Tuesday, May 17, 2016

"ኢየሱስ ክርስቶስ የዐዲስ ኪዳን መካከለኛ"



Part One (www.chorra.net)

በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መካከለኛነት ላይ በዚህ ዐምድ በተከታታይ የወጡትን ጽሑፎች አስመልክተው፣ የተለያዩ አንባብያን የስልክ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን ለዝግጅት ክፍሉ አቅርበዋል። ከአንባብያኑ መካከል አንዳንዶቹ የክርስቶስን መካከለኛነት ላለመቀበልና ለሌሎች ቅዱሳን ለመስጠት አለን ያሉትን ማስረጃ በማቅረብ ጭምር ለመከራከር ሞክረዋል። ለክርክራቸው እንዲረዳቸውም፣ “ስለዚህ እኛ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም፤ ክርስቶስንም በሥጋ እንደ ሆነ ያወቅነው ብንሆን እንኳ፥ አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ አናውቀውም” (2ቆሮ. 5፥16) የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል የጠቀሱ ሲሆን፣ በመጨረሻም፣ “አሁን እርሱ መካከለኛ መሆኑ ቀርቷል፤ አሁን አምላክ ነው” ሲሉ ደምድመዋል። ክርስቶስን ከመካከለኛነቱ ስፍራ አንሥተውም፣ “አሁን መካከለኛው ሥጋ ወደሙ ነው” ሲሉም አክለዋል። ስለ ሥጋ ወደሙ የተባለውን ለቀጣዩ ዕትም እናቈየውና በጥቅሱ ላይ የተላለፈውንና ክርስቶስ አሁን አምላክ እንጂ ሰው አይደለም የሚለውን አውጣኪያዊ ትምህርት በመመርመር የክርስቶስን መካከለኛነት መጽሐፍ ቅዱስንና የአበውን ምስክርነት በመጥቀስ ወደ ማሳየት እንለፍ።
‘ክርስቶስ በዚህ ምድር ሳለ ብቻ ነበረ እንጂ አሁን ወደ ክብሩ ከገባ በኋላ መካከለኛ አይደለም’ የሚሉት በትምህርተ ሥጋዌ ላይ በቂ ዕውቀት የሌላቸው ብቻ ሳይሆኑ፣ ተምረዋል የሚባሉትም ጭምር እንደ ሆኑ ይታወቃል። በተለይም የተማሩት ክፍሎች እንዳልተማሩቱ አፋቸውን ሞልተው አሁን አምላክ ብቻ ነው እንጂ ሰውም አይደለም አይሉም፤ ክርስቶስ ዛሬም ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው መሆኑን እናምናለን ይላሉ። ክርስቶስ አሁን በአብ ቀኝ ተቀምጦ ባለበት ሁኔታ ግብረ አምላክን (የአምላክን ሥራ) እንጂ ግብረ ትስብእትን (የሰውነትን ሥራ) አይፈጽምም ስለሚሉ ግን በክብር የሆነውን ግብረ ትስብእትን ያስተባብላሉ። ለምሳሌ፣ “… ነቢረ የማን (በአብ ቀኝ መቀመጥ) ክርስቶስ ግብረ ትስብእት ከፈጸመ በኋላ እንደ ገና የሰውነትን ሥራ የማይሠራ፥ ነገር ግን ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በክብር መለኮታዊ ሥራውን እየሠራ የሚኖር መሆኑን የሚያስረዳ ቃል ነው”[1] ያሉ ይገኛሉ። አባባሉ ኢየሱስ ክርስቶስ በአብ ቀኝ እስኪቀመጥ ድረስ መለኮት ሥራውን ለትስብእት ትቶ ትስብእት ብቻ ይሠራ ነበር፤ ትስብእት ደግሞ አሁን በተራው የሥራ ጊዜውን ስለ ፈጸመ ሥራውን ለመለኮት ተወ ያሰኛል። እንዲህ ከሆነም ክርስቶስ በዚህ ምድር ሳለ ግብረ ትስብእትን ብቻ እንጂ ግብረ መለኮትን አይፈጽምም ነበር የሚል አንድምታ ያለው ይመስላል። ቅዱሳት መጻሕፍትና በእነርሱ ላይ የተመሠረቱ የአበው ምስክርነቶች ግን የሚነግሩን ከዚህ የተለየ እውነት ነው።

“አንሶሰወ ከመ ሰብእ እንዘ ይገብር ከመ እግዚአብሔር። ርኅበ በፈቃዱ ከመ እጓለ እመ ሕያው ወአጽገቦሙ ለርኁባን ብዙኃን አሕዛብ እም ኅዳጥ ኅብስት ከመ ከሃሊ። ጸምአ ከመ ዘይመውት ወረሰዮ ለማይ ወይነ ከመ ማሕየዌ ኵሉ። ኖመ ከመ ውሉድ ዘሥጋ ነቅሐ ወገሠጾሙ ለነፋሳት ከመ ፈጣሪ። ደክመ ወአዕረፈ ከመ ትሑት ወሖረ ዲበ ማይ ከመ ልዑል። ወኰርዕዎ ርእሶ ከመ ገብር ወአግዐዘነ እም አርዑተ ኀጢአት ከመ እግዚአ ኵሉ።”
ትርጓሜ፥ “እንደ እግዚአብሔር እየሠራ እንደ ሰው ተመላለሰ። ሰው እንደ መሆኑ በፈቃዱ ተራበ፤ ከሃሊ እንደ መሆኑ የተራቡ ብዙ አሕዛብን ከጥቂት እንጀራ አጠገባቸው። የሚሞት እንደ መሆኑ ተጠማ፤ ሁሉን የሚያድን እንደ መሆኑ ውሃውን ወይን አደረገው። እንደ ሥጋ ልጆች ተኛ፤ ፈጣሪ እንደ መሆኑ ነቅቶ ነፋሳትን ገሠጻቸው። ትሑት እንደ መሆኑ ደክሞ ዐረፈ፤ ልዑል እንደ መሆኑ በባሕር ላይ ሄደ። እንደ ተገዢ ራሱን መቱት፤ የሁሉ ጌታ እንደ መሆኑ ከኀጢአት ቀንበር ነጻ አደረገን።”[2]
በዚህ ቃለ ቅዳሴ ውስጥ አንዱ ክርስቶስ በዚህ ምድር ላይ ይመላለስ በነበረ ጊዜ በሰውነቱ የተከናወነውንና ያከናወነውን ግብረ ትስብእትን፣ በአምላክነቱም የሠራውን ሥራ (ግብረ መለኮትን) በንጽጽር እንመለከታለን።
· መራብ የሰውነት ግብር ነው (ማቴ. 4፥2፤ 21፥18)፤ - በጥቂት እንጀራ ብዙዎችን ማጥገብና ዐሥራ ሁለት መሶብ ተረፍ ማስነሣት ደግሞ ግብረ መለኮት ነው (ዮሐ. 6፥10-13)።
· መጠማት የሰውነት ግብር ነው (ዮሐ. 4፥7፤ 19፥28)፤ - ውሃውን ወደ ወይን መለወጥ ደግሞ ግብረ መለኮት ነው (ዮሐ. 2፥7-11)።
· ማንቀላፋት የሰውነት ግብር ነው (ማቴ. 8፥24፤ ሉቃ. 8፥23)፤ - ነፋሱንና ባሕሩን መገሠጽና ጸጥ ማድረግ ደግሞ ግብረ መለኮት ነው (ማቴ. 8፥26-27፤ ሉቃ. 8፥24-25)።
· መድከምና ማረፍ ግብረ ትስብእት ነው (ዮሐ. 4፥6)፤ - በባሕር ላይ መሄድ ደግሞ ግብረ መለኮት ነው (ማቴ. 14፥25-26)።
· ተኰርዖተ ርእስ (ራስን በዘንግ መመታት) ግብረ ትስብእት ነው (ማቴ. 27፥29-30)። - ሰውን ከኀጢአት ማዳን ደግሞ ግብረ መለኮት ነው (1ጢሞ. 1፥15፤ ዕብ. 2፥14-15)።
ክርስቶስ አሁን ያለው በክብር እንጂ በዚህ ምድር በነበረበት ሁኔታ አይደለምና በዚህ ምድር በሰውነቱ የተቀበለው ግብረ ትስብእት ማለትም፦ መራብ፣ መጠማት፣ መድከም፣ ማረፍ፣ ማንቀላፋት፣ ወዘተ. አሁን የለበትም። ይሁን እንጂ ክርስቶስ በዚህ ምድር ሳለ አንድ ጊዜ በፈጸመውና ለዘላለም በሚያገለግለው የአድኅኖት ሥራው አሁን በክብር ባለበት ሁኔታ፣ በእርሱ በኩል አምነው ለሚመጡትና ከመጡም በኋላ ጠላት የሆነው ሰይጣንና ኀጢአት ለሚከሷቸው ሁሉ ዋስትናቸውና መታረቂያቸው ሆኖ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለ መሆኑን መካድ አይቻልም። የሚከተሉት መጽሐፍ ቅዱሳውያን ጥቅሶች ይህን ያስረዳሉ፤
· “እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው፥ የሚኰንንስ ማን ነው? የሞተው፥ ይልቁንም ከሙታን የተነሣው፥ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፥ ደግሞ ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው” (ሮሜ 8፥33-34)።
· “ልጆቼ ሆይ፥ ኀጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኀጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም የኀጢአታችን ማስተስረያ ነው፥ ለኀጢአታችንም ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኀጢአት እንጂ” (1ዮሐ. 2፥1-2)።
በክብር የሆነውና ክርስቶስ በአብ ቀኝ ተቀምጦ ባለበት ሁኔታ የሚያከናውነው ግብረ ትስብእት ከሊቀ ካህናትነቱ ጋር የሚያያዝ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማያት ያለፈ በድካማችንም ሊራራልን የሚችል ታላቅ ሊቀ ካህናት ነው (ዕብ. 4፥14-15)። “ሊቀ ካህናት ሁሉ ስለ ኀጢአት መባንና መሥዋዕትን ሊያቀርብ ከሰው ተመርጦ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ስለ ሰው ይሾማልና፤” ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ ጌታ ሊቀ ካህናት የሆነው በሰውነቱ ነው (ዕብ. 5፥1)። ስለዚህም በሰማያዊቱ ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ የሚከናወነው የሊቀ ካህናትነቱ ተልእኮ ግብረ ትስብእት ነው። እርሱ “በሥጋው ወራት (በዚህ ምድር ሳለ) ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፤ እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ተሰማለት፤ … ከተፈጸመም በኋላ በእግዚአብሔር እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ሊቀ ካህናት ተብሎ ስለ ተጠራ፥ ለሚታዘዙለት ሁሉ የዘላለም መዳን ምክንያት ሆነላቸው” (ዕብ. 5፥7፡9-10)። በዚህ ጥቅስ ውስጥ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር በነበረበት ጊዜ ጸሎትንና ምልጃን እንዳቀረበና እንደ ተሰማለትም ተገልጿል። ከዚያ በኋላ ባለው ጊዜ ደግሞ በሊቀ ካህናትነቱ ለሚታዘዙለት ሁሉ የዘላለም መዳን ምክንያት ሆኖ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአድኅኖት ሥራውን ፈጽሞ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጧል (ማር. 16፥19፤ ሐ.ሥ. 2፥33፤ 7፥55-56፤ ሮሜ 8፥34፤ ቈላ. 3፥1፤ ዕብ. 10፥12፤ 1ጴጥ. 3፥22)። በእግዚአብሔር ቀኝ የተቀመጠውም በዚህ ምድር ሳለ ይፈጽም የነበረውን ግብረ ትስብእትን የማይፈጽም ሆኖ፣ ነገር ግን በክብር የሆነውን ግብረ ትስብእት እየፈጸመ ነው። የዕብራውያኑ ጸሓፊ ይህን ሲያስረዳ እንዲህ ብሏል፤ “ከተናገርነውም ዋና ነገሩ ይህ ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን፤ እርሱም የመቅደስና የእውነተኛዪቱ ድንኳን አገልጋይ ነው፤ እርስዋም በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች ናት” (ዕብ. 8፥1-2)። ልብ እንበል! በእግዚአብሔር ቀኝ የተቀመጠው ሊቀ ካህናት፣ በዚያው ሁኔታ በሰማይ ያለችውና በእግዚአብሔር የተተከለችው የእውነተኛዪቱ ድንኳን አገልጋይ ነው። ወደዚያች የገባውም፣ ስለ እኛ ቀዳሚ ሆኖ በእግዚአብሔር ፊት አሁን ይታይልን ዘንድ ነው (ዕብ. 6፥20፤ 9፥24፡28)። ይህም በክብሩ ሆኖ ግብረ ትስብእትን እንደሚፈጽም ያመለክታል።
ከዚህ ቀደም በተከታታይ ለማስገንዘብ እንደ ሞከርነው ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ እንድ ጊዜ ባቀረበው ምልጃ (ዮሐ. 17፥9፡20-21) እና አንድ ጊዜ ባቀረበው መሥዋዕት (ዕብ. 10፥12፡14) ለዘላለም መካከለኛችን ነው። ይህም ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬም በሰማይ ምልጃና መሥዋዕት ያቀርባል ማለት ሳይሆን፣ አንድ ጊዜ ባቀረበው ምልጃና መሥዋዕት ዛሬም አስታራቂያችንና መታረቂያችን እርሱው ብቻ ነው ማለት ነው። ዛሬ አንድ ኀጢአተኛ ሰው የወንጌልን ቃል ሰምቶ፣ በክርስቶስ አዳኝነት ቢያምንና በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ቢጸልይ ከእግዚአብሔር ጋር የሚታረቀውና የኀጢአቱን ስርየት የሚቀበለው፣ ክርስቶስ አንድ ጊዜ ባቀረበው ምልጃና መሥዋዕት (በደሙ) አማካይነት ነው። በክርስቶስ ያመነውና በልዩ ልዩ ምክንያት በኀጢአት የወደቀ ክርስቲያንም ንስሓ ሲገባ ስርየተ ኀጢአትን የሚቀበለው በዚሁ መንገድ ነው። በእርሱ በኩል አምነው ለሚመጡት ለዘላለም የመዳን ምክንያት ሆነላቸው ተብሎ የተነገረውም ስለዚህ ነው (ዕብ. 5፥9-10፤ 7፥25)።
ክርስቶስን አሁን አምላክ እንጂ ሰው አይደለም፤ ወይም የአምላክነቱ ግብር እንጂ የሰውነቱ ግብር ቀርቷል ማለት ያስፈለገው ታዲያ ለምን ይሆን? ብለን መጠየቅ ይገባናል። የምናገኘው ምላሽም ከሁለቱ ውጪ እንደማይሆን እንገምታለን። የመጀመሪያው ‘ክርስቶስ አሁንም መካከለኛ ነው ካልን የሰውነቱን ግብር መግለጻችን ነውና እርሱን ዝቅ ማድረግ ይሆናል’ ከሚል ሥጋት ነው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ፣ ‘ክርስቶስን አሁንም መካከለኛ ካደረግነው እኛ መካከለኛ ያደረግናቸው ቅዱሳን ምን ሊሆኑ ነው?’ የሚል ይመስላል።

Sunday, May 8, 2016

የፊልም አክተር እንጂ ክርስቶስ አይደለም!!


 በኢትዮጵያ ውስጥ ግን አብዛኞቻችን "የኢየሱስ ክርስቶስ" የመሰለንን ፎቶ በየቤታችን ግድግዳ ለጣጥፈናል። ምንም እንኳን በመለጠፉ ረገድ ኦርቶዶክሳዊያን ቢያይሉም፥ ካቶሊኩም፣ ጴንጠውም፣ ሞርሞኑም፣ ጂሆባውም፣ አድቨንቲስቱም በቃ ሁሉም ለማለት በሚያስደፍረኝ መልኩ በቤቱ ግድግዳ ላይ ወይም የሆነ የሆነ ነገሩ ላይ ለጥፏል። ለምሳሌ በስቲከር መልክ መኪናው ውስጥ፤ ባጃጅ ውስጥ፤ ላፕቶፕ ላይ፤ የሞባይል ስልኩ ላይ እና በመሳሰሉት ላይ ለጥፏል። በነዚህ ሁሉ ባይለጥፍ ደግሞ በየዓመቱ የትንሣኤ በዓልን በማስመልከት የፌስቡክ ግድግዳው ላይ መለጠፉን አይተውም። ከፎቶውም ግርጌ ከሚጻፉ ጽሑፎች መካከል "ያዳነኝ ይኼ ነው፤ የሞተልኝ ውዴ ይኼ ነው፤ የሕይወቴ ትርጉም ይኼ ነው.. ይኼ ነው.. ይኼ ነው" የሚል ይበዛበታል።

   ለመሆኑ ይኽ የሚለጠፈው ፎቶ አንዳንዶች እንደሚሉት ለሰው ልጆች ኃጢአት የሞተው የኢየሱስ ክርስቶስ ፎቶ ነው? እውነታው ግን አይደለም! የኢየሱስ ክርስቶስ ሳይሆን የጂም ካቪዘል መሆኑ መታወቅ አለበት። በመሠረቱ ወንጌልን ለማስረዳትና ለማስተማር ኢየሱስ ክርስቶስን የሚመስል ሰው ማዘጋጀት ነፍሴ ከማትቀበለው ድርጊት መካከል አንዱ ነው። ምክንያቱም እምነት በጆሮህ ሰምተህ፣ በልብህ አምነህ የምትቀበለው እንጂ በሚመስል ነገር ማረጋገጫ ወይም የበለጠ ስዕላዊ ማሳመኛ ሲቀርብልህ “ለካ እንደዚህ ነው?” ብለህ ተደንቀህ፣ የምትቀበለው የማስታወቂያ ውጤት አይደለም። ፊልም ሠሪዎች ገበያቸው ስለሆነ ግድ ላይሰጣቸው ይችላል። ለኔ ለአማኙ የኢየሱስ አዳኝነት በወንጌል ቃል እንደተጻፈው እውነት መሆኑን አምኜ እቀበለዋለሁ እንጂ በጭራሽ እርሱን ሊወክል በማይችል ሰው ትወና ሳለቅስና አንጀቴን ሲበላኝ የማረጋግጠው የፊልም ጥበብ ለውጥ አይደለሁም። ለዚያ ስዕልና ምስል መንበርከክም አይገባንም የምንለው።

ኢየሱስ ምን መልክ አለው? ደም ግባት የሌለው ሆኖልናል ወይስ የአገልጋይና የባርያን መልክ? የውበቱ ነፀብራቅ የሚያበራ ውብ ነው? ወይስ የሕማም ሰው? እኮ የትኛውን ይመስላል። ደቡባዊ አፍሪካውያን ኢየሱስን ጥቁር አድርገው ይስላሉ። ኢትዮጵያውያንም በሚችሉት አቅም የመሰላቸውን ለመሳል ሞክረዋል። በኢየሱስ ላይ ተሳልቆና ፀያፍ ስድብ የጻፈው ሊኦናርዶ ዳቬንቺ ባቅሙ በምሴተ ሐሙስን የነበረውን ሁኔታ ለማስቀመጥ የሞከረበትን ስዕል በየቤታችንና ቤተመቅደሱ ሰቅለናል። ዳቬንቺ በኢየሱስ ላይ የተናገረው ምንድነው? “The Davenci Code” ያነበበ ሰው ከክፉ ሥራው ተባባሪ ሆኖ ዳቬንቺ የሳለውን ስዕል ይቀበል ነበር?




   አንዳንዴ ሀበሻ እያየ ለምን እንደሚታወር፤ እየሰማ ለምን እንደሚደነቁር ግራ ይገባኛል። ይህንን ሰውየ "ዘ ፓሽን ኦፍ ክራይስት" በሚባል ፊልም ላይ ስንመለከተው ኖረናል። በዕድሜአችን በሰል ስንል ግን፥ አንድ ተራ አሜሪካዊ ፊልም ሰሪ መሆኑን አለመገንዘባችን እጅግ ያሳዝናል!! በተለይ ደግሞ በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ ዛሬም ድረስ ሰውየው የኢየሱስ ክርስቶስን ቦታ ወስዶ ስዕሉ በየቤቱ በየቤተ መቅደሱ ሰቅሎ ሲሰገድለት፣ ሲሳለመውና ሲስመው ይገኛል። የተለያየ የሃይማኖት ሥርዓቶች በሚከወንባቸው አድባራት በትልቁ ተስሎ መገኘቱም እጅግ አሳዛኝ ነው። ምክንያቱም ለእግዚአብሔር እንጂ ለፊልም ባለ ሙያ ወይም ለሰዓሊ ሙያ ስገድ የሚል ቃል መጽሐፍ ቅዱስ የለም። ነገር ግን በኢየሱስ ሽፋን የሰው ስዕል እየተመለከ ይገኛል።
    እናም ይኽ አብዛኞቹ ሃይማኖተኞች የሚሰግዱለት ግለሰብ "ዘ ፓሽን ኦፍ ክራይስት" በተሰኘ ፊልም ላይ የኢየሱስ ክርስቶስን ገጸ ባህሪ በመላበስ የተወነ አሜሪካዊ የፊልም አክተር ሲሆን፤ ስሙም ጂም ካቪዘል (Jim caviezel) ይባላል። ወይም ደግሞ በሙሉ መጠሪያው ጃምስ ፓትሪክ ካቪዘል ነው። ሃይማኖቱ ደግሞ የሮማ ካቶሊክ ተከታይ ነው። ተወልዶ ያደገው በአሜሪካ ዋሽንግተን ስቴት ውስጥ ሲሆን ወደ ፊልሙ ኢንዱስትሪ ከመግባቱ አስቀድሞ፥ የተማረባቸውን ትምህርት ቤቶች በመወከል የቅርጫት ኳስ ይጫወት ነበር። በዃላ ግን እግሩ ላይ ጉዳት ስለደረሰበት ሙሉ በሙሉ የቅርጫት ኳስ መጫወቱን ትቶ የፊልም አክተር በመሆን እ.አ.አ በ1991 የመጀመሪያ ፊልሙ ላይ በጥሩ ትወና ተሳትፏል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ "ዘ ፓሽን ኦፍ ክራይስት" የተሰኘውን ፊልም ጨምሮ ከሠላሳ በሚበልጡ ፊልሞች ላይ ተውኗል (በመሪነት፣በረዳትነት እና..) የተወሰኑ ፊልሞቹን ርዕሳቸውን እና የተሰሩበትን ዓመት እንደሚከተለው መጥቀስ ይቻላል…

My own private idaho – 1991
Diggstown – 1992
Wyatt erap – 1994
Ed – 1996
The rock – 1996
G.j. jane – 1997
The thin red line – 1998
Ride with the devil – 1999
Pay it forward - 2000
Frequency – 2000
Madison - 2000
Angel)
Person of interest- series drama (up to 2011) እና ሌሎችን ፊልሞች ሰርቷል።

   እንግዲህ እውነቱ ይኽ ነው። "ዘ ፓሽን ኦፍ ክራይስት" የተሰኘው ፊልም ዳይሬክተር የሆነው ሚል ጊብሰን፥ ይህን ግለሰብ የኢየሱስ ክርስቶስን ገጸ ባህሪ ተላብሶ እንዲጫወት ያደረገበት ምክንያት፥ ሰውየው ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሆነ ወይም ደግሞ በመልክ ኢየሱስ ክርስቶስን ስለሚመስለው ሳይሆን፥ አስቀድሞ በሰራቸው ፊልሞች በተለይም "The thin red line" እና "Frequency" በተባሉ ፊልሞች ላይ ባሳየው ጥልቅ የትወና ጥበብ ነው። እውነቱ እንዲህ ሆኖ ሳለ፥ ያገሬ ህዝብ ግን አምላክ አድርጎት ይሰግድለታል። ….እግዚኦ..!!

    በርግጥ በኦርቶዶክስ ሃይማኖት አስተምህሮ መሰረት በየአድባራቱ ብዙ ታሪክ ያዘሉ ቅርጻ ቅርጾች እና ሥዕሎች እንዳሉ ይነገራል.. ይህንንም አስመልክቶ ዲ/ን ዳንኤል ክብረት SUNDAY, APRIL 25, 2010 "የቤተክርስቲያን ሥዕሎች ታሪካዊ ፋይዳ" በሚል ርዕስ በጻፈው ጽሁፉ እንዲህ ብሎ ነበር፦

"…የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የሀገሪቱን (የኢትዮጵያን) ባሕል እና ታሪክ ለትውልድ ካቆየችባቸው መንገዶች አንዱ ሥዕሎቿ ናቸው፡፡ በዚያ ፎቶግራፍ እና ፊልም ባልነበረበት ዘመን የነበረውን ባሕል፣ሥርዓት እና ታሪካዊ ሁነቶች የምናገኘው በቤተ
ክርስቲያን መጻሕፍት እና ግድግዳ ላይ በሚገኙ ሥዕሎች ነው፡፡ ለምሳሌ በሆሎታ ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን ግድግዳ ላይ የሚገኙት እና ከ100 ዓመታት በላይ ያስቆጠሩት ሥዕላት ለዚህ ምስክር ናቸው፡፡ ከአዲስአበባ 44 ኪሎሜትር በሆሎታ ከተማ የምትገኘው ይህች ቤተክርስቲያን በዐፄ ምኒሊክ አማካኝነት በ1895 ዓ.ም የተገነባች ሲሆን ታቦቷ የገባችው በዚሁ ዓመት የካቲት 16 ቀን ነው፡፡ ሥዕሉን የሳሉት አለቃ ሐዲስ መሆናቸውን ከመቅደሱ ምሥራቃዊ ግድግዳ ላይ ከሣሉት ሥዕል ላይ «ለዛቲ ሥዕል እንተ ሰዓላ አለቃ ሐዲስ እምቤተ ሌዊ፣ ወዘተምህረ በጎንደር» በሚለው ማስታወሻቸው ይታወቃል፡፡
  ሰዓሊው የቤተክህነቱን እና የቤተመንግሥቱን ወግ እና ሥርዓት በሚገባ የሚያውቁ መሆናቸው በአሣሣላቸው ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ ወለተ ሄሮድያዳን ሲሥሏት አለባበሷን እና የፀጉር አቆራረጧን ኢትዮጵያዊ አድርገውታል፡፡ ሹሩባ ተሠርታለች፣ነጭ ሻሽ አሥራለች፣ አሸንክታብ ሠትራ እስክስታውን ታስነካዋለች፡፡ የሄሮድስን የቤተ መንግሥት ሥርዓት ሲስሉት በምኒሊክ ቤተመንግሥት ሥርዓት ነው። ቢላዋው፣የእንጀራው አጣጣል፣ ሙዳ ሥጋው የዘመኑን የግብር ሥርዓት በሚገባ ነው የሚያሳየው፡፡"
   አንባቢ ሆይ ልብ በል፥ እንደ ዳንኤል ክብረት ገለጻ ከሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውሰጥ የምናውቃት ሄሮድያዳ ኢትዮጵያዊ መስላ ስትሳል ምናልባት ሰዓሊው በነበረበት ዘመን የኢትዮጵያ ሴቶች ምን እንደሚመስሉ ሊገልጽ ይችል ይሆናል። ነገር ግን የመጽሐፍ ቅዱሷ ሄሮድያዳን እና የመጽሐፍ ቅዱሱን ታሪክ ያበላሸዋል። ሲቀጥል ደግሞ የምኒልክን ቤተ መንግሥት ለማሳየት የሄሮድስን ቤተ መንግሥት ማረሳሳት ተገቢ አይሆንም። እንግዲህ በየአድባራቱ ታሪክ አዝለዋል የሚባሉ ሥዕሎች ሁሉም እንደዚህ ዓይነት ከሆኑ መሆናቸው ለማወቅ ፈላስፋ ወይም የነገረ መለኮት ምሁር መሆንን አይጠይቅም። በአንድ ዘመን የተከናወነውን መንፈሳዊ ድርጊት ለማስታወስ ወይም ሃሳባዊ እይታን ለማሳየት ተብሎ የሚሳለው ስዕል የእውነታው ነፀብራቅ እንደሆነ አድርጎ በመሳል ለስዕሉ መስገድ፣ መንበርከክና መማፀን ኢክርስቲያናዊ አምልኮ ነው። ያሳፍራል.። ያሳዝናልም!!
ሲጠቃለል ስዕል ለአንክሮ፣ ለተዘክሮና ለማስተማሪያነት ከሚያገለግል በስተቀር በየቤተ መቅደሱ ተሰቅሎ አይታጠንም፣ አይሰገድለትም። መንበርከክና ከፊት አቁሞ መማፀን የወንጌል አስተምህሮ አይደለም። አንዳንዶች ለጥፋታቸው መሸፈኛ “የኪሩብ ምስል በታቦቱ ላይ ነበር” ይላሉ። የኪሩቡን ምስል ማን አዘዘ? ከምን ይቀረፅ፣ ስንትስ ነበረ? ለማን በተሰጠ ኪዳን ላይ ታዘዘ? በቂ መልስ የላቸውም። የዛሬውን ከእግዚአብሔር ትእዛዝ ጋር ለማገናኘት መሞከር ሰማይና ምድር ለማጣበቅ እንደመሞከር ይቆጠራል። እግዚአብሔር አእምሮውን ለብዎውን ያሳድርብን።

   

Friday, April 29, 2016

«በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር…»!

የራስ ቅል ኮረብታ በ19ኛው ክ/ዘመን 

የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ፥ በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው?» ገላ 3፤1
ኢየሱስ ክርስቶስ በየዓመቱ የሚከበርለትን የመታሰቢያ ትንሣኤ ሊመሠርት እንዳልመጣ እሙን ነው። የከበረ እንጂ የሚከብር፤ የሚፈጸም እንጂ የሚታሰብ ትንሣኤ ትቶልን አልሄደም። እንደዚያማ ከሆነ ከሕግ አገልግሎት ገና አልወጣንም ማለት ነው። ለዚህም ነው ሐዋርያው ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች እንደዚህ ያላቸው።

 «የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ፥ በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው?»ብሎ ይጠይቃቸዋል።
 እውነት ነው፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ዕለት፤ ዕለት በዓይናችን ፊት እንደተሰቀለ ሆኖ የሚታይ እንጂ በማስታወሻ መልክ በየዓመቱ «ዬ፤ዬ፤ዬ» እያልን የምናስበው የአንድ ሳምንት አጀንዳ አይደለም። የኦሪት ሕግ በዓላት በተወሰነላቸው ቀናት በየዓመቱ ይከበራሉ። ከዚያን ቀን ውጪ የሕጉ በዓላት በሰው ሕይወት ላይ የተደነገገላቸውን ኃይል ሊፈጽሙ ሥልጣን የላቸውም። አይሁድ ፋሲካቸውን  ከግብጽ ምድር የወጡበትን ዕለት በማሰብ በየዓመቱ ለአንድ ሳምንት በወርኀ ሚያዚያ ያከብራሉ። ያልቦካና እርሾ ያልገባበትን ኅብስት የሚመገቡት በፋሲካ ሳምንት ብቻ ነው። ከዚያ በኋላ የፋሲካው የሕግ ሥልጣን ስለሚያበቃ ወደቀደመው አመጋገብና መደበኛ ኑሮ ይመለሳሉ። የክርስቲያኖች ፋሲካ ግን በአማኞች ሕይወት ላይ ያለምንም የብልጫ ቀናት ልዩነት በእምነት የሚፈጸምና ዓመቱን ሙሉ ኃይልና ሥልጣን ያለው አገልግሎት ነው። እንደገላትያ ክርስቲያኖች ወደ ሕግ ሥርዓት ተመልሰን በዓመት የምናስበውና የምንዘክረው እንዲሁም ከጥሉላት በስተቀር ሌላውን ገድፈንና የገደፍነውን መልሰን የምንረከብበት፣ እስከሆድ ድረስ የምግብ ዓይነት ነጻነታችንን የምናስከብርበት ዘመቻ ምግብ ፋሲካ አልተሰጠንም።  ፋሲካችን «እንኳን አደረሰህና እንኳን አደረሰሽ» በመባባል ያልደረስንበት የድነት ቀን ያለ ይመስል የሚታወስ የአንድ ሳምንት የስጦታ ካርድ መለዋወጫ በዓል በላይ የላቀ ሰማያዊ ነው።
ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው: «በመንፈስ ብትመሩ ግን ከሕግ በታች አይደላችሁም። የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው እርሱም ዝሙት፥ ርኵሰት፥ መዳራት፥ ጣዖትን ማምለክ፥ ምዋርት፥ ጥል፥ ክርክር፥ ቅንዓት፥ ቁጣ፥ አድመኛነት፥ መለያየት፥ መናፍቅነት፤ ምቀኝነት፥ መግደል፥ ስካር፥ ዘፋኝነት፥ ይህንም የሚመስል ነው። አስቀድሜም እንዳልሁ፥ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም"

«ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶአል» ስንል እነዚህን የሥጋ ሥራዎች ሁሉ ከሕይወታችን አስወግደን በመንፈሱ ሥልጣን እየተመራን ነው ማለታችን ነው። እነዚህን ደግሞ የምናስወግደው በየዓመቱ በሚከበር ፋሲካ ሳይሆን ዕለት፤ ዕለት የኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ በፊታችን ተስሎ ሲገኝ ብቻ ነው። አለበለዚያ ከገላትያ ሰዎች የበዓል አከባበር አስተሳሰብ ገና አልወጣንም ማለት ነው። የገላትያ ሰዎች «አባ፤ አባት» ብሎ ለመጣራት የሚያበቃ የተሰጣቸውን የልጅነት ሥልጣን ትተው በባርነት ቀንበር ሥር ወደምትጥል ወደወር፤ ቀንና ዘመንን የማክበር ቁልቁለት ወርደው በተገኙ ጊዜ የተናገራቸው ቃል በዚህ ዘመንም ቦታ አግኝቶ መታየቱ ምን ዓይነት አዚም ቢወድቅብን የሚያሰኝ ነው።

«ቀንንና ወርን ዘመንንም ዓመትንም በጥንቃቄ ትጠብቃላችሁ። ምናልባት በከንቱ ለእናንተ ደክሜአለሁ ብዬ እፈራችኋለሁ» ገላ 4፤ 1-11

ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን ፍለጋ የት መሄድ ይገባናል? የእግዚአብሔር መገኛው የት ይሆን? ከምድራዊት ቤተ መቅደስ? ከገሪዛን፤ ከጌባል? ወይስ በኢየሩሳሌም?
 አንዳንዶች ኢየሩሳሌምን የተሳለመ የ40 ቀን ሕጻን ይሆናል ይላሉ። የቆረበ ደግሞ የበለጠ የ40 ቀን ሕጻን እንደሚሆንም ይሰበካል። ከተሳለመ የ40 ቀን ሕጻን በመሆንና ከቆረበ የ40 ቀን ሕጻን በመሆን መካከል ያለው ልዩነት አይገባኝም።  ኢትዮጵያ በመቁረብና ኢየሩሳሌም ከጎልጎታ ሄዶ በመቁረብ መካከልስ ያለው ልዩነት ምንድነው?  ሰዎች ክርስትናን እንደሕግ ሥርዓት ማክበር ሲጀምሩ የሕግ የብልጫ ልዩነት ክርስትናውን መውረስ ይጀምረዋል። ኢየሩሳሌም ሄዶ በመሳለም ወይም በመቁረብና ኢትዮጵያ በመቁረብ መካከል ልዩነት የሚመጣውም ለዚህ ነው። መቱ ባለች ቤተ ክርስቲያን ጓሮ በመቀበርና ደብረ ሊባኖስ በመቀበር መካከል ያለው የመብት ልዩነትም ውጤቱ የሕግ ተፋልሶ ክርስትናውን በመዋጡ የመጣ ነው። የወንጌል እውነት ግን ያንን እንድል አይነግረንም። እግዚአብሔር መንፈስ እንጂ በቦታና በሥፍራ የሚወሰን አምላክ አይደለም። ስለዚህም እግዚአብሔር በመንፈስ ይመለካል፤ በእምነትም፤ የመንፈስ  የሆነ ሥራ በሕይወታችን ላይ ሊገለጥ ይገባዋል። ያኔ ዲላ ሚካኤል ተቀበርን፤ ደብረ ሊባኖስ፤ ደሴ ቆረብን ሞቻ በማንነታችን ላይ ለውጥ የለውም። በሕይወቱ የክርስትና ማንነት የሌለው ሰው ደብረ ሊባኖስ ጓሮ መቀበሩ በፍርድ ወንበር ፊት ለውጥ አያመጣለትም። ሰው ሲሞት ይዞት የሚሄደው በምድር የነበረውን ሥራ እንጂ በሰማይ የሚፈጸም የክርክር ዳኝነት የለም። «እስመ አንተ ትፈድዮ ለኩሉ በከመ ምግባሩ» እንዳለ ዳዊት በመዝሙር 62፤12
ስለዚህ እግዚአብሔር በመንፈስ ይመለካል፤ በመንፈስ ይሰገድለታል፤ በመንፈስ ይታመናል እንጂ በቦታና በሥፍራ አይደለም። እሱን ይይዝ ዘንድ የሚችል ምድራዊ መቅደስ የለንም። «ለእኔ ምን ዓይነት ቤት ትሠራላችሁ? ይላል ጌታ» የሐዋ 7፤50

«ወትቤሎ፤ አበዊነሰ በዝንቱ ደብር ሰገዱ፤ ወአንትሙሰ ትብሉ ከመ በኢየሩሳሌም መካን ውእቱ ኀበ ይሰግዱ። ወይቤላ ኢየሱስ፤ እመንኒ ብእሲቶ ከመ ትመጽእ ሰዓት አመ ኢበዝንቱ ደብር፤ ወኢበኢየሩሳሌም ዘይሰግዱ ለአብ፤ አንትሙሰ ትሰግዱ ለዘኢታአምሩ፤ ወንሕንሰ ንሰግድ ለዘናአምር፤ እስመ መድኃኒት እምነ አይሁድ ውእቱ። ወባሕቱ ትመጽእ ሰዓት፤ ወይእዜ ይእቲ፤ እመ እለ በርቱዕ በአማን ሰጋድያን፤ ይሰግዱ ለአብ በመንፈስ ወበጽድቅ እስመ አብኒ ዘከመዝ የኀሥሥ እለ ይሰግዱ ሎቱ። እስመ እግዚአብሔር መንፈስ ውእቱ፤ እለሂ ይሰግዱ ሎቱ በመንፈስ ወበጽድቅ ሀለዎሙ ይሰግዱ ሎቱ»

ትርጉም፤ 
«አባቶቻችን በዚህ ተራራ ሰገዱ፤ እናንተም፦ ሰው ሊሰግድበት የሚገባው ስፍራ በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ አለችው። ኢየሱስም እንዲህ አላት፦ አንቺ ሴት፥ እመኚኝ፥ በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል። እናንተስ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፤ እኛ መዳን ከአይሁድ ነውና ለምናውቀው እንሰግዳለን። ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፤ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና፤ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል» ዮሐ 4፤20-24

የኢየሱስ ስቅለት የሚታሰበው በመንፈስ መሆኑን ለማመልከት ጳውሎስ ለገላትያ  ሰዎች እንዲህ አላቸው። ኢየሱስ የተሰቀለው ኢየሩሳሌም እንጂ ገላትያ አለመሆኑን እያወቀ ለገላትያ ሰዎች ግን «በዓይናችሁ ፊት እንደተሰቀለ ሆኖ ተስሎ ነበር» እያለ ይወቅሳቸዋል። ምክንያቱም ስቅለቱ በአማኞች ፊት የሚታየው በየዓመቱ ለሁለት ወር በሚደረግ ጾምና ለአንድ ሳምንት በሚታሰብ  የሕማማት ሳምንት ሳይሆን በየትኛውም ቦታ ብንሆን ያለምንም ዕረፍት በዘመናችን ሙሉ ነውና።
 የሕማማቱ ሳምንት ካለፈ በኋላስ? በዓለ ፍስሐ ወሀሴት፤ በዓለ ድግስ ወግብዣ፤ በዓለ ምግብ ወመጠጥ ነው? የኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ ለሁለት ወር ከምግብ የመከልከል ማዕቀብና ለሁለት ወር ተከልክለው የነበሩ ምግቦች በተራቸው ድል የሚቀዳጁበት በዓል አይደለም። ዓመቱን ሙሉ በፊታችን እንደተሰቀለ ሆኖ የምናስብበት፤ በመንፈስና በእውነት የምንሰግድለት ቋሚ የሕይወታችን መርህ እንጂ በአርብ ቀን የወይራ ጥብጣብ የሚያበቃ ዓመታዊ ልምምድ ካደረግነው ከገላትያ ሰዎች በምን እንሻላለን? 

ለዚህም ነው፤ ብዙ ክርስቲያኖች ከነገሠባቸው የሥጋ ሥራ ሳይላቀቁ ፋሲካን እያከበሩ ዘመናቸውን ሁሉ የሚፈጽሙት። ጋብ ብሎ የነበረው የሥጋ ሥራ ከፋሲካ በዓል በኋላ ይደራል። ዝሙቱ፤ ውሸቱ፤ ስርቆቱ፤ ማጭበርበሩ፤ ሃሜትና ነቀፋው ያለማንነት ለውጥ እንደነበረው ይቀጥላል። ዓመቱን ሙሉ ያጠራቅሙትን ኃጢአት የፋሲካ ጾም ሲመጣ ለማራገፍ እንደሚቻልበት አመቺ ጊዜ ጠብቀው ብዙ ሰዎች ጥሬና ቆሎ ቋጥረው በየዋሻውና ፍርክታው ልክ እንደሽኮኮ ይመሽጋሉ። ሀብት ያላቸው ኢየሩሳሌም ሄደው ለመሳምና ለመቁረብ ገንዘባቸውን በየዓመቱ ይከሰክሳሉ። የክፉ ቃል ምንጭ የሆነውን አንደበቱን ሳይዘጋ ሥጋ መሸጫ ቤቱን የሚዘጋ የት የለሌ ነው። ከተማውን ሁሉ የወረረው የሚዛን መሥፈሪያ በፈሪሃ እግዚአብሔርና ያለማጭበርበር ሳይሰሩበት ጾም የሚሉትን ፈሊጥ የሚጠብቁት ለምንድነው?   አቤት! የዘንድሮ ሚዛን የሚባለው የድሮና የዚህ ዘመን ሚዛን ልኬታ የተለየ ሆኖ ይሆን?

የሕዝብና የመንግሥት ሀብት የሚዘርፉ የሕግ ፋሲከኞች ቁጥራቸው ብዙ ነው። የቤተ ክርስቲያን ደወል ሲደወል የሚከንፉ ነገር ግን የቤታቸውን የፍቅርና የሰላም ደወል የተነጠቁ ቤቱ ይቁጥራቸው። ሠራተኞቻቸውን የሚያስጨንቁ፤ በፍትህ አደባባይ ፍርድን የሚጨፈልቁ፤ በመማለጃም የእንባን ዋንጫ የሚጎነጩ የሁለት ወር ጸዋሚዎችና ተሃ ራሚዎች አያሌ ናቸው። የልምድ ክርስቲያኖች የሕይወት ምስክርነት በሥራቸው ሊታይባቸው አይችልም።  ስለዚህም ይመስለኛል፤ በክርስቲያን ቁጥር ብዙ ሆነን በበረከት መትረፍረፍ አቅቶን እድሜ ልካችንን ከእምነት የለሾች ምጽዋት ጠባቂ ሆነን የቀረነው። እንደእምነት የለሾቹ፤ እምነት የለሾች ብንሆን ያለእምነት ስለሚፈረድብን በሥጋ ረሃብ ባልተገፋንም ነበር። እግዚአብሔርን እየጠራን፤ እንደፈቃዱ ለመኖር ባለመቻላችን በራሳችን የእምነት ጉድለት በሥጋችን እንቀጣለን።  ብዙ ባወቅህ ቁጥር ብዙ ሥራ ይጠበቅብሃል። ካልሰራኸው ግን ባታውቅ ቢቀርብህ ይሻልህ ነበር። ስለዚህ ማወቅህ ለመዳንህ ዋስትና የሆነውን ነገር ካላትርፈረፈልህ ክርስትናህ ምንድነው? ኢየሱስ በባዶ ተስፋ አልተወንም። እኛ ግን አስሮ በያዘን በገላትያውያን አዚም ፈዘን ሳለ ስለገላትያ አዚም እናስተምራለን።

  የኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለትና ትንሣኤ በየዓመቱ እየዞረ የሚመጣ በዓል ሳይሆን ዕለት፤ ዕለት በፊታችን ተስሎ የሚታየን የሕይወታችን አካል ነው መሆን ያለበት። በቦታ፤ በሥፍራና በጉዞ ብዛት የሚከበር ሳይሆን በእውነትና በመንፈስ እንድናመልከው የተደረገልን የማዳን ሥራ ነው። በአዲስ ሰውነት ለውጥ እንጂ በሕግ ሥነ ሥርዓት ልናሳልፈው አይገባም።  ሰላምና እርጋታ በውስጡ መኖሩን መንፈስ ቅዱስ የሚመሰክርለት አማኝ ሀገር ለሀገር፤ ተራራ ለተራራ ትንሣኤውን ፍለጋ ሲዞር አይገኝም። ምክንያቱም፤ ሁል ጊዜ በዓይኑ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ይታየዋልና»! ከተያዝንበት አዚም ተላቀን በልባችን የተሳለውን ትንሣኤ፤ በኑሮአችን ፍሬ የሚታይበት እንዲሆን እግዚአብሔር ይርዳን! አሜን።