አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በተ/ሃይማኖት ስም ስለሚጠሩ
ሦስት ሰዎች ማንነትና ምንነት በሰፊው ጽፈው አኑረውልናል። የትኛው ተ/ሃይማኖት የጻቅድነትን ስያሜ፤ ከማን እጅ እንደተረከበና ይኸው
ጥሪ በዘር ማንዘሮቹ በርስትነት ተይዞ እንዲቆይ በግዝት እንዲጸናና ዜና ታሪኩ በመላው ኢትዮጵያ በሰፊው እንዲናኝ ስላስደረገው ተ/ሃይማኖ
ማንነት ፤ አፍ በሚያስይዝ ጽሁፍ ስውሩን ደባ አጋልጠው ለትውልድ በማስረዳታቸው ይህም አለ እንዴ? ብለን እንድንገረም ካደረጉን
ቆይቷል።
አለቃ ኪዳነ ወልድ ስለሰውዬው ማንነት በነገሩን
ወቅት ይህም አለ እንዴ? ብለን ዝም ከማለት ወይም የምንወደው ጻድቅ ተነካብን ብለን ከማኩረፍ ይልቅ ስለነገሩን ታሪክ እንዴትነት
፤የእውነተኛውንና የጻድቁን ተ/ሃይማኖትን መንፈሳዊ ገድል ስለቀማው ሰው
ማንነት፤ በማወቅ ብቻ ሳንወሰን ያንን መነሻ አድርገን ሌሎችን መረዳቶችም እንድናገኝ ዓይናችን በመግለጣቸው ጭምር አመስግነናቸዋል። ድሮ ከመጽሐፍ ቅዱስ ይልቅ ብዙ የምንታመንበት፤ ዘወትር የምንደግመው፤ ሰውነታችንን
የምናሻሽበት፤ የጸሎት መጽሐፋችን የነበረውንም የገድል መጽሐፍ እንድንመረምር
እድል አስገኝተውልናል።
አለቃ ኪዳነ ወልድ ከታሪክ ጭብጥ ተነስተው ስለገለጿቸው፤
ስለሦስቱ ተ/ሃይማኖቶች ማንነትና ታሪክ ወደፊት ለማቅረብ እንሞክራለን። ለዛሬው ግን ለርእሳችን ወደመረጥነው ጉዳይ እናመራለን።
እግዚአብሔር በቅዱሳኖቹ እጅ ድንቅን አድርጓል።
ፊትም፤ ዛሬም፤ ወደፊትም ይሰራል። ይህ ግን የሚያስደንቀውና የሚያስገርመው ሥራ የቅዱሳኖቹን ኃይል ሳይሆን ኃይሉን በእነሱ የገለጸ
የእግዚአብሔርን ከሃሌ ኩሉነት/ ሁሉን ቻይነት/ የሚነገርበት ዜና ነው። ይህንን እግዚአብሔር በቅዱሳኖች አድሮ የመሥራት ኃይሉን ቅዱስ ጳውሎስ
በአንድ ወቅት ያጋጠመውን ሲገልጽልን፤ በኢቆንዮን ከተማ ውስጥ ከእናቱ
ማህጸን ጀምሮ እግሩ የሰለለች ሆና የተወለደ በልስጥራንም በተባለ ስፍራ አንድ ሰው በፈወሰ ጊዜ፤ ህዝቡ ተገርሞ አማልክት ከሰማይ ሰው ሆነው
ወርደዋል በማለት መስዋእት ሊያቀርቡላቸው በወደዱ ጊዜ እንዲህ አለ።
«ሐዋርያት በርናባስና ጳውሎስ ግን ይህን በሰሙ ጊዜ ልብሳቸውን ቀደው ወደ ሕዝቡ መካከል እየጮኹ ሮጡ፥ እንዲህም አሉ። እናንተ ሰዎች፥ ይህን ስለ ምን ታደርጋላችሁ? እኛ ደግሞ እንደ እናንተ የምንሰማ ሰዎች ነን፥ ከዚህም ከንቱ ነገር ሰማይንና ምድርን ባሕርንም በእነርሱም ያለውን ሁሉ ወደ ፈጠረ ወደ ሕያው እግዚአብሔር ዘወር ትሉ ዘንድ ወንጌልን እንሰብካለን። እርሱ ባለፉት ትውልዶች አሕዛብን ሁሉ በገዛ ራሳቸው ጐዳና ይሄዱ ዘንድ ተዋቸው። ከዚህም ሁሉ ጋር መልካም ሥራ እየሠራ፥ ከሰማይ ዝናብን ፍሬ የሚሆንበትንም ወራት ሲሰጠን፥ ልባችንንም በመብልና በደስታ ሲሞላው ራሱን ያለ ምስክር አልተወም። ይህንም ብለው እንዳይሠዉላቸው ሕዝቡን በጭንቅ አስተዉአቸው»
የሐዋ 14፤ 14-18