Saturday, August 4, 2012

በድንግል ማርያም ትንሣዔና እርገት ታሪክ ላይ ችግር አለ!


ቅዱሳንን ስለማክበር ምንም ጥያቄ የለንም። መታሰቢያ ማድረግም የነገሮችን ሁሉ ባለቤት እስካልተካ ድረስ የሚደገፍ ነው። ነገር ግን  «ጥቂት አሻሮ ይዞ፤ ዱቄት ወዳለው መጠጋት» የሚለውን ብሂል ለመተግበር መሞከር ግን ተቀባይነት አይኖረውም። በተለይም በሃይማኖታዊ አስተምህሮ ወቅት ወንጌል እንደዚህ ስለሚል፤ እኔም እንደዚህ ብል ችግር የለውም የሚለውን ራስን መሸሸጊያ ምክንያት በማቅረብ ለመከለል መሞከር አያዋጣም። ብዙ ጥያቄዎችን የሚያስነሱትና እነዚህ የመሳሰሉ የስህተት ችካሎች አልነቀል ያሉት በምክንያት ስር በመወሸቃቸው ነው። ራሱን የማርያምን እረፍትና ትንሣዔ ሳይሆን በማርያም እረፍት፤ ቀብር፤ ትንሣዔና እርገት ላይ ያሉ አስተምህሮዎችን ለመቃኘት እንሞክራለን።
ስለማርያም እረፍት፤ ትንሣዔና እርገት አብያተ ክርስቲያናት አንድ ዓይነት የእምነት አቋም የላቸውም። እንዲያውም ስለማርያም ሞትና የእርገት ዕለት በግልጽ የሚታወቅ ማስረጃ እንደሌለ በ5ኛው ክ/ዘመን  የኖረው የሳላሚሱ ኤጴፋንዮስ   ተናግሯል። [ 1 ] ዕረፍቷና እርገቷ በኢየሩሳሌም እንደሆነ  የሚናገሩ ቢኖሩም  ይህንን አባባል የማይቀበሉ አብያተ ክርስቲያናትና የቴኦሎጂ ምሁራን ሞልተዋል። በኢየሩሳሌም አርፋለች የሚለውን አባባል የማይቀበሉበትን ማስረጃ ሲያቀርቡም ዮሐንስ በወንጌሉ ላይ እንደተናገረው «እናትህ እነኋት አለው። ከዚህም ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ወደ ቤቱ ወሰዳት»  ዮሐ19፤27 ባለው መሠረት ማርያም እስከ ሕይወቷ ፍጻሜ ድረስ ከዮሐንስ ጋር ስለኖረችና ወንጌላዊው ዮሐንስም ከጌታ ሞት በኋላ በኢየሩሳሌም  ጥቂት ዓመታትን ከቆየ በኋላ በ37 ዓ/ም ገደማ ወደ ቤዛንታይን ከተማ ኤፌሶን ሄዶ ወገኖቹን ወንጌል እያስተማረ መቆየቱንና  ማርያም በሞት እስከተለየችው ድረስ  ከ48-52 ዓ/ም እዚያው እንደነበር ብዙ ተጽፏል። ከማርያም ክፍል ትይዩ ያለው የዮሐንስ መኖሪያ ቤት ፎቶ፤

 በኋላም  በቅርብ ርቀት ባለችው ደሴተ ፍጥሞም  በግዞት መኖሩ ይነገራል ።  አንዳንዶች ከዶሚኒሽን አገዛዝ ቀደም ብሎ የራእይ መጽሐፉን  ከ55-65 ዓም ገደማ እንደጻፈም  ይናገራሉ።
ዋናው ነገር  ማርያም በኤፌሶን ከዮሐንስ ጋር ኖራለች  ወይስ አልኖረችም ነው ጥያቄው።  በኢየሩሳሌም አርፋለች የሚሉ ሰዎች አንድም ጊዜ ከዮሐንስ ጋር በኤፌሶን ኖራለች ሲሉ አይደመጥም። ለምን?  ዮሐንስ ማርያምን እንደእናት ሊይዛት አደራ ተሰጥቶታል የሚባል ከሆነ ከዮሐንስ ጋር ኤፌሶን ስለመቀመጧ የማይነገረው ለምንድነው?  ዮሐንስ እስከ 96 ዓመቱ ድረስ ከኤፌሶንና ከደሴተ ፍጥሞ ውጪ ስለመኖሩ የተነገረ ነገር የለም። ማርያም ከዮሐንስ ጋር በኤፌሶን አልኖረችም ብሎ በመከራከርና በኢየሩሳሌም ኖራ፤ እዚያው ማረፏን በግልጽ በመናገር  መካከል ልዩነት አለ።  «እነኋት እናትህ» ባለው መሰረት አብረው ኤፌሶን ኖረው እዚያው ማረፏን የማይቀበሉና  ኢየሩሳሌም ኖራ አርፋለች የሚሉ ሰዎች እንደልጅና እናት አብረው የመኖራቸውን የወንጌል ቃል መካድ ሊሆንባቸው የግድ ነው። ያ ደግሞ እስከ ሕይወቷ ፍጻሜ በኢየሩሳሌም ኖራ እረፍቷም፤ ቀብሯና እርገቷ ሆነ ከሚለው አስተምህሮአቸው ጋር «እነኋት እናትህ» የሚለው  የወንጌል ቃል ስለሚጋጭባቸው ለዚህ ዓይነት ያፈጠጠ እውነት ምን እንደሚሉ አይታወቅም። ወይ ደግሞ ኤፌሶን ላይ እድሜውን ሙሉ የኖረው ዮሐንስና ኢየሩሳሌም ማርያምን ይዞ የኖረው ዮሐንስ የተለያዩ ናቸው ሊሉ ይገባል።
ሮበርት ክሬው የተባለ የነገረ መለኮትና የታሪክ ጸሐፊ ዮሐንስ ወንጌላዊ ዘመኑን ሁሉ በኖረበት ከኤፌሶን ከተማ 8 ኪሎ ሜትር ወጣ ብላ ባለች ኰረብታ ላይ በተሰራ ቤት ውስጥ እንደኖረና ማርያምም እዚያ ማረፏን ጽፏል።  ይህንን በኤፌሶን ያለውን የማርያምን መቃብር የዓለም ክርስቲያኖች እንዲሆም ሙስሊሞች ሳይቀሩ ይጎበኙታል፤ ይሳለሙታል።  በቱርክ ግዛት ያለው ይህ ስፍራ በቱርካውያን ሙስሊሞች ዘንድ «ሜሪዬማና» ተብሎ ይጠራል።  ይህ ስዕል የሚያመለክተው ያንን ስፍራ ነው።

ቅድስት ድንግል ማርያም ከዚህ ዓለም የተለየችው መቼ ነው? ለሚለው ጥያቄ ጥንታዊያን አብያተ ክርስቲያናት የሚባሉት የምሥራቁና የምዕራቡ ጎራዎች የተለያየ አመለካከት አላቸው።
 በተወለደች በ58 ዓመቷ ዐርፋለች የሚሉ አሉ። በ72 እና 63 እድሜዋም አርፋለች የሚሉ መረጃዎች አሉ። እንደ ግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ግን የሚታመነው በ64 ዓመት እድሜዋ ማረፏ ነው።  ኖረችበት ተብሎ ከሚገመተውና አርፋለች ከሚባለው ቦታ ያለው ልዩነት እንዳለሆኖ በጥር ወር ከዚህ ዓለም ተለይታ በ40ኛው ቀን ማረጓን የሚናገሩ አሉ። በነሐሴ ወር አርፋ ከተቀበረች በኋላ ትንሣዔዋን ሳያዩ መቃብሯ ባዶ ሆኖ ስላገኙት ሐዋርያት ሱባዔ ይዘውበሦስተኛው ቀን ተገለጸችላቸው የሚሉም አሉ። እንደኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ደግሞ በጥር ሞታ፤ በነሀሴ ተቀበረች የሚል ትምህርት አለ። በጥር ወር አርፋ፤ በነሀሴ ተቀብራለች የሚሉ ሰዎች ሥጋዋ በገነት ዛፍ ስር ለስምንት ወራት መቀመጡንና በሱባዔ ጸሎት በተደረገው ልመና የተነሳ ለመቀበር መቻሏን አስፋፍተው ይነግሩናል።

Thursday, August 2, 2012

በአሜሪካ ምዕራብ ስቴቶች እየተደረገ ያለው የካህናት ውይይት ተጠናክሮ ይቀጥል!


«ሕመሙን የሸሸገ መድኃኒት የለውም» እንዲሉ አበው በአሜሪካ ምዕራብ ስቴቶች የአድባራት አስተዳዳሪዎችና ልዩ ልዩ ክፍል ሠራተኞች በመካከላቸው ያለውን ፈውስ ያጣ በሽታ ምንነትና መንስኤ በማጥናት ውሳኔ ላይ ለመድረስ መወያየት ከጀመሩ ሰንብተዋል።
አንዳንድ ተሰብሳቢዎች ግን ስብሰባውንና የውይይቱን መንፈስ የሚደግፉ እየመሰሉ ውጤት ላይ ከመድረሱ በፊት መረጃ በማሹለክና የስብሰባውን የውይይት መንፈስ በማጦዝ ጊዜ ሲገድሉ ታይተዋል። በቅዱስ ፓትርያርኩ በኩል ያላቸውን ተደማጭነት ለማስጠበቅ ጠቃሚ ሃሳብ ለጉባዔው የሚያቀርቡ በመምሰልና በሌላ በኩልም በማኅበረ ቅዱሳን በኩል ያላቸውን ስውር ታማኝነት ላለማጣት  በውይይት ወቅት ጊዜ በመፍጀትና አንድ ሃሳብ ላይ ችክ በማለት የሴራ ጥበባቸውን ለማሳየት ሞክረዋል።
ስለሆነም ለካህናቱ የውይይት መንፈስ የምናቀርበው ሃሳብ በሰዎች ብዛትና ባላቸው ታዋቂነት ላይ እምነት ከመጣል ይልቅ ውጤታማ ሃሳብ በሚያቀርቡና ሥራውን ተፈጻሚ ለማድረግ በሚተጉ ጥቂት በሳል ሰዎች ላይ በመመስረት ለመስራት መሞከሩ የተሻለ ነው። ምክንያቱም ይህንን ቀና ሃሳብ የሚደግፉ ብዙ ካህናት ቢኖሩም እንኳን ሸምቆ ወጊው ማኅበር የስም ማጥፋት ዘመቻውን ይከፍትብናል ብለው ይፈራሉ። አንዳንዶችም ከዚያ መሰሪ ማኅበር ጋር ሳይለያዩ እና በቅዱስ ፓትርያርኩ ጋር ሳይላተሙ አስመስለው መኖር የሚፈልጉ ስለሆኑ እንደዚህ ዓይነት ጠቃሚና አስፈላጊ ስብሰባ ላይ ብዙ ሰው ለማሳተፍ መሞከር ትርፉ መረጃ እያሾለኩ እንጀራቸውን የሚጋግሩ ሆድ አደሮችን ማፍራት ስለሆነ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል።
እንደሚታወቀው ማኅበረ ቅዱሳን በአሜሪካ ባሉት አድባራት ውስጥ በፈለፈላቸው ተባይ ደጋፊዎቹ አማካይነት በየአድባራቱ ጉባዔ ውስጥ ሃሳብ በመጠምዘዝ፤ ካህናቱን በማከፋፈል፤ ሽኩቻ የሚፈጥር አጀንዳ በማስነሳት እንቅፋት ሲፈጥር መቆየቱ ያታወቃል። የትም ቦታ የማኅበረ ቅዱሳን ደጋፊዎች እስካሉ ድረስ ሁከትና ብጥብጥ አለ። ሀገሩ የሕግ ሀገር መሆኑ በጀ እንጂ እንደማኅበሩ መሰሪ አባላቱ አካሄድ የቤተክርስቲያን ኃላፊዎች ማኅበሩን ነቅፈውና ተቃውመው አንድም ቀን ስራቸው ላይ መቆየት አይችሉም ነበር። አስተዳዳሪዎች አሜን ብለው እጃቸውን በመስጠት ኪሳቸውን ማስቦጥቦጥ ይጠበቅባቸዋል። እምቢ ካሉ ደግሞ የስድብና የስም ማጥፋት ዘመቻ ይከፈትባቸዋል። አሁንም እየታየ ያለው እውነታ ይህንን ያመላክታል።
ከዚህ በፊት ባቀረብነው ጽሁፋችን እንዳነሳነው የላስቬጋስ  ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን ጢም አልባው መነኩሴ የማኅበሩን ጭነት ተሸክሞ እየተንገዳገደ ሲበጠብጥ፤ የደብሩን አስተዳዳሪ አስፈንጥሮ ለመጣልና በአቡነ ፋኑኤል ላይ የተልእኰ ዘመቻውን በመክፈት ደብዳቤ ሲጽፍ ከመቆየቱ ባሻገር አሁንም ደግሞ አጠናክሮ መቀጠሉ ይሰማል።

Wednesday, August 1, 2012

ይድረስ ለፖሊስ !! "ማኅበረ ቅዱሳን"ም ያደረገው ይህንኑ ነው!


                         ምንጭ፤ http://dejeselaam-dejeselaam.blogspot.com
የእሁድ ሐምሌ 22 ቀን 2004 የፖሊስና ኅብረተሰብ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ፕሮግራም በሀገራችን ስለተከሰተው የአክራሪ ሙስሊሞች እንቅስቃሴ ሰፊ ሽፋን ሰጥቶ አብራርቶታል፡፡ በዘገባው ክቡር ወርቅነህ ገበየሁ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ ሼህ አህመዲን ሼህ አብዱላሂ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚደንት እንዲሁም ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችና የሥራ ኃላፊዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በተሰጠው ማብራሪያ አክራሪዎቹ በሥራ ላይ የነበሩትን ዑለማዎች ከየመስጊዱ በመደብደብና በማባረር፣ ጥበቃዎችን ከየሥራ ክፍሎች በማሰወገድ፣ የድምፅ ማጉያዎችን ከተቆለፈባቸው ቦታ ነቃቅሎ በመውሰድ የመብራት ሲስተሙን በማጥፋት፣ ለሶላት የሄዱትን ወገኖች በማገት፣ እኛ ያልፈቀድንለት ሰው አያስተምርም፣ በማለት እጅግ አሳፋሪ እና የአሸባሪነት ድርጊት መፈጸማቸውን ገልጸዋል፡፡ ይህ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው የጽንፈኝነት አካሄድ መሆኑ ጭምር ተብራርቷል፡፡
በእርግጥ አንድ ሕጋዊ ተቋም ባወጣው ድንጋጌ መሠረት ሊተዳደር የግድ ነው፡፡ በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት የሚወከሉ ባለሥልጣናቱ ሥራቸውን በአግባቡ መምራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚህ ውጪ በኃይል የሚደረግ እንቅስቃሴ ሁሉ ፀረ ሠላም መሆኑ ሊሠመርበት ይገባል።
የፖሊስ ቴሌቪዥን ፕሮግራም ክፍል ከወደ ሙስሊሞቹ በኩል ያጣራው ሐቅ እንደተጠበቀ ሆኖ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በኩልም የጽንፈኝነት አካሄድ ያለው ቡድን መኖሩ ሀገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው፡፡ ይኸው ቡድን ማለትም "ማኅበረ ቅዱሳን" አባላቶቹ በቤተክርስቲያን የተወከሉ አባቶችን ሥልጣን በመጋፋት፣ የማይተባበሯቸው ካህናቶችን በመስደብ፣ በመደብደብና በማሳደድ፣ ተመሳሳይ ጥፋት ፈጽመዋል፤ እየፈጸሙም ነው፡፡
በተለይም ሀዋሳ እና አዲስ አበባ ላይ የተፈጸመው እንደማሳያ ቢሆን በቅዳሴ ሰዓት የድምፅና የመብራት ሲስተሙን ቆርጠዋል፤ የጄኔሬተር ክፍሉን ቁልፍ በመስበር በራሳቸው ቁልፍ ከርችመዋል፡፡ በጥቅምት 2004 የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ዋዜማ ላይ የአባቶችን ሥርዓተ ፀሎት ደወል በመደወልና ከፍተኛ ድምፅ በማሰማት አውከዋል፡፡ በክብረ መንግሥት ከተማ የየካቲት ኪዳነ ምሕረት ዓመታዊ በዓለ ንግሥ እንዳይካሄድና ታቦት ከመንበሩ ወጥቶ ዑደት እንዳይደረግ የሁከት እንቅስቃሴ ፈጽመዋል፡፡
"ማኅበረ ቅዱሳን" ከመስከረም 12 ቀን 2002 . ከተካሄደው ሀገር አቀፍ የሠላም ጉባዔ ወዲህ እንኳን የፈጸማቸው ድርጊቶች ለቁጥር ይታክታሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ ቤተክርስቲያን ላወጣችው ሕግና መመሪያ እንደማይገዛ በይፋ አሳይቷል፡፡ ፖሊስ በያዘ እጁ ከጠቅላይ ቤተክህነት እስከ አጥቢያ ቤተረክርስቲያናት እንዲሁም ሁከት በተካሄደባቸው ከውጭ ሀገር እስከ ሀገር ውስጥ በአዲስ አበባ፣ በደሴ፣ በኮምቦልቻ፣ በአርባ ምንጭ፣ በክብረ መንግሥት፣ በሞያሌ፣ በዲላ፣ በሐረር፣ በሀዋሳ፣ በአዲግራት፣ በሎስ አንጀለስ፣ በዳላስና በሌሎችም ሀገረ ስብከቶችና ከተሞች የፈጸማቸው የሁከትና የሽብር ድርጊቶች ኅብረተሰቡን ጭምር በማነጋገር ሰፊ ጥናት ቢያካሂድ ሕዝብና ሀገርን፣ መንግሥትንና ቤተክርስቲያንን ይታደጋል የሚል እምነት አለን፡፡ "ማኅበረ ቅዱሳን" አደረጃጀቱና አባላቱ ህቡዕ የሆኑ፣ የገንዘብ ዝውውሩ ሚስጥራዊ የሆነ፣ የንብረትና የገንዘብ አስተዳደሩን ኦዲት ለማስደረግ ፈቃደኛ ያልሆነ፣ በተፈጥሮው ምንም ዓይነት መንፈሳዊነት የሌለው እና ፖለቲካዊ ቅኝት የተቃኘ ሃይማኖት ለበስ ማፊያ ቡድን ነው፡፡
ለዚህም ነው "ማኅበረ ቅዱሳን" የሰለፊያ ግልባጭ ነው የሚባለው፡፡