Thursday, January 2, 2014

ከፈረሱ ጋሪው የቀደመበት በማኅበረ ቅዱሳን የቀረበው የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት አዲሱ ጥናት!



ማኅበረ ቅዱሳን ባልታጠበ እጁ የመቅደሱን አገልግሎት ለመናኘትና የአስተዳደሩን ወንበር ለመጨበጥ ላይ ታች ማለት የጀመረው ገና አቡነ ጳውሎስን ገፍቶ እስከሞት ድረስ ከመታገሉ አስቀድሞ ነው። ተላላኪ ጳጳሳቱን ካሰማራ በኋላ በአዋጅ ባለባቸው ህመም ሳቢያ እንደሞቱ የሚነገርላቸው እና በውስጥ አዋቂዎች ደግሞ ከህመሙ ባሻገር የሰው እጅም አለበት የሚለውን  የስውር አካሄድን ይትበሃል የተመለከተ የአቡነ ጳውሎስ ኅልፈት  ከመድረሱ በፊት ማኅበሩ ራሱን ከሰንበት ት/ቤቶች መምሪያ ነጻ በማውጣት በቀጥታ ተጠሪነቱ ለሲኖዶሱና ለሥራ አስኪያጁ እንዲሆን ነጋሪት አስመታ። ከዚህ አዋጅ በኋላ ማኅበረ ቅዱሳን የማይደፈር፤ የማይነካ የቤተ ክህነቱ አንበሳ ሆነ።  በግንቦቱ የ2004 ዓ/ም  ሲኖዶስ ላይ ይህንን አስወስኖ ድል በድል በሆነበት ዋዜማ ሟቹን ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ እንዲህ ብለን ነግረናቸው ነበር።
«አመኑንም አላመኑም ፓትርያርክ ጳውሎስ፤አንድ ነገር አስረግጠን እንነግርዎታለን። በማኅበረ ቅዱሳንና በደጋፊዎቹ ጳጳሳት ግብዓተ መሬትዎ ሊፈጸም የቀረው ጥቂት ነው» ብለን ነበር። [1]
እንዳልነውም ይህንን ከተናገርን ከሁለት ወራት በኋላ አቡነ ጳውሎስ ወደማያልፈው ዓለም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሄዱ። ነብይ ስለሆንን ወይም ከሰው የተለየ ራእይ ስለመጣልን አልነበረም። በወቅቱ የነበረው የማኅበሩና በገዛ እጃቸው ጰጵሰው የጥላቻ ፈረስ ያሰገራቸው ጳጳሳት አካሄድ ጤናማ ስላልነበር አንድ ነገር ሊመጣ እንዳለ ይጠቁመን ነበርና ነው። ያልነውም ሆነ። ማኅበሩም ተደላድሎ ቤተ ክህነቱን ያዘ። ከእንግዲህ ምን ቀረው ማለት ነው? ቤተ መንግሥቱ? በዚህ ዙሪያ በሌላ ርእስ እንመለስበታለን።

 አሁን አንድ ነገር እዚህ ላይ አስረግጠን በመናገር ወደርእሰ ጉዳያችን እናምራ።
ጳጳሳቱ አንድም በራስ የመተማመን ጉድለት ባመጣው ፍርሃት ለማኅበሩ አጎብድደዋል፤ በሌላም አንድ ምክንያት ግለ ነውራቸውን አደባባይ እንዳያወጣ የበደል ምርኮኝነታቸውን አስበው ራሳቸውን ለማኅበረ ቅዱሳን አሳልፈው ሰጥተዋል። ይሁን እንጂ፤
«አመናችሁም፤ አላመናችሁም እናንተም የአባ ጳውሎስን የጥላቻ ጽዋ ከማኅበረ ቅዱሳን ዋንጫ በተራችሁና በሰዓቱ ትጎነጫላችሁ። ወደማይቀረውም ሞት ተራ በተራ በጊዜአችሁም፤ አለጊዜአችሁም ትሸኛላችሁ፤ በሕይወት እያለን ይህንን የማኅበረ ቅዱሳንን ሚዛን ስትቀበሉ እናያለን፤ ያኔ ደግሞ እንደዚህ ብለናችሁ ነበር እንላለን» ይህም ደግሞ በቅርቡ ይጀምራል»
ከአቡነ ጳውሎስ ሞት በኋላ ሲኖዶስ ማለት ማኅበረ ቅዱሳን ነው። ቀንደኛ የማኅበሩ መዘውሮች ደግሞ አፍንጫና ጆሮ በመቁረጥ በራሱ የተአምር መጽሐፍ ላይ የተመሰከረለት የዘርዓ ያዕቆብ ደቀመዛሙርት ናቸው። በእርግጥ የማኅበሩን እርጥባን እየተቀበሉ በመናጆነት የሚያገለግሉ የሉም ማለት አይደለም። እነዚህ የዘርዓ ያዕቆብ ጉዶች በረቀቀ ስልት ቤተ ክህነቱን በእጃቸው አድርገዋል። ዋነኛ መፈክራቸው ቤተ ክህነትን « በገንዘባችን፤ በጉልበታችን፤ በእውቀታችን እናገለግላለን» ነው። ገንዘባቸውን  እንደሆነ ቤተ ክህነት በጭራሽ አታውቀውም። ጉልበታቸውንም  ቢሆን እንደአበራ ሞላ በአካባቢ ጽዳት ተሰማርተው ወይም  ጥቃቅንና አነስተኛ አቋቁመው ስራ አጥ ካህናቱን ወደስራ ሲያስገቡ አላየንም። እውቀታቸውን ግን እነሆ ለአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ባቀረቡት ጥናት ሽፋን የቁጥጥር መረባቸውን ሲዘረጉ አይተናል። ይህም የረጅም ጊዜ ህልማቸውን እውን ያደረጉበት እውቀት በመሆኑ ቤተ ክህነት የጀመረችው የቁልቁለት መንገድ ነው ብሎ መናገር ይቻላል። መጨረሻውም እንደማያምር ጀማሪውን አይቶ መተንበይ አይከብድም። ይህንን እንድንል የሚያደርጉን ምክንያቶች አሉ። በጥቂቱ እንያቸው።
1/ የፕሮጀክት ጥናቱ አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኒቱ ችግሮችን የዳሰሰ መሆን ነበረበት። የችግሮቹን መግፍኢ ምክንያቶች፤ ያስከተሉት ውጤትና የመፍትሄ መንገዶችን ያመላከተ ሊሆን ይገባዋል።  የጥናቱ ዝርዝር ሁሉንም አሳታፊ በሆነ ውይይት ዳብሮ ለመፍትሄና አፈጻጸም በሚያመች መልኩ ተዘጋጅቶ አተገባበሩ ግን ለናሙና በተመረጠ አንዱ ሀ/ስብከት መሆን በተገባው ነበር እንላለን። እየሆነ ያለው ግን ማኅበሩ በሚነዳቸው ጳጳስ ፈቃጅነትና ማኅበሩ በሚዘውረው ቋሚ ሲኖዶስ ይሁንታ ከማኅበሩ ቤተ ክህነቷን የመቆጣጠር ምኞት ተፈብርኮ አዲስ አበባ ላይ የመዋቅር ብረዛ ችካል መትከል ተጀመረ።
2/ በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኒቱ ችግሮች ላይ ሊደረግ የሚገባው ሁለ ገብ ጥናት የቤተ ክርስቲያኒቱን አባላት፤ ሊቃውንት፤ ምሁራን፤ የሕግ አዋቂዎች፤  ጋዜጠኞች፤ ስልጣን ያላቸው ከፍተኛ ሹማምንት፤ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ፤ የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች የተካተቱበትና የቤተ ክርስቲያኒቱ እድገትና ልማት የሚመለከታቸው ሁሉ ተቀናጅተው ይህን የማስተባባር ኃላፊነት ቢቻል በአንድ ሊቀ ጳጳስ የሚመራ ራሱን የቻለ ክፍል ተዋቅሮ መካሄድ በተገባው ነበር። ጋኖች አለቁና ማኅበረ ቅዱሳን አርቃቂ ሆኖ ጳጳሳቱ ከየትም ይምጣ እንጂ እንቀበላለን ብለው አረፉ። በማፈሪያዎች ዘመን የሚያሳፍር ነገር የለምና ብዙም አያስገርምም።
3/ ቤተ ክርስቲያኒቱ በሥጋዊ ወመንፈሳዊ አገልግሎቷ የሚጠበቅባትን ያህል እየተራመደች እንዳይደለ እርግጥ ነው። በአብዛኛው ውጫዊ ምክንያቶች እንደሆነ ተደርጎ ቢወሰድም፤ ለድክመቷ በዋናነት መነሳት ያለበት ከውስጧ ባለው ጉድለት መሆኑን ማወቅ ተገቢ ነው። ሲኖዶስና የሲኖዶስ የሕግ አመራር የዘመኑን የቤተ ክርስቲያን ሁኔታ የተመለከተ ስለመሆኑ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኒቱ አጠቃላይ የመዋቅር ዝርጋታው፤ አተገባበሩ፤ መመሪያውና ደንቦቿ ሁሉ ችግሮቿን የቃኙ፤ መፍትሄ ማምጣት የሚችሉና የሚያራምዱ አይደሉም። ቃለ ዓዋዲ የተባለው ደንብ በምንም መልኩ የዛሬይቱን ቤተ ክርስቲያን የማስተዳደር አቅም የሌለው ስለመሆኑ በማስረጃ አስደግፎ መናገር ይቻላል። ስለሆነም አጠቃላይ ጥናት ያስፈልጋል ሲባል ይህንን የተመለከተ መሆን ስላለበት ጭምር ነው። አንዱን ጥሎ አንዱን በማንጠልጠል የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን ችግር ለብቻው ለመፍታት በፍጹም አይቻልም። የጳጳሳቱ ስሜትና የማኅበረ ቅዱሳን መንቀዥቀዥ ችግሩን ከማወሳሰብ በስተቀር የችግሩን ሰንኮፍ በፍጹም አይነቅልም።
4/ እስካሁን ያልተነገረለትና ሊነገርም ያልተወደደው የቤተ ክርስቲያኒቱ ችግር መንፈሳዊ ብልጽግናዋን የተመለከተው ክፍል ነው። በእርግጥ የአፄ ዘርዓያዕቆብ ትራፊዎች የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥንታዊነትና ሐዋርያዊ አስተምህሮዋን የበረዘ የብርሃን ወረደልን ደብረ ብርሃናዊ ዜማ በጭራሽ እንዲነካ አይፈልጉም። የአባ እስጢፋኖስና ደቀ መዛሙርቱ የአፍንጫና ጆሮ መቆረጥን ተገቢነት ዛሬም እንደታመነበት እንዲቀጥል ይፈልጋሉ። ቤተ ክርስቲያኒቱ መከራን የተቀበለችበትን የክርስቶስን ወንጌል ወደጎን ገፍተው አለያም ወንጌሉን ጨብጠናል ለማለት ብቻ መሳ መሳ የሚራመዱት ተረት፤ እንቆቅልሽና አልፎ ተርፎም ክህደት ያለባቸው አስተምህሮዎች በጥናቱ ውስጥ በመካተት እርምት ሊወሰድባቸው የሚገባቸውን በቃለ እግዚአብሔር ሚዛንነት የመለየት ስራ ፈጽሞ ሊታለፍ የማይገባው ነው። ዘመናዊው አስተዳደር ያለመንፈሳዊ ልማት በጭራሽ አይታሰብም።
 የሰይጣን መነኮሰ ክህደትና እርምት ሲነገር ለምን ይሄ ተነክቶ በማለት ጸጉራቸው እንደጃርት እሾክ ከሚቆመው መካከል ማኅበረ ቅዱሳን አንዱ ነው። ይህ የተረት አባት የሆነ ማኅበር ነው እንግዲህ ሕግ አርቃቂ የሆነልን። ስለዚህ በወርቅ የቃለ ወንጌል ወራጅና ቋሚ ዐምድ የተተከለችው ቤተ ክርስቲያን በዘመናት ውስጥ ማንም ሳይፈቅድላቸው ገብተው የሸረሪት ድራቸውን ያደሩባት የዘመን እራፊዎች ጸድተው መገኘቷ አገልግሎቷን ምሉዕ፤ ክብሯንም በሚጠሏት ላይ ሳይቀር ከፍ ከፍ እንድትል ያደርጋታል። ደርግም፤ ኢህአዴግም ገፉን እያሉ ማልቀስ መነሻው የቀደመ መንፈሳዊ ክብሯ ስለቀነሰ ካልሆነ ሲያቦኩንና ሲጋግሩን አናይም ነበር።
ስለሆነም ከላይ ባየናቸው አራት ዋና ዋና መግፍኢ ምክንያቶች የተነሳ በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ላይ የቀረበው የማኅበረ ቅዱሳን ጥናት ተብዬ ከፈረሱ ጋሪው የቀደመበት ነው ማለት ይቻላል። በየግል ጋዜጣው የላኩትን ጽሁፍ መልሶ እንደአዲስ ግኝት በዜና መልክ ማቅረብ ወሬ ማብዛት የሚወድ የወፈፌ ስራ እንጂ የቤተ ክርስቲያን ችግር እንደሰጎን እንቁላል አትኩሮ የተመለከተ የመልካም ዘር ተስፈኛ አስተሳሰብ አይደለም። ስለዚህ ይንን ጋሪው ከፈረሱ የቀደመበትን ጥናት በየትም ይምጣ ቀልደኞችን ጥሎ ጋሪው ፈረሱን የሚጎትትበት አግባብ ቶሎ መፍትሄ ይሰጠው።
------------------------------------------------------

Saturday, December 28, 2013

የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የደብር ሃላፊዎችና ሠራተኞች አዲሱን መዋቅር ተቃወሙ


(ደጀብርሃን) ሁሉን ዐቀፍ ጥናት ያልተደረገበትና በአናቱ በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ላይ የለውጥ ሽፋን ሽብልቅ ሆኖ የገባው ማኅበረ ቅዱሳን ካህናቱንና የቤተ ክርስቲያኑን ላዕላይ አመራር ለሁለት እየሰነጠቀ ይገኛል። አባ ሉቃስን፤ አባ እስጢፋኖስንና ሌሎች የማኅበረ ቅዱሳን አገልጋይ ጳጳሳትን የያዘው ማኅበሩ ከጀርባ ሆኖ በቢሮው አርቅቆ ያመጣውንና በቤተ ክህነት መዋቅር ውስጥ የማንነት አሻራውን ለመትከል ታች ላይ እያለ የሚገኝ ሲሆን ቅዱስ ፓትርያርኩ ጉዳዩ እንዲጠናና ሁሉንም አሳታፊ እንዲሆን የነበራቸውን አቋም በማስለወጥ በጓሮ ያቀረበውን «የያብባል ገና» ፕሮጄክት በመደገፍ ላይ እንደሆኑ ውስጥ አዋቂ ምንጮቻችን መረጃውን አድርሰውናል። ሰሞኑን በፓትርያርኩ ቢሮ የከተመው ማኅበሩና አቀንቃኝ ጳጳሳቱ ለውጡን የሚቃወሙት ወገኖች በጣት እንደማይቆጠሩና ለዚያው ሌቦችና ዘራፊዎች ናቸው በማለት በማጠየም ላይ ተጠምዶ ሰንብቷል። ፓትርያርኩ ከዚህ በፊት የነበራቸው ሃሳብ ሁሉን አሳታፊ፤ አጠቃላይ የለውጥ እቅድ እንዲሆንና የቤተ ክርስቲያኒቱ አመራር የሚያወጣውና የሁሉንም ካህናት ሃሳብ ያካተተ ሊሆን እንደሚገባው የነበራቸውን አቋም ትተው ማኅበሩ እየተሯሯጠለት የሚገኘውን እቅድ እንዲደግፉ ሲወተውት ሰንብቶ ፓትርያርኩን የቀደመ ሃሳባቸውን አስጥሎ የራሱን እቅድ እንዳስጨበጠ መረጃችን አክሎ ገልጿል። ጉዳዩ እስከየት ይሄዳል? የሚለውን ወደፊት የምናየው ሆኖ አሁን ባለው ሁኔታ አለቆችን ለብቻ የነጠለ በሚመስል ስልት እየታከከ፤ የካህናቱን የስራ ዋስትና በመንጠቅ የራሱን አዲስ መዋቅር እየተከለ የሚገኘውን እንቅስቃሴ ማኅበረ ካህናቱ በዝምታ የሚያልፈው ከሆነ አሉታዊ ውጤቱ ለቤተ ክርስቲያኒቱም፤ ለሀገርም የሚተርፍ ይሆናል።
ይህንን በመቃወም የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት አስተዳዳሪዎችና ሠራተኞች እያቀረቡ ያለውን አቤቱታ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ዛሬ እንዲህ ዘግቦታል።
ዲግሪ ያላቸው በየአስተዳደሩ እንዲገቡ መደረጉ አግባብ አይደለምበኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት፣ ካለፈው ህዳር ወር ጀምሮ እያካሄደ ያለውን አዲስ የመተዳደሪያ ደንብ የማፅደቅ ሂደት እና መዋቅራዊ ለውጥ አጥብቀው እንደሚቃወሙ የሃገረ ስብከቱ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችና ሠራተኞች ለቅዱስ ፓትሪያርኩና ለጠቅላይ ሚኒስትር /ቤት አስታወቁ፡፡ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለፅ/ቤቶቹ ባስገቡት ደብዳቤ፤ የሃገረ ስብከቱ አዲስ መተዳደሪያ ደንብ ሁሉም የቤተክርስቲያኒቱ ሊቃውንት ሳይሳተፉበት በጥቂት አመራሮች ብቻ የተቀረፀና በውይይት ያልዳበረ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ መተዳደሪያ ደንቡ ከነባሩ ህገ ቤተ ክርስቲያንና ከቃለ-አዋዲ ደንብ ጋር የሚጋጭና የሚጣረስ ነው ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ደንቡ፤ ነባሩን የቤተክርስቲያኒቱን ሠራተኛ በማፈናቀል በምትኩ ስለቤተ ክርስቲያን ትምህርት ምንም እውቀት የሌላቸውን ግለሠቦች በስመ ድግሪና ዲፕሎማ በመሠግሠግ የቤተክርስቲያኗን ሙሉ አስተዳደራዊ መዋቅር ለመቆጣጠር ያለመ ነውሲሉ ተቃውመዋል፡፡

አዲሱን መዋቅር ያዘጋጁት አካላት ማንነታቸው በግልፅ እንደማይታወቅ በደብዳቤያቸው የጠቀሡት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ የቤተክርስቲያኗ የመጨረሻ ስልጣን ያለውን ቅዱስ ፓትርያርክ ስልጣንን በመገደብ፣ ቤተክርስቲያኗ የእነዚህ አካላት ሠለባ እንዳትሆን ስጋት አለን ብለዋል፡፡ የቤተክርስቲያኒቱን ቃለ አዋዲ ያልጠበቀ ነው ያሉትን አዲሱን መተዳደሪያ ደንብ እንደማይቀበሉትም አስተዳዳሪዎቹ ገልፀዋል፡፡ ለቅሬታው መነሻ የሆነው ደንብ፣ ህግ በማርቀቅና በማዘጋጀት ከፍተኛ ልምድና እውቀት ባላቸው ገለልተኛ ምሁራንና የቤተክርስቲያኗ ሊቀ ሊቃውንት እንዲሰናዳ የጠየቁት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ህጉን አርቅቋል የተባለውን ማንነቱ ማህበር ፓትሪያርኩ እንዲያጣሩ ተጠይቀዋል፡፡አዲሱ ደንብ የካህናት ቅነሣ መርሃ ግብርም እንዳካተተ በግልፅ ተረድተናልያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ድርጊቱ መንግስት ስራ አጥን ለመቀነስ የሚያደርገውን ጥረት የሚፃረር ነውሲሉ ያጣላሉት ሲሆን ብዙ ሊቃውንትን ከስራ በማፈናቀል ለችግር እና ለእንግልት የሚዳረግ በመሆኑ ህጉ መፅደቅ እንደሌለበት አሳስበዋል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ የጠየቅናቸው የፓትርያርኩ ልዩ /ቤት ሃላፊ አቶ ታምሩ አበራ የቅሬታ አቅራቢዎቹ ደብዳቤ ወደ /ቤት ሳይገባ በቀጥታ ለፓትርያሪኩ የደረሰ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ ምላሽም ሆነ አስተያየት ለመስጠት እንደሚቸግራቸው ተናግረዋል፡፡ ቅሬታ አለን የሚሉ ወገኖች በተናጥል ከሚቀርቡ፣ ለቤተክርስቲያኗ ይጠቅማል የሚሉትን ኮሚቴ መርጠው ሃሣባቸውን በማደራጀት ቢያቀርቡ እንደሚሻል የጠቆሙት ሃላፊው፤ የእነሡ ሃሣብ ተቀባይነት ባያገኝም እንኳ በውይይት ለመተማመን ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡

በከፊቾ ዞን የጽላት ዝርፊያና ቀበኞቹ "


ባለሃብቶች በእድሳት ስም ቤተ መቅደስ ዘልቀው ጽላት ይቀይራሉ" (የጽሁፍ ምንጭ፤ ጎልጉል የድረ ገጽ ጋዜጣ )
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል በከፊቾ ዞን በጥንታዊ አድባራት ጽላት መዘረፉን እናውቃለን ያሉ ለጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ ገለጹ። የዜናው ምንጮች የዞኑ አገረ ስብከት በዞኑ በሚገኙ አድባራት ላይ ምርመራ እንዲያካሂድ ጠይቀዋል። ዝርፊያውን የሚያካሂዱት “ባለሃብቶች” መቀመጫቸውን አዲስ አበባና ጅማ ከተማ ያደረጉ የክልሉ ተወላጆች መሆናቸውን አስታውቀዋል። ነዋሪነታቸው ቦንጋና ጊምቦ እንደሆነ የሚገልጹት የዜናው ምንጮች “ቀበኞች” በማለት የሚጠሯቸውን የጽላት ዘራፊዎች የዝርፊያ ስልት ተናግረዋል። በመጀመሪያ እድሜ ጠገብ የሆኑትን አድባራት ይለያሉ። በቃፊሮቻቸው አማካይነት መረባቸውን ዘርግተው ሰዎችን ያጠምዳሉ። ህዝበ ክርስቲያን በሚሰበሰብበት ወቅትና ዓመታዊ የበዓላትን ቀን መርጠው በርዳታና በእድሳት ስም ውዳሴ ይቀበላሉ።
በዞኑ የሚገኙት አቢያተ ክርስቲያናት እድሜ ጠገብ በመሆናቸው በርካታ ጥንታዊ ቅርስም እንዳላቸው የሚጠቁሙት ክፍሎች “ያረጁትን አድባራት እናድሳለን በማለት ጥቁር ለምዳቸውን ለብሰው መቅደስ ውስጥ ይዘልቃሉ” በማለት የዝርፊያው ድራማ እንዴት እንደሚከናወን ያስረዳሉ።
ለሃይማኖታቸው የቀኑና የታመኑ የቤተ መቅደስ ጠባቂዎችና አገልጋዮች ሲያጋጥሟቸው መቅደስ ውስጥ ተመላልሰው በሚሰበስቡት መረጃ መሰረት አብረቅራቂ ሃሰተኛ ጽላት በመተካት ዝርፊያ እንደሚካሂዱ፣ ለዝርፊያ የሚመችና ስብናው የወደቀ አገልጋይ ሲያገኙም በግልጽ ያሻቸውን አድርገው ስርቆቱን እንደሚፈጽሙ የዜናው ሰዎች ያስረዳሉ። ድርጊቱ የቆየና ሰዎቹም የሚታወቁ እንደሆኑ የሚጠቁሙት እነዚሁ ክፍሎች፣ “ቀበኞቹ” ካላቸው የገንዘብ አቅም አንጻር እጃቸው ከወቅቱ ጉልበተኞችና የቤተ ክህነት ከፍተኛ አመራሮች ጋርም የጠበቀ ግንኙነት ሊኖራቸው እንደሚችል ከግምት በላይ አመላክተዋል። በዚህ ተነሳ “እንፈራለን፤ ፊት ለፊት ለመግጠምም እንቸገራለን” በማለት ለጎልጉል የአዲስ አበባ ዘጋቢ ምስጢራቸው እንዲጠበቅ አስጠንቅቀው መረጃውን ለመስጠት ችለዋል።
“ይህንን ዜና ጥቅማቸው የሚነካና ችግር ያለባቸው አካላት ዙሪያ ያሉ ጥቅመኞች ሊያስተባብሉት ይችሉ ይሆናል” ሲሉ ዜናው የሚያስደነግጣቸው ክፍሎች የሚወስዱትን የመጀመሪያ ርምጃ ያመላከቱት ተቆርቋሪዎች፣ “የእኛ ጥያቄ ግን ማጣራትና ምርመራ ተደርጎ ውጤቱ ከታወቀ በኋላ እውነታው እንዲረጋገጥ ነው” ብለዋል።
የዞኑ አገረ ስብከት ዛሬ ነገ ሳይል በተቀደሱ የማምለኪያ አድባራት ላይ የተፈጸመውንና እየተፈጸመ ያለውን ዝርፊያ የማጣራት ሃላፊነት እንዳለበት ያሳሰቡት ክፍሎች፣ ቀበኞቹ በርዳታ ስም እድሳት ባካሄዱባቸው አድባራት ላይ የሙከራ ምርመራ ቢደረግ ጥቆማው ምላሽ እንደሚያገኝም በርግጠኛነት ተናግረዋል።
በእድሳትና በርዳታ ስም መቅደስ በመዝለቅ ከሚከናወነው ዝርፊያ በተለየ በድርድር የሚካሄዱም ዝርፊያዎች ስለመኖራቸው ያመለከቱት ክፍሎች “ጉዳዩ እጅግ ጥንቃቄ የሚፈልግ በመሆኑ ስምና ቦታን ለይተን ለመጠቆም እንቸገራለን” ብለዋል። “መልዕክቱ ለቀበኞቹ፣ ለተባባሪዎቻቸውና የሚሰማ ተቆጣጣሪ አካል ካለ ለነሱ ነው” ሲሉም አክለዋል። በዞኑ ያሉ የህዝብ ወኪል እንደራሴዎችም በዚህ ጉዳይ ላይ ጥንቃቄ ወስደው እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
“የቃል ኪዳን ጽላት ዘርፎ ከማነከስና ሰልሎ ከመሞት ውጪ ሌላ ዕድል የለም” ሲሉ ማስጠንቀቂያ ያስተላለፉት ተቆርቋሪ አዛውንቶች በ2005 መገባደጃ ላይ ዋሻ ውስጥ ተገኘ የተባለ ጽላት የት እንደገባ እንደማይታወቅ አመልክተዋል። ዜናው የመገናኛ ሰዎች ዘንድ ሁሉ ደርሶ እንደነበር፣ ነገር ግን በማይታወቅ ሁኔታ ተዳፍኖ መቅረቱ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ አካላትን እስካሁን እንደሚከነክናቸው አመልክተዋል።