1/ እንደመግቢያ፤
መላእክትና ሰዎች በእግዚአብሔር ግብር የተፈጠሩ
ፍጡራን ናቸው። በኦሪት ዘፍጥረት የመጀመሪያዎች ሁለት ምዕራፎች እንደተመለከተው
በላይ በሰማይ፤ ከታች በምድርና በጥልቅ ውሃማ አካሎች ሁሉ እግዚአብሔር በለይኩን ቃሉ (ከአዳም በስተቀር) የፈጠራቸውን ሥነ ፍጥረቶች እናገኛለን። በመሠረተ
እምነት ደረጃ ፍጡር ስንል ፈጣሪ ወይም አስገኚ ያለው ነገር ማለታችን ነው። መፍጠር ወይም የሌለውን ነገር ማስገኘት ማለት አንድን
ነገር መሥራት ወይም መፈብረክ ማለት አይደለም። የነገረ መለኮት ምሁራን መፍጠርን ወይም ማስገኘትን ሲገልጹ «from
nothing to something» በማለት ይገልጹታል። «ከምንምነት ወደአንድ ነገርነት» ማምጣት ማለት ነው። እግዚአብሔር ለመፍጠር መነሻ ሃሳብ ወይም ጥሬ ነገር /substance/ አያስፈልገውም።
ፍጡራን ግን ይህንን ማድረግ አይቻላቸውም። ለምሳሌ
ወንበር የሠራ ሰው ፈበረከ ወይም ሠራ ቢባል እንጂ «ፈጠረ ወይም አስገኘ» ሊባል የተገባው አይደለም ይላሉ ምሁራኑ። ምክንያቱም
«ወንበር» የተባለውን ቁስ ለመሥራት አንዳንድ ነገሮች
«something» የግድ ያስፈልጉታልና ነው። ይህም የሥራ ጉዞ «from something to something» በቅርጽ፤ በመጠንና
በይዘት ይለውጠዋል እንጂ /from nothing to something/ ከምንም ነገር ሳይነሳ «ወንበር» የተባለውን ቁስ ማቅረብ
አለመቻሉ የጉድለቱ አንድ አስረጂ እንደሆነ በአመክንዮ ያቀርባሉ። ያንንም ወንበር እንኳን ለመሥራት ወይም ለመፈብረክ የግድ የሚያስፈልጉት ጥሬ
ሀብቶች /raw materials/ የሠራተኛው የራሱ ግኝቶች አይደሉም።
ስለሆነም ፍጡራን በሙሉ ያላቸው ሁኔታ፤ ችሎታና
ብቃት ያልተወሰነ፤ በአፈጣጠር ያልተገደበ አይደለም። በሥራቸው ሁሉ ምሉዕነት ያለው፤ ጉድለት አልቦነትም የማይጎበኘው አይደለም።
መላእክትና ሰዎች መነሻም፤ መድረሻም አላቸው። መነሻና መድረሻ ያለው ፍጥረት ደግሞ በአንድ ጊዜ በስፍሐትና በምልዓት በሁሉ ሥፍራ
መገኘት አይችልም። በሥራው ሁሉ በብቃትና በራሱ ኃይል የማከናውን ፍጹምነት የለውም።
የእግዚአብሔር ባህርይ ግን ከዚህ የተለየ ነው። እግዚአብሔር የሁሉ ነገር ፈጣሪና
አስገኚ ስለሆነ መነሻም መድረሻም የለውም። ኋለኛ የሌለው ፊተኛ፤ ፊተኛም የሌለው ኋለኛ እሱ ብቻ በመሆኑ አልፋና ኦሜጋ እንለዋለን።
መጽሐፍ ቅዱስ « በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይና
ምድርን ፈጠረ» ዘፍ 1፤1 ሲል እግዚአብሔር ከምንም ነገር «from nothing to something» ለመፍጠር ወይም ለማስገኘት ምንም ተጨማሪ ነገር እንዳላስፈለገውና እሱ ብቻ
እንደተቻለው እንረዳለን። ሰማይና ምድርን ግን የፍጥረት መነሻ ሆነው ተከስተዋል። ሁለቱም በሥፍራ፤ በቦታና በሁኔታ ተወስነዋል።
ምድር በውስጧ የተገኙት ፍጥረታትም ሁሉ መነሻና መድረሻ፤ መጠነ ውሱንነትና መጠነ አኽሎኝነት ይዘው መገኘታቸውን በእያንዳንዱ የሥነ
ፍጥረታት ጠባይዓት ላይ እንመለከታለን። ከፍጥረታት አንዱ ክፍል የሆነው የሰው ልጅን ብንመለከት በፍጥረተ ጠባዩ የአስተሳሰብ፤ የአፈጣጠርና የማንነት ብቃት በተሰጠው እሱነቱ ልክ ተወስኖ ይገኝበታል።
እርግጥ ነው፤ ስለሃይማኖት ጥሩ ግንዛቤ ያለው
ሰው ያለብዙ ምክንያታዊ ውጣ ውረድ «ፍጡራን በአንድ ጊዜ በሁሉ ሥፍራ መገኘት አይችሉም!» ብሎ መልስ ሊሰጥ ይችላል። ደግሞም የሚሠመርበት
እውነት፤ በሁሉ ሥፍራ፤ በአንድ ጊዜ፤ በስፍሐትና በምልዐት
(በምሉዕ ኵለሄነት) የመገኘት ብቃት ከእግዚአብሔር በስተቀር ለፍጡር አይቻለውም የሚለውን እውነት አምኖ
መቀበል ነው። ሁሉን ቻይነት/Omnipotence/ ከእግዚአብሔር በቀር ለማን ይቻለዋል? ለማንም!!
«ከማኅፀን የሠራህ፥ የሚቤዥህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሁሉን የፈጠርሁ፥ ሰማያትን ለብቻዬ የዘረጋሁ ምድርንም ያጸናሁ እግዚአብሔር እኔ ነኝ ከእኔ ጋር ማን ነበረ?» ኢሳ 44፤24
በላይ በሰማይ፤ በታች በምድር በሁሉም ሥፍራ
ያለና የሚኖር፤ የሚሰማም፤ መልስ የሚሰጥም እግዚአብሔር ብቻ ነው።
ቅዱሳን መላእክት ይሁኑ ቅዱሳን ሰዎች በሰማይ
ሥፍራቸው ሳሉ በምድር የሚደረገውን ሁሉ ያውቃሉ? ያያሉ? ይሰማሉ? በፍጹም አያውቁም፤ አያዩም፤ አይሰሙም። በሰማይ ሳሉ በምድር ያለውንም የሚያውቁ ከሆነ በስፍሐትና በምልዓት ይገኛሉ
ማለት ነው። ይህ ደግሞ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ያለ ስህተት ነው። ከላይ ለመግለጥ እንደተሞከረው በአንድ ጊዜ በሁሉም ስፍራ የመገኘትን
ብቃት የፈጣሪ እንጂ የፍጡራን እንዳልሆነ የገለጽነውን እውነታ የሚጻረር ይሆናል።
2/ «እግዚአብሔር ብቻውን በሁሉ ሥፍራ አለ»
የምንለው ለምንድነው?
መልሱ አጭር ነው። እግዚአብሔር በላይ በሰማይ፤
በታች በምድርም፤ በሁሉ ሥፍራ መገኘት የሚችለው በላይ በሰማይ ይሁን በታች በምድር ላለው ነገር ሁሉ ፈጣሪና አስገኚ ስለሆነ ነው።
ከባዶነት ወደአንድ ነገርነት ማምጣት የቻለ ፈጣሪ፤ በፈጠረው ነገር ሊገደብ፤
ሊወሰን፤ ሊከለከል አይችልም። ፍጥረታት ግን በዚህ ብቃት ውስጥ ሊገቡ አይችሉም። ምክንያቱም ፍጥረታት በቦታ፤ በሁኔታና በአፈጣጠር
ውሱን ስለሆኑና ከፈጣራቸው እግዚአብሔር ጋር ሊስተካከሉ ስለማይችሉ ነው። የቅዱሳን መላእክትና የቅዱሳን ሰዎች ብቃት እግዚአብሔር
በሰጣቸው መጠንና ፈቃድ የተወሰነ ነው። መላእክቱ ይሁኑ ሰዎች ፍጡር
እንጂ ፈጣሪዎች ባለመሆናቸው ፍጥረተ ዓለም ይወስናቸዋል። እግዚአብሔር ግን እንዲህ አይደለም። በትንቢተ ዳንኤል ላይ እንዲህ እንደተመለከተው፤
«በምድርም የሚኖሩ ሁሉ እንደ ምናምን ይቈጠራሉ፤
በሰማይም ሠራዊት በምድርም ላይ በሚኖሩ መካከል እንደ ፈቃዱ ያደርጋል፤ እጁንም የሚከለክላት ወይም ምን ታደርጋለህ? የሚለው የለም»
ዳን 4፤35
3/ የቅዱሳን መላእክት ውሱንነትና በስፍሐት
አለመገኘት
እያየን በመጣነው ከእግዚአብሔር ስፉሕነትና ከፍጥረታት
ውሱንነት የተነሳ መላእክት በምልዐት በሰማይም በምድርም ሊገኙ እንደማይችሉ
እናምናለን። ነገር ግን ከላይ የገለጽነውን ጉዳይ ዳግም ማንሳት ያስፈለገን ዐቢይ ምክንያት ብዙ ሰዎች የመላእክትን ውሱን
መሆን፤ በሁሉ ሥፍራ በአንድ ጊዜ አለመገኘት አምነው ሲያበቁ ከዚህ
ተቃራኒ በሆነ አቋም ቅዱሳን መላእክት በአንድ ጊዜ በሰማይና በምድር
የመገኘት ብቃት እንዳላቸው የሚያስተምሩና አምነው የሚያሳምኑ ሰዎች
በመኖራቸው ነው።
ሰው በአንድ ጊዜ አማኝም፤ ከሀዲም መሆን አይችልም።
ምክንያቱም ጣፋጭ ፍሬ የሚሰጥ ዛፍ ፤ በጭራሽ መራራና ጣፋጭ ፍሬ
በአንድ ጊዜ ማፍራት እንደማይቻለው ሁሉ በእምነት የቅዱሳን መላእክትንም ሆነ የቅዱሳን ሰዎችን የውሱንነት ተፈጥሮ ካመንን በኋላ
በምንም ዓይነት መንገድ ከዚህ በተጻራሪ መቆም ስለማይቻለን ነው።
ብዙ ጊዜ ሰዎች አምኛለሁ ባሉበት እምነት ውስጥ
ክህደት መሰል ነገር የለም ብለው የሚከራከሩት ስላመኑት እምነት በቂ እውቀትና ግንዛቤ ስለሌላቸው ነው። ለዚህ ጥሩ አብነት የሚሆነን
ነጥብ፤ በአንድ ወቅት ሰዱቃውያን ወደ ጌታችን፤ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቀርበው ትንሣኤ ሙታንን ለመቃወም «በምድር ሰባት ባል ያገባች
ሴት በሰማይ ለማንኛቸው ትሆናለች?» ብለው በጠየቁት ጊዜ የሰጣቸው መልስ
በየትኛውም ዘመንና ጊዜ ለሚነሳ ጥያቄ እንደአስረጂ አቅርበን እዚህ ላይ ብንጠቅሰው ተገቢ ይመስለናል።
«ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ መጻሕፍትንና
የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ትስታላችሁ» ማቴ 22፤29 አላቸው።
እግዚአብሔርን የሙታን ብቻ አምላክ አድርጎ መንሥኤ
ኃይሉን መካድ ከባድ ስህተት ነው። መጻሕፍት የሕያዋን አምላክ ብለው ሲመሰክሩ ይህንንም አለማወቅ ስንፍና ነው። ለዚህ ሁሉ ምክንያቱ
አንድ ነው።
ሰዎች «እናምንበታለን» ባሉት ነገር ውስጥ የሚገቡ ስህተቶች ሁሉ ተቀባይነት
አግኝተው ሃይማኖታዊ ካባን የሚላበሱት «መጻሕፍቱንና የእግዚአብሔርን ኃይል» በደንብ ካለመረዳታቸው በሚመጣ ጉድለት እንደሆነ ሁሉ፤
በዚህም ዘመን ያሉ ስህተቶችን እንዲሁ እንገነዘባቸዋለን። ሰዱቃውያን
የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን በእጃቸው ይዘው ሲያበቁ ስለትንሣኤ ሙታን አለመኖር አምነው መቀመጣቸው ላያስገርም ይችላል። ምክንያቱም
ሰዎች የእግዚአብሔር ኃይል መገለጫ መንገዶችን ወደሚናገሩ ወደ ቅዱሳት መጻሕፍቱ ይሄዳሉ እንጂ መጻሕፍቱ ወደሰዎቹ ሊመጡ አይችሉም
ነው። በእጃቸው ያለው መጻሕፍትማ የሚሉት እንደዚህ ነበር።
«ስለ ትንሣኤ ሙታን ግን እኔ የአብርሃም አምላክ፥
የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ የሚል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ እናንተ የተባለውን አላነበባችሁምን? የሕያዋን አምላክ
ነው እንጂ የሙታን አይደለም» እያለ እውነቱን ቢናገርም እያየበቡ
ስለማያስተውሉ የትንሣውን ኃይል ክደዋል (ማቴ 22-31-32 ፤ ዘጸ
3፤6 )
ሰዱቃውያኑ ከተቀበሏቸው መጻሕፍት ውስጥ የተጻፈውን
አለማወቃቸው የሚያስረዳን ነገር መጻሕፍትን በመያዝ ወይም በማንበብ እውነት ሁልጊዜ ይገለጣል ማለት አይደለም። መረዳቱ ካላቸው ሰዎችም ዘንድ ለኛ ያልተገለጠን እውነት ስለሚኖር ሌሎችን
በመጠየቅ ወይም የሚሉትን በማስተዋልና እንደእግዚአብሔር ቃል በመመርመር ወዳልደረስንበት እውነት ልንደርስ እንችላለን። እንደዚሁ
ሁሉ በዚህ ዘመንም ያሉ ሰዎች የቅዱሳን መላእክትንንና የቅዱሳን ሰዎችን ውሱንነትና በምልዐት ያለመገኘት ተፈጥሮ አምነው ሲያበቁ
በተግባር ግን ከዚህ አስተሳሰብ በተቃራኒ ቆመው የመገኘታቸው ነገር በመጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነታ ውስጥ ለመኖር ካለመቻል የመጣ እክል
ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
4/ በሰማይ ሥፍራ ያሉ ቅዱሳን በዓለመ ምልዓትይገኛሉን?
ፍጡራን ውሱንና በሁሉ ሥፍራ የመገኘት ብቃት
እንደሌላቸው ከላይ በተደጋጋሚ ለማሳየት በሞከርነው ላይ ካመንን በዓለማት ሁሉ በምልዓት ሊገኙ አይችሉም ብለን ደፍረን መናገር እንችላለን።
እንደመላእክቱ ሁሉ ቅዱሳን ሰዎች በተወሰነ ሥፍራ፤ በተወሰነ መጠንና በተፈቀደላቸው ዓለም የሚኖሩ እንጂ ምሉዕ በኵለኄ ስላይደሉ እንደፈጣሪ ሁሉን
አዋቂነት የላቸውም ብንልም ስህተት አይደለም። ከዚህ በተለየ አስተሳሰብ ላይ ከሆንን ደግሞ ሊሆን የሚችለው ነገር ሁሉን ቻይ በሆነው
በእግዚአብሔር ኃይልና ፍጡር በሆነው ፍጥረት መካከል ያለውን ልዩነት አለመረዳት ስለሚሆን እምነቱ በክህደት የተሞላ ይሆናል። በማወቅም
ይሁን ባለማወቅ የፈጣሪን ኃይል ለፍጡራን ከመስጠት የበለጠ ክህደት የለም። እግዚአብሔርን የሚመስል ምንም ነገር ሊኖር አይችልምና።
«አቤቱ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ በሰማይ ወይም
በምድር አንተን የሚመስል አምላክ የለም፤ በፍጹም ልባቸው በፊትህ ለሚሄዱ ባሪያዎችህ ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ» 2ኛ ዜና
6፤14
መላእክት ቅዱሳን በመሆናቸው ወይም ቅዱሳን ሰዎች
አምላካቸው ስላከበራቸው እግዚአብሔርን የሚመስል ባህርይ እንዳላቸው አድርጎ ማሰብ አስነዋሪ ነገር ነው። ቅዱሳን በዓለመ ሥጋ ሳሉ ወይም በዓለመ መላእክት የሚገኙ
መላእክት የሚሠሩት ሥራ በእግዚአብሔር ፈቃድና በተሰጣቸው ጸጋ ይወሰናል። በዚህ ምድር የሚኖሩ ቅዱሳን ሙት ቢያስነሱ፤ ደዌ ቢፈውሱ
ከተሰጣቸው ጸጋ አኳያ እንጂ በተፈጥሮ ካላቸው ብቃት የተነሳ አይደለም።
በዚያም ጸጋ ቢሆን የሚመሰገነውና ሊመሰገን የተገባው የጸጋው ባለቤት እግዚአብሔር ብቻ ነው። ቅዱሳኑን ማክበር አንድ
ነገር ነው፤ ነገር ግን በማክበር ሽፋን ወይም እግዚአብሔር በነሱ በኩል በሠራው አስደናቂ ነገር የተነሳ ለእነሱ ምሥጋናና ውዳሴ
እንድንሰጥ የሚያደርገን አንዳችም መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ የለም። ጸጋ ማለት እግዚአብሔር በወደደው መንገድ የራሱን ሥራ የሚሠራበት
ኃይል እንጂ ሠራተኞቹ ይመሰገኑበት ዘንድ የተሰጠ የውዳሴያቸው መሣሪያ አይደለም።
«አሁንም ጸጋን ይሰጠን ዘንድ እግዚአብሔርን
ለምኑ፤ ይህ ከእጃችሁ የተሰጠ ሲሆን ከቶ ፊታችሁን ይቀበላልን? ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር» ሚል 1፤9
ጸጋ የሚሰጥ፤ የሚከለከል ኃይል ነው። ጸጋ ሰጪው
በፈቀደው መጠን ለፈቀደው ጉዳይ የሚሰራበት መንገድ እንጂ ወሰን የሌለውና ሁሉን ለማድረግ ክበበ ተፈጥሮን አልፎ የሚሄድ ምሉዕ ኃይል
ያለው ማለት አይደለም።
«እንደ ተሰጠንም ጸጋ ልዩ ልዩ ስጦታ አለን»
ሮሜ 12፤6
«ሐዋርያትም የጌታን የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ
በታላቅ ኃይል ይመሰክሩ ነበር፤ በሁሉም ላይ ታላቅ ጸጋ ነበረባቸው» የሐዋ 4፤33
በአንድ ወቅት ሐዋርያው ጳውሎስ ልስጥራን በሚባል
ሀገር በገባ ጊዜ በልስጥራን የተባለ ከልጅነቱ ጀምሮ እግሩ ሽባ የሆነና የሰለለ ሰው አግኝቶ በኢየሱስ ስም ከፈወሰው በኋላ አማልክት ከሰማይ ወርደዋል ብለው ሲያበቁ ሕዝቡና የድያ ካህን ኮርማ ሊሰዋላቸው
ፈለገ። ጳውሎስና በርናባስ ግን ልብሳቸውን ቀደው እንዲህ አሉ።
«እንዲህም አሉ። እናንተ ሰዎች፥ ይህን ስለ
ምን ታደርጋላችሁ? እኛ ደግሞ እንደ እናንተ የምንሰማ ሰዎች ነን፥ ከዚህም ከንቱ ነገር ሰማይንና ምድርን ባሕርንም በእነርሱም ያለውን
ሁሉ ወደ ፈጠረ ወደ ሕያው እግዚአብሔር ዘወር ትሉ ዘንድ ወንጌልን እንሰብካለን» የሐዋ 14፤14-15
የቅዱሳን መላእክትም ይሁን የቅዱሳን ሰዎች ዋና
የእምነታቸው ማእከል ራሳቸውን በምሥጋናውና በተሠራው ቦታ ማስቀመጥ ሳይሆን እግዚአብሔር በእነሱ በኩል እንዲከብር ማድረግ ነው። ከጳውሎስ ተአምራት የተማርነው ነገር ተአምራቱን የሠራው ጳውሎስ ሳይሆን መክበር
ያለበት የተአምራቱ ባለቤት እግዚአብሔር ብቻ እንዲከብር ሰዎች ሁሉ ዓይናቸውን በእግዚአብሔር ላይ እንዲጥሉ በኃይለ ቃል ሲናገራቸው
የምናነበውም ለዚህ ነው።
5/ በሰማያት ሥፍራ ያሉ ቅዱሳኑ መላእክትና
ቅዱሳን ሰዎች የሰዎችን ልመናና ጸሎት ሰምተው ምላሽ ሊሰጡ ይችላሉን?
የቅዱሳኑን ውሱንነትና በምልዓት ያለመገኘት ብቃት
መመልከት ያስፈለገን ከዚህ በታች ለምናቀርባቸው ጭብጦች ገላጭ አስረጂ እንዲሆኑን ከመፈለግ የተነሳ ነው። ውሱንነትና በምልዓት አለመገኘት
ማለት ከታች ለሚነሱት ነጥቦች መልስ ይሰጡናል።
እዚህ ላይ ሁለት የተለያዩ ነጥቦችን ልናነሳ
እንገደዳለን። አንደኛው ቅዱሳን መላእክት በሰማያት ባለ የምሥጋና ዓለም እያሉ በምድር የሚደረገውን ነገር ሁሉ ያውቃሉ ወይ? የሚለውንና
በገነት ያሉ ቅዱሳን በምድር የሚደረገውን ሁሉ ማየት ወይም መስማት ይችላሉ ወይ? የሚለውን ነጥብ ለይቶ መመልከት ተገቢ ነው።
ከቅዱሳን መላእክትና ከቅዱሳን ሰዎች ተፈጥሮ የተነሳ በምልዐት ያለመገኘትን
ጉድለት የተነሳ በገነት ወይም በዓለመ መላእክት ያሉ ቅዱሳን በዚህ ክበበ ዓለም ያለውን ነገር ሁሉ በአንዴ ሰምተው፤ በአንዴ አውቀው፤
ምላሽ ሊሰጡ አይችሉም። በወሰነ ነፍሳዊ አካል በገነት ሳሉ በዚህ ምድርም የመገኘት ብቃት የሌላቸው ከመሆኑም ባሻገር በተፈጥሮአቸውም በገነት ሳሉ
በምድር ያሉ ሰዎችን ጸሎት በብቃት በመስማት ምላሽ ለመስጠት
ስላይደለ የሁሉን አዋቂነትና ሰሚነት ችሎታ የላቸውምና በምድር ላይ ሆነን በገነት ይሰሙናል ልንል የተገባ አይደለም።
ይህን የማድረግ ባህርይ የእግዚአብሔር የብቻው ነው።
በዚህች ባለንባት ምድር በየትኛውም ማእዘነ ዓለም
በስማቸው የሚደረገን ልመና በገነት ሳሉ ይሰማሉ ማለት ፈጣሪ ናቸው ብሎ በክህደት አዘቅት ውስጥ መውደቅ ማለት ነው።
ቅዱሳን መላእክትን እግዚአብሔር ለፈለገው ዓላማ
ሲልካቸው ወይም እንዲገኙ በተሰወነላቸው ሥፍራ ከመገኘት በስተቀር በፈቃዳቸው ወይም ሰዎች ስለጠሯቸው እንደፍላጎታቸው ሊሄዱ አይችሉም፤
ያልተወሰነ የመስማት ብቃትም የላቸውም። በኢጣሊቄ ይኖር ለነበረ ጭፍራ፤
የመቶ አለቃ የሆነው ቆርኔሌዎስ ጸሎቱና ምጽዋቱ በእግዚአብሔር ዘንድ ስለተወደደ ስሙ ያልተገለጸ የእግዚአብሔር መልአክ በተልእኰ
መጥቶ መልእክት ማድረሱንና ማድረግ ስለሚገባው ነገር ሲናገረው እናነባለን።
እዚህ ላይ ሊሠመርበት የሚገባቸው ነጥቦች ሦስት
ናቸው።
ሀ/ የመልአኩ ድርሻ ማንነቱን ማስተዋወቅ ወይም የራሱን ሃሳብ መግለጽ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ዘንድ
የተላለፈውን መልእክት ማስረዳት ብቻ ነው። ከነበረበት ሰማያዊ ሥፍራም በተልእኰ ወደቆርኔሌዎስ ሲሄድ የነበረበትን ዓለመ መላእክት
ለቆ ይወርዳል እንጂ በስፍሐት በነበረበት ቦታም በተመሳሳይ ሁኔታ ሊገኝ አይችልም። መውጣትና መውረድ ያስፈለገውም ለዚህ ነው።
ለ/ መልአኩ ከቆርኔሌዎስ ቤት የተገኘው መልአኩ
በስሙ ስለተደረገው ጸሎትና ምጽዋት ምላሽ ሊከፍለው መምጣቱን ለመንገር ሳይሆን ቆርኔሌዎስ በአምላኩ ስም ያደረገው ነገር በእግዚአብሔር
ዘንድ ተቀባይነት ማግኘቱን በመግለጽ የእግዚአብሔር መልእክት ለማድረስ
ብቻ ነው።
ሐ/ በዚህ ሥፍራ ስሙ ያልተገለጸውን የመልአክ
ስም በምትሃት ጠቅሰን በመናገር መልእክት አድራሽነቱን እንደባለቤት ቆጥረን እንድናመሰግነው የሚያደርገን አንዳች ነገር የለም።
ይሁን እንጂ በዘጸአተ እስራኤል ታሪክ ላይ ያልተገለጸው መልአክ፤ ሚካኤል እንደመራቸው
ተደርጎ የተጠራውና በትንቢተ ዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ እንደተመለከተውም፤ ሠለስቱ ደቂቅን ከእቶን እሳት ያዳናቸው፤ እግዚአብሔር ባወቀ ያልገለጸውን የመልአክ ስም በመስጠት ሚካኤልና ገብርኤል
ናቸው እያሉ የስህተት ትምህርቶች ምሥጋናውን ሁሉ ከእግዚአብሔር ላይ
ለመውሰድ የተደረገ ትግል ከመሆን አያልፍም። በእግዚአብሔር ሥፍራ ላልተገለጹ መላእክት ክብርና ምስጋናን በመስጠት እግዚአብሔርን
ማስቀናት የጠላት ሴራ ውጤት ነው። በእርግጥም ይህንን የሚያደርገው ሰይጣን ነው። ምክንያቱም በቅዱሳን መላእክት ስም ተሸሽጎ ሰዎችን ከእግዚአብሔር ፈቃድ ለማስወጣት
የብርሃን መልአክ ነኝ ቢል ማስመሰል የቆየ ተግባሩ ነው። በመጽሐፍ
ቅዱስ ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ሳይገልጽ በዝምታ ያለፈውን ነገር እንዳለ
ለሱ በመስጠት በዝምታ እንደመተው የመሰለ ማለፊያ እውቀት የለም።
እንደዚሁ ሁሉ ወደቆርኔሌዎስ የተላከውን መልአከ ማንነት እግዚአብሔር ብቻ ባወቀው
ሁኔታ ስላልተገለጸ ከዝምታ ባለፈ ወደስም ገላጭነት የሚያሸጋግረን ምክንያት የለም። «እንደአናንያ፤ እንደአዛርያ፤ እንደሚሳኤል፤
አድነን ገብርኤል» እንድንል የሚያደርገን ከመጽሐፉ ባለቤትም የተሻለ እውነት እኛ ዘንድ የለም።
ስለሆነም ቅዱሳን መላእክቱ ሰዎች ወደእግዚአብሔር
በሚያቀርቡት ልመናና ጸሎት ወይም እግዚአብሔር እንዲራዱ፤ እንዲታደጉ ሲልካቸው በትእዛዝ ብቻ ተልእኰአቸውን ለመፈጸም ከሚመጡ በስተቀር
ሰዎች ስማቸውን ስለጠሩ፤ በስማቸውም ስለተማጸኑ፤ ለዚያ የሚሆን ዋጋ ለመስጠት ደስ ተሰኝተው፤ ላደረጉትም ትድግና ምስጋና ለመቀበል
ሽተው በጭራሽ አይመጡም። ምክንያታችንም ከላይ ስንገልጽ እንደመጣነው መላእክቱም ይሁኑ ቅዱሳኑ በሰማይ ሳሉ በምድር ላይ በስማቸው
የተደረገውን የሰዎችን ሁሉ ልመና መስማት፤ መቀበልና ምላሽ የመስጠት ብቃት ስለሌላቸው ነው። በምልዓት ተገኝቶ የመስማትና ጸሎት
የመቀበል ችሎታ የእግዚአብሔር ብቻ ስለሆነ!!
ክፍል ሁለት ይቀጥላል ….