Monday, July 24, 2017

ግልጥ የወጣ አውጣኪነት፤ ለቀሲስ ደጀኔ የተሰጠ መልስ ( ክፍል አንድ)



ከቀሲስ መላኩ ተረፈ


ለወንድሜ ቀሲስ ደጀኔ፥በዕብ ፭፥፯ ላይ ያለውን ኃይለ ቃል መሠረት አድርገህ ( የብፁዕ አባታችንና የእኔን ፎቶ አስደግፈህ) የጻፍከውን ተመለከትኩት፤ በአንድ በኵል፥ ከተራ አሉባልታና ክስ ወጥተን፥በክርክርም ቢሆን፥  ስለ ክርስቶስ እንድንነጋገር ያደረገንን አምላክ ሳመሰግን፥ በሌላ በኩል አንተና አንተን ተከትለው በቲፎዞ የሚነጉዱት ስለገባችሁበት ከባድ አደጋ ሳስብ አዝናለሁ። ይህ የልጅ ጨዋታ አይደለም። አሁን እያደረጋችሁ ያላችሁት፥ ቤተ ክርስቲያንን ከአኃት አብያተ ክርስቲያናት ጋር የሚያለያይ፥ አባቶቻችን በስንት ተጋድሎ ያቆዩትን የተዋህዶ ምሥጢር የሚያፋልስ ነው። በመሆኑም የሚቀጥለው ጽሑፌ በአንድ በኩል በጥንቃቄ የአባቶችን ትርጓሜና የቤተ ክርስቲያናችንን ትምህርት እንድታጠናው ለማሳሰብ ሲሆን፥ በሌላ በኩል የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለማሳሰብ ነው። ምንም እንኳ እኔን መናፍቅ ብትለኝም፥ አንዳንዱን የአተረጓጎምህን መንገድ ስመለከት መናፍቅ ለማለት ይከብደኛል። ከምርምርና ከዕውቀት ሳይሆን፥ከአላዋቂነት የመጣ ስህተት ነውና የማየው።  በመሆኑም በመጀመሪያ ጽሑፍህን በትምህርተ ጥቅስ ጎላ ብሎ እንዲቀመጥ በማድረግ፥ ለእያንዳንዱ መልስ ለመስጠት  እሞክራለሁ። በአንቀጽ የተከፋፈለ ባይሆንም ለመልስ እንዲረዳኝ ከፋፍየዋለሁ፤ አላስፈላጊ የሆነና አለቦታው የገባውን ንባብ ግን ከጊዜና ከቦታ አንጻር አልፌዋለሁ፤
ቀሲስ ደጀኔ ስትጽፍ ፦  “ እርሱም በሥጋ ወራት . . . ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፤”ዕብ፡፭፥፯። =ይኸንን ኃይለ ቃል የተናገረው፡-ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ነው።ይህ ሐዋርያ መልእክ ቶቹን ሁሉ የጻፈው በጸጋ እንደ ተሰጠው ጥበብ መጠን ነው።ይኸንንም፡-የሐዋርያት አለቃ ቅዱስ ጴጥሮስ፡-“እን ዲህም የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ ደግሞ እንደ ተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ፥በመልእክ ቱም ሁሉ ደግሞ እንደ ነገረ ስለዚህ ነገር ተናገረ።በእነዚያ ዘንድ ለማስተዋል የሚያስቸግር ነገር አለ፥ያል ተማሩትና የማይጸኑትም ሰዎች ሌሎችን መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ እነዚህን ደግሞ ለገዛ ጥፋታ ቸው ያጣምማሉ።”በማለት ገልጦታል።፪ኛ፡ጴጥ፡፲፭። =ቅዱስ ጴጥሮስ እንደመሰከረው፥መናፍቃኑ፡-አጥፍቶ ጠፊ የሆኑት፥በአብዛኛው፡-የሐዋርያውን መልእክታት በመጠቃቀስ ነው።ይኸውም የንባቡን ትርጓሜና ምሥጢር ካለማስተዋልና መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ሌሎች ልበ ወለድ መጻሕፍት ከመመልከት ነው።» ብለሃል።
ግሩም ነው! ስድቡን ቀነስ ብታደርገውም፥ ዛሬም ያችው የተለመደችው መናፍቃን የምትለውን ቃል ፎቶአችንን አስቀምጠህ ተጠቅመሃል።  ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ የተናገረው ቃል በእውነትም ቅዱስ ጳውሎስ ያስተማረውን የምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንን ነገር ባለማስተዋል የሚያጣምሙትን የገሠጸበት ቢሆንም፥ ዛሬም መጻሕፍትን ለሚያጣምሙት የሚጠቀስ ቃል መሆኑ እሙን ነው። በአንድ በኩል የመጽሐፍ ቅዱስ ገጸ ንባብ ጥሬ ዘሩን ሳይቀር ለመለወጥ የደፈርህ፥ እንዲህ ተብሎ ሊጻፍ አይገባም ያልክ አንተ ነህ፤ በሌላ በኩል የአባቶችን ትርጓሜ እንኳ ሳይቀር፥ ያለምንም ሐፍረት ያጣመምክ አንተ ስለሆንክ « ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ» የተባለው የሚቀጸለው ለአንተ ነው። ትርጓሜ ጳውሎሱን ሳይቀር እንዴት እንዳጣመምከው በግልጥ በማስረጃ አመጣዋለሁ። ወደ እኔ ጽሑፍ ከሄድክ፥ በማስረጃነት ያቀርብኩልህ ትርጓሜ ወንጌልን፥ ሃይማኖተ አበውን፥ የጥንትና የዘመናችን አባቶችን እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስን ነው። ጳውሎሱን አንተም እኔም የምንጠቅሰው ኃይለ ቃሉ ያለበት ስለሆነ ነው። ዛሬም ከእነዚሁ ንጹሐን ምንጮች ነው የምጠቅስልህ፤  መናፍቃኑ ላልከው ግን እኔም እንደ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ እልሃለሁ፤  «ነገር ግን ይህን እመሰክርልሃለሁ፤ በሕጉ ያለውን በነቢያትም የተጻፉትን ሁሉ አምኜ የአባቶቼን አምላክ እነርሱ ኑፋቄብለው እንደሚጠሩት መንገድ አመልካለሁ፤» ሐዋ ፳፬፥፲፬
ቀሲስ ደጀኔ ስትጽፍ፦ « ለመሆኑ፡-ሐዋርያው መልእክት ትርጓሜ ምንድነው? -“ነገርን ከሥሩ፥ውኃን ከጥሩ፤”እንዲል፡-መልእክቱን ለመረዳት በመጀመሪያ የነገሩን ሥረ መሠረት እንመለከታለን። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡-ዕብራውያን ምዕራፍ አምስትን የጀመረው፥ በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበሩት ሊቃነ ካህናት፡-ለአዲስ ኪዳኑ ሊቀ ካህናት፡-ለኢየሱስ ክርስቶስ የነበራቸ ውን ምሳሌነት በማብራራት ነው። በምሳሌውና በአማናዊው መካከል ያለው ልዩነትም የፈጣሪና የፍጡር ነው፥እነርሱ ፍጡራን ፥እርሱ ግን ፈጣሪ ነው፤እነርሱን የሾማቸው እርሱ ነው፥እርሱ ግን ሿሚ የለበትም፤ ሹመት የባሕርይ ገንዘቡ ነው።» ብለሃል።
ይህ ሙሉ የእብራውያንን የሊቀ ካህንነት ትምህርት የገለጠ አይደለም። ለምሳሌ ስለ አዲስ ኪዳኑ ሊቀ ካህናት ስትናገር፥ በምሳሌናው በአማናዊው መካከል ያለው ልዩነት የፈጣሪና የፍጡር ነው ብለሃል፤ መልካም ነው።  ይህ እንዳለ ሆኖ ግን፥ ነገርን ከሥሩ እንዳልከው የዕብራውያን መልእክት በዋናነት የሚያሳየን አንተ ልትናገረው ያልደፈርከውን ነገር ነው። ይኸውም፥ የአዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት፥ በእውነት ሰው የሆነው የእግዚአብሔር ልጅ በእኛ ፈንታ የቆመ፥ ስለ እኛ መከራ የተቀበለ፥ የጮኸ፥ የደከመ፥ የለመነ፥ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበና አሁን በእውነተኛይቱ ድንኳን ያለ አስታራቂያችን ሊቀ ካህናት መሆኑን ነው። ይህን በዕብራውያን መልእክት  ውስጥ በሙሉ እናየዋለን።

አንደኛ፥ ይህ የአዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት፥ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የቆመ ሊቀ ካህናት ነው። « እንግዲህ በሰማያት ያለፈ ትልቅ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ስላለን፥ ጸንተን ሃይማኖታችንን እንጠብቅ።» ( ዕብ ፬፥፲፬ ) አባቶቻችን ይህን ሲተረጉሙ « ብንመለስ ማን ያስታርቀናል እንዳይሉት፥ ብነ ሊቀ ካህናት አለ፤ የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጁ ደግ አስታራቂ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን።»  

ሁለተኛ፥ የአዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እኛን የሆነ ነው። «ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ፥ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም።» ዕብ ፬፥፲፬።  ሊቀ ካህናትም ያሰኘው ይኸው ፍጹም ሰው መሆኑ ነው። « ከግብራችን ሲያወጣው « ዘእንበለ ኃጢአት ባሕቲታ ከኃጢአት በቀር » አለ። ከባሕሪያችን ሲያገባው « ምኩር በኩሉ በአምሳሊነ እንደ እኛ የተፈተነ» አለ» ይለናል፥ ትርጓሜ ጳውሎስ።    ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም በነገር ሁሉ እኛን መምሰሉ እንዴት እንደሆነ ሲናገር፥ « እንደ እኛ ፍጹም ሰው ሆኖ መወለዱ፥ ከኃጢአት ብቻ በቀር፥ እንደ እኛ ለሥጋ የሚስማማውን፥ ሁሉ መሥራቱ ነው እንጂ፤ይኸውም በፈቃዱ ያደረገው መፀነስ፥ መወለድ፥ መብላት፥ መጠጣት፥ መተኛት፥ መድከም፥ መታመም መሞት ነው።» ይላል። ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ም. ፷፫ ክፍል ፪


ሦስተኛ፥ ይህ የአዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት፥ ከኃጢአት በቀር እንደ እኛ የሆነ፥ ስለ እኛ መከራ የተቀበለ ስለሆነ፥  የተቤዣቸውንና ያዳናቸውን « ወንድሞቼ ሊል ያላፈረ፥ « በኵረ አኃው» ነው።  «ብዙ ልጆችን ወደ ክብር ሲያመጣ የመዳናቸውን ራስ በመከራ ይፈጽም ዘንድ፥ ከእርሱ የተነሣ ሁሉ በእርሱም ሁሉ ለሆነ፥ ለእርሱ ተገብቶታልና። የሚቀድሰውና የሚቀደሱት ሁሉ ከአንድ ናቸውና፤ስለዚህም ምክንያት፦ ስምህን ለወንድሞቼ እነግራቸዋለሁ በማኅበርም መካከል በዜማ አመሰግንሃለሁ፤ ደግሞም፦ እኔ በእርሱ እታመናለሁ፤ ደግሞም፦ እነሆኝ እኔን እግዚአብሔር የሰጠኝንም ልጆች ሲል ወንድሞች ብሎ ሊጠራቸው አያፍርም።» ዕብ ፪፥፲-፲፫  ። አስተውል፥ በሥጋዌው ከእኛ ጋር በመዛመዱ፥ « የሚቀድሰውና የሚቀደሱት ሁሉ ከአንድ ናቸው» ተባለ፤ትርጓሜ ጳውሎስ ይህን ሲያብራራው፥ « እነሱን ያከበረ እሱና የከበሩ እነሱ ካንድ ከእግዚአብሔር ካንድ ከአብርሃም ተገኝተዋልና» ይለዋል።

አራተኛ፥ይህ ሊቀ ካህናት በእርሱ መታዘዝ ለእኛም መታዘዝን ያስተማረንና እንደ ሊቀ ካህንነቱ ወደ አባቱ በብርቱ ጩኸትና እንባ ጸሎትንና ምልጃ ያቀረበ ነው።   « እርሱም በስጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፥ እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ተሰማለት፤ምንም ልጅ ቢሆን፥ ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ፤ከተፈጸመም በኋላ በእግዚአብሔር እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ሊቀ ካህናት ተብሎ ስለ ተጠራ፥ ለሚታዘዙለት ሁሉ የዘላለም መዳን ምክንያት ሆነላቸው።» ( ዕብ ፭፥፰-፲)፤ ይህን ገጸ ንባቡን ሆነ የአበውን ትርጓሜ እንዴት እንዳጣመምከው በቦታው እናየዋለን።

አምስተኛ፥ ይህ ሊቀ ካህናት በእርሱ በኩል ወደ አብ የሚቀርቡትን ፈጽሞ የሚያድን ሕያውና ዘላለማዊ ሊቀ ካህን ነው።   «እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።ቅዱስና ያለ ተንኮል ነውርም የሌለበት ከኃጢአተኞችም የተለየ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለ፥ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ይገባልና፤» (ዕብ ፯፥፳፬-፳፮)፤

ስድስተኛ፥ ዛሬ ይህ ሊቀ ካህናችን በሰማያዊት ድንኳን በእጅ ባልተሠራችው፥ስለ እኛ የሚታይልን ነው። «በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን፤ እርሱም የመቅደስና የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ ነው፥ እርስዋም በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች ናት።»( ዕብ ፰፥፩-፪) የእኛ አባቶች « ሊቀ ካህናት ዘይቀውም ሎሙ ለቅዱሳን፥ በደብተራ ስምዕ እንተ እግዚአብሔር ተከላ፤» ብለው ያመሠጠሩት ይህን ንባብ ነው።
ሰባተኛ፥ ሊቀ ካህናችን ወደዚህች ሰማያዊት ድንኳን የገባው፥ የገዛ ደሙን ይዞ ነው፤ ። «ነገር ግን ክርስቶስ ይመጣ ዘንድ ላለው መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ፥ በምትበልጠውና በምትሻለው በእጆችም ባልተሠራች ማለት ለዚህ ፍጥረት ባልሆነች ድንኳን፥ የዘላለምን ቤዛነት አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ እንጂ በፍየሎችና በጥጆች ደም አይደለም. . .  ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሰራች፥ የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደ ምትሆን ቅድስት አልገባምና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ።» ዕብ ፱፥፲፩- ፲፪፡፳፬
ስምንተኛ፥ ሊቀ ካህናችን እርሱ ወደ ገባበት ድንኳን ለመግባት የምንችልበትን ተስፋ ሰጥቶናል፤ ይህችም ተስፋ የነፍሳችን መልሕቅ « እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘለዓለም ሊቀ ካህናት ሆኖ ሐዋርያችን ኢየሱስ ከእኛ በፊት ወደ ገባባት መጋረጃም ውስጥ የምታስገባ ናት።» (ዕብ ፮፥፳፤)

ቀሲስ ደጀኔ ስትጽፍ፦ በንባብ፡-“ተሾመ፥ተቀባ፤”የሚል ቢገኝም ምሥጢረ ተዋህዶን ለማመ ልከት(በተዋህዶ አምላክ ሰው፥ሰውም አምላክ መሆኑን ለመግለጥ፥ወልደ አብ ወልደ ማርያም በተዋህዶ መክበሩን ለማስረዳት) ስለሆነ በትርጓሜ ይቃናል።ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲ ያን፡-ወልደ አብ፥ወልደ ማርያም ኢየሱስ ክርስቶስ፡-በተዋህዶ ከበረ የሚሉት ለዚህ ነው። ምክንያቱም ቅዱስ ቄርሎስ እንደተናገረው፡-በተዋህዶ የመለኮት ገንዘብ ለሥጋ፥የሥጋም ገን ዘብ ለመለኮት ሆኖአል። » ብለሃል።
ቄርሎስን በሚገባ ሳይገነዘብ ገደል የገባውን አውጣኪን ሆነሃል የምልህ እዚህ ላይ ነው። የጻፍከውን ጽሑፍ እንደገና መለስ ብለህ ቃኘው፥ እናም  « በተዋህዶ የሥጋ ገንዘብ» ምንድነው? ሁሉንም ክደኸዋል። ቄርሎስ በድርሳኑ ደጋግሞ እንደገለጠው፥ አንድ ባሕርይ ሲል፥ የቃልና የሥጋን መገናዘብ ሲናገር፥ የክርስቶስን ፍጹም ሰውነት ክዶ አይደለም። የመለኮት ገንዘብ፥ የእግዚአብሔር ልጅ መሆን ፥ አምላክነት፥ ሕይወት መስጠቱ ፥ ማዳኑና  እነዚህን የመሣሠሉት ሁሉ የሥጋም ገንዘብ ሆነዋል። በተዋህዶ። የሥጋ ገንዘብ የሆኑት ደግሞ፥ የዕለት ጽንስ መሆን፥ በየጥቂቱ ማደግ፥ መፍራት፥ መራብ፥ መጠማት፥መጸለይ መማለድ፥ ወደ አብ መጸለይ፥ መሞት እነዚህና እነዚህን የመሳሰሉት ወይም እንደ አባቶች አነጋገር፥ በጥንት በበአት፥ በልደት፥ በሕማምና በሞት እኛን የሆነባቸው የሥጋ ሥራዎች ሁሉ የመለኮት ገንዘብ ሆነዋል። በተዋህዶ። አንተ ግን የአምላክነቱን ገንዘቦች ስታምን የሥጋን ገንዘቦች ግን ፈጽሞ ክደኸዋል። እኛ በሥጋው ይህን አደረገ ስንል ለመለኮት ሰጥተን ነው። በአምላክነቱ ይህን አደረገ ስንል ለሥጋ ሰጥተን ነው። ሳናፋልስ፥ ሳንከፍል፥ ሳንቀላቅልና ሳንለውጥ አንዱን በተዋህዶ የከበረውን አምላክ እንዲህ እንመሰክራለን።   ወልደ አብ ወልደ ማርያም በተዋህዶ ከበረ ማለት፥ ተለወጠ፥ተቀላቀለ አያሰኝምና። ትርጓሜህ በሙሉ ተዋህዶን የሚያፋልስ እንጂ ተዋህዶን የሚጠብቅ አይደለም። ላንተ መገናዘብ ማለት የትስብእትን ነገር እንዳለ መካድ ሆኖብሃል። ይህ አደገኛ ነው።   በትርጓሜ እያቃናህ ሳይሆን እያጣመምከው ነውና።
አሁን ከሊቃውንቱ ስለምጠቅስልህ በእርጋታ አስተውል፤ ጎርጎርዮስ ነባቤ መለኮት  በሃይማኖተ አበው ም. ፷፩ ክፍል ፫ እና ፬ ላይ እንዲህ ይላል። «  አስተርአየ በሥጋ እንዘ ኢያስተርኢ በሕላዌ መለኮት፤ በባሕርየ መለኮቱ የማይታይ ሲሆን፥ በሥጋ ታየ . . . በመለኮት ሞት ሳይኖርበት በሥጋ ሞትን ገንዘብ አደረገ፤ በመለኮት መወሰን ሳይኖርበት በሥጋ ተወሰነ፤የማይመረመር ሰማያዊ እርሱ ሥጋን ተዋህዶ በምድር ተገለጠ።» ካለ በኋላ አንተ ደጋግመህ የካድከውን እርሱ እንዴት እንደሚገልጠው ተመልከት እንዲህ ይላል። «የዕለት ጽንስ መሆን፥ በየጥቂቱ ማደግ፥ የሠላሳ ዐመት ጎልማሳ መሆን፥ የመለኮት ሥራ አይደለም። ይህም ምንም ስለ እርሱ ቢነገር፥ የመለኮት ገንዘብ አይደለም። ሰው ስለሆነ እንጂ »
 

ይህ የተዋህዶ ምሥጢር ወደ ጥልቅ አምልኮ የሚጋብዝ ነው። ከንቱ ከሆነ የቃላት ስንጠቃና ክርክር ወጥተን፥ ክርስቶስ ለእኛ ያደረገውን ነገር እንድናሰላስል የሚያደርግ ነው። ይህ የአእምሮ ጅምናስቲክ አይደለም። የአምልኮ ውበት ነው። እናም ጎርጎርዮስ በ፷፩ኛ ምዕራፉ በክፍል ፭ ላይ እንዲህ ይላል፤ « ቀዳማዊ ዘሀሎ እምቀዲሙ እንበለ ጥንት ኮነ ይእዜ ዘቦቱ ጥንት። ጥንት ሳይኖረው በቅድምና የነበረ ቀዳማዊ እርሱ ዛሬ ጥንት ያለው ሆነ። ዘኢተገብረ አስተርአየ ይእዜ በለቢሰ ሥጋ ዘተገብረ፤ ያልተፈጠረ እርሱ የተፈጠረ ሥጋን ተዋሕዶ ዛሬ ታየ። በከመ ጽሑፍ ዘይብል አእምሩ ዘንተ ሐዋርያ ሊቀ ካህናት እምነትነ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚእነ ምዕመን በኀበ ዘገብሮ። ሊቀ ካህናት ሐዋርያ ባደረገው በአብ ዘንድ የታመነ የምናምንበት አስታራቂያችን መምህራችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ይህን ዕውቁ ተብሎ እንደተጻፈ።  ዘኢያገምሮ መካን አግመረቶ ድንግል በከርሣ። ሰማይ ምድር የማይወስነውን ድንግል በማኅፀኗ ወሰነችው። ባዕል ዘይሁብ ብዕለ ለነዳያን። ብዕል ለሌላቸው ብዕልን የሚሰጥ እርሱ፤  ኮነ ነዳየ በእንተ ሥርዓተ ትስብእት። ሰው ስለ ሆነ ድሀ ተባለ። ከመ አብዓል አነ በንዴተ ዚአሁ። በርሱ ድሀ መባል እኔ እከብር ዘንድ። ነሣዕኩ አርአያሁ ወኢአቀብክዋ እርሱን መም ሰሉን በተፈጥሮ ገንዘብ አደረግሁ፤ ጠብቄም አላስቀረሁትም። ወውእቱሰ ነሥአ ሥጋየ ከመ ያድኅነኒ፥ ሊተ ዘገብረኒ በአርአያሁ ወበአምሳሊሁ። እርሱ ግን በአርአያውና በአምሳሉ የፈጠረኝ እኔን ያድነኝ ዘንድ ሥጋዬን ተዋሐደ። ወረሰዮ ሥጋየ ዘእንበለ ሞት። ሥጋዬንም ሞት የሌለበት አደረገው። . . . ቀዳሚሰ ወሀበነ አርአያሁ ክብርተ። ቀድሞ ክብርን የምታስከትል እርሱን መምሰልን ሰጠን። ወዳግመ ነሥአ ሥጋነ ኅሥርተ። ዳግመኛ ግን ኃሣርን የምታስከትል ሥጋችንን ተዋሐደ። ወዝንቱ ግብር ልዑል። ይህ ሥራ ረቂቅ ነው።»
 በተዋህዶ የከበረው እርሱ ፥ « እከብር የማይል ክቡር፥ እጸድቅ የማይል ጻድቅ ሲሆን»፥ እኔን እና አንተን ያድን ዘንድ በሥጋው ተዋረደ፥ ደሀ ሆነ፥ ወደቀ፥ ጮኸ፥ ማለደ፥ ተሰቃየ፥ ቃተተ፥ አምላኪየ አምላኪየ አለ። በሥጋው።  « ከመ አብዓል አነ በንዴተ ዚአሁ።» በእርሱ ደሀ መባል እኔ እከብር ዘንድ።
ይህን ያህል ስለ ትስብእቱ ሥራ መጨነቃችን ከቶ ለምንድነው? ምክንያቱም የደኅንነታችን ነገር ላይነጣጠል ከእርሱ ጋር ስለ ተያያዘ ነው። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለዚህ ሲናገር እንዲህ አለ፤ « ሰው የሆነም ዘመድ ሊሆነን ብቻ አይደለም። ፈጽሞ ይቅር አለን እንጂ፤ ኃጢአታችንን ለማስተስረይ ከአብ ጋር ለማስታረቅ ሊቀ ካህናትም ይሆነን ዘንድ ወደደ እንጂ፤ ስለዚህም ሰዎችን ሊመስላቸው ይገባል ባለው ነገሩ ላይ ጨምሮ በሁሉ አዛኝ የሕዝቡንም ኃጢአት ለማስተስረይ በእግዚአብሔር ዘንድ የታመነ አስታራቂ ይሆናቸው ዘንድ ነው አለ። ባሕርያችንን ስለተዋሃደ የሰውነቱንም  ነገር ያስተምረን ዘንድ ይህን ተናገረ። ሰው ለመሆን ያበቃው ለማስታረቅ ኃጢአትን ለማስተስረይ ብቻ ነው እንጂ ሌላ ምክንያት የለውም። ከእርሱ ብቻ በቀር ራሱ ብቻውን ኃጢአትን ማስተስረይ የሚቻለው የታመነ አስታራቂ ማነው? ለማስታረቅ ኃጢአትን ለማስተስረይ ያቀረበው መሥዋዕትስ ምንድነው መሥዋዕት ለመሆን የነሣው ሥጋው ብቻ ነው እንጂ»   ይላል።
ቀሲስ ደጀኔ ስትጽፍ፦ ባለፈው እንደ ጠቀስነው፡-ለአማርኛው ጥንት ግዕዝ በመሆኑ፥አማርኛውን ከግዕዙ ጋር እያ ገናዘብን እያንዳንዱን ቃል በዝርዝር እንመለከታለን። (አንዳዶች ይኼ የጠፋኝ ለማስመሰል፥ የመጀመሪያው የግሪኩ ነው ይላሉ።እነዚህ ሰዎች ግሪከኛውን በቅጡ ይወቁት አይወቁት አላ ውቅም።ምናልባት የእግዜር ሰላምታ ያህል ጥቂት ሞክረው ይሆናል።ነገር ግን ግዕዙም፥መጻ ሕፍቱም፥ሊቃውንቱም ከእኛ ጋር መሆናቸውን ማስተዋል ይገባል።ከዚህም ጋር ወደ ሌላ የሚኬደው ሲቸግር ብቻ መሆኑን መዘንጋት አይገባም።እኔ እያልኩ ያለሁት፡-ጥንት ቅዱሳት መጻሕፍት የተተረጎሙት ከባዕድ ቋንቋ ወደ ግዕዝ ነው፥ከዚያ በኋላ ደግሞ ወደ አማርኛ ተተርጉመዋል።ስለዚህ በቅድሚያ ማየት ያለብን የአማርኛው ቅጂና ግዕዙ መስማማታቸውን ነው።) » ብለሃል።
እዚህ ላይ ለአንተም ሆነ ለሌሎች ግልጥ የምናደርገው፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፥ የግእዙ ትርጉም በዓለም ካሉት ትርጉሞች ሁሉ  ቀደምት ከሆኑትና ዛሬም ለምስክርነት የሚፈለግ ትርጉም ነው፤የትርጉሙ ጥንቃቄ፥ ከግሪኩ ጋር ያለው ቅርበት፥  በብዙ ደከመው ለእኛ ያስተላለፉት አባቶች፥ ለቅዱሳት መጻሕፍት ምን ያህል ክብር እንዳላቸው የሚያስረዳ የመንፈሳዊነታቸው ሕያው ምስክር ነው። ። በረከታቸው በእኛ ላይ ይደርብንና ፥ እነርሱ ለእኛ ያስተላለፉትን፥ ዛሬ እናንተ ልታፈልሱት መሞከራችሁ ነው እንድንጮህ ያደረገን።
ባለፈው ጽሑፍህ ስለ ሮሜ ፰፥፴፬ ያስቀመጥከው ከግእዙም ከአማርኛውም የሌለ ነው። ግእዙ ለምሳሌ የሚለው « ወይትዋቀስ በእንቲአነ» ነው። በየትኛው ሰዋስው ነው፥ ወይትዋቀስ በእንቲአነ « ስለ እኛ ይፈርዳል» የሚያሰኘው? በምስጢር ትለኝ ይሆናል። አንተ እኮ እየቀየርክ ያለኸው ገጸ ንባቡን ነው።  የአባቶች ትርጓሜ እንዳትል « ስለ እኛ ይከራከራል» ነው የሚለው እንጂ ስለ እኛ ይፈርዳል አይልም።  በነገራችን ላይ ግእዙና ግሪኩ አንድ ዓይነት አሳብ የያዙ ናቸው። « « ይትዋቀስ ይከራከራል» የሚለውና በግሪኩ “ ἐντυγχάνει  entynchanei “ ይማልዳል ተብሎ የተተርጎመው)  በምስጢር ብቻ ሳይሆን በቀጥታ ትርጉም ይገናኛሉ።  መማለድ ማለት ስለ አንድ ሰው ፈንታ ሆኖ ቆሞ መከራከር ማለት ነውና ። አንዳቸው በአንዳቸው ትርጉም ውስጥ የሚገኙ ናቸው። ይፈርዳል ግን በገጸ ንባቡ በፍጹም የማይገናኝ፥ ከአባቶች መጻሕፍትም ምስክር የማይቀብርለት ነው።  ወደ ግሪኩ የሄድነው አንተ እንደምትለው ግእዙን ንቀን ሳይሆን አሁን ክርክራችን « ይትዋቀስን»  እንዴት እንተርጉመው ስለሆነ ነው።  የአባቶችን ትርጓሜ፥ የቅዱስ ዮሐንስን ትርጓሜ፥ ሃይማኖተ አበውን ወደ ጎን ስላደረጋችሁ፥ ቅዱስ መጽሐፍ ነውና ከመጀመሪያው እንዴት ተጻፈ ማለት የግድ ያስፈልጋል። ቅዱሳት መጻሕፍትን ስለመተርጎም ስናስብ ልንከተለው የሚገባንን አካሄድ  ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ መጽሐፍ ቅዱስን ባስተረጎሙበት ወቅት በጻፉት መቅድም ላይ በሚገባ ገልጠውልናል። እንዲህ ይላሉ፥ « የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጕም ከመሠረታዊ ቋንቋው ከዕብራይስጥና ከፅርዕ ጋር እየተያየ ሊታረም እንደሚገባው ስለ ተመለከትን፥ በቅዱሳት መጻሕፍት ትምህርት ለዚህ ሥራ ተገቢ የሆኑትን ሊቃውንት መረጥን።»   ይላሉ።  እኛም ስንለው የነበረውን ይህን የንጉሠ ነገሥቱን አካሄድ ነው።
የ፪ሺ ዓመቱም መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ፥ ተርጓሚዎቹ በግልጥ ያስቀመጡት ሐቅ አለ። ይኸውም ከትርጓሜው ይልቅ ፖለቲካው ማለትም የእናንተ ተጽእኖ አስገድዶአቸው መሆኑን ለመግለጥ፥ « በግሪኩ ይማልዳል ይላል» ብለዋል። በተጨማሪ ማለት የነበረባቸው፥« ግእዙም እንዲህ አይልም ተገደን ነው እንጂ»  ነበር። ተርጓሚዎቹ የሚያመልጡበትን መንገድ ቢያስቀምጡም፥ ጥቂት የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ለማስደሰት፥ ቤተ ክርስቲያኒቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ አንገት የሚያስደፋ ሥራ ነው ነው የተሠራው። ( ይቀጥላል።)

ከቀሲስ መላኩ ተረፈ) ከቀሲስ መላኩ

Monday, May 15, 2017

የውግዘት ፖለቲካና የቤተ ክርስቲያናችን እጣ ፋንታ


( ክፍል አንድ ) # በቀሲስ መላኩ
መግቢያ
ባለፉት ሃያዎቹ ዓመታት፥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ
ቤተ ክርስቲያን በታሪኳ አይታ የማታውቃቸው ሦስት አበይት
ክስተቶች ታይተውባታል። የመጀመሪያው አንደኛው፥ ከፍተኛ
የሆነ የሕዝብ ፍልሰት ነው። በአዲስ አበባ ያሉት አባቶች
በግልጥ ያስቀመጡት ይፋዊ አኀዙ ሰባት ሚሊየን ይባል
እንጂ፥ ከአስር እስከ አስራ አምስት ሚሊየን የሚሆኑ የቤተ
ክርስቲያኒቱ አባላት ቤተ ክርስቲያኒቱን ትተው ወደ ሌሎች
ቤተ እምነቶችና ተቋሞች ሄደዋል። ሁለተኛው ዓቢይ
ክስተት ቤተ ክርስቲያኒቱ ለሦስት መከፈሏ ነው።
የመንግሥት ለውጥን ተከትሎ አራተኛው ፓትርያክ ብፁዕ
ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከመንበራቸው ከተሰደዱበት
ጊዜ ጀምሮ ቤተ ክርስቲያኒቱ በስደት ያለው ቅዱስ
ሲኖዶስ፥ በአገር ቤት ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ እና ገለለተኛ
በሚል ተከፍላለች። ሦስተኛው እና ቤተ ክርስቲያኒቱ
በታሪኳ አይታው በማታውቀው መንገድ የተከሰቱ ነገሮች
ቢኖሩ በተለይ አዲስ አበባ ባሉት አባቶች ዘንድ፥ «
ውግዘት» እንደ ታላቅ መሣሪያ መያዙ ነው።
በዚህ በያዝነው በ፳፩ኛው ክፍለ ዘመን ሰዎች ተቀራርበው
አሳባቸውን በሚካፈሉበት ዘመን፥ አብያተ ክርስቲያናት
ያለፈ ውግዘታቸውን በይቅርታና በመግባባት አስተካከለው፥
አንድ በሚያደርጋቸው ነገር ላይ ለመነጋገር እየጣሩ ነው።
በቅርቡ የሮም ፖፕና የእስክንድርያው ፓትርያርክ አንዳቸው
የአንዳቸውን ምእመን ዳግም እንዳያጠምቁ
መፈራረማቸው ይታወቃል። ሆኖም ግን ባለፉት 25
ዓመታት ውስጥ በአዲስ አበባ ባሉት አባቶች አማካይነት፥
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በሺዎች የሚቆጠሩ
ምዕመናኖቿን እና አገልጋዮቿን አውግዛለች። ከአንድ
ቢሊየን አባላት በላይ ያላት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን
ባለፉት አንድ መቶ አመታት ያወገዘቻቸውና በአዲስ አበባ
ያሉት አባቶች ያወገዙትን ስንመለከት በቍጥር የእኛው
በልጦ እናገኛለን። በአንድ በኩል የምዕመናኑ በሚሊየኖች
ወደ ሌሎች የእምነት ተቋማት መሄድ በሌላ በኵል ደግሞ
ጳጳሳትን ሳይቀር ምእመናንን ጨምሮ በመቶ ሺዎች
የሚቆጠሩ ምእመናንን ማውገዝ ከየት መጣ ለምንድነው
ይህ ክስተት በእኛ ዘመን የተደጋገመው? ከዚህ ውግዘት
በስተጀርባ ያሉት እነማን ናቸው? ተጠቃሚዎቹስ እነማን
ናቸው የሚለውን ለመመለስ በመጀመሪያ ስለውግዘት
በሚገባ ማወቅ ይኖርብናል።
ሀ. ውግዘት ምንድነው?
ውግዘት ቃሉ፥ ወገዘ ከሚለው ግሥ እንደሚገኝ እና
ፍቺውም መገዘት መለየት መካድ መርገም ማለት እንደሆነ
የሊቁ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ
ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ ይናገራል። ከዚህ ከቃሉ አንጻር
በምንመለከትበት ጊዜ፥ ቃሉ የሚያመለክተን ከዚህ በፊት
ከአንድ አካል ጋር አንድነት (communion) የነበረውን
እንዲለይ (excommuncate) ማድረግ ነው። ይህን
ግልጥ ለማድረግ ቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በእንዴት
ያለ መንገድ እንደተቀመጠ በማየት ትርጉሙን
እንመለከታለን።
1.ውግዘት እርግማን ነው።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች ሲጽፍላቸው
«ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥
ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥
የተረገመ ይሁን። አስቀድመን እንዳልን እንዲሁ አሁን
ሁለተኛ እላለሁ፥ ከተቀበላችሁት የተለየውን ማንም
ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን።» ይላቸዋል። ( ገላ ፩፥፰-
፱) ግእዙም « አትሙሰ መልአክ እምሰማይ ለእመ
መሀረክሙ ካልአ እምዘ መሀርናክሙ ውጉዘ ለይኩን።
በከመ እቤ ቀዳሚ ወይእዜኒ ካዕበ እብል ለእመቦ
ዘመሀረክሙ እምዘመሀርናክሙ ውጉዘ ለይኩን።»
አስተውሉ አማርኛው « የተረገመ ይሁን የሚለውን ግእዙ
የተወገዘ ይሁን ይለዋል። ይህ ውግዘት ወይም እርግማን
ምን ማለት እንደሆነ እንመልከት፥ አዲስ ኪዳን
ለመጀመሪያ ጊዜ የተጻፈበትን የግሪኩን ቃል
በምንመለከትበት ጊዜ፥ የተወገዘ ይሁን አናቴማ ኤስቶ
(ἀνάθεμα ἔστω ) ይለዋል። አናቴማ ቃሉ በብሉይ
ኪዳን « እርም»፥ «ለእሳት የተሰጠ» ማለት ነው። ለምሳሌ
ኢያሱ በኢያሪኮ የተገኘው ሁሉ እርም እንዲሆን ሲያዝ
አካን የተባለው ሰው « እርም ከሆነው ነገር ወሰደ»
ይለናል። ኢያሱ7፥1። እንዲህ ዓይነት ብዙ ጥቅሶች
በብሉይ ኪዳን እናገኛለን። በአዲስ ኪዳንም ይህንኑ ቃል
ሳይስት፥ አናቴማ ( ውግዘት እርግማን) ማለት
በእግዚአብሔር ፍርድ ውስጥ መውደቅ ማለት ነው።
ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ በገላያ መልእክቱ ላይ በሐዋርያት
ከተሰበከው የጸጋ ወንጌል የተለየ ወንጌልን የሚሰብክ
በዚህ የእግዚአብሔር ፍርድ ውስጥ እንደሚወድቅ ሲናገር
እናያለን።
2. ውግዘት ለሰይጣን አልፎ መሰጠት ነው።
አሁንም ወደ ቅዱስ ጳውሎስ መልእክት ስንመጣ
በ1ቆሮ5፥5 ላይ «መንፈሱ በጌታ በኢየሱስ ቀን ትድን
ዘንድ እንደዚህ ያለው ለሥጋው ጥፋት ለሰይጣን
እንዲሰጥ ፍርዴ ነው።» ሲል እናገኛለን። ቅዱስ ጳውሎስ
በዚህ ስፍራ ሐዋርያዊ ውግዘቱን ያሳረፈበት ሰው፥ በሥነ
ምግባር ውድቀት ውስጥ የተገኘ ማለትም የአባቱን ሚስት
ያገባ ሰው ነው። ሐዋርያው ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች
ሲናገር «ይህን ሥራ የሠራው ከመካከላችሁ ይወገድ። እኔ
ምንም እንኳ በሥጋ ከእናንተ ጋር ባልሆን፥ በመንፈስ
ከእናንተ ጋር ነኝ፥ ከእናንተም ጋር እንዳለሁ ሆኜ ይህን
እንደዚህ በሠራው ላይ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም
አሁን ፈርጄበታለሁ፤ እናንተና መንፈሴም ከጌታችን
ከኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ጋር ተሰብስበን፥ መንፈሱ በጌታ
በኢየሱስ ቀን ትድን ዘንድ እንደዚህ ያለው ለሥጋው ጥፋት
ለሰይጣን እንዲሰጥ ፍርዴ ነው።» ይላል።
ይህ የቅዱስ ጳውሎስ ቃል ስለ ውግዘት ሦስት ዋና ዋና
ነገሮችን ያሳየናል። አንደኛ፥ ይህ ነገር በጉባኤ በጥንቃቄ
የሚታይ ነው። ጉባኤው የክርስቶስ ጌትነት የከበረበት
ጉባኤ መሆን አለበት። የሐዋርያው ሥልጣን የከበረበት
መሆን አለበት። « እናንተና መንፈሴም ከጌታችን ከኢየሱስ
ክርስቶስ ኃይል ጋር ተሰብስበን» በዚህ ዘመን ያለውን
በውግዘት ዙሪያ የሚከናወነው፥ ተመሳሳይነቱ ከፖለቲካ
አደባባዮች ጋር ነው። አንደኛ ከብሮ የሚታየው ክርስቶስ
ሳይሆን የሰዎች የተንኮለኛነት ችሎታ ነው። ለምሳሌ
ባለፉት ሃያ አምስት አመታት በኢትዮጵያ ያሉት አባቶች
በአመት ሁለት ጊዜ ሲሰበሰቡ፥ ከስብሰባቸው በፊት፥
የተቃውሞ ሰልፍ፥ የክስ ደብዳቤዎች፥ ዘመቻዎች፥
ይካሄድባቸዋል። ወደስብሰባው የሚሄዱ አባቶች
ስብሰባው ከመጀመሩ በፊት ተወጋዡ ማን
እንደሚሆን፥ውሳኔው ምን መሆን እንዳለበት ተነግሮአቸውና
ተጽእኖ ተደርጎባቸው ነው የሚገቡት። ነገሮችን ከምንም
ነገር ነጻ በሆነ መንገድ ለማየት የሚሞክሩ አባቶች፥
በስድብ በስም ማጥፋት ጥላሸት ይቀባባቸዋል። በዚህ
ምክንያት አንዳንዶች ዝምታን ሲመርጡ አንዳንዶች
ለተጽእኖው ያጎበድዳሉ። ቅዱስ ጳውሎስ « ከኢየሱስ
ክርስቶስ ኃይል ጋር ተሰብስበን» ሲል « ብርታታችንና
ጉልበታችን የሚሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ይሆናል» ማለቱ
ነው። እውነት የምትነግሠውና ሐሰት ሥፍራን የምታጣው፥
በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ኃይልና በመንፈስ ቅዱስ
መሪነት ስንጓዝ ነውና።
ቅዱስ ጳውሎስ ሌላ ታላቅ ነገር ያነሣል። ይኸውም
ውግዘት ምን ያህል አስፈሪ ነገር እንደሆነ የሚያመለክት
ነው። አንድ ሰው ከእድር ቢለይ፥ ሌላ እድር ውስጥ
ይገባል። ወይም በዘመናዊው ዓለም ሌላ ዘዴ ሊጠቀም
ይችላል። ( ላይፍ ኢንሹራንስ ሊገባ ይችላል።)ፋንታ
( ክፍል አንድ ) # በቀሲስ መላኩ
መግቢያ
ባለፉት ሃያዎቹ ዓመታት፥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ
ቤተ ክርስቲያን በታሪኳ አይታ የማታውቃቸው ሦስት አበይት
ክስተቶች ታይተውባታል። የመጀመሪያው አንደኛው፥ ከፍተኛ
የሆነ የሕዝብ ፍልሰት ነው። በአዲስ አበባ ያሉት አባቶች
በግልጥ ያስቀመጡት ይፋዊ አኀዙ ሰባት ሚሊየን ይባል
እንጂ፥ ከአስር እስከ አስራ አምስት ሚሊየን የሚሆኑ የቤተ
ክርስቲያኒቱ አባላት ቤተ ክርስቲያኒቱን ትተው ወደ ሌሎች
ቤተ እምነቶችና ተቋሞች ሄደዋል። ሁለተኛው ዓቢይ
ክስተት ቤተ ክርስቲያኒቱ ለሦስት መከፈሏ ነው።
የመንግሥት ለውጥን ተከትሎ አራተኛው ፓትርያክ ብፁዕ
ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከመንበራቸው ከተሰደዱበት
ጊዜ ጀምሮ ቤተ ክርስቲያኒቱ በስደት ያለው ቅዱስ
ሲኖዶስ፥ በአገር ቤት ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ እና ገለለተኛ
በሚል ተከፍላለች። ሦስተኛው እና ቤተ ክርስቲያኒቱ
በታሪኳ አይታው በማታውቀው መንገድ የተከሰቱ ነገሮች
ቢኖሩ በተለይ አዲስ አበባ ባሉት አባቶች ዘንድ፥ «
ውግዘት» እንደ ታላቅ መሣሪያ መያዙ ነው።
በዚህ በያዝነው በ፳፩ኛው ክፍለ ዘመን ሰዎች ተቀራርበው
አሳባቸውን በሚካፈሉበት ዘመን፥ አብያተ ክርስቲያናት
ያለፈ ውግዘታቸውን በይቅርታና በመግባባት አስተካከለው፥
አንድ በሚያደርጋቸው ነገር ላይ ለመነጋገር እየጣሩ ነው።
በቅርቡ የሮም ፖፕና የእስክንድርያው ፓትርያርክ አንዳቸው
የአንዳቸውን ምእመን ዳግም እንዳያጠምቁ
መፈራረማቸው ይታወቃል። ሆኖም ግን ባለፉት 25
ዓመታት ውስጥ በአዲስ አበባ ባሉት አባቶች አማካይነት፥
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በሺዎች የሚቆጠሩ
ምዕመናኖቿን እና አገልጋዮቿን አውግዛለች። ከአንድ
ቢሊየን አባላት በላይ ያላት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን
ባለፉት አንድ መቶ አመታት ያወገዘቻቸውና በአዲስ አበባ
ያሉት አባቶች ያወገዙትን ስንመለከት በቍጥር የእኛው
በልጦ እናገኛለን። በአንድ በኩል የምዕመናኑ በሚሊየኖች
ወደ ሌሎች የእምነት ተቋማት መሄድ በሌላ በኵል ደግሞ
ጳጳሳትን ሳይቀር ምእመናንን ጨምሮ በመቶ ሺዎች
የሚቆጠሩ ምእመናንን ማውገዝ ከየት መጣ ለምንድነው
ይህ ክስተት በእኛ ዘመን የተደጋገመው? ከዚህ ውግዘት
በስተጀርባ ያሉት እነማን ናቸው? ተጠቃሚዎቹስ እነማን
ናቸው የሚለውን ለመመለስ በመጀመሪያ ስለውግዘት
በሚገባ ማወቅ ይኖርብናል።
ሀ. ውግዘት ምንድነው?
ውግዘት ቃሉ፥ ወገዘ ከሚለው ግሥ እንደሚገኝ እና
ፍቺውም መገዘት መለየት መካድ መርገም ማለት እንደሆነ
የሊቁ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ
ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ ይናገራል። ከዚህ ከቃሉ አንጻር
በምንመለከትበት ጊዜ፥ ቃሉ የሚያመለክተን ከዚህ በፊት
ከአንድ አካል ጋር አንድነት (communion) የነበረውን
እንዲለይ (excommuncate) ማድረግ ነው። ይህን
ግልጥ ለማድረግ ቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በእንዴት
ያለ መንገድ እንደተቀመጠ በማየት ትርጉሙን
እንመለከታለን።
1.ውግዘት እርግማን ነው።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች ሲጽፍላቸው
«ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥
ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥
የተረገመ ይሁን። አስቀድመን እንዳልን እንዲሁ አሁን
ሁለተኛ እላለሁ፥ ከተቀበላችሁት የተለየውን ማንም
ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን።» ይላቸዋል። ( ገላ ፩፥፰-
፱) ግእዙም « አትሙሰ መልአክ እምሰማይ ለእመ
መሀረክሙ ካልአ እምዘ መሀርናክሙ ውጉዘ ለይኩን።
በከመ እቤ ቀዳሚ ወይእዜኒ ካዕበ እብል ለእመቦ
ዘመሀረክሙ እምዘመሀርናክሙ ውጉዘ ለይኩን።»
አስተውሉ አማርኛው « የተረገመ ይሁን የሚለውን ግእዙ
የተወገዘ ይሁን ይለዋል። ይህ ውግዘት ወይም እርግማን
ምን ማለት እንደሆነ እንመልከት፥ አዲስ ኪዳን
ለመጀመሪያ ጊዜ የተጻፈበትን የግሪኩን ቃል
በምንመለከትበት ጊዜ፥ የተወገዘ ይሁን አናቴማ ኤስቶ
(ἀνάθεμα ἔστω ) ይለዋል። አናቴማ ቃሉ በብሉይ
ኪዳን « እርም»፥ «ለእሳት የተሰጠ» ማለት ነው። ለምሳሌ
ኢያሱ በኢያሪኮ የተገኘው ሁሉ እርም እንዲሆን ሲያዝ
አካን የተባለው ሰው « እርም ከሆነው ነገር ወሰደ»
ይለናል። ኢያሱ7፥1። እንዲህ ዓይነት ብዙ ጥቅሶች
በብሉይ ኪዳን እናገኛለን። በአዲስ ኪዳንም ይህንኑ ቃል
ሳይስት፥ አናቴማ ( ውግዘት እርግማን) ማለት
በእግዚአብሔር ፍርድ ውስጥ መውደቅ ማለት ነው።
ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ በገላያ መልእክቱ ላይ በሐዋርያት
ከተሰበከው የጸጋ ወንጌል የተለየ ወንጌልን የሚሰብክ
በዚህ የእግዚአብሔር ፍርድ ውስጥ እንደሚወድቅ ሲናገር
እናያለን።
2. ውግዘት ለሰይጣን አልፎ መሰጠት ነው።
አሁንም ወደ ቅዱስ ጳውሎስ መልእክት ስንመጣ
በ1ቆሮ5፥5 ላይ «መንፈሱ በጌታ በኢየሱስ ቀን ትድን
ዘንድ እንደዚህ ያለው ለሥጋው ጥፋት ለሰይጣን
እንዲሰጥ ፍርዴ ነው።» ሲል እናገኛለን። ቅዱስ ጳውሎስ
በዚህ ስፍራ ሐዋርያዊ ውግዘቱን ያሳረፈበት ሰው፥ በሥነ
ምግባር ውድቀት ውስጥ የተገኘ ማለትም የአባቱን ሚስት
ያገባ ሰው ነው። ሐዋርያው ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች
ሲናገር «ይህን ሥራ የሠራው ከመካከላችሁ ይወገድ። እኔ
ምንም እንኳ በሥጋ ከእናንተ ጋር ባልሆን፥ በመንፈስ
ከእናንተ ጋር ነኝ፥ ከእናንተም ጋር እንዳለሁ ሆኜ ይህን
እንደዚህ በሠራው ላይ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም
አሁን ፈርጄበታለሁ፤ እናንተና መንፈሴም ከጌታችን
ከኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ጋር ተሰብስበን፥ መንፈሱ በጌታ
በኢየሱስ ቀን ትድን ዘንድ እንደዚህ ያለው ለሥጋው ጥፋት
ለሰይጣን እንዲሰጥ ፍርዴ ነው።» ይላል።
ይህ የቅዱስ ጳውሎስ ቃል ስለ ውግዘት ሦስት ዋና ዋና
ነገሮችን ያሳየናል። አንደኛ፥ ይህ ነገር በጉባኤ በጥንቃቄ
የሚታይ ነው። ጉባኤው የክርስቶስ ጌትነት የከበረበት
ጉባኤ መሆን አለበት። የሐዋርያው ሥልጣን የከበረበት
መሆን አለበት። « እናንተና መንፈሴም ከጌታችን ከኢየሱስ
ክርስቶስ ኃይል ጋር ተሰብስበን» በዚህ ዘመን ያለውን
በውግዘት ዙሪያ የሚከናወነው፥ ተመሳሳይነቱ ከፖለቲካ
አደባባዮች ጋር ነው። አንደኛ ከብሮ የሚታየው ክርስቶስ
ሳይሆን የሰዎች የተንኮለኛነት ችሎታ ነው። ለምሳሌ
ባለፉት ሃያ አምስት አመታት በኢትዮጵያ ያሉት አባቶች
በአመት ሁለት ጊዜ ሲሰበሰቡ፥ ከስብሰባቸው በፊት፥
የተቃውሞ ሰልፍ፥ የክስ ደብዳቤዎች፥ ዘመቻዎች፥
ይካሄድባቸዋል። ወደስብሰባው የሚሄዱ አባቶች
ስብሰባው ከመጀመሩ በፊት ተወጋዡ ማን
እንደሚሆን፥ውሳኔው ምን መሆን እንዳለበት ተነግሮአቸውና
ተጽእኖ ተደርጎባቸው ነው የሚገቡት። ነገሮችን ከምንም
ነገር ነጻ በሆነ መንገድ ለማየት የሚሞክሩ አባቶች፥
በስድብ በስም ማጥፋት ጥላሸት ይቀባባቸዋል። በዚህ
ምክንያት አንዳንዶች ዝምታን ሲመርጡ አንዳንዶች
ለተጽእኖው ያጎበድዳሉ። ቅዱስ ጳውሎስ « ከኢየሱስ
ክርስቶስ ኃይል ጋር ተሰብስበን» ሲል « ብርታታችንና
ጉልበታችን የሚሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ይሆናል» ማለቱ
ነው። እውነት የምትነግሠውና ሐሰት ሥፍራን የምታጣው፥
በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ኃይልና በመንፈስ ቅዱስ
መሪነት ስንጓዝ ነውና።
ቅዱስ ጳውሎስ ሌላ ታላቅ ነገር ያነሣል። ይኸውም
ውግዘት ምን ያህል አስፈሪ ነገር እንደሆነ የሚያመለክት
ነው። አንድ ሰው ከእድር ቢለይ፥ ሌላ እድር ውስጥ
ይገባል። ወይም በዘመናዊው ዓለም ሌላ ዘዴ ሊጠቀም
ይችላል። ( ላይፍ ኢንሹራንስ ሊገባ ይችላል።)

Saturday, April 29, 2017

"ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ" የብርሃኑ አድማሴ የቃላት ዝላይ

የአለት ላይ ዝላይ አያዋጣም!

"ወደ አምላኬና ወደ አምላካቸሁ"
ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በስብከቶች እየተፈራ የሚዘለል የእግዚአብሔር ቃል
+++++++++++++++++++++++++++++++++++++
ሰሞኑን በየቤተክርስቲያኑ ዐውደ ምሕረት የሚነገረው ወንጌል ስለ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ቢሆንም የማቅ ሰባክያነ ወንጌል ተብዬ እንደነ ተስፋዬ ሞሲሳ (ተስፋዬ ስለቃሉ ሞዛዛ) እና ብርሃኑ አድማሴ (ብርሃኑ ቃሉን ደርምሴ) እየዘበራረቁም ቢሆን ተያይዘውታል።
የእግዚአብሔርን ቃል እየቀነሱ እና እየዘለሉ ማስተማር ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው?
ጌታ ኢየሱስ ከሙታን መካከል ከተነሳ በኋላ በዮሐ 20፥17 ማርያምን አትንኪኝ አላረኩምና ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ፦ እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ አርጋለሁ ብለሽ
ንገሪአቸው እንዳላት በግልፅ ተፅፎ ሳለ እነዚህ የማቅ አቀንቃ  የክርስቶስ ሰው መሆኑ እንዳበቃ አርገው ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ የሚለውን እየዘለሉ በድፍረት መናገራቸው ያሳዝናል።
ሰው በመሆኑ መከራን ተቀበለ እንጂ ለዘላለም ስጋን ተዋህዶ ይኖራል ብሎ እንደተናገረው ቅዱስ አትናቴዎስ። ሞትን ድል ነስቶ በአብ ቀኝ የተቀመጠው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬም ለዘላለም የማይለወጥ ፍፁም ሰው: ፍፁም አምላክ ነው (ሃይማኖት አበው 1986 ገፅ 80/ ዕብ 13፥8)
ክርስቶስ በአብ ቀኝ ከተቀመጠ በኋላ የሰውነቱን ግብር አቁሞ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር መለኮታዊ ስራውን እየሰራ ይገኛል ብሎ መስብኩ የክርስቶስን መካከለኛነት መቃወም ብቻ ሳይሆን ይኼ አባባል ኢየሱስ በአባቱ ቀኝ እስኪቀመጥ ድረስ መለኮት ስራውን ለስጋ ትቶ ስጋ ብቻ ይሰራ ነበር። አሁን በተራው ሰራውን ስለፈፀመ ስራውን ለመለኮት አስረከበ እንደማለት ነው። ይህ አባባል ደግሞ ሲያረግ ሥጋውን በመለኮት ባህርይ አረቀቀው: መጠጠው የሚለውን የአውጣኪን የክህደትአስተምህሮ መቀበል ይሆናል። ዳሩ ይኄ ስብከት በብዙዎቹ ሰባኪያን ዘንድ ሲነገር ይሰማል። መለኮታዊ ሥልጣኑን በመጠበቅ ሲባል በሥጋ ማረጉን በርቀት ይከላከላሉ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በኦፊሴል አውጣኪን ብታወግዝም አስተምህሮውን በስልት ትቀበላለች። የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት አውጣኪያውያን ናችሁ የሚሏትም አለምክንያት አይደለም። የኢየሱስን እርገት የኢት/ኦር/ ቤተክርስቲያን የምትቀበለው በመለኮታዊ ባህርይ ብቻ እንጂ ዛሬም በሥጋው በአብ ቀኝ እንዳለ አይደለም ማለት ነው? በሥጋው አርጓል የምትል ከሆነም በሥጋው የማረጉን ምክንያት በድፍረት ልታስተምር ይገባታል። ከኃጢአት ለመንጻትም ሆነ ሕይወት ወደሆነው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት አዲስ አማኝ ለመምጣት በስጋው ቀራንዮ ላይ አንዴ በፈፀመው ድኅነት ስለእኛ አሁንም በሰማይ በአብ ይታይ ዘንድ በስጋው አለ ልትል ይገባታል። መለኮት ቃሉ ብቻ ማዳን እየተቻለው ሥጋ የለበሰው በሥጋ ያጣነውን ክብር በልጁ በኩል ልጅነትን እንድናገኝና በሰማያዊ መቅደስ የመግባት ድፍረት እንድናገኝ ስለፈለገ ብቻ ነው።
ይህንንም ሐዋርያው እንደዚህ አስረግጦ ይነግረናል።

" ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሰራች፥ የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደ ምትሆን ቅድስት አልገባምና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ።"
(ዕብራውያን 9:24)
ከዚህ ውጪ የሆነው ሁሉ ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ መሆኑን የሚያስክድ ነው።
ኢየሱስ የመጣበትን በእያንዳንዳችን ፈንታ በመስቀል ላይ የማዳንን ስራ ፈፅሞ ሞቶ ከተነሳ በኋላ አምላኬ ማለቱ የማቅን ሰባኪያን አባባል ገደል ከቶታል።
ለዚህም ሃይማኖት አበው 1986 ገፅ 248 እንዲህ ሲል ይመሰክራል
" እኔ ሰው የሆንኩ አምላክ ነኝና እኔም አንድ ነኝና ይህንንም ያንንም እኔ እላለው ይላል፣ የሰውን ባህሪይ ገንዘብ አድርጌአለውና። ኋጢአት የሌለበት እርሱ እኔ ነፍስን ስጋን ተዋህጃለውና ከእኔ ጋር አንድ ላደረኩት ለስጋ ስርዓት እንደሚገባ እንዲህ አባቴን "አምላኬ" ብዬ ጠራሁት "
እናም ተወዳጆች ሆይ ጌታ ኢየሱስ እንዴ ለዘላለም ባፈሰሰው ደስ ዳግም ማፍሰስ ሳይጠበቅበት ሁል ጊዜ ሲያነፃን ይኖራል። እግዚአብሔር እኛን የሚያይበትብቸኛው መንገድ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው።
"የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል።" 1ኛ ዩሐ 1፥7
ያለፍርሃት የጌታ ምስክሮች እንሁን እኔ ይህን ታዘብኩ እናንተም እስኪ የማቅን ሰባኪያንን የሚፈሩትንና የሚዘሉትን ቃል ንገሩንና ለመማማር እንወያይበት።
የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ፀጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ህብረት ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን