ከእውነቱ (ክፍል ሁለት)
መግቢያ
ስለ ሀልዎተ እግዚአብሔርና ስለ ትምህርተ ድነት በኛ ቤተ ክርስቲያን ተረስቶ ኖሯል፤ አሁንም እንደ ተረሳ ነው፡፡ አምስቱ አዕማደ ምስጢር የሚባል የዶግማ ትምህርት አለ፡፡ ግን እንኳንስ ለህፃናትና ላልተማሩ ሰዎች ዕድሜ ልኩን በቤተ ክርስቲያን ትምህርት ኖርኩ ለሚልም በቀላሉ ሊረዳ አይችልም፡፡ ዋናውና የሕይወት ትምህርት ወደ አንድ ጎን ተጥሎ ነው የኖረው፤ አሁንም ቢሆን ያሰበበት የለም፡፡ ከቃል ትምህርቱ ከዜማው፣ ከቅኔውና ከአንድምታው መቅደም የነበረበት የክርስቶስ ቤዛነት ትምህርት ነው፡፡ ትምህርተ መለኮትን (ቲኦሎጂን) ተማረ ቢባል ትምህርቱ ተንሳፋፊ ነው፡፡ መሠረቱን ለቆ አየር ላይ እየተንጠለጠለ የሚሄድ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን የአመራር መንፈሳዊ አገልግሎትና በምእመናን መካከል እውነተኛው የእግዚአብሔር ፍቅር ፈጽሞ ተረስቷል፡፡ እኔነት፣ ትዕቢት፣ ትምክሕት፣ መናናቅ፣ መገፋፋት፣ መጠላላትና ርኩሰት በክርስቲያኖች መካከል ሰፍኗል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የወንበዴዎች ዋሻ ሆናለች (በጌታችን እንደ ተነገረው)፡፡ ከላይ በጥቂቱ እንደተጠቆመው ከህፃናት ጀምሮ በየዕድሜ ክልሉ ስለ ሀልዎተ እግዚአብሔርና ትምህርተ ድነት መስጠቱ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ፈጽሞ አይታወቅም፡፡ ባሁኑ ጊዜ ሰባክያን ተብዬዎች በየደብሩ ተቀጥረው ምንም ፍሬ የሌለው ጩኸት ያስተጋባሉ፡፡ በሌላ በኩል እያወቁ ዝም ከማለት አሁንም ቢሆን በየደረጃው ትምህርት ለመስጠት የሚያስችል ትምህርትን ብናዘጋጅ ኃላፊነታችንን እንድንወጣ ያስችለን ነበር (ገብረዮሐንስ 2002፡ መግለጫ)፡፡ ይህንን መልእክት የጽሑፌ መንደርደሪያ እንዲሆን የመረጥኩት በውስጤ የሚመላለሰውን የ‹‹ችላ ተብሏልና ወደ እግዚአብሔር ሃሳብና ዓላማ እንመለስ›› ጥያቄ አጭርና ግልጽ በሆነ መንገድ ስለሚያስረዳልኝ ነው፡፡
ደግሞም ቤተ ክርስቲያናችን ያለችበትን መንፈሳዊና አስተዳደራዊ ድክመት እንዲሁም በሰባክያኑ ውስጥ ሳይቀር ተንሰራፍቶ የሚገኘውን ፍሬ አልባነት በማሳየቱ ረገድ በዐይን ያየንና በውስጡ አልፎ ያገናዘበን ሰው ያህል ማስረዳት ስለሚያስቸግር፥ ከእኔ ይልቅ ረዘም ላለ ዘመን ባለፉበት የሕይወት ተሞክሮ ውስጥ ያከማቹትን እምቅ ትዝብት እጥር ምጥን አድርገው ያስተላለፉልንን የእኚህን አባት ቃል ቃሌ አድርጌ መናገር የተሻለ ብቻ ሳይሆን ተገቢም ነው ብዬ ስላመንኩ ነው፡፡ ይህም የሆነው እንደተባለው በውስጡ ላለፉት ሳይቀር ግልጥ ያልሆነ የትምህርት አቅርቦትን፣ ትኩረት ያልተሰጠውንና ወደ አንድ ጎን ተጥሎ የኖረውን ደግሞም አሁንም እንኳ ያሰበበት የሌለውን መንገድ እየተከተልን ይህን ያህል አማኝ አለን እያሉ መመካቱ ገበናችንን ሊሸፍንና በትምህርትና በአስተዳደር ዘርፍ ያለብንን ሥር የሰደደ መንፈሳዊ ችግር ሊሸሽግልን ባለመቻሉ በብዙ ወገኖች ተደጋግሞ እየተነሳ ያለውን ‹‹የትምህርትና የአስተዳደር ተሐድሶ›› ያስፈልጋል ጥያቄ ተገቢነት የበለጠ ትኩረት እንድሰጠውና እኔም እንዳስተጋባው በመገደዴ ነው፡፡ ይህ እንደ ተጠበቀ ሆኖ በክርስቲያናዊ ትምህርት ተኮትኩቶ ያላደገውን ምእመን ግራ እያጋቡ እነርሱ ጭምር በውል ወዳልተረዱትና በምናልባት ወደሚጓዙበት ፍልስፍና ሲጎትቱት የሚስተዋሉት ‹‹ፍሬ የሌለው ጩኸት የሚያስተጋቡት ሰባኪያን ተብዬዎች›› ሁኔታዎች ያስገኙላቸውን ክፍተቶች ተጠቅመው እየዘሩት ያለውን የትምህርት እንክርዳድ ነቅቶ ሊጠብቅና በወቅቱ ሊያስተካክል የሚችል ቢያንስ አንድ መንፈሳዊ አባት ማጣት ያስከተለው ችግር ውስብስብነትም ምንቸገረኝ የሚያሰኝ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡
ከዚህ የተነሳ የእነዚያ ‹‹የሁለቱ ኪዳናት›› መጽሐፍ ጸሐፊ፣ አርታኢና አሳታሚ ማኅበር ቅንጅታዊ ተግባር ይህንን ለዘመናት እውነቱን እንዳያይና በዕውቀት እንዳይመራ የተደረገ ሕዝብ በባሰ የጨለማ ሕይወት እንዲዳክር ለማድረግ በቃልና በጽሑፍ የሚከናወን ጥረት አካል በመሆኑ ይህንኑ ለማሕበረሰባችን ገልጦ በማሳየት የደረሰውንና ሊደርስ ያለውን ብርቱ ችግር መከላከል አስፈላጊ ሆኗል፡፡ በእኔ እምነት ትውፊትንና ልማድን መከለያ አድርጎ የእግዚአብሔርን ቃል መቃወም ከተወቃሽነትና ከተጠያቂነት አያድንም፡፡ በክርስትና ስም ተሰባስቦና ታሪክና ቅርሳ ቅርስ እንጠብቃለን ወደሚል ዝቅታ ዝቅ ብሎ ለባሕልና ለቅርሳ ቅርስ በመወገን የእግዚአብሔር ሃሳብና ፈቃድ እንዳይፈጸም መከላከልም ተቀባይነት የለውም፡፡ ቅርሳ ቅርስ መጠበቁና ማስጠበቁ የሚያስከፋ ባይሆንም ከታሪክና ከቅርሳ ቅርስ በፊት ለእነርሱ መገኘት ምክንያትና ባለቤት የሆነው ክርስቶስ የሞተለት ሕዝብ መንፈሳዊ ሕይወት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ እስከ ዛሬም ድረስ ትኩረት የተነፈገው ምእመን ከሁሉ አስቀድሞ የእምነቱን ቀዳሚ ፍሬ (ድኅነተ ነፍሱን) እንዲያረጋግጥ የሚያስችለውን እውነተኛ የክርስትና ትምህርት ሊገነዘበው በሚችለው መንገድ ግልጥልጥ አድርጎ ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ አቡነ መልኬ ጼዴቅ እንዳሉት ሕዝባችን በእምነቱ ፍጹም መታመን ኖሮት ‹‹… ኢየሱስ ክርስቶስ ብለን ጌታችንን ስንጠራው የዳንን ወገኖች መድኅንም ያለን ሕዝቦች መሆናችንን፤ ክርስቶስ ከግብርናተ ዲያቢሎስ ነጻ ያወጣን መሆናችንን ማመናችንና መናገራችን ነው›› ወደሚልበት እውቀትና ድፍረት መድረስ አለበት (መልከ ጼዴቅ 1984፡37)፡፡
የክርስቲያን መመዘኛው የተጠለለበት ተቋም ህንጻ ውበት አሊያም ተቋሙ የኖረበት ዘመን ርዝማኔና የምእመናን ብዛት ሳይሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በማመኑ ያገኘውን ዘላለማዊ ድኅነትና የሕይወት ዋስትና በእርግጠኛነት ተገንዝቦ እንደ ቀደሙት አባቶቹ፡- ከሰማይ የመጣ የእግዚአብሔርን ቃል በሥጋው ብቻውን ከሙታን ተቀድሞ እንደ ተነሳ እናውቃለን፤ በተነሳ ጊዜ አባቱ በሀብት ስቦ በረድኤት አቅርቦ ለእርሱ የሰጣቸው ምእመናን በትንሳኤ ይመስሉት ዘንድ እንግዲህ ወዲህ በቀድሞው ሰው አዳም ትእዛዝ ማፍረስ ምክንያት ፈርሰው በስብሰው አይቀሩም፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እሺ በጄ ብሎ እስከ ሞት በመድረሱ እነርሱ ፈጽመው ይድናሉ እንጂ (ዘቄርሎስ 1982፡309 ቁጥር 52) እና ያን ጊዜ በዚያ ወራት ነፍሳት ከሥጋቸው በተለዩ ጊዜ ከምድር በታች ወደ ሲዖል ይወርዱ ነበር፤ የሞት ቤቶችም እስኪመሉ ድረስ ወደ ገሃነም ይሄዱ ነበር፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአባቱ ሥልጣን ነፍሱን ከሥጋው በለየ ጊዜ ግን ወደ መንግስተ ሰማያት ለመግባት አዲስ መንገድ አዘጋጀልን፤ እንግዲህ ወዲህ ወደ ገሃነም አንሄድም፤ ፈጣሪያችንን እንከተለዋለን እንጂ … (ዘቄርሎስ 1982፡80 ቁጥር 17)፡፡ እያለ በሚያውጀው የእምነት ቃሉ፥ በሚመራበት የክርስቶስ መንግሥት ትምህርትና ሥርዓት በመኖሩ (በፍሬው) (ዮሐ 15፥16) እንዲሁም የመንግሥቱን ዜጎች በማብዛት ሥራው ሊሆን የተገባ ነው (ማቴ 28፥20፤ ማር 16፥15)፡፡ ለዚህ መጽሐፍ መጻፍም ድምር ምክንያቶቹ እነዚሁ እንደ ዘመን አመጣሽ ትምህርት እየተቆጠሩ ያሉትና ቸል የተባሉ የእምነት ቃሎችና ፍሬዎች አማኝ በሚባለው ሕዝብ ውስጥ ስፍራ ማጣታቸው የፈጠረው ስጋት ነው፡፡ ‹‹ስለ ሀልዎተ እግዚአብሔርና ስለ ትምህርተ ድነት በኛ ቤተ ክርስቲያን ተረስቶ ኖሯል፤ ዋናውና የሕይወት ትምህርት ወደ አንድ ጎን ተጥሎ ነው የኖረው አሁንም ቢሆን ያሰበበት የለም፤ በቤተክርስቲያን የአመራር አካላትና በምእመናን መካከል እውነተኛው የእግዚአብሔር ፍቅር ፈጽሞ ተረስቷል፤ ከህፃናት ጀምሮ በየዕድሜ ክልሉ ስለ ሀልዎተ እግዚአብሔርና ትምህርተ ድነት ትምህርት መስጠቱ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ፈጽሞ አይታወቅም፤ ባሁኑ ጊዜ ሰባክያን ተብዬዎች በየደብሩ ተቀጥረው ምንም ፍሬ የሌለው ጩኸት ያስተጋባሉ›› በሚለው የገብረ ዮሐንስ ገለጻ ተስማማንም አልተስማማን፥ ነቀፍነውም ደገፍነው በእኔ እምነት ደግሞም እውነትን በሚፈልጉና በሚከተሉ ዘንድ ያለንበትን ተጨባጭ ሁኔታ ገልጦ የሚያሳይና የዘነጋነውን የቀደመችውን ቤተ ክርስቲያን ሕይወትና ተልዕኮ እንድናስብ የሚያነቃ ደወል ነው፡፡ በቅንነትና ሽንገላ በሌለበት ኅሊና ከመዘንነው የተጠራንበትን ትክክለኛ ተግባር መፈጸም በሚያስችለን የትምህርት፣ የአስተዳደር፣ የሥርዓትና የአምልኮ ሂደት ላይ አለመሆናችንን የሚያስገነዝብና ልባዊ ተሐድሶ እንድናደርግ የሚያሳስብ ሕያው መልእክት ነው፡፡ ‹‹ማን ያርዳ …›› እንዲሉ ከነበሩትና አሁንም ካሉት በላይ አስረጅ አይገኝምና መስማት ለሚችልና እውነትን ለሚፈልግ ሁሉ የ‹‹ተሐድሶ››ን ማለት የእምነት ለውጥ ሳይሆን እውነቱን ፈልጎ የማግኘትን፣ በፈጸሙት በደል ተጸጽቶ ንስሃ የመግባትንና በከበረው እውነትና መሠረት ላይ ጸንቶ የመኖርን አስፈላጊነት የሚያሳይ ፋና ነው፡፡
ይህንን የተንደረደርኩበትን የገብረ ዮሐንስን አባባል የትምህርት ተሐድሶ አያስፈልግም በሚለው ግትር አቋሙ የሚታወቀው ማኅበረ ቅዱሳን ሳይቀር ይጋራዋል፡፡ ይህንንም በራሱ መንገድ እንዲህ በማለት ይገልጸዋል፡፡ … በሥነ ምግባር የተዋበ ዜጋን የማፍራት አቅሙ እያላት አልሰራችበትም (እንዲያውም ምግባረ ብልሹነት፣ ሙስና ወዘተ አሁን አሁን በቤተ ክርስቲያን ተንሰራፍቷል) የሚሉ ትችቶችና ዘለፋዎች ከየማዕዘኑ ሲሰነዘሩ ተደምጠዋል፡፡ ትችቱ የተጋነነ ቢሆንም እውነትነት የጎደለው ግን አይደለም፡፡ … ከዚህም በተጨማሪ ቤተ ክርስቲያን ወጣቱን በትምህርትና በሥነ ምግባር ኮትኩታ ለማሳደግና ለመያዝ አለመቻሏ ሳይነሳ የሚታለፍ አይደለም፡፡ … እንደዚሁም በ1982 እና በ1983 ዓ.ም በመናፍቃን (በተሐድሶ) እንቅስቃሴ ምክንያት በቤተ ክርስቲያን በቅንዓት የተሰበሰበውን ወጣት ተገቢውን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት በመስጠት በሃይማኖትና በምግባር እንዲጎለምስ፣ አገልግሎቱም እንዲፋጠን አልሆነም፡፡ … ለእረኛነት ተመርጠው በጎቹን በለመለመ መስክ እንዲያሰማሩና ከተኩላ እንዲጠብቁ የተላኩ ካህናት ከተኙበት እንዲነሱ በየዕለቱ ከሚተረከው ዓለም አቀፋዊነት ሌላ የተሻለ ቀስቃሽ ከቶ ሊመጣ አይችልም፡፡ (ሐመር 1999፡53-54) የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሀብተ ብዙ በመሆኗ ብዙ ሥራዎች ይጠብቋታል፡፡ … በዚህ መሠረት ቢያንስ ሁለት መሠረታዊ ሥራዎች ይጠብቁናል፡፡ አንደኛ እውነተኛውን ትምህርት መስጠት … የዋሕ ልጆቿም በእምነት ቢቀበሉትም ዕውቀቱ አላቸው ማለት አይቻልም፡፡ በዕውቀት ያልተደገፈ እምነት ደግሞ እየቆየ መላላቱ አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህ ለአማኞቿ የሚሆንና ችግሮቿን የሚፈታ ለሚጠይቋቸውም መልስ በመስጠት የሚያስጨንቁበት አንዳንዶችንም ከእሳት የሚያድኑበት ትምህርት ከቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ይጠበቃል፡፡ ሁለተኛ መለየትና ማዘጋጀት፡- ምንም እንኳ ቀደም ብለን እንዳየነው የአዋልድን ቁጥር መወሰን ባይቻልም የመለየትና ለአገልግሎት የመለየት ሥራው ግን ለአራተኛው ሺህ ዓመት ሊገፋ አይገባውም፡፡ … እኛ ደግሞ በመግለጽ ጊዜ ስርዋጽ የገባባቸው ካሉ በማጥራት የተጓደሉትን በማሟላት ዲቃሎቹንና እውነተኞቹን አዋልድ በመለየት ለአገልግሎት ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ … ጌታ በሚገለጥ (ዳግመኛ በሚመጣ) ጊዜ በቀኝ የሚቆም መጽሐፍና ቅርስ የለም፡፡ የሚቆሙት ሰዎች ናቸው፡፡ …ካለበለዚያ ቆፍሮ በመቅበር መጠየቃችን አይቀርም፤ እንደ ገብረ ሀካይ (ሐመር 1999፡71)፡፡
ይህንን መሠረተ ሃሳብ መነሻው አድርጎ ትክክለኛውንና ቸል የተባለውን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ገልጦ ለማሳየትና ከአጥፊዎች ለመከላከል የተዘጋጀው ይህ መጽሐፍ በሰባት ምዕራፎች የተከፈለ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ኪዳናት›› የሚል ርዕስ የተሰጠው የመጀመሪያው ምዕራፍ ስለ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ኪዳናት ምጥን፣ ነገር ግን አሁን ለደረስንበት አዲስ ኪዳናዊ ሕይወት መሠረት የሆኑ ሃሳቦችን ያስዳስሳል፡፡ ኪዳናቱ ከአንዱ ወደ ሌላኛው እየተሸጋገሩ ፍጹም ወደ ሆነው የመጨረሻው ኪዳን (አዲስ ኪዳን) እንዴት እንደ ደረሱ ያሳያል፡፡ በተለይም ሁለቱ ኪዳናት (ብሉይና ዐዲስ) ከተሰጡበት ዓላማና ከተመረቁበት ደም አንጻር በክብርም ሆነ በአገልግሎት እንደሚበላለጡ (አንዱ ከሌላው እንደሚለይ) ማሳየት የምዕራፉ ዋነኛ ዓላማ ነው፡፡ ምዕራፍ ሁለት ‹‹የሁለቱ ኪዳናት ቅኝት›› በሚል ርዕስ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡
ምዕራፉ ከዚህ በፊት ‹‹ሁለቱ ኪዳናት›› በሚል ርዕስ በማኅበረ ቅዱሳን ታትሞ ለሕዝብ በተሰራጨ መጽሐፍ መግቢያ ውስጥ የሚገኙ የእውነተኛው ኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ ትምህርት ይዘት የሌላቸው ሁለት ሃሳቦችን ነቅሶ በማውጣት በመጽሐፍ ቅዱስና በቀደሙት አባቶች አስተምህሮ የሚመዘንበት ክፍል ነው፡፡ በተለይም የመጽሐፉ አርታኢና የመግቢያው ጸሐፊ የ‹‹ሁለቱ ኪዳናት››ን (የብሉይና የአዲስን) ውሕደት አስመልክቶ ያስተላለፈውን መልእክት መነሻ በማድረግ ኪዳናቱ ሊዋሐዱ የማይችሉበትን መሠረታዊ ነጥቦች በስፋት ይዳስሳል፡፡ የማይዋሐዱትን ለማዋሐድ የሚደረገውንም መደፋፈር በብርቱ ይሞግታል፡፡ ድርጊቱም ክርስቲያናዊ ተግባር እንዳልሆነ ያስገነዝባል፡፡ ምዕራፍ ሦስት ‹‹ታሪካዊ ስህተትን ላለመድገም›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ይህ ክፍል መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት ያደረጉ ውሳኔዎች የተላለፉባቸውን የመጀመሪያዎቹን ሦስት ዓለም አቀፍ ጉባኤያት መንስዔና የተደረሱባቸውን ውሳኔዎች ያስታውሳል፡፡ በዚህ ክፍል የሚነሳው ሃሳብ መጽሐፍ ቅዱሳዊውን እውነት በ‹‹ሁለቱ ኪዳናት›› መጽሐፍና መሰል የኅትመት ውጤቶች እየተሰራጩ ከሚገኙት ኢ-ክርስቲያናዊ ትምህርቶች ጋር በማነጻጸር ያሳያል፡፡ ይህም አንባቢው ትክክለኛውን መሠረተ እምነት ተገንዝቦ ትክክለኛ ውሳኔ እንዲሰጥ የሚያስችል ዕድል ይፈጥራል፡፡ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ይህ ክፍል ይህንን መጽሐፍ ጨምሮ ማናቸውንም በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ስም ተጠልለው የሚሠራጩ ትምህርቶችን በተለይም በቀጣዩ ምዕራፍ የሚዳሰሱትን ከ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ጎልተው የታዩትን ሦስት ቡድኖች አስተምህሮ ለመመዘንና የየትኛው ወገን ትምህርት ከሦስቱ ዓለም አቀፍ ጉባኤያት ውሳኔዎች ጋር እንደሚስማማና እንደማይስማማ ለመለየት ያስችል ዘንድ እንደ ቱንቢ ሆኖ ተቀምጧል፡፡ እነዚህ ሶስት ዋነኛ ጉባኤያት ሲነሱ ሊታለፉ የማይገባቸው ሁለተኛው የኤፌሶን ጉባኤ (ምዕራባውያን የወንበዴዎች ጉባዔ የሚሉት) እና በምዕራባውያኑ አራተኛው ዓለም አቀፍ ጉባኤ በመባል የሚታወቀው የኬልቄዶን ጉባኤ (በኦርየንታሎቹ ጉባኤ ከለባት የሚባለው) የመጀመሪያዎቹ ሶስቱ ጉባኤያት ያስተላለፏቸውን የእምነት ድንጋጌዎች በግልጽ ለመረዳት ከሚያደርጉልን እገዛ አንጻር ጥቂት ስፍራ ተሰጥቷቸዋል፡፡ በዚህም ከእነዚሁ ጉባኤያት ጋር የተያያዙ ዋና ዋና ሃሳቦች ይዳሰሳሉ፡፡ ምዕራፍ አራት ‹‹የግጭቶቻችን ማጠንጠኛዎች - ቅባት፣ ካራ፣ ጸጋ›› በሚል ርዕስ የቀረበ ነው፡፡ ይህ ክፍል ከ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አንስቶ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የርስ በርስ ግጭቶችና ደም መፋሰስ ያስከተሉትን ሦስት በአመለካከት የተለያዩ ቡድኖች አስተምህሮ አስመልክቶ ምጥን፥ ነገር ግን ጠቃሚ መረጃዎችን የያዘ ነው፡፡ ክፍሉ ዛሬ ዛሬ የ‹‹ተዋሕዶ›› አማኝ ነኝ የሚሉን ቡድኖች አስተምህሮ (ማኅበረ ቅዱሳንን ጨምሮ) ከእነዚህ ከሦስት ቡድኖች (ካራ፣ ቅባት፣ ጸጋ) ቢያንስ ከአንዱ ተቀድቶ አለበለዚያም የአንዱ ቡድን ትምህርት ከሌላው ቡድን ትምህርት ጋር ተዳቅሎ ሲወርድ ሲወራረድ የመጣ በመሆኑ አስተምህሯቸውን አዳምጦና መዝኖ ከየትኛው ወገን እንደሆኑ መገምገም እንደሚያስችል ይታመናል፡፡ በተለይም በቀዳሚው ምዕራፍ የተዳሰሱትን ዓለም አቀፍ ጉባኤያት ውሳኔዎችና ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶች ከእነዚህ ቡድኖች አስተምህሮ ጋር በማነጻጸር የትክክለኛውን ተዋሕዶ ባህለ ትምህርት ለመገንዘብ የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍ ያለ ነው፡፡ በምዕራፍ አምስት ‹‹ልዩነቶቻችን በመጽሐፍ ቅዱስ ሲዳኙ›› የሚል ሃሳብ ይነሳል፡፡ የዚህ ክፍል ዓብይ ዓላማ በዘመናት ሁሉ ለተነሱት ሃይማኖታዊ ችግሮች (ልዩነቶች) መንስኤው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለን አመለካከት መለያየት መሆኑን በማስቃኘት የ‹‹ሁለቱ ኪዳናት›› መጽሐፍ አዘጋጅ መሪጌታ ኃየሎምና አሳታሚው ማኅበር ማኅበረ ቅዱሳን የሚያራምዱት የእምነት አቋም በመጽሐፍ ቅዱስ ከተገለጸው የእግዚአብሔር ሃሳብ የሚቃረንና ጤነኛ የተዋሕዶ ትምህርት አለመሆኑን ማስረጃዎች ጠቅሶ ያሳያል፡፡
በአንጻሩም ቤተ ክርስቲያናችን የምትቀበላቸው ቀደምት ኦርቶዶክሳውያን አባቶች ያስተላለፉትን ትምህርት በእማኝነት በማቅረብ ጥንታዊውንና እውነተኛውን የተዋሕዶ ትምህርት ያስገነዝባል፡፡ ምዕራፍ ስድስት ‹‹ሕግና ትእዛዝ›› በሚል ሃሳብ ላይ የሚያጠነጥን ነው፡፡ ሕግጋትና ትእዛዛት ለጸጋ ስፍራቸውን እንዳልለቀቁና እነርሱን መጠበቅ የጽድቅ ምንጭ እንደሆነ ሊሰብኩን ለሚሞክሩት ‹‹የሙሴ ደቀ መዛሙርት›› ሕግን የምንጠብቀው ገና ለመጽደቅ እያሰብን ሳይሆን በክርስቶስ ኢየሱስ የመስቀል ላይ ሥራ ስለ ጸደቅን መሆኑን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ እያቀረበ ያስረዳል፡፡ ምዕራፍ ሰባት ‹‹መቅደስ - የእግዚአብሔር መገለጫ›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ይህም መቅደስ የተባለውና ክርስቶስ የገባበት ሰማያዊ ስፍራ ‹‹መስቀል›. ነው ለሚለው የስህተት ትምህርታቸው መልስ የተሰጠበት ክፍል ነው፡፡ ከብሉይ ኪዳን የቤተ መቅደስ ጅማሬ አንስቶ ክርስቶስ የገባባት ተብላ እስከ ተገለጸችው ቤተ መቅደስ ድረስ ያለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሃሳብ በአጭሩ በማቅረብ ‹‹ቤተ መቅደስ የተባለው ጌታ የተሰቀለበት መስቀል ነው›› የሚለውን ኢ-ክርስቲያናዊ ፍልስፍና ይፋለማል፡፡ በአጠቃላይ መጽሐፉ ጤናማውን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ባህለ ትምህርት ከጥፋት ለመከላከልና እውነቱን ገልጦ ለማሳየት መጽሐፍ ቅዱስንና የቀደሙ አባቶችን ትምህርት መሠረት አድርጎ የተጻፈ በመሆኑ ስለ እምነቱ ተገቢውን ግንዛቤ ለማግኘትና እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ለመኖር የሚፈልግ ሁሉ ጠቃሚ ትምህርት እንደሚያገኝበት እምነቴ ነው፡፡