የዛሬን አያድርገውና አፄ ሱስንዮስ ኮትልከዋል/ካቶሊክ
ሆነዋል/ በሚል የምታ ነጋሪት፤ ክተት ሠራዊት ዘመቻ የጎንደር አደባባይ በደም መጨቅየቱን፤ ሰማዕትነት አያምልጥህ በሚል ጥሪ በአንድ ቀን ብቻ ከስምንት ሺህ ሰዎች በላይ ማለቃቸውን ከተዘገበው አንብበናል። አፄ ሱስንዮስም ካቶሊክ ከመሆናቸው የተነሳ እግዚአብሔር
ተቆጥቶ ምላሳቸው አንድ ክንድ ያህል ተጎልጉሎና ወደ ቀደመ መጠኑ አልመለስ ብሎ ካስቸገረ በኋላ እያጓጎሩ እንደሞቱ በጽሁፍም፤ በአደባባይም
እስከዛሬ ይተረካል። የያኔው ካቶሊክና የዛሬው የኢትዮጵያ ካቶሊክ በእግዚአብሔር ዘንድ ያላቸው ቅጣት ይለያይ እንደሆነ የአፄውን
የትረካ ታሪክ ፈጣሪዎችን እየጠየቅን፤ እኛ ግን እስከሚገባን ድረስ
ሱስንዮስ ካቶሊክ ለመሆን እምነቱን ስለለወጠ እግዚአብሔር ምላሱን አንድ ክንድ ጎልጉሎ ገደለው የሚለው ታሪክ የፈጠራ ውጤትና ካቶሊክነት ከተቀበልክ ምላስህ እየተጎለጎለ ትሞታለህ የሚል ሽብር በህዝቡ ውስጥ ለመርጨት ረበናት የፈጠሩት ተንኮል እንጂ ዛሬ በኢትዮጵያ ያሉ ካቶሊኮች ሁሉ ምላሳቸው እየተጎለጎለ በየሜዳው ሞተው ባለቁ
ነበር። እየጨመሩ እንጂ እየጠፉ መሆናቸውን አላየንም።
የሚያሳዝነው ነገር እግዚአብሔርን ጨካኝና ርኅራኄ
የለሽ አድርጎ በመሳል ይኼው ተረት እስከ ዛሬ በአደባባይ እየተነገረ መገኘቱ ነው። ሰዎች የእውነትን ወንጌል በተከታዮቻቸው መካከል በማዳረስ ከእምነታቸው ሳይናወጡ፤
ጸንተው ከአምላካቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት የጠበቀ እንዲሆን ማድረግ ሲያቅታቸውና ሌላ ተገዳዳሪ እምነት ብቅ ብሎ ቀዬና መንደሩን
ሰፈርና ሀገሩን በትምህርቱ ሲበጠብጠው፤ ወዮልህ! ኮንትሮባንድ ሃይማኖት
መጣልህ፤ ከእነሱ አዳራሽ ከገባህ አትመለስም፤ ምናምን ያቀምሱሃል! ወደሚል የጭራቅ ሊበላህ ነው ማስፈራሪያ ጩኸታቸው ይገባሉ። ወንጌሉን
በሰዎች ልቡና ዘርተው መልካም ፍሬ ማፍራት ሲሳናቸው ከማስፈራሪያው ባሻገር መጤ የተባሉትን ቤተ እምነቶች ወደማፍረስና አማኞቹንም
ወደ መግደል ይወርዳሉ። ዛሬ ወንጌላውያን የሚባሉት ኢትዮጵያውያን ቤተ እምነቶች አሁን ላሉበት ደረጃ የደረሱት ተገድለው፤ ተሰደው፤
ታስረው፤ ተገርፈው፤ ተቃጥለው ስለመሆኑ ማንም ኅሊና ያለው ሰው የሚዘነጋው ነገር አይደለም።