Saturday, November 22, 2025

የብልጽግና ወንጌል ምንድነው?

ብልፅግና ወንጌል (Dr Dereje Kebede) (2020) ከቤተመቅደስ እስከ ቤተመንግስት! መንግሥታት በቀንደ መለከትና በአዋጅ ሊያግዱት ሲገባ ቸል በማለታቸው በዓመታት መካከል አድጎና ተመንድጎ፣ ብዙሃኑን አራቁቶ፣ ጥቂቶችን ሚሊኒየርነት ማማ ላይ የሰቀለ አስተምሮ ምን እንደሆን የሚገምት ሰው አለ? ታመው የሚማቅቁን ተፈውሳችኋል፣ የደኸዩትን ባለጠጋዎች ናችሁ፣ አንድ ብር ስጡና እግዚአብሔር 10 ብር አድርጎ ይሰጣችኋል የሚለውንስ የተወላገደ ትምህርት ታውቁት ይሆን??? አማኝ የሚታመመውና የሚደኸየው ጠንካራ እምነት ሲያጣ ነው፣ አለበለዚያ ክርስቲያኖች አይደኸዩም አይታመሙም የሚለውን ትምህርትስ ደርሳችሁበት ይሆን? የእግዚአብሔርን በረከት በግል ሥጋዊ ጥቅም፣ በብርና በምድራዊ ቁሳቁስ ብዛት ብቻ የሚገለጥ፣ በካፒታሊስት ዋና መዲናዋ በአሜሪካ ተወልዶ በአፍሪካ ያደገውን “የወንጌል ተጧሪዎች፣ ስራ ጠል ሰዎች” ትምህርትስ ለይታችሁ አውቃችሁት ይሆን??ትክክል ገምታችኋል። የብልፅግና ወንጌል ይሉታል። እኔ ግን “የብልፅግና ወንጀል” እለዋለሁ። ስለብልጽግና ወንጌልና አስተምህሮ በዚህ ጊዜ መፃፍ ያስፈለገበት ዋና ምክንያት ይህ የወንጀለኞች ዶክትሪን የፕሮቴስታንት ክርዝማቲክ አማኞችን በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኖቻቸውን ከማራቆት አልፎ ዛሬ አገራችንን ለመምራት ቤተመንግሥት የተኮፈሱ ጠ/ሚኒስትር አቢይ አህመድንና ጥቂት ጴንጤቆስጤ የሥራ አሥፈፃሚዎቻቸውን፣ ይሄ9ው አደገኛ ዶክትሪን፣ ተብትቦ እንደያዛቸው ግልፅ እየሆነ በመምጣቱ ህዝቡ ሃገራችን የገባችበትን አሌ የማይባል እጥፍ ድርብ ሰቆቃ እንዲረዳ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ነው። ስለመሪዎቻችን በተለይም ስለ ጠ/ሚኒስትሩ እንግዳ የሆነ፣ በአለም ላይ ታይቶ የማይታወቅ የአመራር ክፍተት፣ ፍዘትና፣ ንዝህላልነት ላለፉት ሁለት አመት ከመንፈቅ ፀጉራችንን ስንነጭና ጥርሳችንን ስናፋጭ የቆየን በብዙ ሚሊዮን የምንቆጠር ዜጋዎች፣ መልስ ላጣንበት የአስተዳደር ውድቀታቸው፣ ምክንያት ከሆኑት ነገሮች መካከል አንዱ የሆነውን ይህንን የምናብ እምነት properity Gospel ተንትኖ መረዳትና ማስረዳት አማራጭ የሌለው ጉዳይ እንደሆነ እናውቃለን። አያችሁ ብልፅግና ወንጌልን የሚያምን ወይም የሚከተል ሰው በሃዘን፣ በድህነት፣ በበሽታ፣ በተፈጥሮአዊ መቅሰፍት ሰፈር መገኘት አይፈልግም። ያ ማለት፣ ምርት በአንበጣ ተወሮ ገበሬ ሲያለቅስ ብልፅግና ወንጌልን የሚከተል ሰው የተፈፀመው ውርጂብኝ እንዳልተፈፀመ፣ ቀና ቀናውን በማሰብና (Positive thinking) በእምነት (strong faith) ድልን በማወጅ አንበጣውም ይጠፋል፣ ምርቱም ይተርፋል ነው የሚለው። ጥቃቱም በህዝቡ አለማመን፣ ወይም ሕዝቡ በእግዚአብሔር ላይ በደል ፈፅሞ ወይም እምነት ስለጎደለው የተፈጠረ የሰማይ ላይ ቅጣት ነው ብሎ ነው የሚያምነው። ስለዚህም አዘኔታ የለውም፣ ለተጎዳው ህዝብ መራራት አይችልም። ስለዚህ ነው መሪያችን እርጉዝ ሆዷ ተዘንጥሎ ፅንሱ ሜዳ ላይ ሲጣል፣ ዝንብ የሞተ ያህል እንኳን ርህራሄ ያላሳዩት። ለጠ/ሚኒስትሩ ያ ድርጊት አልተፈፀመም ወይም በሰለባዋ እምነት ጉድለትና ኃጢአት የተነሳ የተፈፀመ ስለሆነ ለሳቸው ምንም ማለት አይደለም። በሰለባዋና በእግዚአብሔር መካከል ያለ ነገር ነው ብለው ስለሚያምኑ ህዝብ ያለቅሳል እሳቸው ያፏጩብናል። ጁዌል ኦስቲን የተባለው በአሜሪካን አገር በጣም የታወቀ የብልፅግና ወንጌል ፓስተር በመጽሐፉ “Become a better you” ላይ ያለው አይነት ነው። “Dwell only on positive, empowering thoughts toward yourself, “You will see God’s blessings and favor in a greater way.” “ሃሳብህን በገንቢ ሃሳቦች ላይ ብቻ አድርግ ያን ጊዜ የእግዚአብሔር በረከትና ሞገስ በህይወትህ በትልቅ መንገድ በሙላትህ ይገለጻል” ብልፅግና ወንጌልን የሚከተሉ መሪዎች፣ የሌሎችን ችግር ማየት አይችሉም (No Empathy) ርኅራኄ የለም። ችግር፣ በሽታና ድህነት ለእምነታቸው ተስማሚ የድል ትርክት ስለማይፈጥር፣ እያለ እንደሌለ መቁጠርና ጭንቅላታቸውን አሸዋ ውስጥ ቀብረው በምድር ላይ ያለውን እውነታ መካድ ይቀላቸዋል። እውነታው ግን አንታመምም ቢሉም ይታመማሉ፣ ሃዘንን ቢክዱም ሃዘን ይደርስባቸዋል፣ የተፈጥሮ አደጋን የለም ቢሉም የተፈጥሮ አደጋ ዙሪያቸውን ሲከሰት ያዩታል። አለበለዚያ ዶ/ር አቢይ እንደሚያደርጉት ሃዘን በሰሜን ሲከሰት ወደ ደቡብ መፈርጠጥ፣ ፅንፈኞች ህዝብን ሲያርዱ ወደ ኢሳያስ አፈወርቂ ግዛት ማቅናት፣ በመተከል ከ 300 በላይ አማራዎችና አብረው የተገኙ አገዎችም በመንግስት በተደገፉ ፅንፈኞች ሲጨፈጨፉ ወደ ደቡብ ሄዶ ስለፓርክ ማውራት፣ ወሎ በአንበጣ ሲመታ እሳቸው በአሩሲ የለማ የእርሻ ማሳን መጎብኘት፣ Go kart እየነዱ፣ ኢላማ ተኩስ እየተለማመዱ መዝናናት፣ በጉራ ፈርዳ አማራዎች ሲታረዱ ስለሃዘኑና ጭፍጨፋው ላለማሰብና ላለመመስከር ዝምታን መምረጥ፣ በጠቅላላ አይንን ጨፍኖ አላየሁም ወይም አልሰማሁም ነበር ማለት ሊኖርባቸው ነው። ሌላስ? በጃልሜዳ ለብዙ አመታት በኦርቶዶክስ ቤተክርስትያናት ተተተክሎ የነበረን መስቀል በአስተዳደሩ ትእዛዝ ከነበረበት ተነቅሎ አልሰማሁም ነበር ብሎ መሸምጠጥ፣ የቡራዩ ማፈናቀልንም አልሰማምሁም ነበር ማለትን ሊጠይቅ ነው። አልያማ ከላይ የዘረዘርኳቸውና ሌሎችም ያልተጠቀሱ በርካታ አሰቃቂ ወንጀሎችና የተፈጥሮ አደጋዎች በምድራችን በተደጋጋሚ አይናችን እያየ መከሰታቸውን የሚክድ ፍጥረት ከብልፅግና ወንጌል አማኞች፣ ሰባኪዎችና ከኦሮሙማ ፖሊቲክስ አመራሮቻችን በቀር ማን ይኖራል? በሃገሪቷ እንብርት ላይ እየተፈፀሙ ያሉትን ጉዶች አላየሁም ነበር፣ አልሰማሁም ነበር በሚል ፌዘኛ መሪ 110 ሚሊዮን ህዝብ ሲመራ እንግዲህ ከዛ በላይ መቅሰፍትስ አለ እንዴ? ጠ/ሚኒስትሩ በዋናነት ኢትዮጵያን የኦሮሞ ምድር ለማድረግ ካላቸው አጀንዳ ጋር የብልፅግና ወንጌል እምነት ፅንሰሃሳብ በአስተዳደር ሥርዓታቸው ገብቶ ታላቁንና የበለፀገውን የኦሮሞ የምናብ ምድር በቅዠትና በሰመመን እያጣጣሙ ወደፊት መሄድን እንጂ ሃዘንን፣ ድህነትን፣ ሞትን፣ የማሰቢያ ጊዜውም ልቦናም የላቸውም። ስለዚህ ለቅሶ ቤት ከመሄድ ሰርግ ላይ ቢገኙ ይመርጣሉ። የጠ/ሚኒስትሩ ፀጥታን አለማስከበርና፣ የጥቃት ሰለባዎችን በጊዜውና በቦታው ተገኝቶ ችግራቸውን አለመጋራት፣ አለማፅናናት፣ አለመካስና ከሚመጡት ጥቃቶች አለመጠበቅ ምክንያት የብልፅግና ወንጌል እምነታቸው ብቻ ነው የሚል ካለ ጭንቅላቱን አሸዋ ውስጥ የቀበረ ሰጎን መሆን አለበት። እንዲያውም ላስረግጥ የምፈልገው ነገር ከብልፅግናውም ቅዠት ይልቅ የኦሮሙማ አጀንዳቸው፣ አማራን፣ አማርኛንና ኦርቶዶክስን የማጥፋት እቅዳቸው እጅግ የከፋና እንደሆነ ነው። አንትያ በትለር (Anthea Butler) የተባሉ የስነመለኮት ፕሮፌሰር ስለፕሮስፔሪቲ ጎስፕል መሪዎች ሲናገሩ “ዶናልድ ትራምፕንና ጆዌል ኦስቲንን ያመሳስሉዋቸዋል። እንደ ፕሮፌሰሯ አባባል ሁለቱም ከአማኞች ትልቅ ቅቡልነት ያላቸው ናቸው፣ በስኬታማነትም ያምናሉ፣ ነገርግ ግን በወንጌል ቃል ላይ የተመሰረቱ ወይም የበሰሉ አይደሉም” ይላሉ። ሁለቱም ማለትም ዶናልድ ትራምፕና ጆዌል ኦስቲን እንደማንኛውም የብልፅግና ወንጌል ተከታይ፣ የአሸናፊነትን እንጂ የውድቀትንና የተሸናፊነትን ወሬ መስማት አይፈልጉም። ፕሮፌሰሯ የበለጠ ግልፅ በሆነ መንገድ ሲያስቀምጡት ታዲያ፣ ትራምፕንና ኦስቲንን የመሰሉ የብልፅግና ወንጌል መሪዎች የጎርፍና የዐውሎ ነፋስ ዜናዎች አይስማሟቸውም፣ ምክንያቱም ከብልፅግና ወንጌል ዶክትሪናቸው ጋር የሚስማማ የድልና የፈንጠዝያ ወሬ ስለማያበስር። በዚያም ላይ የብልፅግና ወንጌል መሪዎች አደጋንና ክፉ ክስተቶችን አደብስብሶና አቃሎ የማቅረብ፣ ሰለባዎች የደረሰባቸውን አደጋና አካላዊ ጉዳት ደግሞ ከግንዛቤ ያለማስገባትና ከጉዳይ ያለመፃፍ ባህሪይ አላቸው ይላሉ። ደግ ደጉን፣ አሸናፊነትን፣ መበልፀግን፣ አዎንታዊ ስነልቦናን (እምነትን) ይዞ ለቅሶና ዋይታ የሌለባትን አሮምያን መገባት። ልብ ብላችሁዋል? የኛም ጠ/ሚኒስትር አንትያ በትለር (Anthea Butler) የገለፀችው የጆዌል ኦስቲንና የዶናልድ ትራምፕን ጠባይና ተግባርን ኮፒ ነው ሲያሳዩን የኖሩት። የማፅናናት ቃል ከአፋቸው እኮ አይወጣም። በወሎው አንበጣ ወረራ ሰአት እሳቸው Go-kart እየነዱ ኢላማ ተኩስ ጨዋታ እየተጫወቱ ልክ እንደነ ኦባማና እንደ ሌሎች የሰለጠኑና ሃብታም አገር መሪዎች ለመሆን፣ ነገረ ዓለሙን ረስተው ይቧርቁ ነበር። በጣም የሚገርም ዓይነት መደንዘዝ ይላሉ ያ ነው እንግዲህ። እነኦባማ ቢጫወቱ ያምርባቸዋል። ኦባማ በኤኮኖሚ የተንኮታኮተች አሜሪካንን ከቡሽ ተረክቦ ሌት ከቀን ሰርቶ ሃገሪቱን ከሪሰሽን (Recession) ያወጣ ጀግና መሪ ነው። ቢጫወትም ያምርበታል። የኛ መሪ የተረከቡትን ሃገር ጥለው አንዴ ዱባይ ሌላ ጊዜ ደግሞ ኤርትራ የሚዞሩ፣ አገር መምራት አይደለም አንድ ሱቅ ማስተዳደር የማያውቁ፣ ለካሜራና ለታይታ የሚንቀሳቀሱ፣ በብሄር ተበጣጥቃ የአንድ ብሔር የበላይነት በፈረቃ የሚለዋወጥባትን አገር ለፅንፈኞች አሳልፈው ሰጥተው አገር ሲታመስ እንዳልሰሙና እንዳላዩ የሚሆኑ መሪ ናቸው። ብልፅግና ወንጌል በቤተክርስቲያን፣ የብልፅግና ወንጌልን አሰራር በቅጡ ለተመለከተ ሰው፣ በውስጡ ያዘለው ትምህርት ህዝብን በባዶ ተስፋና በወሬ፣ ያለውን እምነትና ንብረት የሚያስጥል፣ የመሰሪዎች “ በጨ ጠቆረ” ቁማር እንደሆን በቀላሉ ይረዳል። እንዲያውም የወንጌል አገልግሎት ሳይሆን አይን ያወጣ ዝርፊያ ነው ቢባል ማጋነን እይሆንም። ህዝቡ ያለውን ይሰጣል፣ ወትዋቹ ሰባኪ ግን የብር ፍቅር አስክሮት ጨምሩ በረከቱ በሰጣችሁት መጠን እንዲጨመርላችሁ ይላል። ብልፅግና ሰባኪው መድረክ ላይ ወጥቶ ህዝቡን ሲደልልና ሲሸጥ የጨረታ ገበያ አይነት ልፍለፋ መለፍለፍ አለበት። የምእመናኑን ልብ ለማባባት፣ ዝሩና አስር እጥፍ ታጭዳላችሁ ይላቸዋል። በኢየሱስ ስም የተለበጠ ወንጀል። በእስር ሊያስቀጣ የሚገባ ወንጀል። በካፒታሊዝም ስርአት የተለመደው፣ ግለሰቦችን በብዙሃን ላይ በገንዘብና በስልጣን የመቆለል ልምምድ (Individual achivement) የብልፅግና ወንጌል መሰረቱ ነው። ምን ማለቴ ነው? ብልፅግና ወንጌልን በመስበክ ሃብት ያካበቱ እንደነ ክራፍሎ ዶላር፣ እንደ ቲዲ ጄክ፣ እንደነ ኬኔት ኮፕላንድና እንደነጆይስ ማየር አይነቶች በአባሎቻቸው ላይ ያላቸው ተፅእኖ የአሽከርና የጌታ ያህል ነው። የእነኝህ ብልፅግናውያን አገልግሎትና እንቅስቃሴ ዋና የደም ስር የሆነው አባላቸው ደህይቶ፣ እነሱ ስመጥር ባለፀጋዎች ሆነዋል። በጣም የሚገርመው ነገር ደግሞ የሚንደላቀቁበትን ሃብት የሚሰጣቸውን ህዝባቸውን ራሱን መልሰው ሲንቁትና እንደ ጀሌያቸው ሲቆሩጡት ነው። የብልፅግና ወንጌል አስተማሪዎች ምእመናኑን በእምነት ከጌታ በረከትን እንዲጠብቅ ያስተምሩታል እነሱ ግን “እጅ በእጅ ፍቅር እንዲደረጅ” እንዳለው የሃገሬ ጉራጌ፣ በእምነት ሳይሆን በሚታይና በሚጨበጥ ጥሬ ገንዘብ (cash) ነው የሚደራደሩት። የአባሎቻቸው አስራትና ስጦታ ለሽቶ፣ ለሱፍ፣ ለጫማ፣ ለውድ መኪናዎች፣ ለግል ፕሌኖች፣ ለወርቅ፣ ለብዙ ሚሊዮን ዶላር ቤቶችና ለወፍራም የግል ባንክ አካውንት ነው የሚውለው። ስለብልፅግና ወንጌል ማንበብ የጀመርኩት ከብዙ አመታት በፊት ነበር። ከ 20 አመታት በፊት አሜሪካ በብልፅግና ወንጌል ቴሌቪዢን ሰባኪዎች (Televisionpreachers/Teleevangelists) ቁማርና ወንጀል ታምሳ በነበረበት ጊዜ እኔ እዚሁ አሜሪካ አሁን የምኖርበት ስቴት ነበር የምኖረው። እውቅና የነበራቸው የብልፅግና ወንጌል አስተማሪዎች አንድ በአንድ ወደላይ እንደወጡ እንደ ሉሲፈር ወደታች የተወረወሩባቸውን ወቅቶች በደንብ አስታውሳለሁ። ከፀጋ ከወደቁት የዶክትሪኑ አስተማሪዎች አንዱ የሆነው ጂም ቤከር የምእመናንን ገንዘብ ወደግል አካውንት በማዘዋወር ተከሶ ከሚወዳት ሚስቱ ከታሚ ቤከር (ወደ ጌታ ሄዳለች ከብዙ አመታት በፊት) ተለይቶ በ48 አመታት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተፈርዶበት ወደ እስርቤት ሲላክ ቴሌቪዥን ላይ ተጣብቆ የተከታተለው የአሜሪካ ህዝብ ቁጥር ቀላል አልነበረም። በኋላ ግን የጂም ቤከር ቅጣት በጥሩ ጠባይ ተቀንሶለት ከ 8 አመታት በኋላ ተፈታ። ያ ዘመን የብልፅግና ወንጌል ቴሌቪዥን ሰባኪዎች ዙሪያ ገፃቸውን በህዝብ ቁጣ ተከበው የነበረበት ዘመን ነበር። ሌላው ትልቅ የመነጋገሪያ ርእስ የነበረው የብልፅግና ወንጌል ሰባኪ ኦራል ሮበርት በ 1987 በህዝብ ፊት፣ በህዝብ መገናኛ ወጥቶ “እግዚአብሔር በአንድ ወር ውስጥ 8 ሚሊዮን ዶላር ካልሰበሰብክ እገድልሃለሁ ብሎኛልና እባካችሁ ገንዘብ ስጡኝና ከሞት አድኑኝ” ብሎ ተናገረ። መቼም የአሜሪካን ህዝብ የዋህም ሩህሩህም ነውና የተባለውን ገንዘብ በተባለው ጊዘ ሰበሰበለት። የሚገርመው ግን ያም በቂ አይደለም ብሎ ሌላ 8 ሚሊዮን ብር እንዲሰበስቡለት የጠየቀበት ሁኔታ ነበር ያለው። እግዚአብሔር ብር ካላዋጣህ እገድልሃለሁ ብሎኛል ማለቱ በማያምኑ መካከል ሳይቀር መሳለቂያ ነገር ሆኖ ነበር። ከዚያም ወዲህ በተለያዩ ወቅቶች የብልፅግና ወንጌል ሰባኪዎች እንደነ ቢሾፕ ላንግ (ነፍስ ይማር)፣ ሮበርት ቲልተን፣ ጆዌል ኦስተን፣ ቲዲ ጄክ፣ በኒሂን፣ ክራፍሎ ዶላር፣ ጆይስ ሜየርና ሌሎችም በርካታ ብልፅግናውያን የአገልግታቸውና የዕለት ዕለት አስረሽ ምቺው ሕይወታቸው ጉዳይ ለትልቅ ምርመራ (Scrutiny) ተዳርጎ ነበር። መቼም ምን አለፋችሁ በወንጌል ታሪክ ውስጥ በጴንጤቆስጤና በሌሎችም ክርዝማቲክ ቤተክርስቲያናት ውስጥ በተለያየ ወቅት ከተነሱት ሃሰተኛ ትምህርቶች ሁሉ አንደ ብልፅግና ወንጌል (prosperity Gospel) አማኙን ህዝብ ከምድር ዳርቻ እስከምድር ዳርቻ የጎዳ ትምህርት የለም። ዛሬም እየተራባ ነው። ብልፅግና ወንጌል የማያሻማ ስርቆት ነው። ስለዚህም ይህ የአጭበርባሪዎች ትምህርት በብዙ መንገድ ቤተክርስቲያናት ብቻ ሳይሆኑ መንግስትም ሊከታተለው የሚገባ ነገር ሆኖ ሳለ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ከልካይ ስላላገኘ ከዓመት ወደ ዓመት እየሰፋና እያደገ ነው የሄደው። እውነትን ወዳድ የሆኑ ኢትዮጵያውያን አገልጋዮችም ጭምር ይህንን ትምህርት በሃገራችን ህዝብ መሃከል የሚዘሩ አጭበርባሪ ሰባኪዎችን ሁሉ በአንድነት እንዲያወግዙም ጥሪዬን አቀርባለሁ። ብልፅግና ወንጌል ከየት መጣ እነማን አመጡት? የብልፅግና ወንጌል ፅንሰሃሳብ የተፈጤረው የእምነት ቃል (Word of faith) ከተባለ ትምህርት ነው። የእምነት ቃል በጭሩ አንድ አማኝ ቀና ቀናውን በማሰብና በእምነት ከፈጣሪ እንዲደረግለት የሚፈልገውን ነገር በንግግር/በአንደበቱ በመናዘዝ/በመናገር በአእምሮውም ሳይጠራጠር በመቀበል የልቡን መሻት ሊያገኝ ይችላል ብሎ የሚያስተጋባ ሀተታ ነው። ይህ ዱቄት እንኳን መያዝ የማይችል ወንፊት ትምህርት/እምነት በአጋጣሚ ከሚሊዮን አንድ ካልሆነ በተቀር የማይፈፀም የቅዠት ነፀብራቅ ነው። የእምነት ቃል (word of faith) በ 20 ኛው ክፍለዘመን መጨረሻ በክርስማቲክ ጴንጤቆስጤዎች ጎራ የተፈጠረ ትምህርት ሲሆን ትምህርቱ እግሮች አውጥቶ እንዲሮጥ ያደረጉት ወስላታ የእምነት አስተማሪዎችና መሪዎች አሉት። ከነዚያም ውስጥ ኬኔት ሄገን የተባለው ሰው የትምህርቱ አባት በሚባል ይታወቃል። ነገር ግን ከእሱ በፊት የቃለ እምነትን መሰረት የጣለው ፋይነስ ፓርከርስት ኩዋምቢ (Phineas Parkhurst Quimby (1802-1866) የተባለ ሲሆን ፋይነስ ለኬንዮን፣ ኬንዮን ለኬነት ሄገን እንዳስተላለፉት ነው የሚታወቀው። የእምነት ቃል “የሰው እምነት እግዚአብሔርንም ያዘዋል ነው የሚለው። በዚያም አባባል “”እምነት” ከእግዚአብሔር ውጭ የሚሰራ ራሱን የቻለ ሃይል ያስመስለዋል። እውነታው ግን ሰው እምነትም ኖሮት የጠየቀውን ወይም የፈለገውን ከእግዚአብሔር ላያገኝ ይችላል። ወይም “የፈልጉትን ሰጣቸው ለነፍሳቸው ግን ክሳትን ላከ” (መዝሙር 106: 15) እንደሚል አንዳንዴ የፀለይንበትን አግኝተን ነገር ግን ጥቅሙ ሳይሆን ጉዳቱን እናጭዳለን። የ ”ቃለ እምነት” ወይም “የእምነት ቃል” አስተማሪዎች በቃሉ ላይ ከመመስረት ይልቅ እግዚአብሔር በተለየ መንገድ ለእነሱ የሚገልጠው የተለየ የቃለ እምነት መገለጥ አለ እያሉ ነው ህዝብን የሚያጭበረብሩት። መጽሐፍ ቅዱስን የእነሱን አጀንዳ እንዲደግፍ አድርገው በመተርጎም ያው እንደሚታየው በሕንፃ ላይ ሕንፃ የሚገነቡ ቢሊዮነሮች ሆነው ቁጭ ብለዋል። መጽሐፍ ቅዱስን ቁጭ አድርገው በመገለጥ፣ አየን ወይም ሰማን በሚሉት መሰረት ዬለሽ ቅብጥርጥር ሰውን ይዋሹታል፣ይዘርፉታል፣ ያደኸዩታል፣ ያሞኙታል። የቃለ እምነት (Word of faith) በጨረፍታ 1/ሰዎች ትናንሽ እግዚአብሔሮች ናቸው ምክንያቱም ሲፈጥሩ ሙሉ የእግዚአብሔርን ባህሪይ ተሰጥቶአቸዋል ይላል። ሰው በምድርንና በውስጧ ባሉት ላይ ትንሹ እግዚአብሔር እንዲሆን እንዲያዝና እንዲገዛ፣ እግዚአብሔር ስልጣኑንና ኃይሉን ሰጠው። እግዚአብሔርን የሰማዩን መንግስት ሲመራ ሰው ደግሞ ምድሪቱን ሊገዛ ማለት ነው (Capps, Authority in Three Worlds, pp. 16-17). እውነታው ግን በሰማይም በምድርም አንድ እግዚአብሔር ብቻ ነው ያለው። ሰው መቼም እግዚአብሔር አልነበረም አይሆንምም (ዮሐ 17:3)። ከሱ በፊት ከሱ በኋላም ሌላ እግዚአብሔር አልተፈጠረም አይፈጠርምም (ኢሳያስ 43 : 10). 2/ እምነት በቃል የሚንቀሳቀስ ሃይል ነው። የሚጨበጥ የሚዳሰስ ያህል ነገራትን የሚያንቀሳቅስ፣ እግዚአብሔርን የሚያዝ ገፊ ነው። እውነታው ግን እምነት በእግዚአብሔር ቃልኪዳኖች ላይ መታመን ብቻ ነው። (ዕብራይስጥ 11:1)። እምነት ብቻውን እግዚእብሔርን አያዘውም። እኛ የሰው ልጆች የማናውቃቸው ነገርግን እግዚአብሔር የሚያያቸው፣ የሚያገናዝባቸው ነገሮች ሁሉ ለጠየቅነው ነገር ከእግዚአብሔር ምን አይነት መልስ እንደምናገኝ፣ መቼ እንደምናገኝ ይወስናሉ። እምነት አለኝ ገንዘብ አምጣ የምንለው አምላክ አይደለም የምናመልከው። ብልፅግና ወንጌል ከቃለ እምነት ጋር የተያያዘ ሆኖ ሳለ አንድ ልዩነት ግን አላቸው። ያም ልዩነት የብልፅግና ወንጌል ወሮበላዎች በእምነት ውስጥ ገንዘብን አስተዋወቁ። ለመጀመሪያ ጊዜ “የእምነትን ቅንጣት ዝሩ” ማለት የጀመረው ከላይ የጠቀስነው ኦራል ሮበርት የተባለው የብልፅግና ወንጌል ሰባኪ ነበር። አያችሁ የእምነትን ቅንጣት የምትዘሩት በገንዘብ ነው ማለት ነው። አማኞች ለምን የእምነትን ቅንጣት በእምነት፣ ገንዘብና ወርቅ በሌለበት መዝራት አይችሉም?? ያቺ ለእምነት ቅንጣት የተጠየቀችው ገንዘብ ወደሰባኪዎቹ ኪስ የምትገባ ገንዘብ ናት። ያቺ ገንዘብ ቀላል ገንዘብ አይደለችም። ብዙዎቹን የብልፅግና ወንጌል ሰባኪዎች የግል ጄት ባለቤቶች እንዲሆኑ ያደረገች ያቺ የእምነት ቅንጣት (seed of faith)ብር ናት። በአሜሪካን አገር በ”እምነት ቅንጣት” ዝሩ ሳቢያ የናጠጡ የወንጌል ወስላቶች በአሜሪካን አገር በአንድ ወቅት በኮንግረስ ሳይቀር ገቢና ወጪያቸው እንዲመረመር ተደርጎ ነበር። ብልፅግና ወንጌል ከሌሎች ሃሰተኛ ትምህርቶች ሁሉ የከፋ ነው ብዬ ያልኩበት ምክንያት ምንድነው? የብልፅግና ወንጌል 1ኛ/ የእግዚአብሔርን መለዮና ባህርይ ደልዞ የሌለውን ባህሪይ ይሰጠዋል። እግዚአብሔርንና ምድራዊ ሃብትን ያዛምዳቸዋል። እግዚአብሔርና ገንዘብ ምን ያገናኛቸዋል? ገንዘብ ለሰጡት ገንዘብ የሚሰጥ ላልሰጡት ደግሞ የማይሰጥ? ገንዘብ ከሰጡት ጤንነትንና ስኬትን የሚሰጥ፣ ገንዘብ ካልሰጡት ግን ግድ የሌለው? ለመሆኑ ይህ የእግዚአብሔር ባህርይ ነው? አይደለም (ማቴዎስ 19:23-24 ፣ 1 ጢሞቴዎስ 6:10) 2ኛ/ የእምነትን ምንነት፣ በአማኞች ህይወት ውስጥ የሚጫወተውንም ሚና ፍፁም ያጣምመዋል። የእምነት ቅንጣት (ዘር) ና ገንዘብ ምን አገናኘው? እምነት የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። እምነት ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የሚዋሃድበት መለኮታዊ ልምምድ ነው። በገንዘብ አይገኝም። በገንዘብ አይሸጥም፣ በገንዘብ አይለወጥም (ኤፌሶን 2:8) 3ኛ/ በድህነት የሚማቅቁንና በበሽታ የተጎሳቀሉ ሰዎችን ኢላማ ያደርጋል። ስለዚህም በአሁኑ ወቅት የብልፅግና ወንጌል ዋና መራቢያ ቦታ አፍሪካ ሆኖአል። በኢትዮጵያም በግልፅ ይህንን የሌብነት ወንጌል እየሰበኩ ህዝቡን የሚሰርቁ ሰባኪዎች አሉ። እነሱን በህብረት ማውገዝ ይገባል። ያላችሁን አሟጣችሁ ከሰጣችሁ ሃብታም ትሆናላችሁ፣ ጤና ትሆናላችሁ ፣ በሚል የቀረቻቸውን ቤሳቤስቲን በመውሰድ በእግዚአብሔርም ላይ ያላቸውን እምነት ይነጥቃቸዋል። 4ኛ/ ብልፅግና ወንጌል የሚያበለፅገው ሰባኪውን ወይም መጋቢውንና የእርሱ ፍርፋሪ ለቃቃሚዎች የሆኑትን አጃቢዎቹን ብቻ ነው። ህዝቡ ግን ያለውን ለመጋቢው ወይም ለሰባኪው ሰጥቶ ላም አለኝ በሰማይ እንዳለ በባዶ ተስፋ አይኑን እንዳፈጠጠ ይቀራል። 5ኛ/ ህዝቡ ያለውን እየሟጠጠ ከሰጠ በኋላ በሰባኪው የተነገረው የሰማይ ብርና ወርቅ ሲዘገይና ሳይከሰት ሲቀር፣ ጮሌው ሰባኪ መልሶ እምነት ስለጎደለህ ነው፣ ኃጢአትህን ስላልተናዘዝክ ነው ከእግዚአብሔር ገንዘብ ወይም ጤንነት ያላገኘኸው ወይም ያላገኘሽው ብሎ ጥፋቱን በተዘረፈው(ችው) ደሃ ይላክካል። ይህም አሰራር ዋሾው የብልፅግና ወንጌል ሰባኪ (ዘራፊ) የእኔ ጥፋት አይደለም ብሎ እንዲያሳብብ ቀዳዳ ከመስጠቱም በላይ ተዘራፊዎቹ የደረሰባቸውን ጥቃት በራሳችን ጥፋት ነው ብለው እንዲቀበሉና ወደ ህግም እንዳይሄዱ ያግዳቸዋል። የጥቃት ጥቃት። 6ኛ/ እግዚአብሔርን በፎርሙላ ማንቀሳቀስ ይቻላል ይላል። ልክ እንደ ሂሳብ ትምህርት የተደነገጉ የአሰራር ፎርሙላዎችን ለተከተለ ሁልጊዜ ወደተጠበቀው ውጤት እንደሚወስድ ሁሉ የብልፅግና ወንጌል ትምህርትም አንድ ሰው እምነት ካለውና ይሆንልኛል ብሎ እስካመነና በቃሉም እስከተናዘዘ ድረስ ወይም በአእምሮው የጠየቀውን ነገር ሲቀበል ማየት ከቻለ የጠየቀው ነገር ከእግዚአብሔር ይሰጠዋል ይላል። ይህ ደግሞ ፍፁም ውሸት ነው። የእግዚአብሔር ምላሽ አዎንታ ወይም አሉታ የሚሆንበት ምክንያት ሁልጊዜ ለሰዎች አይታወቅም። እግዚአብሔር ሥራው በተለያዩ ወቅቶች የተለያዩ ናቸው። እምነትም ኖሮን፣ በቃላችንና በስነልቦናችንም ተናዘን የጠየቅነው ነገር ላይሰጠን ይችላል። ወይም ገንዘብ ጠይቀን ጤንነት እንቀበል ይሆናል። እግዚአብሔር በፎርሙላ አይሰራም። ማንም አያዘውም። የአገራችንን ምስኪን ህዝብ የሚግጡ የብልፅግናና የቃል እምነት (word of faith) ሰባኪዎች ደሃውን ህዝብ ሃብታም ትሆናለህ፣ ከበሽታህ በእምነት ትፈወሳለህ፣ ድህነት አይነካህም፣ ከእንግዲህ እያሉ በጋጡት ገንዘብ ሚሊየነሮች ሆነዋል። አንዳንዶቹ ከየክልሉ ሌሎቹም ከዚያው ከአዲስ አበባ የተጠራቀሙ የኢየሱስን ስም የሚሸቅጡ ነውረኞችና ዘራፊዎች ከፍተኛ ድጋፍ ከዚህ ከወንበዴ መንግስት ስላገኙ ያለምንም ፍራቻ ወንጀላቸውን እየፈፀሙ ነው። ዶ/ር አቢይ አህመድ የወንጀለኞች ሿሚ ጠ/ሚኒስትር ቤተ መንግሥታቸው ድረስ ከሚጋብዟቸው ውስጥ የቃል እምነቶችና የብልፅግና ወንጌል ሰባኪ አጭበርባሪዎች ይገኙበታል። እንዲያውም እነኚህ ዘራፊዎችና ጤናማ ወንጌል ሰባኪዎች ይቅር ተባብለው አንድ ማኅበር እንዲጠጡ ባዘዙት መሠረት ከጥቂቶች በተቀር ካውንስል መስርተው በአንድ ተቋዳሽ ሆነዋል። ጤነኛዎቹ ተብለው ይከበሩ የነበሩ ሰባኪዎችና መጋቢዎች፣ ሃሰተኛ ነቢያትንና ሐዋርያትን (እነሱው ናቸው ብልፅግናና ቃል እምነትን የሚሰብኩት) አቅፈው ስመው “ድሮም እኮ ልዩነታችን ጥቃቅን ነበር” “ሥራቸውን እንጂ እነሱን አልጠላም” የሚሉ ሰበቦችን እያዥጎደጎዱ በአንድ ላይ “በካውንስሉ” ስም ይሰራሉ። ጤናማ ዘማሪዎችና ሰባኪዎችም በካውንስሉ ስብሰባዎች እየተገኙ ፕሮግራማቸውን ያደምቁላቸዋል። ዛሬ “ሰው ትንሹ እግዚአብሔር ነው” የሚሉ ወሮበላዎች እድሜ ለጠ/ሚኒስትር አቢይ አህመድ ወደ ከርቸሌ መጋዝ ሲኖርባቸው ምላሳቸውን እያወጡ ያላግጡብናል። ባለዲዛይነር ሱፎች ናቸው። ከየት አመጡት ገንዘቡን አይሰሩ አይነግዱ? ከምስኪን ደሃዎች፣ ከህመምተኞች፣ እምነተ ለጋዎች ኪስ ነው የሰበሰቡት። ይህ ሴይጣናዊ ትምህርት በአሜሪካም ሆነ በአፍሪካ እንደ ሰደድ እሳት የተሰራጨው በኢኮኖሚ በተጎዱት ህብረተሰቦች መካከል ነው። ምክንያቱም ግልፅ ነው። ደሃ ከድህነቱ የሚያላቅቀው ነገር አለ ከተባለ የትም ይሄዳል። ምንም ያድርግ ? ህዝብ ሞኝ ስለሆነ ሳይሆን ቢጨንቀው ነው ብልፅግና ብልፅግና የሚሉትን ሰባኪዎች የሚከተለው። የብልፅግና ወንጌል ሰባኪዎች አፍሪካ ድረስ ዘልቀው ታዋቂ መጋቢዎችን እየተጠቀሙ በቀን ከአንድ ዶላር በታች ከሚያገኘው ህዝብ ሳንቲም ይቃረጣሉ። የዚህ ስህተተኛ ትምህርት አዛማቾች በቀጣዩ ዓለም በእግዚአብሔር ዘንድ የሚጠየቁ ቢሆንም በምድር ደግሞ ብዙ ጥፋት ሳያጠፉ በፍርድቤትና በዳኞች ፊት ሊቀርቡ የሚገባው ነው። እውነትን የሚወድ ሁሉ ደግሞ ሊያወግዛቸው ይገባል። (ዶ/ር ደረጀ ከበደ፣ 2020- 5 years ago)

Friday, August 29, 2025

እንዳንጠፋ ድነታችንን በጸጋው ኃይል አጽንተን እንጠብቃለን!

በጌታችንንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ አንዴ ድነናል፣ በዚህ ድነት በመንፈስ እንመላለሳለን፣ ኃጢአትን አንፈፅምም! “ነገር ግን እላለሁ፥ በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ።” — ገላትያ 5፥16 የሀልዎተ እግዚአብሔር ቤተክርስቲያን መጋቢ ዘነበ ግርማ ድነታችን በሕይወት ዘመናችን በጽድቅና በቅድስና በመመላለስ ካልፈጸምነው ልንጠፋ እንችላለን ብሎ ያስተማረውን ትምህርት የሪል ስቴቱ ባለቤት ነብይ በላይ ሽፈራውና ኢየሱስ ክርስቶስ የሞተው ለተመረጡት ሰዎች ብቻ እንጂ ለዓለሙ ሁሉ አይደለም ብሎ የሚያስተምረው አማን ሻሎም የተባሉት ነብይ ዘነበን ተቃውመው የሙግት ትምህርት ሲለፈልፉ ሰማሁ። አዘንኩም፣ ገረመኝም። ያዘንኩት እነዚህ ተቃዋሚዎች ከእነሱ በስተቀር የቃል እውቀት ማንም እንደሌለው አስበው መናገራቸው ሲሆን የገረመኝ ለከት የሌለው ባዶነታቸውን በአደባባይ ሲገልጹ አለማፈራቸው ነው። የዘነበን፣ የበላይ፣ የአማን ሻሎም እና የተመሳሳይ ሰዎች አስተምህሮ በመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ከመበርበራችን በፊት እንደመግቢያ የመጀመሪያውን ሰው የአዳምን ማንነት እንደማስረጃ እንመልከት። አዳም እንዲኖር የተሰጠው ቦታ የት ነበር ብትባሉ በገነት እንደምትሉ እርግጠኛ ነን። የሰው ልጆች ከዚህ ምድር በሞት ሲለዩ ነፍሳቸው የት ትሄዳለች ብለን ብንጠይቃችሁ መልሳችሁ ምን ሊሆን ይችላል? በገነት ልትሉ እንደምትችሉ ብንገምት የተሳሳትን አይመስለንም። ምክንያቱም ከኢየሱስ ጋር ከተሰቀለው አንዱን ፍርደኛ ኢየሱስ እንደዚህ ሲል ሰምተነዋል። “ኢየሱስም፦ እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ አለው።” — ሉቃስ 23፥43 በፊትም አዳም የኖረበት፣ በኋላም በኢየሱስ ክርስቶስ ያመንን እኛ የምንኖርበት ቦታ ገነት መሆኑን እንረዳለን። አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እስኪፈጠሩ መኖሪያችን ዔድን ገነት ነው። “ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን።” — 2ኛ ጴጥሮስ 3፥13 እሺ! እውነቱ ይህ ከሆነ አዳምን ለዘላለም ይኖር ዘንድ እግዚአብሔር ከሰጠው መልካም ሥፍራ ከሆነው ገነት ያስወጣው ምንድነው? እግዚአብሔር አዳምን በገነት ማኖር ስላልፈለገ ነው እንዴ ከገነት የተባረረው? አይደለም! አዳም ከሚስቱ ጋር የእግዚአብሔርን ቃል በገዛ ምርጫቸው ስላፈረሱ ነው። ባለመታዘዝና የተሰጣቸውን ትዕዛዝ በማፍረሳቸው፣ ከእግዚአብሔር ድምፅ ይልቅ የሰይጣንን ፈቃድ ለመፈፀም ፈቃደኛ ስለሆኑ ነው የተባረሩት። ሁሉን አዋቂ እግዚአብሔር አዳም እንደሚሳሳት አያውቅም ነበር? እግዚአብሔር አስቀድሞ ያውቃል! የእግዚአብሔር ሁሉን አዋቂነት የሰውን ልጆችን ነጻ ምርጫ አይጋፋም። ማወቅና መረዳት የምንችልበትን ነፍስያ ባህርይውን ያካፈለን ለዚህ ነው። በምርጫህ ወደህ፣ አምነህ ታመልከዋለህ፣ አልፈልግህም ብለኸው ለኃጢአት ብትገዛ ከኃጢአት የሚታጨደውን ደመወዝ በምርጫህ ትቀበላለህ። ስለሆነም አዳም በበደለ ጊዜ ዐመጽና ኃጢአት ከእግዚአብሔር አምላካዊ ባህርይ ጋር በገነት አብሮ መኖር ስለማይችል አዳም ከቅዱሱ ከእግዚአብሔር ፊት ተባረረ። የመጀመሪያው አዳም ሕይወት የተጠናቀቀው በዚህ የእውነት ፍርድ ነው። የመጀመሪያው አዳም ከተጠናቀቀበት ፍርድ ነጻ ለመውጣት ዋጋ ከፍሎ ወደ አዳነው ወደ ሁለተኛው አዳም እንምጣ! ሁለተኛው አዳም የመጀመሪያው አዳምንና ልጆቹን ለማዳን ከኃጢአት የነጻ፣ ለእግዚአብሔር አልታዘዝም ከሚል ዐመጽ የተለየ ንጹህ ነበር። ለዚህም የማዳን ሥራ ራሱ እግዚአብሔር ሰው ሆኖ መጣ። “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን።” — ዮሐንስ 1፥14 እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ ሆኖ ሳለ በቃሉ ብቻ አዳምን ወደገነት መመለስ እየቻለ ለምን ሰው መሆን አስፈለገው? ብለን ስንጠይቅ መልሳችን እግዚአብሔር በጽድቅ ፈራጅ፣ በእውነትም ፍትህ ሰጪ ስለሆነ ነው የሚል ይሆናል። ዳዊት በመዝሙሩ እንዳለው። “እርሱም ዓለምን በጽድቅ ይፈርዳታል፥ አሕዛብንም በቅንነት ይዳኛቸዋል።” — መዝሙር 9፥8 ለኃጢአት ዋጋ ፍርድ ሳይሰጥ ጽድቅ የለም። ከእግዚአብሔርም ጋር እርቅ አይኖርም። የስርየት መስዋእቱም ደም ነበር። ለዚህ ነበር እግዚአብሔር ራሱ ሰው የሆነውና ስለአዳም ኃጢአት የደም መስዋእት የከፈለው። ፊልጵስዩስ 2፣6-8 "እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ።" አዳም ለኃጢአት ሲታዘዝ ተባረረ። ኢየሱስ ለጽድቅ ሲታዘዝ ሕይወት ሆነልን። እስከዚህ ድረስ መግቢያ ይሆነን ዘንድ ስለወደቀው የመጀመሪያው አዳምና የዘላለም ሕይወት ስለሆነው ስለሁለተኛው አዳም፣ ኢየሱስ ቤዛነት ይሄንን ያህል ካልን ስለእነዘነበ ግርማ፣ በላይ ሸፈራውና አማን ሻሎም የክርክር ጉዳይ እንግባ። ነብይ ዘነበ ግርማ ስለድነት በተናገረበት አንቀጽ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ በነጻ የተሰጠንን ዋጋ መጠበቅ አለብን፣ ከኃጢአት ካልጠበቅነው የዘላለም ሞት ያገኘናል፣ የተሰጠንን ድነት ልናጣ እንችላለን የሚል ይዘት የነበረው አስተምህሮ አቅርቦ ነበር። በላይ ሽፈራውና አማን ሻሎም የተባሉት ሰዎች ደግሞ በተቃውሞ የሰጡት መልስ የተሰጠንን ድነት እኛ መጠበቅ አይጠበቅብንም። አንዴ ድነናል፣ ይሄንን ድነት የትኛውም ኃጢአት አያጠፋብንም፣ የሚጠፋ ከሆነ ለዘላለም አልዳንም ማለት ነው ሲሉ የሚያግዛቸውን ጥቅስ በማቅረብ እውነቱ በነሱ ዘንድ ብቻ እንዳለ ለማስረዳት ታግለዋል። እዚህ ላይ እኛ ጥያቄ እናንሳ! ከላይ በመግቢያችን ለማብራራት የሞከርነው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እዚህ ላይ ይነሳል። የመጀመሪያው ሰው፣ አዳም ገነት የገባው ለጊዜው ነበር እንዴ? አይደለም! እግዚአብሔር ሰውኛ ድራማ ስለማይጫወት አዳም የተፈጠረው ከእርሱ ጋር ለዘላለም እንዲኖር እንጂ አዳም የበለሲቱን ፍሬ እስኪበላ ድረስ ለጊዜያዊ ማቆያነት አልነበረም። አዳም የተፈጠረበትን ዘላለማዊ ሕይወት የተሰጠውንና ከእግዚአብሔር ጋር ከመኖር ይልቅ የጠላቱን ድምፅ ሰምቶ ሞትን በራሱ ላይ ስላመጣ እግዚአብሔር ጻድቅ ሆኖ ሳለ ዐመጸኛ እንዴት ከእርሱ ጋር ኅብረት ሊያደርግ ስለማይችል በፍርድ ቀንበር ስር ወደቀ። ዐመጸኛ ከእግዚአብሔር ፍርድ ሊያመልጥ አይችልም። የመጀመሪያው አዳም እምቢተኛ ሲሆን ሁለተኛው አዳም የመጣው ደግሞ የአባቱን ትዕዛዝ ለመፈጸም ነው። “ፈቃዴን ለማድረግ አይደለም እንጂ የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ከሰማይ ወርጃለሁና።” — ዮሐንስ 6፥38 በኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ የዘላለም ሕይወት በማመን ያገኘ ሰው፣ ዐመጸኛ ሆኖ የዲያብሎስን ድምፅ ቢሰማ ሊሆን ይችላል? አትጠራጠር፣ የዘላለም ሞት ይፈረድበታል! ኢየሱስ ሞት ዋጋ ያለው በሁለት መንገድ ነው። አንደኛው ዋጋ ኢየሱስ የተወደደ የእግዚአብሔር መስዋእት ሆኖ ከአዳም ኃጢአት መዳንህን ባመንክበት ቅጽበት ስርየት ሆኖልህ የእግዚአብሔር ልጅ ትሆናለህ። “አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና።” — ሮሜ 8፥15 ልጅ በቅዱሱ በአባቱ ፊት ምን መሆን ይጠበቅበታል? ይሄ ሁለተኛው የኢየሱስ የሞት ዋጋ በእግዚአብሔር ፊት ልጆቹ ሆነን የምንመላለስበት ጉልበታችን ነው። ጸጋ ይባላል። “ነገር ግን እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጠን።” ኤፌሶን 4፥7 ይህ ጸጋ በእምነት የዳንነውና የእግዚአብሔር ልጆች የሆንነው እኛን ምን ያደርግልናል? “ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል፤” — ቲቶ 2፥12-13 በኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ አምኖ የዳነ ሰው በጽድቅ መኖር ግዴታው ነው። የተሰጠው ድነት በነጻ ነው ማለት ዋጋ አልተከፈለበትም ማለት አይደለም። “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፥ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም።” — ማቴዎስ 7፥21 አዎ፣ በሥራችን አልዳንም። ይህ ማለት ግን ሥራ የለብንም ማለት አይደለም። በላይ ሽፈራውና አማን ሻሎም ይሄንን ቃል አይወዱትም። በእምነት አገኘነው ያሉትን ድነት ለሥጋ ፈቃዳቸው የሚከለክል ቃል ስለሆነ አይጠቅሱትም። አንዴ የተሰጠን ድነት በእኛ ስራ አይጠበቅም ይላሉ። ባንሰራም ያገኘነው ድነት አይጠፋብንም ብለው ይጮሃሉ። የሚጠፋ ከሆነ ቀድሞውኑ አልተሰጠንም ነበር እያሉ ስጦታቸውን ለፈለጉት የዐመጽ ተግባር እንደማስረጃ እንዲቆጠርላቸው ይታገላሉ። የተሰጠህን ነጻ ውድ ስጦታ ካልጠበከው ስጦታው ቀድሞውኑ አልነበረም ማለት ነው እንዴ? ስጦታው የማይጠፋ ነው። የማይጠፋው የሰማይ ስጦታ ስለሆነ ነው። ነገር ግን የሰው ልጅ አጥፊ ልምምድ ስላለው ሊያጠፋው ይችላል። ምሳሌው የገነቱን አዳም አስብ። “እንደዚሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው።” ያዕቆብ 2፥17 ዐመፀኞች ለተሰጣቸው ድነት ሥራ ስለሌላቸው ዐመጽነታቸውን የሚደግፍ ጥቅስ ይደረድራሉ። አዳም በሄዋን፣ ሄዋንም በእባብ እባብም በዐመጽ ምክንታቸው ስር ቢደበቁም ከፍርድ አላመለጡም። የዚህ ዘመን ወንጌላውያን የተባሉት አብዛኛዎቹ መንፈሳዊ መረዳት የላቸውም። ብዙ አንብበው፣ ብዙ የቲዎሎጂ ትምህርት ቢኖራቸውም ብዙ አነበቡ እንጂ ከመንፈሳዊ እውቀት የተለዩ ዝናብ የሌለባቸው ዳመናዎች ናቸው። ዳዊት ፋሲል የሚባልም ግብዝ ሰው በተሳልቆና እውቀት በሚመስል የፌዝ ንግግር የገነት በር ቁልፍ በእጄ ነውና፣ በኔ በኩል ግቡ በሚመስል መልኩ ብዙ ያወራል። አማን ሻሎም የተባለው ሌላኛው ግብዝ ሰው ራሱን ብዙ ባነበበው መጽሐፎች ውስጥ ደብቆ አዋቂ መስሎ ለመታየት ብዙ ጊዜውን ይጨርሳል። ይጋጋጣል። የተከራካሪዎቹን አፍ ዝም ስላሰኘ በእውቀት የበለጣቸው ይመስለዋል። ከነዚህ ደካማ እውቀቶቹ መካከል አንዱ ኢየሱስ የሞተው ለኛ ለጥቂቶች ነው የሚለውን የጆን ካልቪንን Limited Atonement ወይም Particular Redemption መዳን የሆነው ለተወሰኑት ብቻ ወይም የተመረጡ ብቻ ነው የሚል አስተምህሮ አስፋፊ ነው። ይህ ትምህርት የመጨረሻው የክህደት ጫፍ ነው። እግዚአብሔርን ጨካኝ፣ ፈራጅ አድርጎ የሚከስ ነው። እግዚአብሔር ኢየሱስን የላከው የተወሰኑ ሰዎች ብቻ ለማዳን ከሆነ ከመዳን ውጪ ያሉት ሰዎች ለሲኦል ማገዶነት እግዚአብሔር ያዘጋጃቸው ናቸው ማለቱ ነው። እንዳይድኑ ተደርገው የተፈጠሩ ሰዎችን እግዚአብሔር በእሳት እያቃጠለ ለመደሰት ያዘጋጃቸው ናቸው ማለት እግዚአብሔር ፍቅር አይደለም ማለቱ ነው።። እነዚህ ሰዎች ከዘላለም እሳት ውጪ ለመዳን ምርጫም፣ እድልም የሌላቸው ናቸው ማለት ነው። ይህ ትምህርት ደግሞ ይሄንን የእግዚአብሔር ቃል በቀጥታ ይቃወማል። “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።” — ዮሐንስ 3፥16 እግዚአብሔር አብ አንድያ ልጁን ወደዓለም የላከው የተወሰኑ ሰዎችን ብቻ ለማዳን ብቻ ነው የሚለው አማን ሻሎም Mouthpiece of Satan የሰይጣን አፍ አገልጋይ ነው። በዚህ ቃል ውስጥ ጥቂቶች፣ የተመረጡ፣ የተወሰኑ፣ የተለዩ...የሚል ቃል ይታያችኋል? “ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምኑ ይህ ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክር መጣ።” — ዮሐንስ 1፥7 "ሁሉ" ማለት በግሪክኛ πάντες ፓንቴስ ማለት ሁሉ፣ all, everyone እያንዳንዱ ማለት እንጂ የተወሰኑ፣ የተለዩ ማለት አይደለም። በላይ ሽፈራው አግብቶ የፈታ፣ ዳግመኛ ያገባና ሌላም፣ ሌላም የሚወራበት፣ በሪል ስቴት ገንዘብ ብዙዎች ያለቀሱበት፣ አማን ሻሎም በሱስ የተጠመደ፣ ቀለበት አስሮ የከዳ፣ ሌላም፣ ሌላም ሆነው ሳለ በእግዚአብሔር ፊት በጽድቅ መመላለስ ሲያቅታቸውና ለምኞታቸው ልጓም ማስገባት ሲሳናቸው፣ ለኃጢአታቸው አርነት የሚሰጥ ጥቅስ በማቅረብ የስህተት ደጋፊዎቻቸውን ለማሰባሰብ ይሯሯጣሉ። ማጠቃለያ፣ የዳንነው በኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ በነጻ ነው። በነጻ የተሰጠን ሕይወት ዋጋ ተከፍሎበታል። የከፈለልንን ስለምንወደው ትእዛዛቱን እንጠብቃለን። ትእዛዛቱን የምንጠብቀው ስለምንወደው እንጂ ለመዳን አይደለም። “ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤” — ዮሐንስ 14፥15-16 ያ አጽናኝ ከኃጢአት ይጠብቀናል። ተሳስተን ኃጢአት ብናደርግ ስንኳን የንስሐ እድል አለን። “በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው።” — 1ኛ ዮሐንስ 1፥9 ድነናል፣ ድነታችንን እንጠብቃለን። እንደዴማስ ኢየሱስን ትተን ለዓለም ኃጢአት ባሪያ አንሆንም።

Tuesday, April 22, 2025

“እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን።” ቆላስ 1፥13-14

"ለእኔ ኃጢአት ሥርየት ከሞተልኝ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ ቤዛ የለኝም" “እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን።” — ቆላስይስ 1፥13-14 ቤዛ የሚለውን ቃል አባ ገብርኤል የተባሉ ሊቀጳጳስ ለኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ብለው ለምን ተናገሩ? የሚል ንትርክ ተነስቶ በኦርቶዶክሶች መንደር ጩኸቱ በርክቷል። ይሄ ቤዛ በእንግሊዝኛው/ransom,redemption,deliverer/ በማለት ሲተረጉመው ግሪኩ ደግሞ (λύτρον)ሉትሮን ማለት የተከፈለ ዋጋ፣ (λύτρωσις) ሉትሮሲስ ነፃ መውጣት፣ ከእስራት፣ ከባርነት ለመፈታት የተሰጠ ክፍያ፣ ነጻነት ማለት ነው። የጌታችን፣ የመድኃኒታችንና የአምላካችን ቤዛነት ከየትኛው ምትክነት፣ ነጻ አውጪነት፣ አዳኝነትና ከሞት ታዳጊነት ጋር ለንጽጽር የሚቀርብ አይደለም። በዘመነ ኦሪት በባርነት የተሸጠ ሰው ለባርነቱ ዋጋ የሚከፍል ከተገኘ ነጻ ሊወጣ ይችላል። ለሰው ነፍስ ቤዛው ሀብቱ ነው። ምሳሌ13፣8 የመሳሰሉ ስለቤዛ የተነገሩ የቤዛ ቃል ንግግሮች በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ተፅፈው እናገኛለን። እነዚህ ሁሉ የቤዛነት ትርጉሞች ኢየሱስ ክርስቶስ ካደረገልን ቤዛነት ጋር ለክርክርም፣ ለንጽጽርም፣ ለትርጉም አቻነት የሚቀርቡ አይደለም። የኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት ከዘላለማዊ ድኅነት፣ ከአብ ጋር እርቅ የተደረገበት፣ መርገመ አዳም የተወገደበት፣ የገነት በር የተከፈበት ስለሆነ ከሰማይ በታች የተነገሩ፣ የተጻፉ፣ የተወሩ ስለቤዛ የተተረጎሙ ቃላት፣ ሃሳቦች ለንጽጽር ሊቀርቡ አይችሉም። በእውቀት ለመገራትና ለመመራት እምቢተኛ አእዱገ ገዳም የሆኑ የኦርቶዶክሶች ምእመናን፣ በተረት ተረት ትምህርት ሊቅ የሆኑት ዘበነ ለማ፣ አዋቂ መስሎ ለመታየት ብዙ የሚደክመው ኄኖክ ኃይሌ፣ ክንድ ከስንዘር መስቀል ጨብጠውና አንጠልጥለው ብዙ የሚያጓሩ፣ የተለሰኑ መቃብር መምህራን፣ ቀሳውስትና መነኮሳት ነን ባዮች የጌታችን፣ የመድኃኒታችንና የአምላካችንን ቤዛነትን ከሌሎች ቤዛነት ጋር ለማነጻጸር ወይም ስለቤዛነት የተነገረው ለኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ አይደለም ለማለት ከሰሜን ዋልታ እስከ አንታርክቲካ ሮጠው ያልቆፈሩት ጥቅስ፣ ያልዘበዘቡት ፅሑፍ፣ ያልተረተሩት ትርጉም፣ በእልህና ብስጭት መንጋጋቸው በመንጋ ያላፋጩት ጥርስ የለም። በየፌስቡኩ፣ ቲክቶኩና በየድረገጾቹ ላይ የታየው ጩኸት ተአምር የሚያስብል ነው። እነዚህ ስብስቦች ከኛ ወዲያ እውቀት ላሳር ነው ብለው የአእምሮአቸውን በር የዘጉት ድሮ ነው። ከእነዚህ ሰዎች ጋር ተነጋግሮ መተማመን ላይ መድረስ አይቻልም። አንዳንዴማ ከእኛ በስተቀር የሚጸድቅ የለም ብለው በድፍረት ሲናገሩ መንግሥተ ሰማያት በር ላይ ቆመው አንተ ተመለስ፣ አንተ ግባ ብለው የማዘዝ ስልጣን ያላቸው ያህል ያስባሉ። መንግሥተ ሰማያት የፍትሐት ድግስ የሚበሉበት የደጀሰላም በር ይመስላቸዋል። ለነገሩ አይሁድ ፈሪሳውያን መምህራንና ጻፎችም እንደዚሁ ያደርጋቸው ነበር። እነዚህን መሰል ሰዎች ጌታ በአንድ ወቅት እንዲህ ሲላቸው እናገኛለን። (ማቴ23፣27-32) እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በውጭ አምረው የሚታዩ በውስጡ ግን የሙታን አጥንት ርኩሰትም ሁሉ የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን ስለምትመስሉ፥ ወዮላችሁ። እንዲሁ እናንተ ደግሞ በውጭ ለሰው እንደ ጻድቃን ትታያላችሁ፥ በውስጣችሁ ግን ግብዝነትና ዓመፀኝነት ሞልቶባችኋል። ብሏቸው ነበር። እነዚህኞቹ ወደመንግሥተ ሰማይ ወይ እነሱ አይገቡ፣ ወይ ተከታዮቻቸውን አያስገቡ መንገዱን በተረትና እንቆቅልሽ ስብከት ዘግተውታል። በዚያ ላይ እውቀት አለርጂክ የሆነበት ተከታያቸው ምዕመን በጩኸት ስለሚያጅባቸውና አዋቂ ነን ብለው ስለደመደሙ ከእነሱ የተለየውን ቃል እውነት ቢሆን እንኳን አይቀበሉም። ምእመኖቻቸውም ከመምህራኖቻቸው የባሱ ስለሆኑ ያንኑ የአለቆቻቸውን ትምህርት መልሰው ይጓራሉ። ይጮሃሉ። ማርያም ቤዛ ናት፣ ገብርኤል ቤዛ ነው። ገንዘብ ቤዛ ነው። ወንድምህ ቤዛ ነው፣ ጓደኛህ ቤዛ ነው የሚሉ ቃላትን ለቃቅመው በማምጣት ከኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት ጋር ለንጽጽር፣ ለትርጉምና ለማብራሪያ በማቅረብ ይንጫጫሉ። አንዳንዴ ስትመለከታቸው ክርስቲያን የሚለውን መጠሪያ አምኖ ለመቀበል እስኪከብድህ ድረስ አንደበታቸውና ጽሑፋቸው ልቅ ነው። እነዚህ ተጯጯኺዎች በዘመቻ የተነሱት የቤተክርስቲያኒቱ ጳጳስ አባ ገብርኤል የተባሉት ሰው "ተቀዳሚ፣ ተከታይ የሌለው፣ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻውን የዘላለም ቤዛ ነው" ብለው ስላስተማሩና ማርያምም የዘላለም ቤዛችን አይደለችም ስላሉ ነበር። የዚህን ትምህርት ቃል ለማፍረስና ሌሎችም ቤዛ አሉን ለማለት ያልቆፈሩት የሙግት ትርጉምና ጥቅስ የለም። ዘቤ የተረት አባት በአንድ ወቅት "ያለማርያም አማላጅነት ዓለም አይድንም" ብሎ ሲያስተምር ነበር። ማርያም ማዳን ከቻለች የኢየሱስ ሰው ሆኖ መምጣት ሳያስፈልግ በማርያም ይፈጸም አልነበረም ወይ? ተብሎ ሲጠየቅ እነዲያቆን ያረጋል አበጋዝ ያለማርያም አማላጅነት ዓለም አይድንም ማለት ስህተት ነው ብለው ለማረም ቢሞክሩም ዘቤ የተረት አባት ስህተቱን ሳያምን ዛሬም በተመሳሳይ ስህተት ላይ ይገኛል። ዘበነ ለማን ያክል ቤተክርስቲያኒቱን በአስተምህሮ ስህተት የገደለ ማንም የለም። እነኄኖክ ኃይሌ ላይገባቸው የማሉ ያህል የሚከራከሩት ስለቤዛነት የተሰጠው ትርጉም ለኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ሳይሆን ማርያምን ይጨምራል፣ ሌሎችን ብዙዎችንም በተጨማሪነት ያጠቃልላል ብለው ለመከራከር ሲንደፋደፉ አይተናል። እዚህ ላይ አስረግጠን የሊቀጳጳሱን ትምህርት የተቀበልነውና ስለኢየሱስ ክርስቶስ ብቸኛ አዳኝነትና ቤዛነት ያስተማሩት ትክክል ነው ያልነው ጳጳሱን በተለየ ስለወደድን ሳይሆን ያስተማሩት እውነት ስለሆነ ነው። ለእውቀት አእዱገ ገዳም ለሆኑት ሰዎች የምንነግራቸው ነገር ስለቤዛ የተጻፈና የተነገረ አንድ መቶ ሺህ ጥቅስና ትርጉም ቢኖራችሁ ለንጽጽር የማይቀርብበት የኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት ብቸኛው ነው። የወደቀውን የሰው ልጅ ወደቀደመ ክብሩ ለመመለስ፣ ለበደለው ኃጢአት የተሰጠ ሥርየት፣ የተከፈለ የሞት ዋጋ ምትክ የሆነው ቤዛነት የኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ይሄንን የሚተካ፣ የሚያክል፣ የሚወዳደር፣ የሚቤዥ ሌላ ቤዛ ከሰማይ በታች የለም። ይሄ ቤዛነት ትልቅነቱ ዘላለማዊ፣ መድኃኒትነቱ ሕያው፣ አዳኝነቱ ሞት ያላሸነፈው ነው። ስለቤዛ በትርጉምም፣ በፍቺም በንፅፅርም ከኢየሱስ ቤዛነት ጋር ሊቀርብ የሚችል ሌላ የለም። ስለቤዛ የተነገረ ሌላ ቃል አለ ብለህ ጭንቁር የቃል ክርክር ታቀርብ ይሆናል። ያንን እያነሳህ እንደዚህ ማለት ነው፣ እንደዚያ ማለት ነው እያልክ ውሃ ወቀጣ ክርክር የማንሳት መብት ይኖርሃል። የጻፎችና የፈሪሳውያን ክርክር የወንጌል እውነት ሊቀይረው እንደማይችለው ሁሉ የትኛውም ስለቤዛ የሚሰጥ፣ የተሰጠ ትርጉምና ንጽጽር ጌታችን ካደረግልን ቤዛነት ጋር አይነጻጸርም፣ ለትርጉም ክርክር ሊቀርብ አይችልም። ለነዚህ የተለሰኑ መቃብሮች የምነግራቸው በኔ በኃጢአተኛው ምትክ ቤዛ ሆኖ የሞተ ከኢየሱስ ክርስቶስ በስተቀር ሌላ ቤዛ ማንም የለም ነው የምንላቸው። ቅድስት ማርያም ቤዛ ናት የሚሉ ሰዎችን ታድናለች ወይ? ተብለው ሲጠየቁ አታድንም፣ ግን መድኃኒትን ወልዳልናለች፣ ስለዚህ ቤዛ እንላታለን ይሉናል። በምትክነትና ለኃጢአት ሥርየት እንዳልሞተችልን ከታወቀ በመጽሐፍ እንደተፃፈ "የጌታ እናት" ማለታችን በቂ አይደለም ወይ፣ ባልተፃፈ የቤዛነቷ ትርጉም ላይ ጉንጭ አልፋ ክርክር ለምን ያስፈልጋል? ሲባሉ ጴንጤ፣ ከሀዲ፣ ጸረ ማርያም የሚሉ ስድቦቻቸውን በእውቶማቲክ ይተኩሳሉ። እነዚህ ለእውቀት አእዱገ ገዳም የሆኑ ሊቀ ሊቃውንትና መተርጉመ መጻሕፍት ነን ባዮች በማርያምም፣ በኢየሱስም ሁለት አዳኝ እንዳላቸው ለጎጋ ምዕመኖቻቸው ያለከልካይ እየጮሁ መገኘታቸው ስናይ በነሱ ዘንድ ኢየሱስ ሌላ ብዙ ቤዛ እንዳላቸው እንረዳለን። አሁንም ደግመን እንላለን፣ ለአዳም ልጆች ቤዛ ሆኖ የሞተና ያዳነን ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ ቤዛ የለንም። ስለቤዛ ሚሊየን ትርጉም ቢኖርህ እሱን እያመነዠክ መኖርህ የኢየሱስን ብቸኛ ቤዛነት አይቀይረውም። የኢየሱስን ቤዛነት አምናለሁ ያለ ሰው በኢየሱስ ብቸኛ የቤዛነት ሥራ ላይ ሌላ ትርጉምና ንጽጽር ለምን ይዞ ሊመጣ አይችልም። የሚመስለው፣ የሚተካከለው፣ የዘላለም የሆነ ቤዛነት ከኢየሱስ ውጪ አለ? የለም!!! አዎ! እናውቃለን፣ የኢየሱስን ዘላለማዊ የቤዛነቱን ሥራ በፍጡራንና በምድራዊያን የትርጉም ቃላት ሸፍኖ ለማሳነስና ሰው ሁሉ ወደአንድያ ቤዛው ዓይኑን እንዳያነሳ ለመጋረድ ጠላት በስንዴው መካከል የዘራው እንክርዳድ ነው። እኛ ግን በየትኛውም የቤዛ ትርጉም ሳንወጣ፣ ሳንወርድ፣ ሳንደክም "እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን።” እንላለን። ቆላስይስ 1፥13-14 ሊቀጳጳሱ ስለኢየሱስ ብቸኛና ዘላለማዊ ቤዛነት የተናገሩት ትክክል ነው። ከፍጡራን መካከል ሌላ የዘላለም ቤዛ የሆነልን፣ መሆን የሚችልም የለም። ከሰማይ በታች ቤዛ መሆን የሚችል ስለሌለ ነው አብ አንድያ ልጁን የላከልን። ወስብሐት ለእግዚአብሔር!