Sunday, January 24, 2016

"ቅድስና ለእግዚአብሔር"


(ተረፈ አበራ)
ሰው በክርስቶስ ሲያምን ጽድቅ ሆኖ ይቆጠርለታል ።ሮሜ 4:25 ይህ ማለት በታረሰ መሬት ላይ ተተክሎ እንደ ጸደቀ ወይን ይሆናል።ጻድቅ እንደ ዘንባባ ያፈራል እንደ ሊባኖስ ዝግባ ይለመልማል እንደሚል መጽሐፍ ፍሬ ያፈራል።መዝ 29:92 ፍሬው ቅድስና ይባላል።ጽድቅና ቅድስና እምነትና ሥራ ይባላሉ ።ያዕ 2:14 ቅድስና መለየት ማለት ሲሆን ሰው በክርስቶስ ጸጋ መጽደቁን የሚያረጋግጥበት የመንፈስ ፍሬ ነው ።ይህም ማለት ውስጣዊ ጤንነት እና ንጹህነት ወይም ከእንከን መራቅን ያመለክታል።እግዚአብሔር በባህሪው ቅዱስ ነው ።ሰዎችን በጸጋው ይቀድሳል።
  ቅድስና የሚያስፈልገን ነገር ግን ያልፈለግነው የሕይወት ውበት ነው።ደስታን፣ብልጽግናን፣ሰላምንና ስኬትን በምንፈልግበት መጠን ቅድስናን ፈልገን እናውቅ ይሆን? ቃሉ፦'ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ፥ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚችል የለምና።' ይላል።ዕብ.12፥14 ቅዱሱን ጌታ ለማየት የቅድስና ጥሪውን በመቀበል፣በደሙ በመታጠብ ከዓለም፣ ከኀጢአት፣ ከርኩሰትና ከሥጋ ሀሳብ በመለየት መኖር ያስፈልጋል።'እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ።'1ኛ ጴጥ. 1፥15-16።ክርስትና ለእግዚአብሔር የመለየት ኑሮ ነው።ልዩነቱ የበጎ ተጽዕኖ አቅም ነው።በተራራው ጌታ የሰበከንን የአማኝ ኑሮ ብናጠና ብልጫችንን እንረዳለን። ለሚበልጠው ታጭተን በሚያንስ አኗኗር እንዳንገኝ እናስተውል። በቅዱሱ ፊት በተጣለ ማንንነት መቆም አይቻልም።በሰው ፊት እንኳ ቆሽሾ መቅረብ ምን ያህል ይከብዳል? 'እኔ ኤልሻዳይ ነኝ፤ በፊቴ ተመላለስ፥ ፍጹምም ሁን፤' ዘፍጥረት 17፥1 ያለውን ጌታ ነው የምናመልከው። እግዚአብሔር የምንቀደስበትን መስዋእት አዘጋጅቷል። የተዘጋጀው መስዋእት ልጁ ነው።ህሊናችንን ቀድሶ መንፈሳችንን አንጽቶ በደላችንን አጥቦ ሊያቆመን ወደሚችለው እንቅረብ።አሮጌ(ያደፈ ልብስ)አልብሶ የሚከሰንን በደሙ ኀይል በስሙ ስልጣን ጥሎአል።ራእይ 12፥11 ቀዳሹ እኛን መቀደስ ፈቃዱ ነው እኛ መቀደስ እንፈልጋለን?ብሉይ ኪዳን 'ቅዱሳን ሁኑ'(ዘሌ 19፥2) ያለን ቅዱሱን ልጁን ላከ።ቀዳሹ ጌታም እኛን ተቀዳሾቹን በደሙ አነፃ።ከኀጢአታችን አጠበን(ራእይ 1፥6) ቀደሰን(1ቆሮ 6፥11) ክብሩን እንድናበራ ለየን።በመሆኑም እኛ ለርስቱ የተለየን ቅዱስ ሕዝብ ነን።(1ጴጥ 2፥9)።ለለየን ተለይተን መኖር ይጠበቅብናል።ቅድስና የሕይወት ዘመን ኑሮ ነው፡፡ስለዚህ ሁልጊዜ ሀሳባችንን ልናነፃ፣ንግግራችንን ልንገራ፣ ሰውነታችንን ከርኩሰት በጸጋው ኀይል ልንጠብቅ ይገባል። ቅዱሳን ለመሆን መጠራታችንን አንርሳ።(ሮሜ 1፥7)። የተጠራነው ለርኩሰት አይደለም።'ለርኵሰት ሳይሆን እግዚአብሔር በቅድስና ጠርቶናልና።"1ኛ ተሰሎንቄ 4፥7። ስለዚህ አባታችንን ለመምሰል በአንደበት ብቻ ሳይሆን በሕይወትም በቅድስና ማደግ አለብን።አባታችን መልኩን በኛ ሕይወት ውስጥ የማየት ናፍቆት አለው።የጠራን በባሕርይው ቅዱስ እንደሆነ እኛም በኑሯችን ሁሉ ከአለም እድፍ ራሳችንን በመጠበቅ በቅድስና መኖር አለብን። የቀደሰንን እንድንመስል ተወስኗል።'ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና።'ሮሜ 8፥29።አስቀድሞ ወደታሰበልን ያድርሰን፤ካላደረሰን መድረስ የለምና። ይቀጥላል! እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን !!


Wednesday, January 20, 2016

ተቀባይነት ያጣ እውነት!



ብዙ ብለናል፤ ብዙ ተብሏል።  ችግሩ ያለው የሚነገር እውነት አለመኖሩ ሳይሆን እውነቱን የሚቀበል መጥፋቱ ላይ ነው። ተቀባይነት ያጡ እውነቶችን መጽሐፍ ቅዱስን ዋቢ አድርገን እናቀርባለን።

1/ ታቦት

ታቦት ማለት ማደሪያ፤ማኅደር ማለት ነው።  ቃልኪዳናዊ አሠራሩም ከዚህ የሚከተለውን ይመስላል።
«እኔ እንደማሳይህ ሁሉ፥ እንደ ማደሪያው ምሳሌ እንደ ዕቃውም ሁሉ ምሳሌ፥ እንዲሁ ሥሩት። ከግራር እንጨትም ታቦትን ይሥሩ፤ ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል፥ ቁመቱም አንድ ክንድ ተኩል ይሁን። በውስጥና በውጭም በጥሩ ወርቅ ለብጠው፤ በእርሱም ላይ በዙሪያው የወርቅ አክሊል አድርግለት። አራት የወርቅ ቀለበቶችም አድርግለት፥ እነርሱንም በአራቱ እግሮቹ ላይ አኑር፤ በአንድ ወገን ሁለት ቀለበቶች፥ በሌላው ወገን ሁለት ቀለበቶች ይሁኑ። መሎጊያዎችንም ከግራር እንጨት ሥራ፥ በወርቅም ለብጣቸው። ለታቦቱ መሸከሚያ በታቦቱ ጐን ባሉት ቀለበቶች መሎጊያዎቹን አግባ። መሎጊያዎቹም በታቦቱ ቀለበቶች ውስጥ ይኑሩ፥ ከቶም አይውጡ። በታቦቱም ውስጥ እኔ የምሰጥህን ምስክር ታስቀምጣለህ። ከጥሩ ወርቅም ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል የሆነ የስርየት መክደኛ ሥራ። ሁለት ኪሩቤል ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሥራ፥ በስርየት መክደኛውም ላይ በሁለት ወገን ታደርጋቸዋለህ» ዘጸ 25፤10-18
ይህንን የእግዚአብሔር መመሪያ ያላሟላ ታቦት፤ ታቦት ሊባል አይችልም። ከዚህ የሚጨመርም፤ የሚቀነስም ከእግዚአብሔር  ቃል ያፈነገጠ ነው። ይህ አንዱ ታቦት ሁለቱን የምስክር ጽላቶች ይይዛል። ካህናቱ ሲሸከሙም በመሎጊያዎቹ ጽላቱ ውስጥ እንዳለ አራት ሰዎች በአንድ ጊዜ ይሸከሙታል እንጂ አናት ላይ ቁጢጥ የሚል ጽላት የለም። ይህ ያፈጠጠ ያገጠጠ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ነው። ይህ የእግዚአብሔር ቃል እንዲሻሻል የተነገረበት ጊዜ የለም። ዛሬ ታቦት የሚባለው ከየት የመጣ ነው? ዓላማው፤ አሰራሩ፤ እቅድና ግቡ ምንድነው? ብዙ ሰዎች ስለተከተሉት ወይም እድሜ ጠገብ ስለሆነ ውሸት መቼም ቢሆን እውነት ሊሆን አይችልም። ታቦትን የተመለከተ የእግዚአብሔር ዓላማ በዚህ ዘመን ለማንም አልተሰጠም።

2/ጽላት፤

 ጽላት ሁለቱ የኪዳን ሰሌዳዎች ናቸው። 10ቱ የእግዚአብሔር ትዕዛዛት የተጻፈባቸው ሰሌዳዎች ስለሆኑ ጽላት ተብለዋል። ሙሴ ጽላቶቹን ሊቀበል ሁለት ጊዜ ወደተራራ ወጥቷል። የመጀመሪያውን ጽላት የቀረጸውና በጣቱ የጻፈባቸው እግዚአብሔር ራሱ ነው። «እግዚአብሔርም ከሙሴ ጋር በሲና ተራራ የተናገረውን በፈጸመ ጊዜ በእግዚአብሔር ጣት የተጻፈባቸውን ከድንጋይ የሆኑ ሁለቱን የምስክር ጽላቶች ሰጠው» ዘጸ 31፤18
የመጀመሪያዎቹ ከተሰበሩ በኋላ ጽላቱን ከእብነ በረድ ዳግመኛ የቀረጸው ሙሴ ራሱ ሲሆን በላዩ ላይ ትዕዛዛቱን በጣቱ የጻፈባቸው ግን እግዚአብሔር ነው።
 «ሙሴን አለው፦ ሁለት የድንጋይ ጽላቶች እንደ ፊተኞች አድርገህ ጥረብ፤ በሰበርኻቸው በፊተኞቹ ጽላቶች የነበሩትን ቃሎች እጽፍባቸዋለሁ» ዘጸ 34፤1   ዘዳ10፤4
መጽሐፍ ቅዱስ ስለጽላት በተናገረበት የትኛውም አንቀጽ ውስጥ ሙሴ ጽላቶቹ ላይ ጻፈ የሚል ገጸ ንባብ የለም። ከእብነ በረድ አስመስለህ ቅረጽ የተባለውን ትዕዛዝ አንተው ጻፍባቸው የተባለ በማስመሰል ራሳቸው የሚጽፉባቸው ከየት በተገኘ ትዕዛዝ ነው? በወቅቱም ጽላቶቹ ላይ እግዚአብሔር ራሱ የጻፈባቸው ትዕዛዛት እንጂ ምስል ወይም ስዕል አይደለም። ይህስ ከማን የተገኘ ትምህርት ነው? ስንት ጽላት? ስንት ታቦትስ? እግዚአብሔር ሰጥቷል?

3/ ምልጃና ማስታረቅ

«አማላጅ» የሚለው ቃል የተገኘው «ማለደ» ከሚል ግስ ሲሆን «ማለደ» ማለት ደግሞ «ለመነ» ወይም «ጸለየ» ማለት ይሆናል። « መማለድ ፤ ማማለድ… » ማለት  «መለመን ፣ ማስታረቅ» ሲሆን «አማላጅ» ደግሞ ይህን ተግባር የሚያከናውን ነው፡፡ ተግባሩ ደግሞ «ምልጃ» ይባላል፡፡
አዳም ከእግዚአብሔር ፊት በኮበለለ ጊዜ ወዴት ነህ? ሲባል እነሆ በዚህ ተሸሽጌአለሁ አለ።                         «እግዚአብሔር አምላክም አዳምን ጠርቶ፦ ወዴት ነህ? አለው።እርሱም አለ፦ በገነት ድምፅህን ሰማሁ፤ ዕራቁቴንም ስለ ሆንሁ ፈራሁ፥ ተሸሸግሁም» ዘፍ 3፤9-10
ይህ የኮበለለው ሰው፤ አዳም ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ነበረበት። መቼ? ማንስ? ያስታርቀዋል?
በዘመነ ብሉይ የማስታረቅ አገልግሎት የተሰጠው ለካህናቱ ወገን ብቻ ነበር። የኃጢአት ማስተሰሪያ መስዋዕትም ዕለት ዕለት ይቀርብ ነበር።
« ዕለት ዕለትም ስለ ማስተስረይ ለኃጢአት መሥዋዕት ወይፈኑን ታቀርባለህ፤ ማስተስረያም ባደረግህ ጊዜ መሠዊያውን ታነጻዋለህ ቅዱስም ይሆን ዘንድ ትቀባዋለህ» ዘጸ29፤36 ይህ የማስታረቅ አገልግሎት ፍጹማዊ አገልግሎት አይደለም። በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የተጋረደውን የጥል ግድግዳ ማፍረስ የማይችል ጊዜአዊ አገልግሎት ነበር። ስለዚህም በአዳምና በልጆቹ ላይ የእግዚአብሔር ቁጣ ነበረ። ይህ የበደል ቁጣ ሊመለስ የሚችለው ይህንን መሸከም የሚችል መስዋዕት ሲኖር ብቻ ነው። ለዚህም አገልግሎት ብቁ መሆን የሚችለው ደግሞ ከኃጢአት በቀር በሁሉ የተፈተነ ሊሆን ይገባዋል።
«ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ፥ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም» ዕብ 4፤15
ስለዚህም ሰማያዊ ሊቀካህን ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ፊት ለኮበለልነው ለአዳም ልጆች ሁሉ አስታራቂ መስዋዕት ሆነ። ይህንንም ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ አለ።«ከዓመፀኞችም ጋር ተቈጥሮአልና እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ፥ ስለ ዓመፀኞችም ማለደ»ኢሳ53፤12
ኢየሱስ ክርስቶስ አስታራቂና ማላጅ ባይሆን ኖሮ ሥጋ ከለበሰ ከሰው ልጅ ማንም ቢሆን የማስታረቅ አልገልግሎትን ሊፈጽም አይችልም ነበር። የክርስቶስ ኢየሱስን አስታራቂነት ልዩ የሚያደርገው የማማለድ ብቃቱ ብቻ ሳይሆን ዕለት ዕለት የሚደረገውን የማስታረቅ አገልግሎት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስቀረት መቻሉ ነበር።
«ሊቀ ካህናትም ሁሉ ዕለት ዕለት እያገለገለ ኃጢአትን ሊያስወግዱ ከቶ የማይችሉትን እነዚያን መሥዋዕቶች ብዙ ጊዜ እያቀረበ ቆሞአል እርሱ ግን ስለ ኃጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ» ዕብ 10፤11-12
ስለዚህ የኢየሱስ ክርስቶስ የማስታረቅ አገልግሎት አንዴ የተፈጸመ፤ ነገር ግን ዕለት ዕለት ወደእግዚአብሔር የሚመጡትን ሁሉ የሚያድን የዘላለም መስዋዕት ስለሆነ ዛሬ አዲስ የሚፈጸም የልመናና የማስታረቅ አገልግሎት የለም። አንዳንዶች ዛሬም የሚለምን ያለ የሚመስላቸው አሉ። አንዳንዶች ደግሞ አንዴ የፈጸመው አገልግሎት አብቅቷል፤ ከእንግዲህ አይሰራም የሚሉ አሉ።  አማላጅነትን ለሰዎች ያስረከቡ ሁሉ የክርስቶስን ዘላለማዊ ብቃት ይክዳሉ። በሌላ መልኩም የሰዎችን አማላጅነት ለመከላከል ሲሉ ኢየሱስን ዛሬም የሚማልድ አድርገው የሚስሉም አሉ። ሁለቱም ጽንፎች የኢየሱስን ማንነት ካለማወቅ የሚመነጭ አስተሳሰብ ነው።እውነቱ ግን ዕብራውያን መጽሐፍ እንዳለው፤
«እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው፤ እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል። ቅዱስና ያለ ተንኮል ነውርም የሌለበት ከኃጢአተኞችም የተለየ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለ፥ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ይገባልና፤ እርሱም እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና» ዕብ 7፤23-27
ስለዚህ በአጸደ ነፍስ ያሉ ቅዱሳን፤  ሰዎች ከበደል ወደ ጽድቅ፤ ከኃጢአት ወደቅድስና ሰዎች እንዲመለሱ ይማልዳሉ፤ ይለምናሉ ማለት ለኃጢአተኛው ምትክ ሆነው ያድኑታል ማለት አይደለም። አንዴ የተፈጸመው የማማለድና የማስታረቅ አገልግሎት በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው።

Friday, January 1, 2016

ስለአንዳንድ በኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ ላይ…ከአንዳንድ የኦሮሞ ጸሐፍት የተሰነዘሩ…ያስቀየሙኝ ክታቦች!!


 (በአማን ነጸረ ክፍል 4)

(7.1) ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ በጻፉት በመጀመሪያው ‹‹ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ›› መጽሐፋቸው ገጽ-137 ይሕንኑ ሁኔታ (የቶፋ ሥርዓት) በጥቁምታ ያመላክቱናል፤እንዲህ ሲሉ ‹‹በኢትዮጵያ የካሕናት ቁጥር እጅግ ብዙ ነው፡፡ለነዚሁም ሁሉ መንግሥት ከያውራጃው ከግማሽ እስከ አንድ ጋሻ መሬት ለእያንዳንዱ ካሕን ርስት እያደረገ ሰጥቷቸዋል፡፡ይኸውም ርስት እየሆነ የተሰጠው መሬት ለልጅ ልጅ የሚያልፍ [በመሆኑ] ቤተክርስቲያን ልታዝዝበት አትችልም፡፡በዚህም ላይ ከንጉሠ-ነገሥቱ ዠምሮ መሳፍንቱ መኳንንቱም ሌላውም እነሱን የመሰለው ሁሉ ወይዛዝርት እንኳ ሳይቀሩ የቤተክርስቲያን ገበዞች እየሆኑ ከ200 እስከ 700 ጋሻ መሬት ንጉሠ-ነገሥቱ ርስት እያደረገ ይሰጣቸዋል...›› በማለት ይዞታው በወሬ የኢኦተቤክ እየተባለ ስመ-ንብረቱ (title deed) ግን በተግባር በንጉሡ፣በመሳፍንትና ወይዛዝርት እጅ እንደነበረ፤እነዚህ መሳፍንትና ወይዛዝርት ሲያልፉም ልጆቻቸው የቤ/ክ ትምህርት ባይማሩም ‹ገበዝ› በሚል መጠሪያ ርስቱን ወርሰው ደሃ ካሕናትን እያስቀደሱ በስመ ተዋሕዶ የሚያደርጉትን ብዝበዛ (የቶፋ ሥርዓት) ስሙን ሳይጠሩ ያብራሩልናል፡፡
(7.2) በ1967 ዓ.ም የመሬት-ላራሹ ዐዋጅ ሲታቀድ በካሕናት እጅ እንደዜጋ የነበረውን መሬት ሁሉ በነባሩ ‹‹የሲሶ መሬት ይዞታ›› ትረካ አጠቃሎ የመውረስ አዝማሚያ አስፈርቶ ነበር፡፡ሁኔታው ያሳሰባቸው የጊዜው የኢኦተቤክ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ በ1967 ዓ.ም ለደርግ በጻፉት ደብዳቤ ተቃውሞአቸውን ሲገልጹ ‹‹...ተጋኖ ሲነገር የኖረው ጨርሶ ያልነበረ የመንግሥት ሥልጣን ድርሻና የሀገሪቱ ሲሶ መሬት ወሬ ፈጽሞ ተረት ቢሆንም ያው ያለው መጠነኛ ድጋፍ እስካሁን ድረስ ከመንግሥት ሲሰጣት ቆይቷል›› በማለት ‹‹ያው ያለው መጠነኛ ድጋፍ›› እንዲቀጥል ተማጽነው ነበር፡፡ፓትርያርኩ ጥያቄያቸውን በ7 ነጥቦች አብራርተው ነበር ያቀረቡት፡፡2ቱን ብቻ ልጥቀስላቸው ‹‹1ኛ. የኢትዮጵያ ገዳማት መሬት ያንድነት ማኅበር እንደ መሆኑ መጠን ይኸው በይዞታቸው ያለው የንፍሮ መሬታቸው በይዞታቸው ስር እንዲቆይ እንዲፈቀድላቸው፣እንዲሁም ‹በርሷ (በኢኦተቤክ) ስም ተይዘው ሌሎች ወገኖች ሲጠቀሙባቸው የኖሩ መሬቶች ቢወሰዱ የምትጎዳበት ባይኖርም› እስከ ዛሬ በቀጥታ ስትረዳባቸው የቆዩ አንዳንድ መሬቶች በይዞታዋ ስር እንዲቆዩላት፤2ኛ. በግብርና ስራ የሚተዳደሩ ካሕናት ሁሉ ካሕንነታቸው ኢትዮጵያዊ ማንነታቸውን ስለማይሽረው እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የመሬት ድርሻቸውን የማግኘት መብታቸው እንዳይዘነጋባቸው››ብለው ጠይቀው ነበር (መምህር ኪዳነማርያም ጌታሁን፡ገ.102)፡፡
(7.3) በደስታ ተክለወልድ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ገጽ 1267 ‹‹ወኪል፣ምትክ፣ተጠሪ፣ገባሪ›› ተብሎ ስለተተረጎመው ‹‹ቶፍነት›› ሌላ ዋቢ እንቁጠር፡፡‹‹የኢኦተቤክ አስተዳደር በየዘመናቱ››የተሰኘው መጽሐፍ ደራሲ ብፁዕ አቡነ ገሪማ (ዶ/ር) ስለዚህ ጉዳይ ሲተርኩ ‹‹ለቤተክርስቲያን መግባት የሚገባውን የግብር ገንዘብ መሳፍንቱ፣መኳንንቱ፣ባላባቶችና ወይዛዝርት በግብዝና በእልቅና፣በመሪጌትነት፣በድብትርና፣በቅስና፣በዲቁና እና በልዩ ልዩ [የ]ክሕነት [አገልግሎት] ስም ርስት እየያዙ በግል እየተጠቀሙ በተወሰነ ክፍያ ወይም በቶፍነት ካሕናትን ያስገለግሉ ነበር›› ይሉናል፡፡አቡነ ገሪማ ታሪኩን ሲቀጥሉ ‹‹…የቤ/ክ መተዳደሪያ ብዛት ጎልቶ ከመታየቱ በቀር ለካሕናቱ መተዳደሪያ ይሆን ዘንድ የተፈቀደው ርስተ - ጉልት የሚሰጠው ጥቅም የአገልጋዮች ካሕናትን ችግር ከመሸፈን አኳያ በቂ አልነበረም፡፡…ከሚያጋጥሙት ችግሮች መካከል፡- ያልቀናውንና በረሃማውን መሬት እየሰጡ የለማውን መሬት መቀማት፣ለም የሆነውን መሬት በጠፍ መሬት መለወጥ፣የኩታ ገጠም አቀማመጥ ያለውን ርስት ወደ ግል ይዞታ ማስገባት…ይገኙበታል›› ይላሉ (አቡነ ገሪማ፡ገ.64-70)፡፡
(7.4) ከላይ ያለችውን የ“ቶፍነት” ሥርዓት ጽንሰ - ሐሳብ ለመረዳት ከመርስዔኀዘን ‹‹ትዝታዬ›› መጽሐፍ ገጽ-92 ማሳያ እንጨምር፡፡የድጓ መምህር የነበሩት ኣባታቸው ሲሞቱ የአባታቸውን መሬት ወርሰው እንደ ባለርስት መገበራቸው ቀርቶ እንዴት ወደ ቶፍነት እንደተሸጋገሩ ሲተርኩ ‹‹…እንግዲህ የምትገብረው በአባትህ ሥም አይደለም፣መሬቱ ለፊታውራሪ ጥላሁን ስለተሰጠ ሥመ - ርስቱ ተዛውሯል፤ሆኖም ለፊታውራሪ ጥላሁን በቶፍነት ልትገብር ትችላለህ…›› እንደተባሉ ይገልጻሉ፡፡ከመርስዔኀዘን አባባል እንደምንረዳው የመንግሥት ሹም የነበሩት ፊ/ሪ ጥላሁን ለድብትርና ተብሎ ለይስሙላ የተመደበውን ርስት ወርሰው ይዘው ደብተራውን (መርስዔኀዘንን) ‹‹ቶፋ›› አድርገዋቸዋል፡፡ታሪክ ግን ፊታውራሪ የያዙት ርስት ለስሙ የኢኦተቤክ ስለተባለ ብቻ ‹‹ሲሶ የቤተክሕነት ድርሻ›› ብላ ያልበላነውን ልታስተፋን ትጥራለች!!ቆዩማ ይቺን ታሪክ የሚሏትን ጉድ በጎጃምኛ ልስደባት ‹‹ኧግ!ይቦጭቅሽ!››
(7.5) ይሄን ሀቅ ጠጋ ብለው ያላዩልን እነ መኩሪያ ቡልቻ እና አባስ ሐጂም ነዋሪ ነባሪውን ስሑት የወሬ ጫፍ ይዘው <<...the clergy were....landlords,they owned Oromo peasants as Gabbars...>> ይሉናል!እርግጥ ይሕ በነአቶ አጽሜ ጸረ-ካሕናተ-ኦርቶዶክስ ጥላቻ ተከትቦ እስካሁን የሚናፈስ የታሪክ አረዳድ ኢህአዴጋውያንን ጨምሮ የብዙኃኑ ልሂቅ አረዳድ ስለሆነ እነ መኩሪያ ቡልቻንና አባስ ሐጂን ነጥሎ መውቀስ ኢ-ፍትሐዊ ሊሆን ይችላል፡፡በቁሳዊ ሀብትና በካሕናት ኑሮ ረገድ የዛሬዋ የኢኦተቤክ ያለችበትን ከቅድመ-1967 ዓ.ም የመሬት ዐዋጅ የተሻለ ኢኮኖሚያዊ አቅም ያስተዋለ ሰውማ በእርግጥም አቡነ ቴዎፍሎስ እንዳሉት በኦሮሚያም ሆነ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የሚተረከው ‹‹የሲሶ መሬት›› ድርሻ ‹‹ፈጽሞ ተረት›› እንደነበረ ይገለጽለታል፡፡እኛማ ትናንት በተወረሱባት ሕንጻዎች ምትክ ከደርግ የ5 ሚሊዮን ብር ምጽዋት ትጠብቅ የነበረች ቤ/ክ ዛሬ ገንዘብ አያያዟ ባያስደስተንም እንኳ በጀቷ ቢሊዮን መሻገሩን አይተናል፡፡እናም የትናቱ የተረት ተረት ‹‹ሲሶ ግዛት›› ከቶም አያቃዠንም!!አባቴ እንዲህ ይል ነበር ‹‹ድሮ ካሕን ስሙና ማዕረጉ ብዙ ነው፤በቤቱ ግን ሙሉ እንጀራ ቆርሶ የሚበላ ከስንት አንድ ነው፤በነገሥታቱ ከባቢ ካሉት በቀር ድሆችን ካሕናት የሚፈቅድ የለም፤ከነተረቱም ‹የካሕን ልጅ ስም ይጠግባል፤እንጀራ ግን አይጠግብም› ይባል ነበር፤መምህራኖቻችን የኖሩት ተማሪ ለምኖ እያበላቸው ነው፤አየ!፤ተውኝማ ልጄ!››
(7.6) ትውልዱ ባይገለጽለትም እኛ መከራና ስቃይ ከካሕናት ወላጆቻችን የወረስነው ‹ምድጃ የላቀን፤አመድ የወረሰን፤ደሃ የድሃ ልጆች› ወላጆቻችንን ዘበናይ ሁላ ተማርኩ ብሎ ‹‹ሲሶ-ሲሶ!›› እያለ በእንግሊዝኛ ሲዘባነንባቸው እንገረማለን፡፡በተሳልቆ ‹‹ኡኡቴ!ድንቄም ሲሶ!›› እንላለን፡፡ትናንት በነበሩ ብዙኃን ካሕናት ወላጆቻችን ያልተጠገበ ጥጋብ የዛሬዎቹ ሕያዋን ልጆቻቸው እንድንሸማቀቅ የሚሹትን የባለቅኔውን ድንቅ አባባል ተውሰን፡-
‹‹እስመ-እንዘ-ቦ፡ሕያወ፡እሞተ-ሥጋ፡ግዙፍ፣
ሞተ-ዮሴፍ፡አኃዊሁ፡ነገርዎ፡ለዮሴፍ፡፡››እንላቸዋለን--ለቀባሪው ማርዳት!!ሁሉን ትተን የታላላቆቹን ሊቃውንት የነክፍለ ዮሐንስ መራብና መታረዝ የሚያመላክቱና ቅኔያዊ ቁዘማዎቻቸውን የገለጹባቸውን ቅኔያት እንጠቃቅሳለን፡፡እንዲህ፡-
‹‹...ልብስየሂ፡ምንንት፡መንጦላእተ-ርኅቅት፡ነፍስ፣
እስመ-አነ፡ከመ-ዶርሆ፡እምላእለ-አብራክየ፡እለብስ፡፡››
እያሉ እኒያን የመሰሉ ሊቃውንት እርቃናቸውን እንኳ በቅጡ መሸፈን አቅቷቸው እንደ ዶሮ ከጉልበት በላይ ተራቁተው በ‹‹ሲሶ ግዛት››ተረት አእጽምቶቻቸው እረፍት ሲያጡ ከማየት የሚደርስብንን ሕማም በቅኔያቱ እናስታምማለን፡፡ደግሞም የዋድላው የኔታ ሲራክ ራሳቸውን ከአህያና በቅሎ ጋር እያነጻጸሩ የ30 ብር ዓመታዊ ደሞዝ ሰቆቃዊ አኗኗራቸውን፡-
‹‹አእዱግ፡ወበቅል፡እንዘ-ያወጽኡ፡ስልሳ፣
ሲራክ፡አምላከ-ዋድላ፡ተሰይጠ፤ለሠላሳ፡፡››
እያሉ የገለጹባቸውን ቅኔያት እያስታወስን እንግሊዝኛ ተናጋሪ ደባትሮቻችን ወደ ልባቸው ተመልሰው ሚዛኑን የጠበቀ ጽሑፍ እንዲያቀርቡል እንጸልያለን፡፡አንዳንዴም እንጎተጉታለን፡፡አልፎ አልፎም ሕመማቸው ሕመማችን መሆኑን ሳንስት በተጋነነ ቅሬታና ፍረጃ መስመር ሲለቅቁብን ከወዲህ የላላውን ለመወጠር ከወዲያ የተወጠረውን እንጎትታለን--እንዲህ እንዳሁኑ!
የላላው ይወጠር፤የተወጠረው ይርገብ፡፡ወይኩን ማዕከላዌ!አሜን!ይኹን፤ይደረግ!
፡፡፡፡፡፡፡፡በአማን ነጸረ፡፡መስከረም 2008 ዓ.ም፡፡፡፡፡፡፡፡
ማጣቀሻዎቼ!
ሀ. መጻሕፍት(ሃርድ ኮፒ)
1. ብፁዕ አቡነ ገሪማ (ዶ/ር)፣የኢኦተቤክ አስተዳደር በየዘመናቱ፣ጥቅምት 2000 ዓ.ም፣ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት
2. ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ(M.A)፣የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ታሪክ፣1986 ዓ.ም፣2ኛ እትም፣ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት
3. በኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንትና ጳጳሳት፣የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከልደተ ክርስቶስ እስከ ፳፻(2000 ዓ.ም)፣በ2000 ዓ.ም፣ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት
4. አባ አንጦንዮስ አልቤርቶ (ዶ/ር) (ካፑቺን)፣የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ታሪክ በኢትዮጵያ፡ከብፁዕ አቡነ ጉሊየልሞ ማስያስ እስከ ብፁዕ አቡነ እንድርያስ ጃሮሶ (1841-1941 ዓ.ም)፣1993 ዓ.ም፣ንግድ ማተሚያ ድርጅት
5. ታቦር ዋሚ፣የውገና ድርሰቶችና የታሪክ እውነቶች፣በ2007 ዓ.ም፣3ኛ እትም፣አርቲስቲክ ማተሚያ ድርጅት
6. መርስዔኀዘን ወልደቂርቆስ፣ትዝታዬ፡ስለራሴ የማስታውሰው፣2002 ዓ.ም፣አስቴር ነጋ አሳታሚ ድርጅት፤ሮኆቦት አታሚዎች
7. ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ (1ኛ መጽሐፍ)፣1965 ዓ.ም፣ብርሃንና ሰላም ወዳማዊ ኃይለሥላሴ ማተሚያ ቤት
8. አለቃ ተክለኢሱስ ዋቅጀራ (ሐተታ በዶ/ር ስርግው ገላው)፣የኢትዮጵያ ታሪክ፣2000ዓ.ም፣ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት
9. በቀለ ወልደማርያም አዴሎ፣የካፋ ሕዝቦችና መንግሥታት አጭር ታሪክ፣1996 ዓ.ም፣ሜጋ ማተሚያ ድርጅት
10. ዶናልድ ሌቪን (ትርጉም በሚሊዮን ነቅንቅ)፣ትልቋ ኢትዮጵያ፣2007 ዓ.ም፣አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ
11. ቅዱስ ያሬድ፣መጽሐፈ-ድጓ፣1988 ዓ.ም፣ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት
12. ከአባቶች ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ፣የውዳሴ ማርያም አንድምታ ትርጉም፣1990 ዓ.ም፣ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት
13. የእጅ ጽሕፈት የግእዝ መማሪያ ግስ/መዝገበ-ቃላት(በራሴ ተቀድቶ የተማርኩበት)፡፡
14. እነ አለቃ አፈወርቅ ዘውዴ፣የግእዝ ቅኔያት የስነጥበብ ቅርስ-2፣1980 ዓ.ም፣ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት
15. መምህር ኪዳነማርያም ጌታሁን፣የሐሰት ምስክርነት፣1994 ዓ.ም፣ንግድ ማተሚያ ድርጅት
16. ሰሎሞን ጥላሁንና ሥምረት ገ/ማርያም፣ደማቆቹ፣2000ዓ.ም፣
17. ደስታ ተክለወልድ፣ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት፣1962 ዓ.ም፣አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት
18. የኢትዮጵያ መጽሐፍቅዱስ ማኅበር፣የመጽሐፍቅዱስ መዝገበቃላት፣1992 ዓ.ም፣6ኛ እትም፣ባናዊ ማተሚያ ቤት
19. ላጵሶ ጌ.ድሌቦ (ዶ/ር)፣የኢትዮጵያ ረጅም ሕዝብና ታሪክ አንደኛ መጽሐፍ፣1982 ዓ.ም፣ንግድ ማተሚያ ድርጅት
ለ. የኢንተርኔት መጻሕፍት(ሶፍት ኮፒ) እና መጣጥፎች!
1. የመኩሪያ ቡልቻ፣የገመቹ መገርሳ እና የቶማስ ዚትልማንን ጽሑፎች ለማግኘት http://www.diva-portal.org/…/get/diva2:277262/FULLTEXT01.pdf
2. የመሐመድ ሐሰንን ጽሑፍ https://zelalemkibret.files.wordpress.com/…/jos-volume-7-nu…
3. የአባስ ሐጂን http://69.162.74.242/~iprenewi/r.php… ወይም http://69.162.74.242/~iprenewi/r.php…
4. በወለጋ ስለነበረው የሚሽኖች እንቅስቃሴ GILCHRIST, HORACE ERIC የጻፈው የ2ኛ ዲግሪ ማሙያ http://repository.lib.ncsu.edu/…/bits…/1840.16/844/1/etd.pdf
5. ፕ/ር ታምራት አማኑኤል የአለቃ ዐጽመጊዮርጊስን እና የነአለቃ ታዬ ታሪክ ጨምሮ የቀደምት ጸሐፍያንን ስራዎች ባጭሩ የዳሰሱበት መጽሐፍ http://www.ethioreaders.com/…/About-Ethiopian-Authors-Prof-…
6. ስለኦሮሞ ሕዝብ የሃይማኖት ተዋጽኦ https://en.wikipedia.org/wiki/Oromo_people#Religion
7. ‹‹ጋላ›› የሚለው ቃል በሶማሌ ሕዝብ ታሪክ ውስጥ ያለው የተለያየ ትርጉም https://www.yumpu.com/…/the-galla-myth-on-somali-history-or…
8. ስለ Krapf ሚሲዮናዊ ሕይወት https://en.wikipedia.org/wiki/Johann_Ludwig_Krapf
9. ‹‹ጋላ›› የሚለው ቃል ኬንያም ውስጥ በታሪክ መጻሕፍት ጥቅም ላይ ሲውል ስለመኖሩ የሚያሳይ ደብዳቤ http://yassinjumanotes.blogspot.com/…/stop-use-of-word-gall…
10. በዚች መዝሙር ላሳርግ Ethiopian Orthodox Mezmur in Afaan Oromo- Waldaa Qulqullootaa - Galanni Waaqayyoof haa ta'u https://www.youtube.com/watch?v=tER05f165A8
http://www.diva-portal.org/…/get/diva2:277262/FULLTEXT01.pdf