Sunday, September 16, 2012

«ሰምና ወርቅ»


 ከካሳሁን ዓለሙ ድረ ገጽ ተመርጦ የተወሰደ ቅኔ፤
*********************
እንኳን ደኅና ገባህ ከሄድክበት አገር፣

ጠላቶችህ ሁሉ ይቅር ብለው ነበር፡፡

***************

‹ትግራይ› አይደለም ወይ መለስ ትውልድህ፣

የጁ ነው በማለት የደበደቡህ፡፡
*****************

‹መለስ ዜናዊ› ታላቅ መስፍን፣

ነበሩ ሲሉ ባገራችን፣

እንዲያ ሳያጡ ሰገነት፣

ምነው አደሩ ፈረስ ቤት፣

ሞከሩት እንጂ አልኖሩም፣

ከዳሞት አልቀሩም፡፡

***************
በዓለ ድባብ ንጉሥ ባለ ጥና አቡን፣

እየዞሩ ፈቷት አገራችንን፡፡
****************

አሁን ምን ያደርጋል ሱሰኛ መሆን፣

ብዙ ቤት ፈረሰ ትላንት በዚያ ቡን፡፡
***************

ይድናል እያልን ዓይን ዓይኑን ስናይ፣

እንዲያ እንደፈራነው እውነት ሞተ ወይ?
************

የዛሬ ዘመን ወዳጅም፣

ከሽሕ አንድ አይገኝም፣

አንቱ ብትለው ይኮራል፡

አንተ ያልከው ግን ይኖራል፡፡
*********

አሻግሬ ባይ መንገዱን፣

ኧረ ሰው ምናምን፡፡
************
ተስቦ ገብቶ ከቤቴ፣

አልወጣ ካለኝ ዓመቴ፡፡
**************

ወደ አደባባይ ወጥተህ፣

ከባላጋራህ ተሟግተህ፣

ክርክር ገጥመህ ወደ ማታ፣

ዓለም አፈር ነው ስትረታ፡፡
***************
‹ዋልድባ› ወርጄ ቀስሼ፣

ልብሰ ተክህኖ ለብሼ፣

ታዩኛላችሁ እኔን

ነገ ገብቼ ሣጥን፡፡
**************

ክፉ ቢናገር ተቆጥቶ፣

ጠላትህ ደሙ ፈልቶ፤

እሱም እንዳንተ ሰው ነው

ኧረ ተው ሰብቀህ አትውጋው፡፡

Friday, September 14, 2012

ከተማን በመግዛትህ ሁሉን እገዛለሁ አትበል!


ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ምእራፍ ከተባለ መፅሄት ጋር ያደረጉትቃለመጠይቅ፣
           በጣም የሚወዱትን መዝሙር ይንገሩኝ?
           አቶ ኃ/ማርያም፡- ‹‹እኔም እንደ ዳዊት ጨርቄን ልጣልልህ›› የሚለውን
           ጉባዔ ገብተው ሲያመልኩ ግን እንደ ባለሥልጣን የፕሮቶኮል ነገር አለ፡፡ የጥበቃ ጉዳይ አለ፡፡ ሌላም ሌላም፡፡ ይሄን ሁሉ ረስተው በነጻነት ለማምለክ አይቸገሩም?
አቶ ኃ/ማርያም፡ ምንም አልቸገርም፡፡ ጉባዔ ውስጥ ካለሁ እኔ ስለ ራሴ ጨርሶ አላስብም፡፡ እነ ንጉሥ ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት ጨርቃቸውን ጥለው ያመልኩ ነበር፡፡ እኔስ የማመልከው እግዚአብሔር ፊት እንደሆንኩ እንጂ የማስበው ሌላ ነገር አላስብም ማልቀስ ካለብኝ አለቅሳለሁ፣ መንበርከክ ካለብኝ እንበረከካለሁ፡፡ ጌታ ሁን ያለኝን ሁሉ ለመሆን ዝግጁ ሆኜ ነው የማመልከው፡፡
ልጆችዎ በቤተክርስቲያን ውስጥ የመክሊት (የአገልግሎት) ሥራ ውስጥ ሲሳተፉ ይታያል፡፡ የእከሌ ልጅ ነኝ እኮ ብለው ሳይኩራሩ ወንድሞችና እህቶች የጠጡባቸውን የሻይ ብርጭቆዎች እየዞሩ ሲለቅሙ እንዳየ ወንድሜ ፍጹም ነግሮኛል፡፡ በቤት ውስጥ ምን ብለው ቢያስተምሯቸው ነው?
አቶ ኃ/ማርያም፡- እኔም ባለቤቴም ቤት ውስጥ ሁሉም የምንነግራቸው ነገር እኛ ጋር ምንም እንደሌለ እኛ ምንም እንዳልሆንን ሀብታችን ኢየሱስ እንደሆነ የማወርሳቸውም አምላኬን እግዚአብሔርን ብቻ እንደሆነ ነው የምንነግራቸው፡፡ አንተ የራስህ መኪና እንኳን የለህም፡፡ ቤት የለህም፣ አሁን እናንተ አንድ ነገር ብትሆኑ እኛ ምን አለን? ሲሉኝ እንኳን የምመልስላቸው መልስ የለንም ግን መኪና አጥተን እናውቃለን ወይ? ቤትስ አጥተን ማደሪያ አጥተን እናውቃለን ወይ? መኪና ብገዛም ቤት ቢኖረንም የእኛ አይደለም፡፡ ሁሉንም ትተነው ነው የምናልፈው፡፡ ሀብታችን ጌታ ብቻ ነው እላቸዋለሁ፡፡ በአገልግሎት እንዲበረቱም እንመክራቸዋለን፡፡
ለአገልግሎትና የክርስቶስን አካል ለማነጽ ልዩ ልዩ ጸጋ ይሰጣል፡፡ ለእርሶ የተሰጦት የጸጋ ዓይነት ምንድነው?
አቶ ኃ/ማርያም፡ እንግዲህ ጥሪ የተለያየ ነው፡፡ ሁላችንም መሰዊያ ላይ ቆመን አንሰብክም፡፡ እኔን ደግሞ የሰጠኝ የሚመስለኝ ጸጋ ሕዝብን እና አገርን በመልካም አስተዳደር ማገልገል ነው፡፡ ስለዚህ ለእኔ ሥራዬ ስራ ብቻ ሳይሆን አገልግሎትም ጭምር ነው ብዬ የተቀበልኩት፡፡
አቶ ኃ/ማርያም ጠዋት ከመኝታዎ ስንት ሰዓት ይነሳሉ?
አቶ ኃ/ማርያም፡/ሳቅ ብለው/ መመለስ አለብኝ እኔ ሁልጊዜ ከእንቅልፌ ምነሳው ከለሊቱ 11 ሰዓት ነው፡፡ ጉዞ፣ እንደዚህ አይነቱ ነገር ካልረበሸኝ በስተቀር 11 ሰዓት እነሳለሁ፡፡ ከ11 ሰዓት እስከ 12 ድረስ የፀሎት ጊዜዬ ነው፡፡ ከ12 እስከ 12፡30 ትንሽ ‹‹ኤክሰርሳይስ›› (ስፖርት እሰራለሁ፡፡ በቀሪው ጊዜ የዕለቱን የቢሮ ስራ አዘጋጅቼ 1፡30 አካባቢ ወደ ቢሮዬ እሄዳለሁ፡፡
አዘውትረው የሚጸልዩባቸው ጉዳዮች አሉ ካሉ ቢያስታውቁን?
አቶ ኃ/ማርያም፡እኔ ዘወትር በአራት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ እጸልያለሁ፡፡ አንደኛ ሰላምና በረከት ለዚህች አገር እንዲበዛ እጸልያሁ፡፡ ለመሪዎቿ፣ ለመንግሥት፣ ባለሥልጣናት ጥበብና ማስተዋልን እንዲሰጥ እጸልያሁ፡፡ ሁሉም ሃይማኖቶች ያለ አድልዎ እና ልዩነት በእኩልነት እና በመቻቻል እንዲኖሩ እመኛለሁ፡፡ ሁለተኛ የእግዚአብሔር ቃል ‹‹ሰው ሁሉ ወደ መዳን እንዲመጣ›› ይላል፡፡ ስለዚህ ሰው ሁሉ እንዲድን እጸልያለሁ፡፡ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነውና፡፡ ሶስተኛ እናቴ አልዳነችምና ለወላጅ እናቴ በተለይ እጸልያለሁ፡፡ አራተኛ ለልጆቼና ለቤተሰቤ ዘወትር እጸልያለሁ፡፡
እንደው በግልጽ ለመጠየቅ ያህል ወደ ሥልጣን ሲመጡ አብረው የሚመጡና ለመሥራትም የሚመቹ የኃጢአት ፈተናዎች ይኖራሉ፡፡ እርስዎ እስካሁን ድረስ የገጠምዎትን ፈተና በምን መንገድ አልፈውታል?
አቶ ኃ/ማርያም፡ የእውነት ለመናገር እስካሁን እግዚአብሔር ረድቶኛል፡፡ በፈተናዎቹ አልፌአለሁ እላለሁ፡፡ ይሄን ከልቤ ነው የምልህ፡፡ ንጉሥ ዳዊት የተከበረ በእግዚአብሔር ዘንድም የተወደደ በብዙ ነገር በጣም የተመሰገነ ንጉሥ ነበር፡፡ እስራኤልን የሚመስል ትልቅ ሕዝብ መግዛት የቻለ ዳዊት ግን ራሱን መግዛት አልቻለም ነበር፡፡ ለዚህ ነው መጽሐፍ ቅዱስ ከተማን ከመግዛት ይልቅ ራስን መግዛት ይበልጣል ያለው፡፡ ነገር ግን መጽሐፉ የሚመክረው ራስን ቤተሰብን መግዛት እንድንችል ነው፡፡ አለ አይደል ከተማን በመግዛትህ ሁሉን እገዛለሁ አትበል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ውስጣዊ ሰብዓዊ ውድቀት ሊኖርብህ እንደሚችል አስበህ ጥንቃቄ አድርግ፡፡ ጥንቃቄ ይጠብቅሃል አይደል የሚለው መጽሐፍ ቅዱስ፣ ዝሙት ሊያታልህ ይችላል፡፡ ዝሙት እንዳይጥልህ ጥንቃቄ አድርግ፡፡ የሥጋ ምኞት፣ ገንዘብ ፍቅርና የዓይን አምሮት የሚባሉት አይደሉም ሰውን የሚጥሉት፡፡ ስለዚህ ከተማን የገዛ ሰው፣ በተለይ እነዚህ ሶስት ነገሮች ላይ መጠንቀቅ አለበት፡፡ እኛ ኢህአዴጎች ስኳር ነው የምንለው፡፡ ስኳሩ እንዳያታልልህ ጥንቃቄ መደረግ አለበት ነው ሀሳቡ፡፡ ፓርቲዬን በጣም የምወድበት ትልቁ ምክንያት ሙስናን፣ ያለ አግባብ፣ ጥቅም ለማግኘት የሚደረግን ጥረት ፓርቲዬ የኪራይ ሰብሳቢ አመለካከት የሚላቸው በሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተወገዙ ናቸው፡፡ እነዚህ መሰረታዊ መርሆች ከመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮት ጋር ይጣጣሙልኛል፡፡ አይቃረኑም፡፡ ስለዚህ ሙስና፣ አላስፈላጊ ጥቅማጥቅሞች፣ ውሸት ውስጥ ሳትገባ ሕዝብን ማገልገል አለብህ ስለሚል የኔ ፓርቲ እነዚህን መርሆዎች ስለሚያራምድ ይህ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስለሆነ በጣም ደስ ብሎኝ ነው የምሰራው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ አንተ ራስህ ከእግዚአብሔር ጋር ንስሐ በመግባት የምትፈታው ነገር ከተገኘ ተገምግመህ እንድትስተካከል ይሆናል ወይም ደግሞ ልትባረርም ትችላለህ፡፡ ስለዚህ ፓርቲዬ በዚህ ጉዳይ ላይ በጣም በጣም ጠንካራ አቋም አለው፡፡ እና በዚህ ዓይነት ነው፡፡
የሚጸጸቱበትን ውሳኔ አስተላልፈው ያውቃሉ?

Thursday, September 13, 2012

«ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም!»

«እናንተ ብትገቡበት አያቅታችሁም፤በቤተ ክህነት አጽናኝም አሸባሪም መኖሩን የተናገሩት» አባ  ኤልሳዕ የደቡብ ጎንደር ሊቀ ጳጳስ

«ማኅበረ ቅዱሳን ቅዱስ ሲኖዶስን በዙሪያው ኾኖ የሚጠብቅ፣ የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔዎች በማስፈጸም ረገድም ቋሚ ተጠሪ ነው»
አባ ማትያስ የካናዳ ሊቀ ጳጳስ
«የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነት እንዳይናጋ “በወርድም በቁመትም መሥራቱን” አጠናክሮ እንዲቀጥል» አባ ገብርኤል የሃዋሳ ሊቀ ጳጳስ
«ማኅበሩን መደገፍ ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል እንደኾነ» ቄስ ኃ/ሥላሴ ዓለማየሁ
ከ40 ሚሊዮን ተከታዮች በላይ ያሏትን ቤተክርስቲያን ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ የገጠሪቱ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ድረስ የመምራትና የማስተዳደር ሥልጣን የተረከቡ ሊቃነ ጳጳሳት ከቤተክርስቲያኒቱ የምእመናን ማኅበር አንዱ አባል ለሆነው ለማኅበረ ቅዱሳን ይህን ያህል «ተቀመጥ በወንበሬ፤ ተናገር በከንፈሬ» ዲስኩር ለማሰማት መድረሳቸው በእርግጥም የቤተክርስቲያኒቱ መሪዎች እግዚአብሔርን ተስፋ ከማድረግ ወርደው፤ መንፈስ ቅዱስን አጋዥና መሪ ከማድረግ ወጥተው፤ ማኅበረ ቅዱሳን የቤተክርስቲያኒቱ መንፈስ ቅዱስ ስለሆንክ አንተ ምራን ከሚሉበት ደረጃ መድረሳቸው አሳዛኝም ፤አሳፋሪም ነው።
አባ ኤልሳዕ የደቡብ ጎንደር ሊ ቀጳጳስ በሁለቱ ሲኖዶስ መካከል ያለውን ቅራኔ ለመፍታት ማኅበረ ቅዱሳን ቢገባበት ምንም የሚያቅተው እንደሌለ መናገራቸው ሲሰማ በእርግጥ እኒህ አባት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ይመራሉ? ብለን እንድንጠይቅ እንገደዳለን። የ21 ዓመቱ ክፍፍል ሊያበቃ ያልቻለው ለካ፤ በሥጋዊ መንፈስ እየተመሩና የመንፈስ ቅዱስን ኃይል ታምነው እንዳልነበረ ከማሳየቱም በላይ ዛሬም ከዚያው ስህተታቸው ሳይላቀቁ ማኅበረ ቅዱሳንን ለማስቀደም መድፈራቸውን ስንመለከት ቤተክርስቲያኒቱ የምትመራው በእነማን እንደሆነ ቁልጭ ብሎ ይታየናል።  «እናንተ ብትገቡበት አያቅታችሁም» ማለታቸው የሚያሳየው እስከዛሬ የዘገውም ማኅበረ ቅዱሳን በእርቁ ውስጥ የማሸማገል ሚናውን ስላልተወጣ ነው ማለታቸው ነው። ሲኖዶሱ ደካማና ለእርቁ መፈጸም አቅም የሌለው በመሆኑ እስካሁን የመዘግየቱ ምክንያት እንዲህ ከተገለጸላቸው ታዲያ ለምን ማኅበረ ቅዱሳንን የሲኖዶሱ የእርቁ ቋሚ ተጠሪ አድርገው በመሾም ቶሎ እንዲፋጠን ያላደረጉ? በዚያውም ደግሞ በሲኖዶስ ጉባዔ ላይ እንደፓርላማ ደንብ በአጋር ድርጅትነት ወንበር የማይሰጡት?
ማኅበረ ቅዱሳን የራሱ የሆነ  የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅድ ያለው ድርጅት ነው። በዚህ ስውርና ግልጽ የዓላማዎቹ ጉዞ ላይ የሚቀበሉትን እስከነጉድፋቸው ተሸክሞ ለመጓዝ የማይጠየፍ፤ የማይቀበሉትን ደግሞ ምንም እንኳን ንጹሐን ቢሆኑ አራግፎ ለመጣል ጥቂት የማያቅማማ ድርጅት እንደመሆኑ መጠን እነ አቡነ ኤልሳዕን የመሳሰሉ ታማኞች  «አንተ ስላልገባህ እኛ አቅቶናል» የሚል ድምጸት ያለውን ቃል ቢናገሩለት ማን መሆናቸውን ከሚያሳዩ በስተቀር ስለማኅበረ ቅዱሳን ሁሉን አዋቂነትና የመፍትሄ ቁልፍነት መናገራቸው ማንንም አያሳምንም።
ሌላው አባትም ገና ከወደ ካናዳ ብቅ ከማለታቸው «እስመ አልቦ ነገር ዘይሰዓኖ ለማኅበረ ቅዱሳን» የሚል ትርጉም ያለውን ቃል ሲናገሩ መስማት ለጆሮ ይቀፋል። እሳቸው የተናገሩት ነው ተብሎ በደጀ ሰላም የሠፈረውን ይህን ቃል መዝኑት።
«ማኅበረ ቅዱሳን ቅዱስ ሲኖዶስን በዙሪያው ኾኖ የሚጠብቅ፣ የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔዎች በማስፈጸም ረገድም ቋሚ ተጠሪ ነው»
ማኅበረ ቅዱሳን እውነት የሚታዘዝ ሆኖ ከሆነ ይታዘዛል፤ ይላካል፤ የሲኖዶሱን ትእዛዝ ተግባራዊ ለማድረግ ሲጠሩት አቤት፤ ሲልኩት ወዴት ይላል ብሎ ታዛዥነቱን መግለጽ አንድ ነገር ነው። ነገር ግን ማኅበረ ቅዱሳን፤ ቅዱስ ሲኖዶስን በዙሪያው ኾኖ ይጠብቀዋል ማለት ማኅበረ ቅዱሳን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ኾኗል ማለት ነው።  ቅዱስ ሲኖዶስ ዙሪያውን ሆኖ የሚጠብቀው መንፈስ ቅዱስ ነው ወይስ ማኅበረ ቅዱሳን? የሲኖዶሱ አባል አባ ማትያስ ግን ሲኖዶሱ ዙሪያውን ሆኖ የሚጠብቀው ማኅበረ ቅዱሳን ነው ሲሉ በግልጽ መናገራቸው ማኅበረ ቅዱሳን ሁሉን ማድረግ እንደሚችል የማወጃቸው ነገር አስገራሚ ነው። ሲኖዶሱ በምን ዓይነት ሰዎች እንደተሞላ ከማሳየት አልፎ ፓትርያርክነቱን ለማግኘት ስለማኅበረ ቅዱሳን ታላቅነት መማል ፤ መገዘት የግድ ሆኗል ማለት ይቻላል።
አባ ማትያስ የሲኖዶሱ ጠባቂ ማኅበረ ቅዱሳንን ከማድረጋቸውም በላይ የሲኖዶሱን ውሳኔዎች ለማስፈጸም የሲኖዶስ ቋሚ ተጠሪ መሆኑንም አያይዘው አውጀውልናል። አሁን እንግዲህ ማኅበረ ቅዱሳን ከማኅበር ጣሪያ በላይ ወጥቷል። ከእንግዲህ ማኅበረ ቅዱሳን ድስት ያላጠለቀ ሲኖዶስ ነው ማለት ነው። በንግግር መሳት ካልቀረ እንደእነ አቡነ ማትያስ ጭልጥ ብሎ መንጎድ እግዚአብሔር ሲኖዶስን ይጠብቃል፤ ሥራውን ሁሉ ያከናውናል እስኪባል ድረስ የሲኖዶስ ጣዖት ሆኖ ማኅበረ ቅዱሳን ይቀጥላል ማለት ነው።
እነሱው በሰጡህ ፈቃድ መሠረት የሲኖዶስ ጠባቂ ማኅበረ ቅዱሳን ሆይ እነዚህን ጳጳሳት ጠብቅ፤ ከፍ ከፍም አድርጋቸው!!! እንላለን።
ሌላው ሊቀ ጳጳስ ደግሞ አባ ገብርኤል ናቸው። በመሠረቱ አባ ገብርኤል ከሲኖዶሱ ይልቅ በማኅበረ ቅዱሳን እንደሚታመኑና እንደሚመኩ ይታወቃል። አባ ገብርኤል ወደ ምድረ አሜሪካ ኰብልለው በመሄድ ኢህአዴግ ይውደም፤ አባ ጳውሎስ ይውረዱ በማለት የፖለቲካ ሰልፍ ሲመሩ እንደነበሩ መረጃዎቻችን ያሳያሉ። ከዚያም በድርድር ይሁን በእርቅ ለጊዜው በማይታወቀው ምክንያት ግሪን ካርዳቸውን ይዘው ወደ አዲስ አበባ በሁለት ዜግነት መግባታቸውን ደግሞ አየን። በእርግጥ ሰው ከስህተቱ ቢታረም አያስገርምም። አባ ገብርኤልን ስንመለከት ከስህተት የሚማሩ አይመስሉም። ዛሬ ደግሞ የዳቦ ስሙን ላወጡለት ማኅበር እንዲህ ሲሉ ይደመጣሉ።
«የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነት እንዳይናጋ “በወርድም በቁመትም መሥራቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል»  ማኅበረ ቅዱሳን ያስፈልጋል ይሉናል።ኧረ ለመሆኑ  የቤተክርስቲያኒቱ አንድነት እንዳይናጋ፤ በወርዷም፤ በቁመቷም ለመስራት አልነበረም እንዴ አባ ገብርኤል ጵጵስና የተሾሙት?  በተሰጣቸው ጵጵስና መስራት ካቃታቸው ለሰጠቻቸው ቤተክርስቲያን መመለስ እንጂ ቤተክርስቲያንን እንዲመራ ውክልና ለሌለው ማኅበር ከወርድ እስከቁመቷ እንዲያዝባት እነሱ ደግሞ በተራቸው አሳልፈው እንዴት ይሰጣሉ?
ሲኖዶሱ ከመንበረ ፓትርያርክ አንስቶ እስከ ገጠሪቱ የሳር ክዳን አጥቢያ ድረስ መዋቅሩን የዘረጋው በወርዷም፤ በቁመቷም ለመሥራት አይደለም እንዴ?   አባ ገብርኤል ግን ያቃተቸው ይመስላል። ይልቁንም እኛ ስራውን ሁሉ ለማኅበረ ቅዱሳን እናስረክብና በወርዷም፤ በቁመቷም እሱው ይዘዝባት እያሉ አዋጅ ማስነገር ይዘዋል። አባ ገብርኤልስ የሌላ ሀገር ዜግነት ስላላቸው ነገር ዓለሙ መበላሸቱን ሲያዩ እብስ ብለው ወደ ጥንት የሰልፍ ሀገራቸው አሜሪካ ሊሄዱ ይችላሉ! ማኅበረ ቅዱሳን እንኳን በወርድ በቁመቷ፤ አንዲት ጋት በቤተክርስቲያን ላይ የማዘዝ መብት የለውም የሚሉ የቤተክርስቲያን ልጆችንስ ጅቡ ማኅበር ይዋጣቸው ማለት ነው?
እስከሚገባን ድረስ የቤተክርስቲያኒቱ ራስ እግዚአብሔር ነው። አንዳንድ ጳጳሳት ጠባቂያችን ማኅበረ ቅዱሳን ቢሉም እስከሚገባን ድረስ የሲኖዶሱ ጠባቂ መንፈስ ቅዱስ ነው። እግዚአብሔርን ራስ አድርጎ ሲኖዶሱ በመንፈስ ቅዱስ ኃይልና መገለጥ ቤተክርስቲያንን በወርድና በቁመቷ ይመራታል እንላለን። ከእነ አባ ገብርኤል የተገኘው አዲስ ግኝት ግን በወርድና በቁመቷ ለመሥራት ሥልጣኑ የማኅበረ ቅዱሳን ሆኗል። አባ ገብርኤል ፓትርያርክነቷ ተወርውራ እኔ ጋር ትደርሳለች ብለው አስበው ይሆን?
አንድ ጊዜ ሥልጣናቸው ተገፎ አቶ ኢያሱ የተባሉ፤ ሌላ ጊዜ ደግመው ኮብልለው የፖለቲካ ሰልፍ ሲመሩ የነበረ፤ በኋላም ተመልሰው የወደዷቸውን ጸረ ኢህአዴጎችን ከአሜሪካ ከድተው ፤ የጠሉትን ኢህአዴግን ወደው፤ የጽዋውን ማኅበር ማኅበረ ቅዱሳንን አነግሳለሁ እያሉ በአደባባይ በማወጅ የተጠመዱና በአንድ ቦታ በአንድ ቃል የማይረጉ አባ፤  እንኳን ፓትርያርክ ሊመረጡ ለእጩነትም ሊቀርቡ ተገቢ አይደለም። መጽሐፍ  «በዲያብሎስ ነቀፋና ወጥመድም እንዳይወድቅ፥ በውጭ ካሉት ሰዎች ደግሞ መልካም ምስክር ሊኖረው ይገባዋል» ይላልና። አባ ገብርኤል ለምንም ሹመት የሚበቁ አይደሉም እንላለን። « ሆያ ሆዬ ጉዴ ፤ብሯን ብሯን ይላል ሆዴ» እንደሚሉት የሆያ ሆዬ ጫወታ የእሳቸውም ሆድ ቁንጮዋን መጨበጥ ስለሆነ ሆዳቸውን እየቆረጠ እንዳይቸገሩ ቁርጣቸውን ማሳወቅ ተገቢ ነው።