Thursday, February 6, 2014

ቅድስት ድንግል ማርያም ላይ መዋሸት ይቁም! -


By Mesy Yegetalij (facebook)
ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት" ቆላ 3፤17
ቅድስት ድንግል ማርያም ጸጋን የተሞላች፣ በትሕትናዋ፣ በእምነቷ በቅድስናዋ ተወዳዳሪ የሌላት፣ አስደነቂውን መለኮታዊ ምሥጢር በልቧ በመጠበቅ እስከ መስቀል ድረስ የተገኘች ብቸኛዋ እናታችን ናት።
ቅድስት ድንግል ማርያምን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በእምነታቸው ከተመሠከረላቸው ቅዱሳን ሁሉ ልዩ የሚያደርጋት እምነቷ መለኮትን በማሕጸኗ መሸከሟ እና ምሥጢር ጠባቂነቷ ነው። ያለወንድ ዘር ልጅ ትወልጃለሽ፣ ይህን ለማድረግ እግዚአብሔር አይሳነውም ተብሎ ሲነገራት እንደ ቃልህ ይሁንልኝ በማለት አመነች። እጅግ አስደናቂ እምነት ነው፣ ኤልሳቤጥ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልታ ከእግዚአብሔር ዘንድ የነገሩሽን ቃል የምታምኚ አንቺ ብፅእት ነሽ በማለት አክብሮቷን ገለጠች።
ቅዱስ ገብርኤልም የተላከበትን ምክንያት ከመናገሩ በፊት በእግዚአብሔር ፊት ያላትን ክብር ከሰማይ ያየውንና የሰማውን በመለኮታዊው ዙፋን ዘንድ ያላትን ሞገስ ነበር ያበሠራት። ቅዱስ ገብርኤል በእግዚአብሔር ፊት የሚቆም መልአክ እንደመሆኑ መጠን ድንግል ማርያም በሥላሴ መለኮታዊ ክብር የታሰበች መሆኗን ተረድቷል፣ ስለዚህ በርሷ ላይ ያለው የጌታ ክብር ነውና ተጠንቅቆና ተንቀጥቅጦ ነበር የቀረባት። መልአኩ ወደ ድንግል ማርያም ሲቀርብ በታላቅ ትህትና ነበር። ምክንያቱም እግዚአብሔር ከርሷ ጋር ነውና ልኳን እና መጠኗን ይረዳል። እርሷ በመለኮታዊ ክብር ተሸፍና በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ተሞልታለች።
ድንግል ማርያም መልአኩ ካበሠራት ጀምሮ በእርሷ እየተካሄደ ያለውን ምሥጢር ታውቃለች፣ አካላዊ ቃል ከሰማይ ወርዶ በማሕጸኗ አድሮ ተጸንሷል። በዚህ ጊዜ እራሷን በጌታ ፊት ዝቅ አድርጋ "ነፍሴ ጌታ እግዚአብሔርን ታከብረዋለች መንፈሴ በአምላኬና በመድኃኒቴ ሐሴት ታድርጋለች እርሱ በእኔ ታላቅ ሥራ አድርጓልና" ስትል እግዚአብሔርን አከበረች
ድንግል ማርያም እጅግ አስደናቂው ውበቷ ያለው እዚህ ላይ ነው። ነገሩን በልቧ ይዛ ትጠብቀው ነበር እንጂ ለማንም አላወራችም። የጌታን ምሥጢር ያለጊዜው መግለጥ አልፈለገችም፣ ከተጸነሰ ጀምሮ እስከ ሞቱ ድረስ በምሥጢር ያዘችው ። ለሰላሣ ሦስት ዓመት ያህል ዝም በማለት እግዚአብሔርን ጠበቀች፤ ይህ ነው ቅድስተ ቅዱሳን የሚያሰኛት ድንግል ማርያምን "ከሴቶች ሁሉ ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ" ያሰኛምት ይህ ነው። ድንግል ማርያም ከአእምሮ በላይ የሆነ ትግሥት አሳይታለች፤ እውነትም ጸጋን የተመላች ናት የድንግል ማርያም እንደዚህ የመቀደስ ዋና ምክንያት ግን እግዚአብሔር ከርሷ ጋር ስለሆነ ነው።
"አላዋቂ ሳሚ ንፍጥ ይለቀልቃል" እንደተባለው፣ ድንግል ማርያምን እናከብራለን ያሉ ሐሰቶኞች በድንግል ማርያም ላይ የተናገሩትና አሁንም እያስተማሩ ያሉት ግን በመጽሐፍ ቅዱስ የምናውቃት ድንግል ማርያምን አትመስልም። መናፍቃን በድንግል ማርያም ላይ የፈጸሙትን ስም ማጥፋት ጥቂት እንመልከትና እኛም ድንግል ማርያምን ያከበርን እየመሰለን በርሷ ላይ ሐሰትን ከመናገር መቆጠብ አለብን።
በተዓምረ ማርያም የተጻፈውን ውሸት እውነት በሆነው በእግዚአብሔር ቃል እንመርምር፦t

"ዘከመ ጸለየት እግዝእትነ አመ አሠርቱ ወሰደስቱ ለየካቲት እምድህረ እርገቱ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ወዘከመ ነሥአት ኪዳነ ምሕረት ዘኢይትሄሰው"
ትርጉም "ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካረገ በኋላ እመቤታችን እንደጸለየችና የካቲት አሥራ ስድስት ቀን የምሕረት ቃል ኪዳን እንደተቀበለች"
"ኢያንተገት ገዪሰ ወጸልዮ ኀበ መቃብረ ወልዳ ዘውእቱ ጎልጎታ"
ትርጉም "ወደ ልጇ መቃብር እየሄደች መጸለይን አቋርጣ አታውቅም፣ ይኸውም ጎልጎታ ነው"
ይህ ታምር ነው ከተባለ ደራሲው ሊል የሚፈልገው ጌታ ካረገ በኋላ የካቲት አሥራ ስድስት ቀን፣ ጎልጎታ በሚገኘው የጌታ መቃብር ስትጸልይ፣ ጌታ ተገልጦ ቃል ኪዳን እንደሰጣት፣ እመቤታችንም ጌታ ከሞተ ጀምሮ መቃብሩ ላይ ቆማ መጸለይን አቋርጣ እንደማታውቅ፣ ጌታም ሁልጊዜ ይጎበኛት እንደነበር ነው።
ጌታ የተሰቀለው መጋቢት ሃያ ሰባት ሲሆን የተነሣው ደግሞ መጋቢት 30 እንደሆነ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያስረዳል። እንግዲህ እመቤታችን ኪዳን የተቀበለችው የካቲት አሥራ ስድስት ቀን ከሆነ አንድ ዓመት ሙሉ ወደ ጌታ መቃብር ስትመላለስ ነበር ማለት ነው። ይህ ታሪክ የመቤታችንን ስም ያጠፋል፣ ምክንያቱም እመቤታችን በመንፈስ ቅዱስ የተሞላች በእግዚአብሔር የሆነውን ነገር ሁሉ የምታምን ቅድስት ናት። የጌታን ትንሣኤ አይታለች፣ እርገቱንም ተመልክታለች፣ እርሱ ዓለምን ለማዳን ከእርሷ እንደተወለደ፣ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ፣ ለዘለዓለም ሕያው እንደሆነ፣ ከስም ሁሉ በላይ የሆነ ስም እንዳለው፣ በፍጥረት ሁሉ በላይ ከፍ ያለ ጌታ እንደሆነ፣ በዙፋኑ ላይ የተቀመጠ ልዑል፣ ዳግም ለፍርድ እንደሚገለጥ ከማንም በላይ የተረዳች እናት ናት።
ታዲያ ሞቶ እንደቀረና እንዳልተነሣ፣ በአብ ቀኝ በዙፋኑ እንዳልተቀመጠ፣ በማሰብ መቃብሩ ላይ ዕለት ዕለት እየተገኘች እንዴት ልታለቅስ ቻለች? የጌታን ትንሣኤና እርገት በዓይኗ አይታ በደስታ በመሞላት እንደርሷ ያለ ከየት ይገኛል? ኢየሱስ ክርስቶስ ኃጥአንን ሊያድን እንደመጣ ከርሷ በላይ ማን ሊያውቅ ይችላል? ቅድስት ድንግል ማርያም የጌታን እርገት ያየች ስለሆነ በመቃብሩ ላይ ታለቅስ ነበር የሚለው አባባል የደብተራ ተረት ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ ጌታ ካረገ በኋላ እመቤታችን ትጸልይበት የነበረውን ሥፍራ እንዲህ ሲል አስቀምጦታል።
"በዚያም ጊዜ ደብረ ዘይት ከሚባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ... እነዚህ ሁሉ ከሴቶችና ከኢየሱስ እናት ከማርያም ከወንድሞቹም ጋር በአንድ ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር" የሐዋ 1፥12፡14 ይጸልዩበት ስለነበረው ሥፍራ ሲናገርም "በገቡም ጊዜ ወደሚኖሩበት ሰገነት ወጡ" ይላል ቁ 13። ይህ ሰገነት ጽርሐ ጽዮን የተባለው የማርቆስ እናት ቤት ነው። የጸለየችውም ከሐዋርያት ጋር ነበር በዚያ ቤት ሳሉም መንፈስ ቅዱስ እንደወረደላቸውና ምሥጢር ሁሉ እንደተገለጠላቸው እንጂ ሌላ ታሪክ አናነብም። እስከ ዓለም ፍጻሜ እኔ ከናንተ ጋር ነኝ ስላለ ጌታ ከእመቤታችንም ተለይቶ አያውቅም። እናም እመቤታችን ካረገ በኋላ አብሯት እንደሌለና የማታገኘው ይመስል መቃብር ላይ ቆማ የምታለቅስበት ምክንያት የለም። ብዙ ጊዜ መቃብር ላይ እየቆሙ ሲያለቅሱ መኖር የሥጋውያን ሰዎች ሥርዓት ነው።  ሥጋውያን የሞቱ ዘመዶቻቸውን ከተሰናበቱ በኋላ በዓይን ለማየት፤ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ለመመልከት ስለማይችሉ በተስፋ መቁረጥ ተሞልተው በሚወዷቸው ሟቾቻቸው መቃብር ላይ ሄደው ሲያለቅሱ እናያለን። መንፈሳውያን ግን እደዚህ አያደርጉም። ባህሉም የኢትዮጵያውያን እንጂ የእሥራኤላውያን አይደለም። አልቅሰው ከቀበሩ በኋላ ተስፋ እንደሌለው ሰው ዕለት ዕለት መቃብር ላይ ሄደው ያለቅሱ ነበር የሚል ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጽፎ አናገኝም።
እንደ ዘርዓ ያዕቆብ አባባል እመቤታችን የጌታን ምሥጢር በሚገባ እያወቀች መቃብር የምትጎበኝበት ምክንያት ምንድር ነው? ጌታ በመንፈስ ቅዱስ ሙላት ከርሷ ጋር እያለ፤ ከመቃብር ደጃፍ ተቀምጠው የታዩት መላዕክት «ሕያውን ከሙታን መካከል  ስለምን ትፈልጋላችሁ?» መባሉን ያወቀችና የተረዳች እናት መቃብሩ ላይ ዕለት ዕለት እየሄደች  ለአንድ ዓመት አለቀሰች ማለት ስም ማጥፋት ነው። የጌታን እናት ማርያምን ሳይሆን ሌላ የኦርቶዶክሶች ማርያም መሆን አለባት። በእውነቱ ይህ ጠላት የጠነሰሰው ሐሰት እንጂ የጌታየ እናት ቅድስት ድንግል ማርያም ይህን ታሪክ አታውቀውም። ከሁሉም በላይ ጸጋ የበዛላት በእምነት እና በመለኮታዊ ምሥጢር የተሞላች ናት።
መቃብሩ ላይ ቆማ ጸለየችው የተባለው ጸሎት ደግሞ ኢየሱስ ለምን እንደሞተ የማታውቅ እስኪያስመስሏት ድረስ ዋሽተውባታል።
"በእንተ ዘይገብር ተዝካርየ ወዘየሐንጽ ቤተ ክርስቲያን በስምየ ወዘያለብስ እሩቀ በስምየ ወዘይሄውጽ ድውየ ወዘያበልዕ ርኍበ፣ ወዘያሰቲ ጽሙአ፣ አው ዘይናዝዝ፣ ኅዙነ፣ ወዘያስተፌስሕ ትኩዘ አው ዘጸሐፈ ውዳሴየ፣ ወሰመየ ወልዶ ወወለቶ በስምየ ወዘሐለየ ማኅሌተ በስምየ፣ ወበበዓልየ፣ እሥዮ እግዚኦ ዕሴተ ሠናየ ዘዓይን ኢርእየ፣ ወእዝን ኢሰምዓ ውስተ ልበ ሰብእ ዘኢተሃለየ"
ትርጉም "ተዝካሬን የሚያደረግ፣ ቤ/ክርስቲያኔንንም በስሜ የሚያሠራ፣ በስሜ የታረዘ የሚያለብስ፣ የታመመ የሚጎበኝ፣ የተራበ የሚያበላ፣ የተጠማ የሚያጠጣ፣ ወይም ያዘነ የሚያረጋጋ፣ ቢሆን፣ የተከዘ ደስ የሚያሰኝ፣ ወይም ምሥጋናዬን የጻፈ፣ ሴት ልጁን እና ወንድ ልጁን በስሜ የሰየመ፣ እኔም በምከብርበት ቀን፣ ምስጋና ያመሰገነውን፣ አቤቱ ዓይን ያላየውን፣ ጆሮ ያልሰማውን፣ በሰው ልብ ያልታሰበውን፣ በጎ ዋጋ ስጠው" ታምር 12 ቁ 39-42።
እያንዳዱን ልመና በዝርዝር እንመልከተው
"ተዝካሬን የሚያደርግ"
ተዝካር ማለት መታሰቢያ ማለት ነው፣ ድንግል ማርያም ጌታን ከጸነሰች ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ እስከ ወረደበት እስከ በዓለ ሃምሳ ድረስ መጽሐፍ ቅዱስ ያስባታል።
ጌታን የሚያውቅ ሁሉ እናቱንም ያውቃል፣ ስለጌታ መወለድ ስንናገር ማን እንደወለደው መናገር የግድ ነው። ጌታ ሲሰደድ ማን ይዞት እንደተሰደደ መናገር አያጠያይቅም። የድንግል ማርያም መታሰቢያ መልዓኩ ካበሠራት ጀምሮ ጌታን መውለዷ፣ መሰደዷ፣ በሞቱ ጊዜ እስከ መስቀል ድረስ መገኘቷ፣ በሰርጉ ቤት ለባለሠርጉ ያሳየችው ርኅራሄ፣ ወዘተ ነው። ይህም የተጻፈው ታሪኬን ተናገሩልኝ ውዳሴየን  ጻፉልኝ ብላ ስለለመነች ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የተደረገ ነው። እመቤታችን "ተዝካሬን ያደረገ" ብላ ስትጠይቅ እንደ ዘርዓ ያዕቆብ አባባል ድግስ ደግሶ፣ ጠላ ጠምቆ፣ ንፍሮ ቀቅሎ፣ በየወሩም ሆነ በያመቱ የመገበ ሰው ምሕረት እንዲያገኝ ጌታን ለመነችው ማለት ነው።
ጌታ ብራብ አብልታችሁኛል ብጠማ አጠጥታችሁኛል ወዘተ ብሎ የተራበን ማብላት የተጠማን ማጠጣት እንደሚገባን አስተምሮናል። ይህን የልጇን የወዳጇን ቃል ወደራሷ ወስዳ «በስሜ ያበላውን ያጠጣውን» በማለት እመቤታችን አትዋሽም።  «ብራብ አብልታችሁኛል፤ ብጠማ አጠጥታችሁኛል» በማለት ልጇ ያስተማረውን ቃል ከማንም በላይ እሷ ታውቃለችና።
የፍቅር እናት በመጽሐፍ ታሪኳ እንዲጻፍ ማንንም አልጠየቀችም። ለመጽደቅ ከፈለጋችሁ የምስጋናዬንም ድርሳን ጻፉልኝ ብላ ለማንም አልተናገረችም። «ሁሉን ነገር በልቧ ትጠብቅ» የነበረች የፍቅርና የትህትና እናት  ድንግል ማርያም እንደምድራውያን የነገሥታት ቤተሰቦች ሃሳብ ታሪኬን ጻፉልኝ፤ ድርሳኔንም አባዙልኝ፤ ያኔ አጸድቃችኋለሁ ብላለች ማለት ፈጽሞ ሀሰት ነው። መጽሐፍና ድርሳን የኋላ ሠዎች ታሪክን ሰንደው፤ ገድልን ጠርዘው ለማስታወስ እንዲቻል ያዘጋጁት እንጂ «ትውልድ ሁሉ ብጽእት» እንደሚላት የምታውቅ የጌታ እናት ስሟ እንዲታወስና ሰዎች እንዲጸድቁ ሽታ እኔ ስሞት ጻፉልኝ አላለችም።
ታዲያ በየወሩ በምንሰጠው እንጀራ ለዚያዉም በርሷ ስም እንደምንጸድቅ እንዴት አሰበች? በርግጥ ይህ የድንግል ማርያም ልመና ነው? ወይስ መብላት የለመደ ደሞዙን ለማስተካከል ያለ ሥራ በሰው ትከሻ ለመኖር ያሰበ ደብተራ የፈጠረው ፈጠራ?
ደሞዝን ለቤተ ክርስቲያን በአግባቡ በአሥራት በስጦታ ከመጣው ማግኘት ሲቻል ወሩን እና ዓመቱን ቀኑን ሁሉ የመታሰቢያ ቀን በማድረግ ሕዝብን ለመዝረፍ ለምን ታቀደ?
የምናደረግውን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንድናድረገው መጽሐፍ ቅዱስ ያዝዛል "እግዚአብሔርን አብን በእርሱ እያመሰገናችሁ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት" ቆላ 3፥17
እንግዲህ እመቤታችን በመንፈስ ቅዱስ የተሞላች ናትና እራሷን ከጌታ ጋር በማወዳደር "በስሜ መታሰቢያየን ያደረገ" የሚለውን ልመና አላቀረበችም ብለን እንደመድማለን፤ እመቤታችን ትሑትና ዝምተኛ ሁሉንም በልቧ ይዛ እግዚአብሔርን የምትጠብቅ እጅግ የተቀደሰች እናት ናት። ስሜ ይጠራልኝ በሚል ስሜት ልመና አቀረበች ብሎ በማርያም ላይ መናገር ስድብና ድፍረት ነው።

Friday, January 31, 2014

እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ፥ ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኮለኞች ሠራተኞች ናቸውና! 2ኛ ቆሮ 11፤13-14

 

«የእግዚአብሔር መንፈስ እንዲያድርባችሁ ሳር ጋጡ የተባሉ ደቡብ አፍሪካውያን ሳር ሲግጡ ዋሉ!!» በሚል ርዕስ ከዚህ በፊት በጽሁፍ ያስነበብናችሁ መሆኑ አይዘነጋም። የሣር መጋጡን መርሐ ግብር ተንቀሳቃሽ ምስል እነሆ አቀረብናላችሁ። ፓስተር ሌሴጎ ዳንኤልና ተከታዮቹ በአዳራሽ ተቀምጠው የቀጥታ ስርጭቱን በማየት ይዝናናሉ። ፓስተሩ በመጀመሪያ ረጋገጣቸው፤ በጫማ ጠቀጠቃቸው ከዚያም ልቡናቸውን ሰውሮ እንደከብት ሳር እንዲግጡ አደረጋቸው።

«ነገር ግን ሐሰተኞች ነቢያት ደግሞ በሕዝቡ መካከል ነበሩ እንዲሁም በመካከላችሁ ደግሞ ሐሰተኞች አስተማሪዎች ይሆናሉ፤ እነርሱም የዋጃቸውን ጌታ እንኳ ክደው የሚፈጥንን ጥፋት በራሳቸው ላይ እየሳቡ የሚያጠፋ ኑፋቄን አሹልከው ያገባሉ፤ብዙዎችም በመዳራታቸው ይከተሉአቸዋል በእነርሱም ጠንቅ የእውነት መንገድ ይሰደባል» 2ኛ ጴጥ 2፤2


Wednesday, January 29, 2014

የሶርያ ክርስቲያኖች በአሸባሪዎች እየተገደሉ፤ እየተሰደዱ፤ ገዳማትና አድባራት እየወደሙ ናቸው!




በዴር አልዙር የሚገኘው የሶርያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፍርስራሽ
ክርስትና በደም ተመስርታ፤ በፈተና ወጀብና ማዕበል እየተገፋች እነሆ ዛሬ ላይ ደርሳለች። ዓለም አንድ መንደር ሆናለች፤ ህግና ህግ ብቻ ዓለምን ይመራታል በተባለበት በ21ኛው ክ/ዘመን ላይም ክርስትና ሞትና የእሳት አደጋ አልተለያትም። 

የሚገርመው ደግሞ ክርስትና በእጇ የሚገኘውን መጽሐፍ ቅዱስ ይዛ ከመጓዝ ባሻገር ለእምነቷ መስፋፋት ጦርና ሰይፍ የማትመዝ ቢሆንም ባላጋራዎቿ እንዳትመጣባቸው ለመከላከል ሲሉ ወይም ከመጣች በኋላ ለማጥፋት ሲሹ በተቃራኒው ሰይፍና ጦር እየመዘዙባት ዘመናትን ማስቆጠሯ ነው።
 ይህንን መከራ ካሳለፉት ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት መካከል የሶርያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን( የአንጾኪያ) ወይም ያዕቆባዊት ቤተ ክርስቲያን  ግንባር ቀደሟ ቤተ ክርስቲያን ናት።  በሐዋርያት ሥራ 11፤26 ላይ እንደተመለከተው «ሐዋርያት በመጀመሪያ ክርስቲያን ተባሉ» የሚለውን ቃል የክርስትናቸው መነሻ አድርገው የሚቆጥሩት ሶርያውያን ክርስቲያኖች፤ በሮማውያን፤ በፋርሶችና፤ በቱርኮች ወረራ ብዙ ግፍና መከራ ያሳለፉ ሲሆን ሶርያ ወደእስላማዊ ግዛት በእስላም ወረራ ከተለወጠችበት ጊዜ ጀምሮ ስቃይና ፈተናው ተጠናክሮ እንደቀጠለ ታሪክ ይነግረናል። ሀገሪቱ በአላዋይት የእስልምና ጎሳ በምትመራበት ዘመን የተሻለ ሰላም የነበራት የሶርያ ቤተ ክርስቲያን ዐረባዊ ዐመጽ በዐረብ ሀገራት ከተቀጣጠለ ጊዜ አንስቶ ግን ሰላም ርቋት፤ ገዳማቷ ፈርሰው፤ መነኮሳትና መነኮሳይያቷ ተገድለው፤ ክርስቲያኖቿ ተሰደው፤ አድባራቷ ተቃጥለው ዛሬ ላይ ወደመጥፋት ከተቃረቡት ጥናታዊ አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዷ ወደመሆን ደርሳለች።
በሰሜን ሶሪያ ወናውን የቀረው ገዳም

በቁስይር የሚገኘው የሶርያ ቤተ ክርስቲያን
 እስካሁን በዓለም አቀፍ አኀዛዊ መረጃ መሠረት 400, 000 ክርስቲያኖች የተወለዱበትንና ያደጉበትን ቀዬ ለቀው እግራቸው ወደመራቸው ተሰደዋል። 60 ትላልቅ ጥናታውያን አድባራትና ገዳማት ተቃጥለዋል። ከዚህ ውስጥ ለአብነት የሚጠቀሰው የጦርነቱ ቀውስ በክርስቲያኖቹ ላይ ያደረሰው በደል በታህሳስ ወር መጨረሻ ገደማ ላይ 13 መነኮሳይያት ጦርነቱን ሸሽተው ከተሸሸጉበት ገዳም ውስጥ እጃቸው በጽንፈኞቹ ተይዞ እንደመደራደሪያ መሣሪያ መቆጠራቸው አይዘነጋም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሱኒ/ወሀቢዝም ጽንፈኞች ባሉበት ቦታ ሁሉ ከሳዑዲ ጋር ከጀርባ የማትጠፋው ኳታር ከሊባኖስ መንግሥት ጋር ባደረገችው ሽምግልና አሸባሪዎቹ በመነኮሳይያቱ ላይ ምን ጉዳት እንዳያደርሱና እንደመያዣ መጠቀማቸውን አቁመው በነጻ እንዲለቋቸው በማግባባቷ መለቀቃቸውን የሊባኖሱ ዴይሊ ስታር መዘገቡ አይዘነጋም። ይህንኑ ዘገባ  የኳታሩ «አልጀዚራ ሙባሸር» ቴሌቪዥን መነኮሳይያቱን በምስል በማሳየትም ጭምር የኳታርን ትስስርና የማንነት አቅም መረዳት ችለናል።
በኳታሩ አልጀዚራ ሙባሸር ቲቪ ከቀረቡት የታፈኑ መነኮሳይያት በከፊል

    ይህ በዚህ እንዳለ ብዙ ሶርያውያን ክርስቲያኖች በዚያው ያሉ ሲሆን፤ የሚመጣውን ሞት ለመቀበል የተዘጋጁ መነኮሳይያትና መነኮሳት ከሶርያ ገዳማት እስካሁን አልወጡም። ከእነዚህ መካከል አንዱ የሆኑት ፋዘር ኢዮአቄም የተባሉት ካህን ለሚዲያ እንደገለጹት የሚመጣውን ሁሉ እዚሁ ሆኜ ከመቀበል በስተቀር የትም ለመሄድ አልተዘጋጀሁም። አያይዘው እንደተናገሩት «የሶርያ ክርስቲያኖች ስደትና እንግልት ግን ልቤን ያደማዋል፤ ይህ ሁሉ ለምን ሆነብን? እያልኩ አምላኬን እጠይቃለሁ» በማለት የተሰማቸውን መንፈሳዊ ስብራት ለጋዜጠኞች ገልጸዋል።

«ሞቴን እዚሁ እጠብቃለሁ» ፋዘር ኢዮአቄም ሶርያዊ መነኩሴ
የሶርያ ክርስቲያኖች እየደረሰባቸው ያለው እንግልትና መከራ ትኩረት አግኝቶ ዓለም አቀፍ ክርስቲያኖች ሁሉ ከጎናቸው በመቆም ለችግራቸው በአፋጣኝ እንዲደርሱ የሚያሳስብ ጉባዔ በአሜሪካ የተደረገ ሲሆን በተለይም ምሥራቃውያን ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ፕሮግራሙን በጸሎትና እየጠፉ ላሉት ክርስቲያኖች እንድረስላቸው የሚል ጥሪ በማስተጋባት ማሰማታቸው ታውቋል። ይህንንም ተከትሎ የአሜሪካ መንግሥት በጎረቤት ሀገሮች ላይ ጫና በማሳደር የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ የሚያሳስብ መልዕክት እንድታስተላልፍ ጥሪ የቀረበላት ሲሆን ሳዑዲና ኳታርም የበሽር አልአሳድን መንግሥት በመጣሉ ዘመቻ ላይ ባላቸው ድርሻ ተዋጊዎቹ በክርስቲያኖች ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት እንዲያቆሙ ጥሪ ቀርቧል።
ወሀቢያዊና ሰላፊያዊ  የዐረብ ዐመጽ ከተነሳ ወዲህ በዐረብ ሀገራት የሚገኙ ክርስቲያኖች መከራ፤ስደትና ሞት ከመቼውም ጊዜ የከፋ ቢሆንም እስካሁን የተደረገው ድጋፍ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።
አሸባሪዎች በሶርያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ


  ከዚህ በፊት የሶርያ፤  አሌፖ ከተማ ሊቀጳጳስ ፖል ይዚጊ በአሸባሪዎቹ ታፍነው ከተወሰዱ በኋላ በብዙ ድርድር ሲለቀቁ በሶርያ የፍራንሲስካን ቄስ የነበሩት  ፍራንሶይስ ሙራድ የተባሉት ደግሞ አቡ ባናት በተባለው የአሸባሪዎቹ አለቃ ሌሎች ሦስት ሰዎችን ጨምሮ በሰይፍ« አላሁ አክባር» እያለ እንዳረዳቸው መረጃዎች ያሳያሉ። በኢራቅም ከነበሩት ክርስቲያኖች ውስጥ በመቶ ሺዎች ሀገራቸውን ለቀው ተሰደዋል። በግብጽ፤ በቱኒዚያ ያሉት ክርስቲያኖችም ለመኖር የሚያበቃ መንግስታዊ ጥበቃ ስለሌላቸው እየተሰደዱ ይገኛሉ። 
ከቀኝ ወደግራ በሁለተኛው ረድፍ የሚገኘውና አቡ ባናት (የእስላም ሴቶች አባት) የተባለው የአሸባሪዎቹ አለቃ ቄስ ፍራንሶይስ ሙራድንና ሁለት ዲያቆናትን በሰይፍ ያረደ

 የምሥራቅ ኦርየንታል ቤተ ክርስቲያን አባል የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ላይ መከራና ሞት ለሚደርስባቸው ክርስቲያኖች በዘወትር ጸሎቷ እንደምታስባቸው ቢታወቅም በኦፊሴል የጸሎትና የዓለም ክርስቲያኖች ኅብረት ለተጎጂዎች በፍጥነት እንዲደርስ ማሳሰብ ብትችል መልካም ነበር። በተለይም በአሁኑ ሰዓት ገዳማትና አድባራቷ እየወደሙ፤ክርስቲያኖቿ እየተሰደዱ፤ እየታረዱ፤ ለምትገኘው ለሶርያ ያዕቆባዊት ቤተ ክርስቲያን፤  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንደአኀት ቤተ ክርስቲያንነቷ አጋርነቷን አለማሳየቷ ያሳዝናል። 
የክርስትና ምልክት መስቀል አንገታቸው ላይ በመገኘቱ ብቻ ክርስቲያኖች በገፍ እያተረዱ ነው

ለሶርያ ቤተ ክርስቲያን ሀዘንና ድምጽን ማሰማት የፖለቲካው ክፍል ፈቃድ የሚያስፈልገው ሳይሆን የክርስቶስን አገልግሎት መፈጸም መሆኑ መታወቅ ይገባዋል። በሶርያ ቤተ ክርስቲያን ላይ የእጅ አዙር መንግሥታት ሰይፍና ጦር ሲልኩ ያላፈሩ እኛ በጸሎትና በድምጽ ክርስቲያን ወንድሞቻችንን ለማጽናናት የሚያስፈራን ነገር ሊኖር ባልተገባ ነበር። እዚያ ያለው እሳት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይመጣ ድምጻችን መሰማት ያለበት ዛሬ ነው።