Tuesday, November 5, 2013

የኑሮ መድኅን - ምዕራፍ ሁለት የፀሐይ ዕድሜ

የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ --    ረቡዕ ታኅሳስ ፳፬/ ፳፻፭ ዓ/ም
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፤
 አንድ ሰው በጫካ በተከበበና ጭር ባለ መንገድ ብቻውን ሲሄድ ፍርሃት ይይዘውና «ጌታ ሆይ» ብሎ ይጮኻል፡፡ «ጌታ ሆይ እንደምታየኝ ጫካ ውስጥ ነኝ፡፡ መንገዱም ጭር ያለ ነው፡፡ ብቻዬን ነኝና ፈራሁ፣ እባክህ ድረስልኝ» ሲል ይጮኻል፡፡ ትንሽ እንደ ቆየ ብቻውን በሚሄድበት መንገድ የሁለት ሰው ጥላ ያያል፡፡ ያን ጊዜም ደንግጦ እንደ ገና ወደ እግዚአብሔር «ጌታ ሆይ ፍርሃቴ ጨመረ ብቻዬን እየሄድኩ የሚታየኝ የሁለት ሰው ጥላ ነው፡፡ ነገሩ ምንድነው?» ሲል ጮኸ፡፡ እግዚአብሔርም፡- «አይዞህ ልጄ ብቻህን አይደለህም፣ የምታየው ሁለተኛ ጥላ የእኔ ነው፡፡ እኔ አብሬህ ነኝና አትፍራ» አለው፡፡ በዚያን ጊዜ ሰውዬው ደስ ብሎት ያለ አሳብ ጉዞውን ቀጠለ፡፡ ተጉዞ ተጉዞ ረግረጋማና ዳገታማ ስፍራ ላይ ሲደርስ ዞር ብሎ ቢያይ ጥላው ከአጠገቡ የለም፡፡ ይህን ጊዜ ፍርሃት ያዘውና «ጌታ ሆይ» ይል ጀመረ፡፡ «ጌታ ሆይ ቅድም በተደላደለው መንገድ ስሄድ አንተ ከጎን ጎኔ ትሄድ ነበር፡፡ አሁን ግን እንዲህ ባለ ለጉዞ በማይመች የአንተ እርዳታ እጅጉን በሚያስፈልገኝ ረግረጋማና ዳገታማ ቦታ ላይ ስደርስ ግን ጥለኸኝ ሄድክ፡፡ ጌታ ሆይ ምን አጥፍቼ ነው ይህ የተደረገብኝ?» ሲል ጮኸ፡፡ እግዚአብሔርም «በዝግታ አይዞህ ልጄ የቅድሙ መንገድ የተመቻቸ ስለነበር አብሬህ እንዳለሁ እንዲሰማህ ብቻ ጎን ጎንህ እሄድ ነበር፡፡ የአሁኑ መንገድ ግን ለጉዞ የማይመች አስቸጋሪ መንገድ ስለሆነ ጥላዬ የጠፋብህ አዝዬህ ነውና አይዞህ፡፡ የምታየው የእኔን ጥላ ነውና በርታ» አለው፡፡
እግዚአብሔር አብሮን የሚሆነው እኛ ግድ ስላልነው ሳይሆን ፍቅር ስለሆነ ነው፡፡ በአስቸጋሪ ስፍራም አይለየንም፡፡ ሲደክመንም ጥሎን አይሄድም፣ ይልቁንም ይሸከመናል እንጂ፡፡ የአሕዛብ ጣዖታት ሰዎች የሚሸከሟቸው ናቸው፡፡ የሚያምኗቸውን ግን የሚሸከሙ አይደሉም፡፡ የእኛ ጌታ  እግዚአብሔር ግን የሚሸከመን አምላክ ነው፡ ፡ 
የአገራችን መምህራን የሰውን ዕድሜ በፀሐይ ይመስሉታል፡፡ ፀሐይ በማለዳ ስትወጣ ድካምና ፍርሃት ተወግዶ ሁሉም ሰው አዲስ በሚላት ቀን ተግባሩን ሊጀምርባት ይነሣል፡፡ የጠዋት ፀሐይ ተናፋቂና ተወዳጅ ናት፡፡ ሌሊቱን ሲፋንኑ ያደሩ አራዊትና ሌቦች ወደ ጎሬአቸው ሲገቡ የብርሃን ልጆች ግን ይወጡባታል፡፡ ይህችን የማለዳ ፀሐይ ዱካ ያለው ዱካውን ይዞ የሌለውም በድንጋይ ላይ ተቀምጦ ይሞቃታል፡፡ በቤት ውስጥ የሚሸፋፈኑ አራስ ሕፃናትም በእናታቸው ጉልበት ላይ ሆነው ራቁታቸውን ይሞቋታል፡፡ 
ሰው ሁሉ ተጠራርቶ የሞቃት ያች የጠዋት ፀሐይ ቀትር ላይ ሁሉም ሰው ይሸሻታል፣ ይጠላታል፣ ይመረርባታል፣ በትንሽ ጥላ እንኳን ሊደበቃት ይሞክራል፡፡ ተጠራርቶ እንዳልሞቃት ምን ዓይነት ቍጣ ነው? ይላታል፡፡ ፀሐዩ እስኪበርድም ከቤት አትውጡ ይባላል፡፡ የጠዋቱ አድናቆትና ምስጋና ቀርቶ ምሬት ይተካል፡፡
ቀትር ላይ ሁሉም ሰው የተመረረባት ፀሐይ ሠርክ ላይ ልትጠልቅ ስትል ሁሉም ሰው ይሳሳታል፡፡ ጨርሳ ሳትጠልቅ ይሯሯጥባታል፣ ወደ የቤቱ ይሰበሰብባታል፣ ጥበበኞችም በባሕር ዳርቻ ላይ ከውኃው ጋር የምትሰጠውን ውበት ለማስቀረት ፎቶ ግራፋቸውን አስተካክለው ይጠብቋታል፡፡  ጠዋት ላይ ጨለማን ወደ ፊት እየገፋች የወጣችው ፀሐይ ሠርክ ላይ ጨለማውን ወደ ኋላዋ አድርጋ ትጠልቃለች፡፡ እግዚአብሔር ፀሐይን በውበት አውጥቶ በውበት ያስገባታል፡፡ 
አንዷ ፀሐይ ጠዋት ላይ ሁሉም ሰው የሚሻማት፣ ቀትር ላይ የሚሸሻት ሠርክ ላይ የሚሳሳላት ናት፡፡ ለአንዲቱ ፀሐይ ያለንን ተለዋዋጭ ስሜት ግን አስተውለነው አናውቅም፡፡ የሰው ዕድሜም በፀሐይ ይመሰላል፡፡ ፀሐይ በቀን ውስጥ ሦስት ዓይነት ስሜት ትፈጥራለች፡፡ ሕይወትም እንዲሁ ናት፡፡
ፀሐይ በምሥራቅ ስትወጣ ሁሉም ሰው በናፍቆት እንደሚቀበላት፣ ተጠራርቶ እንደሚሞቃት ሕይወትም ገና በጅምሯ ጣፋጭና የማትጠገብ ናት፡፡ ሕጻን ሲወለድ ሁሉም ሰው ተጠራርቶ ይቀበለዋል፣ ሴቶች በእልልታ ወንዶች በጥይት ተኩስ ደስታቸውን ይገልጣሉ፡፡ ያ ልጅም ሮጦ አይደክምም፣ ዘሎ አይጠግብም፡፡ «ሁሉም ነገር በጠዋቱ ቀዝቃዛ ነው» እንደሚባለው የሕይወት ትግሉም ለእርሱ ቀላል ነው፡፡
አዋቂዎች ስለ ብርቱ ችግር ሲያወሩ ሕጻኑ ግን ስላማረው ምግብና መጫወቻ ያወራል፡፡ የእንግሊዝዋ ንግሥት ልጅ ሰው ተራበ የሚል ወሬ ብትሰማ አይስክሬም አይበሉም ወይ? ቢጠፋ ቢጠፋ አይስክሬም ይጠፋል ወይ? አለች እንደሚባለው ሕፃኑም ልክ እንደዚህች ልዕልት ነው፡፡ አዋቂዎች ሲያለቅሱ ልጆች ግር ይላቸዋል፡፡ ሕይወት ታስለቅሳለች ብለው ማመን በፍጹም አይሆንላቸውም፡፡ 
ያቺ ተናፋቂ የጠዋት ፀሐይ ቀትር ላይ እንደምታስመርር ሕይወትም ልጅነቱን ለፈጸመውና ለራሱ ማሰብ ለጀመረው ወጣት እንግዳና አስፈሪ ናት፡፡ ለራሱ ምንም ባያደርግ እንኳ ለራሱ ማሰብ ብቻውን ወጣቱን ያደክመዋል፡፡ ወጣቱ ጭምብሉን ሲያወልቅ፣ ዓለምን ብቻውን ሲያያት፣ ሁሉም ነገር ሲለዋወጥበት ግር ይለዋል፡፡ ሲወለድ ወንድ ተወለደ ተብሎ የተደሰቱ ሰዎች አሁን እነዚህን ጎረምሶች ይንቀልልን ሲሉ ይደነግጣል፡፡ ሲስሙት የኖሩት አሁን ችላ ይሉታል፡፡ መንገድ ሲጠፋበት ከመምራት ያዋክቡታል፡፡ መንግሥትም ወጣቱ ኃይል ነው ብሎ ስለሚሰጋ ሠራዊት ያደራጅበታል፡፡ ሲወድቅ ጎበዝ ይባል የነበረው ሕፃን አሁን ትንሽ ሲሳሳት ፖሊስ ይጠራበታል፡፡ እደግ ተብሎ የተመረቀው ሲያድግ ይረገማል፡፡ በዚህና በሌሎች የሕይወት ትግል እንዴት እኖራለሁ? የሚለው ጥያቄ ያስጨንቀዋል፡፡  
ቀትሩ ፀሐይ በአናት ላይ የምትወጣበት ሰዓት ስለሆነ ከባድ ሰዓት ነው፡፡ ሕይወትም በወጣቱ ላይ ብርቱ የምትሆንበት ቀትር አላት፡፡ እስከ ዕድሜ ልክ የሚዘልቁ ሱሶችና ስህተቶች የሚጀመሩት በዚህ በወጣትነት ዘመን ነው፡፡ በወጣትነት የተፈጸሙ ስህተቶችና የማይገቡ ምርጫዎች እስከ ዕድሜ ልክ የማይስተካከሉበት ጊዜ ብዙ ነውና ወጣቱ ማስተዋል ይገባዋል፡፡ ሕይወትን ከትዕግሥት በቍጣ፣ ከትሕትና በትዕቢት ለመምራት መሞከር ለቀጣዩ መንገድ መሰናክል ማስቀመጥ ነው፡፡ የአሁን መሳካት የሁልጊዜ መሳካት፣ የአሁን አለመሳካት የሁልጊዜ አለመሳካት አለመሆኑን ወጣቱ ሊያስተውል ይገባዋል፡፡ ዕድል እግዚአብሔር፣ መከራም የጥራት መገኛ መሆኑን ወጣቱ ሊያስተውል ሲገባው መልካም ዕድልም የሚሰጥ ሳይሆን የሚመረጥ መሆኑን መገንዘብ አለበት፡፡ 
የሌለውን እንዳለው አድርጎ የሚያስብ ጉረኝነት የቀትሩ አጉል አመል ነው፡፡ ቀትርን ሁሉም እንደሚሸሸው ወጣቱም ሕይወትን ለመደበቅ ይሞክራል፡፡ ሕይወትን ግን ስንጋፈጣት እንጂ ስንሸሻት አትሸነፍም፡፡ ቀትሩን በትንሽ ጥላ ለመጋረድ እንደሚሞክር የሕይወት ጥያቄ ሲበዛም በሱስ፣ በቁማርና በኃጢአት ውስጥ ለመደበቅ ቀትር ላይ የደረሰው ሰው ይጥራል፡፡ በእርግጥ የወጣትነት ክፉ ባሕርያት ከባልንጀራም እንደሚወረሱ አንዘነጋም፡፡ ወጣቱ ወደዚህ ዓለም ሲመጣ መጀመሪያ የተቀበሉትን ቤተሰቤ ብሎ እንደ ኖረ ከቤቱ ሲወጣም በሰፊው ዓለም መጀመሪያ የተቀበሉትን ቤተሰብ ያደርጋል፡፡ ሕይወት ቀትር የሆነችበት ሰው በቶሎ ተስፋ በመቍረጥ ሞቱን ይመኛል፡፡ ወላጆቹ የእርሱንና የራሳቸውን ደግሞም የቤተሰቡን ሕይወት ተሸክመው ሳለ መኖር የእርሱን ያህል አልከበዳቸውም፡፡ እርሱ ግን በአሳብ ጭነት ለምን እንደሚንገዳገድ አያስተውልም፡፡ 
ያች ተናፋቂ የጠዋት ፀሐይ ቀትር ላይ እንዳስመረረች ልትጠልቅ ስትል ደግሞ ታሳሳለች፡፡ ለዚህ ነው ወጣቱ ሞትን ሲመኝ የታመሙትና ሽማግሌዎች ግን ዕድሜን ይለምናሉ፡፡ በሕይወት ሠርክ ላይ ኑሮን ኖርኩበት ወይስ ኖረብኝ ብለን ሂሳብ እንተሳሰባለን፡፡ ይህ የፈቃዳችን ጉዳይ ሳይሆን ግድ ነው፡፡ ማድረግ በማንችልበት ጊዜ ከማዘን እግዚአብሔር ይጠብቀን፤ ቢሆንም ለንስሓ እስካለን ጊዜ አያልፍምና ንስሓ መግባት ይገባናል፡፡ ንስሓ ከምግባራት ሁሉ ትበልጣለች፡፡ ፀሐይ ስትወጣ ጨለማን ወደ ፊቷ እየገፋች ሲሆን ስትጠልቅ ግን ጨለማን በስተኋላዋ አድርጋ ነው፡፡ ይህን ዓለም ለቀን ስንሄድም ከክርስቶስ ጋር ከሆንን ጨለማው ከኋላችን ነው፡፡ የዚህ ዓለም መከራና ድካም አይከተለንም፡፡ ሕፃኑ ሲወለድ ዙሪያውን የከበቡ ሰዎች እልል ይላሉ፡፡ እርሱ ግን በተፈጥሮው ወደዚህች አድካሚ ዓለም መምጣቱን እያወቀ ያለቅሳል፡፡ ይህን ዓለም ተሰናብቶ ሲሄድም ዘመድ አዝማዶቹ ያለቅሳሉ፡፡ እርሱ ግን ወደ ዕረፍቱ ይሄዳልና ዝም ይላል፡፡ የቆሙት ሰዎች ግን አያስተውሉም፡፡ 
እግዚአብሔር ፀሐይን በውበት አውጥቶ በውበት ያጠልቃታል፡፡ ዕድሜም በሕፃንነትና በሽምግልና ውበት ይልቁንም በጨዋነት እንድትፈጸም የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፡፡ ዘመንህ በውበት እንዲፈጸም በሕፃንነትህ ሽማግሌ አክባሪ፣ በወጣትነትህ ታታሪ ሠራተኛ፣ በሽምግልናህ አስታራቂ ከሁሉ በላይ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታህና መድኃኒትህ የሆነልህ ሰው ሁን፡፡ ምንም ኑሮ ቢከብድብህ ሞትን አትለምን፡፡ ወጣቱ ወደ አንድ አባት ዘንድ ሄዶ «አባቴ መሞት እፈልጋሁ» አላቸው፡፡ እርሳቸውም ዘና ብለው «ሞትን ባትፈልገውም ወዳንተ ይመጣል፤ ካልፈለግሃቸው ግን ወዳንተ የማይመጡ ብዙ መልካም ነገሮች አሉና ለምን እነርሱን አትፈልግም?» ብለውታል፡፡ 
ከኮሚኒስት ርእዮተ ዓለም ወዲህ የብዙ የዓለማችን ወጣቶች ሕይወት ተዘርቶ ያልተሰበሰበ ፍሬ ሆኗል፡፡ ተስፋ የቆረጠ፣ ሞራሉ የወደቀ፣ በቦምብ ኳስ የሚጫወት ትውልድን ያተረፍነው ዓለም እግዚአብሔር የለም ብላ ካወጀች ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ እግዚአብሔር ከሌለ መልካም ሥራ ዋጋ፣ ክፉ ሥራም ቅጣት ሊኖረው እንዴት ይችላል? ስለዚህ ዓለምን ባለቤት የሌላት ቤት ስናደርጋት የዛሬውን የትውልድ መዝረክረክ አተረፍን፡፡ ኮሚኒዝም ከአደባባይ ቢወድቅም ገና የአደባባይ ንስሓ ስላልገባንበት ከሰው ልብ አልወደቀም፡፡ በአዋጅ ክደን በተናጥል ነው ንስሓ የገባነው፡፡ ወጣቱ ትውልድ ወደ እግዚአብሔር ቤት ሲመጣ ብናይም ውስጡ ግን በዚህ ክፉ ሥርዓት ተገዝቷል፡፡ አሁን ያሉት ትልልቅ ሰዎችና የወደፊት ሽማግሌዎችም እግዚአብሔር የለሾች መሆናቸው አይቀርምና ልናስብበት ይገባል፡፡
በአንድ ቀን ውስጥ ሁለት ወጣቶችን ሳማክር በተለያየ ሰዓት ቢመጡም የጠየቁኝ ጥያቄ አንድ ዓይነት ነበር፡- «ይህን ወጣትነቴን ምን ላድርገው? ይህን ዕድሜዬን ምን ላድርገው?» ስሰማቸው ልቤ ቢያዝንላቸውም ነጻ የሚያወጣቸው ክርስቶስ ግን እንደ ተሰቀለ ሆኖ ይታየኝ ስለነበር ደስ አለኝ፡፡ አሁን እነዚህ ወጣቶች ወጣት ለዘፈን፣ ወጣት ለዝሙት የሚለውን መመሪያ ጥለው ወጣት ለክርስቶስ መሆኑ ገብቷቸው ተጽናንተዋል፡፡ ለዛሬ ወጣቶች እግዚአብሔር ለእነርሱ ያለውን ዓላማ ልንነግራቸው ይገባል፡፡ ትዕግሥት የለሾችና በቶሎ ተስፋ የሚቆርጡ ናቸውና፡፡ ፍቅር የተሞላን ሆነን ልንቀርባቸው ይገባል፡፡ በዕድሜ የቀደምን ሰዎች ለእነዚህ ግራና ቀኛቸውን ለማያውቁ ወጣቶች ዕዳ አለብን፡፡ ቤተ ክርስቲያን መማፀኛ ልትሆናቸው ትምህርት ቤቶችም የግብረ ገብ መማሪያቸው ሊሆኑአቸው ያስፈልጋል፡፡ ሕይወት የማይኖር የመሰለህ አንተ ወጣት ወደ ጎዳና ውጣና አረጋውያንን ተመልከት፡፡ ለዚህ የደረሱት በአንተ መንገድ አልፈው ነው፡፡ ሽበታቸው በአንድ ትልቅ ጦር ሜዳ ላይ አሸንፈው የተቀዳጁት ዘውድ መሆኑን ይመሰክራል፡፡ ሽበታቸው ራሱ ደካማነትህን ይነቅፈዋል፡፡ ከሁሉ በላይ መጽሐፍ ቅዱስህን ገልጠህ በእምነትና በጸሎት አንብበው፡፡ እርሱ የመንገድህ ካርታ  /መሪህ/ ነው፡፡  
የፀሐይ ዕድሜ አጭር ነው፡፡ አንድ ቀን እንኳ አይሞላም፡፡ ከመሐልም ጭጋግና ደመና ይጋርዳታል፡፡ ነገር ግን ሃያ አራት ሰዓት እንኳ በማይሞላው የፀሐይ ዕድሜ ብዙ ስሜቶች ይፈራረቃሉ፡፡ ቢሆንም አጭር ነው፡፡ ሰውም በምድራዊ ኑሮው ብዙ ነገሮችን ቢያይም የዚህ ዓለም ቆይታው ግን በጣም ትንሽ ነውና መጨነቅ የለበትም፡፡ ሰባና ሰማንያ ዓመት ማለት ትንሽ ቆይታ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ሺህ ዓመት እንደ አንድ ቀን ነው ይላል 2ጴጥ.3፡8፡፡ ሺህ ዓመት እንደ አንድ ቀን ከሆነ አምስት መቶ ዓመት እንደ 12 ሰዓት ነው፡፡ ሁለት መቶ ሃምሳ ዓመት ደግሞ እንደ 6 ሰዓት ነው፡፡ 125 ዓመት ደግሞ እንደ ሦስት ሰዓት ነው፡፡ 62 ዓመት ደግሞ እንደ አንድ ሰዓት ተኩል ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሰማንያ ዓመት ብንኖር እንኳ በዚህ ዓለም ላይ የምናሳልፈው ዕድሜ በእግዚአብሔር አቆጣጠር ሁለት ሰዓት እንኳ የማይሞላ ነው፡፡ ይህ አንድ አውሮፕላን በአንድ አገር ላይ ነዳጅ ለመቅዳት አርፎ ለመነሣት የሚፈጅበት ሰዓት ነው፡፡ በጣም አጭር ነው፡፡ ሰው በዚህ ዓለም ላይ የሚያሳልፈው ዕድሜ ከዘላለም አንጻር ቢሰላ አንድ ቀን እንኳ አይሞላም፡፡ ከዘላለም አንጻር ቆይታችን ንሥር ሥጋ አይቶ እስኪያነሣ ያለውን ጊዜ የሚያህል ቅጽበታዊ ነው፡፡ ስለዚህ በጣም መጨነቅና ማዘን አይገባንም፡፡
የጽሞና ጊዜ
እግዚአብሔር አይተውህም፣ አይጥልህም፡፡ እንደማይተውህ ቃል ገብቶልሃል ዕብ.13፡5፤ኢያ.1፡5፡፡ እግዚአብሔር ቃል የገባልህ ተገዶ ሳይሆን በፈቃዱ ነውና ለመፈጸም አይፈተንም፡፡ ስለዚህ አሁን ለራስህ ንገረው፡- ጌታዬ አይጥለኝም፣ ፍጹም አይተወኝም፡፡ ደግመህ ለራስህ ንገረው፡፡ አሁን የገጠመህ ሰዎች ከዚህ በፊት የገጠማቸው ነው፡፡ አሁን የደረሰብህ ብዙ ትውልዶች ያለፉበት ነው፡፡ አዲስ ነገር የለም፡፡ አዲስ ነገር የገጠመህ መስሎህ አትደነቅ፡፡ ጉልበት የሚጨርስ መደነቅ ነው፡፡ በእግዚአብሔርና በሥራው ብቻ ተደነቅ፡፡ ደግሞም፡-
- የሚሸከም አምላክ እንዳለህ፣
- ከቀትሩ በኋላ ሠርክ እንደሚመጣ፣
- ሕይወትህ በውበት ወጥታ በውበት እንድትጠልቅ፣
- ከምንም በላይ የሚያስፈልግህ እግዚአብሔር መሆኑን፣ 
- ዘመንህ አጭር ቢሆንም ዘላለማዊ ውሳኔ የምትወስንበት መሆኑን አስብ፡፡
ጸሎት
ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ የዘመኔ ጌታ መሆንህን አምናለሁ፡፡ የሸረሪት ድር ተደግፌ ብዙ ጊዜ ተበጥሶብኛል፡፡ በራሴና በእውቀቴ መመካትም አልጠቀመኝም፡፡ ከሞት የማያድነውን እውቀት ጠልቼዋለሁ፡፡ ዛሬም ልትሠራኝ እንደቆምክ አይሃለሁ፡፡ አንተን መፍራት ስለተሳነኝ ኑሮና ሰዎች ያስፈሩኛል፡፡ ያረፍኩበትን ጊዜ አላውቀውም፡፡ አንዱ ጭንቀት ለአንደኛው መሬት ላይ ሳላርፍ ይሰጠኛል፡፡ ሰላም ይህና እንዲያ ሲሆን እንደማይገኝ ገብቶኛልና እንዲሁ አሳርፈኝ፡፡ መታገሥ እያቃተኝ ገበታ ስገለብጥ፣ የተሻገርኩበትን ድልድይ ስሰብር ኖሬአለሁና አሁንስ አሰልጥነኝ፡፡ ተስፋ መቍረጤን ሳልጨርሰው ቅደመኝ፡፡ በሚያስጠልለው ስምህ በኢየሱስ ክርስቶስ አሜን፡፡ 
የኑሮ መድኅን - ለሰባተኛ ጊዜ የታተመ
በዲ/ን አሸናፊ መኰንን
የመጀመሪያ እትም መጋቢት 2000 ዓ/ም
አድራሻ፡ 0911 39 3521/0911 67 8251
 መ.ሳ.ቁ.  62552

Friday, November 1, 2013

አባ እስጢፋኖስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ላይ እየፈጸሙ ያለው ሙስናና እየነፈጉ ያለው ፍትሕ ብዙዎችን እያማረረ ነው!


 
ከመግቢያችን ለጥቆ ያለው ርዕሱን ገላጭ የሆነው ጽሁፍ የተገኘው ከአባ ሰላማ ብሎግ ነው።

(እንደመግቢያ፤ ከደጀብርሃን)

ቅድሚያ ይድረስ ለፓትርያርክ ማትያስ!!

 ብዙ ጊዜ አስነዋሪ ገመና የተሸከሙ ሰዎች ገመናቸውን በንስሐ ማጠብ እርም ሆኖባቸው መቆየቱ ሳያንስ  ገመናቸውን ተሸክመው አርፈው እንደመቀመጥ ወደአደባባይ ይወጡና ጭራሹኑ የገመናቸውን መጠን ሲያሳድጉ ይታያሉ። አደባባይ ያወቀውን ገመና ተሸክመው ይኖሩ የነበሩትና ተሸፍኖላቸው እንደትልቅ ሰው የጅማ መሪ የሆኑት አባ እስጢፋኖስ የገመናውን ደረጃ ወዳሳደጉበት አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ተመልሰው ሲመጡ «ድመት መንኩሳ አመሏን ላትረሳ» ያሉ ብዙዎች ነበሩ። በእርግጥም እስከመቃብር አብሯቸው የሚዘልቀው ገመና ከሥጋ አልፎ አጥንታቸው ላይ የተጣበቀው አባ እስጢፋኖስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን ከማኅበረ ቅዱሳን ነፍሰ በላዎች ጋር በመተጋገዝ እያጠቡት ይገኛሉ።   ማንም ሳይነካቸውና ገመናቸው ከሰፈር ወሬ ባለፈ የተናገረ ማንም ሳይኖር በራሳቸው ጊዜ  ገመናዬን አደባባይ አውጡልኝ፤ በሚዲያም ተናገሩልኝ ሲሉ በሥራቸው አላፊ አግዳሚውን ተጣሩ፤ እያፈናቀሉና ወሮ በላውን እያሳደጉ የማን ወዳጅ መሆናቸውን በተግባር አሳዩ።   አለመታደል ሆኖ እንጂ ሊቀ ጳጳሱ መልካም አስተዳደርና ሙስናን ተከላክለው ቢሆኑ ኖሮ ገመናቸውን በማውጣት ማንም ድካማቸውን ለመተረክ ጊዜውን ባላጠፋ ነበር። ይሁን እንጂ «ያዳቆነ ሰይጣን » እንዲሉ ክፉ ተግባራቸውን ለመተው መቼም ቢሆን ያልታደሉት የጥፋት ሰው አባ እስጢፋኖስ ደሃውን አስለቀሱ፤ ከስራ አፈናቀሉ፤ በአየር ላይ አንሳፈው ለረሃብና ለመከራ አጋልጠው ሰጡ፤ የሚሸጡትን ሰው ሸጡ፤ የሚገድሉትንም በደብዳቤ እንዳይነሳ አድርገው ጣሉ።  ከዚህ ሁሉ የከፋውና የሚያሳዝነው ደግሞ ፓትርያርክ ማትያስም ለዚህ ወንጀልና ለመጥፎ ድርጊት ተባባሪ ሆነው መገኘታቸው ነው።                                  
ዋናው ምክንያት ፓትርያርክ ማትያስን ላስመረጡበት ውለታ አዲስ አበባ ሀ/ስብከት የተበረከተ ክፍያ ሲሆን በሌላ መልኩም «ግም ለግም አብረህ አዝግም»  የሚለው የብሂል ገመድ እየሳበ ፓትርያርኩን ስላስቸገረ ነው።  አባ ማትያስ ከፓትርያርክነታቸው በፊት የጵጵስና ዘመናቸውን የሚያጋልጥ ከወራት በፊት በእጃችን ላይ የደረሰው አስደማሚ መረጃ ቢኖርም አደባባይ ላይ ማውጣት ያልፈለግነው ለቤተ ክርስቲያኒቱ ክብር ነበር። ቤተክርስቲያኒቱን አክብረው ማስከበር ሲገባቸው ቤተ ክርስቲያኒቱን ለችግርና ለሰቆቃ አጋልጠው ለሚሰጡ አባ እስጢፋኖስን ለመሰሉ የዘመኑ የቤተ ክርስቲያኒቱ እርግማን ለሆኑ ሰዎች ጥላና ከለላ መሆናቸው  ግምት ውስጥ የሚያስገባቸው ብቻ ሳይሆን የኔንም እንደውዴ አባ እስጢፋኖስ አደባባይ አውጡልኝ እያሉ በሰጡት የዐመጻ ድጋፍ አርፎ የተቀመጠውን ፋይል እየቀሰቀሱት መሆኑን ሊያውቁት ይገባል። ከዚያም በተረፈ የነማን ወዳጅ ምን ይመስላል? ለሚለው የሰዎች የጥያቄ እንቆቅልሽ መልስ እንዲያገኝ በር እየከፈቱ መሆንዎን ለፓትርያክነትዎ እንናገራለን። በዚህ ዘመን የተከደነ የማይገለጥ እንደሌለም ይወቁ። የአባ እስጢፋኖስ የገመና ሰማዕት መሆን ከፈለጉ ምርጫው የእርስዎ ብቻ ነው። እኛም ለእንደዚህ ዓይነት ሰዎች የሚኖረን ትዕግስት እስከመቼ ነው? አርፈው እንዲቀመጡ ሊነገራቸው ይገባል? ወይስ እነሱ የዐመጻቸውን ቆሻሻ ሲደፉብን ዝም ብለን እንሸከም? ብለን ራሳችንን እንጠይቃለን።
  በመጨረሻም ለፓትርያርክ ማትያስ የምናቀርበው ልመናና ተማጽኖ ሀገረ ስብከቱን እያወኩ የሚገኙት ሊቀ ጳጳስ ተብዬ ሰው ከቦታው ያንሱልን!!  ጳጳሱ ለዋሉት ውለታቸው ቤተ ክርስቲያንን በመሸጥ ሳይሆን  አሜሪካ ከሚከፈልዎ የመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ደመወዝዎ ላይ ቀንሰው በዶላር ይስጡ። ያለምንም ማስፈራራት ቀጣዩ የአደባባይ ገመና የእርስዎ ይሆናል። ከዚያ በኋላ የትም ሄደው ቢደሰኩሩ እመራዋለሁ ከሚሉት ሕዝብ ፊት የሚታየው እርስዎ ያልተጸየፉትና ተከድኖ ሳይገለጥ የቆየው ገመናዎ ለአባ እስጢፋኖስ የቀረበ መስዋዕት ይሆንልዎታል።  ኃጢአትን የተለማመደ ሰው ይህ ምንም ስሜት ባይሰጠውም፤ ኃጢአታቸውን ለመሸፈን ሲሉ መልካም ለመሥራት ቃል ያልገቡ መሪዎች ሁሉ የሚከተላቸው የኃጢአታቸው ደብዳቤ መሆኑን ስለምንረዳ በመጨረሻው ዘመን የመንፈሳዊ ሰዎች መታጣት ስለሚታወቅ ብዙም አያስገርመንም።
                                                                  
«የአንዳንዶች ሰዎች ኃጢአት የተገለጠ ነው ፍርድንም ያመለክታል፥ ሌሎችን ግን ይከተላቸዋል» 1ኛ ጢሞ 5፤24

የአባ ሰላማ ብሎግ የአባ እስጢፋኖስን ተግባር ያጋለጠበት ጽሁፍ ይህንን ይመስላል።
አባ ገብረ ሚካኤል ለጵጵስና ሲታጩ የዑራኤል አስተዳዳሪ የነበሩት አባ ላእከ የተባሉ አባት ለአቡነ ጳውሎስ “ምነው አባታችን የምናውቃቸውን አባ ገብረ ሚካኤልን ልንድራቸው ሲገባ እንዴት ያጰጵሳሉ? እነዚህ በሚመሯት ቤተክርስቲያን ውስጥ በኀላፊነት መሥራት አልፈልግም” ብለው “ኢታርእየኒ ሙስናሃ ለኢየሩሳሌም” ወይም “የኢየሩሳሌምን ጥፋቷን አታሳየን” እንዳለው ነቢይ የኦርቶዶክስን ጥፋት ላለማየት በመወሰን ወደ መርጡለማርያም ገዳም እንደገቡ ይነገራል፡፡ መልአከ ገነት አባ ኀይለ ማርያም የተባሉ አራዳ ጊዮርጊስ አለቃ የነበሩ አባትም በጊዜው በጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን የነበረውን ገንዘብ ለመዝረፍ ታስቦ እርሳቸው ለጵጵስና ሲታጩ (ከእነአባ ገብረሚካኤል ጋር)፣ “ወቅብዐ ኃጥኣንሰ ኢይትቀባዕ ርእስየ” እና “ወኢይደመር ውስተ ማኅበሮሙ ለእኩያን” የሚሉትን የቅዱሳት መጻሕፍት ቃል በመጥቀስ የሚያስተዳድሩትን ደብር ለቀው ገዳም ሊገቡ ሲሉ በፓትርያርኩ ተለምነው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሆነው ነበር፡፡ ነገር ግን የአባ ገብረሚካኤል የድራፍት ቡድን አላላውስ አላንቀሳቅስ ስላላቸው የሚወዷትን አገራቸውንና ቤተክርስቲያናቸውን ጥለው በመሰደድ በብስጭትና በንዴት በስደት አገር ሳሉ ዐርፈዋል፡፡ እነዚህ አባቶች ያኔ የተናገሩት ቢሰማና አባ ገብረሚካኤል ወደ ጵጵስና ሳይሆን ወደ ትዳር እንዲገቡ ቢደረግ ኖሮ ዛሬ በእርሳቸው እየደረሰ ያለው ጥፋት በቤተክርስቲያን ላይ ባልደረሰ ነበር የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም፡፡

በአባ ገብረሚካኤል እጩነት ላይ አባ ላእከ እና መልአከ ገነት አባ ኃይለ ማርያም ያቀረቡት ቅሬታ ሰሚ ሳያገኝ እነርሱ ወደገዳምና ስደት በኋላም ወደሞት፣ አባ ገብረ ሚካኤልም “አባ እስጢፋኖስ” ተብለው ወደ ጵጵስና መጡ፡፡ አባ እስጢፋኖስን “አባ” ከማለት ይልቅ “አቶ” ማለት ይቀላል ይላሉ የሚያውቋቸው፡፡ በቆብ ውስጥ ትዳር ከመሰረቱና ባለትዳር መሆናቸው ከሚነገርላቸው ጳጳሳት መካከል አባ እስጢፋኖስ አንዱ ሲሆኑ የቆብ ውስጥ ትዳር በመመስረታቸው ብዙዎች የእሳቸው ይሻላል ቢሉም፣ ብዙ ውሽሞች ያሏቸው መሆናቸው እየተጋለጠ ሲመጣ ግን “እኛስ በአንድ በመወሰናቸው ደስ ብሎን ነበር ግን ምን ያደርጋል …” ወደማለት መጥተዋል፡፡
አባ እስጢፋኖስ ሊቀጳጳስነት እንደ ተሾሙ ከሌሎቹ ጳጳሳት ጋር አባ ጳውሎስ አክሱም ይዘዋቸው ሄደው የነበረ ሲሆን፣ ሌሎቹ ጳጳሳት ወደ ጽላት ቤት ይዘዋቸው ሲገቡ ለዚህ ጉዳይ እንጅግ የሚጠነቀቁት አክሱማውያን ካህናት ከጳጳሳቱ መካከል አባ አስጢፋኖስን የጽላት ቤቱን ያረክሱብናል በሚል “አሥመራ የወለድካቸውን ልጆች አሳድግ እንጂ አንተ እዚህ አትገባም” ብለው አግደዋቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ሊቄ ብርሃኑ “ሊቀጳጳስ  ናቸው እኮ” ብለው ሊከራከሩላቸው ቢሞክሩም ካህናቱ በአቋማቸው ጸንተው እንዳይገቡ አግደዋቸው ከደጅ ተመልሰዋል። ቀደም ብሎም ናዝሬት ላይ ሳሉም ሴት በመድፈር ተከሰው የነበረ መሆኑን በቅርብ የሚያውቋቸው ይናገራሉ፡፡ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ መጋቢ እያሉም በአባ ሳሙኤል አምሳል ሴት ያስገቡ ያስወጡ እንደነበር በጊዜው ጥበቃ ከነበሩት አንዳንዶቹ ይመሰክራሉ፡፡

ሁሉ የሚያውቃቸው የትዳር አጋራቸው የዑራኤል ቤተክርስቲያን ጸሓፊ የሆኑት ወ/ሮ ትዕግሥት ሲባሉ አባው ከእርሳቸው ሦስት ወይም አራት ልጆችን አፍርተዋል ይላሉ ምንጮቻችን፡፡ የዚያው ቤተክርስቲያን ሒሳብ ሹም የኾኑትን ወ/ሮ መናንም ወሽመዋል እየተባለ በስፋት ይወራል፡፡ ወ/ሮ መና በሂሳብ ሹምነታቸው ብዙ ሙስና ቢፈጽሙም “ዋ እንዳላወጣው” እያሉ አባ እስጢፋኖስን በማስፈራራት በሀገረ ስብከቱ ያለመከሰስ መብታቸውን አስከብረዋል ነው የሚባለው፡፡ ከእዚህ በተጨማሪ በሙስናው መዋቅር ውስጥ ገንዘብ በማቀባበልና የጉቦን መጠን ደረጃ በማውጣት ከሚደልሉላቸው ደላሎቻቸው መካከል የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ያደረጉት የዮናስ እናትና ሌሎችም ውሽሞቻቸው እንደሆኑ በካህናቱ መካከል የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የየካ ሚካኤል ቁጥጥር የሆነ ኢያሱና የአቡነ ጢሞቴዎስ ሾፌር የሆነው የልቤ ነጋም ልጆቻቸው መሆናቸውን ምንጮቻችን በእርግጥኝነትና በካህናቱ መካከል ሁሉም የሚያውቀው ሐቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተለይ የልቤ የተባለው ልጅ “ነጋ” በሚባል የአባት ስም ይጠራ እንጂ ቁርጥ አባቱን አባ እስጢፋኖስ እንደሚመስል ይናገራሉ፡፡
አባ እስጢፋኖስ በፓትርያርክ ማትያስ ዘመን የመጀመሪያው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስና የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀጳጳስ ሆነው ሲሾሙ፣ በፓትርያርክ ምርጫው ላይ በነበራቸው የአስመራጭነት ሥልጣን አባ ማትያስ እንዲመረጡ ለማድረግ በተጫወቱት ሚና በጅማ ሀገረ ስብከት ላይ አዲስ አበባ እንደተጨመረላቸው የሚናገሩ አሉ፡፡ ከመጰጰሳቸው በፊት በተለይ በ1988 – 89 ዓ.ም ድረስ በነበሩት ዓመታት ውስጥ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ እያሉ በሀገረ ስብከቱ ውስጥ ሕገወጥ የድራፍትና የጉቦ ቡድኖችን በማደራጀት ቅጥርና ዝውውር በጉቦ እንዲፈጸም መሠረት በመጣል ተጠቃሽ ስለነበሩ፣ ሊቀጳጳስ ሆነው ሲመጡ ብዙዎች “የጀመሩትን የሙስና መንገድ እንዲያጠናክሩት ነው የተሾሙት ሲሉ” ስጋታቸውን ገልጸው ነበር፡፡
እርሳቸውም የቀድሞ ክፉ ስማቸው ዳግም እንዳይነሳ በመስጋት ስለሙስና አብዝቶ ማውራት ከሙስና ነጻ የሚያደርግ ስለመሰላቸው በየተገኙበት ሙስናን ሲኮንኑ ቢሰሙም እንደአሁኑ ጊዜ ሙስናና የፍትሕ እጦት የተስፋፋበት እንደ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ያለ ስፍራ የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ስለሙስና አብዝተው እያወሩ በኃይለኛ ሙስና ውስጥ ተዘፍቆ መገኘት የዘመኑ ፋሽን ሆኗል፡፡ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ምክትል ኃላፊ እንደ ነበረው እንደ ገብረዋሕድ ስለሙስና አብዝቶ ያወራ በሙስናም ተዘፍቆ የተገኘ ስለሌለ የገብርኤልን መገበሪያ የበላ ሳይነኩት ይለፈልፋል እንደሚባለው ሙስና ውስጥ የሚገኝ ስለ ሙስና አብዝቶ ማውራቱ እየተለመደ መጥቷል፡፡ እንዲህ ስንል ሁሉም ስለ ሙስና የሚያወራ ሙሰኛ ነው እያልን አይደለም፡፡ - በፍጹም! ሙስናን በቁርጠኝነት ለመታገል የተሰለፉ፣ ሙስናን የሚኮንኑ እውነተኛ የቤተክርስቲያን ልጆችም እንዳሉ እናውቃለን፡፡
አባ እስጢፋኖስ በጅማ ሀገረ ስብከት ላይ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከተጨመረላቸው ወዲህ ሙስናና ብልሹ አሰራር ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እየተስፋፋና በርካታ አገልጋዮች የሙሰኞች ሰለባ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ ለዚህም በሀገረ ስብከቱ ውስጥ ቁልፍ ቦታዎችን የያዙት ማለትም አስተዳደር ላይ የተቀመጠው ዮናስ፣ ደብዳቤ መሪ ተብሎ የተሰየመው ታዴዎስና ስብከተ ወንጌል ክፍሉን የሚመራው ዳዊት ቅጥርና ዝውውር ላይ ኃይለኛ ደላሎች በመሆን ጉቦ እየተቀበሉ አንዱን እየሾሙ ሌላውን በአየር ላይ እያንሳፍፉ ይገኛሉ፡፡ አለቃቸው አባ እስጢፋኖስም ምናልባት ተገኝተው አቤቱታ ሲሰሙ በተለይ ዮናስን በአቤቱታ አቅራቢው ፊት ሰድበውና ሞልጨው ይናገሩትና ከመጋረጃ በስተጀርባ የሚተገበረው ግን ዮናስ ያለው ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ ጉቦው ወደ 30 እና 40 ሺህ ብር ከፍ ያለ መሆኑን እየተነገረ ነው፡፡ ጉቦ ለመብላት የተነደፈው ስልትም በየደብሩ በሐቅ የሚሰሩና ለዘራፊዎቹ ያልተመቹ አገልጋዮችንና በልዩ ልዩ ምክንያት የተጋጯቸውን አገልጋዮች አንዳንድ የደብር አስተዳዳሪዎች ከደላሎቹ ጋር በመነጋገርና በመደራደር እገሌን ቀይርልኝና ይህን ያህል እሰጥሃለሁ ይላሉ፡፡ በዚህ መካከል ደላሎቹ ከአስተዳዳሪውም በዝውውር የተሻለ ቦታ ከተገኘላቸው ሟሳኝ አሟሳኝ ሰራተኞችም ዳጎስ ያለ ጉቦ ይቀበላሉ፡፡ ከፍለው ለሚዛወሩት ነገሩ አልጋ ባልጋ ሲሆንላቸው ያለበደላቸው ከሚያገለግሉበት ደብር እንዲዛወሩ ለሚደረጉት የደላላ ሰለባዎች ግን አባጣ ጎርባጣ ነው የሚሆንባቸው፡፡ ሀብታም ከሆነና መሀል ከተማ ከሚገኝ ደብር ከከተማ ወጣ ብሎ ወደሚገኝና ገቢው አነስተኛ ወደሆነ ደብር እንዲዛወሩ፣ የዝውውር ደብዳቤ ከተጻፈላቸውና የነበሩበትን ደብር ከለቀቁ በኋላ የተዛወሩበት ደብር እንዳይቀበላቸው የማድረግና አየር ላይ የማንሳፈፍ የቀድሞው የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ የአባ ሳሙኤል ስልትም ተግባራዊ ይሆንባቸዋል፡፡
ለመጥቀስ ያህል እንኳ የ1500 ብር ደሞዝተኛ የነበረ አገልጋይ ጉቦ ለዮናስ ሰጥቶ በ2400 ብር በቅርቡ ዝውውር ተፈጽሞለታል፡፡ ቦታውን እንዲለቅ የተደረገው ደግሞ ደሞዝ ቀንሶ ነው የተዛወረው፡፡ እንዲሁም የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ቤተክርስቲያን ሒሳብ ሹም የነበረውን አገልጋይም በቅርቡ አዲስ ተሹሞ የመጣው አለቃ (አባ ነአኩቶ ለአብ) አላስበላ ብሎኛል በሚል ከአባ እስጢፋኖስ ደላሎች ጋር በመመሳጠር ከሚያገኘው ደመወዝ 400 ብር ቀንሶ ወደ ጠሮ ሥላሴ እንዲዛወር ያደረገው ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ወደተዛወረበትም ተቀባይ ሳያገኝ አየር ላይ ተንሳፎ ይገኛል፡፡ ሌላው አገልጋይ ደግሞ የተሻለ ገቢ ከነበረው ከኩርፎ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ከኮተቤ አለፍ ብሎ ወደሚገኘው ገጠር ቀመስ ቤተክርስቲያን ያዛወረው ሲሆን፣ ደብሩ ደሃና ወርሃዊ ደሞዝ እንኳን በቅጡ የማይከፈልበት፣ በየወሩ አንዳንድ ጊዜ የደሞዝ ግማሽ፣ አንዳንዴ ደግሞ ሩቡን ካልሆነም እስከ 20 ከመቶ ያህል የሚከፈልበት ደሃ ቤተክርስቲያን መሆኑ ይነገራል፡፡
ቄስ ለይኩን የተባለ አገልጋይ ደግሞ በደላላው ዳዊት አማካይነት ለአባ እስጢፋኖስ 40 ሺህ ብር ከፍለው ከኮተቤ ሩፋኤል ቤተክርስቲያን የ1600 ብር ደሞዝ ወደ ሰዋስወብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ቤተክርስቲያን 2999 ብር ደሞዝ ከነአበሉ እንዲያገኙ ተደርጎ ተዛውረዋል፡፡ በቅርቡም በተመሳሳይ ተልእኮ ከአራዳ ጊዮርጊስ ወደ መካኒሳ ሚካኤል የተዛወረ አንድ ሰራተኛ የመንግስት ባለስልጣን የሆነ ዘመድ ስለነበረው በተጽእኖ ከመካኒሳ ሚካኤል ወደቅድስተ ስላሴ ካቴድራል እንዲዛወር ተደርጓል፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ የሙሰኞች ሰለባ ሆነው ከደሞዛቸው ቀንሰው ተዛውራችኋል የተባሉና አየር ላይ ተንሳፈው የሚገኙ አገልጋዮች ጥቂት አይደሉም፡፡ አባ እስጢፋኖስ ደላሎቻቸውና በጉቦ ወደሚዘረፍበት ደብር ዓይናቸውን የጣሉ ሙሰኞች የከፈቱት “የዝውውር መስኮት” መቼ እንደሚዘጋ አንድዬ ነው የሚያውቀው፡፡
አባ እስጢፋኖስ በዚህ ብቻ ሳይገቱ አንድ እግራቸውን ጅማ አንድ እግራቸውን አዲስ አበባ ላይ የተከሉ እንደመሆናቸው በአብዛኛው አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በደላሎቹ በኩል ካልሆነ በቀር የማይገኙ ከመሆናቸውም በላይ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አድባራትና ገዳማት ለጅማ ሀገረ ስብከት በሚል ከአንዳንድ የደብር አስተዳዳሪዎች ጋር በመመሳጠር ገንዘብ እየጠየቁና እየተሰጣቸው መሆኑን ምንጮችን ይናገራሉ፡፡ በቅርቡ እንኳ ከአስኮ ገብርኤል 34 ሺህ ብር መውሰዳቸው ታውቋል፡፡ በጅማ ሀገረ ስብከት ስም ለአባ እስጢፋኖስ ፈሰስ የማያደርጉ አለቆች ግን ጥርስ ውስጥ ገብተው የዝውውር ሰለባ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰሞኑን እየተካሄደ ባለው የሲኖዶስ ስብሰባ ላይ የአባ እስጢፋኖስ ጉዳይ ተነስቶ በሲኖዶስ አባላት ከሀገረ ስብከቱ ይነሱ የሚል ውሳኔ በጳጳሳቱ ሁሉ የተላለፈ ቢሆንም ፓትርያርክ ማትያስ ግን “ሀገረ ስብከቱ የእኔ ነው አይነሱም ይቀጥላሉ” ብለው መቃወማቸው ተሰምቷል፡፡ ጳጳሳቱ ግን በግልም ለአባ እስጢፋኖስ “ሳይዋረዱ ቀድመው ቢወርዱ ይሻላል” ብለው ምክር የሰጧቸው መሆናቸውን እየተናገሩ ነው፡፡ በተያያዘም ከድለላው ክበብ ውጪ ያሉ የሀገረ ስብከቱ ሠራተኞች በሌሎች የአድባራትና ገዳማት ሠራተኞች ላይ የሚፈጸምውን ግፍና በደል፣ አቤቱታ ሰሚም በመታጣቱና ፍትሕ እየተዛባ በመሆኑ ምክንያት ከአባ እስጢፋኖስ ጋር አንሰራም በሚል ውስጥ ውስጡን ከፍተኛ ተቃውሞ እያሰሙ ይገኛሉ፡፡

ይህ ሁሉ ሲሆን አብሯቸው እየሠራ ያለውና በሀገረ ስብከቱ እያዘዘ የሚገኘው ማቅ ለምን ዝም አለ? ዝርዝሩን በሌላ ጊዜ እንመለስበታለን፡፡

Thursday, October 31, 2013

«የእግዚአብሔርን ሥራ፥ በምድር ያደረገውንም ተኣምራት እንድታዩ ኑ» መዝ ፵፮፤፰


መዝሙረ ዳዊት
40፥5
አቤቱ አምላኬ፥ ያደረግኸው ተአምራት ብዙ ነው፥ አሳብህንም ምንም የሚመስለው የለም ባወራም ብናገርም ከቍጥር ሁሉ በዛ።
46፥8
የእግዚአብሔርን ሥራ፥ በምድር ያደረገውንም ተኣምራት እንድታዩ ኑ።
86፥10
አቤቱ፥ ድንቅ የምታደርግ አንተ ታላቅ ነህና፥ አንተም ብቻህን ታላቅ አምላክ ነህና።


ቃል ኪዳንህ ከምድረ በዳ ድንጋይ ጋር ይሆናልና የምድረ በዳም አራዊት ከአንተ ጋር ይስማማሉና። ኢዮብ 5፥23