Wednesday, October 10, 2012

‹‹ለእንጀራ ብዬ ›› . . . አይባልም!

በሰላማዊት አድማሱ Selam.admassu@yahoo.com

ሸዋንግዛው፣ በላይነህ፣ ጌታ ነህ፣ ግርማዊ፣ ልዑል፣ ኩራባቸው  . . . እነዚህን እና እነዚህን የመሳሰሉ ስልጣንን፣ ጌትነትን ፣ልዕልናን የሚገልፁ በርካታ ኢትዮጵያዊ ሰሞች አሉ፡፡ ስለ ስም ካነሳን ዘንድ ስያሜ ጠባይን፣ግብርንና ሁኔታን የሚገልጥ ሆኖ በእስራኤል ዘንድ ይሰየም እንደነበር የታወቀ ነው፡፡ ለምሳሌ ምናሴ፡- ‹‹ማስረሻ›› ዘፍ 41፡51 (የስም ሰጪውን ሁኔታ ሲገልጥ) ዮሴፍ ‹‹ይጨምር›› ዘፍ 30፡24 (የዮሴፍን ህይወት ያንጸባርቃል)፡፡ የእግዚአብሔር ስሞችም ባህሪውን ፤ስራውን እና አምላክነቱን ይገልጻሉ፡፡ የእኛዎቹ የኢትዮጵያውያን ስሞችስ ምን ያህሉ ይሆን እኛነታችንን የሚገልጹት? ወይንስ መግለጽ አይጠበቅባቸውም ይሆን?፡፡
    አንድ የቤተሰብ አባወራ ለልጁ የሚሰጠው ኩርማን እንጀራ፤የሚያወርሰው አንድ ክንድ መሬት ሳይኖረው ‹‹ ግዛቸው›› ብሎ ስም ያወጣለታል፡፡ ልጅዬውም ከእናቱ ጓዳ ዳቦውን እየገመጠ፤ ቆሎውን እየቆረጠመ አድጎ ለአቅመ አዳም ሲደርስ እርሱም ተራውን ለልጁ ‹‹በላይ ነህ›› ወይንም ‹‹ጌታ ነህ›› ብሎ ስም ያወጣለታል፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ እስከ አስር ትውልድ ቢቆጠርም አንድም ጊዜ ከቤተሰቡ መሃል ‹‹እንደ ስሙ›› የሆነ ላይገኝ ይችላል፡፡ ‹‹ግዛቸው›› ተብሎ በድህነቱ ሳቢያ ላለው የተገዛ፤ ‹‹በላይነህ›› ተብሎ ‹‹ በታች›› የሆነ እጅግ ብዙ ሰው አለ፡፡ እንዲያው ለመግቢያ ያህል ምን ያህል ሥራችን እንደስማችን ወይንም ስማችን እንደስራችን ይሆን?  ስል መጠየቅ ፈለኩ እንጂ በዋንኛነት ላወራስ የፈለኩት ስለ ሥራ ነው፡፡ እንደው የስሞቻችን ነገር በሥራ ባህላችን ላይ ያመጡት አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖር ይሆን እንዴ? እናንተስ ምን ይመስላችኋል?
የሥራ ፈጣሪው ማን ነው?
   መቼም ሁሉም ነገር መነሻና ጅማሬ አለው ፡፡ ለመሆኑ ሥራን ማን ፈጠረው? ተፈጥሮ ወይንስ ፍጥረት? ሃጢያት ወይንስስተት?  . . ሁሉ የየራሱ መላ ምት ሊኖረው ይችላል፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳችን ግን የሥራ ፈጣሪው ራሱ እግዚአብሔር እንደሆነ ይናገራል፡፡ ዘፍ 1፡28፡፡ ይህንን ሃሳብ መጋቢ ደሞዝ አበበ ሥራ-ሥራ በሚለው መጽሐፋቸው ላይ ‹‹ ሥራ የሰዎች ግኝት አይደለም፡፡ ከእግዚአብሔር የተገኘ አምላካዊ በረከት ነው፡፡ በመሆኑም በአምሳሉ ለፈጠረው ሰው ሥራን ሰጠው ፡፡ እርሱ ቦዘኔ ስላልሆነ ሰውም ቦዘኔ እንዲሆን አይፈልግም፡፡›› በማለት ገልጸውታል፡፡ ስለዚህ በቀላል እና በማያሻማ መንገድ የሥራ ፈጣሪው ራሱ እግዚአብሔር መሆኑ ተገልጾልናል፡፡
ሥራ ለምን? ለሆድ ወይንስ? . . .
    እግዚአብሔር አምላክ በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ ለአዳም ‹‹ሥራን›› የሰጠው ‹‹ለሆዱ›› ወይንም ለሚበላው አይደለም፡፡ ምናልባት እኛ ‹‹ለእንጀራ ብዬ ነው ስራ የምሰራው›› ብለን እንደምንለው አይነት አይደለም፡፡  ምክኒቱም ኤደን ገነት ‹‹ለእንጀራ›› የሚለፋባት አልነበረችም ዘፍ 2፡8፡፡ አንዳንድ መጽሐፍት ‹ገነት›› የሚለውን ቃል ሲተረጉሙት ሁለት ፍቺ ይሰጡታል፡፡ አንደኛው ‹‹ አትክልት ማለት ነው›› ሲሉ ሁለተኛው ‹‹ በቅጥር የተከለለ የአትክልት ስፍራ›› ማለት ነው ይላሉ፡፡ ስለሆነም የአዳም በገነት መቀመጥ እና ሥራን መስራት የተፈለገው የሚበላው ነገር ስለሌለው አልነበረም፡፡ ይልቁንም መልካሙን እና ክፉውን ከሚያሳውቀው ዛፍ በቀር በገነት ካለው ሁሉ እንዲበላ ተፈቅዶለታል፡፡ ታዲያ እግዚአብሔር አምላክ አዳም የሚበላው ነገር ሞልቶት ሳለ  ሰራተኛነቱን ለምን ፈለገ? ብለን ብንጠይቅ አዳም ከተፈጠረ በኋላ ምድርን የማበጀት እና የመጠበቅ ኃላፊነት ስለተሰጠው ነው፡፡ ‹ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ ሰውን በኤደን የአትክልት ቦታ አኖረው ሰው የአትክልቱን ቦታ እንዲያለማና እንዲንከባከበው ነው፡፡› ዘፍ 2፡15

Tuesday, October 9, 2012

የአቡነ ገብርኤል ማካሮቭ ሽጉጥ ጠፋ!

source: www.awdemihret.blogspot.com
ሰርቀሀል ተብሎ የተጠረጠረው ዲ/ን ፍጹም እንዳለ የተባለ አገልጋያቸው እንዲባረር ተደርጓል፡፡

በአቋማቸው ወላዋይነት እና ጠንካራ ነው ብሎ ያመኑበትን ክፍል በመጠጋት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የሚታወቁት አቡነ ገብርኤል በቤታቸው ደብቀውት የነበረው ማካሮቭ ሽጉጥ ጠፋ፡፡ አጣሪ ኮሚቴ አቋቁመው ነገሩን እንዲጣራ እያደረጉ ነው፡፡ የአጣሪ ኮሚቴው ሊቀመንበር ከሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅነት ከተባረረና አሁን አቡነ ጳውሎስ ካረፉ በኋላ በአባ ገብርኤል ወደ ቦታው የተመለሰው አለም እሸት ነው፡፡ አለም እሸት ከስልጣኑ የተነሳው ከ12 መኪና በላይ የሚሆን ህዝብ ከአዋሳ መጥቶ አቤቱታ ስላቀረበበት እንደሆነ አይዘነጋም፡፡ ከቅዱስነታቸው ዕረፍት በኋላ ግን አለምእሸትን አባ ገብርኤል በማን አለብኝነት መልሰውታል፡፡ 

የሽጉጡን መጥፋት በተመለከተም ምንም እንኳ አለም እሸት ማኅበረ ቅዱሳናዊ የምርመራ ዘዴውን ተጠቅሞ ለማውጣጣት ቢሞክርም ልጁ ግን ባልወሰደድኩት ንብረት እንዴት እጠየቃለሁ በማለቱ አባረውታል፡፡ እውነተኛውን ሌባ ፈልጎ እንደማውጣት ድሀን በመግፋት መፍትሔ ሰጠን የሚል አሰራር የእነ አባ ገብርኤልን እና አለምሸትን አምባገነንነት ያሳያል፡፡
ሽጉጥ በጓዳ አስቀምጠው የሀይማኖት አባት ነኝ ለማለት መሞከር በእጅግ አሳፋሪ ነገር ነው፡፡ ነገሩ አሳፋሪ ስለሆነም ለፖሊስ ለማመልከት አልደፈሩም፡፡« እስራኤልን የሚጠብቅ አያንቀላፋም» የሚለውን ቃል ያላነበበቡት አባቶቻችን ራሳቸውን ለመጠበቅ የማያንቀላፋውን ጌታ ትተው ሽጉጥን ተስፋ ማድረጋቸው ይገርማል፡፡ እውነትን ጽድቅን እየሰሩ እግዚአብሔርን ተስፋ ከማድረግ ይልቅ ሁሉን እያደፈረሱ በሽጉጥ መታመን የማይጠቅም ነገር መሆኑን መዘንጋታቸው ገርሞናል፡፡

መንግሥት ፓትርያርክ ማን ሊሆን እንደሚችል በውስጥ መሰየሙን ይነገራል።

ከታማኝ የውስጥ ምንጮች የደረሰን ዜና እንደሚያስረዳው ስድስተኛው ፓትርያርክ በመንግሥት ደረጃ ምልመላው ያለቀ ሲሆን ይህ መረጃም በማኅበረ ቅዱሳንና በቀንደኛ ጳጳሳት ዘንድም  የውስጥ ግንዛቤ እንዲያዝ ተደርጎበታል ተብሏል።
የእርቅ ሂደቱ ቢያልቅና የውጭዎቹ ጳጳሳት ከሀገር ቤቱ ሲኖዶስ ጋር በሚደረገው ስምምነት ወደአንድነት ቢጠቃለሉ ሲኖዶሱ በሚሰጣቸው ቦታ የሚመደቡ ሲሆን፤ አቡነ መርቆሬዎስ ግን ለሥራ ብቁ በማያደርጋቸው የጤናና የእድሜ ክልል ውስጥ ስላሉ በፈለጉበት ቦታ ስመ ማእረጋቸው እንደተጠበቀ በጸሎት ተወስነው እንዲቀመጡ የተፈለገ መሆኑም ተዘግቧል።
የውጪው ሲኖዶስ በሚደረገው እርቅ መሠረት በስምምነት ወደአንድነቱ የማይመጣም ከሆነ ራሱ እንዳልፈለገ ተቆጥሮ በነበረበት ሁኔታ ልዩነቱ እንደሚቀጥልም ይነገራል። ይሁን እንጂ የስድሰተኛው ፓትርያርክ ምርጫ ግን ከጥያቄ ውስጥ እንደማይገባና ወደፊት በሚመቻችለት ጊዜ ውስጥ ተመርጦ መንበረ ሥልጣኑን ተረክቦ ሥራውን እንደሚጀምር መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በዚሁ የፓትርያርክነት የምልመላ መዝገብ ውስጥ በአንደኝነት የሰፈሩት ከዚህ በፊት በሰሜን አሜሪካ ሊቀጳጳስ የነበሩትና አሁን ወደ ኢየሩሳሌም ከተዛወሩ ጥቂት ዓመታትን ያስቆጠሩት አቡነ ማትያስ መሆናቸው ተነግሯል።

ውስጥ አዋቂ መረጃዎቻችን ያንን የሚጠቁሙ ሲሆን ለማንኛውም የሚሆነውን ጊዜው ሲደርስ እናያለን።