Friday, April 22, 2022
ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶልናልና 1ኛ ቆሮ 5፣7
ዕብራውያን פֶּסַח» ፔሳኽ» ይሉታል። ፋሲካ ማለት ነው። በወርኀ ኒሳን በዐሥራ ዐምስተኛው ቀን ይከበራል። ሥርዓቱ የሚጀመረው በዐሥራ አራተኛው ቀን ዋዜማ ሲሆን በፋሲካው ሳምንት እርሾ የገባበት ምንም ዓይነት ምግብ መመገብ ክልክል ነው።ዕለቱን ተቦክቶ ወዲያው የሚጋገር እንጂ የኮመጠጠ ወይም የቦካና የዋለ፤ያደረ መመገብ በሕጉ እንደተቀመጠው ከእስራኤል አንድነት ያስወግዳል። ከማንኛውም እርድ ላይ ጥሬ መብላት ወይም ከበሉትም አስተርፎ ማሳደር አይፈቀድም። ለመስዋዕት የሚቀርበው የበግ ወይም የፍየል መስዋዕትም እድሜው ከአንድ ዓመት ያልበለጠ ጤናማና የተመረጠ መሆን ይገባዋል። በዐሥራ ዐራተኛው ቀን ምሽት መስዋዕቱ ይታረዳል።ሥጋውን ደግሞ ሌሊት ከመራራ ቅጠል ጋር ቀላልቅለው ይበሉታል።
ደሙን ደግሞ የበሩን ሁለት መቃንና ጉበኑን ይቀቡታል። ሁለቱን ቋሚ መቃንና የላይኛውን ጉበን ሲቀቡት ይህንን ቅርጽ ይይዛል።
ይህ ቅርጽ የዕብራውያን ስምንተኛውን ፊደል «ኼ» የተባለውን ይወክላል። (እንደአማርኛው በጉሮሮ ሳይሆን በላንቃ የሚነበብ ነው) «ኼ» ማለት በዕብራውያን ትርጉም «ሕይወት» ማለት ነው። ዕብራውያንም በፊደላቸው በ«ኼ» ቅርጽ በሚቀቡት ደም የተነሳ ወደፈርዖናውያን ሠፈር የሚያልፈው ሞት አይነካቸውም። ምክንያቱም ሕይወት የሚል ማኅተም በራቸው ላይ ታትሟልና። ፋሲካ ማለት ይህ ነው። በደሙ ምልክት የተከለሉ በሕይወት ለመቆየት ዋስትና የያዙ ሲሆን ይህንን ማኅተም ያላገኙና ምን እየሆነ እንዳለ የማያውቁ ደግሞ በሞት የሚወስዱበት የፍርድ ምልክት ነው። ደሙ የሞትና የሕይወት መለያ ምልክት ሆኖ አገልግሏል።
ይህ ሥርዓት እስራኤላውያንን ከባርነት፤ ከጠላት አገዛዝና ከመገደል የታደገ የዋስትና መንገድ ነበር። እንደዚሁ ሁሉ የአዲስ ኪዳኑ ፋሲካ ሕዝብና አሕዛብን ከሰይጣን ባርነትና ከዘላለም ሞት የታደገ በመሆኑ ሐዋርያው ጳውሎስ «እንግዲህ ያለ እርሾ እንዳላችሁ አዲሱን ሊጥ ትሆኑ ዘንድ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ። ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶአልና» 1ኛ ቆሮ 5፤7 በማለት የሚነግረን። የእስራኤል ዘሥጋ ፋሲካ መጻጻና የቦካ ይከለክል እንደነበረው ሁሉ የአዲስ ኪዳኑ ፋሲካም እንዲሁ ይከለክላል። በኃጢአትና በዐመጻ የቦካ የውስጣችንን ሆምጣጣ እርሾ ካላስወገድን በስተቀር በፋሲካው የሚገኘውን ሕይወት በፍጹም አናገኝም። የቀደመው ፋሲካ እርሾ ያለውን ነገር ከቤቱ ያላጠፋ ከእስራኤል ጉባዔ ተለይቶ ይጥፋ የሚል ሕግ ነበረው። ምድራዊው ፋሲካ ይህንን ያህል ከከበረ ሰማያዊውማ እንደምን የበለጠ አይከብር? ፋሲካን መናገርና ፋሲካን አውቆ መኖር የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ስለፋሲካ ብዙ ማስተማርና መናገር ይቻል ይሆናል። ስለፋሲካ የመልካም ጊዜ መግለጫና ስጦታም መለዋወጥ ይቻል ይሆናል። ፋሲካ ግን በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ አይገኝም። ፋሲካ በስግደትና በወይራ ቅጠል በመጠብጠብ የሚገኝም ጸጋ አይደለም። ፋሲካ የአንድ ወቅት ራስን ማስገዛትና በጽኑ እሳቤና ጭንቅ ማለፍ ውስጥ የሚመጣም አይደለም።
ፋሲካ በልባችን መቃንና ጉበን ላይ የደሙን ምልክት በመያዝ ዕብራውያን ከሞት እንዳመለጡበት የ «ኼ» ምልክት ማኅተም በመያዝ ብቻ ነው የምንድነው። ያን ጊዜ ብቻ ነው ሞት በራችን ላይ ያለውን የአዲስ ኪዳኑን ፔሳኽ አይቶ የሚያልፈን። ይህንን የደም ማኅተም ለመያዝም ከክፋት፤ ከሀሰት፤ ከግፍና ከዐመጻ እርሾ መለየት የግድ ነው። ከዝሙት፤ ከስርቆት፤ ከጉቦ፤ ከምኞትና ከኃጢአት ሁሉ እርሾ ሳንለይ ውስጣችን የሞላውን መጻጻ ተሸክመን የፋሲካ ሕይወት አይገኝም። ጳውሎስም እንዲህ አለን።
«ስለዚህ በቅንነትና በእውነት ቂጣ በዓልን እናድርግ እንጂ በአሮጌ እርሾ በክፋትና በግፍ እርሾም አይደለም» 1ኛ ቆሮ 5፤8
እንግዲህ ከፋሲካው ተስፋ የምናደርግ ሁላችን እስኪ ራሳችንን እንመርምር። እንደመጽሐፍ ሊያነበን በሚቻለው ከፋሲካችን ክርስቶስ ፊት እስኪ ራሳችንን እናንብበው። በእውነት እነዚህ እርሾዎች በውስጣችን ከሌሉ ከ2000 ዓመት በፊት ለሕይወት የፈሰሰውን ደም ይዘናል ማለት ነው። ያኔም ሞት በኛ ላይ ምንም ሥልጣን እንደሌለው አረጋግጠናል። እስራኤላውያን የበራቸውን ጉበንና መቃን በቀቡ ጊዜ ሞት እንደማይነካቸው እርግጠኞች እንደነበሩ ሁሉ እኛም የበለጠውንና የተሻለውን የሕይወት ደም በእምነት ስለያዝን ለዘላለማዊ ሕይወት እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ከዚያ ባሻገር በየዓመቱ በሚመጣ በዓል የሚገኝ የደም ምልክት የለም። በጥብጠባና በስግደትም የሚገኝ የሕይወት ዋስትናና የሚሻር ኃጢአት የለም። የተደረገልንን ማሰብ አንድ ነገር ሆኖ ሰው ግን ዓይኑን በዚያ በዓል ላይ ተክሎ የዓመቱ ኃጢአት ወይም ሸክም እንደሚወድቅ ማሰብ ስህተት ነው። ዓመቱን ሙሉ ከክፋትና ከግፍ እርሾ በመላቀቅ፤ አንድም ሰከንድ የማይለይ የልባችንን ጉበንና መቃን ላይ ደሙን በእምነት ይዘን መገኘት የግድ ይሆንብናል። ያኔ ነው ፋሲካችን ታርዷል የምንለው። ያኔም ነው ሁልጊዜ በሕይወት መንገድ ላይ እንዳለን የምናውቀው። መንፈሳዊ ሕይወት እንዲኖረን፤ መንፈሳዊ ጉዞ እንዲሰምርልን ዕለት፤ ዕለት መታደስ መታደስ ይገባዋል እንጂ በዘልማድ መንገድ አንመላለስ!
«ስለዚህም አንታክትም፥ ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል» 2ኛ ቆሮ 4፤16
ፋሲካችን የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ ያደረገልንን ውለታ እያሰብን ውስጣችንን መፈተሽ የግድ ነው። በአምናው እኛነታችንና በዘንድሮው እኛነታችን መካከል የሕይወት ለውጥ ከሌለን ሞት በመጣ ጊዜ ምንም የመዳን ምልክት እንደሌላቸው ፈርዖናውያንን ወደዘላለማዊ ሞት መሄዳችን እውነት ነው። በወይራ በመጠብጠብ 30 እና 40 ለመስገድ ከመሽቀዳደም ይልቅ፤ ከሞት የማምለጫ የፋሲካው ዓርማ ክርስቶስን ከኃጢአት በጸዳ ማንነታችን ውስጥ ዘወትር ይዘነው እንኑር። የሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን እሁድ ነው። ከእሁድ እስከ እሁድ 8 ቀናት አሉት። ዕብራውያን የበራቸውን ጉበንና መቃን የቀቡት ቅርጽ ከዕብራውያን አሌፋት መካከል የ «ኼ» ስምንተኛው ፊደል አምሳል ነው። «ኼ» ደግሞ ትርጉሟ «ሕይወት» ማለት ነው። ይህ የደም ምልክት ነው ሕይወት የሆናቸው። በሳምንቱ የመጀመሪያው ቀን የአዲስ ኪዳኑ ሕይወት በክርስቶስ ትንሣዔ ለዓለሙ ሁሉ ታደለ። ይልቅስ ይህንን ደም በልባችንን ጉበንና መቃን ላይ እንደንጹሕ መስዋዕትለመቀባት እንሽቀዳደም። ያኔምክርስቲያኖች እግዚአብሔርን ፍለጋ የት መሄድ ይገባናል? የእግዚአብሔር መገኛው የት ይሆን? ከምድራዊት ቤተ መቅደስ? ከገሪዛን፤ ከጌባል? ወይስ በኢየሩሳሌም?
አንዳንዶች ኢየሩሳሌምን የተሳለመ የ40 ቀን ሕጻን ይሆናል ይላሉ። የቆረበ ደግሞ የበለጠ የ40 ቀን ሕጻን እንደሚሆንም ይሰበካል። ከተሳለመ የ40 ቀን ሕጻን በመሆንና ከቆረበ የ40 ቀን ሕጻን በመሆን መካከል ያለው ልዩነት አይገባኝም። ኢትዮጵያ በመቁረብና ኢየሩሳሌም ከጎልጎታ ሄዶ በመቁረብ መካከልስ ያለው ልዩነት ምንድነው? ሰዎች ክርስትናን እንደሕግ ሥርዓት ማክበር ሲጀምሩ የሕግ የብልጫ ልዩነት ክርስትናውን መውረስ ይጀምረዋል። ኢየሩሳሌም ሄዶ በመሳለም ወይም በመቁረብና ኢትዮጵያ በመቁረብ መካከል ልዩነት የሚመጣውም ለዚህ ነው። መቱ ባለች ቤተ ክርስቲያን ጓሮ በመቀበርና ደብረ ሊባኖስ በመቀበር መካከል ያለው የመብት ልዩነትም ውጤቱ የሕግ ተፋልሶ ክርስትናውን በመዋጡ የመጣ ነው። የወንጌል እውነት ግን ያንን እንድንል አይነግረንም። እግዚአብሔር መንፈስ እንጂ በቦታና በሥፍራ የሚወሰን አምላክ አይደለም። ስለዚህም እግዚአብሔር በመንፈስ ይመለካል፤ በእምነትም፤ የመንፈስ የሆነ ሥራ በሕይወታችን ላይ ሊገለጥ ይገባዋል። ያኔ ዲላ ሚካኤል ተቀበርን፤ ደብረ ሊባኖስ፤ ደሴ ቆረብን አውስትራሊያ በማንነታችን ላይ ለውጥ የለውም። በሕይወቱ የክርስትና ማንነት የሌለው ሰው ደብረ ሊባኖስ ጓሮ መቀበሩ በፍርድ ወንበር ፊት ለውጥ አያመጣለትም። ሰው ሲሞት ይዞት የሚሄደው በምድር የነበረውን ሥራ እንጂ በሰማይ የሚፈጸም የክርክር ዳኝነት የለም። «እስመ አንተ ትፈድዮ ለኩሉ በከመ ምግባሩ» እንዳለ ዳዊት በመዝሙር 62፤12
ስለዚህ እግዚአብሔር በመንፈስ ይመለካል፤ በመንፈስ ይሰገድለታል፤ በመንፈስ ይታመናል እንጂ በቦታና በሥፍራ አይደለም። እሱን ይይዝ ዘንድ የሚችል ምድራዊ መቅደስ የለንም። «ለእኔ ምን ዓይነት ቤት ትሠራላችሁ? ይላል ጌታ» የሐዋ 7፤50
«ወትቤሎ፤ አበዊነሰ በዝንቱ ደብር ሰገዱ፤ ወአንትሙሰ ትብሉ ከመ በኢየሩሳሌም መካን ውእቱ ኀበ ይሰግዱ። ወይቤላ ኢየሱስ፤ እመንኒ ብእሲቶ ከመ ትመጽእ ሰዓት አመ ኢበዝንቱ ደብር፤ ወኢበኢየሩሳሌም ዘይሰግዱ ለአብ፤ አንትሙሰ ትሰግዱ ለዘኢታአምሩ፤ ወንሕንሰ ንሰግድ ለዘናአምር፤ እስመ መድኃኒት እምነ አይሁድ ውእቱ። ወባሕቱ ትመጽእ ሰዓት፤ ወይእዜ ይእቲ፤ እመ እለ በርቱዕ በአማን ሰጋድያን፤ ይሰግዱ ለአብ በመንፈስ ወበጽድቅ እስመ አብኒ ዘከመዝ የኀሥሥ እለ ይሰግዱ ሎቱ። እስመ እግዚአብሔር መንፈስ ውእቱ፤ እለሂ ይሰግዱ ሎቱ በመንፈስ ወበጽድቅ ሀለዎሙ ይሰግዱ ሎቱ»
ትርጉም፤
«አባቶቻችን በዚህ ተራራ ሰገዱ፤ እናንተም፦ ሰው ሊሰግድበት የሚገባው ስፍራ በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ አለችው። ኢየሱስም እንዲህ አላት፦ አንቺ ሴት፥ እመኚኝ፥ በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል። እናንተስ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፤ እኛ መዳን ከአይሁድ ነውና ለምናውቀው እንሰግዳለን። ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፤ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና፤ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል» ዮሐ 4፤20-24
የኢየሱስ ስቅለት የሚታሰበው በመንፈስ መሆኑን ለማመልከት ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች እንዲህ አላቸው። ኢየሱስ የተሰቀለው ኢየሩሳሌም እንጂ ገላትያ አለመሆኑን እያወቀ ለገላትያ ሰዎች ግን «በዓይናችሁ ፊት እንደተሰቀለ ሆኖ ተስሎ ነበር» እያለ ይወቅሳቸዋል። ምክንያቱም ስቅለቱ በአማኞች ፊት የሚታየው በየዓመቱ ለሁለት ወር በሚደረግ ጾምና ለአንድ ሳምንት በሚታሰብ የሕማማት ሳምንት ሳይሆን በየትኛውም ቦታ ብንሆን ያለምንም ዕረፍት በዘመናችን ሙሉ ነውና።
የሕማማቱ ሳምንት ካለፈ በኋላስ? በዓለ ፍስሐ ወሀሴት፤ በዓለ ድግስ ወግብዣ፤ በዓለ ምግብ ወመጠጥ ነው? የኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ ለሁለት ወር ከምግብ የመከልከል ማዕቀብና ለሁለት ወር ተከልክለው የነበሩ ምግቦች በተራቸው ድል የሚቀዳጁበት በዓል አይደለም። ዓመቱን ሙሉ በፊታችን እንደተሰቀለ ሆኖ የምናስብበት፤ በመንፈስና በእውነት የምንሰግድለት ቋሚ የሕይወታችን መርህ እንጂ በአርብ ቀን የወይራ ጥብጣብ የሚያበቃ ዓመታዊ ልምምድ ካደረግነው ከገላትያ ሰዎች በምን እንሻላለን?
ለዚህም ነው፤ ብዙ ክርስቲያኖች ከነገሠባቸው የሥጋ ሥራ ሳይላቀቁ ፋሲካን እያከበሩ ዘመናቸውን ሁሉ የሚፈጽሙት። ጋብ ብሎ የነበረው የሥጋ ሥራ ከፋሲካ በዓል በኋላ ይደራል። ዝሙቱ፤ ውሸቱ፤ ስርቆቱ፤ ማጭበርበሩ፤ ሃሜትና ነቀፋው ያለማንነት ለውጥ እንደነበረው ይቀጥላል። ዓመቱን ሙሉ ያጠራቅሙትን ኃጢአት የፋሲካ ጾም ሲመጣ ለማራገፍ እንደሚቻልበት አመቺ ጊዜ ጠብቀው ብዙ ሰዎች ጥሬና ቆሎ ቋጥረው በየዋሻውና ፍርክታው ልክ እንደሽኮኮ ይመሽጋሉ። ሀብት ያላቸው ኢየሩሳሌም ሄደው ለመሳምና ለመቁረብ ገንዘባቸውን በየዓመቱ ይከሰክሳሉ። የክፉ ቃል ምንጭ የሆነውን አንደበቱን ሳይዘጋ ሥጋ መሸጫ ቤቱን የሚዘጋ የት የለሌ ነው። ከተማውን ሁሉ የወረረው የሚዛን መሥፈሪያ በፈሪሃ እግዚአብሔርና ያለማጭበርበር ሳይሰሩበት ጾም የሚሉትን ፈሊጥ የሚጠብቁት ለምንድነው? አቤት! የዘንድሮ ሚዛን የሚባለው የድሮና የዚህ ዘመን ሚዛን ልኬታ የተለየ ሆኖ ይሆን?
የሕዝብና የመንግሥት ሀብት የሚዘርፉ የሕግ ፋሲከኞች ቁጥራቸው ብዙ ነው። የቤተ ክርስቲያን ደወል ሲደወል የሚከንፉ ነገር ግን የቤታቸውን የፍቅርና የሰላም ደወል የተነጠቁ ቤቱ ይቁጥራቸው። ሠራተኞቻቸውን የሚያስጨንቁ፤ በፍትህ አደባባይ ፍርድን የሚጨፈልቁ፤ በመማለጃም የእንባን ዋንጫ የሚጎነጩ የሁለት ወር ጸዋሚዎችና ተሃ ራሚዎች አያሌ ናቸው። የልምድ ክርስቲያኖች የሕይወት ምስክርነት በሥራቸው ሊታይባቸው አይችልም። ስለዚህም ይመስለኛል፤ በክርስቲያን ቁጥር ብዙ ሆነን በበረከት መትረፍረፍ አቅቶን እድሜ ልካችንን ከእምነት የለሾች ምጽዋት ጠባቂ ሆነን የቀረነው። እንደእምነት የለሾቹ፤ እምነት የለሾች ብንሆን ያለእምነት ስለሚፈረድብን በሥጋ ረሃብ ባልተገፋንም ነበር። እግዚአብሔርን እየጠራን፤ እንደፈቃዱ ለመኖር ባለመቻላችን በራሳችን የእምነት ጉድለት በሥጋችን እንቀጣለን። ብዙ ባወቅህ ቁጥር ብዙ ሥራ ይጠበቅብሃል። ካልሰራኸው ግን ባታውቅ ቢቀርብህ ይሻልህ ነበር። ስለዚህ ማወቅህ ለመዳንህ ዋስትና የሆነውን ነገር ካላትርፈረፈልህ ክርስትናህ ምንድነው? ኢየሱስ በባዶ ተስፋ አልተወንም። እኛ ግን አስሮ በያዘን በገላትያውያን አዚም ፈዘን ሳለ ስለገላትያ አዚም እናስተምራለን።
የኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለትና ትንሣኤ በየዓመቱ እየዞረ የሚመጣ በዓል ሳይሆን ዕለት፤ ዕለት በፊታችን ተስሎ የሚታየን የሕይወታችን አካል ነው መሆን ያለበት። በቦታ፤ በሥፍራና በጉዞ ብዛት የሚከበር ሳይሆን በእውነትና በመንፈስ እንድናመልከው የተደረገልን የማዳን ሥራ ነው። በአዲስ ሰውነት ለውጥ እንጂ በሕግ ሥነ ሥርዓት ልናሳልፈው አይገባም። ሰላምና እርጋታ በውስጡ መኖሩን መንፈስ ቅዱስ የሚመሰክርለት አማኝ ሀገር ለሀገር፤ ተራራ ለተራራ ትንሣኤውን ፍለጋ ሲዞር አይገኝም። ምክንያቱም፤ ሁል ጊዜ በዓይኑ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ይታየዋልና»! ከተያዝንበት አዚም ተላቀን በልባችን የተሳለውን ትንሣኤ፤ በኑሮአችን ፍሬ የሚታይበት እንዲሆን እግዚአብሔር ይርዳን! አሜን።
Thursday, April 21, 2022
Tuesday, April 19, 2022
Subscribe to:
Posts (Atom)