Wednesday, September 26, 2012

"....ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያውያንስ ምን ተናግረው ይሆን?

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ እና ጠቅላይ ሚ/ር መለስ ዜናዊ በእስትንፋሳቸው መጨረሻ ስለ ራሳቸው፣ ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያውያንስ ምን ተናግረው ይሆን…?

ይህ መጣጥፍ በሪፖርተር ጋዜጣ የእሁድ እትም በፍቅር ለይኩን የተባሉ ጸሐፊ ካስነበቡት ጹሑፍ ለጦማራችን በሚመስማማ መልኩ መጠነኛ ማሰተካከያ ተደርጎበት የተወሰደ ነው፡፡

 ‹‹እግዚአብሔር ሆይ ሁሉንም ነገር ለአንተ እተዋለሁ. . . አሜን!›› (በቅርቡ የሞቱት የጋናው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ሚልስ ከመሞታቸው በፊት ከተናገሩት የተወሰደ፡፡)
ሞት የሰው ልጆች ሁሉ አይቀሬ የሆነ የሕይወት ዕጣ ፈንታ ነው፡፡ ትልቁ ቁም ነገር በምድር ላይ በኖርንበት ወይም እንድንኖርበት በተሰጠን ዘመን የሠራነው ደግ/መልካምም ሆነ ክፉ ሥራችን ግን ሁሌም ከመቃብር በላይ ቋሚ ሀውልታችን ወይም ቅርሳችን ሆኖ እንድንታወስ ሊያደርገን እንደሚችል በቅጡ ማሰብ ይመስለኛል፡፡
ሰዎች ስለ ሞት የተለያየ አመለካከት አላቸው፡፡ ለአንዶንዶች ሞት ትርጉም የለሽ ጸጥታ ነው፡፡ ለሌሎች ደግሞ ሞት ዘላለማዊ እረፍት ነው፡፡ ለአንዳንዶች ሞት ምስጢራዊ እና ረቂቅ ነገር ነው፡፡ በክርስትናው ዓለም ውስጥ ላለን በርካቶች ደግሞ ሞት ወደ ዘላለማዊው፣ ፍፁም ሰላም እና እረፍትን ወደ ተሞላው ሰማያዊ ዓለም እንደ መሸጋገሪያ ድልድይ የሚቆጠር ነው፡፡
ስለ ሞት ያለን ግንዛቤ፣ ትንታኔ እና ፍልስፍና እንዳለንበት እና እዳደግንበት ማኅበረሰብ የኑሮ ልማድ፣ ባሕል እና እምነት/ሃይማኖት የተለያየ ፍቺ ይሰጠዋል፡፡ ሞት የቅርባችን እና የዕለት ተዕለት ክስተት የመሆኑን ያህል በአንፃሩ ደግሞ መቼም የማይለመድ እንግዳ ክስተት ሆኖ መቀጠሉ ለብዙዎቻችን እንቆቅልሽ ነው፡፡ ምነው በአዲሱ ዘመን፣ በወርኻ አደይ፣ ምድር፣ ተራሮች እና ሜዳዎች፣ ጋራ እና ሸንተረሩ በአበቦች አምረውና ተውበው በሚያጌጡበት፣ ሰዎች ሁሉ በአዲስ ራእይ ሕይወትን ውብ እና ፍቅርን የተሞላች ለማድረግ ብሩህ ተስፋን ሰንቀው ‹‹ጉልበቴ በርታ በርታ!›› በሚሉበት ውብ እና ተወዳጅ በሆነችው በወርኻ መስከረም ምን ነክቶህ ነው እንዲህ ሞት ሞት የሚሸት ጹሑፍ ምነው!? እረ…! ደግም አይደል የሚሉኝ ሰዎች አይጠፉም ብዬ እገምታለሁ፡፡
ግና ወደድንም ጠላንም መራሩ እውነታ ሞት ለሁላችንም የማይቀር ዕዳ መሆኑ ነው፡፡ ሞት የሁላችንም ዕጣ ፈንታ መሆኑ ማንኛችንም ብንሆን ለአፍታም ያህል ቢሆን እንዘነገዋለን ብዬ ለመናገር አልደፍርም፡፡ ስለዚህም ሞት ሲመጣ አማክሮ፣ ጊዜ እና ወቅትን ተከትሎ አይደለምና ስለ ሞት ለማውራት ምቹ ጊዜ፣ የተመረጠ ሰዓት ሊኖር ይችላል ብዬ አላስብም፡፡ ሞት አዲስ ዘመን፣ ወርኻ ክረምት፣ በጋ ወይም ጸደይ፣ ትንሽ፣ ትልቅ፣ መሪ ተመሪ፣ ንጉሥ፣ አገልጋይ፣ ሕጻን፣ አዛውንት… ወዘተ አይልምና፤ ለዚህም ነው በለመለመ ብሩህ ተስፋ እና ራእይ ሕይወትን ውብ እና ጣፋጭ ለማድረግ መልካም ምኞታችንን በምንገልጽበት በአዲሱ ዘመን መባቻ ስለ ሞት ለማውራት መጨከኔ፡፡
    የዕብራውያን ጸሐፊ የሆነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- ‹‹ለሰዎችም አንድ ጊዜ መሞት ከእርሱም በኋላ ፍርድ ተመደቦባቸዋል፡፡›› (ዕብ ፱፣፳፯) በማለት የሞትን አይቀሬነት ያስገነዝበናል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደገናም በሮሜ መልእክቱ፡- ‹‹በአዳም ኃጢአት ምክንያት ሞት በሰው ልጆች ሁሉ ላይ መንገሱን እና የዚህ የሞት ኃይል በክርስቶስ ኢየሱስ ሞት ድል መነሳቱን እና በክርስቶስ ሞት ምእመናን የዘላለም ሕይወትን እንደታደሉ›› እንዲህ ይተርካል፡- ‹‹በአንዱም (በአዳም) በደል ሞት በአንዱ በኩል ከነገሠ፣ ይልቁን የጸጋን ብዛት እና የጽድቅን ስጦታ ብዛት የሚቀበሉ በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሕይወት ይነግሣሉ፡፡›› (ሮሜ ፭፣፲፯) ይለናል፡፡

   ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በወንድሟ በአልዓዛር ሞት እጅጉን ልቧ ተሰብሮ እና ሁለንተናዋ በሀዘን ደቆ በእግሩ ሥር ተደፍታ እያነባች፡- ‹‹ጌታ ሆይ አንተ በዚህ ኖረህ ቢሆን ኖሮ ወንድሜ ባለሞተ ነበር!›› ላለችው ለማርታ፡- ኢየሱስም፡- ‹‹ትንሣኤ እና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳን ሕያው ይሆናል፡፡›› በማለት በእርሱ (በሕያው እግዚአብሔር ልጅ) የሚያምኑ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዳላቸው በቃሉ አረጋገጦላታል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ በቅዳሴው ‹‹ሞትን ይሽረው ዘንድ ሞተ!›› በማለት የሞት ኃይል በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ሞት ለዘላለም መሻሩን ይመሰክራል፡፡
ሞት በክርስቶስ ላመኑ በፍፁም የሚያስፈራ እና የሚያስጨንቅ ነገር አይደለም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- ‹‹ለእኔስ ወደ ጌታዬ መሄድ ይሻለኛል ይህንንም እናፍቃለሁ፡፡›› ሲል ሞቱን ወደ ጌታው እና አምላኩ የሚሻገርበት ድልድይ እንደሆነ ለፊሊጵስዩስ ክርስቶሳውያን የወንጌል ልጆቹ በላከላቸው መልእክቱ በግልፅ ነግሯቸዋል፡፡ እናም ሞት በክርስቲያኖች ዘንድ አስፈሪ እና አሳፋሪ አይደለም፣ ሊሆንም አይችልም፣ ሆኖም አያውቅም፡፡ የቀደሙት አባቶቻችን የወንጌል አርበኞች፣ ጻድቃን እና ሰማዕታት ሞታቸውን እግዚአብሔር አምላካቸውን በዝማሬ እያመሰገኑ፣ እያመለኩ፣ በታላቅ ደስታ እና በጸጋ ነው የተቀበሉት፡፡
ወደ ተነሳሁበት ወደ ርዕሰ ጉዳይ ስመለስ 2004 ዓ.ም በሀገራችን በሃይማኖት፣ በሥነ ጥበብ እና በፖለቲካው መስክ አንቱ የተባሉ ሰዎችን ያጣንበት ዘመን ነው፡፡ በተለይም ደግሞ ወርኻ ነሀሴ ከሕይወት ጋር ግብ ግብ የገጠመ በሚመስል አስገራሚ ጥድፊያ፣ ዓመቱ ከማለቁ በፊት ሳልቀደም ልቅደም ያለ ይመስል በዓመቱ መጨረሻ በወርኻ ነሀሴ ሁለት ታላላቅ መሪዎችን በሳምንት ልዩነት ውስጥ ያጣንበት እንደ አየሩ ጠባይ ሁሉ ጨፍጋጋ እና አስደንጋጭ ወር ሆኖ አልፏል፡፡    
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ን አባት እና መሪ የሆኑት ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ እና የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚ/ር አቶ መለስ ዜናዊ የተከታተሉበት የሞት መርዶ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን ከዳር እስከ ዳር ያነጋገረ እና የሀዘን ከል ያለበሰ ክስተት ሆኖ አልፏል፡፡
በዚህ የሞት ክፉ ዜና የተነሳ በሀገራችን ያረበበው የሀዘኑ ድባብ እንደ ሰማዩ ደመና ገና ሙሉ በሙሉ የተገፈፈ አይመስልም፡፡ አሁንም ድረስ የእነዚህ የቤተ መንግሥቱ እና የቤተ ክህነቱ መራኅያን ያልተጠበቀ የሞት ጥሪ ለብዙዎቻችን ባሰብነው ቁጥር እንቆቅልሽ እንደሆነብን ዘልቋል፡፡ ለአንዳንዶች በተመሳሳይ ወቅት በቤተ መንግሥቱ እና በቤተ ክህነቱ የተከሰተው ይህ ያልተጠበቅ የሞት ጥሪ ‹‹የእግዚአብሔር ቁጣ ነው›› እኛም ንስሀ እንግባ ዘንድ ያስፈልገናል በማለት የእግዚአብሔርን ታላቅነት እና ኃያልነት ዳግም እንዲያስቡ እና እንዲያስተውሉ እንዳደረጋቸው ሲናገሩ በአደባባይ ተደምጠዋል፡፡
ለሌሎች ወገኖቻችን ደግሞ የቤተ መንግሥቱ እና የቤተ ክህነቱ የሞት መርዶ ያው እንደተለመደው ተራ የፖለቲካ ጉንጭ አልፋ ወሬ ከመሆን አላለፈም፡፡ እናም አንዳንዶች ለሰሞኑ የቤተ መንግሥቱ እና የቤተ ክህነቱ ያልተጠበቀ የሞት ጥሪ ያልተገባ የስንፍ እና የፍርድ አስተያየት ከመሰጠት ባለፈ ሌላ አንድምታ እንዳልሰጡት በሰሞኑ ከሚነገሩ ወሬዎች፣ በማኅበረሰብ ድረ ገጾች እና በየብሎጉ ከሚጻፉ በርካታ ፍርድ አዘል ጹሑፎች እና አስተያየቶች ታዝበናል፡፡ እንዲያም ሲል ደግሞ እሰይ ስለቴ ሰመረ በሚል የሚያዜሙ እና ፍፁም ኢትዮጵያዊ ጨዋነት እና ባሕል በጎደለው ሁኔታ በእነዚህ መሪዎች ሞት ጮቤ እየረገጡ ያሉ ወገኖችንም እረ ምን ጉድ ነው እያልን ለመታዘብም በቅተናል፡፡ 
እንዲሁ እንደ ዋዛ ለህክምና በሚል ሰበብ እንደ ወጡ እስከ ወዲያኛው የተለዩንና ከአሁን ከአሁን ጤንነታቸው ተመልሶ ይመጣሉ በሚል ተስፋ የጠበቅናቸው ጠቅላይ ሚ/ር መለስ ዜናዊ በስተመጨረሻ ለብዙዎቻችን ጆሮ የማይታመን የሆነውን የሞታቸውን መርዶ ዜና ለማመን እየቸገረንም ቢሆን ለመስማት ነበር የተገደድነው፡፡ ደህና ናቸው፣ ከህመማቸው እያገገሙ ነው፣ በአዲሱ ዓመት ሥራቸውን ይጀምራሉ የተባለላቸው ጠቅላይ ሚ/ር በድንገት በተከሰተ ኢንፌክሽን ምክንያት በድንገት ሞቱ መባላቸው አሁንም ድረስ ለብዙዎቻችን ኢትዮጵያውያን የጠቅላይ ሚ/ሩ ህመማቸው እና አሟሟታቸው ምስጢር ነው፡፡
በዚህ ጽሑፌ ለመዳሰስ የፈለግኩት የቤተ ክህነቱ እና የቤ መንግሥቱ መሪዎች በሕይወታቸው እስትንፋስ መጨረሻ ምን እንደተናገሩ በመጠየቅ የተነሳው የመጣጥፌ ርዕሰ ጉዳይ እንደ አለመታደል ሆኖ አትኩሮቱን ያደረገው በውጩ ዓለም ባሉ መሪዎች እና ታላላቅ ሰዎች ላይ ነው፡፡ የዚህ ዐቢይ ምክንያት ደግሞ በቅርብ በሞት የተለዩን ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስም ሆነ ጠቅላይ ሚ/ር መለስ ዜናዊ በመጨረሻ የሕይወታቸው እስትንፋስ ምን እንዳሉ፣ ምን እንደተናገሩ እና ለሕዝባቸው ምን ዓይነት የመጨረሻ መልእክት እንዳስተላለፉ የነገረን ሰው ወይም እኔ ምስክር አለሁ የሚለን ሰው እሰካሁን አለመገኘቱ ነው፡፡
ፍቅርን፣ ይቅር ባይነትን/እርቅን፣ ግልፅነትን፣ ታማኝነትን… ወዘተ በቃላቸውም ሆነ በተግባራቸው የሚሰብኩ መሪዎች ድርቅ ክፉኛ የመታት እናት ኢትዮጵያ መሪዎቿ እና ሕዝቦቿ በቅጡ ሳይተዋወቁ እና በፍቅር ሳይቀራረቡ ማዶ ለማዶ እንደተያዩ በሞት እስከ ወዲያኛው የሚሸኙባት ምድር የመሆኗ ምስጢር ማብቂያው መቼ እንደሆነ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡
በምስኪኗ ኢትዮጵያ መሪዎቻችን ብዙ ነገራቸው ለሕዝባቸው ምስጢር ነውና እነዚህ ለሁለት አሥርት ዓመታት በቤተ መንግሥቱ እና በቤተ ክህነቱ መሪዎች ሆነው ያስተዳደሩ ፓትርያርክ አባ ጳውሎስ እና ጠቅላይ ሚ/ር መለስ በእስትንፋሳቸው መጨረሻ ምን እንዳሉ ምን መልእክት እንዳስተላለፉ ለማወቅ አልታደልንምና ሳንወድ በግድ ቁጭት እና እልህ እየተፈታተነንም ቢሆን በጀመርኩት ርዕስ ስለ ባሕር ማዶዎቹ መሪዎችና ታላላቅ ሰዎች የመጨረሻ የሕይወታቸው እስትንፋስ መልእታቸው ላምራ፡፡
ከጠቅላይ ሚ/ር መለስ ከጥቂት ሣምንታት በፊት በሞት የተለዩት የጋናው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ሚልስ በጉሮሮ ካንሰር በሽታ ምክንያት በአሜሪካ አገር ህክምና ያደረጉ ቢሆንም በቅርቡ ህመማቸው አገርሽቶ ወደ ሀገራቸው የጦር ኃይሎች ሆስፒታል ገብተው ሕክምና በመከታተል ላይ እያሉ ነበር ያረፉት፡፡ Web Ghana የተባለው ድረ-ገጽ ‹‹Mills’ Last Words Before He Died/የፕሬዝዳንት ሚልስ እልፈት እና ከመሞታቸው በፊት የተናገሩት የመጨረሻ ቃላቸው›› በሚል ርዕስ ባስነበበው ጹሑፍ ፕ/ር ሚልስ ከሞታቸው በፊት ካጠገባቸው የነበሩትን ወንድማቸውን ዶ/ር ካድማን ሚልስን በመጥቀስ የሚከተለውን ዘገባ አስነብቦ ነበር፡-
"Before my brother (Mills) died, the last words that he said that I clearly remember is that, he raised his hands in the air and he said ‘God, I leave it all to you, Amen’. I’ve no doubt that God heard his call. I’ve no doubt that he is now in the bosom of the Lord. I’ve no doubt that he’ll find eternal peace. Pray for him, and May God be with you, Fiifi," Dr Cadman Mills said.

Saturday, September 22, 2012

መንፈሳዊ ሃሳብ ላለው ሰው ሁሉ ከፓትርያርክ ምርጫ በፊት እርቅ ይቀድማል!

ስለእርቅ ብዙ ብዙ ተብሏል።  ሰዎች እርቅን ከሁኔታዎችና ከአዋጭነቱ አንጻር መዝነው ይፈጽማሉ። በእርቁ የሚያገኙትን ሂሳብ ቅድሚያ ያሰላሉ። አንድ የተጨበጠ ነገር ካላገኙ እርቅን ሰማያዊ ዋጋ ከማግኘት ጋር አያይዘው  ለመወሰን ይቸገራሉ። ብዙ እርቆች በዚህ መንገድ የሚከናወኑ ናቸው። ፖለቲከኞቹ እንኳን /Give & Take/ ሰጥቶ መቀበል ይሉታል። ይህ የሥጋዊ እሳቤ ውጤት በመሆኑ በዚህ እርቅ ምድራዊ ስምምነት ካልሆነ በስተቀር ከላይ ከአምላክ ዋጋ ያስገኛል በሚል ስላልሆነ ውጤቱ ጊዜያዊና ምድራዊ ነው። ሰማያዊ አስተሳሰብ ምን ጊዜም የእርቁን ጥቅም ከአዋጭነቱ ወይም ከሚያስገኘው የሚታይ ዋጋ በላይ በመሆኑ ለዚህ እርቅ ራስን የመስጠት ዋጋ እስኪከፈልበት ድረስ ግዴታን ያስከትላልና ከባድ ነው። እንኳን የበደሉትን፤ የበደለንን ይቅር እስከማለት የሚያደርስ ህግጋት ስለሆነ ሚዛናዊነቱ በመንፈስ ዓይን ብቻ የሚታይ ነው። በዘወትር ጸሎት «ከመ ንሕነኒ ንሕድግ ለዘአበሰ ለነ» እኛም የበደሉንን ይቅር እንደምንል…» እያልን በደላችንን ሁሉ በደሙ እንዳጠበው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛም የበደሉንን ይቅር እንላለን እያልን የምናውጀው የጸሎት አዋጅ ዋጋ የሚኖረው በእውነትም ለእርቅ የተዘጋጀ ልቡና ሲኖረን ነው። ያለበለዚያ እየዋሸንና ጌታችንንም ለዚህ ዋሾ አንደበታችን ተባባሪ እንዲሆነን እየጠራነው ካልሆነ በስተቀር  በተግባር ይቅርታ በሌለበት ልባችን ውስጥ መንፈስ ቅዱስ በምንም መልኩ ሊያድር አይችልም። ይቅርታ የሌለው ልቦና መንፈሳዊ አይደለም።


«እናንተ ግን ይቅር ባትሉ በሰማያት ያለው አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም» ማር 11፤26

ይቅርታን የማያውቅ ሲኖዶስ ወይም ማኅበር እንዴት ለሀገርና ለህዝብ ይጸልይ ዘንድ ይችላል? ከማን ዘንድ ይቅርታን ለማግኘት? አንዳንዶች በስም ብጹእና ቅዱስ ተብለው በተግባር ግን ከቅድስና ማንነት የሚመነጨው መንፈሳዊ ብቃት ሲታይ፤ ፍሬ አልባዎች ናቸው። የክብርና ዝና፤ የገንዘብና ሥልጣን ምኞቶች ይቅር ማለት በሚገባው ልባቸው ላይ ተቀምጠው ይገኛሉ። ከዚህም የተነሳ ለሌሎች ይቅርታን ለማድረግ ጊዜን ይፈጃሉ፤ እነርሱ ግን ለኃጢአታቸው ወዲያውኑ ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቅርታ እንዲወርድላቸው ሲጸልዩ ይታያሉ።  በእርግጥም ለጸሎታቸው ምላሽ ያልመጣላቸው ከዚህ እልከኛ ልባቸው የተነሳ ይሆናል። «አድን ሕዝበከ ወባርክ ርስተከ» ብለው ይጸልያሉ። ህዝቡም አልዳነም፤ በበረከትም ተሞልቶ በስደት ከመሞት አልዳነም። በእልከኝነት መንፈስና ይቅር ባለማለት  የእግዚአብሔርን የይቅርታ ፈቃድ በእጃቸው ያሰሩ ሰዎች እንዴት፤ የይቅርታ እጅ ለእነሱ ከሰማይ እንዲወርድ ይለምናሉ? እግዚአብሔር ልብና ኩላሊት ያመላለሰውን እልከኛ ልብ አይመረምርም ማለት ነው? ለይቅርታ ባልተዘጋጀ ማንነት ያሉ ጨካኞችና ክፉዎች ይቅርታን አያውቁም፤ ልበ ርኅሩኆችና ቸሮች እንጂ!!

«እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፥ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ» ኤፌ 4፤32

እንግዲህ እውነት እውነቱን እንነጋገር ከተባባልን ይቅርታን ገንዘብ ማድረግ የማይችሉት ክፉዎችና ጨካኝ መሪዎች ሁሉ ናቸው። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የተባራሪና አባራሪ፤ የውስጥና የውጪ፤ የሕገ ወጥና ሕጋዊ፤ ሲኖዶስ ስያሜ ሕልውና ኖሮት በየራሱ ክፍል ተለያይቶ መኖር ከጀመረ እነሆ ሃያ አንድ ዓመት አስቆጠረ። እንዴትና ምክንያቱን ለመዘርዘር የዚህ ጽሁፍ ዓላማ ባለመሆኑ ወደዚያ የቆሸሸ ታሪክ መግባት አያስፈልግም።   በተወጋገዘ የጳጳሳት ቡድንና ደጋፊ የቤተክርስቲያኒቱ አንድ ማኅበር ልዩነቱ ዛሬም መኖሩን በማመን መፍትሄ በመፈለግ ላይ ለማተኮር ይሻል። 21 ዓመት በልዩነትና በክፍፍል የቆየነው ለምንድነው? አሁን ያህ ክፍፍል እንዳይቀጥል ምን የሚታይ ነገር አለ? ወደፊትስ ምን ማድረጉ ይበጃል? በሚሉት ላይ ጥቂት ለማለት እንወዳለን።

1/ ለይቅርታ የተዘጋጀ ወገን የለም!

በሁለቱም ሲኖዶሶች በኩል በክርስቲያን ይቅርባይ የእምነት ማንነት ላይ ሆኖ ይቅር ለመባባል የፈለገ ማንም  ወገን የለም። የክርስቶስ አማኝ ይቅርታን በሁኔታ፤ በአዋጭነቱና በሚያስገኘው የሚታይ ዋጋ ላይ ተመስርቶ ለይቅርታ ድርድር አይቀመጥም። ይሁን እንጂ ሁለቱም ሲኖዶሶች ለይቅርታ የሚነጋገሩት የሚያዋጣቸውን ስልት ነድፈው ጥቅሞቻቸውን በማስጠበቅ ውጤታማ ለመሆን የሚታገሉለት ምድራዊ አስተሳሰብ የነገሰበት ሆኖ በመቆየቱ አንዳችም ውጤት ማምጣት አልተቻለውም። የቤተክርስቲያን አንድነት ሰዎች ስለፈለጉት  ወይም ስላልፈለጉት ሳይሆን የተመሰረተው በክርስቶስ ደም ስለሆነ አንዳችም ቅድመ ሁኔታ የሌለበት ነገር ነው።
«ቤትም እርስ በርሱ ከተለያየ ያ ቤት ሊቆም አይችልም » ማር 3፤25
«በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ» የሐዋ 20፤28
የክርስቶስን መንጋ ለሁለቱ የከፈሉ ሲኖዶሶች የክርስቶስን ቤት በአንድነት ለማቆም ያለመቻላቸው ዋናው ምክንያት ቤተክርስቲያንን ለመጠበቅ መንፈስ ቅዱስ የሰጣቸውን ሹመት ወደ ሥጋዊ አስተሳሰብና የድርድር ሂሳብ ስላወረዱት ብቻ ነው። እንዲያ ካልሆነማ 21 ዓመት ለእርቅ ያንሳል? ከእንግዲህስ ስንት 21 ዓመት ያስፈልጋል? በሁለቱም ወገን ለቤተክርስቲያን አንድነት የተዘጋጀ ማንነት ባለመኖሩ ውጤቱ ከህልም ዓለም አልፎ እውን መሆን አልቻለም። አሁንም ይህን አስተሳሰብ አስቀምጠው የክርስቶስን ማኅበር መሰብሰብና የቤተክርስቲያንን አንድነት ማስቀደም እስካልቻሉ ድረስ ከመንፈሳዊ ውጤት ላይ መድረስ አይቻላቸውም።

2/ የሀገር ውስጡ ሲኖዶስ የበለጠ ችግር አለበት።

አንዳንዶች ማለትም ማኅበረ ቅዱሳንን ጨምሮ የፓትርያርክ መርቆሬዎስን ሀገር ለቆ መሄድ ሲኮንኑ ይታያሉ።  የመንፈሳዊ አባቶችን የጥንት የስደት ሁኔታ ከታሪክ አምጥተን እዚህ ላይ ብዙ መከራከሪያ ጭብጥ በማቅረብ መሞገት ይቻላል። ይሁን እንጂ ጉልጭ አልፋ እንዳይሆን እንለፈውና የፓትርያርክ መርቆሬዎስን ስደት ተገቢ እንዳልነበረ ብንቆጥረው እንኳን ስህተታቸውን አጉልቶ የማያሳይ ነገር አለ። ይኼውም  ፓትርያርክ መርቆሬዎስ መንፈሳዊ ሥልጣናቸውን የሚጠሉት ኢህአዴግ ሲገባ ሊሆን አይችልም። ታመዋልም ቢባልም እንኳን  በሞት ከዚህ ዓለም ተለይተዋል ማለት አይደለም። በሞት እስካልተለዩ ድረስ በህመም ይሁን በሌላ ምክንያት ከመንበሩ ላይ ካልተገኙ በምትካቸው ሌላ ፓትርያርክ ይመረጣል የሚል ሕግ አለ ወይ?    ምንም እንኳን ፓትርያርክ መርቆሬዎስ እስከመጨረሻው ድረስ ባሉበት መቆየት እንደነበረባቸው ባያጠያይቅም እውነታው ግን የፓትርያርክ መርቆሬዎስን መባረርና ከስልጣን በህመም ይሁን በሞት መሰናበት የሚፈልጉ የሲኖዶስ አባላት መኖራቸውን ልንክድ አይገባም። ምክንያቱም ፓትርያርኩ በሕይወት እያሉ ሌላ ፓትርያርክ አንሾምም ያለ አንድም የሲኖዶስ አባል አልነበረም። ይልቁንም ከባለጊዜው ንፋስ ጋር ሲነፍሱ ታይተዋል። አንዳንዶቹም ለመሾም ሲሯሯጡ ነበር።  በህመም ወይም በሌላ ምክንያት መሥራት ባይችሉ እንደራሴ የማይመራበት ምክንያቱ ምን ይሆን? ሕጉን በሕግ ባለማሻሻል ለመጣስ ያደረሰው ምን ይሆን?  ተወደደም ተጠላ፤ ፓትርያርኩን በመጥላትና በማስወገድ ሥልጣኑን ለመጨበጥ የፈለጉ ቡድኖች ለቤተክርስቲያን መከፋፈል ትልቁን ሚና ተጫውተዋል። ብዙዎቹን ባለድርሻዎች እናውቃቸዋለን። ገሚሶቹም ሞተዋል፤ በህይወት ያሉትም አሉ። ይህ ከሆነ እነሆ 20 ዓመታት አለፉ።  ስህተቶችን በማመን ለማስተካከል መሞከር ግን አሁንም ቁርጠኝነቱ ካለ አልረፈደም። በመሬት ላይ ያለው እውነታ ግን ለመተራረም ያለውን ነገር ብዙም አያሳይም።
 የሀገር ቤቱ ሲኖዶስ ከውጪው ሲኖዶስ ጋር ለሚደረገው እርቅ እንቅፋት ናቸው ብሎ የክስ መዝገቡን በአቡነ ጳውሎስ ላይ ሲለጥፍ የነበረ ቢሆንም  ከሞታቸውም በኋላ ይህ እርቅ በየምክንያቱ እንዲጨናገፍ የሚፈልግ አካል እንጂ ከአቡነ ጳውሎስ በተሻለ መልኩ ለእርቁ ቀናዒ  ስለመሆኑ የምንሰማውና የምናየው ነገር የለም። ይልቁንም ከወዲያ ወዲህ የሚናፈሰው ስለ 6ኛው ፓትርያርክ ምርጫ ነው። ምናልባትም አቡነ ጳውሎስን ከመጥላት የተነሳ  ውንጀላን የሚቆልሉባቸው ከሳሾቻቸው እሳቸው በሞት ዘወር ሲሉ  የከሳሾች የሀሰት ክስ ጊዜውን ጠብቆ እየተገለጸ እያየን ነው። ስለ6ኛው ፓትርያርክ በተዘዋዋሪና በቀጥታ መነገሩ እርቁ አልተፈለገም ማለት ነው። ድሮውንም ፓትርያርክ ጳውሎስን የሚወነጅሉት ለስም ማጥፋት እንጂ እርቁን ፈልገውት አልነበረም። ምክንያቱም እርቁ እውን ሆኖ የውጪዎቹ ጳጳሳት ወደ ሀገር ውስጥ ለመግባት ቢችሉ፤ አሁን ባለው የሀገር ውስጡ ሲኖዶስን ጉባዔ በሚፈልጉት መንገድ የሚጠመዝዙ ቡድኖች ከልዩ ልዩ አስተሳሰብና ከእውቀት ብልጫ አሰላለፍ አንጻር የመዋጥና የያዙትን የወሳኝነት  ወንበር በመልቀቅ ወደጥጉ እንገፋለን የሚል የስነ ልቦና ፍርሃት አላቸው። ያን ጊዜ የማኅበረ ቅዱሳን ነደ እሳት የሚባል ጳጳስ አይኖርም፤ እገሌ ጧፍ ነው፤ እገሌ ደግሞ ሻማ እያሰኘ የሚያሞካሸውን ጀግና ደጋፊ አያገኝም።  ስለዚህ ሁሉም ቡድኖች እርቁ በፍጥነትና በሁኔታዎች አጋጣሚ እንዲፈጸም አይፈልጉም። ከእነዚህም አንዱ የሀገር ውስጡ ሲኖዶስ አጫፋሪ የሆነው ማኅበረ ቅዱሳን ከነተባባሪ አባቶቹ እርቁን አይፈልጉትም።

3/ የውጪውም ሲኖዶስ ችግር አለበት።

 ፓትርያርክ መርቆሬዎስ እድሜአቸው መግፋቱ እውነት ነው። በዚህ እድሜያቸው አሁን ያለውን የቤተክርስቲያን ተግዳሮቶች ፈጥነው በመረዳትና በመንቀሳቀስ ተፈላጊውን መፍትሄ በመስጠት ላይ ተገቢውን አመራር መጠበቅ እንደሚቸግር መረዳት አይከብድም። በዚህ ላይም ሕመም እንዳለባቸውም እንሰማለን።  ብዙ ጊዜም የሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ድምጽ በውክልና ከሚሰማ በቀር የፓትርያርኩ ድምጽ ርቋል። ይህም እንደ አንድ ችግር ቢነሳ አግባብነት ይኖረዋል። ከዚህ በተጨማሪም እርቅን የሚያክል ትልቅ ኃላፊነትና ተልእኮ የሚጠብቀው የውጪው ሲኖዶስ አባላት ለእርቅ እንቅፋት የሚሆኑ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ መሰል መግለጫዎችና አሰላለፎችን ሲያሳዩ ይታያሉ። ከሀገር ውስጥ ሲኖዶስ ጋር በመስማማት ብቻ ያለ ኢትዮጵያ መንግሥት ድጋፍ እርቁ ከግብ ሊደርስ እንደማይችል ይታወቃል።  የውጪው ሲኖዶስ አባላት የፖለቲካ ሰልፎችን በማስተባበር የኢትዮጵያን መንግሥት ማስኮረፍ በራሱ ችግር አለው። መቃወም መብት ቢሆንም የፖለቲካ «ሀሁ» ብዙም በሀገሩ ውስጥ ባላስፋፋ መንግሥት ጉዳይ እየገቡ ወደእርቅ እንደርሳለን ለማለት እንዴት ይቻላል? እርቁ ቢቀርም፤ ይቅር ካልተባለ በስተቀር  እስከ ኤርትራ የደረሰ የሲኖዶስ አባል ያለው የውጪው ሲኖዶስ አቋሙ ጥርት ያለና ለእርቅ ዝግጁነት ያለው ነው ለማለት ይቸግራል።  እስካሁንም እነዚህ ጉዳዮች ለእርቅ ያላቸውን ጉዳት ገምግሞ ዝግጁነቱ እስከየት ድረስ እንደሆነ በግልጽ የሚታወቅለት ነገር የለም። ፖለቲካዊ ጥያቄዎችንም እንደሚያነሳ ይሰማል። ቤተክርስቲያንን አንድ ለማድረግ ካልሆነ በስተቀር ሲኖዶስ ለፖለቲካዊ ጥያቄ መፍትሄ የቅድሚያ ስራው እንዴት ሊሆን ይችላል? የሚቀድመውን ማስቀደምና በሂደት ደግሞ የሚከተለውን ከመስራት ይልቅ አቀላቅሎ ሁሉንም ፍላጎቶች በአንዴ ለማሳካት መፈለግ ሁሉም እንዳይሆን ለማድረግ ከመጣር የተለየ አይደለምና ሊታሰብበት ይገባል።

Thursday, September 20, 2012

የማኅበረ ቅዱሳን ሰዎች በአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ሹመት ደስተኛ አለመሆናቸውን ቤተክህነት አካባቢ በሚያናፍሱት ወሬ እየገለጹ ነው

ዐቃቤ መንበሩ «መናፍቃኑ ኃይለ ማርያምን ጠቅላይ ሚኒስትር ሊያደርጉት እየጸለዩ ነው አሉ፤ እርሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነ ማለት ለእኛ እጅግ ክፉ ነገር ነውና የምንችለውን ሁሉ ማድረግ አለብን» ብለዋል

ምንጭ፦ አባ ሰላማ ድረ ገጽ


 ዐቃቤ መንበሩ «መናፍቃኑ ኃይለ ማርያምን ጠቅላይ ሚኒስትር ሊያደርጉት እየጸለዩ ነው አሉ፤ እርሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነ ማለት ለእኛ እጅግ ክፉ ነገር ነውና የምንችለውን ሁሉ ማድረግ አለብን» ብለዋል.
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የኢህአዴግ ሊቀመንብር ሆነው መመረጣቸውንና በቀጣይም ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ቃለ መሐላ የሚፈጽሙ መሆናቸው ከተገለጸ ጊዜ ጀምሮ፣ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ በመሆናቸው ምክንያት በማኅበረ ቅዱሳን መንደርና በቤተክህነቱ አካባቢ ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር ግንኙነት ባላቸው አካላት ዘንድ «ጴንጤ አይገዛንም» የሚል ቅስቀሳ ውስጥ ውስጡን እየተደረገ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡
በዘመን መለወጫ በዓል ላይ በጠቅላይ ቤተክህነት አዳራሽ በተዘጋጀው መርሀግብር ላይ የተገኙትና ንግግር ያደረጉት አቃቤ መንበር አባ ናትናኤል ትዝብት ላይ የጣላቸውን ንግግር ማድረጋቸውን በስፍራው የነበሩ ምስክሮች እየገለጹ ነው። አቡነ ናትናኤል በአቃቤ መንበርነት ከተሾሙ ጀምሮ ጊዜውን እየተሻሙና ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን ለመምሰል ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን እያደረጉ ካለው እንቅስቃሴ መታዘብ ተችሏል፡፡ «እርሳቸው ወንበር ላይ አስቀምጡኝ» ከማለት «እርሳቸው የሚበሉትን ስጡኝ» እስከማለት መድረሳቸውን ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በየዓመቱ በዘመን መለወጫ በዓል ለሚደረገውና ቅዱስ ፓትርያርኩን እንኳን አደረስዎ ለሚባልበት መርሐግብር ከአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት ለተገኙ የደብር አለቆች፣ ካህናትና ዲያቆናት ባደረጉት ንግግር ውስጥ «መናፍቃኑ ኃይለ ማርያምን ጠቅላይ ሚኒስትር ሊያደርጉት እየጸለዩ ነው አሉ፤ እርሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነ ማለት ለእኛ እጅግ ክፉ ነገር ነውና የምንችለውን ሁሉ ማድረግ አለብን» ያሉ ሲሆን፣ ከበዓሉ ጋር የተገናኙ ሐሳቦችን ካቀረቡ በኋላም መጨረሻ ላይ «ቅድም ያነሣሁላችሁ የመናፍቃኑ ጉዳይ ምሥጢር ነውና በምሥጢር ያዙት» ብለዋል፡፡ ይህም የተናገሩት ተገቢ ያልሆነ ቃል እንደወቀሳቸውና ሀሳቡ መጀመሪያም ቢሆን ከራሳቸው ያመነጩት እንዳልሆነ ግምት እንዲወሰድ አድርጓል፡፡ አባ ናትናኤል ከእርጅናም ዲፕሎማሲያዊ አቀራረቡንም በሚገባ ባለማወቃቸው የተነሳ በብዙዎች ፊት የሰነዘሩትን ይህን ሀሳብ እነማንያዘዋል ሹክ እንዳሏቸው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች ገልጸዋል፡፡
አቶ ማንያዘዋል የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ቀብር እለት ወደቤተመንግስት እገባለሁ አትገባም በሚል ቤተመንግስት በር ላይ ከአስተናጋጆች ጋር ሲወዛገብ በቴሌቪዥን መስኮት ያዩትና የሚያውቁት ሁሉ መነጋገሪያ አድርገውት የሰነበቱ ሲሆን፣ «አባ ናትናኤልን ደግፌ የምይዝ ነኝ» በሚል በትግል መግባቱ ታውቋል፡፡ ይህም ማኅበሩ ቀድሞም ያደርግ እንደነበረ የሚፈልገውን በእርሱ በኩል ወደአባ ናትናኤል እያቀረበ ለመሆኑ በቂ ምስክር ነው ይላሉ ታዛቢዎች፡፡ የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ሹመት በመቃወም በዋናነት እያቀነቀነ የሚገኘው ማኅበረ ቅዱሳን መሆኑን ምንጮቻችን እየተናገሩ ነው፡፡ ቤተክህነት አካባቢ «ጴንጤ ሊገዛን አይገባም» የሚል ወሬ እያናፈሰ ሲሆን፣ አንዳንድ ወዳጆቹ ጳጳሳት ግን «ከዚህ በኋላ አንዳች ስሕተት ከተገኘባችሁ የምትከፍሉት ዋጋ ቀላል አይሆንምና ሁሉን ነገር በጥንቃቄ ነው ማድረግ ያለባችሁ» የሚል ምክር እንደለገሷቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡