Tuesday, April 19, 2022
Saturday, April 16, 2022
ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር ማቴ ፳፩፣፱
«ሆሳዕና» ቃሉ ከሁለት አረማይክ ቃላት የተሰራ ሲሆን ትርጉም «እባክህ እርዳ፣ አሁን አድን» ማለት ነው። እብራይስጡም ይህንኑ ቃል ወርሶ «הושענא » ሆሻአና ሲል ይገኛል። አዎ «አሁን አድን፣ እባክህ እርዳን» ብሎ የአዳም ዘር ያጣውን ልጅነትና የደረሰበትን ሞት ለመላቀቅ የሚያሰማው የጩኸት ድምጽ ነው፣ «ሆሳዕና»!!!
ዳዊት ነቢይ በመንፈስ ቅዱስ ተመልክቶ ማዳኑን ሲጣራና አሁን ናልን ሲል ከዘመናት በፊት አድምጠነዋል። የውስጥ ዓይኖቹ ሩቅ አይተዋል። ማዳኑንም ሽተው እንዲህ ሲል ዘምሮለታል።
«አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አድን አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አቅና» መዝ ፻፲፰፣፳፭
ያ ማለት ደግሞ « אָנָּ֣א יְ֭הוָה הֹושִׁ֘יעָ֥ה נָּ֑א אָֽנָּ֥א יְ֝הוָ֗ה הַצְלִ֘יחָ֥ה נָּֽא » አና ያኽዌ ሆሳአና አና ያኽዌ ሆስሊኻ ና» የሚለው የእብራይስጡ ቃል ነው።
አበው የማዳኑን ነገር አስቀድመው አይተው በተስፋ «ሆሳዕና» እያሉ ዘምረዋል። የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ በክርስቶስ ኢየሱስ እስኪገለጥ ዘወትር በእንባና በዝማሬ ወደ ተስፋው ፍጻሜ ድምጻቸውን ያሰሙ ነበር።
አዎ ንጉሥ ክርስቶስ ከዘጠና ዘጠኙ በጎች መካከል የጠፋውን አንዱን በግ ፍለጋ ንጉሥ ሆኖ ሳለ እንደንጉሥ ያይደለ በአህያ፣ ለዚያውም በውርንጫ ተቀምጦ «የአሁን አድን (ሆሳዕና)» ጩኸት ሊመልስ በጽዮን ከተማ ይመጣል፤ ይህንንም ዘካርያስ ከዘመረው ዘመናት ተቆጥረው ነበር።
«አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እጅግ ደስ ይበልሽ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ እልል በዪ እነሆ፥ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው ትሑትም ሆኖ በአህያም፥ በአህያይቱ ግልገል በውርጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል» ዘካ ፱፣፱
ምንኛ ይደንቅ? ምንኛስ ይረቅ? ንጉሥ ስለመምጣቱ አስቀድመው የተናገሩለትና ከዘመናት በፊት ማዳኑን አይተው በእልልታ የዘመሩለት!!
ሰማያዊ ንጉሥ ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ያለዘርዓ ብእሲ ከስጋችን ተዛምዶ ማዳኑን ሲጠብቁ፤ ከሩቅ አይተው ሲጣሩ፣ ሲዘምሩለትና አንድ ቀን ማዳኑ እንደሚሆን ተስፋ ሲያደርጉት የነበረው ሰዓቱ ደርሶ በመካከላቸው ሲገኝ ይጠብቁት የነበረው ዓይነት ሳይሆን ውበት የሌለውን ንጉሥ ለመቀበል የገዛ ወገኖቹ ተቸግረው ነበር።
አዎ የደም ግባት ብቻ ሳይሆን የንጉሥ ወግ የሌለው፣ በአህያ ለዚያውም በውርንጫ የሚመጣ ንጉሥ እንዴት ይቀበሉት?
«በፊቱ እንደ ቡቃያ ከደረቅም መሬት እንደ ሥር አድጎአል። መልክና ውበት የለውም፥ ባየነውም ጊዜ እንወድደው ዘንድ ደም ግባት የለውም» ኢሳ ፶፫፣፪
አባቶቻቸው ለዘመናት «ሆሳዕና፣ ማዳንህ አሁን ይሁን» ያሉለትና የዘመሩለት በዕለተ ቀጠሮው ማዳኑን ሊያሳይ ከጽዮን ደጃፍ ቀርቦ ሳለ የማያውቁት፣ ያልሰሙት፣ ትንቢቱን ያላነበቡት «ሆሳዕና» ሲሉ ትልልቆቹ ዕብራውያን ግን ዝም አሉ፣ ዝም በሉም አሉ!
«ነገር ግን የካህናት አለቆችና ጻፎች ያደረገውን ድንቃ ድንቅ በመቅደስም፣ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ እያሉ የሚጮኹትን ልጆች ባዩ ጊዜ፥ ተቈጥተው፣ እነዚህ የሚሉትን አትሰማምን? አሉት»
የማዳኑ ጌታም፣
«እሰማለሁ፤ ከሕፃናትና ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን ለራስህ አዘጋጀህ የሚለውን ቃል ከቶ አላነበባችሁምን? አላቸው» ማቴ ፳፩፣ ፲፭-፲፮
ኢየሱስ ክርስቶስ የእነዚህን ሕፃናት ዝማሬና ምስጋናን የሰማው ከቤተ ፋጌ ወደ ኢየሩሳሌም ማዳኑን ሊፈጽም በመጣ ጊዜ ነበር። ቤተ ፋጌ ከኢየሩሳሌም ከተማ ምሥራቃዊ አቅጣጫ በቢታንያና በደብረ ዘይት ተራራ መካከል የምትገኝ መንደር ነበረች። ቤተ ፋጌ ማለት በአረማይክ «ያልበሰለ በለስ ቤት» ማለት ነው። ርቀቱም ከኢየሩሳሌም የሰንበት ያህል ምዕራፍ ነበር።
ጌታ ኢየሱስም ከኢያሪኰ ከተማ ወደኢየሩሳሌም ሲወጣ ካረፈባት ከቤተ ፋጌ መንደር ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ልኰ ውርንጫይቱን ከታሰረችበት ፈትተው እንዲያመጡለት አዟል።
«ወደ ኢየሩሳሌምም ቀርበው ወደ ደብረ ዘይት ወደ ቤተ ፋጌ ሲደርሱ፥ ያንጊዜ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከ፥እንዲህም አላቸው፦ በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ በዚያን ጊዜም የታሰረችን አህያ ውርንጫም ከእርስዋ ጋር ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ» ማቴ ፳፩፤፪
ያን ጊዜም በቀደምት አበው የተነገረው ትንቢትና ዝማሬ ፍጻሜ አገኘ ማለት ነው።
«የሚቀድሙትም ሕዝብ የሚከተሉትም። ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር» ማቴ ፳፩፣፱
ይሁን እንጂ ኢየሩሳሌም ለሆሳዕና አልተዘጋጀችም ነበር። ይልቁንም ቤተ መቅደሱ አካባቢ ስለማዳኑ ዝማሬ በማቅረብ ፋንታ የጦፈ የንግድ ገበያ ደርቶበት ነበር። ቤተመቅደሱ የጸሎት ሥፍራ መሆኑ ቀርቶ የሻጮችና የለዋጮች መድረክ ሆኖ ነበር። ያኔ ማዳኑ የቀረበላት ኢየሩሳሌም በመቅደሱ በራፍ ስትሸጥ፣ ስትለውጥ መድኃኒቱን ሆሳዕና እያለች መቀበልን እንዳልቻለች ሁሉ የዛሬዋ ቤተክርስቲያንስ ንግድና ሸቀጥ የሌለበትን «ሆሳዕና» እያከበረች ነው ወይ? ብለን ብንጠይቅ ራስን ማታለል ካልተጨመረበት በስተቀር፣ መሸጥ መሸቀጡ የሌለበትን «ሆሳዕና» የሚያከብር የለም ነው መልሱ። ዐውደ ምሕረቱ ሱቅ በደረቴ ያልሆነበትን ሥፍራ ማግኘት ከባድ ነው።
ኢየሱስ ማዳኑን ከመፈጸሙ በፊት እነዚህን ነጋዴዎች አስወግዷል። ገበታቸውን ገልብጧል። እየገረፈ አስወጥቷል። የወንበዴዎች ዋሻ የሆነውን የጸሎት ቤት ጠራርጓል። ዛሬስ ቤቱ ስንት ወንበዴ መሽጎበት ይሆን? ወንበዴዎቹ ይዘምራሉ፣ ሆሳዕና ይላሉ፣ የዘንባባ ዝንጣፊ ይይዛሉ፣ በጣታቸው፣ በግንባራቸው ያስራሉ። ወንበዴዎች ናቸው ተብለው እንዳይርቋቸው የአምልኰ መልክ አላቸው። ቤተመቅደሱን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁ ያለው በግብር ውንብድና በመልክ ግን አገልጋይ ይመስሉ የነበሩትን የመቅደሱን ሰዎች ነበር። ዛሬም እንደዚያው!!
በሌላኛው ቀንም በዚያው በመቅደሱ ሲያስተምር ዋለ። የወይኑ ጌታ ስለወይኑ ደኅንነት የላካቸውን አገልጋይ ሠራተኞች ታሪክ አወጋቸው። የሕይወት ለውጥ ለወይኑ ባይሆንለት ይፈሩት እንደሆነ አንድ ልጁን ቢልክም ገበሬዎቹ ወራሹ ይህ ነው እንግደለው ብለው መከሩበት፣ መክረውም አልቀረም፣ ከወይኑ አውጥተው ገደሉት። ስለዚህ የወይኑ ጌታ ገዳዮቹን ምን የሚያደርግ ይመስላችኋል? ሲል ይጠይቃቸዋል። እነሱም መልስ መለሱ። መልሱ ግን በራሳቸው ላይ የሚሆን የምስክርነት ፍርድ ነበር። «ፍታሕ በርእስከ» ማለት ይህ ነው። እነሱም እንዲህ ሲሉ በራሳቸው ፈርደው ተናገሩ።
«እርሱም፦ ክፉዎችን በክፉ ያጠፋቸዋል፥ የወይኑንም አትክልት ፍሬውን በየጊዜው ለሚያስረክቡ ለሌሎች ገበሬዎች ይሰጠዋል አሉት» ማቴ ፳፩፤፵፩
የአይሁድ ፋሲካ ከመሆኑ ሶስት ቀን ቀደም ብሎ ደብረ ዘይት ተራራ ላይ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ይነጋገር ነበር። ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይወድቅ የማይቀረው ለምድነው አሉት?
ስለረገማት በለስና ስለኢየሩሳሌም ጥፋት ተናገረ። ኋላም በሮማዊው ጥጦስ ትንቢቱ ተፈጸመ። ፍሬ አልባዋ በለስ እስራኤል ጠፋች።
ጴጥሮስ ደብረ ዘይት ላይ ሌላ ጥያቄ አነሳ።
«እርሱም፦ መምህር ሆይ፥ እንግዲህ ይህ መቼ ይሆናል? ይህስ ይሆን ዘንድ እንዳለው ምልክቱ ምንድር ነው? ብለው ጠየቁት» የቅርቡን ጊዜና መጨረሻውን ዘመን ምልክቶች ነገራቸው። የቅርቡ ጊዜ የኢየሩሳሌም መከበብ የበለስ መድረቋ ጊዜ መሆኑን እንዲህ አለ። «ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ» ሉቃ ፳፩፤፳ በዚህ የኢየሩሳሌም የመጥፊያ የፍርድ ቀን መድረሱን አሳይቷል።
እንደገናም የኋለኛውንም ዘመን ትንቢት ደግሞ ይህች የተረገመች በለስ ስታቆጠቁጥ በጋ እንደ ደረሰ ታውቃላችሁ፤ ያኔ ደግሞ የመጨረሻው የፍርድ ቀን እንደደረሰ ምልክት ይሆናል አላቸው።
«ምሳሌንም ነገራቸው እንዲህ ሲል፦ በለስንና ዛፎችን ሁሉ እዩ፣ ሲያቈጠቍጡ ተመልክታችሁ በጋ አሁን እንደ ቀረበ ራሳችሁ ታውቃላችሁ።እንዲሁ ደግሞ እናንተ ይህ ሁሉ መሆኑን ስታዩ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ቀረበች እወቁ» ሉቃ ፳፩፤፳፱-፴፩
አዎ ! የመጨረሻው ዘመን ዋናው ምልክት ፍሬ አልባዋና የደረቀችው በለስ ማቆጥቆጥ መጀመሯ ነበር። ያኔ የአጨዳው መከር ስለመድረሱ ጫፏ ሲለሰልስና ማቆጥቆጥ ሲጀምር በጋ እንደደረሰ እወቁ« ተብሏል። እናም የምንዘምረው ዝማሬ ትልቅ ትርጉም አለው። ማዳኑን አይተናል። «ሆሳዕና በአርያም » እያሉ መዘመር ብቻውን ግን ዋጋ የለውም። ኢየሩሳሌም ተዘምሮባት ነበር። ግን ፍሬ የሌለባት በለስ በመሆኗ ደረቀች። በሚያምር ውብ ድንጋይ ፵፮ ዘመን የታነጸውን መቅደስ ማዳን አልቻለም። ተራሮችን ውደቁብን እስኪሉ ድረስ የወረደውን መከራ መሸሸግ የቻለ ዝማሬ አልተገኘም። መቅደሱ በወንበዴዎች ተሞልቶ ነበር። ወንበዴዎቹ ልጁን አልተቀበሉትም። የተቀበሉትም ፍሬ አላፈሩም። ስለዚህ በጭፍራ ተከበው ለሺህ ዘመናት ጠፉ። ዛሬ በኛ የሚሆን ፍሬ አልባነት ጥፋቱ ለሺህ ዘመን አይደለም። ለአልቦ ማኅለቅት እንጂ!!
በእድሜአችን ስንት «ሆሳዕና በአርያም» አሳለፍን? ማዳኑ በተደረገለት ማንነታችን ውስጥ ስንት ፍሬ አፈራን? የተራበው ኢየሱስ ከእኛ የሚፈልገውን ፍሬ ይዘናል? ወይስ ፍሬ አልባ ሆነን ለቁጣ የተዘጋጀን እንሆን? «ሆሳዕና በአርያም» ማለቱ ብቻውን አያድንም፣ ማዳኑንም አያመጣም። የወንበዴ ዋሻ ማንነታችንን እናጽዳ። ከዚህ ዓለም ሽቃጭና ልዋጭ ማስመሰያ ማንነት እንውጣ! በጎ ፍሬ እንዲያፈራ ለተላከው የወይኑ ባለቤት ወራሽ እንገዛ! ያኔ «ሆሳዕና በአርያም» ስንል ማዳኑ ፈጥኖ ይሆንልናል። ከኢየሱስ በቀር ማዳን የሚቻለውና ተስፋ የሚሆነን ማነው? ከሥጋ ለባሽ ማንም የለም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በሰው የሚታመን፣ በሥጋ ለባሽ የሚመካ፣ ልቡንም ከእግዚአብሔር የሚያርቅ የተረገመ ነው።
አዎ ሆሳዕና በአርያም! በዚህም አንተ ብቻ መታመኛ ነህ፣ በወዲያኛውም አንተ ብቻ! ሆሳዕና በአርያም።
ሃሌ ሉያ!!!!!!!!
Friday, April 8, 2022
ቻት ላይ ነን አትረብሹን!
ዮሐንስ 10
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹¹ መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል።
¹² እረኛ ያልሆነው በጎቹም የእርሱ ያልሆኑ ሞያተኛ ግን ተኵላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኵላም ይነጥቃቸዋል በጎቹንም ይበትናቸዋል።
¹³ ሞያተኛ ስለ ሆነ ለበጎቹም ስለማይገደው ሞያተኛው ይሸሻል።
Subscribe to:
Posts (Atom)