|
ፎቶ ከ /britainfirst.org/ |
ኢህአዴግ ችግሮችን ለመፍታት የሚሞክርባቸው
ጥሩ ያልሆኑ መንገዶቹና ሌላውን ለማሳመን የሚጓዝባቸው የህጻናት ጫወታ ዓይነት ስልቶቹ፤ እንከን ሲለቅም ለሚኖር ለሌላ ወገን ቀርቶ ዳር ቆሞ በአንክሮ ለሚታዘበውም ሰው ሳይቀር የሚያሳፍር ሆኖ ይገኛል። ሕዝቡ በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ወድቆ፤ «ዝምታ ቤቴ» ቢል የወደደው መስሎት ከሆነ የውድቀቱ መጀመሪያ መሆኑ ማወቅ ይገባዋል። ለሀገርም፤ ለወገንም የማይበጅ ፍጻሜ ይኖረዋል። የአሜሪካ ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት ባደረገው ጥናትና የመረጃ ትንተና ውጤት መሠረት በ2030 በዓለም ላይ በውስጣቸው በሚነሳ ሽኩቻና በአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ምክንያት ሊፈራርሱ ከሚችሉ ሀገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ናት ሲል ያወጣውን መረጃ ሟርት ነው ብሎ የሚያልፍ ከሆነ ውስጡን ማየት አቅቶታል ማለት ነው። መልኳን በመስታወት ውስጥ ያገኘችው ዝንጀሮ «አቤት የፊቷ ማስቀየም፤ በዚያ ላይ የመቀመጫዋ መመለጥ» ብላ አክፋፍታ መናገሯ የሚያመለክተው
ራሷ ምን እንደምትመስል
ምንም ግንዛቤ የሌላት በመሆኑ ነው። የኢህአዴግም የቁጣ ፊት እያስቀየመ፤ መቀመጫው ሁሉ እየተመላለጠ መጥቶ ሳለ የሌላውን በማየት ሲሳለቅ ሀገሪቷን ይዞ እንዳይወድቅ እንሰጋለን። በተለይም በሃይማኖት ጉዳይ ላይ ለፖለቲካው የሚመች ሥራ ለመሥራት ብቅ ጥልቅ ማለቱ ከእሳት ጋር መጫወት ይሆናል። ኦርቶዶክሱ ውስጥ ውስጡን ቆስሏል። የእስልምናውንም
አያያዝ «ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ፤ አሁን ምን ያደርጋል፤ ድስት ጥዶ ማልቀስ» በማለት እየተናገርንበት
ነው። ጀሃድ በለው፤ ግፋ በለው፤ እሰር በለው የትም አድርሶ አያውቅም። መንግሥት ሰከን ብሎ በማስተዋልና በጥበብ መጓዝ ካልቻለ ስለወደድነው አይቆምም፤ ስለጠላነው አይሞትም። ተግባር ራሱ ወደመጨረሻው ምዕራፍ ይገፋዋልና ያንን ስንመለከት የሚያሳስበን ብዙ ነገር አለ።
ምንም እንኳን በመንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ ብታተኩርም ሀገራችን ለእግዚአብሔር
መንግሥት የምትታዘዝ፤ ሰላምና ፍቅር የሰፈነባት፤ ሕዝቦች በነጻነት የሚኖሩባት ሀገር እንድትሆን ካለን ዓላማ አንጻር ማኅበራዊው፤ ፖለቲካዊውና ኢኮኖሚያው ሁኔታ ያሳስበናልና እንደዜጋ በዚህ ላይም ከወገንተኝነት
በጸዳ ያለውን እውነታ ብሎጋችን ትናገራለች። ኢህአዴግ እንደፖለቲካ ሽንፈት ሳይሆን ለሀገር ሰላምና መረጋጋት ሲል በየምክንያቱ ያሰራቸውን ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ሰዎች በመፍታት ትኩሳቱን ያብርድ እንላለን። አሁን ባለው ሁሉን ነገር የመቆጣጠር ግትርነትና ሥነ ልቡና ሰልቦ አደብ የማስገዛት ስልት ወንጀለኛ ቢሆን እንኳን እንደትክክል ቆጥሮ የሚያምነው ወገን ማግኘት ከማይችልበት ደረጃ ደርሷል። «ሆድ ለባሰው ማጭድ አታውሰው» እንዲሉ ከኑሮው ውድነት ጋር ተስፋ አድርጎ «ሌላ ቀንም አለ» እያለ በተስፋ የሚኖርበትን ሃይማኖት በሆነ ባልሆነው እየነካኩ ዝም ብሎ የተኛውን መቆስቆስ ወደበጎ አያደርስም። ለማንኛውም መንግሥት ወደክንዱ ሳይሆን ወደልቡ ይመለስ። «እመ እግዚአብሔር ኢሐነጸ ቤተ፤ ከንቶ ይጻምዉ እለ የሐንጹ። እመ እግዚአብሔር ኢዐቀበ ሀገረ ከንቶ ይተግሁ እለ ይኄልዉ» «እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ፥ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ እግዚአብሔር ከተማን ካልጠበቀ፥ ጠባቂ በከንቱ ይተጋል» መዝ ፻፳፯፤፩ ጉልበት ብቻውን ልብ ለሌለው ደርግም አልጠቀመም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከታች ለማንሳት ወደፈለግነው ጉዳይ እናመራለን። ኢህአዴግ ከሚታማበት ችግሮች አንዱ እስከአሁን ድረስ በየሚዲያው የምንሰማቸውና
የምናነባቸው ነገሮች የእስልምና ሃይማኖት መብት ኢትዮጵያ ውስጥ እንደተረገጠ እያስተጋቡ ሆነው መገኘታቸው ነው። ከዚህ በፊት በዚህ ጉዳይ ላይ በሁለት ክፍል ብሎጋችን ጽፋለች። እውነት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሌሎች ሃይማኖት በተለየ የእስልምና ሃይማኖት ጭቆና አለ? ብለን ጠይቀናል። ከዚያም በተለየ መልኩ በአፍሪካው ክፍለ አህጉር የእስልምና አክራሪነት እየሰፋ አልመጣም? ኢትዮጵያስ ከእስልምናው የአክራሪነት መንፈስ እንቅስቃሴ ውጪ የሆነች ሀገር ናት? ብለንም ጠይቀናል። ኢህአዴግን በመጥላት ወይም የሚጓዝባቸውን
መጥፎ ስልቶች በመመልከት ብቻ ያፈጠጠውን ሀቅ መካድ ይቻላል? ብለናልም። የኢህአዴግን ድርቅናና ግትርነት ለመነቅነቅ አሁን ካለው የትኛውም አኩራፊ ኃይል ጋር አንድ መሆን ነው የሚል መርህ እውነቱን በመጨፍለቅ ወደእርስ በእርስ ፍጅት ሊያስገባን ይችላል። ስለዚህም በኢትዮጵያችን
ውስጥ ስላለው የእስልምና እንቅስቃሴ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጠባዩን የተመለከተ የጥናት ጽሁፎችን የዳሰሱ መረጃዎችን ለአስተዋዮች ለማቅረብ ወደናል። እውነታውን ማሳየት ችግሩን አውቆ በጋራ የምንኖርበትን
ሀገር ለመገንባት ይረዳናል። ምድሪቱን እንድንጠብቃትና
እንድንንከባከባትም ከእግዚአብሔር
አደራ አለብን። ዘፍ ፪፤፲፭
እስልምና በኢትዮጵያ ታሪክ በሚል ርዕስ ከሚቀርበው ሦስት ሰፋፊ ተከታታይ ጽሁፎች ውስጥ የመጀመሪያውን
እነሆ ብለናል።
ክፍል ፩
የጽሑፉ ባለቤቶች («ለእስልምና መልስ» አዘጋጆች ነው)