Monday, June 30, 2014

በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሊቀጳጳስ በብፁዕ አቡነ ዳንኤል ላይ የገዳሙ መነኮሳት አድመው በረሃብ እየቀጧቸው መሆኑ ተሰማ!



( ምንጭ፤ አባ ሰላማ ድረ ገጽ)



በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ በሆኑት በብፁዕ አቡነ ዳንኤል ላይ አባ ገብረ ወልድ በተባሉ መነኩሴ አሳዳሚነት ሊቀጳጳሱ ላይ ልዩ ልዩ የአድማ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸውንና ሊቀጳጳሱ ላይ አደጋዎች መደቀናቸውን ከስፍራው የደረሰን ዜና አመለከተ፡፡ ብፁዕነታቸው የሲኖዶስን ስብሰባ ለመካፈል ከመጡ ወዲህ ተመልሰው ቢመጡ አናስገባቸውም በሚል የተጀመረው አድማ ምግብ እንዳይቀርብላቸው፣ ሾፌራቸውም መኪናቸውን እንዳያንቀሳቅስ እስከ ማሳደም የደረሰ አሳዛኝ እርምጃ እየተወሰደባቸው መሆኑን ምንጮቻችን የገለጹ ሲሆን ይህም ድርጊት በአንዳንድ ክፉ ቀን ግብጻውያን መነኮሳት ኢትዮጵያውያን መነኮሳት በበሽታና በረሃብ እንዲያልቁ ለማድረግ በራቸውን ዘግተውባቸው እርዳታ ሳያገኙ እንዲሞቱና ገዳማቶቻችን ያለ ሰው እንዲቀሩ ለማድረግ ከሚጠቀሙባቸው በጭካኔ የተሞሉ ስልቶች ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ ከዚህ እርምጃ በስተጀርባ የማን እጅ እንዳለ ለጊዜው የታወቀ ነገር ግን የለም፡፡


ብፁዕ አቡነ ዳንኤል የስኳር በሽተኛ ከመሆናቸው አንጻር በረሃብ እንዲቀጡ አድማ መመታቱ እጅግ አሳዛኝ ተግባር መሆኑ እየተነገረ ሲሆን፣ በብፁዕነታቸው በኩል እስካሁን ነገሩን በትዕግስት ማሳለፋቸው የቤተክርስቲያን ስም በዚህ መንገድ እንዳይነሣ ከማሰብ እንደሆነ የተናገሩት ምንጮች፣ ብፁዕነታቸው የዲፕሎማት ፓስፖርት ያላቸውና እንደዲፕሎማት ስለሚታዩ ለሚመለከተው አካል አቤት ቢሉ ይህን ባደረጉት መነኮሳት ላይ ሕጋዊ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል ስለጉዳዩ የሚያውቁ ይናገራሉ፡፡
በአባ ገብረወልድ የተመራው የአድማ ማኅበር እንዲህ ለማድረግ ያነሳሳው ምን እንደሆነ እስካሁን የታወቀ ነገር ባይኖርም ብፁዕነታቸው የኢየሩሳሌም ሊቀጳጳስ ሆነው ከተሾሙ በኋላ በዚህ ወቅት ሊሆን የማይችለውን በጎልጎታ ምዕራፍ ስምንት የተባለውን ቦታ ለቤተክርስቲያናችን በመግዛት ትልቅ ስራ መስራታቸው ይነገራል፡፡ የመነኮሳቱ ቅናትና አድማ የተነሳው ከዚህ መልካም ስራ ሳይሆን እንደማይቀር አንዳንዶች ይገምታሉ፡፡ የመነኮሳቱ ማኅበርም አይዟችሁ ያላቸው አካል ሳይኖር አይቀርም የሚል ግምት አለ፡፡

Sunday, June 29, 2014

ተአምረ ማርያም የተባለው መጽሐፍ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን እናት የቅ/ማርያምን የቅድስና ባህርይ አይወክልም!


(እዝራ ስነ ጽሁፍ፤ ዘላለም መንግሥቱ)

ክፍል አራት

አንዳንድ  ሰዎች  ማርያምን  እንደሚያከብሩ  እንጂ  እንደማያመልኩ  የሚናገሩት  የቃል  ጨዋታ  ነው።  መጽሐፍ  ቅዱስን  እየጠሉ  ራዕየ ማርያምን  በቃል  እየሸመደዱ  “እንወዳታለን  እንጂ፥  እናከብራታለን፥  የጸጋ ስግደት  እናቀርብላታለን  እንጂ  . . .  አናመልካትም”  ማለት  የራስ  ድለላ ነው።  እንዲህ  ከላይ  እንደጠቀስኳቸው  ያሉቱ  ምዕራፎች  የሚናገሩት  እየተከበረች  ሳይሆን  እግዚአብሔርን  ተክታ  እየተመለከች  መሆኗን  ነው። ደግሞ  ማክበርስ  ከሆነ  መከበር  የሚገባው  ማን  ብቻ  ነው?  ይህ  እኮ አንድን  ባለሙያ  ሰው  ለማድነቅና  ለማመስገን  ከስዕሎቹ   ወይም  ከቅርጾቹ  አንዱ  ፊት  ሄጄ  ለሥራው  ውጤት  ምስጋናና  ውዳሴን  ብደረድር እንደማለት  ነው።  ይህ  እንዲህ  በሚለው  በሮሜ  1፥25  ቃል  ፈጽሞ  የተወገዘ  ነው፤  ይህም  የእግዚአብሔርን  እውነት  በውሸት  ስለ ለወጡ በፈጣሪም  ፈንታ  የተፈጠረውን  ስላመለኩና  ስላገለገሉ  ነው፤  እርሱም ለዘላለም  የተባረከ  ነው፤  አሜን።  ማክበር  ወይም  ማምለክ  የቃል  ጉዳይ አይደለም።  መስተዋል  ያለበት  ተግባሩና  ድርጊቱ  ነው።  ለእግዚአብሔር ብቻ  እንጂ  ለሌላ  ለማንም  መደረግ  የሌለበትን  ነገር  ለሌላ  ማድረግ፤ ለምሳሌ፥  ጸሎትንና  ልመናን፥  ውዳሴና  ስግደትን  ማቅረብ  ማምለክ  እንጂ ሌላ  አይደለም። በአፌ  አላመልካትም  ብል  እና  ውዳሴና  ልመናን ስዕለትንና  ስግደትን  ባቀርብላት  ራሴን  እየደለልኩ  ነኝ።  ወይም  በእርሷ መጋረጃ  ውስጥ  እየተደበቅሁ  ከእውነት  እየሸሸሁ  ነኝ።  ራእ.  4፥10-11፤ 15፥3-4፤  ነህ.  9፥6  ሁሉ  ሊሰግዱለት፥  ሊያከብሩት፥  ሊያመልኩት፥ ሊወድሱት፥  ሊያመሰግኑት  የተገባ  ብቻውን  የሆነ  አምላክ  እግዚአብሔር  ብቻ  መሆኑን  ከሚነግሩኝ  ጥቅሶች  ጥቂቱ  ናቸው።

4.  የተፈናቀለ  ታሪክ።

 በተአምረ  ማርያም  ውስጥ  ታሪክ  የሚያውቃቸው፥  በታሪክ  ውስጥ  ስማቸው  የተጠቀሰና  ዘጋቢዎች  ያወሷቸው፥  ራሳቸውም ታሪካቸውን  የጻፉ  በንጽጽር  እውነቱን  ማረጋገጥ  የሚቻልባቸው  ሦስት ሰዎች  ተጠቅሰዋል።  መጽሐፉ  እነዚህን  የመሰሉ  ታሪካዊ  ገጸ  ባህርያትን  የከተተው  እና  አንድ  ሁለት  ምዕራፎች  ውስጥ  ዓመተ  ምሕረቶችን  ያስገባው  ታሪካዊ  ስርና  መሠረት  ያለው  ለመምሰል  ይህናል  ብዬ እገምታለሁ።  ይህ  መጽሐፍ  እነዚህን  ሰዎች  ሊጠቅሳቸው  ከደፈረ  እኔም ከታሪክ  አንጻር  ልጥቀሳቸው።  እነዚህ  ሰዎች  ንጉሥ  ማርቆስ፥  ዮሐንስ  አፈወርቅ፥  እና ዮስጢን  ሰማዕት ናቸው። ኋላ ላይ  ጥጦስም  ወንበዴ ሆኖ ተጠቅሶአል። ግን ይህ ጥጦስ ኋላ ኢየሩሳሌምን  ያወደመው  ይሁን  ወይም ሌላ  ቀጣይ  ታሪኩ  በዚህኛው  ተአምረ  ማርያም  ውስጥ  አልተነገረም።
ሦስቱን ግን እንመልከት።

ሀ.  ዮሐንስ  አፈወርቅ። 

ታሪኩን  ከእንግሊዝኛ  መዛግብት  የምታውቁ  በተጨማሪ  ከሌላ  ምንጮች  ለመመርመር  ለምትሹ  ይህ  ሰው  እንግሊዝኛው  አጠራር  John  Chrysostom  የሚባለው  ነው።  የዮሐንስ  አፈወርቅ  ተአምረ  ማርያምኛ  ታሪክ  በምዕ.  48  ተጽፎአል።  ታሪኩ  በአጭሩ ምዕመናንን  ሥጋ  ወደሙን  ሲቀበሉ  አንዲት  ሴት  በመርገመ  ደሟ ሳለች  መጣች።  ሕዝቡም  የመንፈስ  ቅዱስ  ረድዔት  እንደራቃት  አውቀው  ወደ  ንስጥሮስ  ፊት  አመጧት።  ጠይቆ  ከተረዳ  በኋላ  ራቁቷን  ተዘቅዝቃ  እንድትሰቀልና  ሕዝቡም  በኀፍረተ  ሥጋዋ  ጢቅ  እንዲሉ  አዘዘ።  እንደ ተአምረ  ማርያም  ጸሐፊ  ንስጥሮስ  ይህን  ያደረገው  እግዚአብሔር  እንዲህ  ከመሰለ  ቦታ  የሚወለድ  እንደሆነ  የሚያምን  የተረገመ  ነው  አሰኝቶ  ነው። ዮሐንስ  የሚባል  ቄስ፥  “እኔ  እግዚአብሔር  በሴት  ሥጋ  እንደተወለደ  አምናለሁ”  ብሎ  ኃፍረተ  ሥጋዋን  ባፉ  ሳመ።  በዚህ  ጊዜ  የማርያም  ስዕል በቤተ  መቅደስ  ውስጥ  ነበረችና፥  “አፈወርቅ”  ብላ  ጠራችው።  ቄሱ ዮሐንስ አፈወርቅ  የተባለው  እንዲህ ነው። ይህ  ምዕራፍ  የንስጥሮስን  ክፋት  ለመግለጥና  ማርያምን  ያለስፍራ ለማግነን  ተብሎ  ረጅም  ርቀት  የተሄደበት  ትረካ  ነው።  መርገመ  ሴትን  አርክሶ  ሥጋ  ወደሙን  ከከለከለ  ኀፍረተ  ሥጋን  ማየትና  በላዩ  መትፋት ዮሐንስን  ከማስመስገን  ይልቅ  የአድራጊዎችን  ሁሉ  ኅሊናን  አያረክስም?  ንስጥሮስ  ኋላ  በ431  በተደረገው  በኤፌሶኑ  ጉባኤ  እርሱም  ትምህርቱም የተወገዙበትን  ክርስቶስ  ሁለት  አካል  የሚል  ትምህርትን  ያስተማረ  ሰው ነው።  ለዚህ  ምላሽ  ሆኖ  ኋላም  በክርክር  የቆየ  የሁለት  ባህርይ (dyophysitism)  እና  አንድ  ባህርይ  (monophysitism)  ጉዳይ ቀጥሎአል።  ሁለት  ባህርይ  ኢየሱስ  ክርስቶስ  አንድ  አካል  ሁለት  ባህርይ ሲል  ተዋህዶ  የኢየሱስ  ስብእና  በመለኮትነቱ   የተዋሃደ  ወይም  ተዋህዶ  ነው  የሚሰኘው  ንድፈ  አሳብ  ነው።  የንስጥሮስ  ትምህርት  ግን  ኢየሱስን  ሁለት  ባህርይ  ሳይሆን ሁለት  አካል  የሚያደርግ  ነው።

 ንስጥሮስ  የማርያምን  ወላዲተ  አምላክነት  (θεοτόκος  ቴኦቶኮስ  መሆን)  የሚቃወም  ሰው  ነው።  ማርያም  ቢበዛ  ሥጋ  የለበሰው  ክርስቶስ  እናት (ክሪስቶቶኮስ)  እንጂ  የአምላክ  ወይም  የእግዚአብሔር  እናት  መባል የለባትም  ያለ  ሰው  ነው።  θεοτόκος  ባለፈው  መጣጥፍ  በመጠኑ የጠቀስኩት  ወላዲተ  አምላክ  ተሰኝቶ  በስሱ  የተተረጎመ  ቃል  ይሁን  እንጂ ትርጉሙ  ከዚህ  የጠለቀ  ነው።  ቀጥተኛ  ትርጉሙ  “የአምላክ  ተሸካሚ፥ የአምላክ  አምጪ፥  አምላክን  ያመጣች፥  ወይም  እንዲመጣ  ያደረገች”  (bringer forth of God)  ማለት  ነው።  Theotokosን  ያጸደቀው  በ431  የተደረገው  የኤፌሶኑ  ጉባኤ  ነው።  ከዚያ  በኋላ  ነው  የማርያም  ስዕሎች ስፍራ  ሊያገኙ  የበቁት።  ቀድሞ  ስዕሎች  የነበሩ  ቢሆኑም  ከስነ  ጥበብ አንጻር  የሚታዩ  እንጂ  ከአምልኮ  ጋር  የተቆራኙ  አልነበሩም።  ኋላ ንስጥሮስ  በስደት  በአንጾኪያ፥  በዐረቢያ  እና  በግብጽ  ኖሮ  በ451 ሞቶአል። 12 የንስጥሮስ  ትምህርት  ዋና  ስሕተት  በክርስቶስ  የመስቀል  ላይ ሞት  ከሁለቱ  አካላት  አንዱ  ሰው  የሆነው  አካል  ብቻ  ከሆነ  የሞተው ለኃጢአት  የተከፈለውን  ዋጋ  መለኮታዊ  ልቀት  ያሳጣዋል የሚል ነው።

ወደ  ዮሐንስ  አፈወርቅ  ስንመለስ፥  ይህ  ሰው  በታሪክ  በጣሙን  የታወቀ ሰው  ነው።  ከሰበካቸው  ስብከቶች  600  ያህል  በጽሑፍ  እና  ወደ  200  ደብዳቤዎቹ  እስከዛሬ  ተጠብቀው  ይገኛሉ።  እንዲህ  እንደ  ተአምረ  ማርያሙ  የመሰለ  ታሪክ  ግን  ከቶም  የለም።  ዮሐንስ  ነበልባል  የሆነ  ሰባኪ ነው።  እነዚህ  ስብከቶቹ  ናቸው  አፈወርቅ  የሚል  ቅጽል  እንዲሰጠው  ያደረጉትም።  ዮሐንስ  ከንስጥሮስ  ጋር  በአንድ  ዘመን  የነበረ  ሰው  ነው። ዘመናቸው  በአጭር  ይገናኝ  እንጂ  የሚተዋወቁና  በአንድ  ላይ  ያመለኩ ሰዎች  ግን  አልነበሩም።  ዮሐንስ  ከ347-407  ዓ.  ም.  13 ንስጥሮስ  ደግሞ ከ386-451  ዓ.  ም.  የኖሩ  ናቸውና  ዘመናቸው  በ21  ዓመታት  ብቻ ይገናኛል።  ንስጥሮስ  ሲወለድ  ዮሐንስ  39  ዓመቱ  ሲሆን  ዮሐንስ  ሲሞት ደግሞ  ንስጥሮስ  ገና  21  ዓመቱ  ነው።  ሁለቱም  በቁስጥንጥንያ  ሊቃነ ጳጳሳት  የነበሩ  ሲሆኑ  ዮሐንስ  ጵጵስና  የተሾመው  በ397  በአምሳ  ዓመቱ ነው።  ንስጥሮስ  የቁስጥንጥንያ  ሊቀ  ጳጳስ  የሆነው  ደግሞ  በ428 (ከ428-431)  ነው።  ዮሐንስ  ከሞተ  ከ21  ዓመታት  በኋላ  ማለት  ነው።  ዮሐንስ  በሚሞትበት  ጊዜ  ንስጥሮስ  ገና  21  ዓመቱ  ነበርና  በተአምረ  ማርያም   እንደ ተጻፈው ጳጳስም  በአንብሮተ  እድ የሚሾም  ሰውም  አልነበረም። ኋላ  የተጻፉ  ምንጭ  የሌላቸው  ታሪኮች  ቢኖሩም  ዮሐንስ  በቀረቤታ  ሲታይ  በተአምረ  ማርያም  የጻፈውን  ማድረጉ  በታሪኮቹ  ሁሉ  የማይገኝ ብቻ  ሳይሆን  እንዲያውም  በተቃራኒው   ዮሐንስ  ሴትን  የመናቅና  ያለማድነቅ  አዝማሚያ  የሚታይበት  ሰው  ነው።  የሴትን  አብዝቶ  ማሸብረቅ  ይጠላ ነበርና  በጵጵስናው  ዘመን  ከንጉሡ  ሚስት  ከአውዶክሲያ  ጋር  ዓይንና  ቁልቋል  ሆነው  ኖረዋል።  ይህችን  ሴት  ከሄሮድያዳ  ጋር እያነጻጸረ  ስለተናገረባት  ሌሎችን  አስተባብራ  ለስደት  የዳረገችውም  እርሷ ናት።  “ከዱር  አራዊት ሁሉ እንኳ  ሴትን  የሚያህል  ጎጂ  ፍጡር አይገኝም”  ብሎ  ስለ  ሴት  ጾታ  ያተተ  አንድ  መጽሐፍ  ዮሐንስን  ተጠቃሽ አድርጎታል። 14 እንዲህ  ለአንስታይ  ጾታ  ወደ  ጥላቻ  የተጠጋ  ንቀት እንዳለው  የሚባልለት  ሰው  ነው  በተአምረ  ማርያም  መርገመ  ደም  ያለባትን  ሴት  ኀፍረተ  ሥጋ  የሳመውና  ስዕሊቱ  አፈወርቅ  ብላ  የሰየመችው።  በተአምረ  ማርያም  ውስጥ  የማርያም  ስዕል  እስኪሰለች  ድረስ  ነው  ድምጽ  እያሰማች  የምትናገረውና  ይህ  ሲጨመርበት  ታሪክ ወደ  ተረትነት  በቀላሉ  ይሻገራል።  እነዚህ  እርስ   በርሳቸው ከተጋጩ  እንደ ባለ  አእምሮ  በመዛግብት  የተጻፈውን  ተጨባጭ  ታሪክ  እንቀበል  ወይስ  በተአምረ ማርያም   የተጻፈውን  ከታሪክ   ጋር የሚጣላ ፈጠራ?

ለ.  ንጉሥ  ማርቆስ።

 የንጉሥ  ማርቆስ  ታሪክ  በተአምረ  ማርያም  በምዕ.  100  የተጻፈው  እንደሚተርከው  ድንግል  ሳለ  በሮም  መንገሡ  ተጽፎአል። 10 ዓመታት  ከነገሠ  በኋላ  ሠራዊቱ  ሚስት  ማግባት  ሞገስ  የሚያስገን  ቁም  ነገር  ስለሆነ  ሚስት  እንዲያገባ  ማለዱት።  እርሱም  ማርያምን  ልማከር  ብሎ  በስዕሏ  ፊት 7 ቀን  ቆሞ ጸለየ።  በጸሎቱ  መጨረሻ  የስዕሊቱ  ፊት  ቦግ  ብላ  በራችና  በድምጽ  እንዳያገባና  በድንግልና   እንዲኖር፥  እንዲያውም  መንግሥቱን  ትቶ  ደብረ  ቶርማቅ  ገዳም  ሄዶ  እንዲኖር  ነግራው  እዚያ  ለመኖር  ማንም  ሳያየው  ጠፍቶ  ሄደ።  በተአምረ  ማርያም  ድንግልና  እጅጉን  የተወደደ  ከመሆኑ  የተነሣ  የተአምረ  ማርያሟ  ማርያምና  የማርያም  ስዕል  ሰው  ሁሉ  ሳያገባ  እንዲኖር  ይፈልጋሉ።  ይህ  ከመጽሐፍ ቅዱስ  ጠቅላላ አሳብ ጋር በትጋት የሚጣላ ነው።
ማርቆስን  በተመለከተ  በሮም  ግዛት  ውስጥ  በታሪክ  የታወቀ  በዚህ  ስም የተጠራ  ንጉሥ  ማርቆስ  አውራልዮስ (Marcus Aurelius)  ነው።  ይህ ሰው  ሳይሆን  ሌላ  ነው  ከተባለ  ታሪካዊ  ማስረጃ  ያስፈልገዋል።  በተአምረ ማርያም  ውስጥ  ስም  ሳይጠቀስም  ‘በአንድ  አገር  የነገሠ  ንጉሥ’  ይባልና  የንጉሡ  ስም  ሳይነገር  መተረክ  የተለመደና  ቀላል  ነገር  ነው።  ስለ  ማርቆስ በታሪክ  መዛግብት  የተጻፈ  ታሪኩ  የሚናገረው  ግን  ከዚህ  የተለየ  ነው።
ማርቆስ  ከ161-180  ለሃያ  ዓመታት  የነገሠ  ንጉሥ  ነው።  ከ20ው  ውስጥ 9ኙን  አብሮት  የነገሠ  ሉቂዮስ  ቬሮስ  የተባለ  ሰው  አለ።  ንጉሥ  ማርቆስ ከታሪኩ  እንደምናነብበው  ሳያገባ  የኖረ  እና  መንግሥት  ትቶ  ገዳም  የገባ መነኩሴ ሳይሆን  14 ልጆች ከወለደችለት ፋውስቲና  ከተባለች  ሚስቱ  ጋር  ለ30  ያህል  ዓመታት  ተጋብቶ  የኖረ  ሰው  ነው።  የቱ  ነው  ትክክል?  በማረጋገጫ  የሚፈትሹትና  ማስረጃ  የሚያቀርቡለት  ታሪክ?  ወይስ ከታሪክ  ጋር  የሚጋጭና  ምንጩ  የማይታወቅ  ተረት?

ሐ.  ዮስጢን  ሰማዕት። 

በተአምረ  ማርያም  ውስጥ  የተጻፈው  በምዕ. 99  ሲሆን ከዮስጢን  ይልቅ  ስለሚስቱ  ታውክልያ  በተጻፈው  ውስጥ  የተካተተ ነው።  የተአምረ  ማርያሙ  ታሪክ  ታውክልያ  የዲቅልጥያኖስን  ክህደት ስለማወቅ  በጸሎት  ላይ  ሳለች  ማርያም  ከእናቷና  ከኤልሳቤጥ  ጋር ትገለጥላታለች።  የዲዮቅልጥያኖስ  ክህደት  በልጇ  (በኢየሱስ)  ዘንድ  የታወቀ  መሆኑን፥  ኢየሱስ  ለዮስጢን  በሰማይ  ስለሚደረገው  ሠርግ (ተዋህዶ)  ሊነግረው  እንደሄደና  እርሷ  ደግሞ  ወደ  እርሷ  እንደመጣች፥ ሁለቱም ከልጃቸው  ጋር  እንደሚሰዉ  ነግራት አበረታታት  ተሰወረች።
እዚህ  ያለው  ትልቅ  ታሪካዊ  ግጭት  ዮስጢን  ከ100-165  የኖረ  መሆኑ የታወቀ  ሆኖ ታውክልያ  የምትጸልየው  ስለ ዲዮቅልጥያኖስ ክህደት  መሆኑ ነው።  ሌላ  ዮስጢን  ካልሆነ  በቀር  ይህ  በታሪክ  የታወቀው  Justin  Martyr  ነው።  ዲዮቅልጥያኖስ  ክርስቲያኖችን  በእጅጉ  ያሳደደ  ሰው ቢሆንም  የኖረበት  ዘመን  ከ244-311  ሆኖ  የነገሠው  ደግሞ  ከ284-305  ድረስ  ነው።  ታውክልያ  ከ120  ዓመታት  በኋላ  ስለሚመጣው  ከሐዲ እያሰበች  ነበር  ካልተባለ  በዚያን  ዘመን  ዲዮቅልጥያኖስ፥  ክህደቱና  አሳዳጅነቱም  አልነበሩም።  ዲዮቅልጥያኖስ  የተወለደው  ዮስጢን  ከሞተ ከ80  ዓመታት  በኋላ  ነውና  ዮስጢን  የተሰዋው  በዲዮቅልጥያኖስ  ሳይሆን  ከላይ  በተጠቀሰው  ማርያም  ከንጉሥነት  ወደ  ገዳም  አስኮበለለችው  በተባለው  በማርቆስ  አውራልዮስ  ዘመነ መንግሥት  ነው።

5.  የተምታታ  ሲዖልና  መንግሥተ  ሰማያት።

በተአምረ  ማርያም  ውስጥ  የሚታዩት  ከሞት  በኋላ  የሚሆኑት  ነገሮች  በመጽሐፍ  ቅዱስ  ከተነገሩት  የተለዩ  ናቸው።  የተአምረ  ማርያሟ  ማርያም  ሰዎችንና  ነፍሳትን  ከሲዖል ታወጣና  ወደ  መንግሥተ  ሰማያት  ታስገባቸዋለች።  ሥጋዋ  ወይም  በድኗ በገነት  በሕይወት  ዛፍ  ስር  ተደርጎ  ነበር።  ያደረጉት  ደግሞ  ሬሳውን  ተሸክመው  የነበሩት  ሰዎች  ናቸው።  ስለዚህ  በአካል  ወደ  ገነትና  ወደ ሕይወት  ዛፍ  ይደረሳል  ማለት  ነው።  ሰዎች  ሲሞቱ  ማርያም  አንዳንዴ  ከመላእክት  ጋር፥  አንዳንዴ  ደግሞ  ከደናግል  ጋር  እየታጀበች  ትመጣና  ትወስዳቸዋለች፤  ለሌሎችም  ትታያለች።
ሰዎች  ከሞቱ  በኋላ  ማርያም  መልሳ  አምጥታ  ታሳያለች።  በምዕ. 18-19 እነ ጊዮርጊስ፥  ቴዎድሮስ፥  መርቆሬዎስ፥  የተመልካቾች  ዘመዶቻቸው  ሁሉ፥ በሕዝቡ  ጥያቄ ደግሞ  አዳምና  ሔዋን፥  አብርሃም፥  ይስሐቅ፥  ያዕቆብ፥  እነ ሙሴና  ዳዊት፥  ነቢያትና  ሐዋርያት፥  ወዘተ  እየተሰለፉ  መጥተው  ከመጋዘን  እያመጡ  ለሸማች  እንደሚያሳዩት  ዕቃ  ይታያሉ።  ከዚያ  በኋላ ምን  እንደሚሆኑ  አልተጻፈም።  በመጽሐፍ  ቅዱስ  ውስጥ  ሰዎች  ከሞት የተነሡባቸው  ጊዜያት  አሉ።  ግን  በሰልፍ  መጥተው  ሊሰወሩ  ሳይሆን ታይተው  ኖረው ሞተዋል።  የዓይንዶሯ  መናፍስት  ጠሪ  ለሳኦል ሳሙኤልን  አስነሥታለች።  በአስማት  የምትሠራ  ሙታን  ሳቢ  ናትና  እንዳስነሣች  መሰለ  እንጂ  ሳሙኤልን  በእርግጥ  አላስነሣችም፤  ልታስነሣም  አትችልም። ሳሙኤል  ተነሥቶ  ኖሮ  ቢሆን  ሳኦልም  ያየው  ነበር  እንጂ  ምን  እንዳየች  አይጠይቃትም  ነበር።  ይህ  በነዚህ  ምዕራፎች  የሚታየው  የመናፍስት ጠሪዎች አሠራር  ሆኖ ልዩነቱ  ለጥቂት  ጊዜ መታየታቸው  ነው።
በምዕ.  28  ጌታ  ለሐዋርያት  በገነት  ተገለጠላቸው  ይላል።  በአካል  ገነት ገብተው  ማለት  ነው።  በምዕ.  54  የአንድ  ደብር  አለቃን  ወደ  ሰማይ አሳረገችው።  ሳይሞቱ  የሚነጠቁበትም  ነው።  በ77  የለማኙን  ፊት  በዳቦ  የገመሰው  ሰው  ሞቶ  ሲዖል  ሄደ።  ማርያም፥  “የለም  ይህ  የኔ  ነው”  ብላ ወደ ሲዖል  እንዳይወርድ  ተከራከረች። ዳቦውን  የተቀበለው  ፊቱ  የተገመሰ  ለማኝ  ሄዶ  መሰከረና  ሰውየው  ሲዖል  መግባት  ቀርቶለት  ነፍሱ ተመለሰችና  ከሞት  ዳነ።  ጌታ  እየተሳሳተ  ወይም  እየተጸጸተ  አሳቡን የሚቀይር  ወይም  የሰው  ምስክር  የሚያስፈልገው  የሰው  ዳኛ  መምሰሉም መታለፍ  የሌለበት  ስሕተት  ሆኖ ሳለ ለማኙ  በምን  አካል  ወደ  ዙፋን  ቀርቦ መሰከረ? በአካል  ወይስ  ያለአካል?

12 ለታሪካዊ ሰዎቹ  Schaff, [electronic version] vol. 3, ch. 1-3. History  of the Christian Church, እና Schaff, Nicene and Post Nicene  Christianity, እንዲሁም ታሪካዊ ክርስትና ላይ ከሚያተኩሩ ድረ ገጾች ያገኘኋቸው ተጨምረውበታል፡
13 በዚህ መጣጥፍ ዓመተ ምሕረቶቹ በግዕዝ ቁጥሮች ካልተጻፉ በጎርጎራውያን አቆጣጠር ነው።
14 http://en.wikipedia.org/wiki/John_Chrysostom
ይቀጥላል,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,

Tuesday, June 24, 2014

ተአምረ ማርያም የተባለው መጽሐፍ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን እናት የቅ/ማርያምን የቅድስና ባህርይ አይወክልም!


ካለፈው የቀጠለ (ክፍል ሦስት)
(እዝራ ስነ ጽሁፍ፤ ዘላለም መንግሥቱ)

በምዕ.  24  የተጻፈው  ለማርያም፥  ለመስቀልና  ለስዕል  የማይሰግዱ የተባሉት  የአባ  እስጢፋኖስ  እና  የነደቀ  እስጢፋ  ታሪክ  መጽሐፉ ተተረጎመ  በተባለበት  ዘመን  እንኳ  ተፈጽሞ  ያላለቀና  ገና  እየተከሰተ  ያለ ነገር  ሆኖ ሳለ  ገና  ያልተፈጸመውን  ነገር  ከብዙ  ዓመታት  በፊት  ግብጽ  አገር  እንደተፈጸመ ተደርጎ የመጣና  የተተረጎመ  ማለት  ጥሬ  ውሸት  ነው።  ዘርዓ  ያዕቆብን ንጉሣችን  እያለ  ከተናገረ  ደራሲው  የዘርዓ  ያዕቆብ  ዜጋ  ነው  ማለት  ነው። ተርጓሚው  ማለት የተጻፈውን  ተርጓሚ  እንጂ  ያልተጻፈውን  ጨማሪ  አለመሆኑ የታወቀ ነው።

2.  የተቃለለ  ክርስቶስ።

 በመጽሐፍ  ቅዱስ  ውስጥ  የምናየው  ኢየሱስ  ለመሞትና ለኃጢአታችን  ስርየት ደሙን  ለማፍሰስ  ከማርያም  ሥጋን  ነስቶ ሰው  የሆነ አምላክና  ፈጣሪ ጌታና  እግዚአብሔር  ነው።  በተአምረ  ማርያም  ውስጥ  ከአምላክና  ጌታ  ይልቅ  የተነገረውን  በፍጥነት  የሚፈጽም ቀልጣፋ  ተላላኪና አገልጋይ  ሆኖ  ነው  የቀረበው። ከመጀመሪያ  እስከ  መጨረሻ  ክርስቶስ  የማርያም  ልጅ  ነው።  ኢየሱስ  ከድንግል  ማርያም  ሥጋን  መንሳቱ  እውነት  ቢሆንም  ማርያምን ጨምሮ የፍጥረታት ሁሉ  ፈጣሪ  በመሆኑ  በግዕዘ  ህጻናት ዘወትር እናቱን ለመላላክና ለማገልገል  የመጣ በማስመሰል አምላካዊ  ኃይሉን በሰውኛ ፈቃድ ፈጻሚነት ስር ማስቀመጥ ትክክል አይደለም።  ሥጋ  የለበሰው  ኢየሱስ  እናትነት  አንድ  ነገር ነው።  የዘመን  መጀመሪያ  ለሌለው  አምላክ  እናት መሆኗ ብቻውን  ማርያምን  ከፍጥረቷ  በላይ  ሊያደርጋት  የተገባ  አይደለም።

 ነገር ግን  በተአምረ  ማርያም ውስጥ  ከማርያም  ጋር  በተጻፈባቸው  ቦታዎች  ስትጠራው  ልጄ  ወዳጄ  ብላ  ነው።  ሰዎች  ደግሞ  ወደ  ማርያም  ሲጸልዩ  እርስዋን  እመቤታችን  (እግዝእትነ)  ብለው  ነው። ክርስቶስን ከመለመን ይልቅ ማርያምን በመለመን ከልጇ ምህረት ማግኘት የቀለለ ይመስላል። አንዳንድ የተአምራት ጽሁፎች ላይ ስንመለከት ኢየሱስ ለሰዎች ፈቃደኛ ያልሆነበትን ጉዳይ ማርያም ስትነግረው ቃሉን ሲያሻሽል ይታያል።  ከክርስቶስ ርኅራኄ ይልቅ የማርያም ልመና ምህረት ያስገኛል የሚል ሃሳብን የያዘ ነው። «ዓለም ያለማርያም አማላጅነት አይድንም» የሚለው አባባል ዓለም በኢየሱስ አምላካዊ ፈቃድ የተደረገለትን ድኅነት አምዘግዝጎ የሚጥል ነው።  ኢየሱስን  ግን  በቀጥታ  ሲያናግሩት  ወይም  ወደ  እርሱ  ሲጸልዩም  ሳይሆን  “ከልጅሽ  ከወዳጅሽ”  እያሉ እርሷኑ  ሲለምኗትና ሲጠይቋት ነው  የሚታየው።  «ለምኑ ይሰጣችኋል፤ አንኳኩ ይከፈትላችኋል» የሚለው የወንጌል ቃል ተሰርዞ በማርያም አማላጅነት ላይ ብቻ ተስፋ ጣሉ የሚለው ክህደት ትምህርት መነሻው ምንድነው?
የክርስቶስ ዘላለማዊ ኅላዌነት ማርያምን ያስገኘ ሳይሆን የማርያም መኖር ኢየሱስን እንዳስገኘ ከሚታሰብ ጭፍን ክህደት የሚመነጭ አስተሳሰብ ነው።  የፈጠረ፤ የቀደሰ፤ ያነጻና ሥጋን የለበሰው በአምላካዊ ፈቃዱ መሆኑ መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ ነው።  ይህንን መዘንጋት ኢየሱስ  በብዙ  የማርያም  ስዕሎች  ላይ  እንደሚታየው  የማርያም  አራስ  ልጅ፥  ጨቅላ  ልጅ፥  ወጣት  ልጅ፥  ታዛዥ  ልጅ፥ ሁሌ ጭኗ ላይ ሲቀመጥ የሚታይ፤ አንድ  ጊዜም  እርሷ የጠየቀችውን  ነገር  እንቢ  ያላለ፥  የተጠየቀውን  ሁሉ  በቅልጥፍና  የሚፈጽም፥  የተሳሳተ  ነገር ጠይቃ እንኳ  ቢሆን  አሳቡን  ስለ  ልመናዋ  ሲል የሚቀይር  ለስላሳ  ልጅ  ነው።

 አንዳንዴ  ስታስፈራራው፥  ለምሳሌ፥ ኢየሱስን  ክዶ ማርያምን  ያመነን  አንድ ሰው  ይቅር እንዲለው በለመነችው ጊዜ  እንደማይሆን  ሲነግራት፥  ልብሷን  ቀዳ፥  “እኒህን  ጡቶቼን እቆርጣቸዋለሁ”  ብላ  ፍርዱን  አስቀይረዋለች፤  (ምዕ.  110ን  ተመልከቱ )። ኢየሱስም  አሳቡን  ቀይሮ  ይቅር  አለው።  በታሪኮቹ  ሁሉ፥  ከትንሣኤ  በኋላ እንኳ፥  ኢየሱስ  በሚታይባቸው  ጊዜያት  ሁሉ  እንደ  ባለ  ግርማ  አምላክ ሳይሆን እንደ ሕጻን  ሆኖ ነው የሚታየው። እዚሁ ምዕራፍ 110 ላይ እንኳ ኢየሱስ  ከዙፋኑ ተነሥቶ  በደረቷ  ላይ ተቀምጦ ተብሎ ተጽፎአል። በምዕ.  90  ልጇ  የተሰቀለባት  አንዲት  ሴት  ማርያም  ልጇን  ከተሰቀለበት ካላወረደችው  እሷም፥  “ልጅሽን  (ኢየሱስን)  ከጭንሽ  እወስደዋለሁ”  አለች።  ኢየሱስ  ሁሌ  በማርያም  ጭን  ተቀምጦ  የሚኖር  ብቻ  ሳይሆን ነጥቀው የሚወስዱትም  ዓይነት ነው። በምዕ. 43  ጴጥሮስ  ለተባለ  ቤተ  ክርስቲያንን  ላነጸ  ሰው  መልኩ  ያማረ ልጅ  ሆኖ  ተገለጠለት።  ‘ቤተ  ክርስቲያን  ያሠራ  ሰው’  ስለተባለ  ምናልባት  በብዙ  መቶ  ዓመታት  በኋላ  ነው  ቢባል  እንኳ  በዚያን  ጊዜ  ጌታ  ሕጻን  አለመሆኑ  ግልጽ  ነው።  ግን ልጅ  (የግዕዙ ሕጻን ነው የሚለው) ሆኖ ነው የተገለጠው።  ኅብስቱ  ሲቆረስ  ደግሞ  የዚህ  ሕጻን  ደም  ፈሰሰና  ታቦቱንና  ልብሱን ሁሉ  አራሰ።  በምዕ. 82  ኢየሱስ በዓለም  ሁሉ ገዢ  የነበረ ንጉሥ  ሳቤላ  የምትባል  ሴት  አስጠርቶ  (ሴቲቱ  በስም  ስትጠቀስ  ንጉሡ አልተጠቀሰም፤  ይህ  የመጽሐፉ አንድ  ደካማ ገጽታ ነው) ምክር  ሲጠይቅ ሴቲቱ  ራእይ አይታ  ለንጉሡ  አሳየችው፤ ያም ማርያም  ሕጻን  አቅፋ  ነው። ኢየሱስ  ሁሌም  ሲታይ፥  ዛሬም  ጭምር፥  በእቅፍ  ያለ  ሕጻን  ሆኖ  ነው ለማርያም  አምላኪዎች  የሚታየው። ኢየሱስ የቀረበበት  አቀራረብም  ከማንነቱ  አውርዶ  ያቃልለዋል።

 በተአምረ ማርያም  ሕጻኑ  ኢየሱስም  ሲራገም  አይጣል  ነው፤  ማርያምም  ስትበቀልና  ስትራገም  የተለመደ  መሆኑ  በቀጣዩ ነጥብ  ይታያል።  በምዕ. 101  ቁ. 108፥ ያፈለቀውን  ውኃ  ለአገሩ  ሰዎች  «መራራ  ይሁንባቸው  የጠጣውም  አይዳን  ብሎ  ባረከው»  ይላል።  ረገመው  ላለማለት  ባረከው  አሉት  እንጂ  ቃሉ ግልጽ  እርግማን  ነው።  በቁ.  125  ግመሎችን  ድንጋይ  ሁኑ  ብሎ  አደነገያቸው።  [“እስከ  ዛሬ  ድረስ  ደንጊያ  ሆኑ”  ይላል።  ኋላ  ኢትዮጵያ ቆይተው  ሲመለሱ  ነፍስ  ተዘርቶባቸው  ተመልሰው  ግመል  ሆነው  ዕቃ ተጭነው እንደሄዱ  የተረሳ  ይመስላል።] በቁ.  159  ኢየሱስ  የግብጽን  አገር  ምድሩንም  ሕዝቡንም  መርገሙ  ተጽፎአል።  ይህ  እዚህ  መርገም የሚያፈስሰው  ኋላ  ላይ  ገና  አፉንም  አልፈታም  የተባለው  ኢየሱስ  ነው። ግጭቱን  ብንተወው  እንኳ  ይህ  የተአምረ  ማርያም  ፈጣሪዎች  የፈጠሩት  እንጂ  የመጽሐፍ  ቅዱሱ  ኢየሱስ  አይደለም።  የመጽሐፍ  ቅዱሱ  ኢየሱስ  ያስተማረውም  ያደረገውም  ጠላትን መርገም  ሳይሆን  መውደድ ነው። «አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው» ብሎ ወደባህርይ አባቱ የጸለየው ኢየሱስ የአገሩ ውሃ መራራ ይሆንባቸው፤ የጠጣውም አይዳን፤ ድንጋይ ሁናችሁ ቅሩ» እያለ በጭራሽ  አይራገምም።

3. የተጋነነች ማርያም።

 ተአምረ ማርያም  እንደ ስሙ የማርያም  ተአምራት  መጽሐፍ ነው። ተአምራቱ  ብዙና የተለያዩ  ናቸው። ማርያም  ብቻ  ሳትሆን በስሟ  የሚደረጉ  ነገሮች  ሁሉ  ክብራቸውና  ክብደታቸው  እጅግ  ነው።
ለምሳሌ፥  በተአምር  12  ውስጥ  78  ሰዎች  የበላ  ጭራቅ  በማርያም  ስም ውኃ  ስላጠጣ  ሞቶ  ወደ  ሲዖል  እንዲሄድ  ጌታ  ፈረደበት።  ማርያም  ቀርባ  78ቱ  ነፍሳትና  ውኃው  በሚዛን  ይደረጉ  ብላ  ተደርጎ  የውኃው  ክብደት  እንዲመዝን በዘዴ ጥላዋን እንዳሳረፈችበት፤ የሞቱት ሰዎች ነፍሳት ስለቀለሉ  ጌታ  አሳቡን  ቀይሮ  ወደ  መንግሥቱ  ያስገባዋል ሲል እናገኘዋለን። ይህ እንግዲህ የፈለጋችሁትን ዓይነት ኃጢአት ብትፈጽሙና አምላክን ስለበደላችሁ ቢፈረድባችሁ እንኳን «ማርያምን ካመናችሁ ትድናላችሁ» ለማለት የተዘየደ የመዳኛ ምክንያት ነው።  የተአምሯ ማርያም ፍርዱን ለመቀየር በጥላዋ ሳይቀር እስከማታለል የመሄድ ብቃት እንዳላት ጥንካሬዋን ለማጎልበት ሲጠቀሙበት ይታያል። በአምሳለ እግዚአብሔር  የተፈጠሩ  78  ሰዎች  ነፍሳት  ከጥርኝ  ውኃ  መቅለላቸው አሳዛኝ ነው።  በምዕራፎቹ  ሁሉ  ማለት  እስከሚቻል  ማርያም  ከእግዚአብሔር  ጋር ተስተካክላ  ነው  የምትገለጠው።  ለምሳሌ፥  በ41፥13  “በእግዚአብሔር  አምነው፥ በወለደችውም  በእመቤታችን  አምነው  ከቤተ  ክርስቲያን ወጡ”  ይላል።  በማን  አምነው?  በእግዚአብሔርና  በማርያም!  እዚሁ  ምዕራፍ  ቁ.  25፥  “እምነቱን  በናቱና  በእግዚአብሔር  ላይ  ያደረገ  ሁሉ  አያፍርምና”  ይላል።  እዚህ  እንዲያውም  ማርያም  ቀድማ  እግዚአብሔር  ተከተለ!  ምዕ.  76  መነኮሳቱ  ሲጸልዩ  እግዚአብሔርንና  ማርያምን  ነው፤  “እንለምንሃለን  .  . .  እንለምናታለን”  ቁ. 15።

  አንዱ  ቄስ  ደግሞ  የማርያምን  ውዳሴ  ብቻ እንጂ  ሌላ  የማያውቅ  ነው፤  ምዕ.  76።  ይህንን  ቄስ  ሌላ  ካላወቀ እንዳይቀድስ  የከለከለውን  ኤጲስ  ቆጶስ  ወደ  አገልግሎቱ  ካልመለሰው በ30  ቀን  ትሞታለህ  አለችው።  ከግዝቱ  ፈታውና  እርሱም  ማርያምን እያደነቀ  አብረው  ኖሩ።  እዚህ  የምትታየው  የተአምረ  ማርያሟ  ማርያም እርሷ እስከተወደሰች ድረስ  እግዚአብሔር  ባይመሰገንም  ደንታ  እንደሌላት ነው።
በምዕ. 86 ማርያምን በፍጹም አሳቧ፥ በፍጹም ልቧ የምትወድ የተባለላት ሴት  ታሪክ  ይገኛል።  እንዲህ  ባለ  መውደድ  መወደድ  ያለበት እግዚአብሔር  ብቻ  መሆኑን  ነው  መጽሐፍ  ቅዱስ  የሚያስተምረን።  እና በቃሉ  (ዘዳ. 10፥12-13፤  ማቴ. 22፥37፤  ማር. 12፥30-32፤  ሉቃ. 10፥27)  እንደተጻፈው ሰው በፍጹም ልቡ መውደድ ያለበት  እግዚአብሔርን  ነውና  ማርያም  ይህንን  ማሳወቅ  ሲኖርባት  አለማድረጓ  የመለኮትን  ፍቅር ማስቀነሷ ነው። በዚህ  ምዕራፍ  የተጠቀሰው ሰው ጠንቋይን  ምክር  የጠየቀ ሰው  ሆኖ  ምንም  ወንጌል  ሳይሰማ  ግን  የማርያምን  ስም  ሲነገረው  በነፋስ  ፊት  እንዳለ  ገለባ  ሆነ።  ሲሞትም  ማርያም  ሬሳውን  አንሥተው  በገዳም እንዲቀብሩት ተናገረችለት።  ማርያም ሰው  የሚሞትበትን  ቀን  የምታውቅ ናት።  ከላይ ለቄሱ  በ30 ቀን እንደሚሞት  ተናግራው  እንደነበር  አይተናል።  ሌላ  ምሳሌ፥  በምዕ.  81  አንድ  መነኩሴን  በአንድ  ሌሊት  ተገልጣ  ወደ  ኢየሩሳሌም  ወስዳ  አዙራ አስጎብኝታ፥  በዮርዳኖስም  አጥምቃ  የሚሞትበትን  ጊዜ  ነገረችው፤ እንደተናገረችው  ጊዜ  ዐረፈ።  ከእግዚአብሔር በቀር የሚያውቃቸው የሌሉ ነገሮችን  ካወቀች  ሁሉን  አዋቂ  ናት  ማለት  ነው?  ሁሉን  አዋቂ  ከሆነች አምላክ ናት ማለት ነው? የዚህ  መጽሐፍ  ማርያም  ስትፈልግ  ርኅሩኅ  ሳትፈልግ  በቀለኛ  ናት።

  ለምሳሌ፥  በምዕ  35  አንድ  እስላም  ዘራፊ  የዘረፈው  በገዳም  የሚኖር  ቄስ ወደ  ማርያም  ስዕል  ሄዶ  ተማጸነ፤  ጸልዮ  ሲወጣ  ዘራፊው  ወድቆ  እጁ ተሰብሮ  አጥንቱ  ገጦ  ወጥቶ  አየው።  እስላሙ  ይቅርታ  ሲጠይቀው ሽማግሌው  ማርያም  ይቅር  ብትልህም  ባትልህም  እንደወደደች  አለው፤ ይህ  ሰው  ቄስ  ሆኖ  ስለ  ይቅርታ  አያውቅም።  ቄስ  ነው  እንጂ  ክርስቲያን  አይደለም  ማለት  ነው።  ክርስቲያን  ቢሆን  ክርስቶስን  ሊመስል  ይሞክር ነበር።  እስላሙ ስላደረገው ጥፋት ይቅርታ ሲጠይቅ፤ ቄሱ «ይቅር ብትልህ ባትልህ» ካለ  እስላሙን ማን አስተምሮና አሳምኖ ሊለውጠው ነው? የሚገርመው ደግሞ ቄሱ ብቻ ሳይሆን የተአምሯ የማርያም  ስዕል  አፍ አውጥታ  «በቄሱ  ላይ  ደፍሯልና  ይቅርታ አይገባውም  አለችው»  የሚለው የበለጠ አስገራሚ ነው።  ስለዚህ  እስላሙ  በቄሱም፤ በተአምሯ  ስዕል አንደበት ወንጌልም  ሳይሰማ፥  ይቅርታም ሳያገኝ ሞተ።  ነገር ግን በተአምር 33፥39 ላይ ደግሞ ማርያም የይቅርታ ሳጥን ተብላለች።  እዚህ ላይ ደግሞ ተቃራኒ ናት። በቀለኛና  የደግነት ባህርይዋ  በወንጌል ላይ ሳይሆን በድርጊቱ  የአተራረክ ሁኔታ ላይ የሚደገፍ ነው።

 በምዕ. 39 ላይ ደግሞ በቀለኛ ማርያም ትታያለች። ሌላ  እስላም  ዘራፊ  ገዳም  ዘርፎ  ሲሄድ  ሰዎች  አግኝተው  ገደሉት፤  ከቤተ  ሰቡ  10  ሰዎች  ከዘመዶቹ  18  ገደሉና  የተዘረፈውን  አምጥተው  ለገዳሙ  ሲመልሱ  በቁ.  35፥ “ልቡናችንን  እርሱን  ለመግደል  ያነሣሳችን  ማርያም  እንደሆነች  ፈጥነን አወቅን”  አሉ።  «መጎናጸፊያህን ለሚወስድ እጀ ጠባብህን ተውለት» ለሚለው የወንጌል ቃል ግድ የሌላቸው መነኮሳቱ  ዘራፊውን  ከመግደላቸውም በላይ በቦታው ያልነበሩትን 10 ቤተሰቦቹንና 18 ዘመዶቹን በመግደላቸው ደስ ተሰኝተዋል። ይህንን የግድያ ስራ እንዲፈጽሙ ያነሳሳቻቸው ማርያም ናት ይላሉ። የተአምሯ ማርያም  ሰዎችን  አስነሥታ  ታስፈጃለች። የሚያሳዝነው  መነኮሳቱም  በዚህ  ነገር  ፍጹም  ደስታ  ተደሰቱ።  ኃጢአተኛ ሲድን  ሳይሆን  ሲሞት  የሚደሰቱ  መነኮሳት  ወንጌልን  ያውቃሉ  ይባላል?  በምዕ.  98  ከአንድ  ሽማግሌ  አስተማሪያቸው  ጋር  ፍልሰቷን  ለማክበር ሲሄዱ  አስተማሪያቸውን  ወደ  ገደል  የጣሉ  40  ተማሪዎች  በእሳት  ጦር እየወጋ  የሚገድላቸው  መልአከ  ሞት  አዘዘችና  በአንዴ  አለቁና  ሽማግሌውን  ግን  ወደ  በዓሏ  መከበሪያ  አደረሰችው።

  በምዕ.  15  አንድ  ግመል  ጫኝን  ጎድኑን  ወግታ  ስትገድለው  ትታያለች።  ደራሲዎቹ  ማርያምን  በቀለኛ  ሲያደርጓት  እርሷን  ለማግነን  ሲሉ  አስቀያሚ  ቀለም እየቀቧት  መሆናቸውን  እንኳ  አያውቁም።  ወይስ  አውቀው  ነው  አያደረጉ ያሉት? የተአምረ ማርያሟ  ማርያም  በቀለኛ ብቻ  ሳትሆን ቀናተኛም  ናት።  በምዕ.  92  የአንድ  ንጉሥን  ወጣት  ልጅ  እርሱ  ከሚወዳት  የበለጠ  እርሷ እንደምትወደውና  እንደምትቀናበት፥  ሚስት  ሳያገባ  እንዲኖርም እንደመከረችውና  በእጇ  ስዕሏን  እንደሰጠችው  ተጽፎአል።  ንግግራቸው  የሁለት  ፍቅረኞች  ይመስላል።  ልጁ  ሲሞትም  ብዙ  መላእክት  እና  ደም ግባቷ  ያማረች  ማርያም  መጥተው  በሰው  ሁሉ  እየታዩ  ይዛው  ሄደች። በእግዚአብሔር  የተደነገገ  ጋብቻ  የተናቀበትና  የተዋረደበት  እንደዚህ  ያለ መጽሐፍ  አላነበብኩም።  ያላገቡ  እንዳያገቡና  ድንግልናቸውን  ለማርያም  ስዕለት  አድርገው  እንዲሰጡ  የሚበረታቱበት  ብቻ  ሳይሆን  የተጋቡ  እንኳ  ከተቀደሰ  መኝታ  የሚከለከሉበት  ነው። መመነን፥ መመንኮስ፥ ተሰባስበው  በገዳም  መኖር  በመጽሐፍ  ቅዱስ  የተደነቀና  የተመሰገነ  ልምድ አይደለም።
ምንኩስናና  ገዳማዊነት  በክርስትና  ታሪክ  ውስጥ  ብቅ  ያለው  ቤተ ክርስቲያን  ከምድራዊ  መንግሥት  ጋር  እንደ  ውኃና  ወተት በተደባለቀችባቸው  ዘመናት  ከምድራዊ  ርኩሰትና  መንግሥታዊ  ሃይማኖት  ጋር  ላለመርከስ  የተደረገ  ሽሽት  ነው።  በዚህ  መጽሐፍ  ግን  ነባር  ልማድ  ብቻ  ሳይሆን  የተሞገሰ  አኗኗር፥ እጅጉን  የተጋነነ ሥርዓትም  ሆነ። ተአምራት  በመጽሐፍ  ቅዱስ  ውስጥ  ብዙ  ጊዜያት  የተደረጉ  ሲሆን የተአምራት  ዋነኛ  ግብ  የእግዚአብሔር  ክብር  ነው።  በተአምረ  ማርያም  በተደረጉት  ተአምራት  ግን  ክብር  እግዚአብሔር  ሲሰጥ  ከቶም  አይታይም።  እያንዳንዱ  ምዕራፍ  ሲጀምር  የእመቤታችን  ተአምር  .  .  .  ብሎ  ይጀምርና  ሲጨርስ  በረከቷና  .  .  .  ይደርብን  ይላል።  ሲጀምር ማርያም፥  ሲጨርስ  ማርያም።  ክብር  ለማርያም  እንጂ  ለእግዚአብሔር  የሚባል  ቋንቋ የለም።
 የኢትዮጵያ  ሰዎች  ለማርያም  የተሰጡ  ዐሥራት  ሆነው  ቀርበዋል።  ዐሥራት ማለት ከዐሥር አንድ እጅ ማለት ነው። ይህ አጠያያቂ  ቃል ነው። የኢትዮጵያ  ሕዝብ እንዴት ነው  1/10ኛ የሆኑት?  9ኙ እነማን  ናቸው?  ሕዝብ  እንደሕዝብ አስራት  ተደርጎ  የተሰጠበት  ታሪክ  ኖሮ  ያውቃል?  እንኳን  ሕዝብ  በሙሉ  ይቅርና  ከአዳም  ጀምሮ  ፈቃድ ያለው  አንድ ሰውስ  ያለ  ፈቃዱ  በመንፈሱ  ላይ  ሌላ  ሊሰለጥን  እንዴት ይገደዳል?  ደግሞስ  አስራት የሰጠው  ኢየሱስ ከሆነና ማርያም  አስራት ተቀባይ ከሆነች በተአምረ  ማርያም  ላይ  ምን  እየተነገረ  ነው?  አስራት ለማን  ነው  የሚሰጠው?  አምላክ  አስራት  ሰጪ፤  ማርያም  ደግሞ  አስራት ተቀባይ  ከሆነች ማርያምን መለኮት ማድረጋቸውም  አይደል? ከመለኮትም  በላይ እንጂ!  እግዚአብሔር ነዋ!  አስራት ሰጪው።
 በምዕ. 84 ሰንበትን  የሻረ አንድ አገልጋይ  ድዳ ሆነ። ጌታው ወደ ማርያም  ጸለየና  ፈወሰችው።  የተሻረው  ሰንበት  ነው።  የምትጠየቀው  ደግሞ ማርያም  ከሆነች  እርሷ  የሰንበት  ባለቤት  ናት  ማለት  ይመስላል።   «የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና» ማቴ 12፤8 የሚለው ቃል በተአምረ ማርያም ላይ ተቀባይነት የለውም።
በምዕ.  110  «እግዚአብሔርን  ክዶ  ማርያምን  ግን  አልክድም»  ያለ  ሰው  በማርያም  ኢየሱስን  አስፈራሪነት  ይቅርታ  ሲያገኝ  ይታያል።  እግዚአብሔርን  ክዶ ማርያምን  ማምለክ  ክቡር  ቦታ  አግኝቶአል።  ጌታ  እግዚአብሔርን  ክዶ ማርያምን  አለመካድ  ወይም  ማምለክና ማንን  የማግነን  ጉዳይ ነው?  የተአምረ  ማርያሟ  ማርያም  ማዕረጓ  ብዙ  ነው።  እመቤት  ናት፤  የአርያም ንግሥት  ናት  ወዘተ፤  ችሎታዋ  ድንቅ  ነው፤  ተፈጥሮ  በቁጥጥሯ  ስር  ነው፤ ተአምራት  ታደርጋለች፤  በሰው  ልብ  የታሰበውን  ታውቃለች፤  በሞትም  ላይ  ሥልጣን  አላት  ወዘተ፤  ሥልጣኗ  የመለኮት  ነው፤  መላእክት ይገዙላታል፥  ፍጡራን  ሁሉ  ያገለግሏታል፤  የመመረቅ፥  የመርገም፥ የመግደል፥  ከሞት  የማንሣት፥  ከእግዚአብሔር  ጋር  በእኩል  የምትለመንና የምትመሰገን  ናት  ወዘተ።  እንዲያውም እግዚአብሔርን የካዱ እርሷን ካመኑ ማዳን የሚያስችል አቅም አላት። እግዚአብሔርን ማመን አያስፈልግም። ማርያምን ብቻ ማመን በቂ ነው። ተአምረ  ማርያም  እንዲህ  በመሰሉ  ማርያምን በመጽሐፍ  ቅዱስ  ካላት  ትክክለኛ  ስፍራ  ፈንቅሎ፥  ተገቢ  ቦታዋን  ነጥቆ፥ ያልሆነችውን  አድርጎ፥  ያልተሰጣትን  ሰጥቶ፥  ያልለበሰችውን  ደርቶ የሚጸለይላት፥  የምትለመን፥  የምትመለክ  አድርጎ  መለኮታዊ  ሥልጣንና ኅልውና  ሰጥቶአታል። 

 ይቀጥላል,,,,,,,,,,,,,,,