ሁለቱ እስላማዊ ርዕዮተ ዓለሞችና ትግላቸው (ጽሁፍ በእስልምና መልስ አዘጋጅዎች)
በወቅቱ በአገሪቱ ውስጥ ያለው የሙስሊሞችን እንቅስቃሴ፣ ለመደገፍ፣ ወይንም ዝም ብሎ ለማየት ወይንም ለመቃወም የሚቻለው እስልምና በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ምን ይመስል እንደበረ በትክክል በመገንዘብ ነው፡፡ የአሁኑ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በእርግጥ የሃይማኖት ነፃነት ጥያቄ ነውን? ብዙዎችን መስሏቸዋል፡፡ በጣም የቅርቡ በኢትዮ ሚዲያ የድረ-ገፅ ጽሑፎች ላይ የቀረበው የኦክላንድ መግለጫ፤ እንዲሁም www.ethiomedia.com/2012_report/4059.html የቀረበው የነጃሺ ካውንስል መግለጫ፣ አሜሪካ ውስጥ ባለው በኢትዮጵያ ክርስትያንና እስላም ካውንስል በJuly 26 2012 በኢትዮ ሚዲያ ላይ የወጣው www.ethiomedia.com/2012_report/4097.html ጋዜጣዊ መግለጫ እንዲሁም በሌሎች ድረገፆች ላይ በተደጋጋሚ የተሰጡት መግለጫዎች በሙሉ ሁኔታውን ያቀረቡት የእምነት ነፃነት ተደፈረ ከሚል አመለካከት የተነሳ ነው፡፡
ይህንን በተመለከተ የሚጻፉትም የተለያዩ ጽሑፎች አስገራሚዎች ሆነው አግኝተናቸዋል፤ በተለይም በዚያው በኢትዮ ሚዲያ ላይ Standing up with our Moslem citizens በሚል ርዕስ በይልማ በቀለ የቀረበው ጽሑፍ ለምሳሌነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ሙሉ ጽሑፉን www.ethiomedia.com/2012_report/4554.html ማንበብ ይቻላል፡፡ አቶ ይልማ በቀለ የሙስሊሞችን እንቅስቃሴ እንደ እውነተኛ የሃይማኖት ነፃነት ጥያቄ አቅርቦ የገዚው ፓርቲ እነርሱን ለማፈን አንዳንድ የፈጠራ ፕሮፓጋንዳዎችን እንደተጠቀመ በማድረግ አስቀምጦታል፡፡ በእርግጥ ይልማ በቀለ እንዳለው ኢትዮጵያን የምንመኛት የሁሉም እምነት ተከታዮች በነፃነት የሚኖሩባት አገር እንድትሆን ነው፡፡ የሙስሊሞች ጥያቄና የዘመናት ዕቅድ ግን በእርሱና በመሰሎቹ ዘንድ የታየው ላይ ላዩን ከሚሆነው ነገርና ከሞኝነትም ጭምር የተነሳ ነው ምክንያቱም ነገሩ ሁሉ እነሱ እንደሚሉት አይደለም፡፡
ሙስሊሞች በተለይም በአሁኑ ተቃውሞ ውስጥ የተሳተፉት መሰረታዊ ፍላጎታቸው በእርግጥ የሃይማኖት ነፃነት ጥያቄ ነውን? የአንድ አገር መንግስትስ በሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ ለመግባታ ስለምን ይገደዳል? በስልጣን ላይ ያለ አንድ መንግስት በሃይማኖት ስም የተቀነባበረና አገሪቱን ችግር ውስጥ የሚጥል አደጋ ሲመጣ እያየና መረጃዎችና ማስረጃዎች እያለውና እያወቀ ዝም ሊልስ ይገባዋል ወይ? ለዚህ ነው የተሰጡት መግለጫዎች እና ይልማ በቀለን በመሳሰሉ ሰዎች የቀረቡት ጽሑፎች ሚዛን የጎደላቸውና ታሪካዊ ምንጮችን ያላገናዘቡ የሆኑት፡፡
የዚህ ድረገፅ አዘጋጆች ካለው ውዥንብርና መወናበድ ባሻገር ያሉትን ታሪካዊ ምርምሮችን እና አቅጣጫ ጠቋሚ እውነታዎችን ማሳየት የተገደዱት ለዚህ ነው፡፡ ከገዢው ፓርቲ መርሆ የተነሳ በአገሪቱ ውስጥ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ የመናገርና የመጻፍ ነፃነት በእርግጥ አለ ማለት አይቻልም፡፡ ለዚህም ነው ብዙ ጋዜጠኞች በእስር ላይ የሚገኙት፡፡ ሰዎች የፈለጉትን እምነት የመከተልም ነፃነት በመጠኑ የለም ማለት ይቻላል፣ ይሁን እንጂ የአሁኑ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የተቃውሞ እንቅስቃሴ መሰረታዊው ጥያቄ የሃይማኖት ነፃነት ጥያቄ ሊሆን አይችልም፣ ምክንያቱም የሃይማኖት ነፃነት አልተነፈጋቸውምና፡፡ እንዲያውም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሙስሊሞች ነፃነት ያገኙት በመለስ ዜናዊ አገዛዝ ስር መሆኑ ለማንም ግልፅ ነው፡፡ ታዲያ ለሙስሊሞች እንቅስቃሴ መሠረታዊው ምክንያት ምንድነው?