Wednesday, November 12, 2014

ግብረ ሰዶማዊነትና የእኛ ዘመን አገልጋዮች

( ከአቤኔዘር ተክሉ )

    ስለግብረ ሰዶማዊነት በሁለት የተለያዩ ክፍሎች መጻፌና በሁለቱ ክፍሎችም ለጊዜው የነበረኝን ሃሳብ ማጠቃለሌን አልዘነጋውም፡፡ ነገር ግን አሁንም ግብረ ሰዶማዊነት የቤተ ክርስቲያንን ቅድስና ከማርከስ፤ ምድራችንን ለከፋ ጉስቁልናና ርኩሰት አሳልፎ ከመስጠት ያላቆመ ፍጹም ወደመስፋፋት የሄደ ክፉ ርኩሰት ነውና ዳግም ይህንን ርዕስ ማንሳት አስፈልጎኛል፡፡ ለዚህ እውነታ ብዙ የቅርብ ጊዜ ማሳያ ብቻ ማንሳቱ በቂ ይመስለኛል፡፡

    ድርጊቱ የተፈጸመው በምስራቁ የሃገራችን ክፍል ነው፡፡ የሠላሳ ሁለት አመት አጐት የአራት አመት የወንድም ልጁን በእረኝነት ሥፍራ በመሄድ ጫት እንዲቅም ያግባባዋል፡፡ ህጻኑ እንቢ ቢልም ያስገድደዋል፡፡ ጫት እንዲቅም ካስገደደው በኋላ ልጁ ራሱን መቆጣጠር ሲያቅተው ልጁን የግብረ ሰዶም ጥቃት ይፈጽምበታል፡፡ የልጁ የሰገራ ማውጫ ሙሉ ለሙሉ ይቀዳዳል፡፡ ከሆዱ የወጣው የውስጠኛው የሰገራው ክፍል ሙሉ ለሙሉ የልጁን ጠረን ይለውጠዋል፡፡ ልጁ ፍጹም ራሱን ስቶ ሲወድቅ ከወደቀበት ቦታ ተሸክሞት ከወላጆቹ ጓሮ አምጥቶ ጥሎት ይሰወራል፡፡ ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የልጁ ህይወት ያልፋል፡፡

    ሌላም ብንጨምር፦ አንድ “ስመ ገናና” አገልጋይ እንዲህ ያለ ነውር እንደሚፈጽም በምስክር ይረጋገጥና ብዙዎች ተረባርበው ሊመክሩት ይፈልጋሉ፡፡ ነገር ግን ከማስመሰልና የሽንገላ እሺታ ከማሳየት በቀር ከነገሩ ሳይታቀብ ይቀራል፡፡ በኋላ ይባስ ብሎ በአቋም፤ የሠራው ትክክል እንደሆነና ይቅርታ መጠየቅ እንደማያስፈልግ ከብዙ ደጋፊዎቹ ጋር በግልጥ በአቋሙ ይጸናል፡፡ ወንድሞቹን ይቅርታ ሳይጠይቅ በግልጥ ለሠራውና ሌሎችን ላሰናከለበት ኃጢአቱ ንስሐ ሳይገባ እንደዋዛ ዛሬም አለ፡፡ በድርጊቱ የተጠቁት ወንድሞች ግን “እንዲህ ያለ ነገር እያደረገ በአንድ የኃይማኖት ጥላ ሥር አንቀመጥም” በማለት ወደሌላ የእምነት ተቋም ራሳቸውን አገለሉ፡፡ (ርቀው ወደሌላ የኃይማኖት ተቋም እንዳይሄዱ ብዙ ርብርብ ቢደረግም አልተሳካም፡፡)

    በመንግስትም ደረጃ በዘንድሮው የይቅርታ መመሪያ ውስጥ ይቅርታ ከሚያሰጡ ወንጀሎች መካከል ግብረ ሰዶማዊነትም እንዲካተት ጥረቶች “መደረጋቸውና መሳካቱንም” ጭምጭምታዎች ይሰማሉ፡፡ ጉዟችን ወዴት ይሆን? እንዲህስ እስከምን ድረስ ነው የምንጓዘው?

      ግብረ ሰዶማዊነት እግዚአብሔር የፈጠረውን ፍጥረት ሙሉ ለሙሉ በመቃረን የሚፈጸም ርኩሰት ነው፡፡ ቃሉም “ስለዚህ እርስ በርሳቸው ሥጋቸውን ሊያዋርዱ እግዚአብሔር በልባቸው ፍትወት ወደ ርኵስነት አሳልፎ ሰጣቸው”(ሮሜ.1፥24) እንዲል ቅዱሱን የእግዚአብሔር ፍጥረት በመቃረናችን ምክንያት የገዛ ኃጢአታችን “ለሚያስነውር ምኞት አሳልፎ እንደሰጠን” ትልቅ ምስክር ነው፡፡(ሮሜ.1፥26)

   ጥቂት የማይባሉ አገልጋዮች “ለአገልግሎት” ወደክፍለ አገር ወይም ወደውጪ አገር ሲወጡና ጨርሰው ሲመለሱ ጥንድ ጥንድ እየሆኑ ሹልክ ብለው ለሴሰኝነትና ለዝሙት እንደሚገባበዙ ፀሐይ የሞቀው እውነት ሆኗል፡፡   በአቶ አስማማው ኃይሉ በተጻፈውና “ኢህአሠ” በተባለው ቅጽ አንድ መጽሐፍ ላይ ከትግል መልስ ደራሲው አንድ ታጋይ ነገረኝ ብሎ ሲጽፍ ፤ ታጋዩ ማደሪያ አገኘሁ ብሎ ወደ አንድ ቤተ ክርስቲያን ሊጠለል ጎራ ባለበት ወቅት ሌሊቱን ሙሉ  የገጠመው ሌላ ትግል ይኸው ከግብረ ሰዶማውያን ጋር ያደረገው ያለመደፈር ትግል እንደነበር በግልጥ አስቀምጦታል፡፡ በእርግጥ ዛሬ በገዳም ካሉት ጥቂት የማይባሉ መነኰሳትና መነኰሳይያት፤ እንዲሁም  በወንዶችም ሆነ በሴቶችም ዘማሪዎቻችን መንደርም የምንሰማው ነገር ጆሮን ጭው የሚያደርግ ነው፡፡ (እንደአገር ስናስብ ደግሞ በካርዲናሎቹና በፓስተሮቹም መካከል አጸያፊ የርኩሰት ነገር ጆሯችን ከመስማት አልታከተም!!)   

     ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ያሉ ኃጢአተኞችን በግልጥ ከመቃወም እየደከመች የመጣች ይመስላል፡፡ ምክንያቱም የግብረ ሰዶማውያን “አገልጋዮችን” የጨለማ ሥራን ከመግለጥ (ኤፌ.5፥11)፤ ሌሎች ሰዎችም ከክፋታቸው እንዳይተባበሩ ከማስጠንቀቅና መክራ እንዲመለሱ ከማድረግ ድምጿን አሰልላለች፡፡ ስለዚህም ሌሎች ብዙዎች ግብረ ሰዶማውያኑን  “በርቱ፤ እኛም ከጎናችሁ ነን” ከማለት አልፈው ለግብረ ሰዶማውያኑ ድጋፍ ሲሰጡና ሲሟገቱላቸው በአይናችን እያየን ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ኩልልና ጥርት ያለ የተቃውሞ ድምጿን ልታሰማ ግድ የሚላት ጊዜ አሁንና አሁን ነው፡፡ ከረፈደ በኋላ መሯሯጥ ድካም እንጂ ሚዛን የሚደፋ ትውልድ የማዳን ሥራ አይሠራም፡፡

    የሰዶም ሰዎች ያደርጉት የነበረው የክፋት ድርጊታቸውን እንደመልካም ከመቁጠር አልፈው እነርሱ የሚያደርጉትን ነውር የማያደርጉትን ሰዎች ይቃወሙ፤ የእነርሱን ነውር እንዲቀበሉ ያደርጉም ነበር፡፡ በአገሪቱ ካሉት ሰዎች ሁሉ ጋር ነውራቸውን ከፈጸሙ በኋላ  እንግዳ ሰዎች በመካከላቸው በተገኙ ጊዜ ከእንግዶቹ ጋር ሊፈጽሙ (በሎጥ ቤት የመጡትን መላዕክት ሲያዩ ወደአዲስ መጎምጀት መጥተዋልና!) የኃይልን መንገድ እንደተጠቀሙ፤ ጻድቁንም ሎጥ እንደተጋፉትና በሩን ሊሰብሩ እንደተገዳደሩ ታላቁ መጽሐፍ ይነግረናል፡፡(ዘፍ.19፥5-9) ሰው ለእግዚአብሔር ባህርይና ለተፈጥሮ እውነት መገዛት ሲሳነው የኃጢአት መሻቱ ድንበር አልባ ይሆናል፡፡ ሁሉንም ርኩሰት ከመፈጸም የሚያግደውም የለም፡፡

   ዛሬ ላይ ድሆች ሃገራትን ለመርዳት የሚዘረጉ ብዙ የእርዳታ እጆች ስውር አጀንዳቸው ግብረ ሰዶምና ሰዶማዊነት ለመሆኑ ብዙ ማስተንተኛ ማቅረብ አያስፈልግም፡፡ ግብረ ሰዶምን በግልጥ የተቃወመች ብቸኛይቱ አፍሪካዊት ሃገር ይህንን በግልጥ አይታዋለችና፡፡ እኛ “ከቃል ባልዘለለ” ክርስትናችን በከንቱ ስንመካ ከአገራችን ቀድማ ግብረ ሰዶማዊነትን በግልጥ አለም አቀፍ በሆነ ዕይታ ህግን አስደግፋ ተቃውሞ ያሰማችው አፍሪካዊት አገር ኡጋንዳ ናት፡፡ በእርግጥ የእኛ ወንጀል ህግ “ግብረ ሰዶማዊነት ወንጀል ነው” ይላል፤ ግን የአገሪቱን ትልልቅ ከተሞች ጎዳና እያጥለቀለቁ ያሉትና ቁጥራቸው የማይናቅ አገልጋዮችን እንደወረርሽኝ በሽታ እየወረሱት ያሉት “ሴት እንተኛ አዳሪዎች” ብቻ ሳይሆኑ ግብረ ሰዶማውያኑም ጭምር ናቸው፡፡ ህጉ ቢኖርም ለነዚህ ምድርን ለሚያረክሱ “ወገኖች” ግን ጥርስ የሌለው አንበሳ ሆኖ ተቀምጧል፡፡

   የኡጋንዳ መሪዎች ያንን የመሰለ ቁርጥ ያለ አቋማቸውን በግብረ ሰዶማዊነት ላይ ሲያሰሙ፤ ሰለጠን ያሉቱ ምዕራባውያን የኡጋንዳን ድርጊት “የሰይጣን ድርጊት” አድርገው ለማቅረብ ጊዜ አልወሰደባቸውም፡፡ (እግዚአብሔርስ ይቅር ሰይጣን እንኳ እንዴት ታዝቦን ይሆን?!)  የእኛ አገልጋዮች ግን ዛሬም ግብረ ሰዶማዊነትን በመካከላችን ያሽሞነሙኑታል፡፡ ከዓመታት በፊት ግብረ ሰዶማውያኑም አለም አቀፍ ስብሰባ አፍንጫችን ስር ባለችው አዲስ አበባ አድርገው አባላታቸውን መልምለው ሲሄዱ እንኳ ዝም ጭጭ ሆኗል ክርስትናችን፡፡ እንኪያስ ወርቁ ለምን ይሆን የደበሰው?
   ግብረ ሰዶማውያንን ለመቃወም የአገልጋዮች “ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ” ማለት ከበለጠብን እንኪያ እኛስ ከእነርሱ በምን እንሻላለን? መንፈሳዊነት መለኪያው የአገልግሎት ስኬት ሳይሆን የህይወት ጥራት ነው፡፡ ጌታ ጥራት ከሌለው ሸንጋይ መንጋ ጋር ህብረት እንደሌለውና ጥራት ካለው ጥቂት አማኝ ጋር ብቻ ህብረት እንዳለው በጌዴዎንና በሐዋርያት ህይወት አይተናል፡፡ ምክራችን፣ ጩኸታችን፣ ተግሳጻችን፣  ቁጣችን … “ምክር ለምኔ” ያሉ ግብረ ሰዶማውያን አገልጋዮች በንስሐ ተመልሰው የበደሏቸውንና ያሰናከሏቸውን ወንድሞች ይቅርታ በመጠየቅ እንዲመለሱ ነው እንጂ በመካከላችን ተቀምጠው ሌሎችን ለማጥቃት እንዲያደቡ አይደለም፡፡

    የእግዚአብሔርን ምህረት የሚያሸንፍ ወይም የሚበልጥ ኃጢአት የለም፡፡  እንዲህ የምንለው ግን በንስሐ ለሚመለሱ እንጂ ልብን ለሚያደነድኑ አመጸኞች አይደለም፡፡ ጌታ ለምድሪቱ ምህረትና የንስሐን ልብ ያውርድላት፡፡ አሜን፡፡

Wednesday, November 5, 2014

ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተ ክርስቲያን መድኅን? ዋስትና? ጠባቂ? ወይስ ምንድነው?



1/ ማኅበረ ቅዱሳን ማነው? 

ከማኅበረ ቅዱሳን መሥራቾች አንዱ እንደሆነ የሚናገረው የሜሪላንዱ ኤፍሬም እሼቴ  ስለማቅ ጥንስስ እንደተረከው ብላቴ ጦር ካምፕ ውስጥ ተቀፍቅፈን፤ ዝዋይ ላይ በመፈልፈልና አዲስ አበባ ላይ ኅልውና አግኝተን ሕይወት ዘራን ሲል ይተርክልናል። የኅልውናቸውም መስራቾችና ፈልፋዮች ማንነት ኤፍሬም ዘለግ አድርጎ ሲናገር በኅብረተሰባዊት ኢትዮጵያ በመንደር ምሥረታ ታሪክ ውስጥ ብዙ ድርሻ የነበራቸው ሰዎች ባሉበት ሁኔታ የዳቦ ስም ወጥቶላቸው «ማኅበረ ቅዱሳን» እንደተባሉ «አደባባይ» በተሰኘው መካነ ጦማሩ እንዲህ እያለ ያወጋናል።
«ተማሪው በጋምቤላ፣ በመተከል፣ በወለጋ … ጎጆ ቤት ሲሠራ፣ ተፈናቃዩን ሲያቋቁም ቆይቶ ተመለሰ። በደህና ወጥቶ ለመመለስ ያልቀናውም ነበር። እነዚያ መንደር ሊመሠርቱ የወጡት ታላላቅ ወንድሞቻችን በየዛፉ ሥር፣ በየመንገዳቸው ጸሎተ ማርያም ማድረሳቸውን፣ ሲችሉም ተገናኝተው ቃለ እግዚአብሔር መስማታቸውን እንዳላስታጎሉ ሲናገሩ ሰምቻለሁ። እኛን ቃለ እግዚአብሔር ያስተማሩን የዚያ “መንደር መሥራች ትውልድአካላት የሆኑ ወንድሞች ናቸው። ወደ ዝዋይም የላኩን እነርሱ ናቸው። እኛ እና እነርሱ በአንድ ላይ ስንሆን ጊዜ በጋራ “ማ/ቅዱሳን” ተባልን።»
በእርግጥ የዚያን ዘመን መንደር መሥራች ትላልቅ ወንድሞች የተባሉት ማኅበሩን የመሠረቱበት ዓላማ ግልጽ ባይሆንም ኤፍሬምን ጨምሮ አብዛኛው የማኅበሩ አባላትን ግን ያሰባሰባቸው እምነታቸው ስለመሆኑ ከጥርጣሬ የሚወድቅ አይደለም። ያሳደጋቸውም የቤተ ክርስቲያን ቅናት ብቻ ነበር። ሲመሰረትም የወንድሞች ማኅበር «ማኅበረ ቅዱሳን» ከዚያ ከትንሹ ጅምር ተነስቶ ይህንን ያህል በመግዘፍ ሀገራዊ ማኅበርና የሲኖዶስ ጉባዔ የየዓመቱ የመነጋገሪያ አጀንዳ ይሆናል ብሎ የገመተ አይኖርም ይሆናል። ምናልባት ትላልቅ ወንድሞች የተባሉት እግር በእግር እየተከታተሉና እየኮተኮቱ ያሳደጉበትን  ኅቡእ አጀንዳ ራሳቸው ያውቁ እንደሆን እንጂ ዛሬም ድረስ ከጥቂቶች በስተቀር አብዛኛው የማኅበሩ አባላት እያገለገሉ ያሉት ቤተ ክርስቲያናቸውን እንደሆነ መገመት ይቻላል።
 ነገር ግን ግዝፈቱ እውን እየሆነ ሲሄድ ወደ ረጅም ህልምና ራእይ የመድረስ ስንቅ ሳይቋጥር አልቀረም። ኅልውናውን የሚያስጠብቅበትን የሕግ ማዕቀፍ መጎናጸፍ፤ የድርጅት ኃይል ማሳደግ፤ የገንዘብ አቅም ማጎልበት፤ የዓላማና ግብ ስትራቴጂ መቅረጽ ወዘተ ራሱን የሚያስጠብቅበት ቅርጽና መዋቅር እየያዘ እንደመጣ እርምጃዎቹ ዋቢዎቻችን ናቸው። ዓላማና ግብ ሳይኖረው ኅልውናውን ማስጠበቅ እንደማያስፈልገው ይታወቃል።  እዚህ ይደረሳል ብለው ያልገመቱ ቢገኙም ሂደት ራሱ በሚፈጥረው ስኬት ከተነሳበት ሃሳብ ወጣ ባለ መልኩ ወደሚፈልጉበት አዲስ ግብ ለመድረስ  ስትራቴጂ ቢኖራቸው አያስገርምም።  ትንሹ ትንሣዔው ስኬትን ሲያጎናጽፈው መድረስ የሚፈልገው ዓላማ ሊኖረው የግድ ስለሆነ ለዚህ ደግሞ ሁሉን መስዋዕትነት እንደሚከፍል አይጠረጠርም።
ማኅበረ ቅዱሳን በጥቂቶች አስተሳሰብ በእቅድ የተመሠረተ፤ በተራው አባል ግን በአጋጣሚ እግዚአብሔር ፈቅዶ የተቋቋመ ያህል የሚታሰብ ድርጅት ነው። መቋቋሙ በቀና ዓይን ቢታይ ባያስከፋም በተግባር ግን እየታየ የቆየው የተገላቢጦሽ መሆኑ እርግጥ ነው።

2/ ማኅበረ ቅዱሳን ለማኅበረ ካህናቱ ምንድነው?

ዛሬ ላይ ማኅበሩ ያለው ስትራቴጂ  የተነሳበት ነበር ወይ? ብለን ብንጠይቅ መልሳችን አይደለም ነው።  ከላይ እንደተመለከትነው ማኅበሩ ሲነሳ አብሮ ለመዘመርና ለማማር የተሰባሰበ እንጂ የዚህን ያህል ስፋት ያለው ርቀት እሄዳለሁ ብሎ አልነበረም። ይህ ሲባል ግን የሚሄድበትን ርቀት እየለኩ የሚመሩት ሰዎች አልነበሩትም ማለት አይደለም። በዚህም የተነሳ ጉዞውን ለማሳካት የሚሄድበት ርቀት ከተነሳበት ዓላማ ጋር በእጅጉ የሚጣረስ ሆኖ ይታያል።  ተወዳጅነት ያገኘውን ያህል የተቀባይነት ማጣት ግጭትና ዓላማን ለማሳካት የሚደረገው ስልት ከፊት ለፊት ተቃውሞ መፍጠሩ አልቀረም። ለዚህም ነው ማኅበሩን ባልተቀበለው የቤተ ክህነቱ አባላት ዘንድ እርቅ ወደሌለው ቅራኔ እየከተተው የሚገኘው። ማኅበሩ አብዛኛውን በሚል ደረጃ በአባልነት የያዛቸው የየአጥቢያውን ሰንበት ተማሪዎች፤ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እንዲሁም በራሳቸው ተነሳሽነት ተሰባስበው በዓመታዊው የጥምቀት በዓል ላይ ታቦታት ሲወጡና ሲገቡ ቄጠማ በመጎዝጎዝ ይሳተፉ የነበሩትን ወጣቶች ማኅበሩ መልክና ቅርጽ በመስጠት ወደራሱ ዓላማ በመሳብ «የጥምቀት ተመላሾች ማኅበር» በሚል ያደራጃቸው ናቸው። ማኅበሩ የፖለቲካ ድርጅት የሆነ ያህል አሁን በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት በሚጠሉ ፖለቲከኞች ሁሉ እንደ አንድ አስፈላጊ አካል መቆጠሩ ሳይዘነጋ መሆኑንም ያስተውሏል። የዚህ አብሮነት ያገናኛቸው የእምነት ስምምነት ውል መኖሩ ሳይሆን ፖለቲካዊ ስልት መሆኑን ለማወቅ ብዙም ምርምር አይጠይቅም።
 ከዚያ በተረፈ ማኅበረ ቅዱሳንን ከጥቂት የጥቅም ተጋሪዎችና በፍርሃት ቆፈን ከተያዙት በስተቀር አብዛኛው የቤተ ክህነቱ ሰው ግን «ዓይንህን ላፈር» እንዳለው ይገኛል። የማኅበረ ቅዱሳን ኅልውና እንደሪፈረንደም በቤተ ክህነቱ አባላት ድምጽ የሚወሰን ቢሆን ኖሮ አንድም ቀን ኅልው ሆኖ ሊኖር እንደማይችል በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።  ምንም እንኳን ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክህነቱን ኃይል ማሳኝና አማሳኝ እያለ በደፈናው ንቆ ቢጨፈልቅም ማኅበሩ እንደሚገምተው በቀላሉ እጁን የሚጠመዘዝ ኃይል አይደለም። የቤተ ክህነቱ ሰው  በክህነት አገልግሎት ላይ ስለሚገኝ  ሕዝበ ክርስቲያኑ ሁሉ ያለው በመንፈሳዊው የክህነት አገልግሎት ስር ነው።  ስለሆነም የማኅበረ ካህናቱን ኃይል ከህዝበ ክርስቲያኑ መነጠል አይቻልም። ስለዚህ የዚህ ኃይል ማኅበረ ቅዱሳንን መቃወም መቻሉ የማኅበሩን የወደፊት ኅልውና የመወሰን አቅም አለው። ማኅበሩ ደግሞ ከዚህ ከክህነት አገልግሎቱ ኃይል ጋር ዓይንና ናጫ ሆኗል። በማኅበሩ የሚደረገው የስለላ፤ የመረጃ፤ የስም ማጥፋት፤ የአድማ፤ ከስራ የማስባረር፤ ዋስትና የማሳጣት፤ መተማመንን የማዳከም ተግባራቱ በክህነት አገልጋዩ ዘንድ በሰፊው ስለታወቀ መቼም ቢሆን መተማመን እንዳይኖር አድርጎታል።

 በማኅበረ ቅዱሳንና በማኅበረ ካህናቱ መካከል ያለው የዓላማ ቅራኔ የሚፈጥረው ሽኩቻ ቤተ ክርስቲያኒቱን ከማዳከም በዘለለ አንዳችም ትርፍ አላስገኘም። ማኅበረ ቅዱሳን ዓላማው አጠቃላይ ማኅበረ ካህናቱን በራሱ ፖሊሲና ስትራቴጂ ማጥመቅ ሲሆን ማኅበረ ካህናቱ ደግሞ ይህ ማኅበር ከቤተ ክርስቲያን ተወግዶ ማየት በመሆኑ ልዩነቱን የማይታረቅ አድርጎታል።
ማኅበረ ቅዱሳን በካህናቱ በኩል የሚታየው እንደፍልስጣ ኃጢአትን መዝግቦ እንደሚከስ ባላንጣ እንጂ እንደቅዱሳን ስብስብ አይደለም። ማኅበረ ቅዱሳን ለማኅበረ ካህናቱ የፈየደው አንዳችም ነገር አለ ተብሎ አይታሰብም። ምክንያቱም ማኅበሩ በክህነት አገልግሎት አያግዝም። በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ከማኅበረ ካህናቱ የተሻለ ዕውቀት የለውም። ከሕዝበ ክርስቲያኑ ጋር ከካህናቱ በተሻለ ሁኔታ በዕለት ዕለት ቅርርብ አይመሰከርለትም። ስለዚህ ማኅበረ ቅዱሳን ማለት ለካህናቱ ምንም ማለት ነው።

ይህ ባለበት ሁኔታ ሳለ መልካም ግንኙነት መመሥረት የሚችልበትን ዕድል በማበላሸት የካህናቱን ሥነ ምግባር በማጉደፍ፤ አደባባይ ላይ በማዋልና ስም በማጥፋት ላይ በመሰማራቱ ከካህናቱ ጋር ለመተሳሰር ምንም ድርሻ የሌለው ማኅበር ሆኖ ቀርቷል።  ሁሉም ሰው «ነግ በኔ» በሚል ፍርሃት በአንድነት በተቃርኖ የቆመበት ማኅበር ነው። ይህ  የቅራኔ ግንኙነት መቼ ይሻሻላል? ቢባል መቼም የሚታረቅ አይደለም እንላለን። የማኅበሩ ዓላማና ግብ በራሱ ጳጳሳት የሚመራ ሲኖዶስ አቋቁሞ፤ በራሱ ጳጳሳት የሚሾሙ ማኅበረ ካህናትን መስርቶ አሁን ያለውንና የማይቀበለውን የማኅበረ ካህናት አስወግዶ የራሱን መዋቅር መዘርጋት በመሆኑ አሁን ካለውና ከሚቃወመው ጋር መቼም ቢሆን እርቅ ይኖረዋል ተብሎ አይጠበቅም።ስለሆነም ማኅበሩ ከአጠቃላይ ማኅበረ ካህናት ጋር ሰላም ሊመሰርት አይችልም ብሎ መደምደም ይቻላል። ማኅበሩም ራሱ ዓላማውን ለማሳካት የሚሄድበት መንገድ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ካህናት ጋር ለመስማማት የሚያስችል ተፈጥሮ ላይ የተመሠረተ አይደለም። 

3/ ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተ ክርስቲያኒቱ ምዕመናን ያበረከተው ምንድነው?

ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ማኅበረ ቅዱሳን በቤተ መቅደሱ የክህነት አገልግሎት ላይ የተሰማራ ባለመሆኑ ለምዕመናኑ ከካህናቱ በተሻለ የሚሰጠው አገልግሎት ይኖራል ተብሎ አይታሰብም።
 በየአድባራቱ ወይም በየገዳማቱ ከምዕመናን አባላቱና ከሰንበት ትምህርት ቤቶች ወጣቶች ጋር ያለውን ቅርርብ በመጠቀም ዓላማና ግቡን ለማስረጽ በሚያደርገው ትግል ውስጥ ከካህናቱ በኩል ያለውን  ተቃውሞ ለመከላከል ሲል ለቤተ ክርስቲያን የሚቆረቆር በመምሰል ስም በማጥፋት፤ በአድማና በህውከት ከቦታቸው እንዲነሱ፤ እንዲጠሉ በማስደረግ ወይም ዝም ጭጭ ብለው፤ አንገታቸውን ደፍተው እንዲኖሩ በሚያደርገው ተግባሩ ያተረፈው ነገር ቢኖር የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት ወደሌሎች ቤተ እምነቶች መኮብለል ብቻ ነው። በሐረር፤ በድሬዳዋ፤ በደቡብ፤ በምዕራብና በምሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት እንደጎርፍ ቤተ ክርስቲያኒቱን ትተው የኮበሉለት ማኅበረ ቅዱሳን በየቦታው በፈጠው ሁከትና ብጥብጥ የተነሳ ነው።

   በእርግጥ አንዳንዶች ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት ባሉበት መርጋት ትልቅ ሚና ተጫውቷል ቢሉም ተረትና እንቆቅልሽ ለማስተማር ካልሆነ በስተቀር ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን የመተካት አንዳችም አቅም የሌለው ድርጅት ነው።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከ1960 ዓ/ም በፊት ከ1% በታች የነበሩት የፕሮቴስታንት ቤተ እምነቶች እስከ 1984 ዓ/ም ድረስ 5.5% ሲደርሱ እስከ 1994 ዓ/ም ድረስ በዐሥር ዓመት ውስጥ ብቻ 10.2% ለመድረስ በቅተዋል። አሁን ባለው ስታስትስቲክ የፕሮቴስታንቱ ቁጥር ከሀገሪቱ ሕዝብ ውስጥ 18.6% ፐርሰንት መድረሱን ያሳያል። በተቃራኒው ደግሞ ከሀገሪቱ ሕዝብ 60% ገደማ የኦርቶዶክስ ቤተ እምነት ተከታይ የነበረው ቁጥር በአስደንጋጭ መጠን ወደ 43.5% ያሽቆለቆለው ባለፉት ዐሥርተ አመታት ውስጥ መሆኑ የሚያሳየን ነገር የማኅበረ ቅዱሳንን የስብከትና እንቅስቃሴ ምዕመናኑን ከመበተን ይልቅ በቤታቸው የማቆየት አቅም እንዳልነበረው አረጋጋጭ ነው። 
ወደፕሮቴስታንቱ ጎራ ከኮበለለው 17% ገደማ የሚሆነው ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የወጣ መሆኑ እርግጥ ነው። ማቅ እንኳን ከሌላ ቤተ እምነት ሰብኮና አሳምኖ ሊያመጣ ይቅርና ያሉት ተረጋግተው እንዳይኖሩ ሲሰራ የቆየ መሆኑ አይታበልም። የማኅበረ ቅዱሳን የተረትና እንቆቅልሽ አስተምህሮ ማንንም ሰብኮ መመለስ እንደማይችል ይታወቃል።

  የሁሉም ነገሮች ችግር መነሻው ማኅበረ ቅዱሳን ነው ባይባልም ምዕመናን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ሲሳሳቱ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት በኩል አስተምሮና ናዝዞ ከመመለስ ይልቅ ተሐድሶ፤ጴንጤ፤ መናፍቅ፤ ሌባ፤ ዘማ፤ ነፍሰ ገዳይ እያለ በመፈረጅ በፍርሃት እንዲኮበልሉና እንዲሰደዱ በማድረግ በኩል የማኅበረ ቅዱሳን ድርሻ ወደር የለውም። ማኅበረ ቅዱሳን ኖሮ ቤተ ክርስቲያን ከተጠቀመችው ይልቅ ማኅበሩ በየቦታው በሚፈጥረው ሁከትና ግርግር የተጎዳችበት ይልቃል።

4/ ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተ ክርስቲያኒቱ ያበረከተው አገልግሎት እውነት እንደሚወራው ነው?

ሲጀመር ጀምሮ ማኅበረ ቅዱሳን የካዝና ቋቱንና ኪሱን ለቤተ ክርስቲያኒቱ አያሳይም። በሞዴላ ሞዴል ተጠቀም! ሂሳብህን አስመርምር! በምትሰራው ነገር ሁሉ የቤተ ክርስቲያኒቱን ፈቃድ ጠይቅ! መባሉ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥር የመሆኑ ማረጋገጫ  ካልሆነ በስተቀር ሀብትና ንብረቱን ስለመውረስ የሚያውጅ ድርጊት አልነበረም።  ከአባ ሠረቀ ብርሃን ጋር ያጋጫቸው ይኸው ዘራፍ ባይነቱ እንጂ አባ ሠረቀ ብርሃን ማኅበሩን የማፍረስ ዓላማ ስላላቸው አይደለም። ማኅበሩ የትኛውንም የቤተ ክርስቲያኒቱን ቁጥጥር መቀበል አይፈልግም። ለምን?

   ማኅበሩ ፈቃደኛ አለመሆኑ የሚያመለክተው ቢኖር አንድም ራሱ ብቻ አዋቂ ስለሆነ የቤተ ክርስቲያኒቱን አሠራር ይንቃል፤ አለያም ምን እየሰራ እንዳለ እንዲታወቅበት አይፈልግም። ስለዚህ ማኅበረ ቅዱሳንለቤተ ክርስቲያን  አበረከትኩት የሚለው አገልግሎት የስም፤ የዝናና ራስን ለማሳበጥ የሚጠቅምበት ስልታዊ እንቅስቃሴ ከመሆን የዘለለ አልነበረም ማለት ነው። 
ለምሳሌ ጣሊያን ኢትዮጵያን ከወረረች በኋላ በመንገድ ሥራ፤ በውሃ ቧንቧ ግንባታ፤ በመብራት ዝርጋታ ላይ ተሰማርታ ነበር። ኢጣሊያ ያንን ማድረጓ ወረራዋን ፍትሃዊ ሊያሰኘው እንደማይችለው ሁሉ ማኅበረ ቅዱሳን ፈጸምኳቸው የሚላቸው አንዳንድ እንቅስቃሴዎች  የማኅበሩን ኢፍትሃዊ እርምጃዎችን ፍትሃዊ ሊያሰኙት በጭራሽ አይችሉም። ስለዚህ ማኅበረ ቅዱሳን ተመስርቶ ከተከናወኑት ሥራዎች ይልቅ ቤተ ክርስቲያኒቱ በማኅበሩ የደረሰባት ወከባና ሁከት ዐሥር እጅ ይልቃል። ደግሞስ በ22 ዓመት ዓመት እድሜው «ጧፍና ሻማ ረዳሁ» ከሚል በስተቀር የጧፍና ሻማ ማምረቻ ሲገነባ አልቆየም። ይልቁንም ቤተ ክርስቲያኒቱን መስሎና አክሎ የሚንቀሳቀስበትን የግሉን ሕንጻና ሀብት ሲገናባ ኖሯል።  ሠራሁ የሚለውም ቢሆን በአካፋ ከዛቀው በማንኪያ እያካፈለ ላለመሆኑ ቤተ ክርስቲያኒቱ ባደረገችው ምርመራ አልመሰከረችለትም።  ያለውን የካዝና አቅም ከቤተ ክህነቱ መሸሸጉ የሚያስረዳን ነገር ቢኖር በአካፋ የዛቀውን በማንኪያ መስጠቱን እንጂ ሐቀኛነቱን አይደለም። አመራሮቹ እስከ 500 ሺህ ብር እየተበደሩ ሳይከፍሉ የውሃ ሽታ የሆነውን የገንዘብ ወጪ መረጃ በምን ሂሳብ ሊያወራርዱት? ተብሎ ለሚቀርበው መጠይቅ ሕጋዊ መልስ የለውም።  ስለዚህ ማኅበሩ ቤተ ክርስቲያኒቱ ጋሻዬ፤ መከታዬ ልትለው የምትችልበት ምንም ምክንያት የላትም።

5/ ለማኅበረ ቅዱሳን አሠራር ሁሉ ዋና ተጠያቂዎች ደጋፊ ጳጳሳቱ ናቸው!

ጳጳስ አይጠየቅም የሚል ልምድ አለ። መታወቅ ያለበት ነገር ጳጳስ ሰው መሆኑን ነው። እንደማንኛውም ሰው መሰናክል የሚገጥመውና ሰውኛ ድክመት ሊታይበት የሚችል ፍጡር መሆኑን መረዳት አለብን። እንዲያውም ቤተ ክርስቲያኒቱ በቀየረችው የጵጵስና ትርጉም የተነሳ የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳደር እየተበላሸ ሄደ እንጂ ጳጳስ መሆን የሚችለው በቤተሰብእ አስተዳደር ልምድ ያለውና የአንዲት ሴት ባል የሆነ ሰው መሆኑን ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈው መልዕክቱ በግልጽ ተቀምጧል። ጳውሎስ «ቤተ ሰብኡን በመልካም በማስተዳደር ያልተመሠከረለት፤ ቤተ ክርስቲያንን እንዴት ይመራታል?» በማለት መጠየቁ ጳጳሳት ስለተባሉት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እንጂ ዛሬ እንደሚነገረው በተናጠል ስለቀሳውስት አይደለም። በዚህ ዘመን ቀሳውስቱ መቼ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሆኑ? መነኮሳቱ መሪነቱን ተረክበው ይዘውት አይደለም እንዴ ያሉት?
ወደርዕሰ አሳባችን ስንመለስ ጳጳሳት እንደማንኛውም ሰው ሊሳሳቱ ይችላሉ። በኃጢአትም ሊወድቁ ይችላሉ። እንኳን በዚህች ምድረ ፋይድ ያለው የሰው ልጅ ቀርቶ በገነት የኖረው አዳምም ተሳስቷል። ስለዚህ ጵጵስና ማዕርግ እንጂ ከኃጢአት የመንጻት ማረጋገጫ አይደለም። ሁለት ፓስፖርት ይዘው የሚኖሩ፤ በሚሊዮኖች ብር የሚገመት ቤት የሚገነቡ፤ እንደውሃ የሚፈስ መኪና በሚነዱበት ሀገርና ገንዘባቸው ባንክን ማጨናነቁ በሚነገርበት ዓለም ስለብቃት መናገር አይቻልም። የዘር ቆጠራውና የወንዜ ልጅ ዜማው የሚገነው በነዚሁ በጳጳሳቱ ላይ ነው። የሚነገረውና የሚወራው ሁሉ እውነት ባይሆንም ስለሥጋ ድክመትና ስለኃጢአት መኖር ግን ማንም ሊያስተባብል አይችልም። ስለዚህ ማኅበረ ቅዱሳንን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በማሳደግ፤ በማግነን አሁን ላለበት ደረጃ በማድረስ በኩል ጳጳሳቱ ኃላፊነት አለባቸው። የትውልድም፤ የታሪክም ተጠያቂነት እንዲሁም በሆነውና በሚሆነው ነገር ሁሉ በእግአብሔር ፊት ተጠያቂዎች ናቸው።
ጳጳሳቱ በተቀመጡበት የቤተ ክርስቲያን አመራር ወንበር ላይ መንፈሳዊ ይሁን ቁሳዊ ልማት የማምጣት፤ ሕዝቡን ወደ እድገትና ራስን ወደመቻል የሥራ አቅም የማሳደግ ኃላፊነት የተጣለባቸው ቢሆንም ይህንን ሲያደርጉ አይታዩም። ከዚህ ይልቅ በማኅበረ ቅዱሳን ባላ እየተደገፉ ስሙን ጳጳሳቱ ተሸክመው ሥራውን ለማኅበሩ በመስጠት ቤተ ክርስቲያኒቱ ከነበረችበት ፈቀቅ እንዳትል አድርገዋታል። ቤተ ክርስቲያኒቱ ካሏት ሁለት ኮሌጆች በስተቀር በሀገረ ስብከት ደረጃ አንድም ጳጳስ ኮሌጅ ወይም ሴሚናሪ ት/ቤት ከፍቶ አልታየም። የጧፍ ወይም የሻማ ማምረቻ ሠርቷል የሚል ዜና አልሰማንም። 
ምናልባት ወደፊት ቤተ ክርስቲያኒቱ የጳጳሳትን ሹመት ይሁን ያሉትን የማዘዋወር ሁኔታ ማከናወን ያለበት ከፈጸሙት ልማትና የሥራ ብቃት አንጻር መሆን እንዳለበት ሊሰመርበት ይገባል። ጵጵስናን በተመለከተ ከማዕርጉ የሚያስሽሩ ሁኔታዎችም ትኩረት ተሰጥቶባቸው የሕግ ማዕቀፎች ካልተሰራባቸው ቤተ ክርስቲያኒቱ የበለጠ ፈታኝ ሁኔታ እንደሚገጥማት ለማወቅ ነብይ መሆንን አይጠይቅም። ከካህናቱና ከሕዝቡ ዓይን የተሰወረ አንዳችም ነገር አይኖርም።
 ቤተ ክርስቲያኒቱ ለሁለት የተከፈለችውም ይሁን ክፍፍሉ ባለበት ቦታ ሁሉ ውስጧ የሚታወከው በጳጳሳቱ በራሳቸው መሆኑን ያየናቸው ተሞክሮዎች ያስረዱናል።

6/ ማኅበረ ቅዱሳንና የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ አይገናኙም!

ቤተክርስቲያን በመዋቅር የሊቃውንት ጉባዔ እንዳላት ይታወቃል። ይሁን እንጂ ይህ የሊቃውንት ጉባዔ የቤተ ክርስቲያኒቱን በዘመኑ ያሉ አስተምህሮዎች እየመረመረ ስህተቶችን እየለየ፤ በሐዋርያት መሠረት ላይ ያሉትን እያጸና እውነታኛውንና የቀደምት አበውን ትምህርት ሕዝቡን መመገብ ሲገባው እስከመኖሩ በማይታወቅበት ደረጃ ላይ መገኘቱ ያሳዝናል። ዛሬ ላይ የሊቃውንት ጉባዔውን ጉባዔ በአጅ አዙር በመረከብ በመመርመር ለስደትና ለውግዘት ተሰልፎ የሚገኘው ይህ ማኅበረ ቅዱሳን የተባለው ያልተማረው ሊቃውንት ጉባዔ ነው። በዚህ ማኅበር የተነሳ እውነት ተደፍቆ ተቀብሯል። ሊቃውንት ተሰደዋል። እነ ሆድ አምላኩና እነልጆቼን ላሳድግበት ብቻ ወንበር ይዘው ቀርተዋል። ይሁን እንጂ ይህ ድርጊት መቀጠሉ መልስ ያልተገኘላቸውን ጥያቄዎች ማስቀረት አልቻለም።ወደፊትም አይችልም። የተለመደው ባህላዊ እምነት ሳይነካ ባለበት ተሸፍኖ እንዲቀመጥ ማድረጉ ኩብለላውን አላቆመም።  ሊያቆምም አይችልም። ትውልዱ የሚነገረውን ብቻ እየሰማ የሚነዳ ሳይሆን የሚጠይቅም በመሆኑ ከፊት እየሄደ የሚመራ ሊቃውንት ጉባዔ ያስፈልግ ነበር። እንዳለመታደል ሆኖ ይህ አልሆነም። አሁን በሚታየው ሁኔታም መቼም ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም። በዚህ ላይ የተረት አባትና የአፄው ዘውግ አንጋች ማኅበረ ቅዱሳንና ጳጳሳቱ እያሉ የወንጌል እውነት ተገልጦ፤ የአበው አስተምህሮ አደባባይ ላይ ይነገራል ማለት ዘበት ነው። ተረትና እንቆቅልሽ፤ ባህልና ወግ እምነት መሆናቸው ያበቃል ተብሎ አይታሰብም። ተኃድሶ የባህሪው የሆነው እግዚአብሔር ነገሮችን በሆነ መንገድ ይለውጥ እንደሆነ ወደሰማይ ማንጋገጥ የወቅቱ አማራጭ ሆኗል። በአጠቃላይ ሲታይ ማኅበረ ቅዱሳን ሳይፈለግ የተገኘ፤ ሳይወደድ የቆየ፤ እየተጠላ ለመኖር የሚታገል በጥቂት አንጃ ጳጳሳት የሚደገፍና ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሸክም የሆነ ድርጅት ነው።
ኤር 29፥12
እናንተም ትጠሩኛለችሁ፥ ሄዳችሁም ወደ እኔ ትጸልያላችሁ፥ እኔም እሰማችኋለሁ።ኤር 29፥12 «እናንተም ትጠሩኛለችሁ፥ ሄዳችሁም ወደ እኔ ትጸልያላችሁ፥ እኔም እሰማችኋለሁ» ያለ እግዚአብሔር ሁሉን እስኪለውጥ በትዕግስት መጠበቅ ብልኅነት ይመስለናል።

Thursday, October 30, 2014

«የሚያስፈራሩን ከሆነ ወደየገዳማችን እንሄድልዎታለን!» አባ አብርሃም፤ «ወደየትኛው ገዳምዎ? ለመሆኑ ገዳም ያውቃሉ?» ፓትርያርክ ማትያስ


ቅዱስ ፓትርያርኩ ስለማኅበረ ቅዱሳን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለውን የፈረጠመ ጡንቻ ሲገልጹ «የፈርዖን አገዛዝ» ነበር ያሉት። ማኅበረ ቅዱሳን የደርግ መንግሥት መውደቅ የወለደውና በዓለት ስንጥቅ መካከል የበቀለ ዛፍ ነው። ዓለቱን አንቆ ይዞ በላዩ ላይ የለመለመ ነገር ግን ከአለቱ መካከል ከወጣ ኅልውና የሌለው ሥር አልባ መሆኑም እርግጥ ነው።  ይህን ሽብልቅ ገብቶ የፈረጠመውን ዛፍ ከማነቃነቅ ባለፈ ከሥሩ ነግሎ ለመጣል ጊዜና ሰው የተገናኙት ዘንድሮ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ዘመነ ፕትርክና ነው። ዋና ዓላማውም ከመሠሪና ስውር የቤተ ክርስቲያን ውስጥ ወረራ ብቸኛዋን ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያንን መታደግ መሆኑን ቅዱስ ፓትርያርኩ በግልጽ ደጋግመው ተናግረዋል።

 «ጊዜ ገቢር ለእግዚአብሔር» እንዲል መጽሐፉ ዘንድሮ ቀኑ ደርሶ ማኅበረ ቅዱሳንም ሆነ በማኅበረ ቅዱሳን እስትንፋስ የሚንቀሳቀሱ ተላላኪ ጳጳሳቱ የቤተ ክርስቲያኒቱን እጅ ጠምዝዘው ለማስረከብ ደፋ ቀና የሚሉበት ዘመን ግብዓተ መሬቱ እየተፈጸመ ይገኛል። ከትናንት በስቲያ በነበረው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ ላይ የጉድ ሙዳይ የሚባለው ሊቀጳጳስ አባ አብርሃም በአቡነ ጳውሎስ ላይ የለመደ አፉን በአቡነ ማትያስ ላይ በመክፈት «የመንግሥትን ኃይል ተማምነው አያስፈራሩን፤ የሚያስፈራሩን ከሆነ ሲኖዶሱን ለቀንልዎ ወደየገዳማችን እንሄድልዎታለን» ብሎ እስከመናገር የደረሰ ሲሆን ቅዱስ ፓትርያርኩም ለሱም ይሁን ለቢጤ ወንድሞቹ ራስ ምታት የሆነ ምላሽ በመስጠት ዝም ጭጭ እንዲል አድርገውታል።

«ኧረ ለመሆኑ የእርስዎ ገዳም የት ነው? እስኪ ንገሩኝ የትኛው ገዳም ነው ያገለገሉት?  ደግሞስ እኔ አባ ማትያስ ለእርስዎ አንሼ ነው የመንግሥትን እርዳታ የምጠይቀው? ምነው! ቤተ ክርስቲያን እንደተሸከመችዎ አውቀው አርፈው ቢቀመጡ?!» በማለት የጳጳሱን ጉድ ጫፍ ጫፉን በመናገር አፉን እንዳስያዙት የውስጥ ምንጮች ገልጸዋል።

ተመሳሳይ በሽታ የነበረባቸው የማኅበሩ ጳጳሳት የጓደኛቸው ጉድ ፊታቸው ሲነገር በመስማታቸው የተሸማቀቁ ሲሆን አንዳንዶቹ በብስጭት ጉባዔውን ለመረበሽና ለምን ተነካን? የማለት ያህል ሲቁነጠነጡ ታይተዋል። ይሁን እንጂ ከቅዱስ ፓትርያርኩ የተሰጣቸው ምላሽ «ምን አለፋችሁ? ዘንድሮ ማኅበረ ቅዱሳንን በሕግና በሥርዓት ሳላስገባው አልተወውም!» በማለት ቁርጡን እንደነገሯቸው ተያይዞ የደረሰው ዜና ያስረዳል።
ቀደም ሲል የማኅበሩ ደጋፊ የነበሩ አንዳንድ ጳጳሳት ግን የፓትርያርኩን የጠነከረ አቋም ያጤኑ በሚመስል መልኩ ተዐቅቦን መርጠዋል። እነአባ ኤልያስ፤አባ ሉቃስ፤ አባ ቀውስጦስና በእድሜ ገፋ ያሉት ጳጳሳት ጥቂት የታገሉ ቢሆንም ከአባ ገብርኤል በስተቀር ወሎዬዎቹ ሊቃነ ጳጳሳት ግን ዝምታን መምረጣቸው ተዘግቧል። ምናልባትም «እነዚህ እኮ መንግሥትን ከአንድ ክፍለ ሀገር፤ ወደ ሌላ ክ/ሀገር ማዛወር የቻሉ ናቸው፤ ዛሬ አቤሲዲ ቆጥረውማ ማን ይችላቸዋል?» የተባለው ኃይለ ቃል ሳይከነክናቸው የቀረ አይመስልም።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የተደረሰበት ውሳኔ እንደሚያሳየው ማኅበረ ቅዱሳን አፈንግጦ ከወጣበት የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ተመልሶ በሥሩ እንዲተዳደር፤ በቤተ ክህነቱ ሞዴላ ሞዴሎች እንዲጠቀም፤ እስከዛሬ የፈጸመው የገቢና ወጪው አጠቃላይ ሂሳብ በቤተ ክህነት ባለሙያዎች እንዲመረመር፤ አዲስ በሚረቀቀውና ፀድቆ በሚሰጠው የመተዳደሪያ ደንብ በቤተ ክህነቱ ቁጥጥር እንዲንቀሳቀስ፤ ማንኛውንም ሥራ ቤተ ክህነቱን እያስፈቀደ እንዲፈጽም የሚያስገድደው ውሳኔ የተላለፈበት መሆኑም ተዘግቧል። ድንቅ ውሳኔና ተገቢነቱም ትክክለኛ እንደሆነ አስምረንበታል።

 ድሮም በዚህ ዓይነቱ ልክና ገደብ ባለው አካሄድ ይስራ ከመባሉ ውጪ ይፍረስ፤ ይውደም ያለው  ማንም አልነበረም። ነገር ግን ማኅበሩ ያለውን ዓላማ ከግብ ለማድረስ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕግና ሥርዓት ዘለለ መልኩ በአባላት ጳጳሶቹ በኩል እንደሚመቸው አጣሞ በማስቀረጽ መንቀሳቀሱ እንዲገደብ ካለመፈለጉ የተነሳ ወደመላተም አድርሶታል።

የሚደርስበትን ጥላቻና ተቃውሞ ለመሸፈንና በቅዱስ ሲኖዶስ ሥር ለመሸሸግ በመፈለግ «ሲኖዶሱ ቀርጾ ከሰጠኝ መተዳደሪያ ደንብ ውጪ አልንቀሳቀስም» እያለ መደዴ አካሄዱን ሕጋዊ ለማስመሰል ይፈልጋል። እንደነአባ የጉድ ሙዳይ አባላቱ የሰጡትን ገደብ አልባ መተዳደሪያ ደንብ በማሞካሸት በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ የተጻፈ ለማስመሰል መሞከሩ ራሱን ከሚያታልልበት በስተቀር ማንንም ማሞኘት አይችልም። «የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው» በሚል ስልት የሚያጨበጭቡለት ጥቂቶች ባይታጡም አብዛኛው የቤተ ክህነት ሰው ዓይንህን ላፈር ካለው ውሎ አድሯል።
ጳጳሳቱ በማኅበረ ቅዱሳን አዚም ነፍዘው ቤተ ክርስቲያኒቱን አጨብጭበው ለማስረከብ በደረሱበት ሰዓት ፓትርያርክ አባ ማትያስ ደርሰው ልጓም አልባ ሩጫውን ገደብ ሰጥተውታል። ምናልባትም በማኅበሩ ግፍና መከራ የወረደባቸው ማኅበረ ካህናት፤ በኃጢአት ገመናቸውን እየገለበ የሚያሳድዳቸው ማኅበረ መነኮሳትና በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት ያለቀሱት ልቅሶና ያፈሰሱት እንባ ከመንበረ ጸባዖት ደርሶ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የመጣ ፍርድ ይሆን ይሆናል።
ወደፊትም ማኅበሩ ጊዜ በመግዛት የራሱን ሌላ አማራጭ ለመፍጠር እስትንፋሱን ያሰባስብ ይሆናል እንጂ አሁን በሚሰጠው ሕግና ሥርዓት ይተዳደራል ተብሎ አይጠበቅም። ለሁሉም አሁን የተያዘው የፓትርያርኩ እርምጃ በቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት ዘንድ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ያለው ነው።
 ሁላችንም ይበል ብለናል!