ሁለቱ እስላማዊ ርዕዮተ ዓለሞችና ትግላቸው (ጽሁፍ በእስልምና መልስ አዘጋጅዎች)
በወቅቱ በአገሪቱ ውስጥ ያለው የሙስሊሞችን እንቅስቃሴ፣ ለመደገፍ፣ ወይንም ዝም ብሎ ለማየት ወይንም ለመቃወም የሚቻለው እስልምና በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ምን ይመስል እንደበረ በትክክል በመገንዘብ ነው፡፡ የአሁኑ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በእርግጥ የሃይማኖት ነፃነት ጥያቄ ነውን? ብዙዎችን መስሏቸዋል፡፡ በጣም የቅርቡ በኢትዮ ሚዲያ የድረ-ገፅ ጽሑፎች ላይ የቀረበው የኦክላንድ መግለጫ፤ እንዲሁም www.ethiomedia.com/2012_report/4059.html የቀረበው የነጃሺ ካውንስል መግለጫ፣ አሜሪካ ውስጥ ባለው በኢትዮጵያ ክርስትያንና እስላም ካውንስል በJuly 26 2012 በኢትዮ ሚዲያ ላይ የወጣው www.ethiomedia.com/2012_report/4097.html ጋዜጣዊ መግለጫ እንዲሁም በሌሎች ድረገፆች ላይ በተደጋጋሚ የተሰጡት መግለጫዎች በሙሉ ሁኔታውን ያቀረቡት የእምነት ነፃነት ተደፈረ ከሚል አመለካከት የተነሳ ነው፡፡
ይህንን በተመለከተ የሚጻፉትም የተለያዩ ጽሑፎች አስገራሚዎች ሆነው አግኝተናቸዋል፤ በተለይም በዚያው በኢትዮ ሚዲያ ላይ Standing up with our Moslem citizens በሚል ርዕስ በይልማ በቀለ የቀረበው ጽሑፍ ለምሳሌነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ሙሉ ጽሑፉን www.ethiomedia.com/2012_report/4554.html ማንበብ ይቻላል፡፡ አቶ ይልማ በቀለ የሙስሊሞችን እንቅስቃሴ እንደ እውነተኛ የሃይማኖት ነፃነት ጥያቄ አቅርቦ የገዚው ፓርቲ እነርሱን ለማፈን አንዳንድ የፈጠራ ፕሮፓጋንዳዎችን እንደተጠቀመ በማድረግ አስቀምጦታል፡፡ በእርግጥ ይልማ በቀለ እንዳለው ኢትዮጵያን የምንመኛት የሁሉም እምነት ተከታዮች በነፃነት የሚኖሩባት አገር እንድትሆን ነው፡፡ የሙስሊሞች ጥያቄና የዘመናት ዕቅድ ግን በእርሱና በመሰሎቹ ዘንድ የታየው ላይ ላዩን ከሚሆነው ነገርና ከሞኝነትም ጭምር የተነሳ ነው ምክንያቱም ነገሩ ሁሉ እነሱ እንደሚሉት አይደለም፡፡
ሙስሊሞች በተለይም በአሁኑ ተቃውሞ ውስጥ የተሳተፉት መሰረታዊ ፍላጎታቸው በእርግጥ የሃይማኖት ነፃነት ጥያቄ ነውን? የአንድ አገር መንግስትስ በሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ ለመግባታ ስለምን ይገደዳል? በስልጣን ላይ ያለ አንድ መንግስት በሃይማኖት ስም የተቀነባበረና አገሪቱን ችግር ውስጥ የሚጥል አደጋ ሲመጣ እያየና መረጃዎችና ማስረጃዎች እያለውና እያወቀ ዝም ሊልስ ይገባዋል ወይ? ለዚህ ነው የተሰጡት መግለጫዎች እና ይልማ በቀለን በመሳሰሉ ሰዎች የቀረቡት ጽሑፎች ሚዛን የጎደላቸውና ታሪካዊ ምንጮችን ያላገናዘቡ የሆኑት፡፡
የዚህ ድረገፅ አዘጋጆች ካለው ውዥንብርና መወናበድ ባሻገር ያሉትን ታሪካዊ ምርምሮችን እና አቅጣጫ ጠቋሚ እውነታዎችን ማሳየት የተገደዱት ለዚህ ነው፡፡ ከገዢው ፓርቲ መርሆ የተነሳ በአገሪቱ ውስጥ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ የመናገርና የመጻፍ ነፃነት በእርግጥ አለ ማለት አይቻልም፡፡ ለዚህም ነው ብዙ ጋዜጠኞች በእስር ላይ የሚገኙት፡፡ ሰዎች የፈለጉትን እምነት የመከተልም ነፃነት በመጠኑ የለም ማለት ይቻላል፣ ይሁን እንጂ የአሁኑ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የተቃውሞ እንቅስቃሴ መሰረታዊው ጥያቄ የሃይማኖት ነፃነት ጥያቄ ሊሆን አይችልም፣ ምክንያቱም የሃይማኖት ነፃነት አልተነፈጋቸውምና፡፡ እንዲያውም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሙስሊሞች ነፃነት ያገኙት በመለስ ዜናዊ አገዛዝ ስር መሆኑ ለማንም ግልፅ ነው፡፡ ታዲያ ለሙስሊሞች እንቅስቃሴ መሠረታዊው ምክንያት ምንድነው?
እነዚህንና ከዚህ ጋራ ተያይዘው የሚመጡ ጥያቄዎችን ለመመለስ የምንችለውና ትክክልም አቋም ላይ የምንደርሰው የእስልምናን እምነት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ምን ይመስል እንደነበረ ስናየው ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ አስፈላጊና ዓይን ከፋች ሆኖ ያገኘነው የፕሮፌሰር ኤርሊችን እና የፕሮፌሰር ካብሃን የምርምር ጆርናል ነው፡፡ እነዚህ ሁለቱም ቢያንስ አሁን በምናየው ጆርናል ላይ የሌላ አገር ተወላጆችና የታሪክ ተመራማሪዎች ብቻ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካም ሆነ ሃይማኖት ውስጥ የተለየና ወደ አንድ አቅጣጫ ያዘመመ አመለካከት የላቸውም፡፡ ስለዚህም የእነርሱን ስራ ማየት ሚዛናዊ አመለካከት ላይ እንድመጣ ይረዳናል፡፡ በመሆኑም ይህንን ክፍል ሁለት ጽሑፍ እናቀርባለን፡፡
የአል-አሕበሽ እድገት፡
ፕሮፌሰሮቹ ስለ አል-አሕባሽ ርዕዮተ ዓለም መስራች ስለ ኢትዮጵያዊው ሼክ አብደላ እንደ ጻፉት፡ በ1983 ወደ እይታ ብቅ እንዳለና እንደ ታዋቂ ፈላስፋ እንዲሁም ጸሐፊ ዝናን እንዳገኘ፣ ቀጥሎም ወደ ሃያ መጽሐፍትንም እንዳሳተመ ከዚህም የተነሳ ሙፍቲ፣ እና ሰባኪም ሆኖ ዝናን እንዳገኘ አቅርበዋል፡፡ የዚህ ሰው ርዕዮተ ዓለማዊው መልእክት ምንድነው?
የእርሱም ዋና መልእክት ሆኖ የቀረበውና የሚሟገትለት ርዕዮተ ዓለም ከኢትዮጵያ ያመጣው ትምህርት ነው፡፡ የእርሱ ትምህርት በሊባኖስም ውስጥ በማዕከላዊነት በጣም ጠቃሚ ሆኖ እንደነበርና መልእክቱም፡ “እስላምና ክርስትያን አብረው በሰላም ይኖራሉ” የሚለው እንደነበር የታሪክ ሊቃውንቱ ይናገራሉ፡፡ ወዲያውም እርሱ ከብዙ እስላማዊ ማህበሮችና በተዘዋዋሪም ከሊባኖስ ክርስትያናዊ ድርጅቶችም እንኳን እርዳታዎችን አግኝቷል፡፡ ከዚህም ባሻገር እርሱ የማህበሩ መሪ የመሆኑ ጉዳይ ሶርያ ሊባኖስን ከመውሰዷ ጋር ተገጣጥሞ እንደነበር ታሪክን ጠቅሰው አስረድተዋል፡፡
ቀጥለውም ያስቀመጡት ነጥብ አዲሶቹም የሶርያ ባለስልጣናት ለያዙት የሴኩላር አረብ ባዝ ዶክትሪን የኢትዮጵያዊው ሼክ “እስላማዊ ክርስትያን” መልእክት ከእነርሱ አቀራረብ ጋር አብሮ የሚሄድ ሆኖ አግኝተወታል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ማህበሩ በጣም በገነነ መልኩ የሚታወቀው “አል-አሕበሽ” ተብሎ ሲሆን በሊባኖስ ፖለቲካም ውስጥ ዘው ብሎ የመግባት ዕድልን አግኝቷል ይላሉ፡፡ ስለዚህም የድርጅቱ አባል ዶ/ር አድናን አል-ታባቡልሲ በ1989 በሊባኖስ ፓርላማም ውስጥ መቀመጫን እንዳገኘ ያስረዳሉ፡፡ የሼኩ ድርጅት አል-አሕበሽ፤ ለሶርያ ባዝ ፓርቲና በሊባኖስ ውስጥ ላሉት የእርሱ ተባባሪዎች፣ ለክርስትያኑ የሊባኖስ ፕሬዚዳንት ኢልያስ አል-ሃዋሪ (1989-1998) እና ለእርሱ ተከታይ ኢሚል ላሁድ (1998 -) እንዲሁም ለሙስሊሙ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳሊም አል-ሑስና ራፊክ አል-ሃራሪ ያበረከተው የማያጠራጥር ትብብር በመንግስታዊ እርዳታ ደረጃ ሽልማትን አስገኝቶለት እንደነበር ያስረዳሉ፡፡
የአል-አሕበሽ ማህበር በሊባኖስ ውስጥ ከፍተኛ ዕድገትን አግኝቷል፡፡ ማህበሩ ወርሃዊ የሆነ ማኑር አል-ሁዳ የሚባልን ጋዜጣ ከ1992 ጅምሮ ሲያወጣ ቆይቷል እንዲሁም ከ1998 ጀምሮ ኒዳ አል-ማሪፋህ የተባለ የራሱ የሆነ የራዲዮ ጣቢያ እንዳለው፡፡ አባላቶቹ በኢንተርኔት ላይ እጅግ በጣም በትጋት እንደሚሰሩ በመሆኑም የሼኩን ቃልና እርሱ በተቃራኒዎቹ ላይ የሚያስተላልፈውን ትምህርት እንደሚያሰራጩ አስረድተዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ማህበሩ የልጆች ትምህርት ኔት ወርክን የኤለመንታሪና የሰከንደሪ ትምህርት ቤቶችንም እንዲሁም ከካይሮው ጃሚያት አል-አዛር ጋር የተቀራረበ እስላማዊ ኮሌጆችን ጭምር እንደሚያካሂድ በምርምር ስራዎቻቸው ላይ አቅርበዋል፡፡
የአል-አሕበሽ መልክእትም ሁልጊዜ ጊዜ በግልጥነት ስለሚሰራጭና እንዲሁም ማህበሩ በሊባኖስ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሕይወት ውስጥ ያለው አስተዋፅዖ ህልውናና ያገኘው ጥሩ ስሜት ብዙውን ጊዜ በሳላፊዎችና በዋሃቢዎች አካባቢ ተቃውሞንና ጥላቻን እንደቀሰቀሰበት የታሪክ ተመራማሪዎቹ ጠቁመዋል፡፡ ከዚህም የተነሳ ከ1980ዎቹ ጀምሮ መጠነኛ የሆኑ ግጭቶችና የጎዳና ላይ ሽብሮች ታይተው እንደነበርና እነዚህም ግጭቶች በ1995 ከፍተኛ ጣሪያ ላይ ደርሰው በቤይሩት የማህበሩ መሪ ኒዛር ሃላቢ ተገድሏል፡፡ ይህም ክስተት በ“ኢትዮጵያውያኖቹ” ማለትም በአል-አሕባሾቹና እና በዋሃቢያዎቹ መካከል ያለውን ጥላቻ (ጠላትነት) ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንዳደረሰው የታሪኩ ተመራማሪዎች ጠቁመዋል፡፡
ዓለም አቀፉ የሊባኖስ ዲያስፖራ አል-አሕበሽን ዓለም አቀፍ ማህበር እንዲሆን በ1980 እረድተውታል፡፡ የድርጅቱም ዓለም አቀፍ ማዕከል ያለው በዩሮፕ በጀርመን ውስጥ ሲሆን በጣም ትጋት ያላቸው ቅርንጫፍ ቢሮዎቹ በምዕራብ ዩሮፕ ውስጥ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እንዳላቸው ምሁራኑ ይጠቁማሉ፡፡ ይህ አል-አሕበሽ በኢንዶኔዥያ በማሌዢያ በፓኪስታን በጆርዳን በግብፅ በአውስትራሊያ እና በአሜሪካ የሚንቀሳቀሱም ቅርንጫፎች አሉት፡፡ አል-አሕበሾች በአፍሪካም ውስጥ በጣም ንቁ እንቅስቃሴ ያደርጋሉ (በናይጀሪያ እና በጋና በጣም በከፍተኛ ደረጃ) ከዚህም የተነሳ በአካባቢያዊ ሙስሊሞችና በመካከለኛው ምስራቅ ማዕከላዊዎች መካከል ድልድይን ለመስራት ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል፡፡ በ1990ዎቹ ላይም አል-አሕበሽ እስላማዊ በሆኑ አገሮች ውስጥ ሁሉ የሚገኝና ዓለም አቀፍ የሆነ እንዲሁም በጣም በጥሩ ሁኔታ የተደራጀ እስላማዊ ድርጅት ለመሆን በቅቶ እንደነበርና በዚያን ጊዜ ብቻ ሩብ ሚሊየን ያህል አባላት እንደነበሩት የነፕሮፌሰር ኤርሊች ጆርናል ያስረዳል፡፡
ኢትዮጵያውያን በአል-አሕበሽ ውስጥ፡
ይሁን እንጂ በአል-አሕባሽ ድርጅት ውስጥ ያሉት ኢትዮጵያውያን አባላት ቁጥር አይታወቅም፣ በማለት የሚናገረው ጆርናል ጉዳዩን የደመደመው በውስጡ ያሉት ኢትዮጵያውያን፤ “ነገር ግን ብዙ አይደሉም” በማለት ነው፡፡ ከሐረር ከሆነው ከሼክ በስተቀር የእንቅስቃሴው አጠቃላይ አባላት ከተለያዩ ሌሎች አገሮችና ቋንቋ የተውጣጡ ሰዎች ናቸው፡፡ እነርሱም እራሳቸውን የሚጠሩት “ኢትዮጵያውያኖች” በማለት እንደሆነና ይህንንም ያደረጉት በከፊል ለመሪያቸው ስላላቸው አድናቆትም ጭምር እንደሆነ የታሪክ ሊቃውንቱ ያስረዳሉ፡፡ የአል-አሕበሽ ተከታዮች ሼክ አብደላን የሚያዩት ከእስላም ሊቃውንት መካከል አንዱና ታላቁ ሊቅ እንደሆነ አድርገው ነው፡፡ ከዚህም በላይ የሚከተለውን የማዕረግ የመጠሪያ ስምን በመጠቀም እንደሚጠሩት ጠቁመዋል፤ “አል-ኢማን አል-ሙሃዲት” ወይንም “ሙሃዲት አል-አሳር”፣ ትርጓሜውም “የሐዲት ሊቃውንት መሪ” እንዲሁም “የጊዜያችን የሐዲት ሊቅ” ማለት እንደሆነም አስቀምጠዋል፡፡ ከዚህም በላይ እርሱ የሚጠራው እንደ አል-ሃፊዝ ተብሎም ነው፤ ትርጉሙም የጥበብና የሊቅነት ጠባቂ ማለት ነው፡፡
ፕሮፌሰሮቹ እንደሚሉት ሼኩ እራሱ አረባዊ ጀርባ አለው ተብሎ የሚነገረውን ነገር እንደሚኮራበትና፤ የእራሱም ሙሉ ስም “አብደላ ኢብን ሙሐመድ ኢብን ዩሱፍ አል-ሐራሪ አል-ሻይቢ አል-አብዳሪ” ይህም የኩራይሽ ዘር ያለው መሆኑን የሚያመለክት እንደሆነ አስቀምጠዋል፡፡ እርሱ ግን አረባዊነትን የሚቆጥረው እንደ ቅዱስ መለያና በሙስሊሞችና በክርስትያኖች መካከል የሚኖር ትክክለኛ ድልድይ አድርጎ እንደሆነም ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ግን በኢትዮጵያዊነቱም ሙሉ ትምክህት ወይንም ኩራትም አለው (ወደ ኢትዮጵያም ሁለት ጊዜ ተመልሶ ነበር በ1969 እና በ1995፣ በወቅቱም በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በጣም በከፍተኛ አክብሮትና ተቀባይነትን አግኝቶ ነበር) ይላሉ፡፡
የእርሱም ዓለም አቀፍ ብዙ ተከታዮች እራሳቸውን የሚያስቀምጡት ኢትዮጵያ ታሳየዋለች ደግሞም ምሳሌ ሆናበታለች ለሚሉት ለለዘብተኛና የመቻቻል ሙስሊምነት ትክክለኛነት መሆኑን ጆርናሉ ያስረዳል፡፡ ለዚህም ነው ይላሉ የሼክ አብደላ ተከታዮች እራሳቸውን አል-አሕበሽ በማለት የሚጠሩት ይህም ለዘብተኛ የሆነን እስልምና በመደገፍ ተስፋ ላይ የመመስረት ፍላጎት ነው፣ መልእክታቸውም ከክርስትያን “ሌላ” ጋር ሙስሊም አብሮ መኖር ይቻላል የሚል ነው፡፡
(To be continued...)