( ክፍል ሁለት )
አንዳንድ ግለሰቦችና ማኅበራት ማለትም ማኅበረ ቅዱሳንና አፈቀላጤው ዳንኤል ክብረትን ጨምሮ ባለፉት ጊዜያት በኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው የእስልምና አክራሪ እንቅስቃሴ
የምስል፤የጽሁፍና የድምጽ መረጃ ለማቅረብ ሞክረው ነበር። እነዚህ
ክፍሎች የቆሙበትን ዓላማ ወደጎን ትተን በወቅቱ ስለአክራሪ እንቅስቃሴ የአስጊነት ደረጃ መናገራቸውንም ደግፈነዋል። ቤተክህነቱ ዝምታን በመምረጡና
መንግሥትም ለማዳመጥ ባለመፈለጉ በሎሌችም ወገኖች ጭምር ሲነገር የቆየው ችግር ዛሬ ላይ ለያዥ ያስቸገረ እስከመሆን ባልደረሰም ነበር።
መንግሥት አብዛኛውን ጊዜ እሱን የሚጠቅም መስሎ እስከታየው
ድረስ ሊያስከትሉ የሚችሉ ጉዳቶችን ከኢምንት ይቆጥራቸዋል ወይም ይንቃቸዋል።
የማንም ስስ ስሜት ተጎዳ አልተጎዳ፤ የራሱ ጉዳይ እስከማይመስለው ድረስ የሚሰሙ ድምጾችን ወደጎን ትቶ ረጅም መንገድ በመሄድ ዓላማውን
ሲተገብር የሌሎች መንጫጫት ግድ የሚሰጠው አይደለም። በዚህ የተነሳ ጠቃሚ የልማት እንቅስቃሴዎች ሳይቀሩ እንደጉዳት የሚታዩበትን
አጋጣሚ እየፈጠሩ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ ውስጥ የእስልምና አክራሪ እንቅስቃሴ ስለመኖሩ
ሲነገር የቆየው ረጅም ጊዜ አስቆጥሯል። ችግሮች ገዝፈው የስጋት ደረጃቸው ከማደጉ በፊት አስፈላጊውን እርምት በወቅቱ መውሰድ ሲገባው
አሁን ተበጠበጥኩኝ ብሎ ዛሬ ላይ ተነስቶ «ሐረካት» በሚል ድምጽ እሱም በተራው ቢጮህ ማን ይስማው? ለዓመታት በአክራሪዎች ጉዳት ያለቀሱ ወገኖችን እምባ ማበስ አቅቶት ዛሬ ምን አገኘ? የሚሉ ጥያቄዎች የሚሰሙት ለዚህ ይመስለናል። በአጭሩ በወቅቱ
የእኛ የተጎጂዎችን ድምጽ ለመስማት ባለመፈለግህ አሁን በተራችን ያንተን
ድምጽ አንሰማም ነው እየተባለ ያለው። ችግሩ አክራሪዎች የሉም ማለት ሳይሆን በአክራሪዎች ላይ መወሰድ የነበረበት የእርምት እርምጃ
ዘግይቷል ነው የሚሰማው ድምጽ። ይህንን የጊዜ መተላለፍን አጋጣሚ
ደግሞ የፖለቲካ ነጋዴዎች ይጠቀሙበታል። አክራሪ፤ ተጎጂ፤ መንግሥትና ፖለቲካ በየራሳቸው መንገድ ሄደዋል።
ሌላው ችግር ልማት የሚባለው ነገር ነው። በመሠረቱ ልማት ለአንድ ሀገር እድገት ወሳኝ ነው። ለድህነታችንም ዋናው ምክንያት ልማት አለመኖሩ ነው። ይህንን ችግር ለመቅረፍ መንግሥት ቢሰራ
የሚጠላ የለም። በእርግጥ መንግሥትን የሚጠሉ አካሎች ልማቱን በአሉታዊ
ጎኑ በመፍታት ለትርፍ አይሰሩበትም አይባልም። መንግሥት አሉታዊ ጎኖችን ለመቀነስ የልማቱን ሃሳብ በሕዝብ ልብ ውስጥ ከማስቀመጡ
በፊት በራሱ ጉልበት ለመወጣት ይፈልጋል። ከዚህ ውስጥ የዛሬማ ወንዝ የስኳር ልማት ተጠቃሽ ነው። ከዋልድባ ገዳም ጋር የሚዋሰነውን
የስኳር ልማት ለማስፋፋት መንግሥት አስቀድሞ ወደሕዝብ ማወያየት መግባት ያልፈለገው ፤ አወያይቶ የሚመጣውን የእምቢታና የተቃውሞ ድምጽ ከማስተናገድ ይልቅ ሥራውን ጀምሮ የሚመጣውን ተቃውሞ
ማቃለል ይሻላል ከሚል እሳቤ የተነሳ ይመስለኛል። ይህ የልማት ስልት ከእስልምናው የሰለፊ እንቅስቃሴ ጋር በተመሳሳይ ጊዜ በመደረጉ
ዋልድባ ተነካብን ከሚሉ ሰልፈኞች ጋር በአንድ ጎራ የማይስማሙትን እንዲስማሙ እድል ከፍቷል። ጳጳሳት ነን የሚሉቱ ሳይቀር «አላህ
አክባር» የሚል አዛን እስከማሰማት የደረሱት የፍቅር መጠናቸው ዛሬ ድንገት ስለጨመረ ሳይሆን መንግሥት ሁለቱንም ወገኖች ምን ያመጣሉ? በሚል ስንጥር በአንድ ወቅት ስለወጋቸው ብቻ ነው። ይህ ደግሞ ለፖለቲካ ነጋዴዎች ጥሩ የትርፍ
ጊዜ ነው። ንግድ ደግሞ አዋጭ ቦታና ሰዓት ይጠብቃል። እውነት ለመናገር በዚህ የተነሳ «ጂሐዳዊ ሐረካት» የተባለው ፊልም ከቀልድ
ጫወታነቱ ያለፈ አልሆነም።