www.goolgule.com |
“አቧራ ይጨሳል። ከዚያ ያፈኑትን ይዘው ይሰወራሉ” አስደንጋጩ ታሪክ ውስጥ ያለው ስዕላዊ ገለጻ ነው። አንድ ወቅት አዲስ አበባ የህጻናት ሌቦች ተበራክተው ነበር። በወቅቱ በርዳታ ስም ተመዝግበው የፈጣሪ ስም እየጠሩ ህጻናትን በመነገድ የከበሩ ወረበሎች በደንብ የተደራጁና የሚቀናቀናቸውን የማስወገድ አቅም ስለነበራቸው “አቧራው ጨሰ” የሚል ስያሜ የኮድ ስም ተሰጥቷቸው ነበር። አሁንም አሉ። “ህጻን እናሳድጋለን” እያሉ በዘረጉት ሰንሰለት የህጻናትን ደም የሚጠጡ “አንቱ” የተባሉ ሰዎች!! የውጪ አገር ዜጎች ጭምር …በሱዳን ሰዎችን በማፈን ሲና በረሃ የሚሰውሯቸው ራሻይዳዎች የተደራጁ ናቸው። ከአረብ ምድር የፈለሱ ናቸው የሚባልላቸው እነዚህ ጎሣዎች በሱዳንና በኤርትራ የሚገኙ ሲሆን በተለይ በኤርትራ ያሉቱ ከዘጠኙ ጎሣዎች መካከል የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ አኗኗራቸው የዘላን በመሆኑ ከኤርትራ መንግሥት ቁጥጥር ውጪ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል፡፡ እነዚህ ጎሣዎች እጅግ አሰቃቂ የሆነ የአፈናና የጭከና ድርጊት ሲፈጽሙ በወጉ ታጥቀውና ዘመናዊ ተሽከርካሪ በመያዝ ነው። የሚታፈነውን ሰው ከተቆጣጠሩ በኋላ አዋራ ይነሳል። የሚከንፉበት ተሽከርካሪ አሸዋውን ተርትሮት ሲወረወር የሚነሳው ጭስ ሲበተን እነሱ የሉም። ቀሪው ተግባር “ሚስትህን፣ ወንድምህን፣ እህትሽን፣ ዘመድሽን ለሚያርዱ የሰውነት ክፍል ሌቦች አሳልፈን ሳንሰጥ ዶላር ክፈል ወይም ክፈይ” የሚለው ድርድር ነው። ይህ ድራማ መሰል ንግድ ሲከናወን ተገደው ይሁን የንግዱ ተባባሪ በመሆን በውል በማይታወቅ ሁኔታ የድርድሩ አስተርጓሚ ሆነው የሚሰሩት ኤርትራዊያን እንደሆኑ ተሰምቷል። ኢትዮጵያዊያኖችም አሉበት ይባላል። ማንም ይስራው ማን ድርጊቱ አሰቃቂ መሆኑ ብዙዎችን አስለቅሷል። አስጨንቋል።
በደላሎች እስራኤል ለመግባት ጉዞ ከጀመሩት ወገኖች መካከል ስንቶቹ በሲና በረሃ ሟምተው እንደቀሩ መረጃ የለም። ከሱዳን ምድር ወጥተው ግብጽ በመሻገር ሲና በረሃ እንደ ከብት ተበልተው የሚጣሉት ወገኖች ስቃይ ለሰሚው ግራ ነው። ወገኖቻችን ላይ የሚደርሰው አሰቃቂ መከራ ከቀን ቀን እየተባባሰ ነው። አሰቃቂ ዜናዎች መስማት ለየእለቱ የሚያስፈልገን መሰረታዊ ጉዳይ እስኪመስል ተለመዷል። ይህ አሳሳቢ ጉዳይ “እስከመቼ በዚህ ይቀጥላል” የሚለው የሁሉም ወገን “ዳር ቋሚዎች” ጥያቄ ነው።
“ለጆሮ የሚሰለች ነው፣ እርዳታ መስጠት ታከተን፣ የሚል መልስ የሚሰጡ አጋጥመውኛል። ድርጊቱ ተደጋግሞ ለጆሮ የሚያሰለች ደረጃ እስኪደርስ እነዚህ ወገኖች የት ነበሩ? ቢያንስ ሌሎች ላይ ተመሳሳይ ችግር እንዳይደርስ ምን ሰሩ? በውጪ አገር ያለን ወገኖች የሚረዳውንና የማይረዳውን መለየት የተሳነን ይመስለኛል” በማለት በሚኔሶታ የሚኖሩት ወ/ሮ ሰብለ አስተያየታቸውንና ተማጽኗቸውን ያሰማሉ።
የካቲት 3፤2005 (2/10/2013) የቪኦኤ አማርኛ ክፍለ ጊዜ ያሰማው እረፍት የሚነሳ ዜና እስካሁን አልተቋጨም። ሱዳን ሸገራብ በሚባለው ሰፊ የስደተኞች ጣቢያ ከባለቤታቸውና ከሁለት ልጆቻቸው ጋር ይኖሩ የነበሩ ወ/ሮ ትዕግስት ገብሬ ጥር 22 ቀን 2005 ዓ ም ቤተ ክርስቲያን ለመሳለም ከቤታቸው ይወጣሉ። በካምፕ ውስጥ ከሚገኘው ቤታቸው ወጥተው በግምት ሰላሳ ሜትር ሳይርቁ ታፈኑ።