Wednesday, January 23, 2013

የውጪው ሲኖዶስ ድርድሩን ቅድሚያ ከመንግሥት ጋር ቢያደርግ ሳይሻል አይቀርም!

ከከፈለኝ ምስጋናው

 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በዘመንዋ ሁሉ ከነበሩ መንግሥታት ጋር እጅና ጓንት ሆና መቆየትዋ እውነት ነው። ከነገሥታቷና ከሹማምንቷ ጋር መሆንዋ በአንድ በኩል ጠቅሟታል። ይኸውም በፈለገችበት የሀገሪቱ አድማስ እንድትስፋፋ፤ በኢኮኖሚ አቅሟ እንድትደላደል፤ ተሰሚነት ያለው ድምጽ እንዲኖራት አግዟታል። በተቃራኒው ደግሞ ከመንግሥታት ጋር ተጠግታ መኖርዋ ራሷን ችላ እንዳትተዳደር፤ ሉዓላዊ የሆነ ሥልጣን እንዳይኖራትና ጉዳይዋን ባላት አቅም እንዳትፈታ በግልጽም፤ በቀጥታም ሲቆጣጠሯት መቆየታቸው አሁን ለደረሰችበት ፖለቲካንና ሃይማኖትን የማቀላቀል ዘመን ላይ እንድትደርስ አድርጓታል። ነገሥታቱ ሌላው ቀርቶ የአድባራትና የገዳማት አለቆችን እስከመሰየም ድረስ ግልጽ ሥልጣን እንደነበራቸው ታሪክ ይነግረናል። እስከ ደርግ መውደቅ ድረስ የጠቅላይ ቤተክህነቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ የሚሾምላት በቤተ መንግሥቱ ነበር። በዘመነ አፄ ኃ/ሥላሴ መነኮሳቱ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል ሆነው በማገልገል በሕዝባቸው ላይ የገባር ሥርዓት እንዲቀጥል ታማኝ አባል በመሆን የነገሥታቱ ባለሟልም ነበሩ።  

  በዚህም ይሁን በዚያ ከመንግሥታቱ ጋር መጣበቅዋ መልካም ገጽታዎችና አሉታዊ መልኮችም አብረዋት እንዲኖር ማድረጉም እውነት ነው።
ይህንኑ ተከትሎ 4ኛው ፓትርያርክ አባ መርቆሬዎስም እንደቀደመው ታሪክ ሁሉ በደርግ መንግሥት ድጋፍና ተቀባይነት ነበራቸው።  ደርግን የሚጠላ ደግሞ እርሳቸውን ቢጠላ አይደንቅም። መደገፍ እንዳለ መቃወምም ሰውኛ ጠባይ ነውና። ገለልተኛ መሆን በማይቻላቸው የቤተክርስቲያን መሪዎች የተነሳ  አንዱ ሄዶ አንዱ ሲመጣ መንግሥታት እንደምትመቻቸው ለማድረግ በመድከም ቁጥጥራቸው ለቤተክህነቷ ቅርብ ነው።  ከዚህም የተነሳ ለደርግ የነበራቸውን አቋም በመመልከትና በእሳቸው ላይ የነበረውን ጥላቻ በራሱ መንገድ ለመፍታት በመፈለግ  ከደርግ ውድቀት በኋላ ወደ ሥልጣን የመጣው የኢህአዴግ መንግሥት እንደቀደሙት መንግሥታት በቤተክርስቲያኒቱ ጉዳይ ላይ እጁን ማስገባቱ አልቀረም።  እውነት እውነቱን ስንነጋገር፤ የአባ መርቆሬዎስን ከሥልጣን መልቀቅ ይፈልግ የነበረው ተረኛው መንግሥት ብቻ ሳይሆን የመንበረ ፓትርያርኩ ብዙዎቹ ኃላፊዎችና ሊቃነ ጳጳሳቱም ጭምር እንደነበር በወቅቱ ከስልጣን የማባረር ተሳታፊዎችን ዘመቻና ግርግር ያስተዋለ አይዘነጋውም። 
  መንግሥትም ሆነ አባ መርቆሬዎስን ለመጣል ጊዜው አሁን ነው ባዮች የዘመቻው አባላት መጻኢውን የቤተክርስቲያን መከፋፈል ከግምት ውስጥ ባለማስገባታቸው የፈጸሙት ስህተት እስከአሁን ላለው ልዩነት ዳርጓል። ቤተክርስቲያን ነጻነቷን ሳታስደፍር እንዳትኖር መሪዎቿ ከመንግሥታት እየተለጠፉ ከመኖራቸው የተነሳ ደርግ መራሹ ቤተክህነት ወደኢህአዴግ መራሽ ተለውጧል። ለዚህ ድጋፍ ሥልጣን ናፋቂ አባላቶችዋ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው።
በእርግጥ ቤተክህነት ውስጥ የተሰገሰገው እውነተኛ አማኝ ብቻ አይደለም።  በቆብና በቀሚስ ስር የተሸሸገ አደገኛ ፖለቲከኛም በመኖሩ መንግሥታት በሌላኛው  ዓይናቸውን ቤተክርስቲያኒቱን ቢከታተሏት ሊደንቀን አይገባም። በዘመነ ደርግ የፓርቲው አባላት ቤተክህነቱ ውስጥ ሥልጣን ሲኖራቸው ሌሎቹ ቀን እስኪያልፍ ሳይወዱ እየሳቁ ቀኑን ማሳለፋቸው አይዘነጋም።  የቤተክርስቲያኒቱ መለያየት ለሃይማኖታዊ ፖለቲከኞችም ሆነ ለግልጽ ፖለቲከኞች መሸሸጊያ  ዋሻ በመሆንዋ መንግሥታት በፖለቲካዊ ፍርሃት የተነሳ እጃቸውን እንዲያስገቡ በመደፋፈር ትንፋሿን ይቆጣጠራሉ።  የእግዚአብሔርን መንግሥት ብቻ የሚያገልግሉ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ መንግሥትንም አጣምረው የሚያገለግሉ ሞልተውባታል። ቤተክህነት ለሁለት ጌቶች ከተገዛች ደግሞ አንዱንም ማጣትዋ የግድ ነው። የሃይማኖተኛ ሰው ፖለቲካው ሃይማኖቱ ብቻ መሆን ነበረበት። ዛሬ የሚታየው ሃይማኖተኛ ግን ፖለቲካዊ ሃይማኖተኛ እንጂ ሃይማኖተኛ አማኝ አይደለም። 

"ከፍሬአቸው ታውቁአቸዋላችሁ"

(በጮራ ቊጥር 5 ላይ የቀረበና ከድረ ገጹ የተወሰደ)
ምሁር ነኝ የሚሉ አረጋዊ ከሰዎች ጋር ሲነጋገሩ፥የእኛን ሃይማኖት የሚያህል ፈጽሞ የለምብለው የማውራት ልምድ ተጠናውቷቸዋል፡፡ እንዲህም ሲናገሩ ስመ ሃይማኖታቸውን እየጠሩ ነው፡፡ ቅያሬ የሌለውና የተጋነነው ከቃል ንግግር በቀር የሕይወት ምስክርነት ያልነበረው ወሬአቸው ወዳጆቻቸውንና ቤተ ሰባቸውን ጭምር አሰልችቷቸው ኖሮአል፡፡
አንድ ቀን ከአንድ ወዳጃቸው ጋር ይጨዋወቱ ነበር፡፡ እንደ ተለመደውየእኛን ሃይማኖት የሚያህል የለም፤ ብቻ ምን ያደርጋልሲሉ፤ በተከታዮች ብዛት ከሆነ እምነት ተከታዮች ይባልጣሉኮ! አለና መለሰላቸው፡፡ ትልቋ ልጃቸው ግንአባባ የእኛ ሃይማኖት ካለማመን የሚለይበትን አንድ ነጥብ ቢነግሩኝብትላቸው ምን ለማለት እንደ ፈለገች አልተረዱላትም፡፡ ልጅቷ የመደነጋገር ምልክት በአባቷ ፊት ላይ እንዳየች በሌላ የአገላለጽ ዘዬ ልታስረዳቸው ሞከረች፡፡ አባቷም ሲረዱ በጣም ተቈጡ፡፡
የአረጋዊው ምሁር አስተሳሰብ እምነታችን ጥሩ ነው፤ የእምነታችን ፍሬ ግን መራራ ነው፤ ወይም እምነታችን ፍሬ አልባ (መካን) ነው እንደ ማለት ነው፡፡ ሊሆን ግን አይችልም፡፡ አንድ ሰው ወይም ቡድን የተቀበለውና የሚመራበት የክርስትና እምነት ሕያው ከሆነ የቃል ምስክር ሳያስፈልገው ጣፋጭ ፍሬ አንዠርግጎ ይታያል፡፡

Saturday, January 19, 2013

እንኳን ለ1975ኛው ዓመት በዓለ ጥምቀት በሰላም አደረሳችሁ!




ውሃ ለሥጋችን ሕይወት ነው። ከዚያም በላይ የፍሳችንን መዳኛ የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስን ሞት የምናዘክርበት ትልቅ ተስፋችን ነው። ውሃ በዘመነ ኖኅ የኃጢአት በትር ሆኖ የሰው ልጆችን የቀጣ ቢሆንም ነገሮችን አዲስ ማድረግ የባህሪው የሆነው እግዚአብሔር ውሃን በልጁ  ሞት ሞተን ፤ በኃይል ስለመነሳታችን  የምስክርነት ተስፋ አድርጎ ሰጥቶናል።
ውሃ የሞት መሣሪያ በሆነበት ዘመን «ለቀደመውም ዓለም ሳይራራ ከሌሎች ሰባት ጋር ጽድቅን የሚሰብከውን ኖኅን አድኖ በኃጢአተኞች ዓለም ላይ የጥፋትን ውኃ ካወረደ» 2ኛ ጴጥ 2፤5  ካጠፋቸው በኋላ በዘመነ ሐዲስ ደግሞ የትንሣዔው ኅብረት ምልክት ሆኖ፤«በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ፥ በጥምቀት ደግሞ፥ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ፥ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ» ቆላ 2፤12 በማለት  በትንሣዔው  ያለንን አንድነት ነግሮናል።
እንደዚሁ ሁሉ በክርስቶስ ያመኑቱ ሁሉ ሊያደርጉት የሚገባና የሕያውነት ምስክርነታቸውን የሚሰጡበት የጥምቀት ዝክረ በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከከተራው ጀምሮ የጌታ ጥምቀት ተፈጽሞበታል ተብሎ እስከሚታሰበው እለት ድረስ ብዙ ሺህ ሕዝብ በተገኘበት፤ የውጪ ቱሪስቶች ለጉብኝት በሚገኙበት ሥርዓት ጥር 11/2005 ዓ/ም በጃንሜዳና በየአድባራቱ ተከብሮ እንደሚውል ይታወቃል።  በአዲስ አበባ ጃንሜዳ የተከናውነውን ሥነ ሥርዓት  ከፊል ምሥል አቅርበናል።