቸው። እንደዚሁ ሁሉ የሃይማኖት ሰዎች የሚባሉት ይህንኑ የንጽጽር ተግባር ዘወትር ሲፈጽሙት ይታያሉ። ግን ሰዎች እውነትን እንዳይናገሩና ውሸትን ሥራቸው እንዲያደርጉ ያስገደደ ማነው?
ሙሉውን ጽሁፍ ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ