Thursday, September 10, 2015

ቅዱሳን መላእክትና ቅዱሳን ሰዎች በሁሉም ሥፍራ በአንድ ጊዜ መገኘት ይችላሉን?

ክፍል ሁለት
በክፍል አንድ ያቆምንበትን ሃሳብ ይዘን ከመቀጠላችን በፊት አንዳንድ ተቺዎች ባነሱልን ሞገት ዙሪያ ለዛሬ ጥቂት ማለት እንደሚያስፈልግ ስላመንን በዚያ ዙሪያ እንቆያለን።
 ሞጋቾቹ የሚያቀርቡት ማስረጃ በመዝሙር 34፤7 ላይ ያለውን ጥቅስ ነው።

«የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል»

ይህንን ጥቅስ በመያዝ ቅዱሳኑ መላእክት ሁልጊዜ በሰዎች ዙሪያ ሰፍረው ስለሚገኙ ማዳን፤ ጸሎት መቀበልና መልስ መስጠት የዘወትር ሥራቸው ነው ይላሉ። በሌላ ደግሞ መላእክት የሚኖሩበት ከተማ ኢዮር፤ ራማና ኤረር እንደሆነም ይናገራሉ። መላእክት ዘወትር በዚህ ምድር ባሉ ሰዎች ዙሪያ ሰፍረው የሚገኙ ከሆነ በኢዮር፤ ራማና ኤረር የሚኖሩት መላእክት ምንድናቸው? ወይስ መላእክት በሰማይም በምድርም በአንድ ጊዜ ይገኛሉ ማለት ነው? ተብለው ሲጠየቁ የመላእክትን ውሱን ተፈጥሮ ለማመን ይዳዳሉ። ነገር ግን በተግባር ይህንን ይቃረናሉ። ለምሳሌ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል በተፈጥሮ ሥፍራው በሰማይ እያመሰገነ ሳለ በማእዘነ ዓለሙ ሁሉ ስሙን የሚጠሩትን  ሰዎች ልመና ይሰማል? መልስም ይሰጣል ወይ? ተብለው ሲጠየቁ አዎ ይሰማል ለማለት አያፍሩም። እንዲያማ ከሆነ ቅዱስ ሚካኤል በአንድ ጊዜ በሁሉም ሥፍራ ይገኛል ማለት ነው። ይህ ደግሞ ትልቅ ስህተት ነው። ፍጡር በተፈጥሮው ውሱን የመሆኑን ማንነት ይንዳል።

  እርግጥ ነው፤ ቅዱሳኑ መላእክት ሰዎችን ይራዳሉ፤ ያግዛሉ። ይህንን ስንል መጋቤ ፍጥረታትየሆነውን  እግዚአብሔርን በሥራ ያግዙታል ማለት አይደለም።  ይህች ያለንባት ምድር ትሁን ዓለማት በሙሉ የሚተዳደሩት በእግዚአብሔር ብቃትና ሥልጣን እንጂ በመላእክት አጋዥነት አይደለም። እግዚአብሔር ብቻውን በቂ ነው። ሁሉን ተአምራት የሠራ እርሱ ብቻውን ነው።
«እርሱ ብቻውን ታላቅ ተኣምራትን ያደረገ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና» መዝ 136፤4
የተአምራትና የድንቅ ነገር ሁሉ ባለቤት እግዚአብሔር ብቻ ነው። ስለሆነም መላእክቱ ከእግዚአብሔር ትእዛዝ አንጻር ያደረጉትን እያየን መላእክቱን በውዳሴና በስባሔ የምናቀርብላቸው አምልኮ የለም። ደግሞም ቅዱሳኑ መላእክት የሚኖሩባቸውን ዓለመ መላእክት ትተው በዚህ ምድር የሚዞሩበትም ሁኔታ እንዳለ መጽሐፍ ቅዱስ አይነግረንም። ይልቁንም ይህችን ምድር ያለመታከት የሚዞርባት ሰይጣን ብቻ ነው።
 ምክንያቱም ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጪ የፈረጠጠ እሱ ብቻ ስለሆነ ተቆጣጣሪ አልቦ ሆኖ ይኖራል። በራሱ ፈቃድ የት፤ የት እንደሚዞር ለፈጣሪው እንዲህ ሲል እናገኘዋለን።
«እግዚአብሔርም ሰይጣንን፦ ከወዴት መጣህ? አለው። ሰይጣንም፤ ምድርን ሁሉ ዞርሁአት፥ በእርስዋም ተመላለስሁ ብሎ ለእግዚአብሔር መለሰ» ኢዮብ 1፤7
ምድርን ለመዞር፤ በእሷ ላይም ለመመላለስ ፈቃድ አይጠይቅም። «ከወዴት መጣህ?» የሚለው የእግዚአብሔር ጥያቄ የሚያስረዳን አፈንጋጭና በፈቃዱ ያለትእዛዝ የሚዞር መሆኑን ነው። ቅዱሳን መላእክቱ ግን እንደዚህ አይደሉም። በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ሥራ አላቸው፤ ትእዛዝ ይቀበላሉ፤ ትእዛዝ ይተገብራሉ እንጂ እንደሰይጣን በሰዎች ስለተጠሩ ወይም ባይጠሩም ስለፈለጉ የትም አይዞሩም፤ ያለትእዛዝም አይንቀሳቀሱም። በሁሉም ሥፍራም በምልዓት አይገኙም።

  መጽሐፍ ቅዱስ በትንቢተ ዳንኤል ላይ የመላእክትን ውሱንነት፤ መውጣት፤ መውረድ በደንብ የሚያስረዳን ቃል እንዲህ ይላል።
«እነሆም፥ አንዲት እጅ ዳሰሰችኝ፥ በጕልበቴና በእጄም አቆመችኝ። እርሱም፦ እጅግ የተወደድህ ሰው ዳንኤል ሆይ፥ እኔ ዛሬ ወደ አንተ ተልኬአለሁና የምነግርህን ቃል አስተውል፥ ቀጥ ብለህም ቁም አለኝ። ይህንም ቃል ባለኝ ጊዜ እየተንቀጠቀጥሁ ቆምሁ። እርሱም እንዲህ አለኝ። ዳንኤል ሆይ፥ አትፍራ ልብህ ያስተውል ዘንድ፥ ሰውነትህም በአምላክህ ፊት ይዋረድ ዘንድ ካደረግህበት ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ቃልህ ተሰምቶአል እኔም ስለ ቃልህ መጥቻለሁ። የፋርስ መንግሥት አለቃ ግን ሀያ አንድ ቀን ተቋቋመኝ እነሆም፥ ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ እኔም ከፋርስ ነገሥታት ጋር በዚያ ተውሁት» ዳን 10፤10-13
ነቢዩ ዳንኤል ያከናወነው መንፈሳዊ ተጋድሎ በእግዚአብሔር ዘንድ ስለተወደደ ስሙ ያልተጠቀሰ አንድ መልአክ የተሰጠውን መልእክት ሊነግረው መጥቷል።   መልእክቱ ለዳንኤል ከመድረሱ በፊት የፋርስን መንግሥት የተቆጣጠረው የተቃዋሚ መንፈስ አለቃ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከውን መልአክ 21 ቀን መንገድ ላይ እየተዋጋ አዘግይቶታል። ያንንም የእግዚአብሔር መልአክ ሊያግዘው ቅዱስ ሚካኤል እንደመጣና ውጊያው ከቅዱስ ሚካኤል በዚያ እንደተወውና ወደእርሱ እንደወረደ መልአኩ ለቅዱስ ዳንኤል ሲነግረው እናነባለን።

ከዚህ ምንባብ የምንረዳው ፤
1/ መላእክት የሰዎች መልካም ሥራና ተጋድሎ በእግዚአብሔር ሲወደድ የማናውቀው መልአክ ሊረዳን፤ ሊያግዘን፤ ሊያድነን ከእግዚአብሔር ዘንድ ሊላክ እንደሚችል፤
2/ መላእክቱን ለእገዛና ለረድኤት የሚያመጣቸው የኛ ስራ በመላእክቱ ዘንድ ተቀባይነትና ተወዳጅነት በማትረፉ እንዳልሆነ፤
3/ አንድ መልአክ ወደተላከበት ስፍራ ሲሄድ የነበረበትን ሥፍራ እንደሚለቅ፤ በቦታ እንደሚወሰን፤ ባለጋራ ሊዋጋው እንደሚችል፤
4/ መላእክት እንደሚተጋገዙ፤ አንዱ ከአንዱ በኃይልና በሥልጣን እንደሚበልጥ፤
5/ መውጣትና መውረድ እንዳለባቸው፤ በሁሉም ስፍራ እንደማይገኙ ያስረዳናል።
ስለሆነም ቅዱሳን መላእክት ይራዱናል፤ ያግዙናል፤ ያድኑናል ሲባል ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር ባላቸው ግንኙነት የተነሳ በተልእኮ ሲመጡልንና ሲደርሱልን ብቻ ነው። ከዚያ ባሻገር ሰዎች ስም እየመረጡ፤ የኃይል ሚዛን እያበላለጡ ስለጠሯቸው የሚመጡ አይደለም።
እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የሚያስረዱን በእግዚአብሔር ትእዛዝ የሚላኩ መሆናቸውን ነው።
«የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር፥ እርሱ መልአኩን በፊትህ ይሰድዳል» ዘፍ 24፤7  «እግዚአብሔር መልአኩን ከአንተ ጋር ይልካል፥ መንገድህንም ያቀናል»ዘፍ 24፤40  «እግዚአብሔርም መልአኩን አዘዘው፥ ሰይፉንም በአፎቱ ከተተው» 1ኛ ዜና 21፤27  «እግዚአብሔርም ጽኑዓን ኃያላኑንና መሳፍንቱን አለቆቹንም ከአሦር ንጉሥ ሰፈር እንዲያጠፋ መልአኩን ሰደደ» 2ኛ  ዜና 32፤21  «መልአኩን የላከ፥ ከአምላካቸውም በቀር ማንም አምላክ እንዳያመልኩ» ዳን 3፤28  «አምላኬ መልአኩን ልኮ የአንበሶችን አፍ ዘጋ» ዳን 6፤22
አምላክ፤ ወልደ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ የማልኮስን ጆሮ ለቆረጠው ጴጥሮስ እንዲህ ብሎት ነበር። «
«ወይስ አባቴን እንድለምን እርሱም አሁን ከአሥራ ሁለት ጭፍሮች የሚበዙ መላእክት እንዲሰድልኝ የማይቻል ይመስልሃልን?» ማቴ 26፤53
 ለኢየሱስ በስቅለቱ ሰሞን የመያዝ፤ የመገፋት፤ የመንገላታት የመገረፍ መከራ ሁሉ ከአብ ዘንድ ትእዛዝ ሳይወጣ የሚያግዙት መላእክት አይመጡም ነበር። ፈቃዱን ሳይሆን የአብን ፈቃድ ለመፈጸም የመጣውም ይህንን ሁሉ ሊቀበል ነውና። ከዚህ ከኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት የምንረዳው እውነታ ቅዱሳን መላእክቱ ከአብ ትእዛዝ ሳይሰጣቸው የትም መሄድ የማይችሉት ወልድ የመጣው የአብን ፈቃድ ሊፈጽም ስለሆነ ነው። ተገቢ ለሆነው የሰዎች ልመናና ጸሎት የሚያስፈልገውን የሚያደርገው ሁሉን አዋቂ በሆነው በእግዚአብሔር ትእዛዝ ሲላኩ ብቻ ነው።
የሰዎች ድርሻ ወደእግዚአብሔር መጮኽና መለመን ሲሆን ምላሹን ደግሞ የሚያውቀው እርሱ ብቻ ነው። «መላእክቱን በስማቸው ስንለምንና ስንማጸናቸው ይሆንልናል፤ ይደረግልናል»የሚሉ ሰዎች ቆንጽለው የሚያቀርቧት የመዝሙር 34፤7 ጥቅስ «የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል» የሚለውን ነጥለው በማውጣት ቢሆንም የዚህ አጋዥ መከራከሪያ ጥቅስ ሙሉ ማስረጃ ግን ከላይ ከፍ ባለው ቁጥርና ከታችም ዝቅ ብሎ በተጻፈው የምንረዳው፤ እግዚአብሔር ላይ ብቻ እንድንታመን የሚያደርጉ ናቸው። ሙሉ ጥቅሱ ይህንን ይመስላል።
«ይህ ችግረኛ ጮኸ፥ እግዚአብሔርም ሰማው፥ ከመከራውም ሁሉ አዳነው።
የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል።
እግዚአብሔር ቸር እንደ ሆነ ቅመሱ እዩም በእርሱ የሚታመን ሰው ምስጉን ነው።
የሚፈሩት አንዳችን አያጡምና ቅዱሳኑ ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ፍሩት» መዝ 34፤ 6-9

ነቢዩ ዳዊት በደረሰው ችግር ወደእግዚአብሔር ጮኸ፤ እግዚአብሔርም ሰማው፤ ከመከራውም አዳነው። የእግዚአብሔርም መልአክ እግዚአብሔርን በሚፈሩ ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፤ በታዘዘም ጊዜ ያድናል። ምክንያቱም በእግዚአብሔር የሚታመኑና እሱንም የሚፈሩት አንዳች አያጡምና። ቁጥር 8 እና 9  በእግዚአብሔር መታመንና መፍራትን ገንዘብ ያደረጉ ሁሉ ምላሽ እንደሚያገኙ ያስረዳናልና።

«ቅዱሳን መላእክቱ በዚህ ምድር እየዞሩ ለሰዎች የሚራዱና የሚያግዙ በመሆናቸው በስማቸው የሚደረገውን የሰዎችን ልመናና ጸሎትም ይሰማሉ» የሚል ክርክር የሚያነሱ ሰዎች መላእክቱ በቀጥታ ታዘው ያደረጉትን መነሻ በማድረግና በማድነቅ እንጂ ቅዱሳኑ መላእክት ራሳቸው ምሥጋናንና ውዳሴን ተገቢያቸው እንደሆነ ሽተው እግዚአብሔርን ከሚያውቁ ሰዎች ሲቀበሉ አናይም። እንዲያውም በራእይ መጽሐፍ ላይ እንደምናነበው ቅዱስ ዮሐንስ፤ እግዚአብሔር በመልአኩ በኩል ስላደረገለት፤ ስለነገረውና ስላሳየው ነገር ሁሉ በፊቱ ወድቆ በሰገደ ጊዜ የተሰጠው ማስጠንቀቂያ እንዲህ የሚል ነበር።

«ልሰግድለትም በእግሩ ፊት ተደፋሁ። እርሱም፦ እንዳታደርገው ተጠንቀቅ፤ ከአንተ ጋር የኢየሱስም ምስክር ካላቸው ከወንድሞችህ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ፤ የኢየሱስ ምስክር የትንቢት መንፈስ ነውና አለኝ»       ራእ 19፤10
ዛሬ ግን ሰዎች «ለእግዚአብሔር ስገድ» የሚለውን የመልአኩን የማስጠንቀቂያ መልእክት ወደጎን ትተው «ለመልአኩም ስገድ» እያሉ ሲሰብኩ ይገኛሉ። መልእክት አድራሹ መልአክ ከዮሐንስ በተሻለ ስለመልእክቱ ምንነት እውቀት እንዳለው እርግጥ ነው። ከዐውደ ንባቡ እንደምንገነዘበውም ስለመልአኩ ቢያንስ ሁለት ዐበይት ነገሮችን እንረዳለን። አንድ፤ መልእክቱን በቀጥታ ከእግዚአብሔር እየሰማ ለዮሐንስ የሚያደርስ መሆኑን። ሁለትም፤ መልአክቱ ከዮሐንስ ዘንድ ከመድረሱ በፊት በመልአኩ ዘንድ የተሰማና የታወቀ መሆኑን ነው። ስለሆነም ዮሐንስ ስግደትን ለመልአኩ መስጠት የፈለገው መልአኩ የፈጣሪ የቅርብ ባለሟል በመሆኑና የሚያየውን ግርማ በመፍራት እንዲሁም ይዞለት የሚመጣው መልእክቶቹ እጅግ ከባድና ከዚህ በፊት በሕይወቱ ሰምቶአቸው የማያውቅ ከባድ የሕይወት ልምምድን የሚያሳዩ በመሆናቸው የተነሳ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል።
ስለዚህ «ተጠንቀቅ» ያለውን ቃል መጠበቅ ብልህነት ነው።
ክፍል ሦስት ይቀጥላል …..

Saturday, September 5, 2015

ባለቤቴን አፈቅረዋለሁ ትዳራችንም ፅኑ ነው !!


ከዚህ በፊት ስለተከስተ ጌትነት የአሜሪካው አማርኛ ድምጽ አየር ላይ ካዋለው መረጃ ተነስተን ዐመጻውን በንስሐ እንዲተው የሚያሳስብ ዘገባ አውጥተን ነበር። በንስሐ ስለመመለሱ እየተናገረ ባለበት ሁኔታ የባለቤቱን ጽናትና ያላትን የይቅርታ ልብ ተመልክተን ወደፍቺና የግድያ ተግባር ላለመሄድ የተጓዘችበትን የክርስትና አርአያነት «አሌክስ አብርሃም» የዘገበውን ልናስነብባችሁ ወደድን።
 


ባለቤቴን አፈቅረዋለሁ ትዳራችንም ፅኑ ነው !!
 (አሌክስ አብርሃም )

ይቅርታ መቸም እንደሚወራው ቀላል ነገር አይደለም !! በተለይም በባልና በሚስት ማሃል በአንድኛው ወገን ለትዳር አለመታመን ሲከሰት የተበደለው አጋር ይቅር ለማለት ይቸገራል …እንዲህ አይነቱ ነገር ሲከሰት ሚስት ባሏን በመፍለጫ …በተኛበት አቅምሳው እጇን ለመንግስት የሰጠችበት ዜና ሰምተናል ….ባልም በገጀራ ሚስቱን አመሳቅሎ ዘብጥያ የወረደባቸውን በርካታ ዜናዎች በቲቪ ተመልክተን አማትበናል ! የራሱ ጉዳይ ያሉም ትዳራቸውን በትነዋል !
ይህን ነገረ ካለነገር አላነሳሁትም …. በዚያ ሰሞን ከወደአሜሪካ የሰማነው ዜና የሚታወስ ነው …..ዘማሪ ተከስተ ጌትነት ሚስቴን አማግጦብኛል ያለ አንድ ሰው በየሚዲያዎቹ ቀርቦ ፍረዱኝ ሲል ሁላችንም ሰምተን ጉድ ጉድ ብለናል ! ማገጠች የተባለችውም ሴት በየሚዲያው እንዴት ካንድ አይሉ ሁለት ሶስት ጊዜ ወዳረፈበት ክፍል ጎራ እያለች ‹‹ሳትፈልግ ›› አብረው እንደተኙ በዝርዝር መግለፅዋ ይታወሳል ….ፓስተር ተከስተ ጌትነትም ይህንኑ አምኖ ይቅርታ መጠየቁ እንደዛው ..ሚዲያውም እስኪበቃው አናፍሶታል !ዘማሪ /ፓስተር ተከስተ በሚያገለግልበት ቤተክርስቲያንም አገልግሎቱን እንዳቆመ ተዘግቦ ነበር !!
ታዲያ ያኔ አገር ይያዝ ያለው ሚዲያ ለዚችኛዋ ዜና ጭጭ ማለቱ ስለገረመኝ …ያው ችግሩን ካወራን መጨረሻውስ ምን ሆነ የሚለውን ዝም ማለቱ ተገቢ አይደለም በሚል ይችን ፅሁፍ እነሆ አልኩ ……. ትላንት ‹‹የእውነት ቃል ጎስፕል ሚዲያ›› ‹‹የእንደገና አምላክ›› በሚል ርእስ እንደዘገበው ከሆነ ዘማሪ ጌትነት ባለፈው ቅዳሜ በምእመኑ ፊት ቁሞ ስለሁኔታው ምስክርነቱን ሰጥቷል … ባለቤቱ የምስራችም የሆነውን ሁሉ ይቅር እንዳለች በሚገልፅ አጭር ቃል እንዲህ ብላለች ‹‹ ባለቤቴን አፈቅረዋለሁ ትዳራችንም ፅኑ ነው ›› ፓስተር ጌትነትም ወደአገልግሎቱ ተመልሷል !! መቸስ ይቅርታ ጥሩ ነው … መልካም የትዳርና የአገልግሎት ጊዜ ይሁን እያልኩ ….ምንም እንኳን የመጀመሪያ ተጎጅዋ እርሷ ብትሆንም እንዲህ በችግር ጊዜ የራሷን ብሶት ትታ ከባሏ ጎን የምትቆም ሚስት ማግኘት መታደል ነው የሚል የግል አስተያየቴን ጨምሬ ላብቃ !!

Wednesday, August 26, 2015

በአመልካች ጣትህ ሌላው ላይ ስትጠቁም፤ ሦስቱ ጣቶችህ ይመሰክሩብሃል!





  አንዳንድ ሰዎች የራሳቸውን ግፍ፤ ዐመጻና ኃጢአት ለመሸፈን የአቻቸውን በደልና ዐመጻ በማቅረብ ለመደበቅ ይሞክራሉ። ነገር ግን የሌላው ሰው ዐመጻና በደል መቁጠር የራስን የኃጢአት ደብዳቤ አይፍቀውም። በየትኛውም ማእዘን የሚገኙ ዐመጸኞች ከዐመጻቸው እስካልተመለሱ ድረስ ዐመጻቸው ሰላማዊውን ሊያጠፋ ይችላል።  ከኋላ ይሁኑ ከፊት ዐመጸኞች የቆሙበት ሥፍራ ብቻውን ንጹሐን አያደርጋቸውም። ይልቁንም ሰላማዊው ላይ በሽታቸው እንዳይጋባ ቢቻል ሸክማቸውን በንስሐ እንዲያራግፉ ሊነገራቸው፤ ሸክሙ ተስማምቶናል ካሉም ራሳቸው ተሸክመው ገለል እንዲሉ ሊደረግ ይገባል።  ተፈጥሮ የሰጣትን ሁለት መልክ በመጠቀም ለማሳሳት ሞክራለች ተብሎ በምሳሌ እንደሚነገርላት የሌሊት ወፍ ከአይጦች ዘንድ ሄዳ ጥርሷን በማሳየት «እኔ የእናንተ ወገን ነኝ» ካለች በኋላ ከወፎችም ማኅበር ተቀላቅላ ክንፏን እያራገበች «የተከበራችሁ ወገኖቼ እንደምን አላችሁ!» እንዳለችው እንስሳ በሁለት ገጽ ለማታለል የሚሞክሩ የዘመኑ ተለዋዋጮች ራሳቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ ሸክም ሆነው ሳሉ የችግሯ ደራሽ ለመምሰል መሞከራቸው በዚህ ዘመን እንደማይቻል በግልጽ ሊያውቁት ይገባል።

   ሰሞኑን የምንመለከተው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደአዞ ሐረግ በጎን በቅሎ በዋናው ግንድ ላይ የተጠመጠመው በቅዱሳን ስም የሚጠራው ማኅበር ተራራ የሚያክል የራሱን ኃጢአትና ዐመጻ ላይደበቅ ሸሽጎ የሙስና ተዋጊና የቤተ ክርስቲያኒቱ አዳኝ ለመሆን ሲታትር እያየን ሲሆን በሞት የሚፈላለጋቸውንም ፓትርያርክ በማወዳደስ ላይ መጠመዱ «ቁርበት አንጥፉልኝ» የተባለውን ብሂል እንድናስታውስ አድርጎናል።

  እኛም ነገሩ ቢገርመን «አመልካች ጣትህን ስትጠቁም፤ ሦስቱ ጣቶችህ በራስህ ላይ ይመሰክሩብሃል» ልንለው ወደድን። ሙሰኞቹም፤ ማኅበሩም የቤተ ክርስቲያኒቱ ጠንቅ ከመሆን ባለፈ አንዳቸው የአንዳቸው አጣሪ፤ ጠቋሚና አባራሪ ሊሆኑ በፍጹም አይችሉም። ከዚህ በፊት በማኅበሩም ላይ ሆነ በነፍሰ በላ ሙሰኞቹ ላይ ተከታታይ ጽሁፍ በማቅረብ ሁሉ አጥፊዎች  መሆናቸውን በግልጽ ተናግረናል። አሁንም የምንናገረው ያንኑ በመድገም ነው። የምናሰምርበትም እውነት «ከማኅበሩና ከሙሰኞቹ የትኛው በመወገድ ሊቀድም ይገባል? የሚለው ካልሆነ በስተቀር በሁለቱም አላስፈላጊነት ላይ አንዳችም ብዥታ የለንም»

   ስለሆነም በማኅበሩ ላይ ከዚህ በፊት በፓትርያርኩ የተያዙ አቋሞች በሙሰኞች ማጥራት ሽፋን የሚታለፍ ወይም የሚቀየር ከሆነ ከሁለት ጅቦች መካከል አንዱን ጅብ ምርጫ የመውሰድ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመታደግ የሚደረግ እንቅስቃሴ አይደለም እንላለን። በመካከላቸው የመጠንና የዓይነት ካልሆነ በስተቀር ቤተ ክርስቲያኒቱን በሚግጡ ጅቦች መካከል የተግባር ልዩነት ስለሌለ ሁሉም ቦታቸውን ሊይዙ የሚገባቸው የጥፋት ኃይሎች መሆናቸው አያጠያይቅም። እንደምንመለከተው ያለው መገፋፋት በሦስት የሚከፈል ይመስለናል።

  1ኛው- ጫንቃው የደነደነ ማኅበር ከቦታው ሊወገድ የተገባው ቢሆንም  የተወሰኑ አስተዳዳሪዎችና ከታች ያሉ ዘራፊዎች፤ ቅዱስ ነኝ የሚለውን ማኅበር የሚጠሉት ማኅበሩ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ስላደረሰው በደልና ግፍ በመቆርቆር ብቻ ሳይሆን በስለላ መረቡ ስለተጠለፉና እዳ በደላቸው ስለተጻፈባቸው፤ ከሚከተላቸው ፍርሃትና ድንጋጤ ለመገላገል ሲሉ በሐቅ ከሚታገሉት ጋር በኅብረት የሚጮኹ አንድ ቡድን ናቸው።

 2/ ማኅበሩ ቤተ ክርስቲያኒቱን መስሎና አኅሎ በላይዋ ላይ ነግሶ በስሟ መነገዱ የታያቸው፤ በመንገድ ላይ ቆሞ እንቅፋት የሆናቸው፤ ለስውር ዓላማው የስለላ ቡድኑን ያወቁ፤ የቤተክርስቲያኒቱን ልጆች ለራሱ መመልመሉ የቆጫቸው፤የገቢ አቅሙን እያደለበ፤ ሀብቷን ለራሱ ዓላማ ሲጠቀም የተመለከቱ፤ የኃጢአት በደል ጸሐፊ፤ ለሲኖዶስ ክፍፍል ረጅም እጅ ያለው መሆኑን የተረዱ በትክክል አምነው የሚታገሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች በሁለተኛ ረድፍ አሉ። ይህ ረድፍ ድምጹን የሚሰማና የሚያስተባብረው የበላይ አመራር ቢኖር ኖሮ ውጤታማ ሥራ ለመስራት የሚችልና በሙሰኛ አስተዳዳሪዎችም ይሁን በማኅበሩ ተግባር የመረረው ቡድን ነው ።

  3/ ራሱን ቅዱስ፤ ጻድቅና የቤተ ክርስቲያኒቱ መድኅን አድርጎ የተነሳ፤ በገንዘቡ፤ በኃይሉ፤ በአስተዳደሩ፤ በሴራ መዋቅሩና በእንቅስቃሴው አደገኛ የሆነ፤ የራሱን የሲኖዶስ አባላት ያደረጃ፤ ስለቤተክርስቲያኒቱ ሳይሆን ከጥቅሙ ጋር ለቆመ ሰይጣንም ቢሆን የሚተባበር፤ ሰዎችን በማጥመድ አገልጋይ ለማድረግ የሚተጋ፤ የሰዎች የእዳ በደል መዝጋቢ፤ ሰላይ፤ በዝሙት የረከሰ፤ ነጋዴ፤ አስመሳይና አታላይ ነገር ግን በሩቅ ሲያዩት ቆዳው ከእባብ የለሰለሰ ማኅበር፤ ማኅበረ ቅዱሳን የሚባለው በሦስተኛ ረድፍ አለ።
በዚህ መካከል ከወዲህም ከወዲያም የሚዘምቱ፤ ነገር የሚያማቱ፤ የሚያወሻክቱ፤ የአስመሳዮች ቡድን እንደወቅቱ ሁኔታ፤ ኃይል ወዳጋደለበት የሚያጋድሉ የአስተሳሰብ ድሆች ከሲኖዶስ ጀምሮ በየደረጃው ቢኖሩም ተጽእኖ ፈጣሪ ሆነው ለእክል የሚበቃ አቅም የላቸውም።

 በሦስቱ ረድፎች ያለውን የኃይል አሰላለፍ ተመልክቶ ተገቢ ከሆነው ወገናዊ ኃይል ጋር በመቆም እንቅስቃሴ መውሰድ የተገባ ቢሆንም እስካሁን ከወሬ ባለፈ የሚታይ እርምጃ ብዙም ሲወሰድ አይታይም።
ወቅቱ በፈጠረው የቤተክርስቲያኒቱ ተግዳሮትና የችግር እሳት መካከል የተገኙትት ፓትርያርክ ማትያስ ምን ዓይነት እርምጃ፤ መቼና ከማን ጋር ሆነው መውሰድ ይችላሉ? የሚለው ጥያቄ ምላሽ የሚያሻው ወቅታዊ ጉዳይ ይመስለናል። አካሄዱን በሳተ፤ ውጤቱም ምን ሊሆን እንደሚችል ባልተጠና ውሳኔ የሚወሰድ እርምጃ ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል። ስለሆነም በገበያ ግርግር መካከል የሚዘለው ማኅበር የራሱን የቤት ሥራ ሳይጨርስ «ከፓትርያርኩ ጋር አለሁ፤ አለሁ» የሚለው ጉዳይ አሳሳቢ ነው።
ስለማኅበሩም ይሁን ማኅበሩን በሚደግፉ ነገር ግን ብዙ ችግር ባለባቸው ሰዎች ዙሪያ ትንፍሽ የማይለው «ሐራ» የተባለው ብሎግ የማኅበሩ ቀኝ እጅ ስለሆኑት አባ ማቴዎስ ለሙስና ውጊያ የመዘጋጀታቸውን ዜና መስራቱ እንዲሁም የፓትርያርኩን ፈቃደኝነት አደበላልቆ ማቅረቡ ችግሩን ለመቅረፍ ሳይሆን የማኅበሩን ጉዳይ ለመሸፈን አጋጣሚ ማግኘቱን የሚያመለክት ነው።
 ስለሆነም ለፓትርያርኩ የመፍትሄ ሃሳብ ሊሆኑ የሚችሉ ነጥቦችን ለመጠቆም እንወዳለን።

  1/ በቅድሚያ ፓትርያርኩ ብቻቸውን ተንቀሳቅሰው፤ ብቻቸውን ጮኸው፤ ብቻቸውን ታግለው የሚያመጡት ውጤት እንደሌለ በመረዳት የተሻለ ግንዛቤ፤ እውቀትና የአስተዳደር ክህሎት ያላቸውን የቤተ ክርስቲያኒቱ ችግር ግድ የሚላቸውን ሰዎች በሥራ አጋርነት በዙሪያቸው ማሰባሰብ ያስፈልጋቸዋል። ከጳጳሳቱም ብዙዎቹ በማኅበሩ የተጠለፉ ወይም ከሙስናና ከዘረኝነት ጋር የተሳሰሩ ስለሆነ ከጳጳሳቱም ሆነ ከበታች ሹማምንት መካከል ጥንቃቄ የታከለበት ምርጫ መደረግ አለበት። የፓትርያርኩ ልዩ ፀሐፊ፤ የፕሮቶኮል ሹም፤ የውጪ ግንኙነት ክፍል፤ የፓትርያርኩ ቢሮ ኃላፊ እና ሌሎች ተጨማሪ ክፍሎችን ማደራጀት ያስፈልጋል። የፓርትያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት በሆነው አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ውስጥ ሥራ አስኪያጅ፤ የሀገረ ስብከቱ ፀሐፊ፤ የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ወዘተ ክፍሎች ፓትርያርኩ ለሚያደርጓቸው ቀጣይ እርምጃዎች ወሳኝ ስለሆኑ ይህንን በተጠናና መልኩ እንደገና ማዋቀር የግድ ይላል። የፓትርያርኩ ጽ/ቤት የየዕለት የሥራ ውሎ ከበታች ክፍሎች ሪፖርት በመቀበልና ለፓትርያርኩ በማቅረብ ተከታታይ የሥራ መመሪያና ትእዛዝ በማስተላለፍ ያልተቋረጠ ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል።

2/ እንደአጭር ጊዜ የማስተካከያ እርምጃ  ከላይ በተራ ቁጥር 1 በተመለከተው ነጥብ ውስጥ ያሉ አካሎችና ሌሎች አጋዦች ያሉበት አጣሪ ኮሚሽን በማዋቀር በሚያደርጉት ምርመራ በሙስና የከበሩ፤ ከሌላቸው ደመወዝና ልዩ ገቢ ውጪ ሃብት ያከማቹ፤ አላግባብ የበለለጸጉ፤ የገንዘብ ብክነትን ያስከተሉ አሰራሮች ሁሉ ዝርዝር መረጃቸውና ከነመፍትሄ ሃሳቦቻቸው በማቅረብ ማስተካከያና የሕግ እርምጃ በማስወሰድ በፍጥነት መግታት ተገቢ ወቅታዊ እንቅስቃሴ መሆን አለበት እንላለን። ነገር ግን እንደረጅም ግብ ሊታይ የሚገባው ጉዳይ በፓትርያርኩ የሚመራ የመዋቅር ጥናትና ማሻሻያ መምሪያ በማቋቋም ከዘመናዊ አስተዳደር ጋር ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማዘመን የመዋቅር ማሻሻያ ጥናት መደረግ ይገባል። 

ከዚያ ባሻገር በማኅበሩ ግፊት፤ በአስፈጻሚ ጳጳሳቱ በኩል ሙስናን እናጣራለን ማለቱ «በቆሻሻ መጥረጊያ ቤት መወልወል ይሆናል»

3/ ማኅበረ ቅዱሳን ከዚህ በፊት እንደተወሰነው ሀብትና ንብረቱን እንዲያስመዘግብ፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሞዴላ ሞዴሎች እንዲጠቀም፤ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ያለውን ሂሳብ በቤተ ክርስቲያኒቱ ኦዲት እንዲያስመረምር፤ ለወደፊትም በቤተ ክርስቲያኒቱ ተወስኖ በሚሰጠው ደንብ እንዲመራ የተላለፈውን ውሳኔ ያለምንም ማመንታት ተግባራዊ ማድረግ የግድ ይላል። በዚህ ዙሪያ ፓትርያርኩ የገቡትን ቃል በመጠበቅ ማስፈጸም እንዳለባቸው እናምናለን።
ስለሆነም ስለሙስናና ስለገንዘብ ብክነት ለመናገር በዘረኝነትና በእከከኝ ልከክህ የተሳሰሩ የጥቅም ተጋሪ ጳጳሳቱና ከኋላ በሚገፋቸው ማኅበር ሳይሆን እጃቸው ንጹህ የሆነ፤ የቤተ ክርስቲያኒቱን የጣሪያ ሳር ያልመዘዙ ልጆችዋ በኩል በመሆኑ ፓትርያርኩ ቆም ብለው በአስተውሎት እንዲመለከቱት ልናሳስብ እንወዳለን። እርግጥ ነው፤ ቤተ ክርስቲያን ችግር ላይ ነች። ነገር ግን ችግሯን ተተግነው ደረስንላት የሚሉ ሁሉ የየራሳቸውን ስውር ዓላማ ደብቀው የተነሱ ስለሆነ ጥንቃቄ መወሰድ ይገባዋል።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፤ 

በቅንነት የምንገልጽልዎ ነገር የቤተ ክርስቲያኒቱ ችግር የሚያንገበግባቸው፤ በታማኝነት፤ በፈሪሃ እግዚአብሔር ለማገልገል መንፈሳዊነቱም ፈቃደኝነቱም ያላቸው የተማሩ ልጆች ስላሉአት በጥንቃቄ አጥንተው ለቀጣይ እርምጃ እንዲበራቱ እንጠይቃለን። ማኅበሩም አጋጣሚዎችን ለራሱ በሚመቸው መልኩ እየተጠቀመ፤ የተወሰነበትን ውሳኔዎች ለማስቀልበስ የሚሄድበትን መንገድ ሊዘነጉ አይገባም። ቁርጠነቱ ካለ ሙሰኞችንም፤ ማኅበሩንም ቦታ ቦታቸውን ለማስያዝ ሰውም፤ ጊዜም፤ ኃይልም አለ!!