ከጥቁሩ የአፍሪካው ዓለም በምድረ እስራኤል ይዞታ ያላት ብቸኛ ሀገር ኢትዮጵያ ናት። መረጃዎች እንደሚያሳዩን ኢትዮጵያ በምድረ
እስራኤል 7 ያህል ገዳማት ያሏት ሲሆን በዐረቦችና በእስራኤል መካከል በተደረገው የ6ቱ ቀን ጦርነት ምክንያት የተዘጋው የዮርዳኖስ
ዳርቻውና በሃሽማታዊው የንጉሥ ሁሴን ግዛት ያለና ምንም ያልተሰራበት ይዞታ ብቻ ሲቀሩ ሌሎቹ 5ቱ ይዞታዎች ክፍት ሆነው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።
ከእነዚህ ይዞታዎች ውስጥ በእስራኤል አሮጌው ከተማ የሚገኘው የኢትዮጵያ ይዞታ የሆነውና በአረብኛው «ዴር ኤል ሡልጣን»
ተብሎ እስካሁን የሚጠራውና በአማርኛው ትርጉም «የመንግሥት ገዳም» የሚባለው በጎልጎታ መካነ መቃብር አጠገብ ያለው ይዞታ ዋነኛው
ነው።
ይህ ይዞታ ለ1600 ዓመታት ያህል በጳጳሶቻቸው ሲመሩን ከነበሩት ከግብጾች ጋር በይገባኛል ጥያቄ እያጨቃጨቀ ሲቆይ ከ230 ዓመት በላይ አስቆጥሯል። ጉዳዩም እስካሁን ማብቂያ ሳይበጅለት ተወዝፎ
ይገኛል። የገዳሙ ባለቤት ማን እንደሆነ እስራኤል ብታውቅም በግብጽ መንግሥት ከፍተኛ የፖለቲካ ድጋፍ ካለው ከኮፕቶች ገዳም ኃላፊዎች
ጋር ለመጋጨት ስለማትፈልግ ጉዳዩን ያዝ ለቀቅ እያደረገች መያዙን እንደስልት አድርጋ ትጠቀምበታለች።
ኢትዮጵያውያን መነኮሳት በቦታው ላይ እየኖሩ ያለው አኗኗር እጅግ አሳዛኝና አስከፊ ከመሆኑ ጋር ገዳሙን በማሻሻል ለኑሮና
ለሰው እይታ እንዲመች አድርገው ለመስራት ፈጽሞ የማይችሉ ሲሆን ግብጾቹ
እያንዳንዷን እንቅስቃሴ እየተከታተሉ በእስራኤል ፖሊስ እየገዛ እንዲቆም ያስደርጋሉ። ካገኘነው መረጃ እንደተረዳነው ከሆነ ማንኛውንም ልማትና እድሳት ለማከናወን
እንዳይቻል የሚቀርበው ብቸኛ ምክንያት በጎልጎታ ዙሪያ ያሉ ቅዱሳን መካናት ሁሉ ቅርጽና ይዘታቸውን ሳይለውጡ ባሉበት ሁኔታ እንዲረጉ
የሚያስገድድ ስታተስ-ኮ /Status-quo/ የሚባል ሕግ አለ በማለት ኢትዮጵያውያንን ያግዷቸዋል።