Monday, March 25, 2013

Sunday, March 24, 2013

ዓለም ለእኔ ብቻ በሚሉ ስግብግቦች የተሞላች ነች!


በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት ሁላችንም የዚህ ስግብግብነት ሰለባዎች ነን። ምናልባት ላይታወቀን  ቢችል ወይም በሌላው ላይ ያደረስነው የስግብግበት መገለጫ ጠባይዓት በግልጽ ባለመታየቱ ብቻ ራሳችን ነጻ እንደሆንን እናስብ ይሆናል። ነገር ግን የሰው ልጅ ከሥጋ ድካምና ከፈተናው ጽናት የተነሳ ስግብግብ ነው። ስግብግብነት ማለት ሁሉን ለእኔ በሚል ፍላጎት ዙሪያ ብቻ የሚሽከከረከር  ሳይሆን ስሱዕ /ስስታምነትን/ ፤መጠን የለሽ ጉጉነትን ይጨምራል።  ስስታምነት ለራስ ማድላትና ራስን ማዕከል ባደረገ ስሜት ስር መታጠር በመሆኑ የስግብግብነት አንድ አካል ነው። ጉጉነት ደግሞ እዚያ ጠርዝ ላይ ለመድረስ የሚጠይቀውን መስዋዕት ሁሉ ለመክፈል መሮጥ ነው። ስግብግብነት ከመጠን በላይ መብላት፤ በብዙ ወጪ ለመርካት መሞከር፤ የፍላጎት ጣሪያ መናር እና የአኗኗር ቅንጡነትንም ይጨምራል። «ሁሉ አማረሽን ገበያ አታውጧት» የሚባለው የፍላጎት ስግብግብነት ልክ ማጣት ማሳያ ነው።
ስግብግብነትን ካምብሪጅ ዲክሽነሪ በምሳሌ እንዲህ ይለዋል።
(industrialized countries should reduce their gluttonous (= greater than is needed) consumption of lifesyle)
የበለጸጉ ሀገሮች የስግብግብ ፍጆታ አኗኗራቸውን መቀነስ አለባቸው እንደማለት ነው።  ምክንያቱም የአኗኗራቸው ቅንጡነት ስግብግቦች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።ለልቅ ኑሮ ጉጉ ናቸው። ጉጉነት /AVID / ያላዩትን ነገር እንዲያዩ ይገፋቸዋል። ጉጉነት ምንጊዜም አንድን እርከን ከመሻገር በኋላ የሚመጣ ፍላጎት ነው።  ምንም የሌለውና በጣም የተራበ ሰው በቅድሚያ የሚታየው ወይም ከፊቱ ድቅን ብሎ የሚመጣበት ጉጉት ምንም ይሁን ምንም ረሃቡን የሚያስታግስበትን የእህል ዘር እንጂ ከትልቅ አዳራሽ ውስጥ ተሰይሞ የበግ አሮስቶ በውስኪ እያወራረደ መርካት አይደለም።  ያ ማለት ግን አይፈልግም ማለት አይደለም። ይህ የቅንጦት እሳቤ ምንም ከማጣት ችጋር ጋር ስለማይቀራረብ ብቻ ነው። የበለጸጉ ሀገሮች ግን በብዙ መልኩ ከችጋር ስለወጡ አመጋገባቸው ሁሉ ጊዜ ሰርግና መልስ ነው። እንደ ችጋር ሀገሮች የበሉት የምግብ ተረፍ ለበኋላ ተብሎ ይቀመጥ ዘንድ በፍጹም አይታሰብም። አዲስ ሞዴል መኪና፤ አዲስ የቤት እቃ፤ አዲስ ሁሉ አዲስ እንዲሆንላቸው ፍላጎታቸው ጣሪያ ነው። ለሌላው አዲስ ለእነሱ አሮጌ ነው። መሪዎቻቸው የእነዚህን ቅንጡ ሰዎች ኑሮ ላለማጓደል ከሌላው ዘርፈው ወይም ቀምተው ያመጡላቸዋል። ዘረፋው በቀጥታ ላይሆን ይችላል። ሚዛናዊ ባልሆነ ንግድ ወይም የምርት ልውውጥ፤ ሽያጭና ጥቅሞቻቸውን በሚያስከብሩ ስምምነቶች ሊሆን ይችላል። በአንዱ ቦታ የመሳሪያ ቅነሳ ወይም ማስተላለፍ እገዳ ፊርማ ቢያኖሩ  በሌላ ቦታ ደግሞ በመርከብ ጭነው ሊሸጡ ይችላሉ። ይህንን ካላደረጉ ሰማይ የደረሰውን ስግብግብ ፍላጎታቸውን መሙላት አይችሉም።

Friday, March 22, 2013

«እስልምና በኢትዮጵያ ታሪክ» ክፍል ሁለት


ሁለቱ እስላማዊ ርዕዮተ ዓለሞችና ትግላቸው (ጽሁፍ በእስልምና መልስ አዘጋጅዎች)

በወቅቱ በአገሪቱ ውስጥ ያለው የሙስሊሞችን እንቅስቃሴ፣ ለመደገፍ፣ ወይንም ዝም ብሎ ለማየት ወይንም ለመቃወም የሚቻለው እስልምና በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ምን ይመስል እንደበረ በትክክል በመገንዘብ ነው፡፡ የአሁኑ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በእርግጥ የሃይማኖት ነፃነት ጥያቄ ነውን? ብዙዎችን መስሏቸዋል፡፡ በጣም የቅርቡ በኢትዮ ሚዲያ የድረ-ገፅ ጽሑፎች ላይ የቀረበው የኦክላንድ መግለጫ እንዲሁም  www.ethiomedia.com/2012_report/4059.html የቀረበው የነጃሺ ካውንስል መግለጫ፣ አሜሪካ ውስጥ ባለው በኢትዮጵያ ክርስትያንና እስላም ካውንስል በJuly 26 2012 በኢትዮ ሚዲያ ላይ የወጣው www.ethiomedia.com/2012_report/4097.html ጋዜጣዊ መግለጫ እንዲሁም በሌሎች ድረገፆች ላይ በተደጋጋሚ የተሰጡት መግለጫዎች በሙሉ ሁኔታውን ያቀረቡት የእምነት ነፃነት ተደፈረ ከሚል አመለካከት የተነሳ ነው፡፡
ይህንን በተመለከተ የሚጻፉትም የተለያዩ ጽሑፎች አስገራሚዎች ሆነው አግኝተናቸዋል፤ በተለይም በዚያው በኢትዮ ሚዲያ ላይ Standing up with our Moslem citizens በሚል ርዕስ በይልማ በቀለ የቀረበው ጽሑፍ ለምሳሌነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ሙሉ ጽሑፉን www.ethiomedia.com/2012_report/4554.html ማንበብ ይቻላል፡፡ አቶ ይልማ በቀለ የሙስሊሞችን እንቅስቃሴ እንደ እውነተኛ የሃይማኖት ነፃነት ጥያቄ አቅርቦ የገዚው ፓርቲ እነርሱን ለማፈን አንዳንድ የፈጠራ ፕሮፓጋንዳዎችን እንደተጠቀመ በማድረግ አስቀምጦታል፡፡ በእርግጥ ይልማ በቀለ እንዳለው ኢትዮጵያን የምንመኛት የሁሉም እምነት ተከታዮች በነፃነት የሚኖሩባት አገር እንድትሆን ነው፡፡ የሙስሊሞች ጥያቄና የዘመናት ዕቅድ ግን በእርሱና በመሰሎቹ ዘንድ የታየው ላይ ላዩን ከሚሆነው ነገርና  ከሞኝነትም ጭምር የተነሳ ነው ምክንያቱም ነገሩ ሁሉ እነሱ እንደሚሉት አይደለም፡፡
ሙስሊሞች በተለይም በአሁኑ ተቃውሞ ውስጥ የተሳተፉት መሰረታዊ ፍላጎታቸው በእርግጥ የሃይማኖት ነፃነት ጥያቄ ነውን? የአንድ አገር መንግስትስ  በሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ ለመግባታ ስለምን ይገደዳል? በስልጣን ላይ ያለ አንድ መንግስት በሃይማኖት ስም የተቀነባበረና አገሪቱን ችግር ውስጥ የሚጥል አደጋ ሲመጣ እያየና መረጃዎችና ማስረጃዎች እያለውና እያወቀ ዝም ሊልስ ይገባዋል ወይ? ለዚህ ነው የተሰጡት መግለጫዎች እና ይልማ በቀለን በመሳሰሉ ሰዎች የቀረቡት ጽሑፎች ሚዛን የጎደላቸውና ታሪካዊ ምንጮችን ያላገናዘቡ የሆኑት፡፡
የዚህ ድረገፅ አዘጋጆች ካለው ውዥንብርና መወናበድ ባሻገር ያሉትን ታሪካዊ ምርምሮችን እና አቅጣጫ ጠቋሚ እውነታዎችን ማሳየት የተገደዱት ለዚህ ነው፡፡ ከገዢው ፓርቲ መርሆ የተነሳ በአገሪቱ ውስጥ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ የመናገርና የመጻፍ ነፃነት በእርግጥ አለ ማለት አይቻልም፡፡ ለዚህም ነው ብዙ ጋዜጠኞች በእስር ላይ የሚገኙት፡፡ ሰዎች የፈለጉትን እምነት የመከተልም ነፃነት በመጠኑ የለም ማለት ይቻላል፣ ይሁን እንጂ የአሁኑ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የተቃውሞ እንቅስቃሴ መሰረታዊው ጥያቄ የሃይማኖት ነፃነት ጥያቄ ሊሆን አይችልም፣ ምክንያቱም የሃይማኖት ነፃነት አልተነፈጋቸውምና፡፡ እንዲያውም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሙስሊሞች ነፃነት ያገኙት በመለስ ዜናዊ አገዛዝ ስር መሆኑ ለማንም ግልፅ ነው፡፡ ታዲያ ለሙስሊሞች እንቅስቃሴ መሠረታዊው ምክንያት ምንድነው?