መነሻ
ሃሳብ «ገመና ዘ81ዱ» መጽሐፍ
ሀተታ፤
በኦርቶዶክሳውያን ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ ከታች ጀምሮ እስከላይኛው እርከን ድረስ ያለው ሰው ስህተት ይኖርብናል ወይም ልንሳሳት እንችላለን ብሎ የሚያስብ ማግኘት አዳጋች ነው። በክርስቶስ ደም የተመሰረተችው ቤተክርስቲያን ፍጽምትና ንጽሕት መሆኗን በመቀበል እንዳለ መሪውና ተመሪው ራሱንም በዚያው ዓይን እያየ እኛ ፍጹማንና ንጹሐን ነን በሚል ከለላ ስር ራሱን በማስጠለል፤ ስህተትን አምኖ ለመቀበል አይፈልግም። የስህተት አስተምህሮ አለ፤ በእግዚአብሔር ቃል ሲመረመር አደጋው የከፋ ነው፤ የክፉ መንፈስ አሰራር ወደማወቅ እንዳንደርስ ቃሉን በክሏል ሲባል የሚሰጠው ምላሽ፤ 2000 ሺህ ዘመን የኖረችን ቤተክርስቲያን ዛሬ የተነሱ አፍቃሬ ተሐድሶ መናፍቃን ሊያርሟትና ሊበርዟት ይፈልጋሉ በማለት ታፔላ መለጠፍ ይቀናቸዋል። የስም ታፔላ መለጠፍ ብቻ ሳይሆን ሽልማት የሚያሰጥ ቢሆን ኖሮ የተመረጡና ለመስማት የሚዘገንኑ ስድቦችና ዛቻዎች ይዥጎደጎዳሉ።
በእርግጥ የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ፍጽምትና ንጽሕት መሆኗ አያጠራጥርም። ምክንያቱም የመሠረታት በዓለቱ ላይ በፈሰሰው ደሙ ነውና። ይህ እውነት ቢሆንም በክርስቶስ ቤተክርስቲያን ውስጥ አባል ሆነው የሚኖሩት የአዳም ልጆች መሆናቸውንም በመዘንጋት የቤተክርስቲያኗን መንፈስና ባህርይ እንዳለ ወደሰዋዊ ማንነት በመውሰድ እኛ ፍጹማንና ንጹሐን ነን በማለት ከስህተት አልባነት የቤተክርስቲያን ማንነት ጋር ራስን መቁጠር ትኩረት የሚያሻው መሆኑን ልናሰምርበት ይገባል። በእርግጥም የተጠራነው ፍጽምት በሆነች ቤተክርስቲያን ውስጥ ፍጹማን እንድንሆን ነው። ነገር ግን ሰው ከተፈጠረበት ማንነት የተነሳ በፍጽምቷ ቤተክርስቲያን ውስጥ ፍጹም ሆኖ መኖር የሚችል ማንነት የለውም።
ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑን የሚችሉት የገላትያ ሰዎች ማንነት ነው። የገላትያ ሰዎች በክርስቶስ አዳኝነት አምነው ወደ ሕይወት መንገድ የተመለሱ ሕዝቦች ነበሩ። ፍጽምትና ንጽሕት በሆነች የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ተጨምረው የቆዩ ሆነው ሳለ ሰብአዊ ማንነታቸው አሸንፎአቸው ወደስህተት መንገድ በመግባታቸው በሐዋርያው ጳውሎስ እጅግ የተወቀሱ ሕዝቦች ሆነዋል።
«የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ፥ በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው?» ገላ 3፤1
ክርስቶስ ኢየሱስ በፊታቸው የተሰቀለ ሆኖ በእምነት ይታያቸው የነበሩት ሕዝቦች ከዚያ የቅድስና ማንነት ወርደውና እውነትን በመተው፤ የጠላት አዚም የወረደባቸው
ሕዝቦች እስከመሆን መድረሳቸውን ሲናገር እናያለን። ሥራቸውን ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የጀመሩ ሆነው ሳለ ቁልቁል ተመልሰው የሥጋን ሃሳብና እውቀት ወደማመን መመለሳቸው በእርግጥም አሳዛኝ የሰው ልጆች ማንነት ማሳያዎች እንደሆኑ የሚያስገነዝበን
ነገር ነው።
«እንዲህን የማታስተውሉ ናችሁ? በመንፈስ ጀምራችሁ አሁን በሥጋ ትፈጽማላችሁን?» ገላ 3፤3 ይላል።
እንግዲህ ክርስቲያኖች ፍጽምትና ንጽሕት በሆነች ቤተክርስቲያን ውስጥ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እምነታቸውን ሊጀምሩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ይህንን ፍጽምና ወደአለማወቅ መመለስም ሊታይባቸው ይችላል። ምን ጊዜም ቢሆን የስህተት መንፈስ አገልግሎቱ፤ የእውነቱን መንፈስ ከሰው ልቡና ላይ በመውሰድ ወደስህተት መንገድ መምራት ስለሆነ በቅድስት ቤተክርስቲያን ውስጥ ባሉ ሰዎች ውስጥ የስህተት አስተምህሮ እንደሚገባ እናረጋግጣለን።
ብዙዎች የአብያተ ክርስቲያናት አባላት በክርስቶስ ፍቅር ላይ ጸንተው ከመቆም ይልቅ ወደ ምድራውያንና ሰማያውያን ፍጥረቶች ፍቅራቸውን ስለለወጡ የሕይወት መንገድን ስተው መገኘታቸው እውነት ነው።
ጳውሎስ ጢሞቴዎስ ልጁን ወደ ተሰሎንቄ የላከበት ዋናው ምክንያትም ተሰሎንቄዎች
ከእምነት ጽናታቸው ወደኋላ እንዳይመለሱ በመንፈስ ያበረታታቸው ዘንድ ነበር። ምክንያቱም ፈታኝ የምንጊዜም አዚሙን የሚያፈሰው
የአማኞችን ልቡና በማደንዘዝ ወደ አልሆነ አቅጣጫ መመለስ
ሥራው ስለሆነ ከዚህ ፈታኝ ይጠበቁ ዘንድ እንደላከላቸው ቅዱሱ ወንጌል ይነግረናል።
«ስለዚህ እኔ ደግሞ ወደ ፊት እታገሥ ዘንድ ባልተቻለኝ ጊዜ። ፈታኝ ምናልባት ፈትኖአቸዋል ድካማችንም ከንቱ ሆኖአል ብዬ እምነታችሁን ለማወቅ ላክሁ» 1ኛ ተሰ 3፤5