የዛሬዋ ኢትዮጵያ በአንድ ወቅት ታላቅ ሀገር እንደነበረች
ታሪክ ይናገራል። በግዛት ስፋት፤ በጦር ኃይል ብዛት፤ በሥነ ሕንጻና
በሥነ ጽሁፍ ገናና ሆና መቆየቷን የሚናገሩ ብዙ የታሪክ ድርሳናት አሉ። በእርግጥ ብዙዎቹም ድርሳናት የተጻፉትና በሰነድነትም የሚገኙት
በውጪው ዓለም ነው። አቢሲኒያ የሚለው ስም የትመጣነት ለታሪክ ሀተታ ይቆየንና ኢትዮጵያ የሚለው / ጥቁር መልክ/ ስያሜ ከመሰጠቱ
በፊት አቢሲኒያ የምትባለው ሀገራችንን ታሪክ አብዛኛው የምናውቀው « የኢትዮጵያ የቀድሞ ስም» የሚለውን ጥሪ ብቻ ነው። ግፋ ቢልም
«አቢሲኒያ ባንክን» !!!
ታሪካዊነቱን የሚገልጽ መታሰቢያ ዩኒቨርሲቲ፤ የጎዳና
ስም፤ ሆስፒታል ወይም ሌላ ተመሳሳይ መጠሪያ እስከምናውቀው ድረስ የለንም። ምናልባት ያልሰማነው ካለ ይታረማል። ታሪክና ቅርስ ለአንድ
ሀገር ሕዝብ ማኅበራዊና መንፈሳዊ ማንነት ወሳኝ ነው። በዘመናት ያለፈባቸውን
የጥንካሬና የድክመት ጉዞዎቹን ይቃኝበታል። መጻዒውንም ያማትርበታል።
እስራኤሎች ታሪካቸውን እየጻፉ ለመጪው ትውልድ
የሚያኖሩላቸው ጸሐፊያን በየዘመኑ ነበራቸው። በሕይወታቸው ያለፈውን፤ ያደረጉትንና የተደረገላቸውን እየከተቡ ያኖሩ ነበር።
1ኛ ነገ 4፥3
«ጸሐፊዎቹም የሴባ ልጆች ኤልያፍና አኪያ፥ ታሪክ ጸሐፊም የአሒሉድ ልጅ ኢዮሣፍጥ»
የእያንዳንዱ
ነጋሲ ታሪክና ሥራ እየተጻፈም ይቀመጥ ነበር። ይህም ለልጅ ልጆች የሚቀመጥ ውርስ ነበርና ነው።
1ኛ ነገ 15፥32
በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
እኛ ለዚህ አልታደልንም።
እንኳን እንደዚህ ዓይነት
ታሪክ ጽፈን ለማቆየት ይቅርና በዘልማድ ስለምናውቀው «አቢሲኒያ»
ስለሚለው የሀገራችን ስም መታሰቢያ የሚሆን ነገር የለንም። ይሁን እንጂ ፈረንጆቹ በመጽሐፍ ቅዱስ «ኩሽ» በታሪክ አቢሲኒያ፤ በመጠሪያ
ደግሞ ዛሬ ኢትዮጵያ ስለምትባለው ሀገራችን የእምነት፤ የጀግንነት፤የታሪክ፤ የቅርስና የመልክዓ ምድር ወዘተ ሰፊ ጥናት አድርገዋል።
መጻሕፍትንም ጽፈዋል።
ፈረንሳዊው የታሪክ ጸሐፊ ጂን ክሪስቶፍ ሩፊን/Jean-Christophe Rufin/ ዘ አቢሲኒያን፤
ሳሙኤል ጆንሰን፤ ጀምስ ብሩስ፤ሪቻርድ በርተን፤ ኢቭሊን ዎግ፣ ዴርቭላ
መርፊ፤ ሲልቪያ ፓንክረስት፤ ኸርበት ቪቪያን፤ ሮማን ፕሮቼስካ ፤
ጆንስ እና ኤልሳቤጥ/ መጽሐፉን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ / ወዘተ እና ሌሎች ብዙዎች ጸሐፊያን ስለአቢሲኒያ
ጽፈዋል።
ይህንኑ ገናናውን የአቢሲኒያን ታሪክ ተከትሎና ከጥቁር ምድር
ቀዳሚ የክርስትና ሀገር ኢትዮጵያ በመሆኗም ጭምር አሜሪካውን ጥቁሮች ቤተክርስቲያኖቻቸውን ጭምር በምድረ አሜሪካ ውስጥ በአቢሲኒያ
ስያሜ ይጠሩ ነበር። ኮሎራዶ በ516ኛው ክሬስትሞር ጎዳና ላይ የሚገኘው
የአቢሲኒያውያን ክርስቲያኖች ቤተክርስቲያን፤ ኒውዮርክ በምእራብ 138ኛው
ጎዳና ላይ በ1808 የታነጸው የአቢሲኒያውያን መጥምቅ ቤተክርስቲያን፤ 1828 ዓ/ም በ75 ኒው በሪ ጎዳና የተመሰረተው የፖርት
ላንድ አቢሲኒያውያን ቤተክርስቲያን፤ እዚው ፖርት ላንድ የሚገኘው የአቢሲኒያውያን የመሰብሰቢያ አዳራሽ፤ ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ በኢትዮጵያ የቀድሞ ስም በአቢሲኒያ ስም የተጠሩ የአሜሪካ
ጥቁሮች የታሪክና እምነት ስያሜ መጠሪያዎች ነበሩ። ዛሬም በዚሁ ስም እየተጠሩበት ይገኛሉ። ብዙዎቹም እናት ምድራችን በሚሏት አቢሲኒያ
/ኢትዮጵያ/ ተገኝተው ታሪኳን ቅርሷን፤ ክብሯን ሁሉ በአካል ለማየት ችለዋል። ያ ሁሉ ዝናና ታሪክ ተንኮታኩቶ የድሆች መናኸሪያ፤
የስደተኞች መፍለቂያ መሆኗን ሲያዩ ምን ብለው ይሆን?
አብያተ ክርስቲያኖቻቸውን በአቢሲኒያ ስም ከመጥራት
ባሻገር አቢሲኒያን በተለያየ ዘመናት የረገጡ ነጮች ከምድረ አቢሲኒያ ድመት፤ ውሻ፤ ፈረስ፤ ድብ፤ አሳማ፣ እጽዋት በመውሰድ በሀገራቸው
አራብተዋል፤ አዳቅለዋል።
ዛሬ በአሜሪካ የአቢሲኒያ ድመት፤ ውሻ፤ ፈረስ ወዘተ በስም ተለይቶና ተመርጦ የሚገዛበት ትልቅ ስም ነው። እንዲያውም ተፈላጊ መለያ ነው።
የአበሻ ውሾች ቁጡዎችና ኃይለኞች፤ ድመቶቹ አይጥ
አዳኞች፤ ፈረሶቹ የጦር ሜዳ ዘመቻ ጋላቢዎች ስለነበሩ እየወሰዱ ተዳቅለዋል። ሳንዲያጎ በሚገኘው ግዙፉ የእንስሳት ፓርክ ውስጥ
ከኢትዮጵያ የተወሰዱ አእዋፍና አሞራዎች አሉ። የአቢሲኒያ ድመቶች ማደቀያ ማኅበር ራሱን ችሎ በአሜሪካና በእንግሊዝ የተቋቋመ ነው።
እንስሳዎቹም በአቢሲኒያ ስም እስከዛሬ ይጠራሉ።
ከታች የሚታዩት ስእሎች በ«አቢሲኒያ» ስም ከሚጠሩ
መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።