(ተሐድሶ ተስፋዬ)
ለኦርቶዶክስ የተከለከለ ፅሑፍ !!
ድንገት እንኳ ብታነቡም እንዳትጨርሱት !!
በሰላም አለቃ በክርስቶስ ኢየሱስ ስም ሰላም ብያለሁ፣ሰላሙ ይብዛላችሁ !! እስኪ ደግሞ ትንሽ ለክርስቶስ ብዬ ልሰደብ !!
የኦርቶዶክስ ህዳሴ በኛ በልጆቿ ከግብ ይደርሳል !! አሜን የምትሉ ለምልሙልን !! እንደምንም አንብቧት ።
ከተሀድሶ እንቅስቃሴዎች ዉስጥ በትንሹ ላካፍላችሁ...
1.1. ""ማርታን ወደ ማርያም የመቀየር ተሐድሶ""
ሰዎች ወደ እግዚአብሔር ቃል ካልተመለሱ ወደ እግዚአብሔር አይመለሱም፤ ጌታ እንዳለው
“የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው፤ ማርያምም መልካም ዕድልን መርጣለች፤ ከእርስዋም አይወሰድባትም አላት ።” (ሉቃ.10፥42)፡፡ እነማርታ ቤተ ክርስቲያኑን ሞልተውታል፤ ዳቦ ጋግሩ፤ ወጥ ሥሩ፤ልብስ እጠቡ፤ከበሮ ምቱ ሲባሉ አይሰለቻቸውም፤ የክርስቶስን ወንጌል ተማሩ ሲባሉ ግን እንኳንስ ሊማሩ የሚማሩ እኅቶችና ወንድሞችን እንኳን ማየት አይፈልጉም፡፡ በዓመት አንድ ቀን የጥምቀት በዓል ሲመጣ ለማይሰማ ታቦት መንገድ ይጠርጋሉ፤ ምንጣፍ ያነጥፋሉ፤ ጉልበታቸውን ሳይሰስቱ ያገለግላሉ፤ የሚሰሙት ወንጌል ግን የለም፤ የእነዚህ ሰዎች አገልግሎት የቅናት እንጅ የእምነት አይደለም፡፡
ለእግዚአብሔር ቃል ቅድሚያ ካልሰጡ ደግሞ ለማይሰማና ለማያይ ታቦት ምንጣፍ እንዳነጠፉ፣ ግብር እንደገበሩ ይኖራሉ እንጅ ዕረፍትን አይገኙም፡፡ እነዚህ ሰዎች ለጊዜው ደስተኞች ናቸው፡፡ ዐሥር ዐመት በዚህ መልኩ ካገለገሉ በኋላ “አሁን ለመዳናችሁ እርግጠኞች ናችሁን?” ብለን ብንጠቃቸው እንኳንስ እርግጠኞች ሊሆኑ እንዲያውም ፍርሐታቸው ጨምሮ እናገኛቸዋለን፤ ስንጠይቃቸው የሚሰጡን መልስ “ማንም ከመሞቱ በፊት ለመዳኑ እርገጠኛ መሆን አይችልም” የሚል ነው፡፡
እነዚህ ሰዎች ይንም አይነቱን ወንጌል ከየት እንዳገኙት እናውቃለን፡፡ አዲሱ ትምህርት ነው፤ ሐዋርያት ያወገዙት፣ “ማንም እኔ ካስተማርኋችሁ የተለየ ወንጌል ቢያስተምራችሁ የተወገዘ ይሁን” (ገላ.1፡8) ብለው ያስጠነቀቁን ትምህርት ይህ ነው፡፡
ስለ ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ክርስቶስ ለመሄድ መናፈቅ አልሰሙም ማለት አንችልም፤ የሰሙትን እንዳላመኑት ግን እናያለን፡፡ ክርስቶስ በቃሉ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖረው እንጅ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወድዶአልና፤ በእርሱ የሚያምን አይፈረድበትም ፤ በእርሱ የማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስላላመን አሁን ተፈርዶበታል ” (ዮሐ.3፡16-17) ያለው ቃል ዕረፈት ካልሰጠና እርግጠኛ ካላደረገን በምን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን? ከዚህ ከጸና እውነት ያንሸራተተንና ከዓለቱ ነቅሎ በአሸዋ ላይ የሠራን ማነው? ይህን ከእግዚአብሔር እውነት የሚነቅል ትምህርት በእግዚአብሔር ቃል መዋጋት ተሐድሶ ነው፡፡
ብዙዎቻችን “የአገልግሎት ማኅበራት አባላት ነን” እያልን ከበሮ ለመምታት፣ ለመዘመር፣ ታቦት ለማክበር፣ ምንጣፍ ለማንጠፍ፣ የቤተ ክርስቲያን ቅጥረ-ግቢ ለማጽዳት፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ታቦት የሚሄድባቸውን መንገዶች ተከትሎ ለማጽዳትና ሰንደቅ ዓላማ ለመስቀል እንጅ የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ጊዜ የለንም፡፡ ቃለ እግዚአብሔርን መስማት እግዚአብሔርን ማገልገል ነው ብለን የምናምን ስንቶቻችን ነን? ማርታ ማርያምን ለምን ተቃወመቻት? ቃለ እግዚአብሔርን መስማት እግዚአብሔርን ማገልገል እንደሆነ ስላልገባት ነበር፡፡ ክርስቶስ ግን ለሁሉ የሚበቃውን አንድ ታላቅ አገልግሎት አከበረ፤ እርሱም ቃሉን መስማት ነው፡፡ ተሐድሶ የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት የመታደስ አገልግሎት ነው፡፡
የጸጋ ስጦታዎቻችን የተለያዩ ናቸው፤ ለአንዱ የተሰጠው ለሌላው ላይኖረው ይችላል፤ የሚዘምር ላይሰብክ፣ የሚሰጥ ላያስተምር ይችላል፤ ለሁላችንም የተሰጠን ጸጋ ግን የእግዚአብሔርን ቃል የመስማት አገልግሎት ነው፤ በዚህ አገልግሎት ውጤታማ ያልሆነ ሰው ደግሞ በሌላ አገልግሎት ውጤታማ መሆን አይችልም፡፡ እግዚአብሔርን ስለማያውቀው የሚያገለግለው የሚያውቀውን ራሱን፣ አለቃውን፣ ታቦቱን፣ ገንዘብን፣ ክብርንና እውቅና መፈለግን፣ ተቃውሞን፣ ሥርዐትንና ታሪክን፣ እኔ ብቻ ትክክል ነኝ ማለትን እንጂ እግዚአብሔርን ሊያገለግል አይችልም፡፡ ተሐድሶ ከዚህ አይነት እስራት ነጻ ወጥቶ እግዚአብሔርን እንደቃሉ በእውነትና በመንፈስ ማምለክ (ማገልገል) ነው፡፡
.
1.2. የሚያስፈልገን ጸበል ወይስ ወንጌል?
ለነማርታ እነርሱ ካልደከሙ የእግዚአብሔር ጸጋ አይበቃም፡፡ የእነርሱ ማሰሮ የምትሞላው የእግዚአብሔር ጸጋ ሲፈስስባት ሳይሆን እነርሱ የፈጩት ዱቄት ሲጨመር ብቻ ነው፡፡ ቃሉን መማር መሥዋዕት አይደልም፤ ጸበል ካልጠጡ፣መክፈልት ካልበሉ እግዚአብሔርን አላገለገሉትም፡፡ ቃሉን ካልሰሙ ቤተ ክርቲያን መሳለም ምንድን ነው? ጸበል ውሃ አይደለምን? ህሊናችንን ከሞተ ሥራ ሊያነጻ የሚችል መለኮታዊ ጸበል የእግዚአብሔር ቃል ነው፤(ዕብ.9፡14) ዲያቆናት በኩስኩስት ጸበል ከሚቀዱ ይልቅ ከመለኮታዊው ጸበል ከቃሉ ለምእመናን የማጠጣት አገልግሎት ቢጀምሩ ምናለበት? እስከመቼ ምእመናን በውሃ እየተታለሉ ይኖራሉ? የሕይወት ውሃ መጽሐፍ ቅዱስ ተከድኖ ወይም አልባሌ ቦታ ተጥሎ ዘወትር የውሃ መቅጃ ኩስኩስት ስናጥን የምንኖረው እስከ መቼ ነው? ኧረ ተዉ ጎበዝ የእግዚአብሔር ፍርድ ሳይገለጥ ወደ ቃሉ እንመለስ! ተሐድሶ ከውሃና ከመክፈልት ወደ ሕይወት ውሃ ወደ እግዚአብሔር ቃል መመለስ ነው፡፡
እግዚአብሔር የሕይወት ምግብ አዘጋጅቶ እየጠበቀን እኛ እግዚአብሔር የሰበሰበውን ሕዝብ የሚያልፍ ምግብ ያውም ውሃ አጠጥተን የምንልከው እስከመቼ ነው? ወደ እግዚአብሔር ቃል ከመመለስ የበለጠ ምን ተሐድሶ አለ? ሰውን ወደ እግዚአብሔር ቃል ከመመለስ የበለጠ አገልግሎትስ የት ይገኛል? ተሐድሶ አዲስ ነገር አይደልም፤ እግዚአብሔር ተረስቷልና ይታሰብ፤ እግዚአብሔር ክብሩንና ቦታውን ተነጥቋልና ወደ ክብሩ ይመለስ የሚል ተጋድሎ ነው፡፡ ክብሩን ለማንም እንደማይሰጥ የተናገረው እግዚአብሔር ያስነሳው አገልግሎት እንጂ አንዳች የሰው ፍላጎት የለበትም፡፡ እናውቃልን ስንዴ፣ ሰልባጅ፣ ብር ፈልገው የሚሠሩ፣ የፕሮቴስታንት ተላላኪዎች እንደምንባል፡፡ እኛ ግን የቤተ ክርስቲያኒቱ መቆሳቆል፤ የነገሮች ቅጥ ማጣት፣ በእግዚአብሔር ቦታ የማይሰሙና የማያዩ ታቦታት መቀመጥና መክበር፣ ንስሓ መግባት አለመቻላችን ቤተ ክርስቲያናችንን እየጎዳ ያለ መሆኑ፣ ያሳሰበን የቤተ ክርስቲያን ልጆች እንጂ በምንም ምክንያት በቤተ ክርስቲያን ላይ ክፉ አሳብ ያለን ሰዎች አይደለንም፡፡ እንዲውም በአመንነው እውነት ምክንያት ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር የሚጠቅም ልዩ ሸክም (ራእይ) ያለን ሰውች ነን፤ ራእያችን እንዳይዘገይ፣ መባረካችን እንዲፈጥን በመንገዳችን እንቅፋት አትሁኑብን እንላለን እንጂ በፍጹም እግዚአብሔር የማይፈልገው፣ ቤተ ክርስቲያንንም ሆነ ሀገርን የሚጎዳ አጀንዳ የለንም፡፡ አገልግሎታችን ሰማያዊና የከበረ መሆኑን እናውቃለን፤ ለዚህም ነው በነገር ሁሉ ስንፈተን “የማምነውን አውቀዋለሁ” ብለን ጸንተን እየተጓዝን፣ በየጊዜው ደግሞ እየበዛን ያለነው፡፡ የሚያበዛን የሕይወት ቃል የሆነው የእግዚአብሔ ቃል ነው፡፡ በተሐድሶ ያለ ሕዝብ በውሃ ዳር የተተከለ ዛፍ ነው፤ ቅጠሉ አይጠወልግም፤ ዘወትር ያፈራል እንጂ የመድረቅ ሥጋት የለበትም፡፡ ተሐድሶ ይህ ነው!
.
1.3. የምንሰብከው እግዚአብሔርን ወይስ የእኛን ሥነ ምግባር?
የሚያስፈልገው ነገር አንድ ነው፤ የእግዚአብሔር ቃል፡፡ የእኛ ገድልና ድርሳን፣ የእኛ አመለካከትና ዕወቀት፣ የእኛ ቅኔና ትርጓሜ በቦታው ጠቃሚ ቢሆንም በእግዚአብሔር ክብር ላይ መጋረጃ ሲሆን ግን ጉዳት እንጂ ጥቅሙ አይታየንም፤ የሕይወት መንገድ የተገለጠበት መጽሐፍ “መጽሐፍ ቅዱስ” ነው፡፡ ይህን እውነት ማንም ማስተባበል እንደማይችል እናምናለን፡፡ ወደ እግዚአብሔር ቃል እንመለስ! (Back to the word of God!) ምንም ብንሰብክ፣ ምንም ብንቀኝ፣ ምንም ብናከማች የእግዚአብሔር ቃል ካልሆነ ይበተናል፡፡
ይህ ነገር ለምን ያሳስበናል? ሰዎች እንዲለወጡ፣ ንስሓ እንዲገቡ፣ እንደእግዚአብሔር ቃል እንዲመላለሱ እግዚአብሔር ይፈልጋል፤ ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ እግዚአብሔርን በቃሉ መሠረት ስናውቀው ብቻ ነው፡፡ የግብፅ ፓትርያርክ የነበሩት አቡነ ሺኖዳ የተናገሩትን ምሳሌ አድረገን እንመልከት፤ “I confess before You, O Lord that I ought to have changed my trend of writing. I confess-in shame-that I often talked to people about virtue but little did I talk to them about you, though you are all in all” (The release of the spirit p.14) መልእክቱ ወደ አማርኛ ሲመለስ እንዲህ የሚል ነው፡፡ “ከአሁን በፊት ስጽፍበት የነበረውን ልማዴን መለወጥ እንደነበረብኝ አቤቱ በፊትህ እናዘዛለሁ፤ ለሕዝቡ ስለ ምግባራት (ስለመልካም ምግባር) ዘወትር ብዙ እንደ አስተማርሁ፣ ብንም እንኳን አንተ ሁሉ በሁሉ ብትሆንም ስለአንተ ግን ጥቂት እንደነገርኋቸው በሐፍረት እናዘዛለሁ፡፡” ስለ እግዚአብሔር ሳይሆን ስለ ሥነ ሥርዐት ስንሰብክ ከኖርን የምናልመውን ለውጥ ማምጣት አንችልም፤ የሚለውጠው እግዚአብሔር እንጅ የእኛ ቃል አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ በቃሉ እንጅ በእኛ የስብከት ጥበብ አይሠራም፡፡ እግዚአብሔር በቃሉ እንጂ በእኛ ተረት ለመጽናት ቃል ኪዳን የለውም፡፡
ዛፉን እየነቀልንና እያደረቅን ፍሬ የምንፈልገው ከየት ነው?
እስኪ ልብ በሉ! እግዚአብሔርን ከሰው ልብ የሚያፈናቅል (እንደዛፍ ተክል የሚነቅል) ትምህርት እያስተማርን በጎ ምግባር የምናገኘው ከምኑ ነው? አቡነ ሺኖዳ እንዳሉት ስለ እግዚአብሔር ሳይሆን ስለ በጎ ሥራ ስንሰብክ የምንኖረው እስከመቼ ነው? መቼም ቢሆን የሰይጣንን አሳብ አንስተውም፤ ዛሬስ ብሎ ብሎ ተሐድሶ መልካም ሥራን መቃወም ጀመረን? ተመልከቱ! ተሐድሶ ለየለት! የሚል ሰው አይጠፋም፡፡ እያልን ያለነው በዛፉ የማይኖር ፍሬ አያፈራም፤ ሰውን ከዛፉ የሚቆርጥና የሚያደርቅ ለመጥፋትና ለመቃጠል የሚያዘጋጅ የሐሰት ትምህርት ከቤተ ክርስቲያን ይራቅ፤ ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት ትታደስ ነው፡፡ይህ ነው ተሐድሶ!
በክርስቶስ የምንኖረው በቃሉ ስንኖር ብቻ ነው፤ ቃሉን እየተቃወምን ወይም ቃሉን ከአትሮንስ አውርደን የእኛን ተረት አትሮንስ ላይ የምንሰቅል ከሆነ፣ ዐውደ ምሕረቱን እንደ ስሙ የምሕረት ማወጃ አደባባይ ሳይሆን የሚያስር ትብትብ መስበኪያ ካደረግነው፣ እግዚአብሔር በቃሉ ነጻ ሊያወጣው የሚፈልገውን ሕዝብ የበለጠ የእስራት ቀንበር ከጫንንበት የት አለ የእኛ የክርስቶስ መልእክተኞች መሆን? የምንሟገተው ለማን ነው? ለራሳችን ወይስ ለክርሰቶስ? ለክርስቶስ ከሆነ ቃሉን ለምን አናጠናም/አንሰብክም? ዓለምን መቃወም የምንችለው በቃሉ ብቻ ነው፡፡ ለእኛ የተለየ ጥበብ የለንም፤ያለን ማረጋገጫ ቃሉ ብቻ ነው፡፡ ተሐድሶ ይህ ነው! ወደ እግዚአብሔር ቃል መመለስ! እግዚአብሔር ይመልሰን! የቤተ ክርስቲያናችንን የተሐድሶ ተስፋ በቃሉ እንደገና ወደ ክብሯና ቅድስናዋ የመመለስዋን ትንሣኤ ለማየት ነው!!!
ኢየሱስ ያድናል !!