(በጮራ ቊጥር 5 ላይ የቀረበና ከድረ ገጹ የተወሰደ)
ምሁር ነኝ የሚሉ አረጋዊ ከሰዎች ጋር ሲነጋገሩ፥ “የእኛን ሃይማኖት የሚያህል ፈጽሞ የለም” ብለው የማውራት ልምድ ተጠናውቷቸዋል፡፡ እንዲህም ሲናገሩ ስመ ሃይማኖታቸውን እየጠሩ ነው፡፡ ቅያሬ የሌለውና የተጋነነው ከቃል ንግግር በቀር የሕይወት ምስክርነት ያልነበረው ወሬአቸው ወዳጆቻቸውንና ቤተ ሰባቸውን ጭምር አሰልችቷቸው ኖሮአል፡፡
አንድ ቀን ከአንድ ወዳጃቸው ጋር ይጨዋወቱ ነበር፡፡ እንደ ተለመደው “የእኛን ሃይማኖት የሚያህል የለም፤ ብቻ ምን ያደርጋል” ሲሉ፤ በተከታዮች ብዛት ከሆነ የ… እምነት ተከታዮች ይባልጣሉኮ! አለና መለሰላቸው፡፡ ትልቋ ልጃቸው ግን “አባባ የእኛ ሃይማኖት ካለማመን የሚለይበትን አንድ ነጥብ ቢነግሩኝ” ብትላቸው ምን ለማለት እንደ ፈለገች አልተረዱላትም፡፡ ልጅቷ የመደነጋገር ምልክት በአባቷ ፊት ላይ እንዳየች በሌላ የአገላለጽ ዘዬ ልታስረዳቸው ሞከረች፡፡ አባቷም ሲረዱ በጣም ተቈጡ፡፡
የአረጋዊው ምሁር አስተሳሰብ እምነታችን ጥሩ ነው፤ የእምነታችን ፍሬ ግን መራራ ነው፤ ወይም እምነታችን ፍሬ አልባ (መካን) ነው እንደ ማለት ነው፡፡ ሊሆን ግን አይችልም፡፡ አንድ ሰው ወይም ቡድን የተቀበለውና የሚመራበት የክርስትና እምነት ሕያው ከሆነ የቃል ምስክር ሳያስፈልገው ጣፋጭ ፍሬ አንዠርግጎ ይታያል፡፡