Friday, March 15, 2013

እስልምና በኢትዮጵያ ታሪክ



ፎቶ ከ /britainfirst.org/


ኢህአዴግ ችግሮችን ለመፍታት የሚሞክርባቸው ጥሩ ያልሆኑ መንገዶቹና ሌላውን ለማሳመን የሚጓዝባቸው የህጻናት ጫወታ ዓይነት ስልቶቹ፤  እንከን ሲለቅም ለሚኖር ለሌላ ወገን ቀርቶ ዳር ቆሞ በአንክሮ ለሚታዘበውም ሰው ሳይቀር የሚያሳፍር ሆኖ ይገኛል። ሕዝቡ በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ወድቆ፤ «ዝምታ ቤቴ» ቢል የወደደው መስሎት ከሆነ የውድቀቱ መጀመሪያ መሆኑ ማወቅ ይገባዋል። ለሀገርም፤ ለወገንም የማይበጅ ፍጻሜ ይኖረዋል።  የአሜሪካ ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት ባደረገው ጥናትና የመረጃ ትንተና ውጤት መሠረት 2030 በዓለም ላይ በውስጣቸው በሚነሳ ሽኩቻና በአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ምክንያት ሊፈራርሱ ከሚችሉ ሀገሮች አንዷ ኢትዮጵያ  ናት ሲል ያወጣውን መረጃ ሟርት ነው ብሎ የሚያልፍ ከሆነ ውስጡን ማየት አቅቶታል ማለት ነው። መልኳን በመስታወት ውስጥ ያገኘችው ዝንጀሮ «አቤት የፊቷ ማስቀየም፤ በዚያ ላይ የመቀመጫዋ መመለጥ» ብላ አክፋፍታ መናገሯ የሚያመለክተው ራሷ ምን እንደምትመስል ምንም ግንዛቤ የሌላት በመሆኑ ነው። የኢህአዴግም የቁጣ ፊት እያስቀየመ፤ መቀመጫው ሁሉ እየተመላለጠ መጥቶ ሳለ የሌላውን በማየት ሲሳለቅ ሀገሪቷን ይዞ እንዳይወድቅ እንሰጋለን። በተለይም በሃይማኖት ጉዳይ ላይ ለፖለቲካው የሚመች ሥራ ለመሥራት ብቅ ጥልቅ ማለቱ ከእሳት ጋር መጫወት ይሆናል። ኦርቶዶክሱ ውስጥ ውስጡን ቆስሏል። የእስልምናውንም አያያዝ «ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ፤ አሁን ምን ያደርጋል፤ ድስት ጥዶ ማልቀስ» በማለት እየተናገርንበት ነው። ጀሃድ በለው፤ ግፋ በለው፤ እሰር በለው የትም አድርሶ አያውቅም። መንግሥት ሰከን ብሎ በማስተዋልና በጥበብ መጓዝ ካልቻለ ስለወደድነው አይቆምም፤ ስለጠላነው አይሞትም። ተግባር ራሱ ወደመጨረሻው ምዕራፍ ይገፋዋልና ያንን ስንመለከት የሚያሳስበን ብዙ ነገር አለ።   
ምንም እንኳን በመንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ ብታተኩርም ሀገራችን ለእግዚአብሔር መንግሥት የምትታዘዝ፤ ሰላምና ፍቅር የሰፈነባት፤ ሕዝቦች በነጻነት የሚኖሩባት ሀገር እንድትሆን ካለን ዓላማ አንጻር ማኅበራዊው፤ ፖለቲካዊውና ኢኮኖሚያው ሁኔታ ያሳስበናልና እንደዜጋ በዚህ ላይም ከወገንተኝነት በጸዳ ያለውን እውነታ ብሎጋችን ትናገራለች። ኢህአዴግ እንደፖለቲካ ሽንፈት ሳይሆን ለሀገር ሰላምና መረጋጋት ሲል በየምክንያቱ ያሰራቸውን ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ሰዎች በመፍታት ትኩሳቱን ያብርድ እንላለን። አሁን ባለው ሁሉን ነገር የመቆጣጠር ግትርነትና ሥነ ልቡና ሰልቦ አደብ የማስገዛት ስልት ወንጀለኛ ቢሆን እንኳን እንደትክክል ቆጥሮ የሚያምነው ወገን ማግኘት ከማይችልበት ደረጃ ደርሷል። «ሆድ ለባሰው ማጭድ አታውሰው» እንዲሉ ከኑሮው ውድነት ጋር ተስፋ አድርጎ «ሌላ ቀንም አለ» እያለ በተስፋ የሚኖርበትን ሃይማኖት በሆነ ባልሆነው እየነካኩ ዝም ብሎ የተኛውን መቆስቆስ  ወደበጎ አያደርስም።  ለማንኛውም መንግሥት ወደክንዱ ሳይሆን ወደልቡ ይመለስ።  «እመ እግዚአብሔር ኢሐነጸ ቤተ፤ ከንቶ ይጻምዉ እለ የሐንጹ። እመ እግዚአብሔር ኢዐቀበ ሀገረ ከንቶ ይተግሁ እለ ይኄልዉ»   «እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ፥ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ እግዚአብሔር ከተማን ካልጠበቀ፥ ጠባቂ በከንቱ ይተጋል» መዝ ፻፳፯፤፩ ጉልበት ብቻውን ልብ ለሌለው ደርግም አልጠቀመም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከታች ለማንሳት ወደፈለግነው ጉዳይ እናመራለን። ኢህአዴግ ከሚታማበት ችግሮች አንዱ እስከአሁን ድረስ በየሚዲያው የምንሰማቸውና የምናነባቸው ነገሮች የእስልምና ሃይማኖት መብት ኢትዮጵያ ውስጥ እንደተረገጠ እያስተጋቡ ሆነው መገኘታቸው ነው። ከዚህ በፊት በዚህ ጉዳይ ላይ በሁለት ክፍል ብሎጋችን ጽፋለች። እውነት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሌሎች ሃይማኖት በተለየ የእስልምና ሃይማኖት ጭቆና አለ? ብለን ጠይቀናል። ከዚያም በተለየ መልኩ በአፍሪካው ክፍለ አህጉር የእስልምና አክራሪነት እየሰፋ አልመጣም? ኢትዮጵያስ ከእስልምናው የአክራሪነት መንፈስ እንቅስቃሴ ውጪ የሆነች ሀገር ናት? ብለንም ጠይቀናል። ኢህአዴግን በመጥላት ወይም የሚጓዝባቸውን መጥፎ ስልቶች በመመልከት ብቻ ያፈጠጠውን ሀቅ መካድ ይቻላል? ብለናልም። የኢህአዴግን ድርቅናና ግትርነት ለመነቅነቅ አሁን ካለው የትኛውም አኩራፊ ኃይል ጋር አንድ መሆን ነው የሚል መርህ እውነቱን በመጨፍለቅ ወደእርስ በእርስ ፍጅት ሊያስገባን ይችላል። ስለዚህም በኢትዮጵያችን ውስጥ ስላለው የእስልምና እንቅስቃሴ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጠባዩን የተመለከተ የጥናት ጽሁፎችን የዳሰሱ መረጃዎችን ለአስተዋዮች ለማቅረብ ወደናል። እውነታውን ማሳየት ችግሩን አውቆ በጋራ የምንኖርበትን ሀገር ለመገንባት ይረዳናል። ምድሪቱን እንድንጠብቃትና እንድንንከባከባትም ከእግዚአብሔር አደራ አለብን። ዘፍ ፪፤፲፭
እስልምና በኢትዮጵያ ታሪክ በሚል ርዕስ ከሚቀርበው ሦስት ሰፋፊ ተከታታይ ጽሁፎች ውስጥ የመጀመሪያውን እነሆ ብለናል።

ክፍል  
             የጽሑፉ ባለቤቶችለእስልምና መልስ» አዘጋጆች ነው)

በወቅቱ ያለው የሙስሊሞች የተቃውሞ ሰልፎች ቅንብር እና ይህንን አስመልከቶ የገዢው ፓርቲ ወስዶ የነበረው አሁንም እየወሰደ ያለው እርምጃ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው፡፡ ለዚህ የሙስሊሞች ተከታታይ የተቃውሞ ሰልፎችና ስር የሰደዱ የተለያዩ ድርጊቶች ምክንያቱና የትኩረት አቅጣጫው ምንድነው? ለአገሪቱና በአገሪቱ ላይ እንዲኖር ለምንፈልገው አብሮ ማደግ፣ ሰላም፣ የሰብዓዊ መብት መጠበቅና የእምነት ነፃነት ይጠቅማልን? .. የሚሉ ጥያቄዎችን ማንሳትና መወያየት ለመፍትሄም መዘጋጀት አስፈላጊ ናቸው፡፡ ማንኛውም የኢትዮጵያ ዜጋ በሚከተለው ሃይማኖት፣ የፖለቲካ አመለካከት፣ ዘርና ፆታ ተፅዕኖ ሳይደረግበት የሚኖርባት ኢትዮጵያን ማየት ሁሉም ሰው መውደድና መፈለግ ለዚህም የተቻለውን ጥረት ማድረግ ይኖርበታል፡፡ 
እስልምና በኢትዮጵያ ታሪክበሚለው አምድ ስር በታሪክ ተመራማሪዎች የቀረቡ ታሪካዊ እውነቶችን በተከታታይ እናቀርባለን፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የአሁኑ ጽሑፍ የሚዳስሰው ሁለቱ ዋና ዋና የሙስሊም የአመለካከት ትግሎች ወይንምሙስሊማዊ ርዕዮተ ዓለሞች ከየት መነጩ ወዴት ተሰማሩ አሁን በዓለማችን ላይ ምን ተፅዕኖ አላቸው፣ በተለይም የኢትዮጵያን የወደፊት እጣ እንዴት ሊቀርፁ ወይንም ቀለል ባለ ቋንቋ ሊነኩ ይችላሉ የሚለውን ለማሳየት እንደ መጀመሪያ ታሪካዊ መነሻ የቀረበ ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ጽሑፍ በአንድ ክፍል ማቅረብ ከባድ ስለሚሆን አንባቢዎችንም እንዳያሰለች በሦስት ክፍሎች ለማቅረብ ተገደናል፡፡
የዚህ ገፅ አዘጋጆች ፖለቲከኞች ወይንም የአንድ የፖለቲካ ቡድን ደጋፊዎች አይደለንም፣ እኛ ተራ ኢትዮጵያውያን ነን፡፡ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ የአገሪቱ ወቅታዊና የወደፊት ጉዳይ ያሳስበናል፡፡ የኛ ድረ ገፅ ስያሜውለእስልምና መልስየሚልና ትኩረቱም መንፈሳዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ በአገሪቱ ውስጥ አሁን ባለው የእስልምና እምነት እንቅስቃሴ አማካኝነት እየቀረቡ ያሉትን ወቅታዊ ጽሑፎች፤ ታሪካዊ መረጃዎችን መከታተል እና ለነዚህም መልስ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ በመሆኑምየእስልምና ታሪክ በኢትዮጵያአምድ ስር እኛ ያገኘናቸውን ግንዛቤዎች ለአንባቢዎች ለማስተላለፍ እንሞክራለን፡፡
አዲስ የኢትዮጵያ ታሪክ፡
የአሁኗ ኢትዮጵያ 18ኛው መቶ ዘመን መጨረሻ ላይ በፖርቹጋሎች እርዳታ ተመሰረተች የሚሉ ጽሑፎች በተለያዩ የሙስሊም ጸሐፊዎች በተለያዩ ቦታዎች እንዲሁም ቋንቋዎች እየተሰራጩ ነው፡፡ እነዚህ ታሪኮች እውነት ናቸውን፣ ለመሆኑ ዓላማቸው ምንድነው? ኢትዮጵያውያንን ይጠቅማሉ ወይንስ ይጎዳሉ? በኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚታተመውየሰላምታ መጽሔትሐሙስ ነሐሴ 3 2004 በድረ ገፅ ላይ ባቀረበው አምድ ላይ ጽሑፍ ያበረከተው Najib Mohammed የሚባል ሰው ነው፡፡ እርሱም ጽሑፉን ሊያጠቃልል ሲል በአስራ አራተኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ የሰባት እስላማዊ ሱልጣኔቶች አገር እንደነበረች ጠቅሶ አሁን የምናያት ኢትዮጵያ 18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ በፖርቱጋሎች እርዳታ እንደተመሰረተች አቅርቦልናል፡፡ ናጂብ ይህንን አዲስ ታሪክ ያስቀመጠው ማስረጃዎችን በመጥቀስ ታሪክ በማገናዘብ አይደለም፤ የጻፈውን እውነታ እንድናገናዝብም የሰጠው ምንም ማስረጃ የለም፡፡
የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ፀደይ በምትባል ጸሐፊ የተቀናበረ ሌላ ‘A leap of Faith’ tseday.wordpress.com/tag/harar/ የሚልና ጥሩ ጥናታዊ ታሪካዊ ጽሑፍን አንብቧል፡፡ ይህ የፀደይ ታሪካዊ ጽሑፍ እስልምና በኢትዮጵያ ላይ በግራኝ መሐመድ በኩል ያደረሰውን ጥፋት አሳይቷል፡፡ ፖርቹጋሎች የኢትዮጵያን መንግስት ከእስልምና ውድመትና እስላማዊ አገር ከመሆን እንዳዳኗት ያሳያል፡፡ በእርግጠኝነት ታሪክ የመሰከረው ኢትዮጵያ ለእስልምና በዓለም ላይ መኖር ከየትኛውም የዓለም ክፍል በበለጠ መልኩ ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳደረገች ነው፡፡
አዲሱ የኢትዮጵያ ታሪክ እየተውጠነጠነ ያለው የሙስሊም የመጀመሪያ ስደትንና ከዚያ በመያያዝ ወደ እስልምና ተለውጧል የመጀመሪያ የእስላም ንጉስ ሆኗል፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ የእስላም አገር ናት የሚለው ታሪክ ነው፡፡ ፀደይ ባቀረበችው ጽሑፍ ላይ ይህ በዚያን ዘመን ተለወጠ ተብሎ የሚጠራው ንጉስ ንጉስአሻማወይንምነጃሺበኢትዮጵያ ታሪክም ሆነ በኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ታሪክ ውስጥ እንደማይታወቅ ነው፡፡
ይሁን እንጂ በዶ/ መስከረም መላኩ በተሰራ የምርምር ጽሑፍ  ‘Comparative Religion’ submitted to Spiritual institute of New York 2009 Addis Ababa Ethiopia ጽሑፍ፣ ጽሑፉን ከሚቀጥለው ድረገፅ ላይ አግኝቶ ማንበብ ይቻላል፡፡ dcbun.tripod.com/id18.html የሰፈረው አስገራሚ አዲስ ታሪክ ነው፡፡ ንጉስ እስልምናን ከተቀበለ በኋላ መሐመድ ስሙን አህመድ አል-ነጃሺ ብሎ እንደቀየረው፣ ቤተሰቦቹ እስልምናን እንደተቀበሉ፡፡ ከዚያም ቀጥሎ መንግስቱን ከአክሱም ወደ ውቅሮ ከቀየረ 15 ዓመታት በኋላ እንደሞተ ይናገራል፡፡ የዶ/ መስከረም ጽሑፍ ለዚህ ታሪክ እውነተኛነት የመሐመድ 43 ቀጥታ ዘር የሆነውንና የውቅሮውን መስጊድ የጎበኘውን / ኤም ኤን አለምን ጠቅሶ፣ በነጃሺ አዲስ እራዕይ መሰረት ንጉሱ እስልምናነ በኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉ እንዳስፋፋ የዚያም ውጤት እስልምና እስከ አልጀሪያ ሞሮኮ ድረስ ክፍት በርን እንዳገኘ ያስረዳል፡፡ ይህ ጽሑፍ እንዳለ በሌላ / ሰላሃዲን እሸቱ በተባለ ሰው ደግሞ በሌላ መልኩ “Authentic History of King Negash of Abyssinia (Currently Ethiopia)” በሚል ርዕስ ቀርቧል፡፡
እንዲህ ዓይነት ጽሑፎች ሲዘጋጁ የበለጠ እውነት እንዲመስሉ ልዩ ልዩ ማስረጃ ሰጪ የሆኑ ቅንብሮች ማያያዝ የተለመደ ሆኗል፡፡ በፀደይ ጽሑፍ ስር ተያይዞ የቀረበውን ጥናታዊ ፍልም እንደምሳሌ ለመጥቀስ እወዳለሁ፡፡ ጥናታዊው ፊልሙ የተቀናበረው Dr. Abdullah Hakim በተባለ አሜሪካዊ ዜጋ ሲሆን ርዕሱ ‘Untold Ethiopia an Islamic Journey’ የሚል ነው፡፡ የጥናታዊ ፊልሙ ዓላማ ኢትዮጵያ ድብቅ የሆነ እስላማዊ ታሪክ እንዳላት ከሐረር ጀምሮ አክሱም ድረስ የዘለቀ እና የነጃሺንም ተረቶች ሁሉ ያያዘ ነው፡፡ የመናገር፣ የመጻፍና ፊልም የመስራትን መብትን ተጠቅሞ ማንም ሰው የፈለገውን ለማቅረብ መብቱ ሊጠበቅለት እንደሚገባ እኛ እናምናለን፣ አንባቢዎች ግን የቀረቡላቸውን ጽሑፎችም ይሁን የፊልም ቅንብሮች ከታሪክና ከእውነት ጋር የማገናዘብ ግዴታና በእውነት ላይ መቆም ስህተትንም ባገኙት አጋጣሚ መግለጥ ይኖርባቸዋል፡፡
እንደዚህ ዓይነት እንቅስቃሴዎች በረቀቀና ብዙዎች ባልነቁበት መንገድ የኢትዮጵያ ታሪክ በአዲስ መልኩ እየተጻፈና እየተቀናበረ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ እንቅስቃሴው ስር የሰደደ ታሪካዊና ጥልቅ እንዲሁም በሚገባ በዕቅድ ተይዞ የሚመራ ውጤቱም ለአገሪቱ አስፈሪ ነው ብሎ መናገር ስህተት አይመስለንም፡፡
የዛሬው ጽሑፍ መሠረት፡
ይህ ጽሑፍ ሙሉ ለሙሉ የተመሰረተው የታሪክ ተመራማሪውና እጅግ ብዙ አስደናቂ ኢትዮጵያዊ ታሪኮችን በመፈልፈል ኢትዮጵያና እስላማዊ እንቅስቃሴ ላይ የምርምር ስራ በሰራው በፕሮሴፈር ኤርሊች ስራ ላይ ነው፡፡ በተለይም ፕሮፌሰር ኤርሊች ከሌላ ዕውቅ የታሪክ ፕሮፌሰር ከሙሰጠፋ ካብሃ ጋር ባዘጋጁትና በካብሪጅ ዩኒቨርሲቲ በታተመው የጆርናል ጽሑፋቸው Mustafa Kabha and Haggai Erlich, "The  Ahbash and the Wahhabiyya -- Interpretations of Islam",  International Journal of Middle East Studies,  2006, pp. 519 - 538. ላይ የተመሰረተ ነው፡፡
ፕሮፌሰር አርሊችየክርስትያን ኢትዮጵያ ዓይናችን እያየ አዲስ ትርጉም ልትይዝ ምንም አልቀራትምበማለት ስጋቱን ከአቅጣጫ ጠቋሚ እውነቶች ጋር ‘Saudi Arabia & Ethiopia’ በተባለው መጽሐፍ ውስጥ አቅርቧል፡፡ኢትዮጵያ አዲስ ትርጉም ልትይዝ ነውየሚለውም እስላማዊ አገር እንድትሆን ከፍተኛና ስር የሰደደ ታሪካዊ እንቅስቃሴ መኖሩን በመጠቆም ነው፡፡ በእርግጥ አስገራሚና አስደንጋጭ ትዝብት ነው፡፡ እርሱ በታሪክ ጥናት ላይ ተመስርቶ እንደተናገረው ሊሆን ይችላል ወይንስ አይችልም የሚለው ከዚህ ጸሐፊ ችሎታና ግምት በላይ በመሆኑ ጊዜ የሚነግረን ነገር ነው በማለት ብቻ ያልፈዋል፡፡
ከስድስት ወራት በላይ ያስቆጠረው የሙስሊሞች የተቃውሞ እንቅስቃሴ ቀላል አይደለም፡፡ ብዙ ዋጋም እያስከፈለ ነው፡፡ ከበስተኋላ ሆኖ የሚመራው አካል እና ርዕዮተ ዓለም ይኖራልን? ለዚህ ጥያቄ አጭሩ መልስ ምንም ጥርጥር የለውም ነው፡፡ የሙስሊሞቹ የተቃውሞ ሰልፍ በተለያዩ የፖለቲካ፣ የሃይማኖት ተቋማትና ጋዜጠኞች ከፍተኛ የድጋፍ ሽፋን ተሰጥቶታል፣ መግለጫዎችም ማሳሰቢያዎችም ቀርበዋል፡፡ የተሰጡትን የተለያዩ ድጋፎች፤ ከኢአግ ጀምሮ የወጡትን መግለጫዎች፤ ሁሉንም ለማለት ባይቻልም አብዛኛዎቹን ጸሐፊው በቅርቡ ለመከታተል ሙከራ አድርጓል፡፡ ስለዚህም የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪካዊ እውነታዎችን ከምርምር ማህደራት መመልከት አለበት በማለት ያምናል፣ ይህም መጪዎቹን ጊዜዎች ለመተለምና መጪውን ትውልድ ለመመስረትና ለመቅረፅ የሚቻለውን እንዲያደርግ ይረዳዋልና፡፡
የታሪክ ተመራማሪዎቹ አመለካከት፡
ሁለቱ የታሪክ ተመራማሪዎች እንደሚሉት ከሆነ እስልምና ከፍተኛ የሆነ ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖ ቢኖረውም አገራዊና ማህበረሰባዊው ተፅዕኖም እንዲሁ ከፍተኛ እንደሆነ ነው፡፡ በጆርናላቸው ላይ እንዳሰፈሩትና እውነትም እንዳስተዋሉት ሁሉ እስልምና ሌላውን ማህበረሰብ መቅረፅ ብቻ ሳይሆን እንዳለበት አገርና ማህበረሰብም እራሱ የሚቀረፅ እንደሆነና ይህንንም በዘመናት እንዳሳየው ይገልፃሉ፡፡ ይህንን እውነት ለማሳየት እንደዋነኛ የሰርቶ ማሳያ ቦታ የሚጠቀሙበት የኢትዮጵያን ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም የእስልምና አገር አቀፍም ሆነ ዓለም አቀፍ ቅርፁ ከኢትዮጵያ ጋር የተቆራኘ ነው ይላሉ፡፡
እኛ ሁላችንም እንለው የነበረውን  ኢትዮጵያ የክርስትያን ደሴትየሚለውን አባባል ጥንታዊነት የታሪክ ሊቃውንቱ በጆርናላቸው ላይ ጠቀስ አድርገውታል፡፡ ይህም አገሪቱ በእስላም አገሮች የተከበበችና በዋና ዋናዎቹ እስላም አገሮች አፍንጫ ስር በመሆኗም የማያቋርጥ ትኩረት እንደተደረገባት ጠቁመዋል፡፡ ይህ የእነርሱ ታሪካዊ የምርምር ግንዛቤ በምዕራቡ ዓለም ላሉ የታሪክ ተመራማሪዎችና በብዙ ኢትጵያውያኖች፤ ማለትም ከላይ እንደጠቀስኩት በፖለቲከኞችና በአንዳንድ የሃይማኖት ቡድኖች ዘንድ በጭራሽ የታየ አይመስልም፡፡ በአገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ሙስሊሞች ዘንድ ስለ ኢትዮጵያ ያለውን አመለካከት ስረ መሰረት በእርግጥ ብዙዎች አላጤኑትም፡፡ እንደ እውነቱ ግን የኢትዮጵያ ጉዳይ የኣለም አቀፍ ሙስሊሞች ጉዳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ጉዳይ ለሙስሊሞች ትርጉም ያለውና በጣም የሚያስቡበት ጉዳይ ነው፡፡
ሁለቱ የታሪክ ፕሮፌሰሮች የሚሉትየኢትዮጵያ ጉዳይ በአሁኑ ጊዜ ላለው ዓለም አቀፍ እስልምና እጅግ በጣም ከፍተኛ አጀንዳ እንደሆነ ነው፡፡ለዚህም ነው ከላይ የጠቀስኳቸው ዓይነቶች እጅግ ብዙ ታሪክ መሳይ ጽሑፎችና ጥናታዊ ፊልሞች መቀናበርና መሰራጨት ያለባቸው፡፡
ሁለቱ እስላማዊ አመለካከቶች
ኢትዮጵያ የሁለት ዓይነት አለም አቀፍ የእስልምና ርዕዮተ ዓለም የትግል መድረክ ናት የሚሉት የታሪክ ተመራማሪዎች ሁለቱ ቡድኖች የሚከተሉት መሆናቸውን ያስረዳሉ፡
        አንደኛው፡አል-አህባሽየሚባለውና ዋና መስሪያ ቤቱ ሊባኖስ የሆነው ዓለም አቀፍ እስላማዊ ድርጅት ሲሆን በብዙዎች ዘንድ የሚታወቀውኢትዮጵያውያኖቹበሚባለውም ስያሜ ጭምር ነው፡፡
    ሁለተኛው፡ዋሃቢያየሚባለው አለም አቀፋዊ እስላማዊ ድርጅት ሲሆን በሳውዲ አረቢያ መንግስት የሚደገፍና አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ተቃውሞ እንቅስቃሴ የሚመራው ነው፡፡
 ምሁራኖቹ ታሪክን ቆፍረውና አጥንተው የሚነግሩን እነዚህ ሁለቱም ድርጅቶች በቀጥታ ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ነው፡፡ ሁለቱ ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግንኙነትና በውስጣቸው ያለውን ቅራኔና ጥላቻ መረዳት ለኢትዮጵያውያኖች ሁሉ ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም በአሁኑና በመጪው ጊዜ አገሪቱ ምን ዓይነት ሁኔታ ፊት ለፊቷ እንደተጋረጠና እንዴትስ ከዚያ አዘቅት ልትወጣ ትችላለች የሚለውን በትክክል ለመረዳት ያስችላል፡፡ በፕሮፌሰሮቹ ጥልቅ ጥናት መሰረትና አሁን በአገሪቱ እየተካሄደ ያለው ትግል የአጠቃላይ የዓለም አቀፉ ሁለት እስላማዊ ርዕዮተ ዓለም ትግል ነፀብራቅ ነው፡፡ ማለትም ኢትዮጵያ ለሁለት እስላማዊ ትግሎች የጦርነት ሜዳ ስትሆን፣ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ደግሞ የዚያ ጦርነት ተፋላሚ መጠቀሚያዎች ናቸው፡፡
የሁለቱንም እስላማዊ ርዕዮተ ዓለም በዝርዝር የምንመለከት ቢሆንም ፍንጭ ለመስጠት ያህል አንባቢው የሚከተሉትን እንደ አሲድ የመለያ ምልክት ሊወስዳቸው ይችላል፡፡
የአል-አሕባሽን ርዕዮተ ዓለም የሚከተሉት ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ካሉ፣ በየትኛውም አገር ካለ የገዢ መደብ ጋር በኢትዮጵያም ጭምር እስልምና በሰላም መኖር ይችላል የሚል አመለካከት ያለው ነው፡፡
የዋሃቢዝምን አመለካከት የሚደግፉት ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች እስልምና ባለበት አገር ሁሉ የበላይነትን መያዝ አለበት የሚሉት ናቸው፡፡ ለእነዚህ መለያቸውነጃሺ በተመለከተ ከተፈጠረው ተረት (ይህ ጸሐፊ የነጃሺን ታሪካዊ እውነታ በቅርቡ ያቀርባል) ጋር ያላቸው ቀረቤታ ነው፡፡ በነጃሺ ድረ ገፅ ላይ የተጻፉትን ወቅታዊ አንቀፆች ስታነቡ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች በተለይም የዋሃቢዝምን የሚደግፉት እንቅስቃሴያቸውየጊዜ ፈንጂሆኖ ለመፈንዳት ጊዜ የሚጠብቅ እንደሆነ ኢትዮጵያዊ የሆነና ይችን አገር እወዳለሁ የሚል ሁሉ መረዳት ያስፈልገዋል፡፡ blog.ethiopianmuslims.net 
የአል-አሕበሽ ወይንምኢትዮጵያዊያኖቹስያሜ ታሪካዊ ግንዛቤ፡-
ኢትዮጵያዊያኖቹእነማናቸው፣ የሚወክሉትስ ምን ዓይነት የእስልምና ርዕዮተ ዓለምን ነው? የእነርሱ ስም የሚወክለውስ መልእክት ምንድነው? የሚሉትን ጥያቄዎች የታሪክ ተመራማሪዎቹ የመለሱት እንደሚከተለው ነው፡፡አል-ሐበሻወይንምአል-አህባሽ” (እንዲሁም ደግሞ አል-ሁባሻን፣ አል-ሁቡሽ) የሚለው ስያሜ ኢትዮጵያውያን በጥንታዊ አረቦች የሚታወቁበት ስምና ከቀይ ባህር ማዶ ያሉ የአረቦች ጎረቤቶች አፍሪካውያን መጠሪያ ነው፡፡
ይሁን እንጂ በእስላማዊው ዓለም ፅንሰ ሐሳብ ውስጥ አል-ሐባሻ የሚለው መጠሪያ  በጣም ጠቃሚ የሆነ ሌላም ትርጉም እንዳለው የታሪክ ሊቃውንቱ አሳይተዋል፡፡ እንደሚታወቀው ሁሉ የኢትዮጵያ መንግስት በአብዛኛው በክርስትያኖች የተያዘ ቢሆንም በጣም ብዙ ሙስሊሞች ስለሚኖሩበት ሙስሊሞችም የሚኖሩበት አገር ነው፡፡ሐበሻየሚለውም የአረብኛ ቃል በአፍሪካ ቀንድ ላይ ላሉት ክርስትያኖች ብቻ የተሰጠ ሳይሆን ለአጠቃላይ ሕዝቡ ነውና ሙስሊሞችንም ይጨምራል፡፡ በነ ፕሮፌሰር ኤርሊች ጥናታዊ ጽሑፍም መሰረትሐበሻየሚለው ቃል በሃይማኖት ላይ ያተኮረ ሳይሆን በቆዳ ቀለም ላይ ነው፡፡ በአረቦችና በእስልምና ዓይን አል-ሃባሻ ከጥቁር አፍሪካውያን ማለትምዙኑጅይሏቸው ከነበሩት ከሱዳኖች የተለዩ ነበሩ ይሉናል፡፡
የታሪክ ተመራማሪዎቹ እንደሚሉትሓባሺ ሙስሊሞችን በተመለከተ ሁለት የፅንሰ ሐሳብ ክፍፍል ነበረ፡፡ ሐበሾች ይወሰዱ የነበረው ከሌላ የአፍሪካ ባሪያዎች በጣም ጥሩዎቹ ተደርገው ነበር፣ እስከ አንደኛው የዓለም ጦርነት ድረስ በአሪቢያ ውስጥ በቆየው የባሪያ ንግድ ከኢትዮጵያ ይጋዙ ከነበሩት ሐበሻዎች ውስጥ ብዙዎቹ አኒሚስቶች (ተፈጥሮ አምላኪዎች) የነበሩ ሲሆን ጥቂቶቹ ግን ክርስትያኖች ነበሩ፡፡ ስለዚህም ፕሮፌሰሮቹ የሚሉትሐበሻየሚለው ቃል በእርግጥ ሃይማኖታዊ ያልነበረ፣ ነገር ግን መጠነኛ የሆነ የዘር ዝቅተኝነትን የሚያንፀባርቅ መጠሪያ እንደነበር ነው፡፡ ከዚህም ቀጥሎ ተመራማሪዎቹ የሚከተለውን ነገር በምርምራቸው ላይ አስፍረዋል ይህም፡የሰው ዘር ሁሉ እስልምናንለሚያራምዱት ማለትም ዘረኛ ያልሆኑት ዘመናዊና ዓለም አቀፋዊ ሙስሊሞች ዘንድ የክርስትያን ኢትዮጵያ ተቀባይነት ይያያዝ የነበረው የሐባሺ ሙስሊሞችን አሁንም ከማመስገንና ከማድነቅ ጋር ነው፡፡ ስለዚህም ብዙ ጠቆር ያሉና ድብልቅ ሙስሊሞች በቅፅል ስም የሚጠሩትአል-ሐበሺተብለው ነው፡፡ እንደተመራማሪዎቹ ጽሑፍ በታሪክ በተለያየ መደብ ላይ የነበሩ ብዙ ታዋቂ ሰዎች ላይ በዚህ ስም ተጠርተውበታል፡፡ እጅግ በጣም ብዙ ትውፊቶችም ለአሁኑ ጊዜ ሙስሊሞች ጥሪ የሚያቀርቡት ሙስሊሞች ሁሉ ኢትዮጵያውያንን እንዲያከብሯቸውና እንዲያውም እነርሱን እንደመሪዎች ጭምር እንዲቀበሏቸው ነው፡፡ በዘመናትም ባሉ እጅግ በጣም ብዙ ጽሑፎች ውስጥ ሙስሊም-ኢትዮጵያውያንን የሚያነሱና የሚያወድሱ ጽሑፎች እንዳሉ የታሪክ ሊቃውንቱ አሳይተዋል፡፡
እነዚህም ሁሉ ጽሑፎች ለሙስሊሞች ሁሉ ጥሪ የሚያደርጉት መቻቻልን እንዲያሳዩና በተለይም ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በመቻቻል እንዲይዙት ነው፡፡ ይህንን በተመለከተ እነ ፕሮፌሰር ኤርሊች በምርምር ጽሑፋቸው ውስጥ ከዚህ በታች ያሉትንና ከብዙ ጥቂት ያሏቸውን የመቻቻል ምሳሌዎች ጠቅሰዋል፡
ጃላል አል-ዲን አል-ሱዩት 15ኛው ክፍለ ዘመንየኢትዮጵያውያንን ደረጃ ከፍ አድርጎታል እንዲሁም አህድ አል-ሂፍኒ አል-ኪናይ አል-አዛህሪበኢትዮጵያውያን ታሪክ ውስጥ ውቦቹ አልማዞች20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን፡፡ ከታወቁት (እውቅና ከላቸው) የኢትዮጵያ ሙስሊሞች እንደ ቢላል ቢን ራባህ (ቢላል አል-ሃባሺ) የመጀመሪያው ሙአዲዲን እንዲሁም እራሱ ናጃሺ እጅግ በጣም እስላማዊና ታሪካዊ ሰዎች እንዲሁም ቅዱሳን ሁሉ ተብለው ተቆጥረው ነበር፡፡ 16 መቶ ዘመን በመዲና የተጻፈ ሌላ ጽሑፍ ደግሞ (1583-4) የሚከተለውንና አረቢያኖች ስለባርነትና ስለሐበሻ ያላቸውን አመለካከት ይዟል፡
ለአላህ ምስጋና ይሁን ሰውን ከአፈር ጭቃ የፈጠረውና አንዳንዶቹን ከሌሎቹ የመረጠው፡፡ በእነርሱ መካከል ያለው ልዩነት ሰማይ ከምድር እንደሚርቀው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ እያንዳንዱ ቡድን አላህን ያመሰግናል ያስደስታልም፡፡ እርሱም ጌታዎችና ባሪያዎች ገዢዎችና ተገዢዎች አድርጓቸዋል፡፡ አላህ የኖህን አንዳንድ ዘሮችን ለይቶ በነቢይነትና በባለስልጣንነት፣ ለአንዳንዶቹ ደግሞ አገልጋይነትንና ባርነትን እስከ ትንሳኤ ቀን ድረስ መድቦላቸዋል፡፡ ... እርሱም የኢትዮጵያውያንን ቡድኖች ... እንደ ቢላል እንደ አል-ናጃሺ እንዲሁም ሌሎቹንም በእርሱ ያመኑትንና እስልምናን የያዙትን በፀጋና በመሪነት ለይቷቸዋል፡፡ ብዙዎቹም የነቢዩ ተከታዮች እንዲሁም ቅዱሳን የሆኑ ፃድቃን፣ በጣም ታዋቂ ሰዎች ሆነዋል በምድርም በገነትም እንዲሁም የሃይማኖት መሪዎችና ጊዜያዌ መሪዎች ሆነዋል፡፡ይላል፡፡
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን በሁለት ዓይነት ክፍል ከፍሎ መመልከት ግልፅ እንደሆነ ምሁራኑ ያስቀምጡና ለዚህ ጥሩ ማስረጃው በሱኒ ባህል ውስጥ ያለውንና፡በእናንተ ላይ ማንም በስልጣን ላይ ይሁን ታዘዙ፣ ምንም እንኳን እርሱ አፍንጫው ደፋጣ ኢትዮጵያዊ ባሪያም ቢሆንየሚለውን አባባል ይጠቅሳሉ፡፡
ስለዚህም ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በአረቦች ዘንድ የሚታዩት በአንድ በኩል ምንም ባሪያዎች ቢሆኑ በእስልምና ውስጥ ብቃት ያላቸው መሪዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ሲሆን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያውያንን በማህበረሰቡ ውስጥ በዝቅተኛው ደረጃ ላይ ያስቀምጣቸዋል ይላሉ፡፡ ለዚህ ሁለት ከፍል ላለው የአመለካከት ውዝግብ ግልፅ የሆነውና በሕይይት ያለው ማስረጃ ሼክ አብደላ አል ሃባሺ አል ሃራሪ የአሁኑ የአል-አህባሽ ዓለም አቀፍ እስላማዊ ማህበር መሪና በሊባኖስ የሚኖረው እስላማዊ ሊቅ ነው ይላሉ፡፡
ኢትዮጵያ የእስልምና ጠላት፡
የኢትዮጵያ ታሪክ በሰላምታ መጽሔት በናጂብ መሐመድ እንዲሁም በፀደይ በዌብ ሳይት እንደቀረቡት 18ኛው መቶ ዘመን ታሪክ ሳይሆን በመሐመድም ዘመን የታወቀ ነበር፡፡ የሐበሾቹ ሐገር ኢትዮጵያ ክርስትናን እንደ ሃይማኖቷ አድርጋ የተቀበለችው የእስልምናው መስራች መሐመድ ከመነሳቱ ከሶስት መቶ ዓመታት በፊት እንደነበር በታሪክ የታወቀ ነው፡፡ ከላይ የጠቀስኩት የፀደይ ጽሑፍና የእነ ፕሮፌሰር ኤርሊቺም ጥናት የሚያሳየው አብርሃ የተባለው ክርስትያን የኢትዮጵያ ንጉስ 570 . በየመን ይገዛ እንደነበር እንዲያውም በመካ ያለውን የከዓባ ጣዖት ለማፍረስ በዝሆኔዎቹ ዓመት ተብሎ በሚታወቀው ዓመት ዘምቶ እንደነበረ ግን እንዳልተሳካለት ነው፡፡ በቁርአን ምዕራፍ 105 የተጻፈው የዝሆኖቹ ጦርነት አፈታሪክ ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ አገሪቱ በአረብ ባህረ ሰላጤ ጉዳዮች ላይ ለዘመናት ትካፈል ስለነበር እንደ ክርስትያን አንድ አማላክ አምላኪሌላአገር ተብላ በመሐመድና በእርሱ ዘመን በነበሩት ሁሉ ዘንድ የታወቀች ነበረች፡፡ በእርግጥም ኢትዮጵያ በእስልምና እምነት እንቅስቃሴ የውጭ ግንኙነት የመጀመሪያዋ አገር ናት፡፡ ስለዚህም 615-616. ለተደረገው ሂጂራ ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ አገር ነበረች፡፡ ሙስሊሞች ነጃሺ በማለት የሚጠሩት ክርስትያኑ የኢትዮጵያ ንጉስ  በዚያን ጊዜ ለነበሩት አጠቃላይ እስላማዊ ማህበረ ሰብ ለማለት ይቻላል የፖለቲካ ጥገኝነትን ሰጥቶ ነበር፡፡
በሙስሊሞች ሁሉ ዘንድ ፃድቁ ተብሎ አሁንም የሚጠራው የክርስትያን ኢትዮጵያ ንጉስ ሙስሊሞችን ያዳነውና ዘለቄታዊ የቸርነት መልእክትን ለሙስሊሞች ዓለም ሁሉ የሰጠው አገሪቱ የክርስትያን አገር ስለነበረች እንደነበር ግልፅ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ከላይ እንደጠቀስኩት ኢትዮጵያ የራሷ ሕጋዊ አስተዳደርና የአገር ክልል የነበራት አገርም ነበረች፡፡ ይህም ለማንም ግልፅ የሆነ እውነታ ነበር ነቢዩ የሚከተለውን አባባል ተናግሯል ተብሎ እንዲነገርለት ያደረገውኢትዮጵያውያንን ተዋቸው እናንተን እስካልነኳችሁ ድረስ” (utruku al-Habasha ma tarakukum)፡፡ ስለዚህም አሁን የምናያት ኢትዮጵያ በፖርቱጋሎች እርዳታ የተገኘች ናት የሚለው አዲስ ታሪክ የሺዎች ዓመታትን ታሪክ የሚያዛባና መሰረተ ቢስ ነው፡፡
ይሁን እንጂ የታሪክ ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት በሌላ ጎኑ ደግሞ 615-616 ከሆነውና ከታወቀው የክርስትያን ኢትዮጵያ ደግነት ታሪክ የተለየ እንዲሁም በጣም አከራካሪ የሆነ ትውፊት ቆየት ብሎ መጥቷል፡፡ እርሱም 628 ማለትም ኢትዮጵያ ስደተኞቹን ካስተናገደች ከአስራ ሁለት ዓመት በኋላ የኢትዮጵያው ንጉስ ነጃሺ እራሱ እስልምናን እንደተቀበለ፤ በዙሪያው የነበሩት የኦርቶዶክስ ካህናትና የራሱ ሕዝብ ግን እንዳልተቀበሉት የሚነገረው አፈታሪክ ነው፡፡ እንደ ምሁራቹ ጥናታዊ ዘገባ ይህ አፈታሪክ መሰረታዊ የሆነ ታሪካዊ የእውነትነት ድጋፍ የለውም አወዛጋቢም ነው፡፡ ይሁን እንጂ ብዙ የፈጠራ ጽሑፎችና ፊልሞች ተቀናብረውለታል፡፡ በጥልቅና በጥንቃቄም የሚመራውክርስትያን ኢትዮጵያ “”ሌላ”” ናት ወይንምክርስትያን ኢትዮጵያን አትንኳትየሚለውን አባባል ወደ ጎን ተጥሎክርስትያን ኢትዮጵያ ጠላት ናትደግሞምክርስትያን ኢትዮጵያ የመጀመሪያው እስላም ንጉስ የተገደለባትማለትም በመጀመሪያ ትርጉም ወደ ተቃራኒና ሕጋዊ አገር አለመሆኗን ወደሚያሳይ ጥላቻ፤ነው፡፡
በክርስትያን ኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ጥላቻ እንዲመጣ ያደረገው የፈጠራ ታሪክኢትዮጵያን ሕገ ወጥለማድረግ የተጠናከረው ከእስልምና አስቀድሞ 570 ዓም ከሆነው ክስተት ጋር ተያይዞ እንደሆነ የታሪክ ተመራማሪዎቹ በጆርናላቸው ላይ ጠቁመዋል፡፡ በዚያን ጊዜ ኢትዮጵያውያኑ የመንን ቅኚ ግዛት አድርገው ይዘው በነበሩበት ሰዓትበዝሆን ዓመት ውስጥበመካ ከተማ ያለውን ጣዖት ካዓባን ለማጥፋት ያልተሳካ ሙከራን አድረገው ነበር፡፡ ከዚህም የተነሳ በኣረብ አገሮች በተለይም በሳውዲ አረቢያ እስካሁን ድረስ የሚፈራው ትንቢት ማለትም (እነዚያ ቀጫጭን እግር ያላቸው ኢትዮጰያውያን በስተመጨረሻው ካኣባን ያጠፋሉ) የሚለው እንደተነገረ ተመራማሪዎቹ ያሳያሉ፡፡ ይህ እንዲህ ከሆነ ለእስልምናው ዓለም ከኢትዮጵያ የበለጠ ጠላት ሊኖር አይችልም፡፡
ስለዚህም በታሪኩ ምርምር መሰረት ኢትዮጵያን በተመለከተ ያሉት ሁለቱ ዓለም አቀፍ እስላማዊ ትግሎች ሁሉ የሚሽከረከሩት በእነዚህ ሁለት ፈርጅ ባላቸው አመለካከቶች ላይ መሆኑን ነው ፕሮፌሰሮቹ የሚያስረዱት፡፡ እነዚህ ሁለት አመለካከቶችኢትዮጵያን አትንኳትእናኢትዮጵያ ጠላት ናትየሚሉት ናቸው፡፡ እንግዲህ አገራችን ኢትዮጵያ ከአረብ አገሮችና ለመካከለኛው ምስራቅም ጎረቤት ከመሆኗ የተነሳ እነዚህ ሁለት ነገሮች የኢትዮጵያን ጉዳይ የዓለም አቀፍ እስላሞች ሁሉ ዋና ጉዳይ አድርገው ያቀረቡታል፡፡
አል-አህባሽና የዋሃቢያ ጠላትነት መሰረት፡
በአሁኑ ጊዜ ያለው የተቃውሞ ሰልፍ መሰረታዊ የሆነ ጥንታዊ ታሪካዊነት አለው፡፡ የታሪኩ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ኤልሪች ያቀረበው የሁለቱ ቡድኖች የጠላትነት ታሪክ መሠረቱ በኢትዮጵያ ከተማ በሐረር ውስጥ ነው፡፡ ሐረር በአፍሪካ ቀንድ የእስላም ዋና ከተማና የሙስሊም ሊቃውንት መኖሪያ ነበረች፡፡ የሐረር የረጅም ዘመን ታሪክ እራሱ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ሙስሊሞችን አጣብቂኝ ሁለት ምርጫ መኖርን ያንፀባርቃል፡፡ በአንድ መንገድ በግንብ የተከበበችው ከተማ 10ኛው ክፍለ ዘመን እስከ 19ኛው ድረስ ግልፅ ካልሆነ ጅማሬ ተነስታ እራሷን የቻለች የእስልምና ግዛት ሆና የራሷ ፖለቲካዊ አመራርን ይዛ ነበረች፡፡ በእነዚያ ዘመናት ውስጥ ሐረር በብዙ መንገድ ከአረቢያ ጋር ግንኙነት የነበራትና የእስላማዊ ጂሃድ ማዕከል ነበረች ይህም በክርስትያን የኢትዮጵያ መንግስት ላይ የተነጣጠረ ነበር፡፡ በሌላ ጎኑ ደግሞ 1887 በኢትዮጵያ ከተወረረች በኋላ ሐረር ያደገችው በኢትዮጵያ ባህል፣ ማህበረ ሰብ እንዲሁም በክርስትያን ባመዘነው የፖለቲካዊ ስርዓት ሁሉ ውስጥ በመዋሃድ እንደ እስላማዊ የመዋሃድ ሞዴልነት ነበር፡፡
ከፋሽስት ጣሊያን የአጭር ጊዜ ወረራ (1936-1941) ትርምስ በኋላ ግን የሐረር ማህበረሰብ እንደገና ወደ እነዚህ ተቃራኒ ታሪካዊ ሁኔታዎች አማካኝነት ተከፋፈለ፡፡ ወደ መካ ሐጂ እንዲያደርጉ በጣሊያኖች ወደ አረቢያ የተላኩት የመሪ ቡድኖች በዋሃቢ ተፅዕኖ በጣም ተነሳስተው ስለነበር 1941-1948 ድረስ ከኢትዮጵያ የመገንጠልን የእስላማዊ ነፃነትን እንቅስቃሴ ሙከራ አድርገው እንደነበር ሊቃውንቱ ያስረዳሉ፡፡ ከዚያም ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ከተደረገ የረጅም ጊዜ ትግል በኋላ ቡድኑ ተሸንፎ እንደተበታተነ፡፡ በመካና በመዲና 1928-1938 የተማረው የእንቅስቃሴውም መሪ ሼክ ዩሱፍ አብደ አል-ራህማን አል-ሃራሪ ወደ ሳውዲ አረቢያ መዲና ተመለሰ፡፡ የሼክ ዩሱፍን ታሪክ በተለያየ መንገድ የሚቀርብ ቢሆንም እርሱ በአሁኑ ጊዜ ዋሃቢ በስተጀርባ ካሉት መሪዎች አንዱ ሲሆን ከአል-አህባሽ ጋር የቃላት ጦርነት ከሚያደርጉት በስተጀርባ ነው፡፡
የአል-አህባሽ መሪ፣ ሼክ አብዳላ ኢብን ሙሐመድ ኢብን ዩሱፍ አል-ሃራሪ 1941-1948 በሐረር እና በኢትዮጵያ በነበሩት ጊዜያት የእርሱ ማለትም የዋሃቢ መሪው ዋና ተቃዋሚ ነበር፡፡ እርሱም የተወለደው 1901 ሲሆን እስላማዊ ትምህርቱን ደግሞ ያገኘው በኢትዮጵያ ውስጥ እና ያደገው በኢትዮጵያ ክርስትያን - እስላም አብሮ መኖር ጥልቅ እምነት ውስጥ ነበር፡፡ ስለዚህም በሐረር ላይ ተደርጎ በነበረው ትግል ላይ በእነዚያ ዓመታት ውስጥ እርሱ ተሳትፎ ነበር፡፡ ትግሉም ያጠንጥን የነበረው በሁለት ጉዳዮች ላይ ነበር እዚህም ላይ የምንጠቀሰው በጣም በመጠኑ ብቻ ነው፡፡
አንደኛውም በሐረር ውስጥ የሚሰጠው የእስላማዊ ትምህርት ባህርይ ላይ ነበር፡፡ 1941 የሐረሪ እስላማዊ አገር ብሄርተኞች ትምህርት ቤቱን እንደገና ያቋቋሙት በዘመናዊ ትምህርት ቤትነት በዋሃቢ አክራሪነት መሰረት በሚያምን ቡድን ፍላጎት ላይ እንደነበር እነዚህ የታሪክ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡ ከጥቂት ወራት በኋላ ችግሩን በሚገባ ያጤነው የኢትዮጵያ መንግስት ትምህርት ቤቱን ዘጋው ከዚያም በዚህ ላይ የተሳተፉትን ግለሰቦች ወደ እስር ቤት ወይንም ወደ ስደት ላካቸው፡፡
ሁለተኛው ደግሞ 1946-1948 ድርስ የተሞከረው ጥረት ነበር ይህም ከክርስትያን ኢትዮጵያ ተገንጥሎ የመውጣት ሙከራ እንደነበር ሊቃውንቱ ያስቀምጣሉ፡፡ ይህንንም ያደራጁት እነዚያም እስላማዊ የሐረሪ ዜግነት አለን የሚሉት ነበሩ በዚህም ጥረታቸው በዚያን ጊዜ ከነበረው የሶማሊያ ብሄራዊ እንቅስቃሴ ጋር በማበር ሐረርን ከክርስትያን ኢትዮጵያ ገንጥሎ ከእስላማዊ ሶማሊያ ጋር ማዋሃድ ሙከራ አድርገዋል፡፡ እነርሱም እንደገና በኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ተጋለጡና ተቀጡ፡፡
የታሪክ ተመራማሪዎቹ እነ ፕሮፌሰር ኤርሊች እንዳጠኑት በሁለቱም ሁኔታ ላይ የተሸነፉት ቡድኖች የአል-አህባሹን መሪ ሼክ አብደላን ወንጅለውት ነበር፡፡ የከሰሱትም ለኢትዮጵያ መንግስት መሳሪያ ሆነሃል በማለት ነበር፡፡ ሼክ አብደላ እና ተከታዮቹ ግን ፀረ እስላማዊ ዘመቻ ላይ ትብብር እንዳላደረጉ ሲናገሩ ቆይተዋል፤ ለዚህም ማስረጃቸው ሼክ አብደላ 1948 በኢትዮጵያ ንጉሳዊ መንግስት ተጠርጥሮ ለተወሰነ ጊዜ መታሰሩንም እንዲሁም አገሩን ለቆ እንዲወጣ መገደዱንም ይጠቁማሉ፡፡ እንዲያውም እርሱና የእርሱ ተከታዮች የዋሃቢው መሪ የሆነውን ሼክ ዩሱፍ አብድ አል-ራህማናን ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ይተባበራል በማለት ይከሳሉ፡፡ (የዋሃቢው መሪ ሼክ ዩሱፍ ቆይቶ ቁርአንን ወደ አማርኛ እንዲተረጎም የበላይ ጠባቂ እንዲሆን በንጉሱ መንግስት ተሾሟል)፡፡ ለአንባቢዎች ግልፅ መሆን ካለበት ነገር ውስጥ እነዚህ ሁለት ከሐረር የተነሱትና የሁለት እስላማዊ ርዕዮተ ዓለም አለም አቀፍ መሪዎች አሁንም በሕይወት እንዳሉ ነው፡፡ የአል-አህባሹ በሊባኖስ ቤይሩት ሲሆን የዋሃቢው ደግሞ በሳውዲ መዲና ይገኛሉ፡፡ በሁለቱ መካከል ያሉት ቅራኔዎችና መካሰሶች ቀጥለዋል፤ በእነርሱ መካከል ያለው መራራ ጠላትነት በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ሙስሊሞች ለሀሉት ከፍሏቸዋል፡፡ የታሪክ ተመራማሪዎቹ በጆርናላቸው ላይ እንደምሳሌ ያቀረቡት 1995 ዓም. ሼክ አብደላ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚከተለውን ጽሐፉ የያዘ በራሪ ወረቀት አሰራጭቶ እንደነበር ነው፡-
ይህንን (የዋሃቢውን መሪ) ሼክ ዩሱፍ አብ አል-ራህማ የተባለውን ሰው ተጠንቀቁት፣ ከብዙ ጊዜ በፊት ኢትዮጵያን ጥሎ ወደ መዲና ሄዶ የነበረውን ሰው በዚያን ጊዜም እርሱ የዋሃቢያን መርሆዎች ከአጎቱ በዋሃቢዎች መካከል ተምሮ ነበር፡፡ እነርሱም ገንዘብ ሰጡትና የእነርሱን ቃል ለማስፋፋት ወደ ሐረር ተመለሰ፡፡ ከዚያም በኋላ የኃይለስላሴ የቅርብ ሰው ሆነና ቁርአንን ወደ አማርኛ ለመተርጎም ረዳው፡፡ ንጉሱም ለዚህ ስራው ሽልማት እንዲሆነው መሬትን ሰጡት፡፡ መንግስቱ ኃይለማርያም በኢትዮጵያ ውስጥ ኮሙኒዝምን ሲያስፋፋ ደግሞ (1974-1991) ወደ ዋሃቢዎች ተመልሶ ፈረጠጠ፡፡ እነርሱም ገንዘብ ሰጡትና የእነርሱን የሐሰት ትምህርት ለማስፋፋት እንደገና ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ፡፡ ይህንን ሰው ተጠንቀቁት ማንኘውንም ነገሩን ጭምር፣ የሐረርን ሕዝብ ሁሉ አስጠንቅቁ እንዲሁም መላውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ሁሉ፡፡

ይህንን ዓይነቱየአሕባሽ-ዋሃቢያክርክርና እሰጥ አገባ በስፋት በሁሉም እስልምናዊ ጠቀሜታዎች ላይ የሚታይ ነው፡፡ የታሪክ ፕሮፌሰሮቹ የሚሉት ዋናው ጠቃሚ መታወቅ ያለበት ነገር ይህየአል-አህባሽትምህርት ያደገው (የወጣው) ከዚህ ከኢትዮጵያ ታሪክ ጫፍ ላይ መሆኑን ነው፡፡ ሼክ አብደላ 1948 ኢትዮጵያን ከለቀቀ በኋላ በኢየሩሳሌም የተወሰነ ጊዜን አሳልፏል ከዚያም ወደ ደማስቆ ገብቷል፡፡ ሼኩ ወደ ቤይሩት ሊባኖስ 1950 ገብቶ እስካሁን ድረስ እዚያው ነው የሚኖረው፡፡ እነ ፕሮፌሰር ኤርሊች እንደሚሉት ሼኩ በሊባኖስ ከተማ እስከ 1983 ድረስ ለሕዝብ ታይቶ አያውቅም ነበር፡፡ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ውስጥ የአካባቢያዊ የእስልምና በጎ አድራጊ ድርጅት መሪዎች ከሆኑ የእስልምና ሊቃውንት ጋር አብሮ ቆይቷል፡፡ እርሱንም የሚያራምደውን ርዕዮተ ዓለም ሼክ ሙክታር አል-አላሊ በእርሱ ዳር አል-ፋትዋ ማህበር ውስጥ ድጋፍ አድርጎለታል፡፡ እንዲሁም ሼክ ሙሂይ አል-ዲን አል-አጁዝ ደግሞ በተመሳሳይ መንገድ በእርሱየእስላማዊ በጎ አድራጎት ድርጅት ፕሮጀክት ውስጥ ድጋፍን አድርጎለታል፡፡ሼክ አጁዝ ሲሞት 1983 ሼክ አብደላ የማህበሩ መሪ ተብሎ ተዋወቀ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ድርጅቱ በጣም የሚታወቀውአሕበሽተብሎ ነው፡፡
የአል-አሕበሽ እስላማዊ ርዕዮተ ዓለም ከዋሃቢያ እስላማዊ ርዕዮ ዓለም በጣም የተለየ ነው፡፡ የአል-አሕበሽ ርዕዮተ ዓለም ካለው መንግስት ጋር በሰላም መኖር እንደሆነ የሚያራምዱትን ትምህርት በምናነሳበት ጊዜ እንመጣበታለን፡፡ ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ውስጥ ተከታዮች የሉትም፣ ምክንያቱም ብዙዎቹ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የሚከተሉትና ለማራመድም የሚፈልጉት የዋሃቢያውን አመለካከት ነውና፡፡ ያለፉትን ወራቶች ተቃውሞዎችና የተሰጧቸውን ድጋፎች ሁሉ ልንገመግም የምንችለው ከእነዚህ ታሪካዊ እውነታዎች በመነሳት መሆን ይኖርበታል፡፡ አንድ አገር ውስጥ ያለውንና የማንወደውን አገዛዝ የሚቃወም ሁሉ ወደጃችን ነው ለማለትና ለመደገፍ ግን ጊዜው ገና ነው፡፡ የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው የሚለውን የድሮውን  አባባል ከመቀበላችን በፊት እንደገና፣ እንደገና ልንጨምቅ ይገባናል፡፡
የዚህ ድረ-ገፅና ጽሑፍ አዘጋጆች ፖለቲከኞች አይደለንም ነገር ግን ለታሪካዊ እውነታዎች የምናውቀውን የማስቀመጥና መልስ የሚሆኑ ነገሮችን ለወገኖቻችን ማሳየት ጠቃሚ ነው ብለን እናምናለን፡፡ በነፕሮፌሰር ኤርሊች ጆርናል ላይ የተመሰረተው የዚህ ጽሑፍ ክፍል ሁለትና ሦስት በተከታታይ ከቀረቡ በኋላ ሌሎች አስደናቂ ታሪካዊ እውነቶችን ልናቀርብላችሁ እንሞክራለን፡፡