በመምህር ሙሴ ኃይሉ
ምንጭ፤ የሰንበት ት/ቤቶች ማ/መ/ ድረ ገጽ
መድኃኒተ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ማር እንደ ወተት የሚጣፍጠውን ትምህርቱ ለመስተማርና በተለያዩ ምክንያቶች (ተአምራትን ለማየት፣ ምግበ ሥጋን ለመመገብ፣ ሐሰት አግኝተው ለመፈተን...) ከአምስት ገበያ በላይ ሕዝብ ተሰብስበው በተመለከተ ጊዜ ከፍ ወዳለ ተራራ ወጥቶ በወርቃማ አምላካዊ አንደበቱ በተራራማ ስብከቱ ካስተማራቸው የመንፈሳዊነት፣ የሐዋርያዊነት፣ የአገልግሎት፣ የምግባርና የትሩፋት ትምህርት አንዱ ነው፡፡ ይኸው ትምህርት ቅዱሳን አባቶቻችን ሐዋርያትና በሐዋርያት እግር ሥር የሚተኩ የቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ ምዕመናንና ምዕመናትን የሕይወት መርህ በማድረግ እስከ መጨረሻ ህቅታ ድረስ አጽንተው እንዲጠብቁ የተሰጠ የምግባርና የትሩፋት (የሥነ ምግባር) አስተምህሮ ነው፡፡ ብርሃን በተለያዩ ዓይነት የትምህርት ዘርፎች የተለያዩ ትርጉም ቢኖረውም መጽሐፍ ቅዱስ መሠረተ ዕውቀታችን አድርገን ለምናምን ለኛ ግን ብርሃን የእግዚአብሔር የባሕርይ መገለጫው ነው፡፡ ከዚህም በመነሳት ብርሃን ፈጣሬ ዓለማት፣ ሠራዔ ዓለማት፣ መጋቤ ዓለማት እግዚአብሔር ነው፡፡ ስለሆነም ብርሃን ሀሉን ያስገኘ፣ ሁሉን የፈጠረ እንጂ በዚህ ዘመን ተገኘ፣ ከዚህ ዘመን በኋላ ያልፋል ተብሎ የማይነገርለት ምሥጢረ መለኮት ነው፡፡ እውነተኛ ዘለአለማዊ ብርሃን እግዚአብሔር መሆኑ ዘመነ መርገም አብቅቶ የዘመነ ምሕረት የምሥራች በተነገረበት ጊዜ ድኅነት ሰጪው፣ አዳኙም ሆነ ድኅነት ተቀባዩ ራሱ የሆነ የባሕርይ ዘለአለማዊ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሯል፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ (ነባቤ መለኮት) ስለ እውነተኛ ብርሃን ምሥጢር በመጀመሪያ ምዕራፉ ሲጽፍ፡-"...ብርሃን በጨለማ ይበራል ጨለማም አላሸነፈውም፡፡ ...ለሰው ሁሉ የሚያበራ እውነተኛ ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር፡፡ በዓለም ነበረ ዓለሙም በእርሱ ሆነ ዓለሙም አላወቀውም'' (ዮሐ. 1፡1-10) በማለት ጀምሮ የረቀቁ የሥነ መለኮት ትምህርቶችን በምጥቀት ያትታል፡፡ይህ ማለት አማናዊ ብርሃን እግዘአብሔር መሆኑንና በዚሁ አማናዊ ብርሃንም ሁሉን እንደተገኘ እንረዳለን፡፡ መምህረ ወንጌል ኢየሱስ ክርስቶስ ስለዚህ እውነተኛ አስተምህሮ በግልጽ ሲያስረዳ ማለት እውነተኛ (አማናዊ) ዘለአለማዊ ብርሃን ራሱ "ወልደ አብ ወልደ ድንግል" ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑ ለደቀ መዛሙርቱና በወቅቱ ለተሰበሰቡት ሕዝብ በግልጽ በአደባባይ አስተምሮአል፡፡ "ደግሞም ኢየሱስ እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም ብሎ ተናገራቸው" ዮሐ. 8፥12 "በዓለም ሳለሁ የዓለም ብርሃን ነኝ" ዮሐ. 12፥36 "የብርሃን ልጆች እንድትሆኑ ብርሃን ሳላችሁ በብርሃን እመኑ" ዮሐ. 12፥46 እንዲል፡፡ የዓለም ሕዝብ በተለይ ደግሞ ሕግ ተሠርቶላቸው፣ ጽላት ተቀርጾላቸው፣ ነቢያት ተልኮላቸው የነበሩ እስራኤላውያን ሕግን እንጠብቃለን ሲሉ ሕግን እየሻሩና ወደ ራሳቸው (ወደ ሥጋዊ ፍላጎታቸው) ብቻ እየተረጐሙ በኃጢአት ጨለማ ውስጥ ሲኖሩ የጨለማ ጠላት የሆነው እውነተኛ ብርሃን መምጣቱንና ሰዎቹም አለመቀበላቸውን ቅዱስ ዮሐንስ ሲገልጽ፣ "ብርሃን ወደ ዓለም ስለመጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለወደዱ ፍርዱ ይህ ነው" (ዮሐ. 3፥19) በማለት ይገልጽልናል፡፡ የመድኃኒተ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃንነት ከነቢያት ጀምሮ "በጨለማ የተቀመጠው ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ በሞት አገርና በጥላ ለተቀመጡትም ብርሃን ወጣላቸው" (ማቴ. 4፥14-16) በማለት ሲገልጽ የመጣ ሲሆን ይህንኑ አማናዊ ብርሃን አንቀበልም ብለው ኃጢአት ሳይኖርበት እንደ በደለኛ በብርሃኑ ላይ ማመጻቸውም ነቢያት በመንፈሰ እግዚአብሔር ተመርተው አስቀድመው ተነብየውታል፡፡ "እነዚህ በብርሃን ላይ የሚያምጹ ናቸዉ፡፡ መንገዱን አያውቅም በጐዳውም አይጸኑም" (ኢዮብ.24፥13) እንዲል እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነታዎች መረዳት የሚችለው አማናዊ (እውነተኛ) ብርሃን እግዚአብሔር መሆኑን ነው፡፡ የፀሐይና ጨረቃ እንዲሁም የክዋክብት ተፈጥሮስ? አንዳንድ ሊቃውንት ብርሃንን ሲተረጉሙ የተፈጠረ ብርሃንና ያልተፈጠረ ብርሃን በማለት ይተረጉማሉ፡፡
