Thursday, April 14, 2016

ውስጤ መኖር ያለበት ቃና ቲቪ ሳይሆን መንፈስ ቅዱስ ነው!!

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከወዳጅ ጓደኞቼ ጋር በተገናኘን ቁጥር የመወያያ አጀንዳችን የሆነው ጉዳይ የዛሬውን ፅሁፍ እንድፅፍ አስገደደኝ፡፡ ዋና መቀመጫውን በዱባይ አድርጎ በቅርብ ጊዜ በሀገራቸን ስርጭቱን የጀመረው ቃና ቴሌቪዥን በአማረኛ እየተረጎመ (dubbing) በሚያቀርባቸው የቱርክ፣ የጣሊያን፣ የህንድ፣ የጃፓን እና የመሳሰሉት ሀገሮች ተከታታይ ፊልሞቹ የበርካታ ሰወችን ቀልብ እንደገዛ ሁላችንም እናውቃለን፡፡ በእጅጉ የሚገርመው ደግሞ በዙሪያየ ያሉና የማውቃቸው በርካታ ክርስቲያኖች ጭምር ለእነዚህ የባህር ማዶ ፊልሞች እጅ ሰጥተው በጉጉትና በከፍተኛ ናፍቆት ሲጠብቁ ማየት ነው፡፡ የቃና ቲቪ ፊልሞች የሚታዩበት ሰዓት ደግሞ ወላጆች ከስራ፣ ልጆች ከትምምርት ቤት፣ ወጣቶችም ከሚውሉበት ስፍራ በቤት በሚሰበሰቡበት፣ የእግዚአብሔርን ቃል በሚያጠኑበት፣ በጋራ በሚፀልዩበት ሰዓት ነው፡፡ እውነትም በስጋ አይን ለተመለከታቸው ፊልሞቹ በከፍተኛ ሁኔታ የሰውን ቀልብ የመግዛት አቅም እንዲኖራቸው ሆነው ተሰርተዋል፡፡ አንደኛው ፊልም ሲያልቅ በቅፅበት ሌላው ይቀጥላል፡፡ በዚህ ሁኔታ ከምሽት 12፡00 ሰዓት የተቀመጠ ሰው እስከ ምሽት 4፡00 ሰዓት ሌላ ስራ ሳይሰራ ያለምንም እንቅስቃሴ ይቀመጥ ዘንድ ግድ ይለዋል ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ልብ እንበል የተቀማነው ወትሮ ለፀሎትና ለእግዚአብሔር ቃል ጥናት በእጅጉ ይመቸን የነበረውን ሰዓት ነው፡፡ ከዛም ደክሞን እንተኛለን፡፡ እዚህ ጋር ግን እንደመንፈሳዊ ሰው ልንነቃ የሚገባን ይመስለኛል፡፡ ሰባት በየቀኑ ለየአንድ አንድ አዓት የሚታዩ መሳጭ የባህር ማዶ ፊልሞች እቤታችን ድረስ መጥተው በራሳችን ቋንቋ እየተመለከትናቸው ነው፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ቀድሞ ለጌታ የምንሰጠውን ሰዓት እየተውን፣ በፀሎት የምናሳልፈውን ጊዜ እየሸረሸርን ከክርስትና በእጅጉ የራቁ ሐገሮች ሰርተው በሚልኩልን ነገር ስንጠመድ የእነሱን ባዕድ፣ አምልኮ ኢ-ክርስትናዊ ነገሮች በሙሉ ወደ ውስጣችን እየሰገሰግን ነው፡፡ ልጆቻችንም ከክርስትና በእጅጉ ያፈነገጠ ነገር በየቀኑ እየተመለከቱ እንዲያድጉ እየተፈረደባቸው ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳችን በቆላስይስ 2፥8 ላይ ‹‹ እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፥ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ›› ብሎ በዓለማዊ ነገር እንዳንጠመድ ያስጠነቅቀናል፡፡ ኢየሱስም በማርቆስ ወንጌል 4፥24 ‹‹ምን እንድትሰሙ ተጠበቁ›› ብሎ ከምንሰማውና ከምናየው እንድንጠበቅ ያዘናል፡፡ ዓለማችን ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ ኢየሱስ በማቴዎስ ወንጌል ስለመጨረሻው ዘመን የተናገራቸውን የዘመን መጨረሻ ምልክቶች አንድ በአንድ አስተናግዳ ወደ ማገባደደዱ ትገኛለች፡፡ ብዙ ነገሮች ሆነዋል ብዙ ነገሮች ተፈፅመዋል፡፡ ባጠቃላይ ሰይጣን ዲያብሎስ ጥቂት ጊዜ እንደቀረው አውቆ ከመቸውም ጊዜ በላይ በኃይለኛ ቁጣ እየተጋ ያለበት ዘመን ነው፡፡ ዲያብሎስ በዚህ ዘመን በተለይም ወጣቱን ክፍል ከቤተክርስቲያን ለማራቅ ወደ እግዚአብሔር ቃል ትኩረት እንዳያደርግ ከሚጠቀምባቸው ዋና ነገሮች መሀል የፊልምና የሙዚቃው ኢንደስትሪ እጅግ ወሳኙን ድርሻ ይዟል፡፡በዘመናችን የሚሰሩ ፊልሞች በአብዛኞቹ ሰወችን ለዓለማዊ ምኞትና ለርኩሰት አብዝተው የሚጋብዙ ናቸው፡፡ ስለዚህም እኛ ክርስቲያኖች እንንቃ። ሰይጣን በረቀቀ መንገድ በእኛ ላይ እንዲሰለጥን እድል አንስጠው፤ የቱርክና የህንድ ፊልሞችን እያሳየ ከእግዚአብሔር መንግስት የሚለየን ጣቢያ ውስጣችን "ቃና ውስጤ ነው" እያልን ውስጣችን ሊሆንብን አይገባም፡፡ ምክንያቱም እኛ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ ነን፡፡ ውስጣችን እሱ ብቻ ነው መኖር ያለበት። ብናምንም ባናምንም ዘመኑ የመጨረሻ ነው፡፡ ያኛው መንግስት እኛን በመዝናኛ ነገር ጠምዶ ከጌታ መንግስት ሊለየን እየተጋ ነው። እኛ ታዲያ ነቅተን ብዙ ምርኮ ልንበዘበዝ ሲገባን በወጥመዱ ከገባንለት እጅግ ከባድ ይሆናል፡፡ ስለዚህም እንንቃ በኢንተርቴመንት ስም ውድ ጊዜያችንን እንዳናስበላ፤ ይልቀንስ የእግዚአብሔርን ዓለምን በልጁ የመጠቅለል አላማ ለማሳካት አብሮ ሰራተኞች እንሁን!ስለወንጌል ግድ ይበለን፡፡
እኛ "መንፈስ ቅዱስ ውስጣችን ነው!"

Friday, April 8, 2016

ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም!!!


ማቴ 7፣21
በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፥ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም። እንዳለው ጌታችና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌላውያን ነን ባዮቹ የእግዚአብሔርን ቃል እንዲሰደብ እያደረጉ. "ጌታ ሆይ፣ ጌታ በማለታቸው የዳኑ ቢመስላቸውም የተጠበቁት ለፍርድ ነው። በነሱም የከፋ አድራጎት ሰዎች ወደተገለጠው እውነት እንዳይደርሱ በማድረግ ላይ ተጠምደዋል። በተለይም በአፍሪካ ክፍለ አህጉር ክርስቲያን ነን በሙሉ ፓስተሮች እየተፈፀመ ያለው ዘግናኝ ድርጊትና በቤታችን በኢትዮጵያ ላይ መርገም የሚያመጣ ፀረ ክርስትና ሁኔታ እየተፈፀመ ነው። ሌብነት፣ ዝሙት፣ የእግዚአብሔርን ቃል ማጣመም፣ መዋሸት፣ አድማና ክፍፍል ዋነኛ መለያ ሆኗል።  ከዚህ በታች የቀረበው ጽሁፍ (ከምስባከ ጳውሎስ) የፌስቡክ ገጽ የተወሰደ ሲሆን ነገሩ ከዚህ በፊት እየታየ ከቆየው አሳፋሪ ተግባራት አንዱ ክፍል ነው።

ነገሩ መታወቅ የጀመረው እንዲህ ነው፡፡ አንድ ወዳጃችን በራሱ ምክንያት “ፓስተር” ተዘራ ያሬድ ወደሚያስተዳድሯት ቤ/ክ ይሄዳል፡፡ በዕለቱ የአምልኮ ፕሮግራም እየተካሄደ ነበር፡፡ መባ እና ዐሥራት ተሰበሰበ፤ ከዚያ በኋላ ማስታወቂያ ተነገረ፡፡ ማስታወቂያው ይህን መሳይ ነው፤ “ፓስተራችን የተዘራ ያሬድ ዳግመኛ የተወለደበትን ዕለት በየዓመቱ እንደምናከብር ይታወቃል፡፡ ለዚህም ዓመት ክብረ በዓል ብዙዎቻችሁ ገንዘብ ማዋጣታችሁ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ገንዘብ መስጠት እየፈለጋችሁ ሳትሰጡ ለገንዘብ ማሰባሰቡ የተመደበው ጊዜ ያለፈባችሁ ሰዎች መቸገራችሁን ነግራችሁናል፡፡ በመሆኑም ፓስተራችንን ተጨማሪ ዕድል እንዲሰጣችሁ ለምነነው፣ አንድ ዕድል ብቻ - ይኸውም ዛሬን ሰጥቶናል፡፡ ስለዚህ ገንዘብ መስጠት የምትፈልጉ ሰዎች ዛሬ ካልሰጣችሁ በቀር ሌላ ዕድል አይኖራችሁም፡፡ ምናልባት የተለየ ፈቃድ በፓስተራችን ካልተሰጠ በቀር …”፡፡

ከዚያ ደግሞ፣ ሌሎችም መረጃዎች በየጊዜው ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ፡፡ በእርግጥ ፓስተሩ ለልደታቸው ራቭ4 መኪና ስጦታ የተሰጣቸው በመሆኑ፣ በልደት ማክበር ስም የሚገኘው ጥቅማጥቅም ይጠፋቸዋል ተብሎ አይታሰብም፡፡

በቅርቡ ለማጣራት እንደ ተሞከረው ደግሞ፣ መዳናቸውን እንኳን ከሰውዬው መዳን ጋር የሚያስተሳስሩ አባላት መኖራቸው ነው፡፡ ለልደቱ ገንዘብ የሚያዋጡት መዳናቸውን እያሰቡ ነው!

እኚህ “ፓስተር” “ሬማና ሎጎስ” የተሰኘ መጽሐፍ ሲኖራቸው፣ ለጉባኤያቸው እንደተነናገሩት ከሆነ፣ “ማንም ሰው መጽሐፋቸውን አንብቦ መጠቀም የሚችል ሲሆን ከዚያ ባሻገር ግን መጽሐፋቸውን የመተቸትም ሆነ የመቃወም መብት እንደሌለው፣ ለዚህም ከፌዴራል መንግሥት ፈቃድ እንደ ተሰጣቸው” ይናገራሉ፡፡ “ፓስተር” ተዘራ፣ ከአባላቶቻቸው መካከል በርካታ የደኅንነት አባላት መኖራቸውንና የሚፈልጉትንም ነገር በቀላሉ ማስፈጸም እንደሚችሉ በድፍረት በመናገር ይታወቃሉ፡፡

እንዲህ ዐይነት አገላለጾች “ፓስተር” ተዘራ ያሬድ ስለ ራሳቸው ያላቸውን ግምት የት ድረስ የተወጠረ እንደሆነ ያስረዱናል፡፡

Tuesday, April 5, 2016

ደቀ መዝሙር ከፍያለው ቱፋ ወደኮሌጁ እንዲመለስ ተወሰነለት!



ሰበር ዜና
       ደቀመዝሙር፥ ዲያቆን፥ ዘማሪ፥ መምህር ከፍያለው ቱፋ ‹‹በሰዋሰወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ›› በነጻነት እየወጣ እየገባ እንዲማር የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ምድብ አንድ ፍ/ብሔር ችሎት ወሰነ!!
       የሞት ጣር የሚያቅረው ማህበረ ቅዱሳን የተባለ የባንዳ ስብስብ፥ ባሳለፍነው ሳምንት ደቀመዝሙር ከፍያለው ቱፋ ከሰዋሰወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ፥ ከትምህርት ገበታው እንዲነሳ በላካቸው ጀሌዎቹ በኩል ተሟግቶ ‹‹እንዲታገድ›› ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡ ይህችም እንደትልቅ ድል ተቆጥራ ‹‹ሐራ ዘተዋህዶ›› በተባለችው የደከመች ብሎጋቸው ላይ ሁለት ጊዜ ዜና ሰርተው ማናፈሳቸውም የሚታወስ ነው፡፡ የሚገርመው ግን ደቀመዝሙሩ እንዲታገድ በተወሰነው ‹‹ውሳኔ›› ላይ የኮሌጁ የበላይ ኃላፊ ‹‹ብጹዕ አቡነ ሕዝቅኤልና የኮሌጁ ዋና ዲን ሊቀ ኀሩያን ሰርጸና ብዛት ያላቸው የኮሌጁ አመራሮች›› አለመፈረማቸውን ሸሽገዋል፡፡ ያልፈረሙበት ምክንያት ደግሞ ደቀመዝሙሩን ከኮሌጁ የሚያስወጣ የሃይማኖት ሕጸጽ ባለማግኘታቸው ነው፡፡ የማህበሩ ጀሌዎች ግን ኃላፊነቱን በመውሰድ፥ ያልስልጣናቸው የኮሌጁን ማህተም ተጠቅመው፥ ደቀመዝሙሩን ያሰናበቱት፡፡ ይህ ደግሞ ወንጀል በመሆኑ ምክንያት ደቀመዝሙር ከፍያለው ቱፋ ለሚመለከታቸው የቤተክርስቲያናችን አባቶች በማሳወቅ፥ ጉዳዩን ‹‹ወደ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ምድብ አንድ ፍ/ብሔር ችሎት›› ለመውሰድ ተገድዷል፡፡
        ከታች ለማስረጃነት ያቀረብነው የፍርድ ቤት ትዕዛዝ፥ በቀን 23/07/2008 ዓ/ም፥ የፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት/ኮ/ቀ ምድብ 1ኛ ፍ/ብሔር ችሎት፥ በቁጥር የኮ/መ/ቁ 50074 ያሳለፈው ውሳኔ ሲሆን፥ ደቀመዝሙር ከፍያለው ቱፋ ላይ በኪራይ ሰብሳቢነት የማህበረ ቅዱሳን ጀሌዎች በኮሌጁ ስም ያሳለፉትን ውሳኔ፥ ከመሰረቱ ያፈረሰ ‹‹አጭርና ግልጽ›› ትዕዛዝ ነው፡፡ ትዕዛዙም እንዲህ የሚል ነው፡-
“ሌላ ተለዋጭ ትዕዛዝ እስከሚሰጥ ድረስ ተከሳሽ በከሳሽ ላይ ትምህርቱን እንዳይማር የሰጠው ውሳኔ እንዳይፈጸም ታዟል፡፡ ለሚመለከተው አካል ይጻፍ፡፡ ማለትም በደብዳቤ ቁጥር 399/2/233/08 በ19/07/2008 ዓም የተጻፈው እንዳይፈጸም ታዟል፡፡”
       እንግዲህ ሽንፈት ለማን ነው? ለጠላት፥ ለዲያብሎስ አይደለምን? አሸናፊውስ፥ የልባችን ንጉስ፥ ጌታችን ኢየሱስ አይደለምን? እነሆ መስፋትና ማሸነፍ ለእግዚአብሔር ልጆች ሲሆን በአንጻሩ ደግሞ መክሰር ለዲያብሎስ ሆኗል!!
      ይህ በእንዲህ እንዳለ ደቀመዝሙር ከፍያለው ቱፋ ከትምህርት ገበታው እንዲነሳ ውሳኔ በማሳለፍ ሥራ ላይ የተጠመደው፥ በሙስና የኮሌጁ ምክትል ዲን የሆነው አቶ ማሞ ከበደ፥ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ አልፈጽምም በማለቱ ምክንያት እስራት ይጠብቀዋል፡፡ በተጨማሪም አቶ ማሞ ከበደ በማህበሩ የተሰጠውን አጀንዳ ለማስፈጸም ሲል ብቻ፥ ብጹዕ አቡነ ሕዝቅኤልና የኮሌጁ ዋና ዲን የሆኑት ሊቀ ኀሩያን ሰርጸ ፊርማቸውን ሳያስቀምጡ፥ ካለስልጣኑ በኮሌጁ ስም በወሰነው ወንጀል ሌላ ዘብጥያ ይጠብቀዋል፡፡ ሲጀመር አቶ ማሞ ከበደ የኮሌጁ ሠራተኛ ነው እንጂ የሃይማኖት ህጸጽ መርማሪስ ማን አደረገው? የሃይማኖት ህጸጽ ቢኖር እንኳ ሊጠይቀው የሚገባው፥ ቤተክርስቲያን ሥልጣን የሰጠችው አካል የሊቃውንት ጉባኤ ነው እንጂ፥ አንድ ጤና የጎደለው ሠራተኛ አይደለም፡፡ ሲኖዶስ ያልወሰነውን፥ ሊቃውንት ጉባኤ ያልወሰነውን ግለሰቡ የማሕበረ ቅዱሳንን አጀንዳ ተሸክሞ ለማስፈጸም መድከሙ ነውረኛነቱን የሚሳይ ነው፡፡ ሲቀጥልም ግለሰቡ የሃይማኖት ሕጸጽ የመመርመር ሥልጣንም ይሁን ብቃት የለውም፡፡ በርግጥ አቶ ማሞ ከበደ በደቀመዝሙሩ ላይ የእግድ ደብዳቤ የጻፈው ‹‹የሃይማኖት ህጸጽ›› ተመልክቶ ሳይሆን፥ ከማኀበሩ በሚያገኘው የኪራይ ሰብሳቢነት ልክፈት በመለከፉ ምክንያት እንደሆነ የቅርብ ወዳጆቹ ይመሰክሩለታል፡፡
ይህን ጉዳይ እየተከታተልን የምናቀርብ መሆኑን ከወዲሁ እንገልጻለን፡፡