ማናቸውም ሰው ከሴት ጋር እንደሚተኛ ከወንድ ጋር ቢተኛ ሁለቱ ጸያፍ ነገር አድርገዋል ፈጽመው ይገደሉ ደማቸው በላያቸው ነው» ዘሌ 20፣13
በኢትዮጵያ የአራቱም ሃይማኖቶች መሪዎች በአዲስ አበባ በቅርቡ በሚካሄደው 16ኛው የአይካሳ ጉባዔን አስታክኮ በአገሪቱ ጸያፍ፣ ከሥነ ምግባር ውጭና ባህልን የሚያንቋሽሽ አጀንዳ ለማስፈጸም ተነሣሥቷል ያሉትን የአንድ ቡድን እንቅስቃሴን በመቃወም ትናንት ሊሰጡት የነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ላልተወሰነ ጊዜ ተላለፈ፡፡
የሪፖርተር ፎቶግራፍ ጋዜጠኛ መሪዎቹ መግለጫ ለመስጠት እንደተዘጋጁ ያነሳውም ፎቶግራፎች እንዲጠፉ ተደረገ፡፡
መሪዎቹን በመወከል መግለጫው ለሌላ ጊዜ መተላለፉን ያስታወቁት ከኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ቄስ ኢተፋ ጎበና ሲሆኑ፣ የጋዜጠኛው ፎቶ ግራፎች እንዲጠፉ ያደረገውም በሥፍራው የነበረ አንድ የደኅንነት አባል ነው፡፡
መግለጫው የሚሰጥበት ትክክለኛው ቀን መቼ ነው ተብሎ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ‹‹ከጉባዔው በፊትም ሆነ በኋላ ሊሆን ይቻላል፡፡ ከዚህ ውጭ ትክክለኛው ቀን ይህ ነው ብዬ ለመናገር ያስቸግረኛል፤›› ሲሉ ቄስ ኢተፋ መልሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ መሪዎች በተወካያቸው አማካይነት መግለጫው ላልተወሰነ ጊዜ መተላለፉን ያስታወቁት፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶክተር ቴዎድሮስ አጽሃኖም በተገኙበት የዝግ ስብሰባ አድርገው በጉዳዩ ላይ ለአንድ ሰዓት ያህል ከተወያዩ በኋላ ነው፡፡